Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ሲገቡ አማካሪያቸውን አስጠሩት

ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ሲገቡ አማካሪያቸውን አስጠሩት

[ለክቡር ሚኒስትር በጠዋቱ አንድ ወዳጃቸው ደወለላቸው]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • እንኳን ደስ አለዎት፡፡
 • ደግሞ ለምኑ ነው?
 • ሥራ ጀመረ አይደል እንዴ?
 • ኧረ ገና የፊንሺንግ ሥራ እየሠራሁ ነው፡፡
 • የምኑን ክቡር ሚኒስትር?
 • ስለ ሕንፃዬ አይደል እንዴ የምታወራው?
 • እኔ እንኳን ስለሕንፃዎት አልነበረም ያወራሁት፡፡
 • ታዲያ ስለምንድን ነው የምታወራው?
 • ፓርላማውን ማለቴ ነው፡፡
 • እ… ተከፈተ አይደል?
 • ክቡር ሚኒስትር ሙሉ ለሙሉ ዞሩ እንዴ?
 • ወዴት ነው የምዞረው?
 • ማለቴ የፓርላማውን ሥራ ትተው ወደ ንግዱ ዓለም ሙሉ ለሙሉ ገቡበት ወይ?
 • የፖለቲካ ሥራዬንማ ሙሉ ለሙሉ አልተውኩትም፡፡
 • እንደው ችላ ያሉት ስለመሰለኝ ነው?
 • ፖለቲካውንማ እንዴት እተወዋለሁ? ለንግዱ መሠረት የሆነኝ ሥራ እኮ ነው?
 • ታዲያ የፓርላማውን መከፈት አስመልክቼ እንኳን ደስ አለዎት ስልዎት ምንም አላስታወሱትም ብዬ ነው?
 • የደወልከው እንኳን ደስ አለህ ለማለት ነው?
 • የደወልኩት እንኳን በጣም ስለናፈቁኝ ነው፡፡
 • አልገባኝም?
 • እርስዎ እኮ አባቴ ማለት ነዎት፡፡
 • ምን?
 • ያው ልጅ አባቱ ጋ ቢደውል ምን አለበት?
 • ምነው እንደዚህ ቀባባኸኝ?
 • ኧረ እየቀባባሁዎት አይደለም፣ ከልቤ ነው፡፡
 • አሁንም አስፈለገህ እንዴ?
 • ምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ሌላ ብድር ነዋ፡፡
 • ኧረ በፍጹም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ ምን ፈልገህ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር ወዳጆች መሆናችንን ረሱት እንዴ?
 • ወዳጅ መሆናችንንማ አውቃለሁ፣ ለዛ ከሆነ የደወልከው ደህና፡፡
 • ግን እርስዎ ደስተኛ ነዎት?
 • በምኑ?
 • ማለቴ በሥራዎትም ብቻ በሁሉም ነገር፡፡
 • ምንም እየገባኸኝ አይደለም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የእርስዎ ጤንነት እኮ ያሳስበኛል፡፡
 • ከመቼ ጀምሮ?
 • ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር ከእርስዎ በላይ ለእኔ ማን አለ?
 • ዛሬ በእርግጥ የፈለካት ነገር አለች ማለት ነው?
 • ኧረ በእውነት ሰላም ለማለት ነው የደወልኩት፡፡
 • ብቻ እንዳታስቀኝ?
 • ምን ብዬ ክቡር ሚኒስትር?
 • ይሰረዝልኝ ብለህ ነዋ፡፡
 • ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
 • ብድሩ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እርስዎ እኮ በክፉ ቀኔ የደረሱልኝ ወዳጄ ነዎት፡፡
 • እሱስ ትክክል ነህ፡፡
 • እንደዚህ ዓይነት ነገር ላደርግም አልችልም፣ ላስብም አልችልም፡፡
 • እንግዲያው ፓርላማው ሥራ ጀመረ ብለህ ከደወልክልኝ ደግሞ ሥራ ፈተሃል ማለት ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር የደወልኩት እንኳን አዘጋጅቼያለሁ ለማለት ነው፡፡
 • ምኑን ነው ያዘጋጀኸው?
 • ያው ከቅድም ጀምሮ ሲሉኝ አልነበረ?
 • ብድሩን?
 • አዎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ያህሉን ነው ያዘጋጀኸው?
 • ሙሉውን ነው ያዘጋጀሁት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሁሉም እንዳንተ ቢሆን ደስ ይለኝ ነበር፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ ገና ለሕንፃዬ ያበድሩኛል ብዬ ስለማስብ በቃሌ ነው የምገኘው፡፡
 • በዚህ እንኳን አትታማም፡፡
 • እውነት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ያው የብር ተመን ላይ ማሻሻያ መደረጉን ሰምተሃል፡፡
 • እሱን ሰምቻለሁ፣ ከእኔ ብድር ጋር ምን አገናኘው ክቡር ሚኒስትር?
 • መቼም በድሮ ተመን ልትከፍለኝ አልመጣህም?
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • መንግሥት ያወጣውን መመርያ ማክበር አለብህ፡፡
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ብድሩን የምቀበልህ…
 • እ…
 • በአዲሱ ተመን ነው!

 

[ክቡር ሚኒስትሩ ከቤት ሊወጡ ሲሉ ልጃቸውን አገኙት]

 • አንተ ትምህርት ቤት አትሄድም እንዴ?
 • ዛሬ አልሄድም ዳዲ፡፡
 • ለምን? የለም እንዴ?
 • አለ ግን ሰስፔንድ ተደርጌ ነው፡፡
 • ምን?
 • ሰስፔንድ ተደርጌያለሁ፡፡
 • ምንድነው የምትለው አንተ ልጅ?
 • አስተማሪዬ ትናንትና ግቢ ውስጥ ረብሸሃል ብሎ ሰስፔንድ አደረገኝ፡፡
 • እና ምንድን ነው የሚደረገው?
 • ዛሬ ቤት ነው የምውለው ዳዲ፡፡
 • ተበላሽተህልኛላ?
 • ኧረ ምንም አልተበላሸሁም ዳዲ፡፡
 • እኔ እንደውም ስለአንተ ብዙ ነገር ነው የምሰማው፡፡
 • ምን ሰማህ ዳዲ?
 • ተቆጣጣሪ የሌለው ዱርዬ ልጅ መሆንህን ሰምቻለሁ፡፡
 • ኧረ ውሸት ነው ዳዲ፡፡
 • ትምህርት ቤት አትገባም፣ መጠጥ ትጠጣለህ አሉ፣ ሲጋራም ጀምረሃል ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡
 • አሁን ይኼ ወሬ ተብሎ ለአንተ ተነግሮህ ነው?
 • በጣም ጋጠወጥ ሆነሃል ማለት  ነው፡፡
 • ኧረ ዳዲ ፋራ አትሁን?
 • ምን አልከኝ አንተ?
 • ዳዲ እሱን ተወውና አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡
 • የምን ጥያቄ?
 • መኪና ግዛልኝ፡፡
 • ገና ከመሬት ሳትነሳ መኪና ግዛልኝ?
 • ዳዲ በጣም ስለሚያስፈልገኝ መኪና ግዛልኝ?
 • ለምንድን ነው የሚያስፈልግህ?
 • ምክንያቴን የምናገረው አንድ ነገር ሲሆን ነው፡፡
 • ምን ሲሆን?
 • ጥያቄዬ ተቀባይነት ሲያገኝ!

 

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር ወደ ቢሮ እየሄዱ ነው]

 • ምነው ዛሬ በጠዋት ፊትህ ጠቋቁሯል?
 • ደብሮኝ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ሆነህ ነው የደበረህ?
 • አየሩን ራሱ አይመለከቱትም? ፀሐይ ወጣ ስንል ዝናብ እየሆነ ያስደብረናል፡፡
 • አንተ በሜትሮሎጂ ነው እንዴ ፊትህ የሚበራውና የሚጨልመው?
 • ምን ክቡር ሚኒስትር ኑሮ ራሱ ከፍ ዝቅ እያለ ያሰቃየናል፡፡
 • ይኼኔ ማታ አረቄህን ልፈህ ነው ጠዋት ደበረኝ የምትለው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ወድጄ እኮ አይደለም አረቄ የምጠጣው?
 • ታዲያ ምን ሆነህ ነው?
 • የኑሮ ውድነቱን ለመርሳት፡፡
 • አረቄ ያስረሳል ብለህ ነው?
 • ቢሳካልኝማ ውስኪ ነበር የምጠጣው?
 • ስማ አረቄ በመጠጣትህ ደስ ነው ሊልህ የሚገባህ፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • የአገር ውስጥ ምርትን እያበረታታህ ነዋ፡፡
 • ኧረ አይቀልዱብኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለማንኛውም የመንግሥት ፖሊሲ ትደግፋለህ ማለት ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር አንድ ጥያቄ  ግን ነበረኝ፡፡
 • የምን ጥያቄ?
 • ደመወዝ ይጨመርልኝ፡፡
 • ለምን?
 • ምክንያቴን የምናገረው በአንድ ነገር ነው፡፡
 • በምን?
 • ጥያቄዬ ተቀባይነት ሲያገኝ!

 

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ሲገቡ ጸሐፊያቸው ተከትላቸው ገባች]

 • ደህና አደሩ ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት አደርሽ?
 • ዛሬ ለአንድ ጉዳይ ነው የመጣሁት፡፡
 • እንግዳ አለኝ እንዴ?
 • እንግዳ እንኳን የለዎትም፡፡
 • እሺ ምን ፈለግሽ?
 • ይቺን ወረቀት ይመልከቷት፡፡
 • የምን ወረቀት?
 • እንኩ ይመልከቷት፡፡
 • የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ?
 • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምነው የተሻለ ሥራ አግኝተሽ ነው?
 • አይ ክቡር ሚኒስትር የተሻለ ሥራ ከየት ይመጣል?
 • ማለት?
 • ያው በትምህርቴም ብዙ ስላልገፋሁ፣ የተሻለ ሥራ ከየት አመጣለሁ ብለው ነው?
 • ታዲያ ሥራውን ጠልተሽው ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ የምፈልገው መልቀቅ ነው፡፡
 • ባለፈው ለሠራሽው ሥራ የተከፈለሽ ኮሚሽን አንሶሽ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ይኼን ደብዳቤ ተቀብለውኝ ከሥራ ያሰናብቱኝ፡፡
 • ለምንድን ነው የማሰናብትሽ?
 • በቃ ከዚህ በኋላ ሥራውን መሥራት አልፈልግም፡፡
 • እኮ ምክንያትሽ ምንድን ነው?
 • እሱን የምናገረው አንድ ነገር ሲሟላ ነው፡፡
 • ምን ሲሟላ?
 • ጥያቄዬ ተቀባይነት ሲያገኝ!

 

[ክቡር ሚኒስትሩ ለምሳ ቤት ሲሄዱ ሚስታቸውን አገኟቸው]

 • አንተ ምንድነው የሚወራው?
 • ምን ሲወራ ደግሞ ሰማሽ?
 • ያልደወለልኝ ሰው እኮ የለም፡፡
 • እኮ ለምን?
 • ሊለቅ ነው ወይ እያሉኝ ነዋ፡፡
 • ምንድነው የምለቀው?
 • ሥራህን ነዋ፡፡
 • በቃ ቡና ላይ የሚወራውን ጐሲፕ እዚህ እንደ ቁምነገር ከእኔ ጋር ታወሪያለሽ አይደል?
 • የቡና ጐሲፕ አይደለም፣ ብዙ ሰው ነው የደወለልኝ፡፡
 • ፌስቡክ ላይ ተጥደሽ መዋል ጀመርሽ እንዴ?
 • ተደውሎልኝ ነው አልኩህ እኮ?
 • ለነገሩ ሥራ ስለሌለሽ ፌስቡክ ላይ ብትውይም አይገርመኝም፡፡
 • ምን ላድርግ ሥራ እንደሆነ ከቀዘቀዘ ቆየ?
 • አገሪቷ ላይም ሁሉ ነገር ተቀዛቅዟል፡፡
 • በነገራችን ላይ ፌስቡክ ላይ የመመለሱን ዜና ሰምቼ ነበር፡፡
 • ማን ነው የተመለሰው?
 • ኤክስፖርት የተደረገው ስኳር፡፡
 • አዎ ተመልሷል፡፡
 • ታዲያ እናንተ መሸጥ ካልቻላችሁ ለእኔ ለምን አትሰጡኝም?
 • ምን ሆነሻል ሴትዮ?
 • ስማ እዚህ እኮ ኪሎ 50 ብር ደርሷል፡፡
 • ስኳሩ የመንግሥት ዓይኑ ውስጥ ስለገባ እንደዛ ማድረግ ከባድ ነው፡፡
 • አገር ውስጥ ብሸጠው ጥሩ ገንዘብ አገኝበታለሁ ብዬ ነው፡፡
 • ይልቁኑ አንድ ሥራ እሰጥሻለሁ፡፡
 • የምን ሥራ?
 • ኮፍያና ቲሸርት እንድታትሚ አስደርጋለሁ፡፡
 • ለምኑ?
 • ለአቀባበል ፕሮግራሙ!

 

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ሲገቡ አማካሪያቸውን አስጠሩት]

 • አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በአፋጣኝ ኮሚቴ ይቋቋም፡፡
 • የምን ኮሚቴ?
 • አንድ እንግዳ ወደ አገራችን እየመጣ ነው፡፡
 • የምን እንግዳ?
 • እሱን ተወውና አሁን መሥራት ያለብህን እነግርሃለሁ፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • መጀመርያ ለአቀባበሉ ቲሸርትና ኮፍያ መታተም አለበት፡፡
 • እሺ፡፡
 • ለአቀባበሉ ፕሮግራም የሚጠሩ ሰዎች መመረጥ አለባቸው፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለዚህ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በአቀባበሉ ላይ መገኘት አለባቸው፡፡
 • ማን ነው የሚጠራው?
 • ሁሉም የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ አርቲስቶችና ታዋቂ ግለሰቦች መገኘት አለባቸው፡፡
 • ሌላስ?
 • ከሕዝብ ክንፍ፣ ከወጣቶች ፎረም፣ ከደጋፊ ነጋዴዎች ብቻ በአጠቃላይ ከተለያዩ አደረጃጀቶች እንግዶች ይጠራሉ፡፡
 • ግን ይኼን ሁሉ ሰው የት ነው የምናስተናግደው?
 • ስነግርህ ፕሮግራሙ ቀላል አይደለም፡፡
 • መልካም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለእያንዳንዱ ተሳታፊ ኮፍያና ቲሸርት መዘጋጀት አለበት፡፡
 • መቼ ጨረታ ልናወጣ?
 • ጊዜ ስለሌለ እሱን ለእኔ ተወው፡፡
 • አያስጠይቀንም ክቡር ሚኒስትር?
 • ትልቅ እንግዳ እኮ ነው የሚመጣው?
 • ለመሆኑ በቲሸርትና በኮፍያው ላይ ምንድነው የሚጻፈው?
 • እንኳን ለአገርህ አበቃህ፡፡
 • እንግዳው ኢትዮጵያዊ ነው እንዴ?
 • እህሳ?
 • ይኼን ያህል ክብር የተሰጠው እንግዳ ማን ነው?
 • ስኳሩ!