Skip to main content
x

ዴሞክራሲን የህልውና ጉዳይ ያደረገው ማን ነው?

ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ባለፉት 26 ዓመታት አገሪቷን ከብተና በመታደግ፣ ታዳጊና ሕዝቦችንም የሥልጣን ባለቤት ያደረገ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ስለመመሥረቱ ይናገራል፡፡ በዚህ ሳያበቃም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ለመቀልበስ የሚደረግ ማንኛውንም ዓይነት ሙከራ እንደማይታገስ ያስታውቃል፡፡ መንግሥትን ከተቃዋሚው ጎራ ጋር በስፋት ከሚያነታርኩት ጉዳዮች መካከል ‹ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ መሞከር› የሚለው ዋናውን ድርሻ ይይዛል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ዴሞክራሲን እያጣቀሱ የሚካሄድ ውንጀላ ግን ለገዥው ፓርቲ የተሰጠ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁኑም ባለፉት ሁለት አሥርታት የተመሠረቱ ፓርቲዎች መነሻና መድረሻም ይኼው የዴሞክራሲ ጉዳይ ነው፡፡

አንዳንዶቹ ፓርቲዎች በስማቸው ሳይቀር ዴሞክራሲ የሚለውን ቃል ያካተቱ ሲሆን፣ ኢሕአዴግ ግን የሚከሱትም የፖለቲካ ምኅዳሩን በማጥበብ ከዚያም ከፍ ሲል ፍፁም ኢዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ነው በሚል ነው፡፡ እንዲህ ያለው የሁለቱ ወገን ክርክር ግን አንድ መሠረታዊ ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡ ለመሆኑ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ  ህልውና መሠረት ነው?

ዴሞክራሲ ሀሳዊ መንገድ

ሳሙኤል ሀንቲንግተን “Democracy’s Third Wave” በተሰኘ ጥናቱ ዓለም በሦስት የዴሞክራሲ ማዕበሎች ተመትታለች ይላል፡፡ የመጀመሪያው እ.ኤ.አ. በ1820ዎቹ ተጀምሮ እስከ 1926 የዘለቀው ሲሆን፣ 29 ያህል አገሮችም ዴሞክራሲያዊ ሆነዋል፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተነሳው የዴሞክራሲ ሞገድ በአንፃሩ 36 አገሮችን በምዕራባውያኑ ዴሞክራሲ አጥምቋል፡፡ በቀዝቃዛው ጦርነት ማግሥት የጀመረው ሦስተኛው የዴሞክራሲ ማዕበል ግን ከቀድሞዎቹ የተለየ ነበር ለማለት ያስደፍራል፡፡

 የሶቭየት ኅብረትን መፈራረስ ተከትሎ ከምዕራቡ ዓለም የተነሳው ሦስተኛው የዴሞክራሲ ሞገድ እ.ኤ.አ. እስከ 2010 ብቻ 120 አገሮችን ከዴሞክራሲ ጋር ያስተዋወቀ ሆኗል፡፡ ከአፍሪካ አገሮችም 42 ‹ዴሞክራሲያዊ ምርጫ›ን እንዲያደርጉ ምክንያት ሆኗል፡፡ እንዲህ ያለው ዴሞክራሲን የተቀበሉ አገሮች ቁጥር ማደግ ግን ለሳሙኤል ሀንቲንግተን የእንቧይ ካብ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ዛሬ ዴሞክራሲን ተቀበሉ ሲባሉ ነገ ተመልሰው አምባገነን የሚሆኑ መንግሥታት ቁጥር እየበረከተ መሄድ ነው፡፡ በመጀመሪያው የዴሞክራሲ ሞገድ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ከተቀበሉ 29 አገሮች መካከል 12ቱ ብዙም ሳይቆዩ ወደ ነበረቡት የአምባገነን ሥርዓት ተመልሰዋል፡፡

በሁለተኛው ሞገድም ከ36 አገሮች ስድስቱ ‹ከማናውቀው መላዕክ የምናውቀው ሰይጣን ይሻለናል› ብለው ከአምባገነን ሥርዓት ጋር አብረዋል፡፡ የ120 አገሮችን ከዴሞክራሲ ጋር አብሮ መኖር የሚገልጸው ሦስተኛው ሞገድ ግን እንደ በፊቱ በርካታ አገሮቸ ከገቡበት የዴሞክራሲ ሥርዓት ሲያፈገፍጉ የሚስተዋልት አይደለም፡፡ እንዲህ ያለው ገለጻ ግን በዓለም ላይ 120 አገሮች ዴሞክራሲያዊ ሆነዋል ማለትን አያመለክትም፡፡ 42 የአፍሪካ መንግሥታትም ዴሞክራሲያዊ ናቸው ከሚል መደምደሚያ አያደርስም፡፡ ይህ ተቃርኖ አንድ መሠረታዊ ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡ 120 የሚሆኑት መንግሥታት ዓመታትን ቆጥሮ በሚመጣ ምርጫ ሥልጣነ መንበሩን ከያዙ በኋላ ለምን ዴሞክራሲያዊ አይባሉም?

ፋሪድ ዘካሪያ ‹‹The Future of Freedom Illiberal Democracy at Home and Abroad ›› በተባለ መጽሐፍ ከላይ ላነሳነው ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል፡፡ በዘካሪያ ዕምነት አዲስ የአገሮች ዴሞክራሲያዊ ምርጫን ቢያካሂዱ እንኳን ዴሞክራሲያዊ እንዳይባሉ ያስገድዳል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምርጫን ከአምባገነናዊ ሥርዓት ጋር አጣምረው የያዙ መንግሥታት መበራከት ነው፡፡ ለዘካሪያ ወቅትን ጠብቆ በሚመጣ ምርጫ በተለያየ መንገድ አሸንፈው ሥልጣነ መንበሩን ከተረከቡ በኋላ፣ ከዴሞክራሲ የራቀ ድርጊት የሚያካሂዱ አምባገነኖች የኢሊበራል ዴሞክራሲ (ለእኛ አገር አንባቢ ሀሳዊ ዴሞክራሲ ብዬ ተርገሜዋለሁ) አራማጆች ናቸው፡፡ አገሮቹ የሚከተሉት ሥርዓትም ሀሳዊ ዴሞክራሲ ይባላል፡፡

ሀሳዊ ዴሞክራሲ (ኢሊበራል ዴሞክራሲ) ዓለም ላይ በፍጥነት እየተሰፋፋ የመጣ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ከ1990 እስከ 1997 በነበሩት ሰባት ዓመታት ብቻ ከነበረበት 22 በመቶ ወደ 50 በመቶ ከፍ ማለቱን ዘካሪያ ይጠቅሳል፡፡ ይህም ዛሬ በምርጫ ሥርዓት ሥልጣን ላይ ከወጡ 120 መንግሥታት 60 ያህሉ ሀሳዊ ዴሞክራሲን የሚከተሉ መሆናቸውን ይጠቁማል፡፡ ፎርይን አፌርስ መጽሔት ላይ ጽሑፋቸውን ላሠፈሩት ሮናልድ ኢንግላርትና ክርስቲያን ዌልዜል በእነዚህ አገሮች የሚኖሩ ዜጎች የዴሞክራሲያዊ ጭቆና ተጋላጭ ናቸው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ግን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ወይም አምባገነናዊ ሥርዓቱ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ ሁለቱ ጸሐፊያን የዴሞክራሲን ቅንጡ ኑሮ መውደድ ያነሳሉ፡፡

ዴሞክራሲ እንደ ስለት ልጅ

የሥነ ማኅበረሰብ ተመራማሪው ሳይሞር ማርቲን ሊፒሴት ከአምስት አሥርታት በፊት ባቀረበው ጥናቱ ዴሞክራሲ ከደሃ አገሮች ይልቅ ለሀብታም አገሮች የተፈጠረ ሥርዓት ነው የሚል ሀቲት አቅርቦ ነበር፡፡ ይህ የሊፒሴት ሙግት ግን በወቅቱ ብዙ ተቀባይነት ያገኘ አልነበረም፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ዴሞክራሲን በስፋት እየተቀበሉ የነበሩት የደቡብ  አውሮፓ አገሮች ስኬታማ መሆን ነው፡፡  ሊፒሴት በጊዜው ከተለያዩ ወገኖች ነቀፌታ ቢቀርብበትም፣ ዴሞክራሲ እንደ ስለት ልጅ ከፍተኛ እንክብካቤ የሚፈልግ የሀብታም አገሮች ሥርዓት መሆኑን ግን ከመናገር ወደ ኋላ አላለም፡፡ ዛሬ ላይ ሆነን ይህን ሀልዮት ስንመለከተው የሊፒሴት ሐሳብ የትንቢት ያህል የሰመረ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ግን አንድ ጥያቄ እናንሳ፡፡ ከ120 አገሮች ለምን 60ዎቹ ብቻ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ለመሆን ወደዱ?

ሳሙኤል ሀንቲንግተን ከላይ በተጠቀሰው ጥናቱ ለአገሮች ዴሞክራሲያዊ አለመሆን ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያት አለው ይላል፡፡ በሶቭየት ኅብረት ሥር የነበሩ  አገሮች በጊዜው ዴሞክራሲያዊ ለመሆን ቢፈልጉ እንኳን የሚቻላቸው አልነበረም፡፡ እንዲህ ያለው የዴሞክራሲ ተግዳሮት ውጫዊ ሊባል የሚችል ነው፡፡

 ከሶቭየት ኀብረት መፈራረስ በኋላ ዓለም ላይ ልዕለ ኃያል ሆና ብቅ ያለችው አሜሪካ ዴሞክራሲን ለማስፈን በምሥራቅ አውሮፓም ሆነ በቀረው ዓለም ተንቀሳቅሳለች፡፡ በዚህ የተነሳም በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ዴሞክራሲያዊ  ሥርዓትን ለማስፈን ብድርና የተለያዩ ድጋፎቿን መያዣ አደርጋለች፡፡

እንዲህ ያለው በውጭ ኃይል የተጫነ ዴሞክራሲ ግን ዓለም ከአንድ ልዕለ ኃያል ወደ ብዙ ኃያላን ስትለወጥ ብዙ የሚያስኬድ አልሆነም፡፡ ከአሜሪካ በዴሞክራሲ ቅደመ ሁኔታነት ብድርና ዕርዳታ የሚያገኙት አፍሪካዊያንም ፊታቸውን ወደ ቻይና ማዞር ጀመሩ፡፡ በዚህ የተነሳም በአሜሪካ ልክ የተሰፋውን ልብስ እኛ እንድንለብስ አንገዳድም ሲሉ በዴሞክራሲ ላይ ተሳለቁ፡፡

ይህ ዓይነቱ ዴሞክራሲን የምዕራቡ ዓለም ድሪቶ አድርጎ አሽቀንጥሮ የመጣል ጉዳዩ ከላይ ካነሳነው የሊፒሴት ትንቢት ጋር አብሮ የሚታይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሀንቲንግተን ሁለተኛው የዴሞክራሲ ተግዳሮት ያለው ውስጣዊ ችግር ላይ ያደርሰናል፡፡

ዴሞክራሲ በአንድ አገር መሠረቱን እንዲጥል በመጀመሪያ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ  ጉዳዮች ወሳኝ ናቸው የሚለው የሀንቲንግተን መከራከሪያ  ዛሬ ከሞላ ጎደል በበርካታ የሥነ ማኅበረሰብና ፖለቲካል ሳይንስ ተመራማሪዎች ሰፊ  ቦታን ያገኘ ሆኗል፡፡ ለመሆኑ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንዴት የአንድ አገር ዴሞክራሲያዊ በመሆን አለመሆን ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ የሚለው ሐሳብ ግን ለዚህ ውይይት ከባዱ ጥያቄ ነው፡፡ ሀንቲንግተን ራሱ እንደሚለውም ‹‹የምዕራቡ ዓለም ባህል ብቻ ነው እንዴ ለዴሞክራሲ የሚሆነው?›› የሚል ሙግትን ያስከትላል፡፡

የዘመናዊው ዓለም የሥነ ማኅበረሰብና ፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ባህል አንድ አገር ዴሞክራሲያዊ እንድትሆን በማድረግ ደረጃ ወሳኝ ሚና አለው ይላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ አብነት ሆነው የሚቀርቡት የዓረብ አገሮችና የእስያ አገሮች ናቸው፡፡ ሁለቱ አካባቢዎች ከዴሞክራሲያዊ አገዛዝ መንነው እንዲኖሩ ያደረጋቸው ዋነኛ ምክንያት ባህላዊ መሠረቱ ስሌላቸው ነው፡፡

ቻይናውያን ዛሬ የዴሞክራሲ ሥርዓት አቀንቃኝ መሆን ያቃታቸው በምንም ሳይሆን ኮንፊሸየስ የባህል መንገዳቸው በመሆኑ ነው፡፡ አምባገነናዊ ሥርዓተ ማኅበር የገነነበት የዓረቡ ዓለም ለዴሞክራሲ የሚሆን መደላድል የሌለው ነው፡፡ በዓረቡ ዓለም ውስጥ በታሪክ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመከተል ረጅም መንገድ ጀምራ በአጭር የተቀጨችው ሊባኖስን ብንመለከት እንኳን፣ 40 በመቶ ሕዝቧ ክርስትናን የሚከተል መሆኑ ባህል ለዴሞክራሲ ሥርዓት የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ያሳያል፡፡ በዚህ ብቻ ሳናበቃ እስከ 1990ዎቹ ድረስ ዴሞክራሲያዊ ለመሆን የሞከሩት ሁለቱ የእስያ አገሮች ፊሊፒንስና ጃፓን ለዚህ ሙከራ ያነሳሳቸው፣ ፊሊፒንስ ከኮንፊሽየስ ይልቅ የካቶሊክ ዕምነት ተከታይ ስለሚበዛበት፣ ጃፓን ደግሞ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአሰቃቂ ሁኔታ በምዕራባዊያን ስለተሸነፈች ነበር፡፡ ይህ ሽንፈቷም በሯን ከፍታ ከእነ አሜሪካ ብዙ መማር እንዳለባት አሳውቋታል፡፡

ባህል ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ ጉዳይ እንጂ ብቸኛ ቅድመ ሁኔታ ግን አይደለም፡፡ ለአብነት የእስያ አገሮች የሆኑት ደቡብ ኮሪያና ታይዋን ዛሬ ዴሞክራሲያዊ የሆኑት ባህላቸው ከአካባቢው አገሮች በጣም ስለተለየ ሳይሆን፣ ኢኮኖሚያዊ የሆነ ገፊ ምክንያት ስላለባቸው ነው፡፡

 በጥያቄ የታጀበ ጉዟችንን ለመቀጠል አሁንም ሌላ ጥያቄ እናንሳ፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያመጣው? ወይስ የኢኮኖሚ  ዕድገት ነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የሚያመጣው? እንዲህ ያለው ክርክር አንድም የሄግልስን የሰው ልጅ መሠረታዊ ጥያቄ ነፃነት ነው የሚልን ሐሳብ የሚያስታውስ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ኢኮኖሚ ቀዳሚ ነገር ነው የሚለውን የካርል ማርክስ  ሙግት ያስታውሰናል፡፡ ወይም ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እስከሌለ ድረስ የኢትዮጵያ ዕድገት ዘበት ነው የሚሉ ተቃዋሚዎችን  ሐሳብ ለመፈተሽ ይረዳናል፡፡

 ሁለቱ የማኅበረሰብ ሳይንስ ፕሮፌሰሮች ሮናልድ አንግላርትና ክርስቲያን ዌልዜል ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማኀበረሰብ ለውጥም ሆነ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ምሥረታ ቅድሚያውን ቦታ ይይዛል ይሉናል፡፡ በእነሱ እምነት የኢንዱስትሪ መስፋፋት የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ ይቀይራል፣ የከተሜነት መስፋፋትን ያመጣል፡፡ እንዲህ ያለው ለውጥ ታዲያ በትምህርት የታጀበ በመሆኑ አመክኗዊ መሆንን ይፈጥራል፡፡ ማኅበረሰቡ ለጥያቄው መልስ ለመስጠትም የተለያዩ ማኅበራትን ይመሠርታል፡፡ እነዚህ ማኅበራት ደግሞ የተከታዮቻቸውን ጥያቄ ለመመለስ ወደ ፓርቲነት አድገው ፉክክር ይጀምራሉ፡፡ የዴሞክራሲ መሠረቱም በዚህ መንገድ ይጣላል፡፡ የእንግሊዙ ሌበር ፓርቲ ለዚህ ማሳያ የሚሆን ነው፡፡ እንዲህ ያለውን የሁለቱ ምሁራን አመክንዮ ግን በሌላ ጥያቄ መፈተን ይቻላል፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት ቀዳሚ ሆኖ የማኅበረሰብ ለውጥ ከተከተለ ከዚያም ዴሞክራሲን ካሰፈነ፣ የእነ ጃፓንን መንገድ በምን ልንፈርጀው እንችላለን?

ሀን ጀን ቻንግ ‹‹Bad Samartians›› በተባለ መጽሐፍ እ.ኤ.አ. በ1933 በአሜሪካዊው አገር አሳሽ ሲድኔይ ጉሊክ የተጻፈውን ‹‹Evolution of the Japanese›› ጠቅሶ ጃፓኖች በ1930ዎቹ ሰነፍ ሕዝቦች እንደነበሩ ይገልጻል፡፡ ሥራ የማይወዱ የተባሉት እነዚህ ሕዝቦች በጊዜ ሒደት ለሥራ እጆቻቸውን በመዘርጋታቸው ኢኮኖሚያዊ ለውጥን ከዚያም ዴሞክራሲን ለማስፈን ቻሉ፡፡

 ሌላም ማስረጃ እንጥቀስ፡፡ እኤ.አ. በ1960ዎቹ ደቡብ ኮሪያና ጋና በተመሳሳይ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የነበሩ አገሮች ናቸው፡፡ ደቡብ ኮሪያዊያን በጠንካራ የሥራ ባህላቸው ዛሬ የዓለምን ኢኮኖሚ ድርሻ በአስገራሚ ፍጥነት እየተቀራመቱ ሲሆን፣ ጋናውያን ግን የሰፌድ ላይ ሩጫቸውን ቀጥለዋል፡፡

‹‹ባህል ነው ኢኮኖሚያዊ ለውጥን የሚፈጥረው? ወይስ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ነው የባህል ለውጥን የሚፈጥረው?›› የሚለው ሐሳብ በእንዲህ ያለ ሰፊ ልዩነቶች የታጀበ ቢሆንም ምላሽ ግን የሚታጣለት አይደለም፡፡ ሮናልድ አንግላርትና ክርስቲያን ዌልዜል ኢኮኖሚ ለባህል ለውጥ መነሻ ነው ሲሉ ከአውሮፓዊ መነጽር አይተውት እንደሆነ ብዙ አያከራክርም፡፡ ምክንያቱም አውሮፓዊያን ከኢንዱስትሪ አብዮት በኋላ ሥር ነቀል ማኅበረሰባዊ ለውጥ አምጥተዋልና፡፡ ጥያቄው ግን ለምን አውሮፓውያን ለዚህ ኢንዱስትሪ አብዮት በቁ የሚለው ነው፡፡ በእኔ እምነት ምላሹ ቀላል ነው፡፡ የባህል መዋቅራቸው ለኢኮኖሚውም ይሁን ለዴሞክራሲ ለውጥ መሠረት መሆኑን እንረዳለን፡፡ በዚህ መሠረትም  ባህልን ተንተርሶ የሚመጣ የኢኮኖሚ ለውጥ ለዴሞክራሲ መሠረት መሆኑ እንረዳለን፡፡

በዓለም ላይ ዛሬ አብዛኞቹ የበለፀጉ አገሮች ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት የተሸጋገሩት በዋነኝነት ባህልን ተንተርሶ በመጣው የኢኮኖሚ ዕድገታቸው ነው፡፡ ይህን መሰሉ ሐሳብ ለፋሪድ ዘካሪያ በነፍስ ወከፍ ገቢ ሳይቀር የተመሠረተ ነው፡፡ በእሱ አገላለጽ አገሮች ስኬታማ የሆነ የዴሞክራሲ ሽግግርን ለማድረግ የዜጎቻቸው የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ3,000 እስከ 6,000 ዶላር ሊሆን ይገባል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1820 አብዛኞቹ የአውሮፓ አገሮች የነፍስ ወከፍ ገበያቸው 1,700 ዶላር የነበረ ሲሆን፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በስፋት ባሰፈኑበት እ.ኤ.አ. በ1945 የነፍስ ወከፍ ገበያቸው 6,000 ዶላር ደርሶ ነበር፡፡ እዚህ ላይ ግን መጠንቀቅ የሚያስፈልገው ጉዳይ የነፍስ ወከፍ ገቢ ብቻውን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያበቃ አለመሆኑን ነው፡፡ የነፍስ ወከፍ ገቢ ብቻውን ለዴሞክራሲ መሠረት ቢሆን የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና ኩዌት ቁጥር አንድ የዴሞክራሲ ሥርዓት ባለቤት በሆኑ  ነበር፡፡

ውስብስቡ የዴሞክራሲ ፈለግ በመሠረታዊነት ዴሞክራሲ በማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች መዳበር ላይ የሚበቅል ሥርዓት መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡

ላም አለኝ በሰማይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ ባለፈው ዓመት በተሳተፉበት አንድ መድረክ ላይ ማኅበረሰባችን ለሥልጣን ያለው አመለካከት ለዴሞክራሲና ለመልካም አስተዳደር ግንባታው ተግዳሮት ሆኗል ሲሉ ገልጸው ነበር፡፡ ሐሳቡ ቃል በቃል የተወሰደ አይደለም፡፡

እንዲህ ያለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በመሪ ደረጃ መቅረቡ ካልሆነ በስተቀር ለፖለቲከኞቻችን ግን አዲስ አይደለም፡፡ ባለፉት 26 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰማይ ሥር ጎልተው የሚጠቀሱት የተቀዋሚ ፓርቲ መሪዎች ልደቱ አያሌውና ሌሎች ፖለቲከኞች በመጽሐፎቻቸው ማኅበረሰቡ በራሱ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምቹ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለምሳሌ ልደቱ አያሌው ‹‹መድሎት›› በተባለ መጽሐፉ በፌደራላዊና በወታደራዊ ሥርዓት የኖረ ከዚያም ከፋ ሲል በአለቃና በበታች ሠራተኛ፣ በባልና በሚስት፣ በአባትና በልጅ፣ በሃይማኖትና በብሔር ላይ የተመሠረተ ተዋረድን የተከተለ ማኅበረሰብ ባህሉን ጠብቆ ዴሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም ይላል፡፡

ከፍ ብየ እንደገለጽኩት አገሮች ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር ከፈለጉ ቢያንስ የዜጎቻቸው የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ3,000 ዶላር በላይ ሊሆን ይገባል፡፡ የዓለም ባንክ እ.ኤ.አ. በ2016 ባወጣው ሪፖርት ግን ኢትዮጵያ የዜጎቿ የነፍስ ወከፍ ገቢ 590 ዶላር ብቻ ነው ይለናል፡፡ ይህም ከቀጣናው አገሮች ጋር ሲነፃፀር በራሱ አነስተኛ የሚባል ነው፡፡ ታዲያ ዛሬ ላይ ሆነን ለዴሞክራሲ ሥርዓት የሚበጅ ማኅበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ መሠረት በሌለበት ሁኔታ ዴሞክረሲን ለምን ለህልውናችን መሠረት አድርገን እናያለን? የሌለ ነገርስ እንዴት ለህልውና መሠረት ሊሆን ይችላል?

ሀብታሙ አለባቸው የኢትዮጵያን ፖለቲካ በጥልቀት በተነተነበት መጽሐፍ ከሦስት ነገሮች አንፃር የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ ለመገምገም ይሞክራል፡፡ ከሲቪክ ማኅበራት፣ ከሶሻል ካፒታልና ከሲቪክ ባህል አንፃር የተቃኘው የሀብታሙ መመዘኛ  ይህንን ጉዳይ አንድ እውነት ላይ ያደርሰዋል፡፡ እሱም ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ የለም የሚል ነው፡፡ የሀብታሙ መንገድ በዚህ የተገታ አይደለም፡፡ ይልቁኑም ዴሞክራሲ ከሌለ ምን አለን የሚል አንድምታ ያለው ጥያቄ ያነሳል፡፡ መልሱም ‹ዴሞክራታላይዜሽን› ነው፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሒደት ልንለው እንችላለን፡፡

ፋሪድ ዘካሪያ የዴሞክራሲ ሥርዓት መሠረት በሌለበት ሁኔታ የሚካሄድ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሒደት እጅግ አደገኛ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ይህ እውነታ በአስገራሚ የቁጥር መረጃም የታገዘ ነው፡፡ ጃክ ሰኔደርና ኤድዋርድ ማንስፊልድ እንደሚሉት፣ ባለፉት 200 አመታት ውስጥ ያለውን እውነት ከተመለከትነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ከመሠረቱ አገሮች ይልቅ ዴሞክራሲያዊ ባልሆነ ሥርዓት ውስጥ ያሉ አገሮች የተረጋጉ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በምርጫ የሚሳተፉ ኃይሎች ለማሸነፍ ይረዳናል ያሉትን የማኅበረሰቡን ደካማ ጎን ስለሚቀራመቱ ነው፡፡ ይህን መሰሉ የፓርቲዎች መቀራመት በተለይም በርካታ ብሔሮች ባላቸው አገሮች አደገኛ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡

ዶናልድ ሀኖዊትዝ እንደሚለው ደግሞ የዴሞክራሲ ሒደት ትልቁ ክሽፈቱ ማኅበረሰብን በመከፋፈል አንዱን ከአንዱ ማጋጨቱ ነው፡፡ ለእንዲህ ያለው የሀኖዊትዝ መከራከሪያ ከኢትዮጵያ በላይ ማሳያ ያለ አይመስልም፡፡ ሀብታሙ ለዚህ መፍትሔው ፈጣን የሆነ ልማትን በማስፈን የእኛና የእነሱን አመለካከት በትስስር ማከም ነው ይላል፡፡ እዚህ ላይ ሌላም ተስፋ የሚጭር ነገር መጨመር መልካም ይመስለኛል፡፡ በአሜሪካ መጀመሪያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመመሥረት የተሞከሩባቸው 50 ዓመታትም በመበተንና ባለመበተን ሥጋት የታጀበ ነበር የሚል፡፡

ከዴሞክራሲ ጋር ማን አፈራርሞ አጋባን?   

ፍራንሲስ ፋኩያማ በሁለት ተከታታይ መጻሕፍቱ ‹‹The End of History and the Last Man and Political Order and Political Decay›› ሌበራል ዴሞክራሲ የሰው ልጆች የመጨረሻ መድረሻ ነው ይላል፡፡ ከምዕራቡ ዓለም በራቀ መንገድ የመጣችው ቻይናና መሰሎቿም ዴሞክራሲያዊ የመሆን ጉዳይ የውዴታ ግዴታቸው ነው ሲል ይሞግታል፡፡ ያ ካልሆነ ከዴሞክራሲ የተኳረፋችው ቻይና አደጋ ውስጥ መግባቷ እንደማያጠራጥር ይገልጻል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የፉኩያማ ክርክር ግን ለሳሙኤል ሀንቲንግተን ፌዝ ነው፡፡

ሀንቲንግተን ‹‹THE Clash of Civilization>> በተባለ መጽሐፉ እንደሚገልጸው፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምዕራቡ ዓለም ሥልጣኔ ለሰው ልጆች ያበረከተው መልካም ጉዳይ እንጂ፣ የሰው ልጆች አስተዳደር አልፋና ኦሜጋ አይደለም፡፡ ሀንቲንግተን ዴሞክራሲን የምዕራቡ ዓለም የሥልጣኔ ገጸ በረከት ሲያደርገው አንድ ጉዳይ ሊነግረን እንደሞከረ መረዳቱ ተገቢ ነው፡፡ የየትኛውም አገር ሥልጣኔ ባህሪው እንደ ሰው ልጆች መወለድ፣ ማደግና መሞት ነው፡፡ በዚህ መሠረትም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከምዕራቡ ዓለም ሥልጣኔ ጋር አብሮ እየጠለቀ መሄዱ የማይቀር ነው፡፡ ይህን መሰሉ የሀንቲንግተን ትንበያ ከባዶ ሜዳ የበቀለ ሳይሆን በተጨባጭ ማስረጃ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ አሜሪካና እንግሊዝ የዜጎቻቸውን የነፍስ ወከፍ ገቢ በዕጥፍ ለማሳድግ 47 እና 58 ዓመታት በቅደም ተከተላቸው የወሰደባቸው ሲሆን፣ ቻይና ግን በቢሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ይዛ የዜጎቿን የነፍስ ወከፍ ገቢ በአሥር ዓመት እጥፍ አድርጋለች፡፡

በዚህ መነሻም የዓለምን ኢኮኖሚ መምራት ለመጀመር እየተንደረደረች ትገኛለች፡፡ የቻይና ልዕለ ኃያል መሆን ደግሞ የምዕራቡ ዓለም ሥልጣኔ ፀሐይን መጥለቅ የሚያውጅ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ የምዕራቡ ዓለም ሥልጣኔ አካል የሆነው ዴሞክራሲም በዚህ መንገድ መረታቱ የሚቀር አይደለም፡፡

ለሀንቲንግተን የምዕራቡ ዓለም ኢኮኖሚ ባለበት ሲርመጠመጥ የቻይናዊያን በራሳቸው መንገድ እዚህ መድረስ ለዓለም መንግሥታት የሚያስተላልፈው መልዕክት ትልቅ ነው ይላል፡፡ ማን ከዴሞክራሲ ጋር አፈራርሞ አጋባን?  ብለው እንዲጠይቁ ያስገድዳል፡፡ ከዚያም በኮንፊሽየስ ሥርዓት እንደተመራውና በራስ ባህል ላይ መሠረቱን እንዳደረገው የቻይና “ዴሞክራሲ” አገሮች ራሳቸውን ለመምሰል መጣራቸው አይቀርም፡፡ አርባ በመቶ የሚሆኑ አገሮች የአውሮፓውያኑን ዴሞክራሲ እስካሁን አለመተግበሩም፣ ከዚህ በኋላ ያለው ጦርነት በየራሳቸው መንገድ ‹‹ዴሞክራሲ››ን በተረዱ አገሮች መካከል ያደርገዋል፡፡

የሚከተለው ጥያቄ  ለበዛበት ጽሑፌ የመጨረሻ  ነው፡፡ ለመሆኑ ዴሞክራሲ በራሱ ለዴሞክራሲ ህልውናው ካልሆነ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው? ፋሪድ ዘካሪያ ምላሹ በጣም አጭር ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ማስፈን ለአገሮች ህልውና ወሳኝ ጉዳይ ነው ይላል፡፡ ይህ የዘካሪያ ሐሳብ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለይተን እንድናጤን ያደርገናል፡፡ አውሮፓዊያን ለሊበራል ዴሞክራሲ መሠረት ከሆነው ካፒታሊዝም ደጃፍ ከመድረሳቸውም በፊት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ተግብረዋል፡፡ ለአውሮፓ አገሮችና ለአሜሪካ ሕገ መንግሥት መሠረት የሆነው ማግና ካርታ ሥራ የጀመረው በ1215 እንደነበር ታሪክ ያስታውሳል፡፡ ይህ ሕግ ሲጀመር ለነገሥታት ያደላ ቢሆንም በጊዜ ሒደት የግለሰቦችን ነፃነት በማስጠበቅና የሕግ የበላይነትን በማስፈን የጎላ ሚናን ተጫውቷል፡፡

እንዲህ ያለው የአውሮፓውያን መንገድም ከዘመናዊ ዴሞክራሲ ሥርዓት ትግበራ በፊት የሕግ የበላይነት የሰፈነበትን ማኅበረሰብ ለመፍጠር አስችሏቸዋል፡፡ ይህ የአውሮፓውያን የትናንት ታሪክ ነገ የሀንቲንግተን ትንቢት ቢሰምር እንኳን፣  ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓታቸውን የሚነጥቃቸው እንደሌለ እንዲያምኑ የሚያስገድዳቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንገድም ከዚህ የራቀ ሊሆን አይገባም፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን የሚያከብርና የሚያስከብር መንግሥት መገንባት ለነገ የማይባል የቤት ሥራ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሩቅ ሳይሄዱ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት መግቢያ ብቻ ማየት በቂ ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ አላለም፣ የመጨረሻ ግቡ አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መፍጠር ነውና፡፡

በይነገር ጌታቸው

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡