Skip to main content
x

የልማት ኢኮኖሚ ሰው በቅጽበት የገበያ ኢኮኖሚ ሰው አይሆንም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከጥቅምት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጠባ ወለድ መጣኝና በውጭ ምንዛሪ መጣኝ ላይ ማስተካከያ አደረገ ተብሎ በመገናኛ ብዙኃን ተነገረ፡፡ በመርህ ደረጃ ማስተካከያው አስፈላጊ መሆኑን፣ ብዙ ጊዜ በባለሙያዎች አስተያየት ሲሰጥበት እንደነበርና መንግሥት ጆሮ ዳባ ብሎት እንደከረመ ማስታወስ ይቻላል፡፡

በተግባር የማስተካከያ ዕርምጃው ምን ውጤት እንደሚኖረውና አገሪቱ ከገባችበት ቀውስ ያወጣት እንደሆነም ሙያዊ አስተያየት መስጠት ይቻላል፡፡ መንግሥት ይኼን ዕርምጃ የወሰድኩት ቁጠባን ለማበረታታትና የውጭ ምንዛሪ ዕጥረትን ለማስወገድ  ነው ብሏል፡፡ 

የወለድ መጣኙ አሁንም ቢሆን ከዋጋ ንረት መጣኙ ያነሰ ስለሆነ፣ ቆጣቢዎችን ያበረታታል ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ ሰዎች ከፍጆታ ወጪያቸው ቀንሰው የሚቆጥቡት በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ አንዱ ወደ ፊት የሚገጥማቸውን ችግር ለመቋቋም ሲሆን፣ ሁለተኛው በቁጠባው ወለድ አግኝተው ለማትረፍ ነው፡፡

ከሸቀጥ ንግድ እስከ መቶ በመቶ ትርፍ እየተገኘ ሰዎች አምስትና ሰባት በመቶ ወለድ ለማግኘት ብለው በማትረፍ ዓላማ ቆጥበው ጥሬ ገንዘብ በባንክ ያስቀምጣሉ ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የጥሬ ገንዘብ ቁጠባ ሙሉ በሙሉ የወደፊት ችግርን በመፍራት እንጂ ለማትረፍ አይደለም፡፡ የወለድ መጣኙ ከአምስት ወደ ሰባት ማደጉ ሰውን አጓግቶ ቁጠባውን ይጨምራል ከማለት ይልቅ፣ የወደፊቱን የችግር ሥጋት ቀንሶለት ቁጠባውን እንዲቀንስ ያደርገዋል ማለት ይሻላል፡፡

የውጭ ምንዛሪ መጣኙ ኤክስፖርተሮችን ለማበረታታና ኢምፖርትን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት ነው ተብሏል፡፡ አዚህ ላይም ጽንሰ ሐሳብን ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ለማገናዘብ አልተሞከረም፡፡

በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ሲታይ ልክ ነው፡፡ በብር ዋጋ መርከስ ምክንያት ኤክስፖርተሩ ከአንድ ዶላር ሸቀጥ ወደ ውጭ ሽያጭ አሁን ከሚያገኘው በላይ ብር በማግኘት ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ 

የኢትዮጵያ ኤክስፖርት የግብርናና የምግብ ምርቶች፣ ጥራጥሬዎችና የቅባት እህሎች፣ ሥጋና የቁም ከብት እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ እነዚህ የምግብ እህሎች ባለፉት ሃያ ዓመታት ዕድሜ ለታዋቂው የምርት ገበያ ድርጅት ዓለም አቀፋዊ ተነጋጅ ሆነዋል፡፡ የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ሰላሳና አርባ ሺሕ ዶላር የሆኑ እስያውያንና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በሚሸምቱበት የገበያ ዋጋ በአምስት መቶ ዶላር ነፍስ ወከፍ ገቢያችን ለመሸመት ተገደን፣ በአገር ውስጥ ምን ያህል እንደተወደዱብንና በዋጋ ንረት የቁም ስቃያችንን እያየን እንደሆነ እናውቃለን፡፡

ኤክስፖርተሮች ወደ ውጭ አውጥቶ መሸጥ ይበልጥ የሚያዋጣቸው ከሆነ፣ ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረባቸውን ይቀንሳሉ ወይም የምግብ እህሎች ፍላጎት በዋጋ ለውጥ ብዙ የማይለወጡ (ኢተለዋጭ) ስለሆኑ፣ የአገር ውስጥ ሸማቾች በሌሎች ሸመታዎቻቸው እየተጎዱም ቢሆን የውጭ ሸማቾቹ የሚከፍሉትን ለመክፈል ተገደው የእህል ዋጋ መናሩ ይቀጥላል፡፡

በዚህም ላይ አንድ ዶላር ለመግዛት በገበያ ውስጥ የሚሰራጨውን ተጨማሪ አራት ብር ገደማ ብሔራዊ ባንኩ ቦንድ ,ጦ ከገበያ በማውጣት ካላመከነ፣ ገበያ ውስጥ የገባው ብር በዝቶ የዋጋ ንረትን ይፈጥራል፡፡

ገበሬው ተጠቅሟል ማለት የሚዳዳቸው ባለሙያዎች ቢኖሩ ገበሬው ሁሉንም ዓይነት ምርቶች ራሱ አያመርትም፡፡ በምስርና አተር ንግዱ አትራፊ የሆነ ገበሬ በቃሪያ፣ በሽንኩርት በቲማቲም ንግዱ ተጎጂ ስለሚሆን የግብርና ምርት መወደዱ ለገበሬውም ቢሆን እዚያው ሞላ እዚያው ፈላ ነው፡፡

ደርግ የእርሻ ሰብል ገበያ ድርጅትን አቋቁሞ ከተሜው በተመጣጣኝ ዋጋ እህል እንዲገበይ ያደረገውን ሙከራ ጥቂት የደርግ ባለሥልጣናት የተጠቀሙበት ይመስል ያወገዙ ምዕራባውያን፣ በአገር ውስጥ ገበያ  በአቅማችን ልክ ዋጋቸው ይተመን የነበሩ የምግብ ሰብሎች እኛ እየተራብን የመግዛት አቅም ላላቸው እስያውያንና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ተላልፈው መሸጣቸውን ዓለም አቀፋዊ የንግድ ውድድር ወይም ግሎባላይዜሽን ተፈጠረ በማለት አሞግሰውታል፡፡

ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ሥርዓት ቢኖር ኖሮ ወይ የእኛም ነፍስ ወከፍ ገቢ ከእስያውያኖቹና ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች መስተካከል ነበረበት ወይ? የእኛ የምግብ እህል ዋጋ ለእኛ ብቻ በእኛ ገበያዎች ብቻ መወሰን ነበረበት፡፡ በእርግጥ ይኼ የሕዝብ ስቃይ ቦሌ ተቀምጠው በኢትዮጵያ ምድር የአሜሪካዊያን የኑሮ ደረጃ እየኖሩ ኢኮኖሚው አደገ ተመነደገ ለሚሉ ዳያስፖራ ምሁራንና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሠራተኞች አይታያቸውም፡፡

የኢትዮጵያን ሕዝብ ኑሮ ለዛሬውም ሆነ ለወደፊቱ ምድራዊ ሲኦል የሚያደርገው የነፍስ ወከፍ ገቢያችን ከዓለም የመጨረሻው ደረጃ ላይ ሆኖ፣ የኤክስፖርትም የኢምፖርትም ሸቀጦች ዋጋ ግን ሰላሳና አርባ ሺሕ ዶላር ነፍስ ወከፍ ገቢ ባላቸው በዓለም አቀፍ የገበያ ዋጋ መወሰኑ ነው፡፡

በግሎባላይዜሽን ፍልስፍና በሁሉም አገሮች የሚመረቱ ሸቀጦች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተነጋጅ (Internationally Tradeable) እየሆኑ ስለሚመጡ፣ የገበያ ኢኮኖሚን ሳንለማመድ ልማታዊ እያልን ከደሃው በምንሰበስበው ግብር ለሀብታሙ እስከ ደጃፉ መሠረተ ልማት እያነጠፍንለት ከቀጠልን ተጎጂነታችን እየባሰበት ይመጣል፡፡

ባለፉት ሃያና ሰላሳ ዓመታት በግሎባላይዜሽን አብሮ መኖር በውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ ከተፈጠረው ተጨማሪ እሴት ወይም የአገር ውስጥ ምርት የታዳጊ አገሮች ሕዝቦች በደመወዝተኛነታቸው የዕለት ፍጆታ ወጪዎቻቸውን ብቻ ሲሸፍኑ፣ የበለፀጉት አገሮች ባለሀብቶች ግን የመዋዕለ ንዋይ ትርፋቸውን ወደ አገራቸው በመላክ ካፒታል አከማችተው ስምንቱ የዓለም ሀብታም ሰዎች ብቻ የዓለምን ግማሽ ሦስት ተኩል ቢሊዮን ሕዝብ የሚያህል ሀብት እንዳካበቱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ኢምፖርትን በማስወደድ ደረጃም የምንዛሪ መጣኝ ማሻሻያው በመርህ ደረጃ ትክክል ቢሆንም፣ ከውጭ ለሚገቡት ሸቀጦች ምትክ የሚሆኑ ምርቶች በአገር ውስጥ ደረጃ መቼ ተመርተው ነው ኢምፖርትን ለመተካት ተብሎ ነው የሚባለው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተስፋፉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሰማንያ አምስት በመቶ የባንክ ብድር ተሰጥቷቹ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ፋብሪካ ግቡ ቢባሉ፣ ባለሀብቶች ለመግባት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት ራሳቸው እየተናገሩ ነው፡፡

ባለሀብቶቹ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ሊገቡ ያልፈለጉበትን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ አንዱ ምክንያት የሰው ልጅ ሠርቶ ለማግኘት የሚሞክረው ተስፋ ሲኖረው ብቻ ስለሆነና ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ እንኳንስ የከርሞውን የነገውንም ተስፋ ማድረግ እያቃተ በመሆኑ ነው፡፡

ሁለተኛውና ዋና ምክንያት ነው የምለው ሃያ አምስት ዓመታት ሙሉ የልማት ሰው ሆኖ ከልማት አትርፎ ሀብት ያካበተ ሰው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የገበያ ኢኮኖሚ ሰው ሊሆን ስለማይችል ነው፡፡ በሃያ ዓመታት ውስጥ የልማት ራስና ደጃዝማቾች ሆነው የከበሩ ሰዎች ያጠራቀሙትን ሀብት ቁጭ ብለው ይበላሉ እንጂ ከሸቀጥ ማገለባበጥ ወዳለፈ ሥራ አይገቡም፡፡

እንደ እነ አቶ በቀለ ሞላ የገበያ ኢኮኖሚ አመለካከት ያለው ሰው ከእንቁላል ንግድ ወደ ታላላቅ ሆቴል ቤቶች ባለቤትነት ያድጋል እንጂ፣ ሀብቱ እንዴት እንደመጣ የማያውቅ ሰው በአንዴ ተነስቶ የገበያ ኢኮኖሚ አመለካከት ያለው ሰው አይሆንም፡፡ ላለፉት ሃያ ዓመታት ኢሕአዴግ በሰው የአመለካከት ለውጥ ላይ መሠራት እንዳለበት በባለሙያዎች ቢመከርም፣ ድንጋይ ሲደረድርና ሲያስደረድር ኖሮ ዛሬ በድንገት ባንኖ ለአመለካከት ለውጥ ራሱን ያዘጋጀ ይመስላል፡፡

ሃያ ዓመታት ሙሉ በልማት ኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ ብቻ አትኩሮ የሠራ መንግሥት፣ ድንገት ተነስቶ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ነድፌ ነጋዴውን ወደ ተወዳዳሪ አምራችነት ቀይሬ የኢኮኖሚውን ቀውስ አስወግዳለሁ ብሏል፡፡ እሳት ሲቆሰቆስ ያይላል እንጂ አይበርድም፡፡ እነዚህ የጥሬ ገንዘብ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች የብሔራዊ ኢኮኖሚውን አለመረጋጋት አባብሰው ሌሎች የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጦችን ይጠራሉ እንጂ፣ ብቻቸውን ለብዙ ጊዜ ተረስቶ ለተተወ የገበያ ኢኮኖሚ መፍትሔ አይሆኑም፡፡ 

የገበያ ኢኮኖሚ የማምረቻ ወጪዎችን ዓይነት፣ መጠንና የዋጋ ቅንብራቸውን አውቆ ተመጣጣኝ ትርፍ የሚያገኝበትን አደረጃጀት መርጦ ወደ ሥራ የሚገባበት እንጂ፣ በሃያ ዓመት አንዴ የታወጀ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲን አንድምታ የማያውቅ መንገደኛ ዘው ብሎ የሚገባበት አይደለም፡፡

ሃያ ዓመት ሙሉ አክራሪ የገበያ ኃይላት እያለ ሲያጥላላ ሰውን ሁሉ በልማት ኢኮኖሚ ሰውነት አመለካከት ሲቀርፅ የነበረው ኢሕአዴግ፣ ዛሬ ችግር ሲመጣ በአንድ ጊዜ ወደ የገበያ ኢኮኖሚ ሰውነት አመለካከት ሊቀይር ይችላል ወይ? እኛስ ይቅናህ እንላለን፡፡ ነገር ግን ‹ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ቆሞ ማውረድ ይቸግራል› የሚባለው እንደዚህ ያለው ነገር ነው፡፡

በጌታቸው አስፋው 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው  [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡