Skip to main content
x
ከ300 በላይ ሰዎች ያለቁበት የሞቃዲሾ ፍንዳታ

ከ300 በላይ ሰዎች ያለቁበት የሞቃዲሾ ፍንዳታ

በመኪና ላይ በተጠመዱ ወይም በእጅ በሚወረወሩ ቦምቦች ሶማሊያውያን ሕይወታቸውን ማጣት ከጀመሩ ሦስት አሠርታት አልፈዋል፡፡ በተለይ ከአሥር ዓመታት ወዲህ ጥንካሬውን ማሳየት የጀመረውና አሁን በሙሉ አቅሙ መንቀሳቀስ እንደተሳነው የሚነገርለት የሶማሊያው አልሻባብ ታጣቂዎች በሚፈጽሙት ግድያና ጠለፋ፣ ቀድሞውንም አቅም ያጣችውን ሶማሊያ መሰባበር ከጀመረም ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሶማሊያ አንድ ሳምንት ያለምንም የግድያ ዜና ካሳለፈችም እንዲሁ፡፡

 በታጣቂዎች የሚፈጸም ግድያ ፅድቅ እስኪመስል ድረስ ሕፃን፣ አዋቂ፣ ሴት፣ ወንድ ሳይል ታጣቂውንም ሆነ ወታደሩን እንዲሁም ንፁኃኑን ዕለት ከዕለት እየቀጠፈ ይገኛል፡፡ 

በየወሩ በሶማሊያዋ ሞቃዲሾ በአማካይ ሁለት ፍንዳታዎች ይከሰታሉ፡፡ ባለፈው ሰኔ ብቻ ታጣቂዎች በአንድ ምግብ ቤት ላይ በፈጸሙት ጥቃት ከ30 በላይ ተገድለዋል፡፡ ፖለቲከኞችና ነጋዴዎች በቀን ብርሃን ይገደላሉ፡፡ የዕርዳታ ሠራተኞች ይታገታሉ፡፡ ንፁኃን የመንገዱ በተጠመዱ ቦምቦች ድንገት የሞትን ፅዋ ይጨልጣሉ፡፡

ከ300 በላይ ሰዎች ያለቁበት የሞቃዲሾ ፍንዳታ
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመታደግ ጥረት ሲደረግ

 

በሞቃዲሾ የተቃጠሉ ቤቶችንና መኪናዎችን ማየቱ፣ በጥይት ተመትተውና በቦምብ አካላቸው እንዳልነበረ ሆኖ አውራ ጎዳና ላይ የተዘረጉ አስከሬኖችን በየመገናኛ ብዙኃኑ መመልከቱም፣ እንኳን ውስጡ ለሚኖሩት ለሩቅ ተመልካችም ከቃላት በላይ ነው፡፡

ሶማሊያውያን እንዲህ ባሉ ሁነቶችና አለመረጋጋት 30 ዓመታትን ቢያሳልፉም፣ ከመደበኛ ጦርነት ውጪ አሰቃቂና ዘግናኝ የተባለውንና ቅዳሜ ጥቅምት 4 ቀን 2010 ዓ.ም. የተፈጸመውን የተሽከርካሪ ቦምብ ፍንዳታ ዓይነት አስተናግደው አያውቁም፡፡ በሞቃዲሾ ሳፋሪ ሆቴል አካባቢ በሁለት ተሽከርካሪዎች ላይ በተጠመደ ቦምብ የተፈጸመው ጥቃት መጠኑም ሰፊ ነው፡፡

በተሽከርካሪዎቹ ላይ የተጠመዱት ቦምቦች ከ300 በላይ ንፁኃን ዜጎችን ገድለዋል፡፡ ቁጥሩ በግልጽ ባይታወቅም ብዙዎች ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡ 70 ያህል ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ለሕክምና ወደ ቱርክ ተልከዋል፡፡ የዕርዳታ ሠራተኞችም ጥቃቱ ከተፈጸመ አምስት ቀናት ቢሆነውም ከፍርስራሽ ሥር የወደቁትን ለማውጣት ርብርብ ላይ ናቸው፡፡ ይህ በሶማሊያ ከዚህ ቀደም ከተፈጸሙ የቦምብ ጥቃቶች ዘግናኝና በቁጥርም ሲታይ ከፍተኛው ነው፡፡

ኒውዮርክ ታይምስ እንዳሠፈረው፣ ከዚህ ቀደም ጥቃቶችን ፈጽሞ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ይናገር የነበረው አልሸባብ ድምፁን ያጠፋ ቢሆንም፣ አባላቱ እንዳቀነባበሩት እየተነገረ ነው፡፡ በሞቃዲሾ የሚገኙ ‹ንፁህ መሳይ› አባላቱም ትብብር አድርገው ይሆናል የሚል መላምት አለ፡፡

ከ300 በላይ ሰዎች ያለቁበት የሞቃዲሾ ፍንዳታ
ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ግለሰብ ሕይወቱን ለማትረፍ አውሮፕላን ላይ ሲጫን

 

ለመረጋጋት በመፍጨርጨር ላይ በምትገኘው ሶማሊያ በተለይም ሞቃዲሾ የሚገኙ ነዋሪዎች ድርጊቱን ተቃውመው ሠልፍ የወጡ ሲሆን፣ ጥቃቱንም ከአሜሪካው 9/11 ጋር አመሳስለውታል፡፡ የአገሪቱ ፕሬዚዳንትም የሦስት ቀናት ሐዘን አውጀዋል፡፡ የአልሸባብን አካሄድ በመቀየር ዳግም የተቋቋመው ሸባብ መሪም በጥቃቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ደም ሲለግሱ ተስተውለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም አብረዋቸው ለነበሩና አሁን ላይ ከአልቃይዳና ከአይኤስ ጋር ግንኙነት እንደመሠረቱ ለሚነገርላቸው ሚሊሻዎችም፣ ‹‹ከዚህ ቀደም ስናደርግ የነበረውን ጥቃት እናቁም፡፡ የቀድሞ ልማዳችንን እንተው፡፡ ከሕዝባችን ጋር አንድ ከመሆን ውጪ ለችግራችን መፍትሔ የለንም፤›› ሲሉም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

የደኅንነቱ አቅም ደካማ በሆነባት በሶማሊያ ሰላም ለማስፈን የተሰማራው ዓለም አቀፍ ኃይል እ.ኤ.አ.  በ2018 መጀመርያ ይወጣል የሚል ሐሳብ ከዚህ ቀደም ተሰንዝሯል፡፡ ሆኖም የዚህ ዕውን መሆን በየጊዜው ፍንዳታ የሚንጣትን ሶማሊያ የባሰ ውጥንቅጥ ውስጥ ይከታታል፡፡ ከዚህ ባለፍም በሶማሊያ ከሚገኘው አልሸባብ ተነጥሎ ከአልቃኢዳና አይኤስ ጋር የወገነው ታጣቂ ቡድን አገሪቷን ይቆጣጠራትና ለሶማሊያም ሆነ ለቀጣናው ብሎም ለዓለም ከፍተኛ ሥጋት ይሆናል፡፡

የሶማሊያ መንግሥት የአገሪቱን ደኅንነት ለማስጠበቅ አቅም የለውም ተብሎ ይወቀሳል፡፡ በየጊዜው በተሽከርካሪ ላይም ሆነ በመንገድ በሚጠመዱ ቦምቦች አሊያም በተኩስ የሚፈጸሙ ግድያዎች መኖራቸውም የመንግሥቱ ውድቀት ማሳያዎች እንደሆኑ ይነገራል፡፡

ከዚህ ቀደም ሰላም ለማስከበር የሄዳቸው ርቀቶችና ከአልሸባብ ያፀዳቸው አካባቢዎች ላይ በቂ ድጋፍ ማድረግ ካልተቻለ፣ ሶማሊያ ወደ ቀድሞ ውጥንቅጧ ትመለሳለች ሲልም በሶማሊያ 22 ሺሕ ሰላም አስከባሪ ያሉት የአፍሪካ ኅብረት አስጠንቅቋል፡፡

ከ300 በላይ ሰዎች ያለቁበት የሞቃዲሾ ፍንዳታ
የሞቃዲሾ ነዋሪዎች ከፍርስራሾች ውስጥ ተጎጂዎችን ሲፈልጉ

 

ባለፈው ክረምት የሶማሊያ የፓርላማ አባላትና አንዳንድ ዓለም አቀፍ ዕርዳታ ሰጪዎች ታጣቂው አልሸባብ መዳከሙን ገልጸው ነበር፡፡ በሶማሊያ የሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ‹‹አሚሶም››ም በአልሸባብ ተይዘው የነበሩ ሥፍራዎችን ማስለቀቁንና ወሳኝ አባላቱን መግደሉንም ገልጾ ነበር፡፡

በግንቦት በለንደን በተደረገ ኮንፈረንስም፣ የበለፀጉት አገሮች የሶማሊያን ወታደሮች በመደገፍና በማሠልጠን የአሚሶምን ሚና እንዲተኩ ከስምምነት ደርሰው ነበር፡፡

ሆኖም የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ አልሸባብ የሚያደርሰውን ጥቃትና ብጥብጥ ለማስቀረት ብዙ ዓመታት ያስፈልጋሉ፡፡ ለዚህ ማሳያውም ቅዳሜ በሞቃዲሾ የቦምብ ፍንዳታው በተከሰተበትና ከ300 በላይ ንፁኃን ሞተው የተጎዱ ሰዎች ቁጥር በግልጽ ባልታወቀበት ቅፅበት፣ ከሞቃዲሾ 31 ማይል ርቃ የምትገኘውን ባሪሬ አልሸባብ መቆጣጠሩ መነገሩ ነው፡፡

በእንግሊዝ በዋርዊክ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ፖለቲካ ጉዳዮች ፕሮፌሰር ዴቪድ አንደርሰን እንደሚሉት፣ ‹‹አልሸባብ አልጠፋም፡፡ በሚያደርሰው ጥቃት ሁሉ ውጤታማ የሆነ ሽምቅ ተዋጊም ነው፡፡ ጥቂት ጥቃት ሰንዝሮ ብዙ በመግደልም ተክኖበታል፡፡ ዒላማውን በመምታትም የተሻለ ነው፡፡

አልሸባብ ስላለመጥፋቱ ወይም ስላለመዳከሙ ማሳያውም የቅዳሜው ጥቃት ነው፡፡ ምንም እንኳን ለተፈጸመው ግድያ ኃላፊነቱን ባይወስድም፣ ሁለቱ ቦምብ የተጫኑ ተሽከርካሪዎች በተለያዩ አቅጣጫዎች በወታደር ተሽከርካሪ የሚጠበቀውንና በየመግቢያ ሥፍራው በመኪኖች ላይ ፍተሻ ከሚያደርገው የደኅንነት አካል አልፈው በሞቃዲሾ ንፁኃን ዜጎች በሚበዙበት ሥፍራ ጥቃቱን መፈጸማቸው አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ጥቃቱ አልሸባብ በሶማሊያ ደኅንነት አባላት ውስጥ ሰርጎ ገብቷል የሚል ጥርጣሬንም ጭሯል፡፡

ፕሮፌሰር አንደርሰንም፣ በአብዛኞቹ የሶማሊያ መንግሥት ተቋማት ውስጥ አልሸባብ ሰርጎ መግባቱን፣ ሆኖም ብዙዎች ስለዚህ ጉዳይ ማውራት አይፈልጉም ብለዋል፡፡