Skip to main content
x

ለመውጣት ግፊያ ለመውረድ ግፊያ!

እነሆ ጉዞ እነሆ መንገድ! ከጀሞ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። መስኮቶች ተከፋፍተዋል። በተከፈቱት መስኮቶች ተሻግሮ እየነፈሰ የሚገባው አየር ግን የተዘጋ ነው። እንዲያ ነው! “የቆጡን እናወርዳለን ብለው የብብታችንን አስጣሉን እኮ እናንተ?” ይላል አንዱ። ደንዳና ሰውነቱ መተማመኛ ዛኒጋባ እንዳጣ ያስታውቅ ነበር። ‘እንዴት? እነማን  ናቸው እነሱ?’ መሰል ተመሳሳይ ጥያቄዎች የሚጠይቀው ሰው አጠገቡ የለም። ውለውም ሆነ አድረው ተጠያቂዎቹና ተተችዎቹ ተመሳሳይ ናቸው። በምንመላለስበት ጎዳና ሁሉም የሰው ጉድፍ ጠቋሚ ነው። ራሱን የሚታዘበውና የሚተቸው ማን ነው? ወደ ውስጥ ከመተንፈስ ወደ ውጭ እየቀለለን አንዳንዱ አተነፋፈሳችን ግብዝነት እያጠቃው የመጣ ይመስላል። ከትናንት እስከ ዛሬ ምናልባት ነገም ይኼ ክፉ አመል ከመንገዱ የሚጠፋ አይመስልም።  ከጥግ እስከ ጥግ በዘርፍ በዘርፉ ወግ ይሰለቃል። የዶላር፣ የቲማቲም ዋጋ ንረት፣ የኳስ ሜዳው የዘቀጠ ተግባር ብዙ ይባልበታል፡፡ የባለሥልጣናት የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ጉዳይም ይነሳል፣ ይጣላል።

ሐሜቱ፣ ብስጭቱ፣ ምሬቱ፣ እንጉርጉሮው ልክ አልነበረውም። ልክ ያለው ነገር ጠፍቷል። እንቅስቃሴውና ሒደቱ ግን ያለማቋረጥ ቀጥሏል። በትናንቱ ጎዳና ላይ ዛሬም የሰለቹ ኮቴዎች ከእነ እንጉርጉሯቸው አቧራ ማቡነኑን ገፍተውበታል። ትዝታ አዘሉ ሒደት በማድያት የተወረረ ነው። ትውልድ ሊያጠራው ያልቻለ ችኮነት አለበት። እንኳን ሰውን መንገዱም ይኼ ችኮነት ሳይሰለቸው አልቀረም። ከግዑዝ እስከ ነፍስ አዋቂው የዚች ምድር ቋጠሮ ያላማረረው የለም። ግን ለመኖር ነገን መናፈቅ ግድ ነው፡፡ ያልታየን መመኘት አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነውና ከመሞት መሰንበት ዛሬም የኃይል ሚዛኑን እንደ ተቆጣጠረ ነው። “ይህ ባይሆን ምን እንሆን ነበር?” ይላል ከጎኔ የተቀመጠ ወጣት። አባባሉ ብቻ ከሐሳቤ ገጠመ እንጂ በምን ሰበብ እንዲያ እንዳለ አልተረዳሁትም። ይኼም አንድ ገጽታችን ነው። አለመደማመጥ!

ጉዟችን ተጀምሯል።“አያ ሞኛ ሞኝ ሰው ጥበብ የጎደለው፣ እህል ያከማቻል ስንቅ እየመሰለው” ይላል በገና ደርዳሪው። ወያላው፣ “ወይ ስምንተኛው ሺሕ! ሁዳዴ ሳይመጣ ምናለበት ማስመሰሉን ትተህ ዘፈን ብትከፍትልን?” እያለ ሾፌሩን ይለክፈዋል። ሾፌራችን፣ “ግዴለም ፆም ይምጣና እኔና አንተ እንገናኛለን፤” ሲል ይዝታል። “ጉድ ነው የዘንድሮ ሰው የሰፈረበት ጋኔን እንኳን በሁለት ወር በዓመት ፆምና ፀሎትም የሚለቀው አይመስልም። እንዲያው ብቻ ለይምሰል ካጨበጨቡት ሲያጨበጭብ፣ ከሰከሩት ሲሳከር፣ ከካዱት ሲወዳጅ፣ ካመኑት ሲስማማ መኖር ሲችልበት፤” ትላለች ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠች ጥርሰ ፍንጭት።

ደግሞ አጠገቧ ወዳለሁት ዘወር ብላ “ምን ዝም ትላለህ? እንቢም አንድ ነው። እሺም አንድ ነው። ዝም ምንድነው?” ስትለኝ ደንግጬ አያታለሁ። ጥያቄው አዕምሮዬ ውስጥ እየተጉላላ ጆሮዬ ላይ ቃሏ ይደውላል። ‘ዝም ምንድነው?’ ሾፌራችን በበገና ቅኝት ተመስጦ በቅኔ ማሳ እየዳከረ ከራሱ ጋር  ጥሞና ይዟል። “አንተ ሰውዬ በየት አገር ነው ሰው በገና እየደረደረና ትዝታ እየተጫወተ ወደፊት ሲጓዝ ያየኸው? በማታስ ግዴለም በቀን እንዳታስገኘን እባክህ?” አዛውንቱ ከምናቡ ዓለም ገሃድ ወደ ሆነው ጎዳና ሊመልሱት ያባብሉታል። ትንሽ ቆየት ይሉና ደግሞ፣ “ወይ አዲስ አበባ! ታጭታ ሳትዳር ጥሎሿ ቆሻሻና ግርግር ብቻ ሆነ። ምን ይሆን ሳንካዋ? ምን ይሆን ሕመሟ? ይኼ ቀለበት መንገድ እኮ ከጥቅሙ ጥፋቱ በዛ! ሳንተነፍስ ልንሞት ይሆን ግን?” አሉ፡፡ 

አንድ ‘ሲኖትራክ’ እና ‘አይሱዙ’ ተጋጭተው ቆመዋል። የደቀቀ መስታወት በሐሴት እንደ ጎዘጎዙት ጠጅ ሳር ሿ  ብሏል፡፡ “ምንድነው የሚሉት ሰውዬው? መንገድ ስጋጃ ነው? አልረባም ተብሎ ይጠቀለላል እንዴ? አሁን ገና በኢሕአዴግ ብቸኛ ታሪክ መጡ፤” ስትል ከአጠገቤ “አይ ሰው! ይኼኔ ባለፈው ወጣ ከተባለው የቤት ዕጣ ባለዕድል ሆና ቢሆን ኖሮ ምስክርነቷን አንችለውም ነበር። እንዲያው ግን የሃይማኖታችን፣ የፖለቲካችን፣ የልማዳችን ድምዳሜ ሁሉ ከጥቅማችን ውጭ ከሆነ ‘ኤክስ’ ነው ማለት ነው?” ወይዘሮዋ መጨረሻ ወንበር ወደ ተቀመጡበት ዞራ በለሆሳስ ጠየቀች። “ቢሆን ነዋ! ባይሆንማ ዛሬ  በአንብሮና በተቃርኖ መሀል ሦስተኛውን የመፍትሔ አስተምህሮ መንገድ በመፈለግ መጠመድ በተገባን ነበር። አለመታደል ከጽንፍ ጽንፍ ሆነን በደቦ ፉከራ፣ በጥቅም ተሳስረን በዘርና በሃይማኖት እየተሻኮትን ‘ኤክስና ራይት’ ለመለጣጠፍ እሽቅድምድም ጀምረናል፤” አለች ሞንሟኒት። መጨረሻ ወንበር የተደላደለ ጨብራራ፣ “እውነት ነው። በተለይ ይኼ ተቧድኖ መተራረብ ‘ፌስቡክ’ን  ወደ መልመጃ ደብተርነት ሊቀይረው ምንም አልቀረው፤” ብሎ ተናገረ። “ፌስቡክ ተከፈተ እንዴ?” ሲለው አጠገቡ የተቀመጠው፣ ‹‹መቼ ተዘግቶ ያውቃል ወንድሜ? ፌስቡክ አፍ መሰለህ እንዴ? ሶፍትዌር እኮ ነው፤›› ብሎ በምፀቱ አሽኮርምሞ አስፈገገን። አወይ ሰውና አፉ!

ጉዟችን እንደተጋመሰ ሁለት ተሳፋሪዎች ወርደው በምትካቸው አራት ተጫኑ። ሾፌሩ በመስኮቱ አሻግሮ በተቃራኒ አቅጣጫ የሚመጣ ባለታክሲ ወዳጁን በመጣበት መንገድ የትራፊክ ፖሊስ መኖር አለመኖሩን ይጠይቀዋል። “የለም!” ብሎ ይመልሳል። “ጫን በደንብ!” ይለዋል ሾፌሩ ወያላውን። እኛ ዝም። “ለማን አቤት ይባላል? ቢባልስ እስካሁን ያልነው አይበቃም ነበር?” ይላል ጎልማሳው። ጠይሟ ቆንጆ ወጣት በበኩሏ፣ “ትራፊኮቻችን ጠጥቶ ማሽከርከርን ለማስቆም ማታ ማታ ማምሸት ስለጀመሩ የቀኑን ትተውታል። ሳስበው ሳስበው ግን የማታዋ ጠቅ ጠቅ ታዋጣለች መሰለኝ፤” አለች። አልኩ ለማለት ደግሞ አንዱ፣ “አስተዳዳሪዎቻችን እንኳን ተነግሯቸው ላያቸው ላይ አስተዳደር ቢገነባባቸውም አይነቁ፤” አለ። የሚስቅ ይስቃል። ሌላው፣ “በፈጠራችሁ ስለቲማቲም አውሩ እስኪ። ሳንበላ እንዴት ብለን ነው ጠጥቶ ስለማሽከርከር የምንጨነቀው? አይደል እህት?” ይላታል ከመጨረሻ ወንበር። “ተስፋ መቁረጥ የለም!” ብሎ አንዱ ሲጮህ ሁላችንም ዞረን ዓየነው።

ሙሉ ልብስ ነው የለበሰው። በእጁ የ’ላፕቶፕ’ ቦርሳ ይዟል። “እኔን ከመረጣችሁኝ ችግራችሁን ሁሉ ገደል ነው የምሰደው፤” ብሎ ቅስቀሳውን ጀመረ። “እሺ ትራምፕ?” አለው ወያላው። ሰውዬው ወዲያው ለመጪው ምርጫ ዕጩ የግል ተወዳዳሪ ለመሆን ማሰቡን ነገረን። “ለመሆኑ . . .” አለው አንድ ተሳፋሪ አጠገቡ ቁጭ ብሎ ኖሮ። “. . . እንዴት ብለህ ነው የታክሲ ሠልፍንና የዶላር ጭማሪን በቁጥጥራችን ሥር የምታውለው? ቲማቲምን ከአልማዝነት እንደ ስፔኖች ወደ መጫወቻነት የምትቀይረው? መቼም እንደ ትራምፕ ሠልፈኛው እንዳይታይ ግንብ እገነባለሁ፡፡ ቲማቲም ነቅዬ ጫት እተክላለሁ እንዳትለን. . .” ብሎ አንዱ ጠየቀው። ሙሉ ፈገግታ ፊቱን ወርሶት “ይኼማ ቀላል ነው። አያችሁ ብዙዎቻችን ከእንቅስቃሴ ጋር ተቆራርጠናል። ጠንካራና ጤናማ ዜጋ ለአንድ አገር ህልውና ወሳኝ ነው። ጠንካራና ጤነኛ ኅብረተሰብ የአገሩን ዳር ድንበር  ከማስከበር አልፎ በጥሩ ሁኔታ ሳይደክመው እየሠራ ጥሩ ግብር ከፋይ ይሆናል። ስለዚህ የታክሲ ችግርን መቅረፍ የሚቻለው በእግር ለመሄድ ስንወስን ነው። ጤናችሁንና ገንዘባችሁን ገና በብዙ ጉዳዮች ዙሪያ ስለማተርፍላችሁ ግዴለም እኔን ምረጡ! አመሰግናለሁ፤” ሲል ታክሲዋ ደም በለበሱ ዓይኖች ንዴት በሚያቁነጠንጣቸው ተሳፋሪዎች ተሞላች። “ወሬ እንደሰለቸን የሚገባው ቢኖር ኖሮ ምላስ በመቁረጥ ቅስቀሳ ድምፅ ይሰጠው ነበር!” የሚሉት አዛውንቱ ነበሩ።  

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። በተቀደደው ስፒከር በኩል ‘ወገኔ ያገር ልጅ ወገኔ’ የሚል ዜማ አትኮሮታችንን ሰርቆ ይሰማል። ‘እንሟገትላት እናንሳት እያሏት፣ መቼም ያፈራችው አይጠላት አይጠላት’ የሚል ስንኝ ተሳፋሪውን ከንፈር ያስመጥጠዋል። “ይገርማል እኮ እናንተ አላችሁ በሚሉን ሕገ መንግሥታዊ መብት ተጠቅመን ከምንጮኸው ይልቅ በአምባሰልና በትዝታ ቅኝት የምንተነፍሰው ተሻለን እኮ፤” ይላል ከመሀል። ሌላው ደግሞ ተቀብሎ፣ “በባዶ ሆድና በባዶ ጭንቅላት መብት ብሎ ነገር ነው የማይገባኝ!” ይላል። ሰው የሚናገረው በገባውና በሚያውቀውን ልክ መሆኑን አስምረንበት እንደማመጣለን። “ታዲያ መብታችንን ለሆድና ለጥቅም አሳልፈን እየሰጠን ሙሰኛውና አምባገነኑ ቢፈነጭብን ምን ይገርማል?” ትላለች ወጣቷ። “ንሺማ ጠይቂው?” ይላል በወዲህኛው መደዳ ጋቢ የለበሰ የአገር ቤት ሰው።

“ይኼ እኮ ነው የአገሬው ችግር። ሦስተኛው ዓለም  ውስጥ እንደምንኖር እንረሳዋለን። የዕውቀትና የምግብ ዋስትናችንን ሳናረጋግጥ የመብት ዋስትና ለማረጋገጥ የኋሊት እንራመዳለን። በዴሞክራሲ ስም ዲክታተር እንኮለኩላለን። በአብዮት ስም ትህትናን ጥለን ትዕቢት እንሸላለማለን፤” እያለ ወጣቱ አባባሉን ለማስረዳት ተጣጣረ። “አቦ አትፈላሰፍ! ፍልስፍና እንኳን ለአንተ ለእነ ማርክስና ለእነ ሌኒንም አልጠቀመ፤” ሲል ከወዲያ ማዶ አንዱ ቀጠን ባለ ድምፅ፣ ‹‹አልሰማህም እንዴ? ብሔረዝም የሚባል ፍልስፍና ሊታተም ነው አሉ። ወሬውን ያገኘሁት ከቢቢሲ ነው፤” አለ። ወዲህ ደግሞ፣ “አንዳንዱ ሰው እኮ ይገርማል! አንዱ ስሙን በቋሚነት ለማይኖር ሐውልትና ዝና ቀርፆ ኖሮ ለማለፍ ይፍጨረጨራል። ሌላው እንደምታዩት ፈሪና ጭስ መውጫ አያጣም ዓይነት ጨዋታ ይጫወታል። እኔም ሰሞኑን እያሰብኩ ያለሁት ከኃላፊነቴ ለመሸሽ ነው። ምን ትመክሩኛላችሁ? ምክንያቱን ወደፊት እነግራችኋለሁ፤” ሲል ተሳፋሪዎች በሳቅ ታመሱ። ወያላው ‹‹መጨረሻ!›› ሲለን ተጋፍተን እንደተሳፈርን እየተጋፋን ወረድን፡፡ ለመውጣት ግፊያ ለመውረድ ግፊያ፡፡ መልካም ጉዞ!