Skip to main content
x
ከክቡር ሚኒስትሩ ጋር ውጭ አገር ቢዝነስ የሚሠራ ወዳጃቸው ደወለላቸው

ከክቡር ሚኒስትሩ ጋር ውጭ አገር ቢዝነስ የሚሠራ ወዳጃቸው ደወለላቸው

[ክቡር ሚኒስትሩን ለማነጋገር አንድ ሰው ቢሯቸው መጥቷል፡፡ ጸሐፊያቸው ቢሯቸው ገባች]

 • ክቡር ሚኒስትር የመጣ እንግዳ አለ፡፡
 • ዛሬ ቀጠሮ አለኝ እንዴ?
 • ቀጠሮ እንኳን አልነበረዎትም፡፡
 • ታዲያ ማን ነው ያለ ቀጠሮ የሚያገኘኝ?
 • ክቡር ሚኒስትሩን ካላገኘኋቸው ከዚህ አልሄድም እያለ ነው፡፡
 • ሥራ ላይ ናቸው ለምን አትይውም?
 • ሥራ ግን አልያዙም ብዬ ነው፡፡
 • አንቺ ነሽ እንዴ ሥራ የምትሰጪኝ?
 • እንደዛ ማለቴ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ታዲያ ምን እያልሽ ነው?
 • ሰውዬው የሚሄድ ዓይነት አይደለም፡፡
 • ለመሆኑ ምን ፈልጐ ነው?
 • ጉዳዬ እሳቸው ጋር ነው ስላለኝ ምን እንደፈለገ አላወቅኩም፡፡
 • እኔ እኮ የአገር እንጂ የግለሰብ ጉዳይ አልመለከትም፡፡
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ማንም ግለሰብ ካላናገርኩት ስላለ ማናገር አለብኝ?
 • ምናልባት ሰውዬው የያዘው የአገር ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡
 • ይኼኔ ገንዘብ እርዳኝ ሊል ይሆናል፡፡
 • መጀመርያ ገብቶ ጉዳዩን ቢሰሙት አይሻልም?
 • እሺ አስገቢው፡፡

[ግለሰቡ ክቡር ሚኒስትር ቢሮ ገባ]

 • እስቲ ተቀመጥ፡፡
 • አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምንድን ነበር ጉዳይህ?
 • ምነው ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ምን ሆነሃል?
 • ረሱኝ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • እንተዋወቃለን እንዴ?
 • ተው እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ሆነሃል ሰውዬ?
 • ረስተውኛል ማለት ነው፡፡
 • እኔ እኮ ብዙ ሰው ነው የማገኘው፡፡
 • ምንም ትዝ አላልኩዎትም?
 • እንግዲህ ሥራዬ ከብዙ ሰዎች ጋር ስለሚያገኛኘኝ አላስታወስኩህም፡፡
 • የእኔ ግን ለየት ያለ ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለየት ያለ ስትል?
 • እርስዎ አይደል እንዴ የተቀበሉኝ?
 • ሰውዬ ከአንተ ምንም ዓይነት ጉቦ አልተቀበልኩም፡፡
 • እኔ ስለጉቦ መቼ አወራሁ?
 • ኮሚሽን ቢሆንም ከአንተ አልተቀበልኩም፡፡
 • ምን ያለበት ዝላይ አይችልም አሉ፡፡
 • ምን?
 • እኔ ስለጉቦም ስለኮሚሽንም አይደለም የማወራው፡፡
 • ታዲያ ምንድነው የተቀበልኩህ?
 • ባለፈው እርስዎ ነበሩ ከኤርፖርት የተቀበሉኝ፡፡
 • ዘመዴ ነህ እንዴ?
 • ኧረ አይደለሁም፡፡
 • ምንድን ነው የምታወራው ታዲያ?
 • ከሳዑዲ ተመላሾች መካከል አንዱ ነኝ፡፡
 • እሺ፡፡
 • ባለፈው ከእርስዎ ጋር በየሚዲያው ኢንተርቪ ስደረግ ነበር፡፡
 • ውይ ውይ ውይ፡፡
 • ችግር የለውም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ዛሬ ታዲያ ከየት ብቅ አልክ?
 • ግራ ገብቶኝ ነው የመጣሁት ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ሆንክ?
 • ያኔ ስንት ነገር ሰብካችሁን ወደ አገር ቤት ተመለሱ ባላችሁን መሠረት ተመለስን፡፡
 • ታዲያ አገሪቷ በልማት እየተመነደገች አይደል እንዴ?
 • ስለየትኛዋ አገር ነው የሚያወሩት?
 • ስለኢትዮጵያ ነዋ፡፡
 • ይኸው ባለፈው አገራችሁ ውስጥ ሠርታችሁ ማደግ ትችላላችሁ ተብለን ብንመጣም ምንም ዓይነት ሥራ የለም፡፡
 • እስካሁን ሥራ አልጀመርክም?
 • ጭራሽ አዲስ ባወጣሁት ስልክ ላይ ከሳዑዲ ተመላሾችን ለማቋቋም ገንዘብ እርዳ ተብሎ ተላከልኝ፡፡
 • ታዲያ ብትረዳ ምን አለበት?
 • ለነገሩ ውጭ የሚወራውና አገር ውስጥ ያለው ነገር በጣም የተለያየ መሆኑን አረጋግጫለሁ፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • አገሬ ስመጣ ሠርቼ አድጋለሁ ብዬ አስቤ ነበር፡፡
 • ከሠራህማ መለወጥህ አይቀርም፡፡
 • እንደገባኝ አገሪቷ ላይ ሠርቶ ማደግ አይቻልም፡፡
 • ታዲያ ምንድነው የሚቻለው?
 • ሠርቆ ማደግ!

 

[ከክቡር ሚኒስትሩ ጋር ውጭ አገር ቢዝነስ የሚሠራ ወዳጃቸው ደወለላቸው]

 • ሄሎ ክቡር ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • የት ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትር?
 • አገሬ ነዋ፡፡
 • አሁን እንደው አፍ ሞልቶ አገር አለ ማለት ይቻላል?
 • ምን እያልክ? ደግሞ ምን ተፈጠረ?
 • ይኸው በየቀኑ የምንሰማው እልቂት፣ መፈናቀል፣ ግጭትና ረብሻ አይደል እንዴ?
 • እባክህ ይኼ የፀረ ሰላም ኃይሎች ወሬ ነው፡፡
 • እና አገር ሰላም ነው እያሉኝ ነው?
 • ሰላም ቢሉህ ሰላም ነው እንዴ?
 • ኧረ ተው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እውነቴን ነው የምልህ፤ ሰሞኑን ራሱ ከአንድ ሥራ ያገኘሁት ትርፍ ቀላል እንዳይመስልህ?
 • ከምንድን ነው ትርፍ ያገኙት?
 • ከዶላር ጭማሪው፡፡
 • እውነት?
 • በቃ የጀመርኩትን ሕንፃ የሚያስጨርሰኝ ነው ስልህ?
 • ግብር ከፈሉ ታዲያ?
 • የምን ግብር?
 • ይኼን ንፋስ አመጣሽ ታክስ ምናምን የሚሉትን ነዋ፡፡
 • ንፋሱን ያመጣሁት እኔ አይደለሁ እንዴ?
 • ለነገሩ እርስዎ እንኳን ንፋስ አውሎ ንፋስ ማስነሳት ይችላሉ፡፡
 • ስለዚህ ስለአገሪቷ ብዙም አትጨነቅ፡፡
 • እኔማ አንድ ነገር ላማክርዎት ነበር፡፡
 • ምንድን ነው የምታማክረኝ?
 • ማለቴ አገሪቷ ውስጥ ያለው ሁኔታ የሚያስፈራ ነው፡፡
 • ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
 • ያው ያሉንን ሕንፃዎች፣ ፋብሪካዎችና ንብረቶች ወደዚህ ብናሸሽ ብዬ ነው፡፡
 • ለምን ሲባል?
 • እንደነገርኩዎት የአገሪቷ ሁኔታ እያስፈራኝ ነው፡፡
 • ስማ ዝም ብለህ አትምቦቅቦቅ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሀብታችንን ሳናሸሽ አንድ ነገር ቢፈጠር እኮ ክፉኛ ነው የምንጐዳው፡፡
 • እዚህ ልማትና ልማት ብቻ ነው ያለው ስልህ?
 • ይኼ የሚሰማው ብጥብጥ ግጭት ምንድነው?
 • የፀረ ልማት ኃይሎች ሥራ ነው ስልህ?
 • እኔ ግን ብዙም አላማረኝም፡፡
 • ምንም አትፍራ አልኩህ?
 • ሕዝብ እኮ እምቢ እያለ ነው፡፡
 • ከቁጥጥራችን ውጪ አይወጣም ስልህ?
 • ብቻ ጐርፉ ይዞዎት እንዳይሄድ?
 • የቱ ጐርፍ?
 • የሕዝቡ ጐርፍ!

 

[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ የአገር ሽማግሌ ደውሉላቸው]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት ነዎት ጋሼ? ዛሬ ከየት ተገኙ?
 • መቼም እኔ አገር ሲታመስ ነው የምደውለው፡፡
 • ኧረ ሁላችንም ጤና ነን፡፡
 • ተው እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምነው?
 • ምንድን እየተሠራ ነው?
 • ግድብ፣ ባቡር፣ የኢንዱስትሪ ፓርክና ሌሎችም እየተሠሩ ነው፡፡
 • ለጊዜው ባልቱን እንተወው፡፡
 • የምን ቧልት ነው?
 • አገሪቷ አጣብቂኝ ውስጥ እኮ ናት ያለችው፡፡
 • የምን አጣብቂኝ ነው ጋሼ?
 • እኛ ይህቺ አገር እንዳትፈርስ ምን ያህል መስዋትነት እንደከፈልን ያውቃሉ?
 • እሱን በሚገባ አውቃለሁ፡፡
 • ለልጆቻችን ግን ምን ዓይነት አገር ጥለን ነው የምናልፈው?
 • የበለፀገችና ተወዳጅ አገር፡፡
 • የበለፀገች አገር ለማድረግ እየሠራን ነው ብላችሁ ታምናላችሁ?
 • ይኸው የአገሪቷ ኢኮኖሚ በ11 በመቶ ሲያድግ እኮ የእኛ እንቅልፍ በ11 በመቶ ቀንሷል፡፡
 • ታዲያ የማትተኙት ስትሠሩ ነው ስታሴሩ?
 • ምን እያሉን ነው ጋሼ?
 • ይኸው የሴራ ፖለቲካ እኮ አገሪቷን ቁልቁል እየወሰዳት ነው፡፡
 • ስለምን እያወሩ እንደሆነ አልገባኝም?
 • አገሪቷ ውስጥ ሰዎች እየሞቱ አይደል እንዴ?
 • ይኼ እኮ አንዳንድ ሚዲያዎች የሚያናፍሱት ተራ አሉባልታ ነው፡፡
 • እኔ እንደሚያገባኝ ግን የሚዲያ ጨዋታውን ወደ ጎን ትቶ ለሕዝቡ ምላሽ መስጠቱ ያዋጣል፡፡
 • ጋሼ አገሪቷ ለምን  አልታመሰችም ብሎ ወሬ የሚያራግቡት ሚዲያዎቹ ናቸው፡፡
 • ኧረ የምትመሯት አገር ትልቅ ናት፡፡
 • እሱንማ እናውቃለን፡፡
 • ታዲያ የሕዝቡን ጥያቄ ለምን አትመልሱም?
 • ሁልጊዜ የሕዝቡን ጥያቄ እንደመለስን አይደል እንዴ?
 • ክቡር ሚኒስትር ለሚዲያ መግለጫ እየሰጡ አይደለም እኮ፡፡
 • ምን እያሉ ነው?
 • አገሪቷ ላይ እየተካሄደ ያለውን ነገር በሚገባ አውቀዋለሁ፡፡
 • የሰሞኑ ግርግር እኮ በፀረ ልማት ኃይሎች የተቀነባበረ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር በአጠቃላይ አገሪቷ እኮ በብሔር ፖለቲካ እየተናወጠች ነው፡፡
 • ኢትዮጵያዊነት ላይ ወጥረን እየሠራን ነው፡፡
 • በፊት እሱን ስንመክራችሁ መቼ ሰማችሁ?
 • ይኸው አንድነትን እየሰበክን እኮ ነው፡፡
 • መቼም ገበሬ ስንዴ ዘርቶ ብርቱካን አይጠብቅም?
 • እንዴት ሆኖ ጋሼ?
 • እናንተስ እንዴት አንድነት ይመጣል ብላችሁ ትጠብቃላችሁ?
 • ለምን አይመጣም?
 • ክፍፍል ዘርታችሁ…
 • እ…
 • አንድነት ሊመጣ?

 

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ዲፕሎማት ደወለላቸው]

 • በአገር አሉ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ከአገሬ ወዴት እሄዳለሁ ብለህ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር በየቦታው ግጭትና ረብሻ በዛ እኮ፡፡
 • የምን ግጭት ነው?
 • አስቸኳይ ጊዜው በድጋሚ ታውጇል እንዴ?
 • ከተነሳ መቆየቱን አታውቅም?
 • ይኸው ለሥራ ከከተማ መውጣት አልቻልኩም ብዬ ነዋ፡፡
 • ምን ነካህ አገሪቷ በጣም የተረጋጋች ናት?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ መረጃ ላይ ተመሥርቼ ነው የማወራዎት፡፡
 • ቢሆንም መረጃህን ማጣራት አለብህ፡፡
 • ይኼ አካሄድ ለማንም የሚያዋጣ አይመስለኝም፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር ከሕዝቡ ጋር ቁጭ ብላችሁ ለምን አታወሩም?
 •  ምን ብለን ነው የምናወራው?
 • ጥያቄውን መስማት አለባችሁ፡፡
 • እኛ ሁሌም የሕዝብ ጥያቄ እንደሰማን ነው፡፡
 • ለማንኛውም ክቡር ሚኒስትር ይህቺ አገር ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግባለች፡፡
 • ዕድገታችንማ ተጧጡፎ ይቀጥላል፡፡
 • ዕድገቱ የመጣው ዳግም አገሪቷ ሰላም በመሆኗ ነው፡፡
 • እሱስ ልክ ነህ፡፡
 • የአገሪቷ ሰላም መሆን በርካታ የውጭ ኢንቨስተሮች ወደዚህ እንዲመጡ ያደርጋል፡፡
 • አንተም የአገርህን ኢንቨስተሮች መጋበዝህን አትርሳ፡፡
 • በዚህ ሁኔታማ እንኳን ሌላ ሊመጣ ያለውም ሊለቅ ይችላል፡፡
 • ለምን ሲባል?
 • ክቡር ሚኒስትር የአገሪቷ ሰላም ይታሰብበት፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ችግራችሁን ፍቱ፤ ያበለዚያ…
 • እ…
 • የ11 በመቶ ዕድገት ይቀለበሳል፡፡
 • ወደ ምን?
 • ወደ ኔጌቴቭ 11!