Skip to main content
x
ኢትዮጵያ ለደን ያደላ ኢኮኖሚ ብትመሠርት ኖሮ ይህን ያህል የምግብ ዋስትና ችግርም ሆነ ድህነት ይኖራል ብዬ አልገምትም

‹‹ኢትዮጵያ ለደን ያደላ ኢኮኖሚ ብትመሠርት ኖሮ ይህን ያህል የምግብ ዋስትና ችግርም ሆነ ድህነት ይኖራል ብዬ አልገምትም››

ሙሉጌታ ልመንህ (ዶ/ር)፣ በፋርም አፍሪካ የምሥራቅ አፍሪካ የደንና የተፈጥሮ ሀብት ኃላፊ

ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በደን ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪቸውን ያገኙት ሙሉጌታ ልመንህ (ዶ/ር)፣ ከኔዘርላንድስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሲያገኙ፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በስዊድን ተከታትለው በመምጣት ላለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ የደን ሳይንስ መስክ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ ጊዜ ውስጥ 18 ዓመታትን ያሳለፉት በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በደን ሳይንስ መስክ በማስተማር እንደሆነ ገልጸው፣ የወንዶ ገነት የደን ምርምር ማዕከልን ተቀላልቀው ከማስተማር ባሻገር 90 የሚደርሱ በርካታ ምርምሮችን ከሙያ አጋሮቻቸው ጋር ሲያከናውኑና የምርምር ውጤቶቻቸውንም ሲያሳትሙ ቆይተዋል፡፡ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በእንግሊዝ የፋርም አፍሪካ ተራድኦ ድርጅት ውስጥ የምሥራቅ አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብትና የደን አስተዳደር ኃላፊ ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ አቶ ሙሉጌታ በቅርቡ በባሌ አካባቢ ሲካሄድ ከቆየው ማኅበረሰብ አቀፍ አሳታፊ የደን አስተዳደርና ክብካቤ ሥራ ምክንያት ከ12 ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት ከመጨፍጨፍ ተርፎ፣ ለአገሪቱ የካርቦን ንግድ አስተዋጽኦ የሚያረክት የ5.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ክምችት መገኘቱን ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርገው ነበር፡፡ ስለአገሪቱ የደን ሀብት በሙያዊ ቁጭት የሚያብራሩት አቶ ሙሉጌታ፣ የደን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በአግባቡ ሊታይና ሊታወቅ ባለመቻሉ ምክንያት አገሪቱ እንደ ቻይና፣ ፊንላንድና ስዊድን ከደን ማግኘት የሚገባትን ትልቅ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማግኘት እንዳልቻለች ይናገራሉ፡፡ ደን መጠበቅና መንከባከብ ውጤት የሚኖረው የኅብረተሰቡ ተጠቃሚነት ሲረጋገጥ እንደሆነ የሚያምኑት አቶ ሙሉጌታ፣ ኢትዮጵያ በደን ልማትና አጠቃቀም መስክ ልትከተል ስለሚገባት አቅጣጫዎች፣ ስለደን ይዞታ እየተምታቱ የሚቀርቡ የትርጓሜ አገላለጾችና ሌሎችም ጉዳዮችን በተመለከተ ከብርሃኑ ፈቃደ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- የደን ክብካቤ ከእርሻ ሥራ ጋር የሚቃረንባቸው አጋጣሚዎች ይስተዋላሉ፡፡ እርስዎ በጥናት ያቀረቡት ውጤት የደን ክብካቤ በባሌ አካባቢ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ያሳየ ነው፡፡ አካባቢው በግብርናም ትልቅ ድርሻ ያለው ነው፡፡ ባሌ በአገሪቱ የስንዴ ሰንሰለት ተብለው ከተለዩ አካቢባዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በሌላ በኩል የደን ጥበቃ ሥራዎችም እየተካሄዱበት ነው፡፡ አገኘን ያላችሁት ውጤት ሲመጣ ፈተናውስ ምንድን ነበር? አንዱን ለማግኘት ሲባል ሌላኛው ላይ የነበረው ጫና ወይም ‹‹ኦፖርቹኒቲ ኮስት›› በሁለቱ መካከል እንዴት ነው የሚታየው?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- ደንና ግብርና እንደምታሳየው ዓይነት የሁለቱ ጥምረት ተቃራኒም ተደጋጋፊም የሚሆኑበት አጋጣሚ አለ፡፡ ሁለቱም መሬት ይፈልጋሉ፡፡ ሁለቱም በተወሰነ መሬት ላይ የሚወዳደሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ተደጋግፈው መሄድ የሚችሉ ቢሆኑም፣ አንዱ ሌላውን የሚጋፉበትና የሚቃረንበት አጋጣሚም አለ፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት አንደኛው የአገሪቱ የልማት ፖሊሲ ላይ የሚመረኮዝ ነው፡፡ ያደጉ አገሮች የግብርና መሬታቸው እየጠበበ የደን መሬታቸው እየሰፋ ነው፡፡ ይህ የሚሆንበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ግብርና ላይ ኑሮውን የመሠረተው የሕዝብ ቁጥር እየቀነሰ በመምጣቱ ነው፡፡ ወደ ኢንዱስትሪው፣ ወደ አገልግሎት መስክ፣ ወደ ከተማውና ወደ ሌላውም ዘርፍ እየገባ ሲሄድ የገጠር መሬት እየተስፋፋና የግብርና መሬት እየቀነሰ ስለሚመጣ የደን መሬት እየጨመረ የሚሄድባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ እያደገ ያለ አገር፣ የአገሩ ኢኮኖሚ ግብርና ላይ የተመሠረተ ከሆነ ግን የግብርና ጉዳይ ይጎላል፡፡ በግብርና ፈጣን ገቢ ይገኛል፡፡ መሬት ታርሶ በአንድ ዓመት ውስጥ የሆነ ገቢ ማግኘት ይቻላል፡፡ እርሻን ትቶ ወደ ደን ልማት ለመግባት ግን የ15 ወይም የ20 ዓመታት ጥበቃ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ያህል ጊዜ የሚያስጠብቅ ጉሮሮ ግን የለም፡፡ ሆኖም የደንን ዋጋ ብናውቀው ግን መለወጥ ይቻላል፡፡

በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ያሉ አርሶ አደሮች የእርሻ መሬታቸውን ወደ ባህር ዛፍ ይዞታነት እየቀየሩት ነው፡፡ ባህር ዛፍን ወደውት አይደለም፡፡ ከባህር ዛፍ የተሻለ ገቢ እንደሚገኝ ስላረጋገጡ ነው፡፡ በከተሞች አካባቢ የሚታየው የግንባታ ዕድገት የባህር ዛፍ የአጠና ዋጋን እያናረው በመምጣቱ፣ ከትንሽ ባህር ዛፍ ሽያጭ የሚያገኘው የገቢ መጠን ከእርሻው ከሚያገኘው የበለጠ ስለሆነ ወደ ባህር ዛፍ እየቀየረው ነው፡፡ የእርሻ መሬት ምርታማነቱ እየቀነሰ በመሆኑም ጭምር ይህ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖለታል፡፡ ጭልሞ አካባቢ በፋርም አፍሪካ በኩል ትንሽ መሬት ላይ ሰው ሠራሽ ተከላን በማስፋፋት አርሶ አደሩ ከእንጨት ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ጋር በማገናኘት ትስስር እንዲፈጠር ለማድረግ ሞክረናል፡፡ የግል ባለሀብቱ እየፈራ አርሶ አደሩ ግን የደን ውጤቱን እያለማ ሲሠራ ታይቷል፡፡ ይሁንና የሥልጠና እና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል፡፡ ስለዚህ ከሰብል ልማት ወደ ደን ልማት የሚሸጋገሩበትን የ15 ወይም የ20 ዓመታት የሚደግፍ ሥርዓት ያፈልጋል፡፡ መንግሥት ወይም የግል ዘርፉ ይህንን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

እንደ ኡጋንዳ ባሉ አገሮች የደን ልማት ፈንድ የሚባል አሠራር አላቸው፡፡ የፋይናንስ ተቋማት ቤትና ሌላውን ንብረት እንደ ብድር ማስያዣ ይጠቀማሉ፡፡ ደንም አንዱ የንብረት ዋስትና ቢደረግ ትልቅ ለውጥ ያመጣል፡፡ ደኑን እንደ ዋጋ ብንቆጥርለት ትልቅ ጥቅም ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ደኑን ለአሥር ዓመታት ጠብቆ አሥር ሺሕ ብር የሚያገኝ ከሆነ፣ ይህንን ገንዝብ እንደ ብድር ብንሰጠውና በየዓመቱ ለሚያስፈልገው ፍጆታው እንዲያውለው ብንከፍለው ትልቅ ውጤት ያስገኝ ነበር፡፡ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የደን ኢንተርፕራይዞች አሉ፡፡ እነዚህን እንደ ሙከራ ብንጠቀምባቸውና ከደን የሚያኙትን ትርፍ አርሶ አደሩን ለመደገፍ ቢያውሉ፣ ደኑ ከእርሻ የተሻለ ገቢ እንደሚያመጣ ብናሳይ ደንና እርሻ አይቃረኑም ነበር፡፡ ደንና እርሻ የሚቃረኑት በሰው ሠራሽ ምክንያቶች እንጂ በተፈጥሮ አይደለም፡፡ ዳገታማ ቦታዎችን ለደን እያዋልን የተንጣለለውን ሜዳማ መሬት ለእርሻ ብናደርገው ጎርፍን በማስቀረትና የአፈር መታጠብን በመቀነስ ለምነቱን ማስጠበቅ ይቻል ነበር፡፡ ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ሰነድ ውስጥ ይህ አሠራር በጉልህ ተቀምጧል፡፡ ወደ ተግባር መቀየሩ ላይ ብዙ ይቀረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በአደጉና ባላደጉ አገሮች መካከል የነበረ ክርክር አለ፡፡ ያደጉ አገሮች አብዛኛውን ብክለት እያመነጩ ያላደጉ አገሮችን ተጎጂ እያደረጉ ነው፡፡ ያላደጉ አገሮች የተፈጥሮ ሀብታቸውን እንዳይጠቀሙ ጫና እያደረጉ ነው፡፡ ደን ጠብቁ፣ ተንከባከቡ፣ ወዘተ. በማለት ያላደጉ አገሮችን የልማት ጥያቄ እየገደቡ ነው በማለት እንደ ህንድ ያሉ አገሮች ሲከራከረኩ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በተጨባጭም ያደጉ አገሮች ያላደጉ አገሮችን ለመደገፍ የሚገቡትን ቃል ሲያከብሩ አልታዩም፡፡ ስለዚህ የአየር ንብረትና የተፈጥሮ ሀብት መንከባከብ የሚባለው ጉዳይ በውስጡ የተደበቀ አጀንዳ አለው ወይ ያሰኛል፡፡ እንደ እርስዎ ያሉ ባለሙያዎች ይህንን እንዴት ታዩታላችሁ?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- በሁለት መልኩ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ማንኛውንም ስትራቴጂ ስትቀበል አዋጭነቱን ሳታይና ሳታረጋግጥ መቀበል የለብህም፡፡ ለእኔ ደንን ማልማትና መንከባከብ ለአደጉ አገሮች ጥቅም አይደለም፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድሩን ትተን፣ የኢትዮጵያን የሥነ ምኅዳር ሁኔታ ስናየው እኮ ፈተና ውስጥ  ነን፡፡ አንዱ ትልቁ ፈተናችን የአፈር ለምነትን እያጣን መምጣታችን ነው፡፡ ደን የሚያመጣው ውኃ ነው፡፡ ሥነ ምኅዳር የሚስተካከለው ደን ሲኖር ነው፡፡ ወንዞች ያለችግር ውኃ የሚኖራቸው በደን ምክንያት ነው፡፡ ስዊድን ብንሄድ ከ70 እስከ 80 በመቶ የአገራቸው መሬት በደን የተሸፈነ ነው፡፡ ፊንላንድ ብንሄድ ከእነ ቮልቮና ከእነ ኖኪያ ኩባንያዎች በላይ የደን ዘርፉ ነው ለኢኮኖሚያቸው ትልቅ ድርሻ ያለው፡፡ እንደ ኢንዶኔዥያ ያሉትም በሥራ ዕድልና በወጪ ንግድ ምርታቸው ውስጥ ደን ዋጋ አለው፡፡ የደን ውጤቶች የሆኑትን የወረቀት ምርቶች የምናስመጣው ከእነሱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓመት እስከ 185 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የደን ውጤቶችን ከውጭ እንደምታስገባ፣ ከአትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ይህንን ገንዘብ ግን በአርሶ አደሩ አካባቢ ኢንቨስት ብናደርገው ምን ያህል ለውጥ እናመጣበት ነበር፡፡ ደን ለአካባቢ ጥበቃ ብቻ የተተወ አድርገን ማየት የለብንም፡፡ ግብርና እንደሚፈጥረው የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ሁሉ የደን ውጤቶችንም ወደ ውጭ መላክ ይቻላል፡፡ ማር በተዘዋዋሪም ቢሆን የደን ውጤት ነው፡፡ ወደ ሱዳን የመላክ አቅም አግኝተናል፡፡ የባህር ዛፍ ስልክ እንጨቶች እስከ ሊቢያ ድረስ እየተላኩ ትንንሽ ገቢዎች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ዕጣንና ሙጫ በመላክም ገንዘብ እየተገኘ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሥነ ምኅዳር እውነቱን ለመናገር ከግብርና ይልቅ ለደን የተመቸ ነው፡፡ ልክ ስዊድንና ፊንላንድ ለደን ያደላ ኢኮኖሚ እንደ መሠረቱት ሁሉ ኢትዮጵያም ከመሠረቷ ለደን ያደላ ኢኮኖሚ ብትመሠርት ኖሮ እንደ ባለሙያ ይህን ያህል የምግብ ዋስትና ችግርም ሆነ ድህነት ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡ ምክንያቱም ጠቅላላ ነገሩ ለዚህ የተሰጠ አመቺ ነገር ስላለን ነው፡፡ ሸዋ የሚባለው ክፍል፣ ጎጃም፣ አርሲ፣ ባሌ ለጥ ያለ መሬት አለው፡፡ እነዚህ ላይ የተስፋፋ ግብርና በማካሄድ ወደ ወሎ ወደ ትግራይ ያለውን መሬት የእንስሳት ሀብት እንዲስፋፋበት በማድረግ በየመሀሉ ያለውን ተራራማ መሬት ደግሞ በደን ብንሸፍነው፣ ሁሉም ዘርፎች የሚደጋገፉበት ኢኮኖሚ መገንባት ይቻል ነበር፡፡ ትልቁ ችግር ግን ከደን ዘርፍ በቂ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ስላላየን፣ ደኖቻችን በደንብ ስላልተንከባከብናቸው እንደ አገር የደን ጥቅም እየገባን አይደለም፡፡ የደን ውጤት በ20 እና በ30 ዓመታት ውስጥ የሚታይ በመሆኑ፣ ለሽግግር የሚሆን የኢኮኖሚ አቅም ስላጣን በግብርና ላይ ብቻ ተንጠልጥለን ቀርተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ የሚሉት ሽግግር እንዴት ሊመጣ ይችላል? የሚጠይቀውስ ገንዘብ ምን ያህል ነው? ስለዚሁ የተሠራ ጥናትስ ይኖር ይሆን?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- ሽግግሩ ረዥምና ውስብስብ በመሆኑ ትልቅ ቁርጠኝነትን  ይጠይቃል፡፡ በተዳፋት አካባቢ የሚኖረውን ኅብረተሰብ ከእርሻ ወደ ደን አምራችነት እንዲሸጋገር ለማድረግ ሁለት ነገሮች ያስፈልጋሉ፡፡ አንደኛው ደኑ በስሎ እስኪሸጥ ድረስ የሚያቆየው የቅድመ ክፍያ ገንዘብ መክፈል ይጠበቅብናል፡፡ ይህ ለ15 ወይም ለ20 ዓመታት የሚሆነውን ወጪ የሚሸፍን ነው፡፡ ሁለተኛ ደኑ ተቆርጦ ወደ ፋብሪካ መግባት መቻል አለበት፡፡ የደን ውጤቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች መኖር አለባቸው፡፡ ቻይና ከዓለም ዙሪያ ጥሬ ዕቃ ሰብሰባ መልሳ ለዓለም የምትሸጠው በፋብሪካ ያቀነባረቻቸውን ውጤቶች ነው፡፡ እነሱ ጥሬ ዕቃ ከውጭ እየገዙ የሚሠሩትን እኛ አገር ውስጥ በማምረት የሚጋፉ ኢንዱትሪዎችን ማፍራት የምንችልበት ዕድል ስላለን በርካሽ መጠን እንችላለን፡፡ እንዲህ ያለው ሥርዓት ሳይፈጠር ዝም ብለህ ዛፍ ትከል ብትለው የሚሆን ነገር አይደለም፡፡ ወደ ደን ልማት ለመግባት የሽግግር ጊዜው ቀላል አይሆንም፡፡ ከፍተኛ ቁርጠኝነትም ይጠይቃል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያለውን ትስስር ለመፍጠር የሚረዳ፣ ኢንዱስትሪውን ከአምራቹ በዘላቂነት የሚያስተሳስር የደን ሀብት እንዴት ነው የሚፈጠረው? ቻይና እኮ እንደነ ዚምባብዌና ሞዛምቢክ ካሉ አገሮች የደን ሀብቶችን በገፍ ለማስገባት እየተገደደች ነው፡፡ 

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- ዘላቂ የደን ሀብት መፍጠር የሚያስችሉ የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች አሉ፡፡ ለምሳሌ የአማራ የደን ኢንተርፕራይዝን ብናየው በአጋርነት አሠራር ቆሞ ያሉትን ደኖች ከቻይኖችና ከደቡብ አፍሪካ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት በማድረግ ለመሥራት እየሞከረ ነው፡፡ እነሱ ቴክኖሎጂውን ያመጡልሃል፡፡ በ51 ለ49 በመቶ የትርፍ ድርሻ ተደራድረህ ስትሠራ ቆይተህ ዕውቀቱንና ቴክሎጂውን ስታገኝ በራስህ ትገባበታለህ፡፡ በአውሮፓ ለደን ኢንቨስትመንት የሚመደብ ብዙ ገንዘብ አለ፡፡ እንዲህ ያሉ ዕድሎችን ለመጠቀም ፖሊሲ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በባሌና በጭልሞ አካባቢ የሠራችሁትን እንመልከት፡፡ ከዚህ ቀደም የዓለም ባንክ በሰጠው የገንዘብ ድጋፍ የጭልሞ ጥብቅ ደን ለነዋሪዎቹ ጠቀሜታ እንዳስገኘ ይነገራል፡፡ ይሁንና የአካባቢው ነዋሪዎች ብቸኛ መተዳደሪያ ደን እንደ መሆኑ የጭልሞ ደን ጥቅም እንደሚባለው ሆኖ አልተገኘም፡፡ ሌላ የገቢ ምንጭ ይጠይቃል፡፡ የባሌ አካባቢ ደንስ ከዚህ የተለየ ምን ጥቅም አስገኝቷል?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- ትክክለኛ ነገር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ደን ሲባል ጥበቃ የሚለው ሐሳብ ነው የሚጎላው፡፡ ደን የሚጠበቅ እንጂ የሚበላ ወደ ገንዘብ የሚቀየርና ደን ውስጥ ብዙ ገንዘብ እንዳለ አናስብም፡፡ ለእኔ እንደ ባለሙያ ትልቅ ፈተና በመሆን የደን ዘርፉን እየገደለ ያለው እንዲህ ያለው አመለካከት ነው፡፡ የደን ማንነት እየተጠበቀ መቆሙ አይደለም፡፡ ደኑ የሚይዘው ቦታ እኮ በራሱ ለሌላ ሥራ ቢውል እኮ ብዙ የኢኮኖሚ ጥቅም አለው፡፡ ይህ ሁሉ ግን ኢኮኖሚያዊ በሆነ መንገድ አይታሰብም፡፡ ጭልሞ ላይ ያነሳኸው ነገር ትክክል ነው፡፡ እኔ ራሴ ወደዚህ ሥርዓት ከመምጣቴ በፊት የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ሁሉ የአሳታፊ ደን አስተዳደር የሚባለው ላይ ጥያቄ ነበረኝ፡፡ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ኅብረተሰቡ ያንተ ደን ነው፣ ከመንግሥት ጋር ሆነህ ተጠቀም አስተዳድር ነው ሳይንሱ የሚለው፡፡ ነገር ግን ሰዎቹ ሊጠፋ የነበረውን ደን እስካሁን ጠብቀው ቢያቆዩትም ከደኑ ያገኙት ጥቅም ግን እዚህ ግባ የማይባል ነው፡፡ እየሞተ ያለ ዛፍ ግን ደን ውስጥ አለ፡፡ ይህ ዛፍ ዕድሜውን ሲጨርስ ተቆርጦ ለሕዝቡ ጥቅም እንዲሰጥ ቢደረግ ሳይንስም ይደግፈዋል፣ ሕዝቡም ይበልጥ ተጠቃሚነቱን ያረጋግጣል፡፡ አሁን ግን የመጠበቅ እንጂ የመጠቀም አዝማሚያ አይታይም፡፡

በነገራችን ላይ ኅብረተሰቡ ላይ ጫና በማድረጋችን ነው ደኑ እየተጠበቀ የሚገኘው፡፡ ከአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር እንዲሁም ከኦሮሚያ የደንና የአየር ንብረት ባለሥልጣን ጋር በመሆን ዘላቂ የደን አስተዳደር የሚባል አዲስ ፕሮጀክት ባሌ ላይ ጀምረናል፡፡ ከአሳታፊ የደን አስተዳደር ጋር የሚስማማ ሆኖ ሊሞቱ የደረሱና ያረጁ ዛፎች ከደን ውስጥ እንዲወጡና ለጣውላ ሥራ እንዲውሉ እየተደረገ ሕዝብ እንዲጠቀም የማድረግ የሙከራ ሥራ ጀምረናል፡፡ የተጠቃሚነት ጥያቄው ግን ዛሬ አይደለም መነሳት የጀመረው፡፡ ከአሥር እስከ 15 ዓመታት ሆኖታል፡፡ ፖሊሲው ግን መጠቀምን አይፈቅድም፡፡ በእኛ አገር በ30 ዓመታት ዑደት ውስጥ ደን መልሶ የማብቀል፣ የማልማትና የመጠቀም ዕድል አለ፡፡ በዚህ ሁኔታ እንሂድ በማለት መንግሥትም እየተገነዘበው በመምጣቱ ወደዚያ እያመራ ነው፡፡ የተጠቃሚነት ጉዳይ በባሌም ይነሳል፡፡ የካርቦን ንግድ እየቀዘቀዘ የመጣበት አጋጣሚ በመምጣቱም ጭምር ነው ደን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው እንዲታይ ማድረግ ስለሚያስፈልግ ወደዚያ እየተኬደ ነው፡፡ በባሌ ያሉ አርሶ አደሮች ከደኑ የጫካ ቡና፣ ማር እንዲሁም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የተፈቀደ የእንስሳት አደን በማካሄድ በትንሹ እንዲሆን እያደረግን ነው፡፡ ከዚህ በመውጣት ግን ደኑ የተሻለ ጠቀሜታ እንዲሰጥ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

ሪፖርተር፡- ደንን መጠበቅ የሚለው አገላለጽ የመጣው አርሶ አደሩ ከደኑ የሚያገኘው ጥቅም ስለነበር ይመስለኛል፡፡ ቤት መሥራት ሲፈልግ፣ መሸጥ ሲፈልግ ዛፍ ቆርጦ ይጠቀማል፡፡ ይህንን መከላከል ስላስፈለገ መሰለኝ የደን ጥበቃ የሚለው የመጣው፡፡ ደኑን በመጠበቁ ደግሞ ወደፊት ሊያገኝ የሚችለው ጥቅም እንዳለ ነው እየተነገረው ያለው፡፡ እናንተ የምታቀርቡትን ሳይንሱ የሚያቀርበውን ጥቅም ለማየት ያውም ፖሊሲው በማይፈቅድበት ሁኔታ ውስጥ በምን እርግጠኛ መሆን ይቻላል?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- ይህ ፈተና ነው፡፡ ፋርም አፍሪካን ብትወስድ ከ20 ዓመታት በላይ በአሳታፊ የደን አስተዳደር ሥራ ውስጥ ቆይቷል፡፡ የመጀመሪያውን አሳታፊ የደን አስተዳደር የጀመረው በ1995 ዓ.ም. ነው፡፡ አሳታፊ የደን አስተዳደር ማለት ምንድን ነው ብለህ ስትጠይቅ፣ መንግሥት ከደርግ ጊዜ ጀምሮ ደንና መሬትን የሕዝብና የመንግሥት አድርጎ ወስዶታል፡፡ ይህ በራሱ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ በተለይ ደን አካባቢ ያለው ሁኔታ ለየት ይላል፡፡ ደን የመንግሥት ነው የተባለው ኅብረተሰቡ መንግሥት ማለት ቤተ መንግሥት ውስጥ ያለው አስተዳደር፣ ወይም የወረዳ አስተዳደር ስለሚመስለው ደኑም የዚህ አካል እንጂ የእኔ ነው የሚል የባለቤትነት ስሜት አይሰማውም፡፡ ከዚህ ባሻገር ደኑ የሕዝብና የመንግሥት ነው ተባለ፡፡ ነገር ግን ንብረት እንደ መሆኑ መጠን የሚጠብቅ፣ የሚያለማና የሚጠቀም አካል ያስፈልገዋል፡፡ ነገር ግን ይህ አካል ለረጅም ዘመን ጠንካራ ሆኖ አያውቅም፡፡ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የደን ዘርፍ አንዴ በአካባቢ ጥበቃ አንዴ በግብርና ሚኒስቴር ሥር እየሆነ ሲቸገር ነበር፡፡ የግብርና ሰዎች በተለይ ትልልቆቹ ባለሥልጣናት በአብዛኛው ከግብርና ስለሚመጡ አንዳንዴ ደን የእርሻ ፀር እንደሆነ አድርገውም ያስባሉ፡፡ የበጀት አመዳደብ ላይም ለግብርና እንጂ ለደን ትኩረት አይሰጥም፡፡ ከዚህ የተነሳ ደኑ እየመነመነ ሌላው ዘርፍ እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ ደን ባለቤት ከማጣቱ የተነሳ በአካባቢው የሚኖረው አርሶ አደር ደን መንጥሮ ግብር በመክፈል የእርሻ መሬት ሲያስፋፋ ይታያል፡፡ ደኑ በቆመበት አንዲት እንጨት ቆርጦ ሲያወጣ ቢገኝ ግን ሕገወጥ ተብሎ ይታሰራል፡፡ ይህ ሥርዓት ነው ደኑን ያመናመነው፡፡

በመሆኑም አሳታፊ የደን አስተዳደር የሚለው ነገር የመጣው፡፡ የእሱ ነው የሚለው ቀርቶ የሁላችንም ነው የሚለውን አመለካከት ለመፍጠር ያስቻለው አሳታፊ የደን አስተዳደር ነው፡፡ ሕዝቡ ደኑን ይንከባከባል፣ ይጠብቃል፣ እንዲሁም ይጠቀማል የሚል መር­ህ አለው፡፡ ሆኖም ይጠቀማል የሚለው የፖሊሲ አቅጣጫ እስካሁን ግልጽ አይደለም፡፡ የማገዶ እንጨትና ማገር ከደን ማግኘቱ እንዲጠብቀው ማበረታቻ ይሆነዋል ወይ? ብለን እየጠየቅን ነው፡፡ ላለፉት 20 ዓመታት እየታገልን ቆይተናል፡፡ አሁን ወደ መተማመኑ በመምጣት ለውጦች መታየት ጀምረዋል፡፡ ሌሎች አገሮች ግን በደን አጠቃቀም ላይ እየሠሩ ነው፡፡ ቻይና የደን ይዞታን ለቤተሰቦች አሳልፋ ሰጥታለች፡፡ መጀመሪያ ላይ እምነቱን ስላጡ ጨፍጭፈው ገበያ አወጡት፡፡ መንግሥት ዝም  አላቸው፡፡ ወደ እርሻ መመለስ አትችሉም ተብለዋል፡፡ የራሳቸው እንደሆነ ሲገነዘቡ መልሰው ማልማት ጀምረዋል፡፡ ባልተማከለ የደን አስዳደር ቻይና ትልቅ የደን ሽፋን አስመዝግባለች፡፡ በዓለም ላይ በከፍተኛ ደረጃ የደን መሬት ሽፋን የፈጠሩ ሕዝቦች ሆነዋል፡፡ በዚህ መሠረት አርሶ አደሩን እየደገፍነው የደን መሬትን ወደ እርሻ እንዳይቀየር እየጠበቅን በቴክኒክ እየያዝን ከደገፍነው እኛም ጋ ለውጥ ይመጣል፡፡ ጥቅሙን በዚህ ደረጃ ማሳየት ይቻላል፡፡ ጥቅሙ ካልታየ ደን መጠበቅ ከባድ ነው፡፡ ደንን ከኢኮኖሚ ጠቀሜታው ትኩረት ብንሰጠው ፈርጀ ብዙ ጥቅም ያስገኝልናል፡፡ ከአገሪቱ መሬት 30 በመቶ የደን ይዞታ እንዲሆን ይጠይቃል፡፡ ይህም ያግዛል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በተደረገ ምዘና የአገሪቱ የደን ሽፋን 15.5 በመቶ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በአንፃሩ የሚጨፈጨፈው ደን መጠንም ከሚተከለው በላይ ነው፡፡ የደን ሽፋን ጨምሯል አልጨመረም በሚለው ክርክር ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- እውነቱን ለመናገር ከማንም ሰው ጋር የምጋፈጠው ነገር ነው፡፡ የኢትጵያ ደን ሽፋን 15.5 በመቶ ወይም 17 ሚሊዮን 200 ሺሕ ሔክታር መሬት በደን የተሸፈነ ነው የተባለው አገላለጽ ስህተት ነው፡፡ የደን ሽፋኑ በዚህ ደረጃ አድጎ ሳይሆን ያለው የደን መጠን በአዲሱ ትርጓሜ መሠረት ሲታይ ይህንን ቁጥር ስለሚሰጥ ነው፡፡ ለደን አዲስ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ኮንቬንሽን ፎረም አገሮች ለደን ሽፋናቸው የራሳቸው ትርጓሜ መስጠትና በዚያም ሊዳኙ ይችላሉ ብሏል፡፡ ኢትዮጵያም የራሷን አዲስ ትርጓሜ አስቀምጣለች፡፡ በ2004 ዓ.ም. የታተመ በካናዳ መንግሥት የሚደገፍ ‘ውዲባዮማስ’ የሚባል ትልቅ ፕሮግራም ነበር፡፡ አገር አቀፍ የደን ዳሰሳ ጥናት የተካሄደው በዚህ ፕሮግራም ወቅት ነው፡፡ ሦስት የደን ትርጓሜን አስቀምጦ ነበር፡፡ ደጋማ ደን፣ ስምጥ ሸለቆ አካባቢ ያለውን ዓይነት ዛፍ የቆላማ ደን፣ እንዲሁም የቁጥቋጦ ደን በማለት በሦስት ይለያቸዋል፡፡ የደጋማው ደን የዛፉ ቁመት ከአምስት ሜትር በላይ የሆነው የደጋ አካባቢ ረጃጅም ዛፎችን ለይቶ በዚህ ትርጓሜ ፈርጇቸዋል፡፡ ሦስቱን በመደመር 56 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በደን ተሸፍኗል ተብሎ ይገመት ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ የደጋማው ደን አራት ሚሊዮን 200 ሺሕ ሔክታር ወይም 3.6 በመቶ ገደማ ይይዝ ነበር፡፡ የቆማላው 28 ሚሊዮን፣ የቁጥቋጦ ደኑ ወደ 26 ሚሊዮን ሔክታር ገደማ ይሸፍን ነበር፡፡ ወደ አዲሱ አሠራር ሲመጣ ማለትም የሬድ ፕላስ ፕሮጀክት ማለት ነው፣ የዓለም የእርሻና የምግብ ድርጅት (ኤፍኤኦ) በየአምስት ዓመቱ የዓለምን የደን ይዘት የሚያስስ ሪፖርት ያቀርብ ጀምረ፡፡ የኤፍኤኦ ትርጓሜ ድሮ በውዲባዮማስ ከተሰጠው ትርጓሜ ይለያል፡፡

ኤፍኤኦ የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ዳሰሳ ጥናት ሲሠራ የራሱን ትርጓሜ እንደሚጠቀም አስታወቋል፡፡ በተቋሙ ትርጓሜ መሠረት ደን የሚባለው 0.5 ሔክታር የሚሸፍን፣ ቁመቱ ሁለት መሬት የሚደርስ ዛፍ ደን ተብሎ ይጠራል አለ፡፡ ድሮ እኛ 29 ሚሊዮን ሔክታር የሚሸፍነው የቆላማ ደን ነው ያልነውን፣ በደንና በቁጥቋጦ መካከል የሚገኘው ኤፍኤኦ ደን ብሎ ጠራው፡፡ አራት ሚሊዮን 700 ሺሕ እንደሚሸፍን የሚታወቀውን ኤፍኤኦ 17.2 ሚሊዮን ሔክታር የሚሸፍን የደን መሬት ነው ብሎ በመተርጎሙ ነው የኢትዮጵያ ደን ሽፋን 15.5 በመቶ ነው እየተባለ የሚገኘው፡፡ ነገር ግን ደን ብሎ ያስቀመጠው የቆላማው ደን ወደ 33 ሚሊዮን ሔክታር ገደማ ይሸፍናል፡፡ ያኛው ግን 56 ሚሊዮን ሔክታር ነበር፡፡ በውዲባዮማስና በኤፍኤኦ ትርጓሜ ልዩነት ምክንያት ቁጥቋጦውን ትተን 16 ሚሊዮን ሔክታር አጥተናል ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሬድ ፕላስ አባል ለመሆን የመጀመሪያው መጠይቅ ያላት የደን ሀብት መመናመኑን ማረጋገጥ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2000 እስከ 2013 ባለው ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ በየዓመቱ 80 ሔክታር መሬት እንምታጣ ለተመድ ሪፖርት አቅርባለች፡፡ ይህ ማለት በየዓመቱ የደን ጭፍጨፋ መጠኑ 120 ሺሕ ሔክታር መሬት እንደሚሸፍን፣ በየዓመቱ የምታለማው 40 ሺሕ ሔክታር መሬት በደን ስለምትሸፍን ልዩነቱ 80 ሺሕ ሔክታር የደን መሬት እየታጣ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በየዓመቱ 80 ሺሕ ሔክታር የደን መሬት እያጣህ የደን ሽፋን ሰፍቷል ልትል አትችልም፡፡ በመሆኑም የደን መጠን ጨመረ አትበሉ፡፡ ይልቁንም አዲስ ትርጓሜ ስለሰጠን የኢትዮጵያ የደን ይዘት፣ ድሮ ደን አይደለም ያልነውን አሁን ወደ ደን በማካተታችን አሁን ያለን የደን ይዘት ይህን ያህል ነው በሉ እያልን በየመድረኩ እየተነጋገርን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የደን ተከላ ሲነሳ ሌላ አስገራሚ ነገር አለ፡፡ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ችግኝ ለመትከል ብዙ በጀት ይመደባል፡፡ ቁጥሮቹን ካልተሳሳትኩ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በዓመት ከአምስት ቢሊዮን በላይ ችግኝ እንደተተከለና ወደፊትም እስከ 15 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እንደሚታሰብ ይነገራል፡፡ በተግባር የሚታየው ውጤት ግን ለየቅል ነው፡፡ እንደ ባለሙያ እንዴት ይታዘቡታል?

ዶ/ር ሙሉጌታ፡- ሁለት የተለያዩ ችግሮችን አያለሁ፡፡ በመስኩ ያለነው ባለሙያዎች የምናነሳቸው ችግሮች አሉ፡፡ ዘንድሮ እንኳ አራት ቢሊዮን ያህል ችግኝ ተተክሏል ሲባል ነው የሰማሁት፡፡ የመጀመሪያው ጥያቄ ቁጥሮቹን እንዴት ነው የሰበሰብናቸው የሚለው ነው፡፡ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ የአገሪቱ የችግኝ ማፊያ ጣቢያዎችና የደን ይዘት ስከታተል ቆይቻለሁ፡፡ በመሆኑም እውነት ኢትዮጵያ ውስጥ አራት ቢሊዮን ችግኝ የሚያፈላ ችግኝ ጣቢያ አለን ወይ ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ አራት ቢሊዮን ችግኝ በጣም ብዙ ነው፡፡ ይህን ያህል ችግኝ የሚያፈላ ጣቢያ ግን የለንም፡፡ የአማራና የኦሮሚያ የደን ኢንተርፕራይዞች በትጋት እየሠሩ የሚገኙ ተቋማት ናቸው፡፡ እነሱን እንኳ ብትጠይቋቸው በዓመት አንድ ሚሊዮን ችግኝ አያፈሉም፡፡ አንዳንድ ጊዜ በዘርፉ ያሉትን ሰዎች ስንጠይቅ አኃዙ የመኖ ችግኞችን ጨምሮ ነው ይሉናል፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የበቀለ የመኖና የዛፍ ችግኝ ነው ተብሎ ቢገለጽ እኮ ሰው በቀላሉ ይረዳል፡፡ እውነትም የተባለው የችግኝ መጠን የመኖም ከሆነ የአገላለጽ ችግር ያለ ይመስለኛል፡፡ ሌላው ችግኞቹ የሚተከሉት የተራቆተና የደቀቀ መሬት ላይ ነው፡፡ ችግኝ ለም አፈርና ለም ቦታ የሚፈልግ ነው፡፡ ድንጋያማና ተራራማ ቦታ ላይ ወስደን የምንተክለው ችግኝ እንዴት አድርጎ ነው የሚያድገው? ትልቁ ስህተት የደን ተከላ ማለት የተራቆተ መሬትን መልሶ አረንጓዴ የሚያለብስ አድርገው ማሰባቸው ነው፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡ የተራቆተ ቦታ ታጥሮ እንዲያገግም በመተው ነው ዳግመኛ አረንጓዴነትን እንዲላበስ የሚደረገው፡፡ ወይም ደግሞ ለተራቆተ ቦታ የሚመቹ እንደ ቁጥቋጦ ያሉ ችግኞች መትከል ይቻላል፡፡

የደን ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች በመቀላቀላቸው ችግር እየተፈጠረ ነው፡፡ አካባቢ ጥበቃ እንደ ደን ልማት ሊከተላቸው የሚችሉ ነገሮች ቢኖሩም፣ የደን ልማት ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ የደን ልማት ልክ እንደ እርሻ ሥራ ለም ቦታ፣ የተመቸ ቦታ ፈልጎ በማብቀል ነው ውጤት የሚገኘው፡፡ የምትተክለው የዛፍ ዝርያ ሳይንሳዊ ሒደቶችን መከተል  አለበት፡፡ ሥነ ምኅዳሩን ማወቅና ተስማሚነቱን ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ወይም ጤፍ ያለቦታው አይዘራም፡፡ ሌላው መነሳት ያለበት የባለቤትነት ጉዳይ ነው፡፡ ችግኞቹን የት ነው የምንተክላቸው? ማን ነው የሚንከባከባቸው? ችግኞቹ ስለተተከሉ ብቻ ዛፍ ይሆናሉ ማለት አይደለም፡፡ ከብቶችና ሰዎች ሲራገጡባቸው የሚውሉ ናቸው፡፡ ችግኝ እንደሚፈለገው መጠን እንዳያድግ ያደረጉት እነዚህ ችግሮች ናቸው፡፡ ከዚህ ይልቅ የወል መሬት ላይ የምንተክል ከሆነ የኅብረት ሥራ ማኅበራት እንዲጠብቁትና እንዲጠቀሙበት ጭምር ኃላፊነት ሰጥተን መንከባከብ ይገባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሌላው ችግር እነዚህ ሰዎች ሰርቲፊኬት ቢሰጣቸው የበለጠ ደኑን ለማስጠበቅ ይጠቅማል፡፡ የተራቆቱ መሬቶች ደን እንዲያለሙ ጭምር ለወጣቶች እየተሰጡ ቢሆንም፣ በስምንት ዓመታት ውስጥ ስለተገደበ የወጣቶቹን ተጠቃሚነት ይገድበዋል፡፡ ይህ መሻሻል አለበት፡፡ በመሠረቱ የመንግሥት ፍላጎት እየተቀየረና መነሳሳቱም እየታየ ነው፡፡