Skip to main content
x
ከቻን አፋፍ ላይ የቆመው የዋሊያዎቹ ዕጣ ፈንታ

ከቻን አፋፍ ላይ የቆመው የዋሊያዎቹ ዕጣ ፈንታ

  • ሆቴል የገቡ ተጨዋቾች እንዲበተኑ ተደርጓል

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የብሔራዊ ቡድኑን ዝግጅትን አስመልክቶ ከሰሞኑ ይፋ ያደረገው መረጃ በአነጋጋሪነቱ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ ውሳኔው ወትሮም በደካማነቱ የተለያዩ ትችቶችን ሲያስተናግድ ለቆየው የዋሊያዎቹ ዝግጅት ውጤት አልባነት ማረጋገጫ ለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡

በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የአፍሪካ አገሮች የእግር ኳስ ዋንጫ (ቻን) ከጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል፡፡ በሱዳን አቻው ተሸንፎ ከ2018 ቻን ሻምፒዮና ተሳትፎ የተሰናበተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ)፣ ምንም እንኳ ቀደም ሲል በወጣው ማጣሪያ ከውድድር ውጪ የነበረ መሆኑ ቢታወቅም፣ ነገር ግን ካፍ የግብፅ ብሔራዊ ቡድን በራሱ ፈቃድ መውጣቱን ተከትሎ በሰጠው ዕድል ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንድትሆን መወሰኑ አይዘነጋም፡፡ ውሳኔው የኢትዮጵያ ቡድን ከሩዋንዳ አቻው ጋር በሚያደርገው በደርሶ መልስ ጨዋታ የሚያስመዘግበው ውጤት ዕድሉ እንደሚወሰንም መነገሩ ይታወሳል፡፡

ይሁንና ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ በተገኘው ዕድል መሠረት ከቻን አፋፍ ላይ የቆመው የዋሊያዎቹ ዕጣ ፈንታ ያበቃለት ይመስላል፡፡

እንደ መረጃው፣ በካፍ መልካም ፈቃደኝነት ለብሔራዊ ቡድኑ የመጣው የደርሶ መልስ የጨዋታ መርሐ ግብር የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አመራሮች የቀን ይራዘምልን ጥያቄ ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡ ይህንኑ የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አካልና የዋሊያዎቹ የቡድን መሪ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ አረጋግጠዋል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለካፍ በጻፈው ደብዳቤ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ አቻው ጋር እሑድ ጥቅምት 26 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚያደርግ የካፍ ዕቅድ መሆኑን ጭምር አቶ ዘሪሁን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ይህንኑ መነሻ በማድረግ ፌዴሬሽኑ የተለያዩ ምክንያቶችን በመጥቀስ ጥያቄውን አቅርቧል፡፡

የመጀመርያውና አንደኛው ወቅቱ የአገሪቱ የሊግ ውድድር የሚጀመርበት እንደመሆኑ ገና ከመጀመሩ በቻን ውድድር ምክንያት እንዳይቋረጥ፣ ከተቋረጠም ወደ ክረምት ሊገባ ይችላል ከሚል ሥጋት ይመነጫል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የሎጂስቲክና የቪዛ ውጣ ውረዶችን ይጠቅሳል፡፡ ሌላኛውና ብዙዎችን ያስገረመው ምክንያት ቡድኑ አሁን ፌዴሬሽኑን እያስተዳደረ በሚገኘው ሥራ አመራር ተደጋጋሚ ሽንፈቶችን በማስተናገዱ ምክንያትና በፊፋም የአገሮች ወርኃዊ የእግር ኳስ ደረጃ ባልተጠበቀ ፍጥነት ማሽቆልቆል ላይ መሆኑና በዚህ የደርሶ መልስ ጨዋታ ደግሞ ሌላ ሽንፈት ሲጨመር ሊመጣ የሚችለውን ጫና በመፍራት ሊሆን እንደሚችል የሚናገሩ አሉ፡፡

የዋሊያዎቹ የቡድን መሪ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ይህንኑ ሲያጠናክሩ፣ ‹‹ቡድኑ ጊዜ አግኝቶ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ቀደም ሲል ያጋጠሙት ተደጋጋሚ ሽንፈቶች ራሱን የቻለ ተፅዕኖ አለው፡፡ በዚያ ላይ ፌዴሬሽኑ ከፊት ለፊቱ የቀጣዩን አራት ዓመት የአመራሮች ምርጫ ዝግጅት ላይ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ መደበኛው የሊግ ውድድር የሚጀመረው የኢትዮጵያና የሩዋንዳ ጨዋታ በሚደረግበት ሳምንት ነው፡፡ ክለቦች ከወዲሁ ተጨዋቾቻቸውን ልቀቁ ቢባሉ ፈቃደኛ መሆን አይችሉም፡፡ እነዚህንና ሌሎችም ተዛማጅ ምክንያቶችን ግምት ውስጥ በማስገባት ካፍ ውድድሩን እንዲያራዝምልን ጠይቀናል፡፡ በዚሁ መሠረት የሚራዘምልን ከሆነ ጥሩ ዝግጅት አድርገን ለመወዳደር ዝግጁ ነን፡፡ የማይራዘም ከሆነ፣ ግን አንጫወትም፤›› ብለዋል፡፡

በአንፃሩ ብሔራዊ ቡድኑ ለትልልቅ ጨዋታዎች ከማቅናቱ በፊት የወዳጅነትም ሆነ ሌሎች ውድድሮችን ሳያደርግ ወደ ውድድር መግባቱ ሲተች ቆይቷል፡፡ ለዚህም ሲባል ቡድኑ ቀደም ሲል ለቦትስዋናና ለሞሮኮ ብሔራዊ በዓላት በሚል ከአገሮቹ በቀረበት ጥያቄ መሠረት አስቸጋሪውን የጉዞ ውጣ ውረድ አድርጎ መጫወቱ ይታወቃል፡፡ አሁን ደግሞ ጨዋታው ለ2018ቱ የአፍሪካ ዋንጫ (ቻን) ቢሆንም፣ ውድድሩ ሲገኝ ያውም ለቻን ተሳትፎ የደርሶ መልስ ጨዋታ ከሩዋንዳ ጋር የተደለደለ ከመሆኑም ባሻገር ለሁለተኛ ጊዜ የተገኘን ዕድል ላለመጠቀም ማቅማማቱ ግርምትን የፈጠረባቸው ብዙዎች ሆነዋል፡፡ ከዚህም በላይ የብሔራዊ ቡድኑ ወቅታዊ አቋም ትልቅ ችግር ውስጥ ለመግባቱ የፌዴሬሽኑ ውሳኔ ጥሩ ማሳያ እንደሆነ የሚገልጹ አሉ፡፡

የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ አቶ አሸናፊ በቀለ በበኩላቸው፣ ከ11 ክለቦች 25 ተጨዋቾችን መርጠው ካፒታል ሆቴል አስገብተው ዝግጅት ጀምረው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ዋና አሠልጣኙ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በሆቴል ያሰባሰቡዋቸውን ተጨዋቾች እንዲያሰናብቱ ተነግሯቸው ተጨዋቾቹም ወደየክለቦቻቸው መመለሳቸውን ጭምር ተናግረዋል፡፡

የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ በበኩላቸው፣ ምንም እንኳ በተገኘው ዕድል ደስተኛ እንደሆኑ ቢገልጽም፣ ነገር ግን ፌዴሬሽኑ መደበኛውን የሊግ ውድድር ጨምሮ ከፊት ለፊቱ ተደራራቢ አጀንዳዎችና ሥራዎች ስላሉበት ውድድሩን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ለማስተናገድ ይቸገራል፡፡ ይሁንና ፌዴሬሽኑ ለካፍ ያቀረባቸው ምክንያቶች አሳማኝ በመሆናቸው ፕሮግራሙ የሚራዘምበት ዕድል እንዳለው በእርግጠኝነት ተናግረዋል፡፡