Skip to main content
x
አሳሳቢው የድምፅ ብክለትና የመዲናችን ነዋሪዎች

አሳሳቢው የድምፅ ብክለትና የመዲናችን ነዋሪዎች

በዓለማየሁ ገረመው 

መንግሥት ከ1998 እስከ 2008 ባሉት ዓመታት ውስጥ ለ11 ጊዜ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ለተጠቃሚዎች አስተላልፏል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ለንግድና መሰል ተግባራት አመቺ የሆኑትን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ምድር ቤቱን ለይቶ በጨረታ ለአሸናፊዎች አስተላልፏል፤ እያስተላለፈም ይገኛል፡፡ ይህም መንግሥት ለነዋሪዎች የሚደጉመውን የግንባታ ወጪ በተወሰነ ደረጃ ያቀልለታል ተብሎ ይታመናል፡፡

ሆኖም ታዲያ መንግሥት የግንባታ ወጪውን ይቀንስለታል፣ ነዋሪዎችም መሠረታዊ ፍላጎታቸውን በአቅራቢያቸው ከሚገኙት ንግድ ቤቶች በመሸመት በቀላሉ ሊያሟሉ ይችላሉ ተብሎ ይሁንታን ያገኙት ንግድ ቤቶች ቀስ በቀስ ከፍተኛ ድምፅ ወደሚያመነጩ የቪዲዮ ካሴት ኪራይ ቤቶች፣ መዝሙር ቤቶች፣ ሬስቶራንቶች፣ ግሮሰሪዎች፣ የእግር ኳስ መመልከቻ ቤቶችና ጫት ቤቶች እየተቀየሩ ሕፃናትን እንኳ ወደ ውጪ አውጥቶ ማዝናናት ወደማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ሲሉ ነዋሪዎች በምሬት ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ በአካባቢው የሚኖረው ማኅበረሰብም ሁኔታውን እያደር እየተላመደውና እንደ አንድ የኑሮው አካል አድርጎ ከሁኔታው ጋር ተስማምቶ ለመኖር እየተቸገረ ይገኛል፡፡

ይኼ ትዕይንት በዕለት ተዕለት ኑሯችን የምንረበሽበት፣ የምናየውና የምንኖረው ጉዳይ ከሆነ ሰንበትበት ብሏል፡፡ መጠጥ ቤቶች ክፍት ሆነው የሚቆዩት እስከ እኩለ ሌሊትና እንደየአካባቢው ሁኔታ ከዛም በላይ ዘለግ ላለ ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ታዲያ እዚህም እዚያም ተቀራርበው ከተሰደሩት መጠጥ ቤቶች የሚወጡት፣ ከፍተኛ አቅም ባላቸው የድምፅ ማጉያዎች የሚለቀቁት ሙዚቃዎችና በጭፈራ የታጀበ የሰዎች ሁካታ ሕፃናትና አቅመ ደካማዎች ሰላማዊ እንቅልፍ እንዳይተኙ፣ ቀን በተለያየ ሥራ ላይ ተሰማርተው ማታ ወደቤታቸው የሚገቡ ነዋሪዎችም እንቅልፋቸውን አጥተው በሥራቸው ውጤታማ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡

በተለያዩ የንግድና ሌሎች መሰል ተግባራት ከሚደርሱ የድምፅ ንውፀት በተጨማሪ አንዳንድ መንፈሳዊ በዓላት በሚከበሩበት ጊዜያት በምሽትና ሌሊት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ነዋሪዎችን እንቅልፍ በመንሳት ለሥነ ልቦናዊና አካላዊ ጫና የሚዳርጉ የአምልኮ ስፍራዎችም እንዳሉ በዕለት ተዕለት ኑሯችን የምንጋፈጠው፣ ማኅበራዊ መስተጋብርን ያበላሻል ብሎ በመሥጋት ይፋ ለማውጣት የማንደፍረው ጉዳይ መሆኑ ‘ለቀባሪው ማርዳት’ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ያገባኛል ብሎ ለጉዳዩ መፍትሔ የሚሻ አካል እምብዛም አይስተዋልም፡፡ ሌላው የነዋሪዎች ችግር ሳይፈታ ለዓመታት እንዲቆይ ያደረገው የኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማነስ ሊሆን ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡

ዜጎች የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ድምፅን በተመለከተ ያወጣው መመሪያ እንዳለና በቀንና በሌሊት የተፈቀደ የድምፅ መጠን ልኬት በሕግ እንደተወሰነ ግንዛቤ ያላቸው ጥቂቶች በመሆናቸው አብዛኞቹ ከችግሮቹ ጋር እየኖሩ ይገኛሉ፤ ጥቂቶቹም ቢሆን ባወቁት ልክ ለመብታቸው ከመቆም ይልቅ ዝምታን ሲመርጡ ይስተዋላል፡፡ ከአምልኮ ቤቶች ውስጥ የሚመነጨውን ከፍተኛ ድምፅ መቃወም በፀረ ሃይማኖታዊነት ሊያስፈርጀን ይችላል በሚል ሥጋት ችግሩን ችለው እየኖሩ ይገኛሉ፡፡

ከዚህ ባሻገር በተለያዩ የመዲናችን መንደሮች ውስጥ ቤት ሠርተው የሚኖሩ ነዋሪዎችም በየአካባቢው ከላይ የተዘረዘሩት ችግሮች እንዳሉ ሆነው በተጨማሪ እዚህም እዚያም ተሠርተው ወይም የግለሰብ ቤት ተከራይተው የሚያመልኩባቸው የአምልኮ ሥፍራዎች በከፍተኛ የድምፅ ልቀት የአካባቢውን ነዋሪዎች እያማረሩ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የአምልኮ ሥፍራዎች በአብዛኛው ፕሮግራማቸውን የሚያካሂዱት ቀን ነው፡፡ በሌሊት ጭምር የአምልኮ ሥፍራዎቹ ድምፆችን በሚያጎሉ የአደባባይ መሣሪያዎችና ‹‹ጩኸት›› በመጠቀም የአካባቢውን ሰላም በቀን መደበኛ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ የአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ጭምር ሲረበሹ ይስተዋላል፡፡

አንዳንድ ነዋሪዎች እንደሚናገሩት፣ በአምልኮ ሥፍራዎቹ አጠገብ ባሉ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎችም ፕሮግራሙ እስኪያልቅ ቤታቸውን ዘግተው እስከ መሄድ እንደደረሱ ይገልጻሉ፡፡ ተማሪዎች ምሽት ትምህርታቸውን እንዳያጠኑ፣ የቤት ሥራቸውን በተረጋጋ መንፈስ እንዳይሠሩ፤ በሥራ የዋለ ሠራተኛ የተረጋጋ ዕረፍት እንዳያገኝ፣ ሕፃናት ለሰላማዊ እንቅልፍ እንዳይታደሉ እየዳረገ መሆኑ የየዕለቱ ገጠመኝ ሆኗል፡፡  ጉዳዩ አሳሳቢ እንደመሆኑ መጠን ዘላቂ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል፡፡ ነዋሪዎችም ከድምፅ ብክለት ከሚመነጭ ሥነ ልቦናዊ ጫናና አካላዊ ጉዳት የመጠበቅ ሕጋዊ መብት እንዳላቸው አውቀው የድምፅ ብክለት የሚያደርሱትን የንግድ ቤቶችና የአምልኮ ሥፍራዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ሊያሳስቡ ይገባል፡፡ መንግሥትም የኅብረተሰቡን በተስማሚ አካባቢ የመኖር መብት ለማስከበር በሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 44 ላይ ሰፍሮ የሚገኘውን ሁሉም ሰዎች ንፁህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት እንዳላቸው የሚገልፀውን ሕግ ሊያስከብር ይገባል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 92 ላይ የተዘረዘሩትን ማለትም መንግሥት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንፁህና ጤናማ አካባቢ እንዲኖረው የመጣር፣ ማንኛውም የኢኮኖሚ ልማት ዕርምጃ የአካባቢውን ደኅንነት የማያናጋ መሆኑን የመከታተል፣ የሕዝብን የአካባቢ ደኅንነት የሚመለከት ፖሊሲና ፕሮግራም በሚነደፍበትና ሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ የሚመለከተውን ሕዝብ ሁሉ ሐሳቡን እንዲገልፅ የማድረግ፣ እንዲሁም መንግሥትና ዜጎች አካባቢያቸውን የመንከባከብ ግዴታ አለባቸው የሚሉትን ሐሳቦችና በሕዝብ ጤና አጠባበቅ አዋጅ ቁጥር 200/1992 ንዑስ አንቀፅ 5 ላይ ጤና ማለት በበሽታ አለመያዝ ብቻ ሳይሆን ፍፁም የሆነ የአካል፣ የአዕምሮና የማኅበራዊ ኑሮ ደኅንነት እንደሆነ የሚያመለክተውን፣ በተዛማጅም ከመጠን በላይ ድምፅ በሚያሰማ መሣሪያ መጠቀም የተከለከለ ነው፤ የሚለው ሐሳብም ምን ያህል ድምፅ ዜጎችን እንደሚጎዳና መንግሥትም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ዜጎች በድምፅ ብክለት ያለመጎዳት መብታቸውን እንደሚያስከብር የሚያጠናክር በመሆኑ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በጉዳዩ ላይ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ዘዴዎች አማካይነት ለዜጎች ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ሊሠራና በቀጣይም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለዕድለኞች ሲተላለፉና ምድር ቤቶቹ ለጨረታ ቀርበው ለአሸናፊዎች ሲሰጡ የድምፅ ልቀትን አስመልክቶ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሊሰጥ ይገባል፡፡

 በመጨረሻም ሕግን አለማወቅ ከጥፋተኝነት አያድንምና እስካሁን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የዜጎችን ጤና ሲያውኩ የነበሩ በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ ተሰድረው የሚገኙ በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ የአምልኮ ሥፍራዎች በአገራችን ሕገ መንግሥት፣ በአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ በፍትሐ ብሔር እንዲሁም በማስታወቂያ አዋጅ የወጡ የአካባቢ ብክለት መቆጣጠሪያ ደንቦችና ሕጎች በግልፅ ሰፍረው እንደሚገኙና ከተፈቀደው የድምፅ ልቀት መጠን በላይ ማስጮህ እንደሚያስቀጣ አውቀው የድምፅ ልቀታቸውን ሊቀንሱ ይገባል፡፡ በመኖሪያ አካባቢ ቀን ላይ ከ45 ዴሲ ቢል በታች፣ በማታ ደግሞ ከ55 ዴሲ ቢል በታች ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ይኼ ሁኔታ የማይተገበር ከሆነ መንግሥት በአካባቢ ብክለት መቆጣጠሪያ አዋጁና በሌሎች የሕግ ማዕቀፎች ውስጥ የተገለፁትን ቅጣቶች ሊተገብርባቸውና ዜጎችን በተለይም ታማሚዎችን፣ ሕፃናትንና አቅመ ደካማዎችን በድምፅ ምክንያት ከሚደርስባቸው ተጨማሪ ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ጉዳት ሊታደጋቸው ይገባል፡፡ ዜጎችም በያገባኛል መንፈስ የድምፅ ብክለት የሚያደርሱ አካላትን በሕጉ መሠረት የሚጠበቅባቸውን በመንገርና ስለ ሕጉ በማስረዳት ከዛም ካለፈ ለመንግሥት በመጠቆም መብታቸውን ሊያስከብሩ ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡