Skip to main content
x
ትኩረት የሚሹ የግብርናው እክሎች

ትኩረት የሚሹ የግብርናው እክሎች

 

በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ከተያዙ ዕቅዶች መካከልም የግብርናውን ዘርፍ ዘመናዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ዋናው ነው፡፡

አርሶ አደሩ ገበያን ታሳቢ አድርጎ እንዲያመርት፣ አነስተኛ መስኖዎችን በማስፋፋት የተሻሻሉ ዝርያዎችንና ግብዓቶችን በመጠቀም ምርታማነቱን እንዲያሳድግ፣ በገበያ ላይ ያለውን ተወዳዳሪነት እንዲጨምር፣ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችን የመጠቀም ልምዱን እንዲያዳብርና የምርት ብክነቱን እንዲቀንስ በማድረግ ዘርፉ በየዓመቱ የስምንት በመቶ አማካይ ዕድገት እንዲያስመዘግብም ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ቢሆንም፣ ዕቅዱን ለማሳካት የተለያዩ ችግሮች ማነቆ ሆነዋል፡፡

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ እንደ ድርቅና ጎርፍ ያሉ ተፈጥሯዊ አደጋዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የድኅረ ምርት ብክነት በምርታማነት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነው የግብርና ምርትም ከማሳ ጀምሮ ባሉ ሒደቶች ይባክናል፡፡

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ብክነቶችን ለመከላከልም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የግብርና ሚቲሪዎሎጂ ግብረ ኃይል በማቋቋም የምርት ሒደቱን እያሳለጠ ይገኛል፡፡ ግብረ ኃይሉ ከጥቅምት መግቢያ ጀምሮ ባሉት ተከታታይ አሥር ቀናት ውስጥ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የተመዘገበውን የዝናብ መጠን መሠረት በማድረግ ሊወሰዱ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች አስቀድሞ በምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ ምክረ ሐሳቡ በመኸር ወቅት ከሚፈጠሩ የአየር ፀባይ ተለዋዋጭነት ጋር ተያይዘው ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችንና መፍትሔዎቻቸውን ያካተተ ነው፡፡  

በተባሉት አሥር ቀናት የነበረው የዝናብ መጠን ከአገሪቱ የቦታ ሽፋን አንፃር ሲገመገም፣ በአማራ የሰሜንና የደቡብ ጎንደር፣ የባሕር ዳር፣ የምዕራብና የምሥራቅ ጎጃም፣ እንዲሁም የአዊ ዞን፤ የቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ የጋምቤላ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የከፋ ዞን፣ የቤንች ማጂ ዞን፣ ደቡብና ሰሜን ኦሞ፣ የሲዳማ ዞን እንዲሁም የሰገን ሕዝቦች፤ በኦሮሚያ በምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ የኢሉአባቦራ፣ የጅማ፣ የቦረናና የባሌ የደቡብ ምዕራብ ዞኖች ከ4 እስከ 10 ቀናት ያህል     ከ25 ሚ.ሜ. እስከ 188 ሚ.ሜ. የሚደርስ ዝናብ አግኝተዋል፡፡

ደቡብ ትግራይ፤ ከአማራ የሰሜንና የደቡብ ወሎ፤ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የጉራጌና የሐዲያ ዞኖች፤ ከኦሮሚያ የሰሜንና የምዕራብ ሸዋ፣ አዲስ አበባ የአርሲና የባሌ ሰሜናዊው ክፍል፣ የምዕራብና የምሥራቅ ሐረርጌ ዞኖች እንዲሁም አብዛኛው የሶማሌ ዞኖች ከ5 ሚ.ሜ እስከ 25 ሚ.ሜ የሚደርስ ዝናብ ከሁለት እስከ አራት ቀናት ያህል ያገኙ ሲሆን፤ የተቀሩት የአገሪቱ ክፍሎች ከ5 ሚ.ሜ በታች  የዝናብ መጠን ነበራቸው፡፡ በእነዚህ የአገሪቱ ክፍሎች የተመዘገበው የዝናብ መጠን በክልሎቹ በስፋት የሚመረቱ እንደ ሰሊጥ ያሉ የእህል ዓይነቶች ላይ ከባድ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ በፍጥነት ከማሳ ላይ እንዲሰበሰቡ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በአገሪቱ የሚገኘው አጠቃላይ የሰሊጥ ምርት 863,122 ሔክታር የሚሸፍን ሲሆን፣ 70 ከመቶ የሚሆነው ምርት በትግራይና በአማራ ክልሎች በተለይም በሁመራና አካባቢው እንዲሁም በመተማና መተማ ዙሪያ ይመረታል፡፡ ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት፣ ፀጥታ፣ ጤናና ትራንስፖርት ሴክተሮች የተውጣጣ ግብረ ኃይል በማቋቋም የሰብል አሰባሰብ ተግባሩን ለማከናወን በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት እየተገኘ መሆኑን በሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊው አቶ ዓለማየሁ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡

እስከ ጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በተሰበሰበ መረጃ መሠረት በሰሊጥ ከተሸፈነው መሬት በ590,093.5 ሔክታር ላይ የነበረውን ምርት ማለትም 68.4 ከመቶው መሰብሰብ ተችሏል፡፡

የሰሊጥ ምርት ከ15 ቀናት ያልበለጠ አጭር የመሰብሰቢያ ወቅት ያለው በመሆኑ በተቀሩት የመኸር ጊዜ ሰሊጥ አምራች አካባቢዎች በተለይም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከፍተኛውን የሰሊጥ ምርት የሚያመርቱ እንደ ዳንጉር ያሉ ወረዳዎች ዘግይተው ስለዘሩ የአጨዳ ወቅታቸው እስከ ኅዳር 15 ሊዘገይ እንደሚችል ከክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የተገኘ መረጃዎች ያሳያል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎችም የዝናብ ክስተት ሊኖር እንደሚችል የሚትሮሎጂ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊኖር ስለሚችል በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ፣ የደረሱ ሰብሎች ከማሳ እንዲሰበሰቡ ማድረግ፣ በወቅቱ መውቃት፣ በአግባቡ ማከማቸት፣ ውኃ በሚፈልጉ አካባቢዎች በማሳ አናት ላይ የውኃ ማስረጊያ ጉድጓድ በማዘጋጀት ዝናቡ ሳይባክን ወደ መሬት እንዲሰርግ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አቶ ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡

የሚኖረው ደረቃማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታም በመስኖ ውኃ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳድር፣ ነፋሻማው የአየር ሁኔታም በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያስከትል  ሰብሎችን በፍጥነት ከማሳ ላይ መሰብሰብ መሆኑን፣ የውርጭ ክስተት በሚጠበቅባቸው የአገሪቱ ከፍተኛ አካባቢዎችም በዕድገት ላይ ባሉ ሰብሎችና በቋሚ ተክሎች መደበኛ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳድሩ አርሶ አደሩ በማሳው አካባቢ ጭስ ማጨስ፣ በደጋፊ መስኖ መጠቀም በሰብሉ ላይ ውኃ መርጨት፣ በችግኝ ጣቢያዎችም ተገቢውን ከለላና የችግኝ ዳስ መሥራትና የመሳሰሉትን ባህላዊ ዘዴዎች መተግበር  እንደሚያስፈልግ አክለዋል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ ከሰብል ጥበቃ አኳያ አርሶ አደሩ የሰብል በሽታዎችን ለምሳሌ ዋግና ሌሎች ፈንገስን  የመከላከልና መቆጣጠር ሥራ በተጠናከረ መልኩ ማከናወን፣ የሰብል ተባዮችን ለምሳሌ የአሜሪካ መጤ ተምችን ባሉት አማራጮች በመጠቀም መከላከል አለበት፡፡

የግሪሳ ወፍ መንጋ በሞቃታማና በቆላማ የአገሪቱ አካባቢዎች ይከሰታል በሚል ሥጋት የአሰሳ ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፣ በተገኙባቸው ቦታዎችም ተገቢው የመከላከል ሥራ እየተሠራ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በመስኖ የሚለሙትን የአትክልት ሰብሎች ከአረም፣ ከበሽታና ከተባይ መጠበቅ፣ የመኸርና የበልግ ሥራ በተጠናከረ መልኩ እንዲጀመር የበቆሎ ገዳይ ቫይረስን በተመለከተም አርሶ አደሩ ምልክቱን በማሳው እንዳየ ቶሎ ነቅሎ እንዲያስወግድ፣ ዘግይተው የተዘሩ የብርዕ ሰብሎችን ከዋግ በሽታ ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራትም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው  ሰሞኑን በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክቷል፡፡