Skip to main content
x

አገር የሚያድነው ዴሞክራሲያዊነት ብቻ ነው!

 በያሲን ባህሩ  

የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ከሚያጓጓ ተስፋ ወደ አስከፊ ሁኔታ መንሸራተት የታየበት ነው፡፡ በእርግጥም እየታያ ያለውን የፖለቲካ ቀውስ፣ አለመተማመንና ሕዝባዊ ሥጋት ሕዝቡ፣ መንግሥት፣ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች፣ የሃይማኖት ተቋማትና የሲቪክ ማኅበራት ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ተደማምጠው ካልፈቱት መካረሩና መቋሰሉ ይዞን ወደ ማጥ ላለመግባቱ ዋስትና የለም፡፡ ከዚህ በኋላም ኢሕአዴግ ያለውን ችግር ብቻዬን እፋታለሁ በሚል አጉል ተስፋ ውስጥ ከቀጠለ ስንዝር እንደማይራመድ ማጤን ከብልህነትም በላይ አስተዋይነት ነው፡፡

ከታሪካችን እንደምንረዳው በተለይም ባለፉት 26 ዓመታት በተጨባጭ እንዳረጋገጥነው ሰላምን ማረጋገጥ ማለት ለሁሉም ነገር መሠረት ማበጀት ማለት ነው። እንበለ ሰላም ልማት፣ እንበለ ሰላም ዕድገትና ብልፅግና አይታሰቡም። ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም መግባት የሚችሉት፣ ሠርተው ኑሯቸውን የሚያሻሽሉትና ብሎም ሀብት የሚያፈሩት አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ሲረጋገጥ ብቻ ነው። በድምሩ መንግሥት፣ ድርጅትም ይባል ሕዝብ ተረጋግተው የሚኖሩት ሰላም ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ለነገሩ ሰላም ከሌለ አገርስ ምን ኖረ ይባላል!!?

በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ የሚመራው የኢፌዴሪ መንግሥት የሕዝብን የተከማቹ ጥያቄዎች ሙሉ ለሙሉ መመለስ ባለመቻሉ፣ የአገር ሰላም ክፉኛ ለአደጋ ተጋልጧል፡፡ የዜጎች ሞት፣ የአካል መቁሰል፣ የንብረት መውደም፣ ስደትና የሕዝብ መፈናቀል ብሎም ብልጭ ድርግም የሚል የብሔር ግጭት እየታየ የመጣው ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በዚህም ከመደማማጥና በዴሞክራሲው ምኅዳር ከመታገል ይልቅ ባለቤት የሌለው ትርምስ፣ በማኅበራዊ ድረ ገጽ የሚመራ ቀውስ አገሪቱን ይለበልባት ይዟል፡፡ ይህን ሁኔታ እንደ ምቹ አጋጣሚ የተጠቀሙበት አንዳንድ የውጭና የአገር ውስጥ ኃይሎች በፈጠሩት ቀውስ፣ የአገር ህልውናን ከመፈታተን ጀምሮ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው።

እነዚህ በተለይ የማኅበራዊ ድረ ገጽ ፅንፈኛ ኃይሎች (በመንግሥትም በተቃዋሚውም ወገን) የሕዝቡን ጥያቄ ይጠምዝዙት ዘንድ ማስቻሉ፣  የመንግሥት አሠራርን ለሕዝብ ግልጽ ያለማድረግና በአንዳንድ ዘርፎች በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው የተጠያቂነት አሠራር መጣሱ ሁኔታውን ይበልጥ አባብሶታል የሚል እምነት ግን የብዙዎች ነው፡፡

ተደጋግሞ እንደተገለጸው ከተሃድሶው በፊት በሥርዓቱ ውስጥ አደገኛ አድርባይነትና ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ለመልካም አስተዳዳርም ሆነ ለውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲው እንቅፋት መሆኑ ታይቷል፡፡ ራሳቸውን ከሕግ በላይ ያደረጉ ግለሰቦችና ቡድኖች ሕዝብን ንቀው የነበረ መሆኑም በግላጭ ከመታየቱ ባሻገር፣ ሊገነደስ የማይችል ኔትወርክ እየፈረጠመ ራሳቸው ግንባሩን የመሠረቱ ብሔራዊ ድርጅቶችን ሲያፈላቅቅ እየታየም ነው፡፡ ይህን ችግር እንዴት ተሃድሶው ሳያስተካክለው ቢቀር ነው ችግሩ እስካሁንም ተባብሶ የቀጠለው የሚለው ጥያቄ ግን አሁንም እንዳነጋገረ ነው፡፡ የተሃድሶውን ጥልቀትም ጥርጣሬ ላይ ጥሎታል፡፡

በዚያ ላይ በተለያዩ የተሃድሶ መድረኮችና ግምገማዎች እንደተወሳውና ከሕዝቡ ዘንድ በተለያየ መንገድ እየደረሰ እንዳለው መረጃ፣ በመንግሥትና በመሪ ድርጅቱ በየደረጃው በሚገኙ አመራሮች የተፈጸሙ ጥፋቶች ከሚገመቱት በላይ መሆናቸውን  ነው፡፡ እነዚሁ አመራሮችም በየጥልቅ ተሃድሶው መድረክና በየመገናኛ ብዙኃኑ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሲሰጡ ከመደመጥ ባለፈ፣ በዚያው የተለመደ የብሔርተኝነት ጨዋታ ለመቀጠል መሻታቸው ነው፡፡ ተተኩ የተባሉት አብዛኛው አዳዲስ ምሁራን የካቢኔ አባላትም ከተፅዕኖ ሊላቀቁ የማይችሉ መሆናቸው የሕዝቡን የለውጥ ተስፋ አሰናክሎታል።

ከግለሰብ ፍላጎትም በላይ የሥርዓት መገለጫ እየመሰለ የመጣው የፓርቲና የመንግሥት ሥራን በመቀላቀል ሕገወጥ ተግባራት መፈጸማቸው፣ በኔትወርክ በመቧደን የአገር ሀብት ያለቅጥ መዘረፉ፣ አንዳንዶች የግዥና የጨረታ ሕጎችን እየጣሱ ራስንና ቢጤዎቻቸውን ማበልፀጋቸው፣ መብታቸውን ለማስከበርና አገልግሎት ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ ዜጎችን ማንገላታታቸውና የመሳሰሉትን ችግሮች መፈጸማቸው በኑሮ ውድነትና በዴሞክራሲ ምኅዳር መጥበብ የዛለው ሕዝብ ላይ ሌላ ብሶት እየጨመረበት መሆኑ ታይቷል፡፡

በዚህ ላይ እነዚህ የታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ጊዜ መስጠት ባያስፈልግም  መንግሥት ችግሩን ለማረም፣ የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስና የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል እስከ ሕዝቡ ድረስ የወረደ ጥልቅ ተሃድሶ ቢያስፈልግም በተሟላ ደረጃ አልተካሄደም፡፡ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የሚገኙ ጎምቱ ፖለቲከኞችና ድርጅታቸውን ያሳተፉ የሰጥቶ መቀበል መርህን የተከተለ ምክክር አለመጀመሩ፣ በተለያየ መንገድ የታሰሩ የፖለቲካ ተከሳሾችን ለመልቀቅ አለመሞከሩ፣ እንዲሁም ከፌዴራሊዝሙ የአፈጻጸም ጉድለት በመነጨ ክልል ከክልልና ሕዝብ ለሕዝብ የሚያጋጩ ድርጊቶችና አስተሳሳቦች አለመስተካከላቸው ሕዝባዊ ቅሬታውንና የሰላሙን መታወክ ዳግም ቀስቅሰውታል፡፡    

ከተሃድሶ በኋላ የአገሪቱ ልማት ባለቤት ሕዝብ መሆን ሲገባው፣ በተለይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማትና አመራሮች በጭፍን ሲወስዱት የነበረው ዘረፋና የሙስና ወንጀል መጋለጥ ጀምሯል፡፡ ሕዝቡ አሁንም ያልተነኩ ቱባ ሙሰኞች አሉ ቢልም፣   ዛሬም ቢሆን ይጠብቅ የነበረውን አገልግሎት ማጣቱ እያስቆጨው ነው፡፡ በተለይ በአዲስ አበባና በዋና ዋና ከተሞች፣ በማዘጋጃ ቤቶችና በተለያዩ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት የዜግነት መብታቸው ተገፎ ለእንግልት የተዳረጉና በገንዘባቸው ፍትሕ እንዲገዙ የተገደዱ ዜጎች እንዳሉ የታወቀ ነው፡፡

እነዚህና በወሳኝነት የሚገጥሙ የኢኮኖሚ ጥያቄዎችና የሀብት ክፍፍል ጉዳዮች ሕዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ ሆነው ሊደማመጡ የማይችሉ እያስመሰሉ ነው፡፡ በዚህም መዘዝ በተለያዩ ክልሎች የበርካቶች ሕይወት ተቀጥፏል፣ ብዙዎች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፣ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት ወድሟል፣ አሁንም ድረስ ተደጋጋሚ ጥፋት እየታየ ይገኛል፡፡ ከዚህ ባልተናነሰ በብዙዎች ዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሥነ ልቦና ቀውስ ተፈጥሯል፡፡ በተለይ ደግሞ የብሔር ግጭት እየመሰሉ የመጡ የጥፋት ድርጊቶች የአገርና የሕዝብ ህልውናን ለአደጋ እንዲጋለጥ የሚያደርጉ መሆናቸውም ብዙዎችን አሥግቷል፡፡  

ባለፈው ዓመት በአገሪቱ በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራና በአንዳንድ የደቡብ ክልል አካባቢዎች በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት የአሥር ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ፣ ችግሮችንማርገብ እንደረዳ ሲነገር ቆይቷል። ያም ሆኖ ግን ለዘላቂ ሰላም የሚበጁ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መምከር ሁነኛ መፍትሔ ቢሆንም፣ መንግሥትም የጥልቅ ተሃድሶ መድረኮችን አዘጋጅቶ መነጋገሩ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እየገነባሁ ነው ከሚል መንግሥት የሚጠበቅ ቢሆንም፣ መፍትሔውን ከልብ አምኖ ፈጣን ዕርምት ከመውሰድ አንፃር አሁንም የመንግሥት ቁርጠኝነት አናሳ መሆኑን ብዙዎች እየተቹት ነው፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ሚናቸው የማይናቅና ምናልባትም ከገዥው ፓርቲ እንደሚስተካከል ከማያጠያይቁት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር መደራደርንም የጥልቅ ተሃድሶው አካል ማድረጉ የሚበረታታ ነበር፡፡ ይሁንና አንደኛ ድርድሩ ሁሉንም የፖለቲካ ወገኖች አለማሳተፉ (እዚህ ላይ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ የራሳቸው የተደራዳሪ ፖለቲከኞቹ ድክመትና አስመሳይነትም እንዳለ ሆኖ)፣ ድርድሩም የሚጨበጥ ውጤት ከማሳየት ይልቅ ጊዜ መግዣና በተለመደው የትናንቱ መንገድ ዕውን እየሆነ መምሰሉ ብዙዎችን እያሳዘነ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ከሰላም ይልቅ የአመፃ በሮች እንዲበረገዱ እያደረገ ነው፡፡

ከተሃድሶው በኋላ ገና በሕዝቡ የተነሱ ጥያቄዎች በወጉ ተለይተው መፈታት ሳይጀመሩ በተሃድሶው በርካታ ችግሮች እየተቀረፉ እንደሆነ፣ በጥልቅ ተሃድሶው ሁሉም ነገር በሰላምየተጠናቀቀ እንደመጣ መለፈፉና በተለመደው የፕሮፓጋንዳ መንገድ ወቅቱን ያላገናዘበ የመረጃ ልውውጥ መቀጠሉ፣ ጠያቂውን ሕዝብ በተለይ ወጣቱን ዳግም ወደ አደባባይ እንዲወጣ አድርገዋል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ፡፡

ከዚህ እውነታ በመነሳት ነው አሁንም ስለአገራዊ ሰላማችንና አብሮነታችን ሲባል በዋናነት ከመንግሥትና ከገዥው ፓርቲ በአፋጣኝ የሚጠበቁ ዕርምጃዎች አሉ የምለው፡፡ በቀዳሚነት አሁንም በጣም መሠረታዊ የሚባሉ ጥያቄዎች ምላሽ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለሆነም፣ የመንግሥትና የገዥው ፓርቲ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊን ሁላችንም እፎይ ብለን የምንቀመጥበት ሰዓት ላይ እንዳልደረስን ተገንዝበን በየፊናችን በነፃነትና በአገራዊ ስሜት የየድርሻችንን ልንወጣ ይገባል።

በመቀጠል መንግሥት የሕዝቦችን የሰላም ዋስትና ለማረጋጋጥ በየቦታውና በየመንደሩ ወታደር ሊያቆም ስለማይችል ስለይቅር መባባል፣ አብሮነትና አገራዊ አንድነት ማስተማር፣ በተግባር መቆምና እንዲህ ዓይነት ተግባራትን ለመፈጸም የሚችሉ ኃይሎችን ማነቃነቅ ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ ረገድ የመገናኛ ብዙኃንን ቅኝትም አስተካክሎ ለእውነተኛ ዕርቅና በእኩልነት መንፈስ ለሚደረግ ፀረ ዘረኝነትና ፀረ ጎጠኝነት ዘመቻ ሕዝቡን ማነሳሳት ይገባል፡፡

በተለይ በፓርቲዎች መካከል የሚደረገው ድርድር ላይም ማንም ሸምጋይ ሳያስፈልግ ሕዝቡ የሚለውን ብቻ በማዳመጥ (ታደሱ ወይም ፍረሱ፣ ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ፣ በፅናት ታጋሉ ወይም አርፋችሁ ቁጭ በሉ) ዘላቂ መፍትሔ በጋራ ማስቀመጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ተወቃሹም ሆነ ተመሥጋኙ ኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን፣ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና ሁሉም የዴሞክራሲ ተቋማት እንደሆኑ መገንዘብም ይጠበቃል፡፡

በእርግጥ እስካሁን እየታየ ያለው የፓርቲዎች ድርድር ከጅምሩ ጭንጋፍ  የመሰለውና በቀጣይ የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋት ስለማስቻሉ ተስፋ ያላሳደረው ለምንድነው ብሎ መጠይቅ ያስፈልጋል። ዴሞክራሲ ሥርዓት ሆኖ እንዲቀጥል ኃላፊነቱ የመንግሥት ወይም የገዥው ፓርቲ ብቻ እንዳልሆነ ስለድርድሩ ስኬት ሕዝቡ ሊገነዘብም ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎችን ሁሉ እገዛ ይፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ እንደ ሱቅ በደረቴ መሥርቶ አለሁ በማለት የተበታተነ ትግል ከመምራት ይልቅ፣ በርዕዮተ ዓለምና በዓላማ እንግባባለን የሚሉ ተሰባስበው ጠንካራ ድርጅት መፍጠር ላይ ማተኮርም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ሕዝቡ ከስሜትና ከሁከት በመውጣት ሰላሙንና አንድነቱን ጠብቆ ይወክለኛል በሚለው የፖለቲካ ኃይል (ገዥው ፓርቲን ጨምሮ) ላይ ሁሉ ግፊት ማድረግ ይገባዋል፡፡ ያስፈልጋልም፡፡

በመሠረቱ አሁን በምርጫው የቅይጥና የመደበኛ ድምፅ አቆጣጠር ስምምነቱ ላይ  እንደታየው በተለያዩ የፖለቲካ አሳታፊ ምኅደሮችም ኢሕአዴግ ከድርቅና ወጥቶ፣ ፓርቲዎቸም አንድ ዕርምጃ የተሻለ ሐሳብ ይዘው መነጋጋር ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ  በብሔራዊም ይሁን በኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀት ውስጥ ሆነው በምርጫ ጊዜ ብቻ ከያሉበት እየተጠራሩ በመምጣት፣ ‹‹ምኅዳሩ ጠበበብን›› የሚሉትን የስም ፖለቲከኞችን  በቃችሁ ሊላቸው ይገባል። በግለሰቦች ተክለ ሰውነት ሥር የተከለሉ፣ አባላቶቻቸውም ሆኑ ደጋፊዎቻቸው የማይታወቁ መናኛ ፓርቲዎች ለአገር የሚፈይዱት ምንም ነገር የለም፡፡ ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋርም አይሄዱም፡፡

በአገራችን ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ብልጭ ብሎ ድርግም ያለውና የተደናበረው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ብልሹውን የፖለቲካ ባህል እንዲያስወግድ ከተፈለገ፣ የዜጎች ሐሳብን የመግለጽ መብትና የፕሬስ ነፃነት በተጨባጭ መረጋጋጥም አለበት፡፡ በመሠረቱ ሥልጡን ዴሞክራሲ የሚፈልገው ሰከን ያለና የሠለጠነ ግንኙነት እንጂ፣ የቀደመውን የቡድንተኝነትና የድርቅና ፖለቲካን አይደለም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡

ከዚህ አንፃር በአገሪቱ በብዛት የተንሰራፉ መንግሥትና ፓርቲ መንቻካ መገናኛ ብዙኃን በማስተካካልና ነፃነታቸውን በማቀዳጀት፣ አዳዲስና ነባር ፕሬሶችም እንዲበረታቱ በማድረግ ዴሞክራሲያዊ ሐሳቦች በነፃነት የሚሽንሸራሸሩበት፣ ዜጎች የማያስማሙ ጉዳዮችን እያቻቻሉ በሚያስማሙ ጉዳዮች ላይ የሚግባቡበት፣ ከኃይል ይልቅ ውይይትን የሚያስቀድሙበትና ለሕዝብ ፍላጎት ተገዥ የሚሆኑበት ነፃ መድረክ እንዲጎለብቱ መደረግ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ወገኖች ከፍ ያለ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

አሁን በአገራችን ውይይትም ሆነ ድርድር እያደረጉ ያሉት ፓርቲዎች፣ በዝግጅት ላይ የሚገኙትም ሆኑ በጽንፈኛ ፖለቲካ ተወጥረው ከዳር የቆሙት ስለሕዝቡና የአገር ጥቅም ሲባል ተቀራርበው የሚነጋገሩበት ሁኔታም ፈጥኖ ዕውን መሆን ይኖርበታል፡፡  ሁሉም ወገኖች ለሕዝብ የሚጠቅሙት ያለፉትን ቂምና ቁርሾዎች ወደ ጎን በማድረግና ለአገርና ለሕዝብ ምንም ጥቅም እንደሌላቸው ከልብ በማመን፣ አዲሱን ጉዞ በሠለጠነ መንገድ ላይ በመጓዝ ሲጀምሩት ብቻ እንደሆነ መጠራጠር አይገባም፡፡

በዚች አገር ዴሞክራሲ እንዲገነባ ብቻ ሳይሆን ሰላምና የሕዝብ ደኅንነት እንዲረጋገጥ፣ ብሎም እንደ አገር አብሮነታችን ተጠብቆ እንዲቀጥል ሁሉም ወገኖች በአገራቸው ጉዳይ በእኩልነት መንፈስ መሳተፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ከጥላቻ ፖለቲካ በመውጣት፣ ያለፉት 27 ዓመታት የአገሪቱ አዲሱን ጉዞም በጅምላ ከማጨለም በመውጣት መነጋገርን ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከፖለቲካ ፍጆታነት የማይዘሉ አጓጉል ድርጊቶችን በማስወገድ የዜጎችን አንገት ሲያስደፋ የኖረውን አስከፊ የፖለቲካ ባህልመለወጥ ጊዜው አሁን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ቁጠርኛ መሆን የሁሉም ግዴታ ነው፡፡

የዚህ ጽሑፍ ማጠቃለያ ግን ሁሉንም ችግሮችን ለመፍታት በዋናነት ኳሱ በእጁ ያለችው መንግሥትን (ገዥው ፓርቲ) በአፅንኦት በመምከር ላይ የሚያተኩር ይሆናል፡፡ አሁንም ከብዙ ችግርና ወጣ ውረድ በኋላ ኢሕአዴግና መንግሥትን (ከሁለት አካል ይልቅ አንድ ስለሆኑ) እንደ ሕዝብ ምክርን ስማ፣ ተግሳጽንም ተቀበል ማለት የሚያስፈልገውም የብዙኃኑ ሕዝብ ስሜትም ከዚህ እንደማይርቅ በማመን ነው፡፡  ‘ምክርን የማይሰማ ተግሳጽንም የማይቀበል ሰው ዕውቀትን አይወድም... ጠቢብም አይሆንም... ፍፃሜውም አያምርም...’ እንደሚለው የመጽሐፍ ቃል፡፡

በኢሕአዴግ መንግሥትነት ታሪክ ውስጥ በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡና ተስፋዎች የታዩ ቢሆንም፣ በሕዝቡ ውስጥ ጠንካራ አንድነት አለመፈጠሩ፣ ከኅብረት ይልቅ ልዩነትና የታሪክ ሽኩቻ ላይ ብቻ ሲለፈፍ መክረሙ፣ ፌዴራሊዝሙ ዴሞክራሲ አልባ በመሆኑ ችግር መፍታት እያቃተው መምጣቱ፣ የመልካም አስተዳዳር እጥረትና አንዱ የበላይ ሌላው የበታች የሚያስመስል የፖለቲካ ዝንፈት እያቆጠቆጠ መምጣቱ ችግሮች እየተደራረቡ እንዲመጡ ሆነዋል፡፡

ይህ ሁኔታ ደግሞ ከመንግሥትና ከሕዝብ አለመግባባትም አልፎ ሕዝብን ከሕዝብም ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት እንቅፋት እንደሆነ በየመድረኩ ይነገራል፡፡ ጉዳዩም ከፖለቲካ ተገዳዳሪዎች የቅስቀሳ ማጠንጠኛነት አልፎ ሕዝቡና የማኅበራዊ ድረ ገጹ የዕለት ከዕለት አጀንዳ ማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን፣ በተጨባጭም የአገር ሰላም ሥጋት እንደሆነ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ  በስፋት ታይቷል፡፡

ይሁንና መንግሥት ጉዳዩን እንደለየ ከመግለጽ አልፎ በተለመደው ጠባብ የፖለቲካ ምኅዳር ከእግሩ ወጣሁ ለማለት ከመባዘን አልፎ፣ አዲስ የመፍትሔ ሐሳብ ሲያመጣ አልታየም፡፡  በሚገርም  ደረጃ ብዙዎቹ መንግሥት ኃላፊዎችና ባለሥልጣናት  ጠባያችሁ... አሠራራችሁ... አካሄዳችሁ... አመለካከታችሁ... የክስተቶች አያያዛችሁ፣ የችግር አፈታት ዘዴያችሁ ወዘተ ጉድለት ይታይበታልና አስተካክሉ፣ መልካሙንም መንገድ ያዙ ሲባሉ እሺ አይሉም፡፡ በፓርቲ ግትርነት ታጅለው ሕዝባዊ ተራማጅነት ግን የራቃቸው ሆነዋል፡፡ በዚህ መንገድ ደግሞ ‘አንጋፋ ታጋይ’ የሚባሉት ሁሉ በሐሳብ ተለያይተዋል፡፡

በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት ደጋፊም ሆነ ተቃዋሚ ከሚያቀርብላቸው ‘ከሚሰነዝርባቸው’ ምክርና ተግሳጽ መካከል ቢያንስ የተሻለውን ሰምተውና መዝነው የማስተካከያ ዕርምጃ ቢወስዱ፣ ጥቅሙ ለራሳቸውና ለአገር መሆኑን መገንዘብ ይቸግራቸዋል፡፡ ከዚህ ይልቅ ‹‹የጠላት ወሬ ነው... መሠረተ ቢስ አሉባልታ ነው... ድብቅ ዓላማ ከጀርባቸው ያዘለ ነው... ምን ያመጣል? የት ይደርሳል? እንደ እኛ መሆን ሲያቅተው ነው... ምቀኛ ነው... በውጭ ኃይል ተገፋፍቶ ነው... እሱን ብሎ መካሪና ተቺ ... ወዘተ…›› ማለት የሚቀናቸው ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ያፈርሰን ይሆን እንጂ የትም አያደርሰንም፡፡

መደማመጥ ከራቀና በጥላቻ ወደ ብሔር ግጭትና እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ካመራን መዳኛ አናገኝም፡፡ አሁን እየታየ ካላው አስከፊ ዝንባሌ አንፃር የአገሪቱ ሰላም በቀላሉ ከመንግሥት እጅ ሊወጣ የሚችል መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ መልሶ ለማምጣትም ፈተና መሆኑ አይቀርም፡፡ ስለሆነም እንደ አገር ውስጣችንን ማየት፣ ያልተቋረጠ የፖለቲካ መፍትሔና ሁሉን አቀፍ የዴሞክራሲ ትግል ማካሄድ፣ እያንዳንዷን እንቅስቃሴ መለካት፣ መገምገምና አርቆ ማገናዘብ ያስፈልገናል፡፡ ቅንነትና አርቆ አሳቢነት ሳይኖር በእልህና በስሜት አገር ሊገነባ አይችልምና፡፡

በየአካባቢው የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችንና ፍላጎቶችን እያሳነሱ፣ የገለልተኛ ወገኖችንና ምሁራንን ጥሞናዊነት የተላበሰ ሂስ እያቀለሉ ምክር ባለመስማት፣ ወይም የትም አይደርሱም በማለት አሳንሶ ከማየት በሚመጣ አለማስተዋል አገር አደጋ ላይ እንዳትወድቅ የመንግሥት ኃላፊነት ትልቅ ነው፡፡ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በአገራችን እየታዩ ያሉት ሕዝባዊ እምቢተኝነቶች ተጨባጭ ለውጥን እያነፈነፉ ነው፡፡ በገዥው ፓርቲ ተሃድሶ፣ በግለሰቦች መቀያየር፣ በፓርቲዎች ስም በሚደረግ አስመሳይ ድርድርና በአንዳንድ አካባቢዎች በተሞከሩ የመቻቻል ኮንፈረንሶች ብቻ ነገሩ የተረሳ ወይም ችግሩ የተፈታ ከመሰለ ግን ወቅታዊ ሁኔታውን ያለመገንዘብ ውጤት ነው፡፡ እንግዲህ ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነውም ስንፈራው የኖርነውን ለአገራዊ ዕርቅና ለብርቱ ብሔራዊ መግባባት መላው ኢትዮጵያዊን ገጠር፣ ከተማ፣ ስደተኛ፣ ባላገር ሳይባል ተሰባስቦ በመደራደርና በመነጋጋር  የጋራ መፍትሔ ማስቀመጥ  ብቻ ነው እላለሁ፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡