Skip to main content
x

የነገውን ሰው ማነፅ - ይድረስ ለወላጆችና መምህራን

ውድ አንባቢያን እንደምን ሰነበታችሁ? በዛሬዋ መልዕክቴ የምንመለከተው ዐቢይ ነጥብ ጨዋታ በሕፃናት አስተዳደግ ላይ መሠረታዊ መማሪያ መድረክ መሆኑንና የማሰብ ችሎታቸው እንዲዳብር፣ የግንዛቤ አድማሳቸው እንዲሰፋ፣ የቋንቋ ክህሎታቸው እንዲጠናከር፣ ጥበብን እንዲካኑና የእጅ ሥራ ዕውቀታቸው እንዲጎለብት የጨዋታ መድረኮችን ማመቻቸት በእጅጉ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን ማሳየት ነው፡፡ በመሆኑም የዛሬዋ መጣጥፌ የምታተኩረው በሕፃናት አስተዳደግ ሒደት ላይ ጨዋታ ስላለው ጤናማና አይተኬ አስተዋጽኦ ይሆናል፡፡  

በሕፃናት አስተዳደግ ሒደት ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች የጨዋታን ጠቀሜታ እንደሚከተሉት አስፍረውታል፡፡ ሕፃናት በአካል፣ በአዕምሮ፣ በስሜትና በማኅበራዊ ለጋና ታዳጊ ስለሆኑ የሚያዩት፣ የሚሰሙት፣ የሚዳስሱትና የሚያሸቱት ሁሉ ከህልውናቸው ጋር በፍጥነት ይዋሃዳል፡፡ ሕፃናት መንቀሳቀስ የሚወዱና በአንድ ሥራ ላይ ብቻ ለረዥም ጊዜ ተጠምደው መቆየት የማይችሉ ናቸው፡፡ ጨዋታ ይወዳሉ፡፡ ጨዋታ ሲባል ቧልት፣ ፌዝና ቀልድ ሳይሆን የአካል ቅልጥፍናን፣ የአዕምሮ ንቃትን፣ በሥራ መደሰትን፣ በዕቅድ መመራትን፣ ግምትን፣ ፈጠራን፣ መውድድንና መወደድን፣ ማኅበራዊ ግንኙነትንና ባህልን ሊያስተምር የሚችል በቁም ነገር የተሞላ ጨዋታ ማለት ነው፡፡ ሕፃናት በጨዋታ ደስታንና እርካታን ያገኛሉ፡፡ ጥናቶች እንዳረጋገጡት ተጫዋች ሕፃናት ጤናማ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በአገራችን የጨዋታን ጠቀሜታ ባልተረዱ ቤተሰቦች ውስጥ የሚፈጠሩና ለጨዋታ ነፃ ጊዜ ተነፍጓቸው የሚያድጉ ሕፃናት ቁጥር ቀላል አለመሆኑን መገመት አያስቸግርም፡፡ 

ጨዋታ በይዘቱ የሕፃናትን አዕምሮ፣ አካል፣ ስሜት፣ ቋንቋ፣ ኪነ ጥበብና የሥራ ፍላጎትን ያዳብራል፡፡ የመማር ፍላጎትንም የማነቃቃትና የማጎልበት ኃይል አለው፡፡ ሕፃናት በጨዋታ አማካይነት የነገሮችን አንድነትና ልዩነትን የመለየት ክህሎት ያዳብራሉ፡፡ በጨዋታ ቀለም፣ መጠን፣ አቅጣጫና የመሳሰሉ ሐሳቦችን ይማራሉ፡፡ ጨዋታ የሕፃናትን የማስታዎስ ችሎታ ለማዳበር የሚረዳ በመሆኑ በትምህርት ዓላማዎች ላይ ተመሥርቶ እንዲዘጋጅ ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡ ለተፈላጊው ዓላማ፣ ዕድሜና የዕድገት ደረጃ ተስማሚ እንዲሆን አድርገን ማዘጋጀት እንችላለን፡፡ ጨዋታን ለመፍጠር የሚጠይቀው ጥቂት ጊዜና ማሰብ ብቻ ነው፡፡

ለመሆኑ ለአፍታ መንገድዎን አቋርጠው የሕፃናትን ጨዋታ ተመልክተው ያውቃሉ? በሥራ ተጠምደው በስሜት የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ በዚህም ንቁ ተሳትፏቸው ከአካባቢያቸው ይማራሉ፡፡ ለበርካታ ስዓታት የመንገድ ቅያሶችን በወረቀት ላይ ሲሠሩ፣ የቃላትን ድምፀት ሲቀዱና ሲኮርጁ ይውላሉ፡፡ ሕፃናት በአካልና በአዕምሮ ዕድገት ላይ ስለሆኑ በተወሰነ አካባቢ ለረዥም ጊዜ እንዲቀመጡ ማስገደድ የሚደገፍ አይደለም፡፡ በተሻለ ሁኔታ ይበልጥ መማር የሚችሉት ተጨባጭ ነገሮችን ሲነካኩ፣ ሲፈትሹና ሲጠበቡ ነው፡፡ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ልናበረታታቸው ይገባል፡፡ ምናባዊ ችሎታቸውን እንዲያዳብርላቸው ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይኖርብናል፡፡ ይህ ሁኔታ ምቾትና ደኅንነታቸው የተጠበቀ መሆኑ እንዲሰማቸው ይረዳል፡፡ ካልሆነ ግን በነገዪቱ ዓለማቸው ከሚከሰቱት አዳዲስና ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር ለመጣጣም ይከብዳቸዋል፡፡

ሕፃናት ስሜት ቀስቃሽ ከሆኑ የተለያዩ ጨዋታዎች ብዙ መማር ይችላሉ፡፡ የወረቀት ላይ እንቆቅልሾችን ሲገጣጥሙ ወይም በመቀስ ቆርጠው ሲያጣብቁ የትናንሽ ጡንቻዎቻቸውን፣ የዓይኖቻቸውንና የእጆቻቸውን ቅንጅቶች ያዳብራሉ፡፡ እነዚህ ጨዋታዎች ሕፃናት ለማንበብና ለመጻፍ ዝግጅት በሚያደርጉበት ወቅት ይረዷቸዋል፡፡ ከቁርጥራጭ እንጨቶችና ድንጋዮች ቅርጾችን ለመሥራት በጨዋታ ሲሳተፉ ከጓደኞቻቸው ጋር በመግባባት መተባበርን ይማራሉ፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ሐሳብን የመግለጽና የሌላውን ሐሳብ የመቀበል ችሎታቸውን ያዳብራሉ፡፡ አካባቢያቸውን ይበልጥ እንዲያውቁ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ ከማዕዘናት ቅርጾች፣ ከማመዛዘን ሕግጋትና ከሌሎች ትምህርቶች ጋር ያላምዳቸዋል፡፡ ሕፃናት በጣም የሚፈልጉት ተግባር  ጨዋታ በመሆኑ አስፈላጊነቱን እኛ አዋቂዎች ልናንኳስስባቸው አይገባም፡፡ ሕፃናት ሲጫወቱ ይማራሉና ቢቻል መደሰት ይኖርብናል፡፡ አንድ የጥንት ቻይናውያን አባባል ይህንን ሁኔታ እንዲህ ይገልጸዋል፡፡

“ሰማሁ - ረሳሁ፣
አየሁ - አስታወስኩ፣
ሞከርኩ - ተማርኩ፣
ተማርኩ - አወቅሁ፡፡” 

ይህ የዕድገት ደረጃ ሕፃናት በዙሪያቸው ያለችውን ዓለም በመፈለግ፣ የሚመራመሩበት፣ የሚፈትሹበት፣ የሚያጠኑበት፣ ወደ ውስጣቸው የሚያደርሱበትና ከፍላጎታቸውና ምኞታቸው ጋር ማስማማት የሚጀምሩበት ወቅት ነው፡፡ በመሆኑም ለሕፃናት የሚቀርቡላቸው የመጫወቻ ዕቃዎችና መሣሪያዎች ዓይነት፣ መጠንና ብዛት የሚወሰነው በመኖሪያ አካባቢያችንና በእጃችን ውስጥ ባሉ ነገሮች ላይ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በጣም አዋጪ ዕቃዎች ወይም መሣሪያዎች የሚገኙት ጠቀሜታቸውን ካለማወቅ ከቤት ከሚወገዱ ቁሶች ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ የፕላስቲክ ጠርሙሶችና ስኒዎች (የጠሩና ዕይታ አስተላላፊ ቢሆኑ ይመረጣል)፣ ቡሾች፣ ማጥለያዎች፣ ማንቆርቆሪያዎች፣ ወንፊቶች፣ ከፕላስቲክ የተሠሩ ጎድጓዳ ሳህኖች፣ ቅሎች፣ ማንኪያዎች፣ ዝርግ መጥበሻዎች፣ ዱላና አርጩሜ፣ ቀርከሃ ወይም ሽመል፣ ምግብ ማሸጊያ ቆርቆሮዎች (ሹል፣ ስለታም፣ ያፈነገጡና ያገጠጡ መሆን የለባቸውም)፣ የጠርሙስና የገንቦ ክዳኖች፣ የቀንድ አውጣ ሽፋኖች፣ የለውዝ ሽፋኖችና ቀለል ያሉ እንጨቶች ከሚጠቀሱት ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ብረት ነክ ነገሮች ከዝገት የነፁ መሆን አለባቸው፡፡ ብርጭቆዎች ተሰባሪ በመሆናቸው አደጋ ያስከትላሉና ፈጽሞ ጥቅም ላይ መዋል የለባቸውም፡፡

ሁሉም የጥበብ መሣሪያዎች በአካባቢያችን ይገኛሉ፡፡ ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤት ከመሄዳቸው በፊት እነዚህን ቁስ አካሎች ከአካባቢያቸው በቀላሉ አግኝተው በመጠቀም ጥበባዊ በሆነ መልኩ ራሳቸውን መግለጽ ይጀምራሉ፡፡ አንድ ሕፃን እጆቹን በአሸዋ ውስጥ ባሽከረከረ ወይም በጣቶቹ ሥዕል በሣለ መጠን በፈጠራ ሥራ ራሱን እያዳበረ ነው፡፡ አንድ ሕፃን በመሬት ላይ በእንጨት እየሞነጫጨረ ሥዕሎችንና ምልክቶችን ሲሠራ በዙሪያው ያለችውን ዓለም በተዘዋዋሪ እየተመለከተ ነው፡፡ በመሬት ላይ እንጨት ወይም በወረቀት ላይ የቀለም እርሳስ የሚጠቀሙ ሕፃናት ራሳቸውን ለመግለጽ በአካባቢያቸው የሚገኙ ነገሮችን እየተጠቀሙ ነው፡፡   

ሕፃናት ነገሮችንና ሁኔታዎችን የመረዳት፣ የማስተዋል፣ የመገንዘብና የመምረጥ ቀላል የማይባል ችሎታ አላቸው፡፡ በመሆኑም እኛ የምንሰጣቸው አስተያየቶች ገንቢ ካልሆኑ ሕፃናት ተጠራጣሪነትንና እምነት ማጣትን ይማራሉ፡፡ በአጠቃላይ ነገሮች ሁሉ ጥሩ እንዳልሆኑ ሕፃናት የማወቅ ችሎታ ያላቸው ስለሆነ እኛ ሁልጊዜ ታማኝ፣ ትክክለኛ፣ እውነተኛ፣ ቅንና አመዛዛኝ ሆነን መቅረብ ይኖርብናል፡፡ በዕቃ ጥራት (ለስላሳነት፣ ሸካራነት፣ ቀለም፣ ውበትና ቅርፅ) ላይ የምንሰነዝራቸው አስተያየቶች በአመለካከት ላይ ተፅዕኖ ያላቸውን ያህል በሕፃናት ተሳትፎ ላይ የምንሰነዝራቸው አስተያየቶች በሰብእናቸው ላይ ተፅዕኖ አላቸው፡፡ ለምሳሌ አንድን ሕፃን “ምን ዓይነት አስደሳች ቀለሞች መረጥክ? ሥራህን በጥንቃቄ እየሠራህ እንደሆነ ይታየኛል፤ መልካም ሥራ ነው፤ ልንለው እንችላለን፡፡ ይህ አቀራረብ ተገቢ ከመሆኑም ባሻገር ደኅንነታቸውንና ሰላማቸውን ይጠብቅላቸዋል፡፡

በአጠቃላይ  እንደ ምሁራኑ የጥናት ውጤት አንድ ሕፃን ሰው የሚያሰኙትን ልዩ ልዩ ባህርያት የሚቀዳጅበት የመጀመርያው ትምህርት ቤት ጨዋታ ነው፡፡ ስለሆነም ሕፃናት እንዲጫወቱ አመቺ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ጠቃሚ ነው፡፡ የጨዋታ ተፈጥሯዊ መብታቸውን መግፈፍ አግባብ አለመሆኑን ከወዲሁ መረዳት ይኖርብናል፡፡ እንኳንስ ሕፃናት አዋቂዎችም ይጫወታሉ፡፡ እየተጫወቱ ይማራሉ፡፡ የመስኩ ተመራማሪዎች ምንም ዓይነት የመጫወቻ መሣሪያና ሥፍራ እንዲሁም የመጫወት ዕድል የተነፈጋቸው ሕፃናት ግዑዝ ዕቃዎች ናቸው የሚለው አባባላቸው በቂ ማጠቃለያ ይሆናል ብዬ ተስፋ በማድረግ በቀጣይ መጣጥፌ የጨዋታ ዓይነቶችንና ጠቀሜታቸውን ይዤ እስከምንገኛኝ ድረስ ቸር እንሰንብት እያልኩ እሰናበታለሁ፡፡ መልካም መልካሙን ለሕፃናት!

ከአዘጋጁ፡- መምህር ሳህሉ ባዬ ዓለሙ፣ የሕፃናት አስተዳደግ ስፔሻሊስትና ፕሮጀክት ማናጀር ሲሆኑ፣ በትምህርት ዝግጅታቸው፣ ‹‹MA in Chid Development, BA in Psychology, MBA & IDPM in Project Management›› አግኝተዋል፡፡  ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] and/or [email protected]/ www.enrichmentcenters.org  ማግኘት ይቻላል፡፡

የነገውን ሰው ማነፅ - ይድረስ ለወላጆችና መምህራን
በመምህር ሳህሉ ባዬ ዓለሙ