Skip to main content
x

የሳምንቱ ገጠመኝ

መሰንበቻውን ከማያቸውና ከምሰማቸው የቃረምኳቸውን ገጠመኞቼን ልንገራችሁ፡፡ በአንዱ ቀን ጠዋት ከቤቴ ወጥቼ አረንጓዴና ቢጫ ቀለም ያለው ሊፋን ታክሲ ተኮናትሬ ወደ ጦር ኃይሎች አካባቢ እሄዳለሁ፡፡ ዕለቱ የእረፍት ቀን ስለነበር ወደዚያ አካባቢ የሄድኩት አንድ የታመመ ወዳጄን ለመጠየቅ ነበር፡፡ ዋቢ ሸበሌ ሆቴልን በማለፍ ላይ እያለን በሬዲዮ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች ተጣልተው የውኃ ፕላስቲክ መወራወራቸውን የስፖርት ጋዜጠኞች ያወራሉ፡፡ ነገሩ ገርሞኝ አንድ ለፌዴሬሽኑ ቅርብ የሆነ የማውቀው ሰው ዘንድ ስደውል እሱም አረጋገጠልኝ፡፡ ኳስ ያላደገበት አገር ውስጥ ስቴዲየም ተረብሾ የሰው አካል ሲጎዳና ንብረት ሲወድም በቅርቡ ዓይተናል፡፡ አሁን ደግሞ እግር ኳሱን ካለበት አረንቋ ውስጥ ማውጣት የተሳናቸው ወይም ችሎታው የሌላቸው ሰዎች ሲደባደቡ እንሰማለን፡፡ ይህንን ጉዳይ አንስተን ከታክሲው አሽከርካሪ ጋር ስናወራ፣ ‹‹ጋሼ ያልበሰሉት ወጣቶች መደባደባቸው አይገርመኝም፡፡ እኔ የሚገርመኝ ላይበስሉ ማገዶ የሚፈጁት ናቸው፤›› ሲለኝ ጦር ኃይሎች ደርሼ ተለያየን፡፡

የታመመው ወዳጄ ቤት ደርሼ ስለሕመሙና ሕክምናው ስንወያይ አንዲት ጠያቂ መጣች፡፡ በ30ዎቹ ዕድሜ መጀመርያ ላይ የምትገኝ ቆንጆ ወጣት ተቀላቅላን ወሬ ጀመርን፡፡ የባጡን የቆጡን ስናወራ ቆይተን ወጣቷ፣ ‹‹እኔ እዚህ አገር ምን እየገረመኝ እንደመጣ ታውቃላችሁ?›› በማለት ያልጠበቅኩትን ጥያቄ አቀረበች፡፡ የምትናገረው አጓጉቶኝ ነው መሰል፣ ‹‹እስኪ ንገሪና?›› አልኳት፡፡ ‹‹ይኼውላችሁ በቀደም ማታ አንዱ ስልክ ደወለልኝ፡፡ አንድ አሪፍ ቢዝነስ ልንጀምር ስለሆነ ገንዘብ አዘጋጂ፡፡ በአጭር ቀናት ውስጥ ያዋጣሽውን እጥፍ ታገኛለሽ. . . እያለ ሲያማልለኝ አመሸ፡፡ ምን ያህል እንደማዋጣ ስጠይቀው 500 ሺሕ ብር አለኝ፡፡ በቀናት ውስጥ አንድ ሚሊዮን እንደምቆጥር በኩራት ነገረኝ፡፡ ላስብበት ብዬው ስልኩ ተቋረጠ፡፡ በጠዋት ደውሎም ፈጠን በይ እንዳያመልጥሽ አለኝ፡፡ ግራ ገባኝ፡፡ የምሣ ሰዓት ደርሶ ከጓደኞቼ ጋር ምሳ እየበላን ሳለ ወንድሜ ደወለልኝ፡፡ ‹ሰማሽ ወይ?› ሲለኝ ‹ምኑን?› አልኩት፡፡ ለካ ያ ሰው ቀደም ሲል ተቀብሎ ያቀለጣቸው ሰዎች ረፋድ ላይ በፖሊስ አስይዘውታል. . .›› ብላ ስትስቅ አብረናት ሳቅን፡፡

ሳቋን ከጨረሰች በኋላ፣ ‹‹እኔ ገንዘቡን እንደማልሰጠው ለራሴ ቃል ገብቻለሁ፡፡ ላስብበት ያልኩትም አውቄ ነው፡፡ በጣም የገረመኝ ግን ይህ ዝንጥ ያለና አንደበተ ርዕቱ ልክ እንደኔ እያግባባ ወደ አምስት ሚሊዮን ብር ከሌሎች ተቀብሎ ተሰውሮባቸዋል፡፡ የእሱን መያዝ የሰሙ አራት ያህል ሰዎችም እንዲሁ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ መበላታቸውን ማመልከታቸውን ሰምቻለሁ፡፡ ይኼ የምላችሁ ሰው ተናግሮ በማሳመንና ራሱ ላይ ኢንቨስት በማድረግ በሚለብሳቸው ውድ ልብሶችና መጫሚያዎች የታወቀ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ከመንግሥት ባለሥልጣናትና ከታዋቂ ባለሀብቶች ጋር እንደሚገናኝና በርካታ ጉዳዮችን እንደሚያስፈጽም ይነገርለታል፡፡ ለዚህ ሲባል ደግሞ የሠራውንና ያልሠራውን እያጋነኑ የሚያስወሩለት ብዙ ጀሌዎች አሉት፡፡ አሁን አሁን ስሰማ ይኼ ሰው ያላጭበረበረው የለም፡፡ በጣም የሚገርመው ለገንዘብ የሚንገበገቡ ሰዎች የእዚህ አደገኛ ሌባ ሰለባዎች መሆናቸው ነው፡፡ እጥፍ ታገኛላችሁ ሲባሉ ይዘረግፉለታል. . . ምድረ ንፋስ አመጣሽ ራስ ወዳድ ሁሉ. . .›› ብላ ንግግሯን ስትቋጭ እየተገረምኩ ከማዳመጥ ውጪ ምንም ማለት አልቻልኩም ነበር፡፡

ባለፈው ሰሞን ደግሞ ምሽት አካባቢ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ቢራ እየጠጣን ስንጫወት ሌላ ጓደኛዬ ደውሎ፣ ‹‹አንተ ሰማህ እንዴ?›› አለኝ፡፡ ምንድነው የምሰማው በማለት ‹‹ምኑን?›› አልኩት፡፡ ‹‹አንዱ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራር ያለውን ነዋ፤›› ሲለኝ፣ ‹‹ኧረ እባክህ ንገረኝ?›› ማለት፡፡ ያላንዳች ኃፍረት የሚቀጥለው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ጉባዔ መቐለ ቢካሄድ ቆንጆ ቆንጆ ሴቶች አሉላችሁ ስለማለቱ ነበር የነገረኝ፡፡ መቼም ሥነ ምግባርና ይሉኝታ ባለበት አገር ውስጥ ይህንን ዓይነቱን ጉድ ከአንድ ትልቅ ሰው በአደባባይ መስማት በእጅጉ ያሳፍራል፡፡ ግለሰቡ በይፋ ይቅርታ ጠየቀ መባሉንም ሰምቻለሁ፡፡ ይቅርታ መጠየቅ ደግ ነው፡፡ ‹‹የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም›› የሚባለውን የአበው ምሳሌ ለሚያስብ ሰው ግን ነገሩ ከባድ ነው፡፡ ከገዛ ቤተሰብ ጀምሮ እስከ ማኅበረሰቡ ድረስ ጥቁር ጠባሳ ይጥላል፡፡ የሆነስ ሆነና ይቅርታ ከመጠየቅ ባለፈ ተግሳፅ ወይም ቅጣት የለም ወይ? የሕግ ዓላማ ማስተማር እንደመሆኑ መጠን፣ ለአጥፊውም ሆነ ለሌላው ማስተማሪያ የሚሆን ነገር ካልታየ፣ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› መሆን አይቀርም፡፡ ‹‹ምነው በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ›› ያለው ሌባ በልጀነቱ እናቱ ብትቀጣው ኖሮ፣ ሲያድግ በረት ዘርጣጭ አይሆንም ነበር፡፡ የሚገባው ይግባው፡፡

ከቀናት በፊት ከቦሌ መድኃኔዓለም ወደ አትላስ በእግሬ ስጓዝ፣ ሁለት ወጣት ሴቶች አስቆሙኝ፡፡ ምክንያታቸው የአንድ ኩባንያ አክሲዮን እንድገዛ ሊያግባቡኝ ነው፡፡ ይህ በምሥረታ ላይ ያለ ኩባንያ ሆስፒታል መሰለኝ፡፡ እኔ ደግሞ ከባንክ ውጪ አክሲዮን መግዛት ስለማልፈልግ ይቅርብኝ አልኩኝ፡፡ አንዷ ጥላኝ ስትሄድ አንደኛዋ ለማግባባት ሙከራዋን ጀመረች፡፡ ከመሥራች አባልነት የሚገኝ ዳጎስ ያለ ጥቅም እንዳለ ከሽያጭ ልምዷ በመነሳት ልታስረዳኝ ብዙ ለፈለፈች፡፡ እኔ ደግሞ እንደ ብሔራዊ ባንክ ያለ ብርቱ ተቆጣጣሪ የሌለበት ኢቨስትመንት ላይ ገንዘቤን ማውጣት እንደማልፈልግ፣ ከተቻለ አክሲዮን የሚሸጥ ባንክ ካለ ጠቀም ያለ ገንዘብ እንደማወጣና ጥሩ ኮሚሽን እንደምከፍላት ነግሬያት ልገላገላት ብሞክር አልተበገረችም፡፡ በስንት መከራ እንደማልፈልግ አስረድቼ ስገላገላት፣ ከኋላችን ታዘግም የነበረች አንዲት ቆፍጠን ያለች ወጣት ራመድ ራመድ ብላ መጥታ፣ ‹‹ሃይ›› አለችኝ፡፡ በመገረም እያየኋት፣ ‹‹እንተዋወቃለን?›› ከማለቴ፣ ‹‹ባንተዋወቅም ዛሬ መተዋወቅ እንችላለን እኮ?›› አለችኝ፡፡ ፋታ ሳትሰጠኝ፣ ‹‹የባንክ አክሲዮን የምትገዛበትን ለምን አብረን አንሠራበትም?›› ብላኝ ቢዝነስ ካርድ ከቦርሳዋ አውጥታ ሰጥታኝ እንድ ደውልላት ከነገረችኝ በኋላ በፍጥነት ሄደች፡፡

ለምን አብረን አንሠራም? ልጅቷ ሲያዩዋት ዘናጭና ቀልጣፋ ትመስላለች፡፡ በዚያ ላይ የሚያምረው የቢዝነስ ካርዷ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች የምትሳተፍ መሆኗን ይናገራል፡፡ ከዚህች ጋር አብሮ መሥራትማ ያስፈልጋል እያልኩ ሳስብ የሆነ ነገር አዕምሮዬን ጠቅ አደረገኝ፡፡ ባለፈው ሰሞን ታሞ ልጠይቀው የሄድኩት ወዳጄ ዘንድ  ደውዬ የእዚያችን ቆንጆ ልጅ ስልክ እንዲሰጠኝ ነገርኩት፡፡ የፈለግኳት ለሌላ ነገር እንዳይመስለው ብዬ ምክንያቴን አስረዳሁት፡፡ እሱም ሰጠኝ፡፡ ወዲያው ደውዬ የገጠመኝን ነገርኳት፡፡ እሷም ቦታውን ስትጠይቀኝ ያለሁበትን ጠቆምኳት፡፡ ‹‹መጣሁ!›› ብላ እንድጠብቃት ነገረችኝ፡፡ ከሃያ ደቂቃዎች በኋላ ደረሰች፡፡ እሷ መኪና ውስጥ ሆነን ለአዲሷ ‹ሸሪኬ› ደወልኩላት፡፡ የእኔ በፍጥነት መደወል ግራ አጋባት መሰለኝ የተለያዩ ጥያቄዎች አቀረበችልኝ፡፡ መለስኩላት፡፡ የት እንዳለሁ ጠየቀችኝ፡፡ የቅድሙ ቦታ ላይ ነኝ አልኳት፡፡ እሷም ‹‹መጣሁ!›› ብላ ስልኳን ዘጋች፡፡ ከአምስት ደቂቃ በኋላ ደውላ፣ ‹‹የቱ ጋ ነህ?›› ስትለኝ፣ ጥቁር ሰማያዊ ኮሮላ ውስጥ መሆኔን ስነግራት፣ ‹‹እሺ መጣሁ!›› ብላ ስልኳን ዘጋች፡፡ ብንጠብቅ፣ ብንጠብቅ፣ ብንጠብቅ አንድ ሰዓት አለፈ፡፡ ሰላሳ ደቂቃ ጨመርን ወፍ የለም፡፡ ይህች ብልጥ ልጅ ግን ገባት፡፡ እሷን የምታውቅ ሌባ እንደምትሆን ነገረችኝ፡፡ ገርሞኝ እንዴት ልትጠረጥር እንደቻለች ስጠይቃት፣ ‹‹መኪናዬን ስታይ ብን ብላ ጠፍታ ነው፡፡ ይኼኔ የዚያ ሌባ  ምልምል ትሆናች. . .›› ብላ ተንከትክታ ስትስቅ፣ እኔ ደግሞ አገሩ የእነ አምታታው በከተማ ሆነ ወይ እያልኩ ነበር፡፡

(ደ.መ.፣ ከሳልኮስት)