Skip to main content
x
የ359ኛው ቀን ጎርፍ

የ359ኛው ቀን ጎርፍ

የዓመቱ 359ኛ ቀን ዓመቱ ሊያበቃ 6 ቀን በቀረበት ነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በአብዛኞቹ የአዲስ አበባ አካባቢዎች በእኩለ ቀን (ስድስት ሰዓት ግድም) አካባቢ ጀምሮ የጣለው ከባድ ዝናብ የአዲስ አበባን ጎዳናዎች በጎርፍ እንዲጥለቀለቁ አድርጓል፡፡ ለወትሮው ፀዳ ያሉና ጎርፍ ቢመጣም በዋና ጎዳናቸው ላይ አይተኛባቸውም በሚባሉ ጎዳናዎችም ጎርፍ ተንጣሎ ታይቷል፡፡ ከቦሌ መገናኛ፣ ከመገናኛ በሲግናል ካዛንችስ፣ ከቦሌ በአፍሪካ ጎዳና መስቀል አደባባይ፣ ከቦሌ መድኃኔዓለም በአትላስ ዑራኤል፣ ከቦሌ መሰናዶ ትምህርት ቤት ወደ አክሱም ሆቴል እንዲሁም ኃይሌ ገብረሥላሴ ጎዳና የሚያስወጡ መንገዶች፣ ብሔራዊ ሆነ ስታዲየም በአብዛኞቹ ቦታዎች በጎርፉ ሳቢያ በመኪና ተጨናንቀው ነበር፡፡ እንኳን እንዲህ ከባድ ዝናብ ጥሎ፣ ጠብ እንኳን ሲል በመኪና የሚተሳሰሩት የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ከጎርፉ ጋር ተደምሮ የትራፊክ መጨናነቅም ተስተውሎባቸዋል፡፡

ከተማዋ የረባ የፍሳሽ ማስወገጃ ባይኖራትም፣ አሉ የሚባሉትም በግንባታ ሰበብ ከጥቅም ውጪ ሆነዋል፡፡ ከግንባታ ቁፋሮና ነዋሪው በቆሻሻ ከሚደፍናቸው ያመለጡ ጥቂት የፍሳሽ ማስወገጃዎችም፣ በየሥፍራው ገርበብ ባለው ክዳናቸው መጥፎ ጠረን የቀላቀለውን ጎርፍ ሲያስተነፍሱም ነበር፡፡ ከእነዚህ አንዱ ከቦሌ ወደ ወሎ ሠፈር ሲጓዙ ከአትላስ የሚመጣውን ‹‹ፍላይ ኦቨር›› አለፍ ብሎ ከሚገኘው ድልድይ በላይ የሚታየው ከየሕንፃዎች የሚወጣ ፍሳሽ አንዱ ነው፡፡ ከዚህ የፍሳሽ ቱቦ በአናቱ የሚወጣው ጠረን ያለው ፈሳሽ ለእግረኛውም ሆነ ለማንም የሚመች ባይሆንም የዘንድሮው ክረምት ከጀመረ ወዲህ በዘነበ ቁጥር ሲገነፍል ይታያል፡፡

በዕለቱ ጎርፍ በዋና መንገዶች ብቻ ሳይሆን የገበያ ሥፍራዎችንም ያጥለቀለቀ ነበር፡፡ ከየገበያ ሥፍራ ቆሻሻውን እያጥረገረገ ሲወጣም ተስተውሏል፡፡ ቆልቆል ያሉ የኮብል ስቶን መንገዶችም መንገድ ሳይሆን የፍሳሽ መተላለፊያ እስኪመስሉ ጎርፉን አስተናግደዋል፡፡ በመጪዎቹ አሥር ቀናት አዲስ አበባን ጨምሮ አብዛኞቹ የአገሪቱ ክፍሎች ከባድ ዝናብ እንደሚያስተናግዱም ተነግሯል፡፡ ቀድሞውንም ያልተሳለጠ የፍሳሽ ማስወገጃ ላላት አዲስ አበባ ዝናቡን ቀላሉን ያድርግልሽ ከማለት ውጪ ምን ማለት ይቻላል?

* * *

በል ንፈስ በል ንፈስ አንተ ሞገደኛ የክረምት ወጨፎ

በል ንፈስ፤ በል ንፈስ፤ አንተ ሞገደኛ፤ የክረምት ወጨፎ

ምንም እንኳን ባትሆን የዚያን ያህል ክፉ

ምስጋና እንደካደ እንደሰው ልጅ ጥፉ፡

እስተዚህም ባይሆን የጥርስህ ስለቱ፤

ሆኖም ብትሰወር ምንም በትታይ፤

ስትንፋስህ ጭምር ባልጎ የለም ወይ፡፡

ሆያ ሆዬ በሉ! ሆያ ሆዬ በሉ!

ለዛፍ ለቅጠሉ፣

የሸፍጥ ከሆነ አብዛኛው ሽርክና፤

አብዛኛው ፍቅርም ተራ ድንቁርና፤

ለዛፍ ለቅጠሉ፤ ሆያ ሆዬ በሏ!

የዚች ዓለም ኑሮ፤ አቤት መጣፈጧ፤

ከዊሊያም ሼክስፒር/ ስድ ትርጉም በዳዊት ዘኪሮስ

* * *

ጳጉሜን 3  እና የልጅነት ትዝታዬ!

በመላኩ አላምረው

በየዓመቱ ጳጉሜን 3 (ሩፋኤል) ሲሆን ከጓደኞቼ ጋር በጠዋቱ እንነሳለን፡፡ ከእኛ ቤት ፊት ለፊት ካለው ለምለም ሳር እንሰባሰባለን፡፡ ሰማይ ሰማዩን እናያለን፡፡ ከሰማይ የምንጠብቀው ከዝናብ ጋር የሚወርድ በረከት ስላለ በዚህ ቀን ዝናብ አልዘነበም ማለት… በቃ ዕድለ ቢስነት ነው፡፡ የሩፋኤል ጠበል በቀጥታ ከሰማይ የሚወርድበት ቀን ነዋ፡፡ ስንሰማ ያደግነውና ታላላቆቻችንም ሲያደርጉት ያየነው በዚህ ቀን ዝናብ ሲዘንብ እራቁት ሆኖ በደስታ እዘለሉ መጠመቅ ነው፡፡ ሰማያዊ የበረከት ጥምቀት… እንዴት ደስ ይል ነበር፤ ዝናቡ ሲዘገይ ይህንን ግጥም በዝማሬ እንጫወት ነበር፡-

ዝናቡ ናና ናና

ታዝለህ በጳጉሜን ደመና

ሩፋኤል ናና ናና

አዝዘው ይህን ደመና

ካፊያ ክፍክፍ… ክፍክፍ

ከሰማይ ደጅ በረከት አርግፍ

ዝናብ ዱብዱብ… ዱብዱብ

ለነፍሳችን ጽድቅ ለሥጋ ምግብ፡፡

ዝናቡ እስኪመጣ እያረፍንም ቢሆን እንዘምራለን… እንጨፍራለን… እንቦርቃለን፡፡ ልክ ዝናቡ እንደመጣ (ገና ማንጠባጠብ ሲጀምር) ልብሳችንን ለማውለቅ እንጣደፋለን፡፡ ባዶ መለመላችንን… ምንም ዓይነት ልብስ መልበስ ከበረከቱ የሚቀንስብን ስለሚመስለን ውልቅልቅ… አይ ልጅነት! ማፈር የለ… መኩራት የለ… በቃ ለበረከት መጣደፍ ብቻ፡፡ ታዲያ ዝናቡ ቀላልም ይሁን ከባድ ጉዳያችን አልነበረም፡፡ በዝናቡ መሐል እየዘለልን…

ሩፋኤል ገደፋዬ

እንደማዬ እንዳባዬ

ትልቅ ልሁን አሳድገኝ

ከክፉ ሁል - ታደገኝ

ጠበልህን ተጠመቅሁት

ዝናብ ሆኖ አገኘሁት

በጳጉሜን ወር ዓመቱ ሲያልቅ

በረከትህን ስንጠብቅ

ይኸው ሰማይ ተከፍቶልን

በረከትህ ወረደልን

የዛሬ ዓመት በዚች ቀን

እንመጣለን ልብስ አውልቀን….

* * *