Skip to main content
x
‹‹አሁን የምንፈልገው የሰዎችን አመለካከት የሚቀይር ሐሳብ ማውረድ ነው››

‹‹አሁን የምንፈልገው የሰዎችን አመለካከት የሚቀይር ሐሳብ ማውረድ ነው››

ዶ/ር ዳዊት ወንድማገኝ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር

ዶ/ር ዳዊት ወንድማገኝ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን በወጣትነታቸው የተቀላቀሉት ለሕክምና ትምህርት  ነው፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ ከትምህርት በኋላም በሥራ እያገለገሉበት ያለውን ሆስፒታል የኖርኩበት ቤቴ ነው ሲሉ ይገልጹታል፡፡ ካለፉት አምስት ወራት ወዲህም የሆስፒታሉ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ሆነዋል፡፡ በሆስፒታሉ የሚታዩ የአሠራር ችግሮችን ለመቅረፍ ከሥራ ባልደረቦቻቸውና ከወጣት የሆስፒታሉ ማኅበረሰብ ጋር በመሆን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ እንደ አንድ መፍትሔም ወጣቶችን የችግሩ ፈቺ ለማድረግ የሚያስችልና ለአንድ ዓመት የሚቆይ የወጣቶች አመራር ሥልጠና ባለፈው ሳምንት ተጀምሯል፡፡ በዚህና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ምሕረት ሞገስ ከዶ/ር ዳዊት ወንድማገኝ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡

ሪፖርተር፡- በአስተዳደር ሥራ መሳተፍ ከጀመሩ አምስት ወራት አስቆጥረዋል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ከዚህ ቀደም ከሚያውቁት የተለየ ምን አስተውለዋል?

ዶ/ር ዳዊት፡- ጥቁር አንበሳ የተማርኩበትና የምሠራበት ነው፡፡ ከ16 ዓመቴ ጀምሮ ቤቴ ነው፡፡ ወደ ማኔጅመንቱ ስመጣ የተለየ ነገር ያየሁት በሆስፒታሉ ብዙ ነገር ሊስተካከል እንደሚችል ነው፡፡ አሁን ካለው በጣም በተሻለ አገልግሎት መስጠት የምንችል ተቋም እንደሆንን፣ የምንሰጠው አገልግሎት ውስጡ እንኳን ሆነን በተለየ መልክ ሳንረዳው በጣም ግዙፍ እንደሆነና ቀላል የማይባል አገራዊ ፋይዳ ያለው ተቋም እንደሆነ ገብቶኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ከታዳጊ ወጣትነትዎ ጀምሮ እያዩት በመጡት ጥቁር አንበሳ ብናሻሽላቸው የሚሏቸው ችግሮች ምንድናቸው?

ዶ/ር ዳዊት፡- በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አራት ትምህርት ቤቶች ማለትም የሕክምና ትምህርት ቤት፣ የማኅበረሰብ ጤና ትምህርት ቤት፣ የነርሶች፣ የአዋላጅ ነርሶችና የላቦራቶሪ ትምህርት ቤት እንዲሁም የፋርማሲ ትምህርት ቤት አሉ፡፡ በተጨማሪም ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አለ፡፡ አንዳንዶቹ ትምህርት ቤቶች በፊት በሕክምና ትምህርት ቤት ሥር ሆነው አሁን እንደ አዲስ የመጡ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሲሆን የተቀላቀሉ ናቸው፡፡ ቀድሞ ራሳቸውን ችለው የተቋቋሙ ተቋማት ነበሩ፡፡ ለምሳሌ እኔ ጥቁር አንበሳን መጀመርያ ሳውቀው አንድ የሕክምና ትምህርት ቤት ነበር፡፡ የተሻለ የአገልግሎት መሳለጥም ነበረው፡፡ አሁን ግን እነዚህን ትምህርት ቤቶችና በርካታ ባለሙያዎችን ይዟል፡፡ በከፍተኛ ልህቀት የተማሩ ባለሙያዎችም በየትምህርት ቤቱ አሉ፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋ የፋርማሲ ትምህርት ቤት አለው፡፡ ፋርማሲያችን የዕድሜውን ያህል የሚመጥን አገልግሎት ይሰጣል ወይ? ብንል እየሰጠ አይደለም፡፡ በጣም የተሻለ የፋርማሲ አገልግሎት መስጠት እንችላለን፡፡ ስለዚህ ትምህርት ቤቱን ለብቻ ፋርማሲውን ለብቻ አድርገን ሁለቱ የተለያየ ነገር እየሠሩ በቂ አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ማድረስ ከባድ ነው፡፡ ሰዎች ስለመድኃኒት ያላቸው ዕውቀት ምን ያህል ጨምሯል? ብንል መሻሻሎች ቢኖሩም ጉድለቶች አሉ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ብዙ መድኃኒት በየዓመቱ ይባክንብናል፡፡ በመድኃኒት አገዛዝና አወጣጥ ሥርዓት ላይ ያለን ዕውቀትና ዕቅድ ደካማ በመሆኑ ብዙ ሚሊዮን ብር አውጥተን የገዛናቸው መድኃኒቶች ይከስሩብናል፡፡ አንጋፋ የፋርማሲ ትምህርት ቤት ይዘን ይህ ሊሆን የሚገባው አይደለም፡፡ ትልቅ የላቦራቶሪ ችግር አለ ይባላል፡፡ ሕሙማን ከግቢ ውጪ ላቦራቶሪ አሠርታችሁ ኑ ይባላሉ፡፡ ሆኖም በርካታ ላቦራቶሪዎች፣ ትምህርት ቤትና ባለሙያዎች አሉ፡፡ የምንሰጠው አገልግሎት ግን ማንኛውም ላቦራቶሪ የሚሰጠውን አገልግሎት ዓይነት ነው፡፡ ይህ ደካማነት ነው፡፡ መሠረታዊው ችግር ያለመቀናጀት ነው፡፡ ስለዚህ ሥራውን አቀናጅተን መሥራት ያስፈልገናል፡፡ ትምህርቱን፣ ምርምሩንና አገልግሎቱን ወደ አንድ ማምጣት አለብን፡፡ ዋናው ዓላማችን የምንሠራበትን ሆስፒታል አሁን ካለው የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ማስቻል ነው፡፡  ቁeza

eseru

 

ሪፖርተር፡- ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን እንዳየነውም ሆነ ታካሚዎች እንደሚሉት ከጥበቃ ጀምሮ ችግሮች አሉበት፡፡ አገልግሎቱ ላይም ቅሬታ ይሰማል፡፡ ይህንን ለመቀየር ‹‹ሊደርሽፕ ኢንሽየቲቭ ፎር ያንግ ፋኩልቲ›› በሚል ወጣት የሆስፒታሉ ማኅበረሰብ አባላት የመሪነቱን ሚና እንዲጫወቱ የሚያስችል የአንድ ዓመት ሥልጠና ተጀምሯል፡፡ ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ዳዊት፡- በሥልጠናው የሚሳተፉት 15 ወጣት የሆስፒታሉ ሠራተኞች በሆስፒታሉ የሚታየውን ችግር ባንዴ ይለውጡታል ብለን አናስብም፡፡ ለኮሌጁ ማኅበረሰብ ልናስተላልፍ የምንፈልገው መልዕክት እያንዳንዱ ሰው በሚሠራበት ቦታ ኃላፊ መሆኑን ነው፡፡ ለምሳሌ ጥበቃ ለሥራው ኃላፊ ነው፡፡ ጥቁር አንበሳ ሊታከም የሚመጣ ሰው የታመመና የጨነቀው መሆኑን ተረድቶ በአግባቡ ሊያስተናገድ ይገባል፡፡ ይህ የማይሆንባቸው አጋጣሚዎች ግን አሉ፡፡ ስለዚህ የጥበቃ ሠራተኞች ይህንን በምን እናሻሽለው? ብለው እንዲያቅዱ ነው የምንፈልገው፡፡ 15ቱ ወጣቶች በአንድ ዓመት ሠልጥነው ችግሩን ይፈቱታል የሚል አካሄድ የለንም፡፡ በእያንዳንዱ የትምህርት ክፍል ውስጥ ሁሉም ሰው አንድ አንድ ኃላፊነት እንዲወስድ እንፈልጋለን፡፡ ለምሳሌ የኛ ማኔጅመንት ቢሮ ያለበት ቦታ ወደ አራት ዳይሬክተሮች አሉ፡፡ እያንዳንዳችን አንድ ወይም ሁለት ጸሐፊ አለን፡፡ እያንዳንዳችን ትልልቅ ማተሚያ (ፕሪንተር)፣ ፎቶኮፒ ማሽኖች አሉን፡፡ ነገር ግን እዚያ ኮሪደር ላይ ያለነው በሙሉ በአንድ ፕሪንተርና ፎቶኮፒ ማሽን ልንሠራ እንችላለን፡፡ ይህን ማምጣት እንፈልጋለን፡፡ በያለንበት ቦታ ብክነትን እንዴት እንቀንሳለን? የአገልግሎት ጥራት እንዴት እንጨምራለን? የሚለውን ማምጣት እንፈልጋለን፡፡ ጥቁር አንበሳ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ሰው የት እንደሚሄድ አያውቅም፡፡ በቂ መረጃ የሚያገኝበትን መንገድ መፍጠር እንችላለን፡፡ 8,000 ያህል ተማሪዎች በግቢው አሉ፡፡ ከመማራቸው ጎን ለጎን ግቢው ውስጥ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ፡፡ እነሱን ልንጠቀምባቸው እንችላለን፡፡ ተማሪዎችን አገልግሎት በመስጠቱ ረገድ በምን መልኩ እንጠቀምባቸው? ለሕመምተኛ እንዴት አገልግሎት መስጠት ይችላሉ? የሚለውን መንገድ በማሳየት፣ አገልግሎት ወደሚያገኙበት በማድረስ፣ የደከመውን በመደገፍና በሌሎችም በተለያየ መንገድ ወደ ሆስፒታሉ የሚመጣውን ማኅበረሰብ የሚረዱበትን መንገድ ማመቻቸት እንፈልጋለን፡፡ ከሆስፒታሉ ውጭ በዙሪያችን ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ያሉ ወጣቶች ምን ዓይነት ማኅበራዊ በጎ አድራጎት ሊሰጡ ይችላሉ? ብለን አስበናል፡፡ ሐሳባችንን ወደ መሬት በማውረድ በግቢያችን ያለውን ችግር ለማቃለል ጭምር ነው የተነሳነው፡፡ ሠልጣኞቹ ይህን ማሻሻል እፈልጋለሁ ብለው የሚያመጡትን ሐሳብ እኛ ደግፈን ወደ ተግባር በመለወጥ ለውጥ ማምጣት እንፈልጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በ15ቱ ወጣቶች በአንዴ ለውጥ እንደማይመጣ እሙን ነው፡፡ እነሱ ያሰቡትን ውጥንም ካለው የሥራ ስፋት አንፃር ማውረዱ ቀላል አይሆንም፡፡ ከዚህ ቀደም የተለመደውን አሠራር መቀየርም እንዲሁ፡፡ ለዚህ ሲባል በሆስፒታሉ አዲስ የአሠራር መዋቅር ይዘረጋል ማለት ነው?

ዶ/ር ዳዊት፡- አዲስ የሚመጣ መዋቅር አይኖርም፡፡ ወደ ታች የምናወርደውም ሐሳብ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሠራተኛ የሐሳብ ለውጥ እንዲያመጣ ብቻ ነው የምንሠራው፡፡ የምንፈልገው ለውጥ ለምሳሌ ጥበቃ አካባቢ ቢሆን፣ ጥበቃ ላይ የሚሠራ ሰው ለራሱና ለተቋሙ ለሚሰጠው አገልግሎት ያለው አመለካከት ግልጽ እንዲሆንለት ማድረግ ነው፡፡ ይህ የማኔጅመንት ተቀባይነትም አለው ማለት ነው፡፡ ሕመምተኛውን በር ላይ በአግባቡ አነጋግሮና ተንከባክቦ ካላስገባው በኋላ ቢታከምም ከፍቶት ነው የሚወጣው፡፡ ይህንን ሐሳብ ጥበቃዎች እንዲረዱት እንፈልጋለን፡፡ የታቀደ፣ በፕላን ያለና በአምስት ዓመቱ ስትራቴጂክ ፕላናችን የተቀመጠው ወደ ታች ይወርዳል፡፡ ለዚህም ነው በዓመት 500 ሺሕ ሰው የምናክመው፡፡ ነገር ግን በዚህ የሚወርደው አሠራር ነው፡፡ አሁን የምንፈልገው የሰዎችን አመለካከት የሚቀይር ሐሳብ ማውረድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሐሳብ በማውረዱ ላይ ሥጋት የምትሉት ምንድነው?

ዶ/ር ዳዊት፡- ሥጋት ሁሌም አለ፡፡ ለምሳሌ በግቢው 3,000 ያህል ሠራተኞች አሉ፡፡ እነዚህ አንድ ዓይነት አመለካከት እንዲኖራቸው ማድረግ ረዥም ጊዜ ይፈጃል፡፡  ሥልጠና የጀመሩት 15 ልጆች ሲጨርሱ ሰርተፍኬት አያገኙም፡፡ ውስጣቸውን ነው የሚያሳድጉት፡፡ አንድን ችግር የመፍታት ክህሎት ነው የሚያዳብሩት፡፡ እነሱ ከሥራቸው አምስት አምስት ሰው ቢይዙ፤ ቀጥሎ ያለውም እንዲህ ቢያደርግ፤ የሐሳብ ለውጥ መጥቶ መልካም ሥራና አገልግሎት የሚሰጠው የግቢው ማኅበረሰብ እየበዛ ይሄዳል፡፡ ይህ ገንዘብ የምናወጣበት አሠራርም አይደለም፡፡ በሌላ በኩል የተቀባይነት ሥጋት አለን፡፡ ይህ ምን ዓይነት ሐሳብ ነው? የሚሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ለውጥ የሚመጣው በትንሽ ሰዎች ነው፡፡ ከ15 ተነስተን መቶ ሰው ያህል የመለወጥ ሐሳብን ከተቀበለውና ከተገበረው ሌላው ይለወጣል፡፡ አሁን እንኳን በጥቂት የተጀመረው ለውጥ ወደ ሌላውም እየሄደ መሆኑን ዓይተናል፡፡ የጀመርነው የሚሳካ ሐሳብ ነው፡፡ ምኞታችንም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ባሉን ኮሌጆች ይህ እንዲሆን ነው፡፡ አንድ አንድ ሰው በየቦታው ቢኖር፣ የእነዚህ ጥርቅም አሠራሮችን ይቀይራል፡፡ አብዛኛውም ሰው አንድ ሰው የሚያመጣውን ለውጥ የሚቀበል ነው፡፡ ተባባሪም ነው፡፡ መሪዎች ግን ይፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙ ጊዜ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሚተቸው ለታካሚዎች በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ነው፡፡ በሆስፒታሉ ብዙ ሠራተኞች አሉ ቢባልም ይህ ከተገልጋዩ አንፃር የሚመጣጠን አይደለም፡፡ ይህንን ለማስተካከል ምን ታስቧል?

ዶ/ር ዳዊት፡- ከኢትዮጵያ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አንፃር ሲታይ ሦስት ሺሕ ሠራተኞች በአንድ ቦታ መሥራታቸው ብዙ ያስብላል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንድ ሦስተኛው ድጋፍ ሰጪ አንድ ሦስተኛው በቴክኒክ በላቦራቶሪ፣ በነርስና በፋርማሲ አንድ ሦስተኛው ደግሞ በማስተማር፣ በምርምርና በአገልግሎት (ሕክምና) ላይ ያለ ነው፡፡ በከፍተኛ ደረጃ የሠለጠኑ የምንላቸው ቁጥራቸው አነስ ቢልም አገሪቷ ውስጥ ካለው አንፃር ሲታየ በጥቁር አንበሳ ብዙ ልሂቃን አሉ፡፡ በየደረጃው ከሌክቸረርነት ጀምሮ እስከ ፕሮፌሰር ደረጃ የተማሩ ሰዎችም አሉን፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ድኅረ ምረቃ ላይ ሦስት ሺሕ ተማሪዎች አሉን ብንል፣ እነዚህ ማለት ሐኪሞች ሆነው አገልግሎት መስጠት የሚችሉ፣ የተገደበና በተወሰነ ደረጃ መሥራት የሚችሉት ነገር ያላቸውና የሚያውቁ ናቸው፡፡ የውስጥ ደዌ ሕክምና ስፔሻሊስት ልሁን ብሎ የሚመጣ ትምህርቱን በነበረው ዕውቀት ላይ እየጨመረ ማከም የሚችል ነው፡፡ እነዚህ አገልግሎት የሚሰጡ ስለሆኑ አገልግሎት የሚሰጠው ሠራተኛ ቁጥር ሰፋ ያለ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን በዓመት ለሚመጣው 500 ሺሕ ሰው ይበቃል ማለት አይደለም፡፡ መለወጥ ከምንፈልጋቸው ነገሮች አንዱ መግቢያ እንጂ መውጫ ለሌለው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መውጫ ማበጀት ነው፡፡ ማንም ሰው ከአገሪቱ ዙሪያ ለሕክምና ጥቁር አንበሳ ይመጣል፡፡ ከታከመ በኋላ ተመልሶ የሚሄድበት የለውም፡፡ ተመልሶ የሚሄድበት የሌለው ሕመሙ እዚህ የሚያስቀረው ሆኖ ሳይሆን እዚህ መታከም ያለበት ሕመም ከዳነ በኋላ ተመልሶ ለመሄድ የሥርዓት ዝግጅቱነት ስለሚያስፈልግ ነው፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ ላይ ደረጃቸው ከጥቁር አንበሳ አነስ ያሉ ብዙ ሆስፒታሎች አሉ፡፡ በእነዚህ ውስጥ በርካታ ልሂቃን የሕክምና ባለሙያዎች አሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጤና ጣቢያዎች አሉ፡፡ ለማድረግ ያሰብነው ከጥቁር አንበሳ የመጀመሪያ ሕክምና የጨረሱ ሰዎች ለክትትል ሪፈር የሚደረጉበትን ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ አንድ ሰው በየሦስት ወሩ መድኃኒት ለማስፈረም ብቻ ጥቁር አንበሳ ይመጣል፡፡ መድኃኒት ለማግኘት ሥርዓት መዘርጋትና ቦታ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ ይህን ብናደርግ በጥቁር አንበሳ ካለው መጨናነቅ ሁለት ሦስተኛውን መቀነስ እንችላለን፡፡ አሁን በአንደኛ ደረጃ ላሉም ሆነ በሦስተኛ ደረጃ ላሉ ሕሙማን አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ መስጠት የሚጠበቅብን ግን ከፍተኛውን አገልግሎት ነበር፡፡ ይህ መሠረታዊ ችግር ነው፡፡ ከሚመጣው ሰው አብዛኛው ጥቁር አንበሳ መታከም የማያስፈልገው ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ሌላ ቦታ ለማይሠራ ከባድ ቀዶ ሕክምና ጥቁር አንበሳ ይመጣል፡፡ ቀዶ ሕክምናው ከተሠራ በኋላ ለምሳሌ ስኳር ወይም ደም ግፊት ቢኖር ጤና ጣቢያ መሄድ እየተቻለ ተመልሶ ጥቁር አንበሳ ይመጣል፡፡ ለምን ጤና ጣቢያ አልሄደም ሲባል? ጤና ጣቢያ ምናልባት መድኃኒት ወይ ባለሙያ ወይ ችሎታ የለም፡፡  የኛ ደግሞ ትልቅ የትምህርት ተቋም ነው፡፡ ስለዚህ በጤና ጣቢያዎች ያሉትን ባለሙያዎች ማሠልጠንና ማስተማር እንችላለን፡፡ ይህንን ካደረግን እዚህ ከባድ ሕክምና ጨርሰው የወጡትን ለክትትል ሪፈር ማድረግ እንችላለን፡፡ የሐሳብ ለውጥ የምንለው ይህንን ነው፡፡ ከጤና ጥበቃና ከጤና ቢሮዎች ጋር መክረን ሕሙማን ጥቁር አንበሳ ታክመው ጨርሰው ለክትትል ሪፈር የሚደረጉበት ሥርዓት ለማዘጋጀት አስበናል፡፡