Skip to main content
x

የኮንግረንስ አባላቱ ጨዋታ አራምባና ቆቦ

በአርጋው ጥ.

ማኅበራዊ ሚዲያ አዲሱ የዓለማችን ክስተት ነው፡፡ የተለምዶ ሚዲያዎችን (ሬድዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ጋዜጣ፣ ወዘተ.) ታሪክ የሚሆኑበት ዕድል አለ፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያ ሁሉም ሰው ጋዜጠኛም፣ አርታኢም እንዲሆን ዕድል ፈጥሮለታል፡፡ በቅርቡ አሜሪካ ውስጥ የተካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው 23 በመቶ የሚሆኑ ወጣቶች አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ያልተገባ መረጃ በማኅበራዊ ሚዲያ ያስተላልፋሉ፡፡ አጀንዳ ይቀርፃሉ፣ ፖሊሲ ያስቀይራሉ፡፡ ሐሰተኛ ዜና (Fake News) አገሩን ይንጣል፡፡ በዚህ ውስጥ ከተነገረላቸው ጉዳዮች መካከል አንዳንድ የአሜሪካ የኮንግረንስ አባላት ያቀረቡት ኤችአር 128 የሚባለው የውሳኔ ሐሳብ ነው፡፡ አንዳንዶች ይኼንን የውሳኔ ሐሳብ በአሜሪካ የተላለፈ ያደርጉታል፡፡ ይሁን እንጅ ውሳኔው በኢትዮጵያና በአሜሪካ ግንኙነት ምን ተፅዕኖ አለው የሚለው መታየት ይገባዋል፡፡

የሁለቱ አገሮች ግንኙነት

የኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነት ትናንት የተጀመረ አይደለም፡፡ ዕድሜ ጠገብ ነው፡፡ የአገሪቱ ቱባ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል፡፡ ባራክ ሁሴን ኦባማ፣ ጆርጅ ደብሊው ቡሽ፣ ጀምስ ኤርል ካርተር፣ ሒላሪ ክሊንተን፣ ጆን ኬይሪ፣ ኮንዶሊዛ ራይስ፣ ማድሊን ኦልብራይት፣… ተጠቃሾች ናቸው፡፡

 

ሁለቱ አገሮች በዓለም አቀፍ የፀረ ሽብር ትግል (Counter Terrorism)፣ በአፍሪካ ቀንድ የፀጥታ ሁኔታና በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር፣ እንዲሁም በልማት፣ በመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ ለማስፈን በጋራ ይሠራሉ፡፡

ሁለቱ አገሮች በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት፣ በሰላምና በደኅንነት፣ እንዲሁም በኢኮኖሚ፣ በንግድና በፋይናንስ የሚመክሩባቸው መደበኛ መድረኮች አሏቸው፡፡ ለዚህም ንዑስ ቡድኖች (Three Working Groups) ተቋቁመው ሥራውን ያሳልጣሉ፡፡ ይኼ አሠራር ሁለቱ አገሮች ስለፈለጉት የሚካሄድ ነው።

በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ግንኙነቱን ለማሳደግ እንቅስቃሴዎች ይታያሉ፡፡ በተለይም በአሜሪካ ፖለቲካ ተፅዕኖ ካላቸው ከሴኔትና ከኮንግረንስ አባላት ጋር የሚደረገው ምክክር ከዚህ ቀደም ከነበረው ከፍ ብሏል፡፡ በጋራ ጉዳዮች ላይ ተደጋጋሚ ግንኙነቶችና ውይይቶች ይደረጋሉ፡፡

 

አሜሪካ ልበ ቡቡ ወይስ. . .

በዲፕሎማሲ የተለመደ ይትብሃል አለ፡፡ ‹‹ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅ የለም›› ይባላል፡፡ ሁለቱ አገሮች የሚፈላለጉት ለፅድቅ አይደለም፡፡ ለአገሮቹ አንዳች ጥቅም እስካገኘ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር ናት፡፡ እኛ የምንፈልጋትን ያህል አሜሪካ ትፈልጋታለች፡፡

በአደጉ አገሮች ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር፣ ሰብዓዊ መብት፣ ወዘተ የሚባሉት የጥቅም ማስጠበቂያ ቁማሮች እንጂ ለአንዱ አገር የሌላው አገር ሕዝብ አንጀቱን በልቶት አይደለም፡፡ በሺዎች ከሚቆጠር ማይል ርቀት ላይ ሆኖ ደረስኩልህ የሚለው የራሱ የሆነ የሒሳብ ቀመር ስላለው ነው፡፡

 

አሜሪካም እንደ ሌሎች መሰል አገሮች ጨዋታውን ትጋራዋለች፡፡ በቅርቡ ዶናልድ ትራምፕ በትረ ሥልጣናቸውን እንደያዙ የመጀመርያ ጉብኝታቸውን ያደረጉት ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ነው፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ የሰብዓዊ መብት ይገፈፍባታል፣ ዴሞክራሲው በበሯ አያልፍም ተብላ ወቀሳ የሚደርስባት አገር ነች፡፡ በሞት ቅጣት ላይ እጇ የማይሳሳው ሳዑዲ ዓረቢያ፣ እንደ ኦሳማ ቢን ላደን ዓይነቶቹ ቱጃር አሸባሪዎች የሚፈልቁባት ናት፡፡ ይሁን እንጂ ሳዑዲ ዓረቢያ የአሜሪካ ሁነኛ ሸሪክ ናት፡፡

የአገሮች ግንኙነት የሚወሰነው በሰብዓዊ ጥሰት መኖር አለመኖር አይደለም፡፡ እከከኝ ልከክህ እስከሆነ ድረስ ነው፡፡ የማይወራረድ ልገሳም ሆነ ሙገሳ የለም፡፡ 

የፖለቲካ ወይስ የኢኮኖሚ ጥገኝነት

አሜሪካ ከየትኛውም አገር የሄደን የፖለቲካ ጥገኝነት ጠያቂ እጇን ዘርግታ ትቀበላለች፡፡ ጥገኝነት ጠያቂው ምንም ይሁን ምን ትቀበለዋለች፡፡ አንጀቷ ስስ ስለሆነ አይደለም፡፡ ለማስፈራሪያነት ስለምትጠቀምበት እንጂ፡፡ ከአይዲዮሎጂዋ ፈንገጥ ለሚለው አገር ጨንገር ነው፡፡ ሁለቱ በጥቅም ተፈላላጊዎች ናቸው፣ ይግባባሉ፡፡ ልዩነታቸው ጥገኝነት ያገኘው ለግል ጥቅሙ የሚሯሯጥ ሲሆን፣ አሜሪካ ደግሞ ለሕዝቧ ጥቅም አልማ መንቀሳቀሷ ነው፡፡

በማደግ ላይ ካሉ አገሮች የሚኮበልሉ ግለሰቦች የችግሩ ሰለባዎች እንደሆኑ ብዙዎቹ ምሁራን ይስማሙበታል፡፡ ችግሩ የኢኮኖሚ ሆኖ እያለ የፖለቲካ በማስመሰል ጥገኝነቱን ይላበሰዋል፡፡ ጥገኝነት መጠየቅ ለብዙዎቹ የዕለት ጉርስ ማግኛ ሆኗል፡፡

የተቃውሞ ሠልፍ ላይ ጠጋ ብሎ ፎቶ ለመነሳት የሚሯሯጠው በርካታ ነው፡፡ ፎቶዋ ለጥገኝነት መጠየቂያ ዋነኛ መሣሪያ በመሆኗ ነው፡፡ በሰላም ፓስፖርትና ቪዛ አግኝቶ ከአገሩ ወጥቶ ሳምንት እንኳ አይቆይም አገሬ ከተመለስኩ መንግሥት ያስረኛል፣ ይገለኛል በማለት ሲደሰኩር። የዚህ ዓይነት ውሸት በማደግ ላይ ካሉ አገሮች ከሄዱ ግለሰቦች የሚሰማ ነው፡፡ የጥገኛ ተቀባይ አገሮችም ሐሰት እንደሆነ አላጡትም፡፡ ነገር ግን እስከጠቀማቸው ድረስ ውሸቱን ያስተናግዳሉ። በአይዲዮሎጂ ፈንገጥ ለሚለው እንደ ጨንገር ስለሚጠቀሙበት፡፡ በሚፈልጉበት ጊዜ ይለቁትና ያስጮሁታል፡፡

የሰሞኑ የኮንግረንስ ውሳኔ ሐሳብና እንድምታው

አንዳንድ የኮንግረስ አባላት ኤችአር 128 የሚባል የውሳኔ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ የውሳኔ ሐሳቡ አቅራቢ የኒውጀርሲ ምክር ቤት አባል ክሪስ ስሚዝ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትን ለሚቃወሙ አክራሪ የዳያስፖራ አባላት አንደበት ናቸው ይባላሉ፡፡ የአሜሪካው አና ጎሜዝ የሚሏቸው አይጠፉም፡፡ የኮንግረስ አባላቱ የኢትዮጵያ መንግሥት የተሃድሶ (Reform) ዕርምጃ እንዲያደርግ ለማስገደድ፣ ይኼን መልዕክት ለማስተላለፍ ሲባል የውሳኔ ሐሳቡ እንዲያልፍ ይናገራሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2012 አሜሪካ ከሰሃራ በታች ያሉ አገሮችን በተመለከተ የምትከተለው የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂ ለዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ትኩረት ይሰጣል ይላል፡፡ የዴሞክራሲ ምኅዳሩ እንዲሰፋ ይጠይቃል፡፡ እስከማውቀው ድረስ ይኼ የኢትዮጵያ መንግሥትም አቋም ነው፡፡

የውሳኔ ሐሳቡ የሰብዓዊ መብት ማክበርን መደገፍና አሳታፊ የአስተዳደር ሥርዓት እንዲኖር መደገፍ የሚል ነው፡፡ መልካም ሐሳብ። እነዚህን ጉዳዮች ካየናቸው ምንም ችግር የላቸውም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት የሰብዓዊ መብት እንዲከበርና አሳታፊ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲኖር ከእነ ጉድለቶቹም ቢሆን እየሠራ በመሆኑ፡፡ እንከን የለሽ ዴሞክራሲን ያያችሁ?

እንደ እኔ እምነት የውሳኔ ሐሳቡ ባይወጣ ነበር ትልቅ ብቻ ሳይሆን ሰበር ዜና መሆን የነበረበት፡፡ ምክንያቱም የውሳኔ ሐሳብ ማመንጨት የተለመደ የምክር ቤቱ አሠራር ነው፡፡ በዓመት ውስጥ በሺዎች በሚቆጠሩ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ የውሳኔ ሐሳብ ያወጣል፡፡ በያዝነው በጀት ዓመት ብቻ ከሰባት ሺሕ በላይ አውጥቷል፡፡ የውሳኔ ሐሳቡ ስለአገር፣ ግለሰብ፣ ቡድን፣ ውኃና አየር ሊሆን ይችላል፡፡ የምክር ቤቱ አባላቱ የሙሉ ጊዜ ሥራ ይኼ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ መንገድ ወጥቶ ብዙ ርቀት አልሄድም፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 ‹‹H.R 861›› የሚባል መውጣቱ ይታወሳል፡፡ እንዳለ ቆርጦ መቀጠል ይበዛዋል፡፡ ርዕሱ ሳይቀር ተመሳሳይ ነው፡፡ አልበርት አንስታይን፣ ‹‹አንድን ነገር በተደጋጋሚና በተመሳሳይ መንገድ እየሠሩ የተለየ ውጤት መጠበቅ እብደት ነው፤›› ይላል፡፡

ኤችአር 128 በምክር ቤቱ አመራር መሠረት የውጭ ግንኙነት የንዑስ ቋሚ ኮሚቴው ሊቀመንበር ክሪስ ስሚዝና አምስት አባላት ፈርመውት ለቋሚ ኮሚቴው ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት፣ ኤድ ሮይስ ለሚመሩት ከፍተኛው ቋሚ ኮሚቴ ቀርቦ በቅርቡ 435 የኮንግረንስ አባላት ሊያዩት ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 2 ቀን 2017 ለሙሉ ኮንግረስ መቅረብ የነበረበት ቢሆንም ሳይቀርብ ቀርቷል፡፡

የውሳኔ ሐሳቡ የአሜሪካ መንግሥትን ማዕቀብ እንዲጥል ያስችለዋል ቢባልም ከእውነት የራቀ ነው፡፡  ውሳኔው ተምሳሌታዊ (Symbolic) ነው፡፡ የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ሕግ ሆኖም አይፀድቅም፡፡ ማዕቀብ የሚሆን ነገር የለውም፡፡ ለሥራ አስፈጻሚው አይቀርብም፡፡ የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር አያውቀውም፡፡ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬነር በቅርቡ ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ያረጋገጡት ይኼንኑ ነው፡፡ ክሪስ ስሚዝና ተባባሪ አባላት፣ እኛ የምናየው እንደዚህ ነው የሚል መልዕክት ከማስተላለፋቸው የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ ውሳኔው እሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ ያሉ መራጮችን ለማስደሰት የቀረበ ገጸ በረከት ነው። ከዚያ ውጪ የተጻፈበትን ቀለም ያህል ዋጋ የለውም፡፡

የውሳኔ ሐሳቡ ጉድለቶች

የውሳኔ ሐሳብ የተሳሳተ ለመሆኑ ማሳያዎችን መጥቀስ ጠቃሚ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይነሳ ይላል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ ከተነሳ ቆይቷል፡፡  ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ማለት ነው፡፡ የምዕራቡ ዓለም አጋራቸው ፈረንሣይ ተመሳሳይ አዋጅ አውጥታለች፡፡ ማንም የተናገራት የለም፡፡ ይኼ ፍርደ ገምድልነት ይታይበታል፡፡ ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ እንዲሁም በላቡ ያገኘው ሀብት እንዳይወድም መንግሥት የሚወስደው ዕርምጃ ነው፡፡ ባይነሳ እንኳ ይኼ የኢትዮጵያውያን ብቻ መብት ነው፡፡ አንዳንዶቹ የሚነሱት ጉዳዮች ከሦስት ዓመታት በፊት የተፈቱ ናቸው፡፡ ያለፈባቸው (Outdated) ናቸው፡፡ ይኼ የመረጃ ጉድለት ሳይሆን ንዝህላልነት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንን መናቅ ነው፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት ከተቃዊሚ ፓርቲዎች ጋር የሚያደርጋቸውን በጎ መስተጋብሮች የዘነጋ ነው፡፡ የውሳኔ ሐሳቡ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት እንዲከበር አዎንታዊ ጠቀሜታ የለውም፡፡ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ከኢኮኖሚያዊና ከማኅበራዊ መብቶች ተለይተውና ተነጥለው የሚታዩ አይደሉም፡፡ መንግሥት በእነዚህ መስኮች ረዥም ርቀት ሄዷል፡፡ የትምህርት፣ የጤና፣ የመሠረተ ልማት፣ ወዘተ  ተደራሽነትን ለማስፋት ሰፊ ተግባር አከናውኗል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የተለያዩ ሕጎችን በማውጣት ተቋማዊ አቅሙን ለማጎልበት እየሠራ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብቶችና የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋማት እንዲጠናከሩ ሠርቷል፡፡ አሁንም ብዙ ይቀረናል፡፡

ከውሳኔው ምን ይጠበቃል?

ውሳኔ ቢፀድቅም ባይፀድቅም በሁለቱ አገሮች ግንኙነት ላይ ለውጥ አያመጣም፡፡ ውሳኔው ወጣም ቀረ ኢትዮጵያና አሜሪካ ሁለገብ ትብብር ከማድረግ አያግዳቸውም፡፡ አንዳንድ ወገኖች የግላቸውን ፍላጎት ለማሟላት ተራ የሚዲያ ጨዋታ ቢፈልጉም ሀቁ ይኼ ነው፡፡ ከመልካም ወዳጅህ ጋር ያለህን ግንኙነት ጥሩ ለማድረግ አስተያየት ቢመጣ ጉዳት የለውም፡፡

ኢትዮጵያም እንደ አገር ከአሜሪካም ሆነ ከሌሎች ወዳጅ አገሮች የሚሰጣትን አስተያየት እስከጠቀማት ድረስ በበጎ ትወስዳለች፡፡ የማይጠቅማትን ደግሞ ወደ ጎን በመተው በሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ እንደተለመደው በጋራ ትሠራለች፡፡ ሳትወድ የምትጋተው አንዳችም ነገር የለም፡፡ ይኼ አቋሟ የፀና ለመሆኑ በተለያዩ ጉዳዮች በተደጋጋሚ የታየ ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ ሁለቱ አገሮች የጋራ ጥቅሞች አሏቸው፡፡ በግለሰቦቹ ጫጫታ የሚፈጠር ነገር የለም፡፡ የአንዳንድ የኮንግረንስ አባላት የተለመደ ጩኸት ከአገሮቹ መሠረታዊ የጋራ ግንኙነት ጋር የሚጠጋጋ ሳይሆን የሚላተም ነው፡፡ የኮንግረንስ አባላት ጨዋታና የአገሮቹ ወቅታዊ ግንኙነት አራምባና ቆቦ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡