Skip to main content
x

የግብፅ ነገር ‹‹በቅሎ ማሰሪያዋን በጠሰች ቢሉ አሳጠረች›› እንዳይሆን 

በንጉሥ ወዳጅነው ማሙየ

ለዛሬ የጽሑፌ መግቢያ ያደረግኩት በማኅበራዊ ድረ ገጽ (ፌስቡክ) ላይ ታማኝ  የምለው የአገራችን አንድ የውኃ ተመራማሪ በቅርቡ ያሠራጨው ቅንጫቢ የአኃዝ  መረጃን ነው፡፡ መረጃው የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ የቅርብ ጊዜውን ወደኋላ የሚመልስ ንግግር ተከትሎ፣ ከፍተኛ የሚባል ጫጫታ ያስነሱትን የካይሮ  ሚዲያዎች በመታዘብ፣ እኛ በተፈጥሮዊ ሀብታችን ሳንጠቀም እንዴት ወደኋላ እንደቀረን የሚያሳይ ንፅፅር ነው፡፡ ግብፅና ኢትዮጵያ ሲነፃፀሩ፣

የወንዞች ብዛት
ኢትዮጵያ 12
ግብፅ አንድ (ዓባይ)

የመስኖ ልማት
ኢትዮጵያ ሁለት በመቶ

ግብፅ 75 በመቶ

የመብራት ተጠቃሚ
ኢትዮጵያ ከ60 በመቶ በታች
ግብፅ 98 በመቶ
የንፁህ ውኃ ተጠቃሚ
ኢትዮጵያ 70 በመቶ
ግብፅ 100 በመቶ
የኃይል ምንጭ በሜጋ ዋት
ኢትዮጵያ 4,200
ግብፅ 23,000

የነፍስ ወከፍኤሌክትሪክ ኃይል ድርሻ
ኢትዮጵያ 100 ኪሎ ዋት
ግብፅ 1,425 ኪሎ ዋት
የነፍስ ወከፍ ገቢ 
ኢትዮጵያ 792 ዶላር
ግብፅ 3,212 ዶላር (አራት እጥፍ ብልጫ) 
የአፈር መሸርሸር

ኢትዮጵያ አንድ ቢሊዮን ቶን
ግብፅ ዜሮ በመቶ

ኢትዮጵያና ግብፅ ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍል በመፍጠር፣ በጋራ መልማት፣ በጋራ የሚሸረሸር አፈር መከላከልበጋራ የደለል ማስወገድ፣ በጋራ ድርቅን ቀንሶ ማኅበራዊ ቀውሶችን መቆጣጠር ካልተቻለ አገራችን ኢትዮጵያ ወንዙን (ህዳሴ ግድቡን) የመጠቀም መብቶችን በራሳችን ማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ ነው ይላል፡፡

ይህ ንፅፅርም ሆነ ገለጻ እንደ ዋዛ የሚታይ አይደለም፡፡ አሁንም ድረስ ብሔራዊ ቁጭትን የሚጭር ቁም ነገርን ያዘለ ነው፡፡ የቀደመው ዘመንን የዓባይ ውዝግብና ታሪክ እንተወውና ቢያንስ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ወዲህ፣ በግብፅ መገናኛ ብዙኃን አማካይነት አንዳንድ የአገሪቱ ኃላፊዎችንና ሙሁራንን ዋቢ በማድረግ እየወጡ ያሉ ተከታታይ ዘገባዎች፣ ቀደም ሲል ሲነሱ ከነበሩ ሥጋቶች ሙሉ በሙሉ የተለየ ይዘት አልነበራቸውም። በቅርቡ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የግብፅ ፕሬዚዳንትም ቢሆኑ ግራም ነፈሰ ቀኝ ‹‹ከቀደመው የውኃ ተጠቃሚነታች ጠብታ ያህልም ቢሆን መቀነስ የለበትም፤›› ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡ ይህ አነጋገር ደግሞ ከድርድር መንፈስ ያፈነገጠ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም፡፡

የእሳቸው አገላለጽም ሆነ የሚዲያዎቹ ትንታኔ በተለይ በሦስቱ አገሮች (ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን) ለ17 ጊዜ ሲካሄድ የከረመውን ድርድርም የሚያውክ ነው፡፡ በእርግጥ ከዚህ ቀደምም ለይስሙላ ድርድር የሚባለውን ፎረም ያስቸገረውም፣ ግብፅ በቅኝ ግዛት ወቅት በእንግሊዝ መንግሥት አማካይነት ከሱዳን ጋር ተፈራረምኩ የምትለው ‹‹ስምምነት››ን ደጋግማ ማንሳቷ እንደነበር የታወቀ ነው፡፡ 

ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ይህን የአንበሳውን የውኃ ተጠቃሚነት ድርሻ የሚያረጋግጥ ኢፍትሐዊ ውሳኔ መለስ ቀለስ እያለች ማንሳቷ ብቻ ሳይሆን፣ አሁንም ይህንኑ መሠረት አድርጋ ‹‹ከናይል ወንዝ ጠብታ ውኃ ማስነካት የሞት ሽረት ጉዳይ ነው፤›› በማለት ላይ ነች፣ ‹‹አመንጪዎችም ብትሆኑ ዓባይን አትንኩብኝ፤›› የሚያስመስል ስሜት የተቀላቀለበት አስተያየት በተለያዩ ጊዜያት፣ በተለያዩ ኃላፊዎች ሲንፀባረቅ የሚደመጠውም ለዚሁ ነው።

በናይል ውኃ ረገድ እ.ኤ.አ. በ1929 እና በ1959 የተደረጉት ‹‹ስምምነቶች›› በሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች በቅኝ ገዥዎች ውክልናና በኋላ ላይም በግብፅና በሱዳን መካከል የተደረጉ ናቸው። ግብፅ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዓባይ ተፋሰስ አገሮች የሚከናወን ማንኛውም ዓይነት የልማት ፕሮጀክት የመከታተልና የማምከን (ከብድር ማስከልከል ጀምሮ፣ የአገሮችን የውስጥ ችግር በማባባስና በማስፈራራት) ዕርምጃዎችን የመውሰድ እንቅስቃሴ ስታደርግ የቆየችውም፣ በዚሁ ፍርደ ገምድል የአንድ ወገን ውሳኔ ላይ ተመሥርታ እንደነበር ይታወቃል። 

 

በመሠረቱ እ.ኤ.አ. የ1959 ስምምነት ተብዬው የውኃ ሀብት ንጥቂያ እንኳን ሲፈረም፣ ኢትዮጵያንም ሆነች ሌሎች የላይኛው የዓባይ ተፋሰስ አገሮችን ያካተተ  እንዳልነበረ መረጃዎች ያሳያሉ። በሱዳንና በግብፅ ብቻ የተፈረመ እንደነበርም ይታወቃል። ከዚህ አንፃር እነዚህ አገሮች የተፋሰሱ የላይኛው አገሮችን ለማስገደድ ሕጋዊም ሆነ ሞራላዊ መሠረት እንደሌቸለው የዘርፉ ምሁራን ደጋግመው ተናግረዋል። ስምምነቱም ከዓለም አቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የጋራ ተጠቃሚነት አንፃር ሲታይ ቅቡልነትን ሊያገኝ እንደማይችል የታወቀ ነው፡፡  

የውኃው አመንጪዎችና ባለቤቶች የሆኑትን አገሮች ወደ ጎን ትቶ የተፈረመ ሰነድ በሁሉም የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ተፈጻሚነት ሊኖረው እንደማይችል፣ በናይል ተፋሰስ አገሮች የስምምነት ማዕቀፍ ሰነድ ላይ ጭምር ተጠቅሷል። ፈራሚዎቹም በወቅቱ (በተለይ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች በእጅጉ በተዳከሙበት ወቅት) በእጃቸው የሌለና የማያመነጩትን ሀብት ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ካላቸው ፍላጎት አንፃር ምኞታቸውን የገለጹበት እንጂ፣ አሁን ድርጊቱ ፉርሽ እንደሆነ በተለይ ሱዳኖች ተገንዝበውታል። ይህ መሆኑ እየታወቀ ለምን የግብፅ ፖለቲከኞች ጉዳዩን የሙጥኝ ብለው እንደቆዩ ግን አነጋጋሪ ነው፡፡

ከዚህ ኢፍትሐዊና ምክንያት አልባ የውኃ ተጠቃሚነት አካሄድ እስረኝነት በመላቀቅ፣ አገራችን የብዙኃኑን የተፋሰሱ አገሮች የጋራ ውሳኔ ተከትላ በዓባይ ወንዝ ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት መነሳቷም፣ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ተግባር ነው፡፡ ግንባታው ስድስት ዓመታትን እያስቆጠረ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከፍታው 145 ሜትር፣ የጎኑ ርዝመት 1.8 ኪ.ሜ. ሲደርስ፣ በግድቡ ምክንያት የሚከማቸው የውኃ መጠንም የጣና ሐይቅን ሁለት ዕጥፍ  መሆኑም ከአገር አልፎ ቀጣናዊ ፋይዳውን የሚያጎላ ነው።

ይኼ ማለት ግድቡ ሲጠናቀቅ 1,680 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ወደ 74 ቢሊዮን ኪዮቢክ ሜትር የውኃ መጠን መሬት ይይዛል። ከግድቡ ወደ ኋላ ሜዳማ ሥፍራውን አልፎ በርቀት የሚታዩት አነስተኛ ተራራማ ሥፍራዎች ጭምር ወደ 246 ኪሎ ሜትር ወደኋላ የውኃ ሐይቅ ተሞልተው ደሴት ይሆናሉ መባሉም በሁሉም ዜጋ ልብ ውስጥ ሰርፆ የሚገኘውን ያህል፣ በግብፃውያኑ ፖለቲከኞች ዘንድ የውኃ የኃይል ሚዛንን የሚያስቀይርና ኢትዮጵያም ለዘመናት ከተደነቀረባት የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ትብትብ የመውጣት ምልክት ተደርጎ ተወስዷል። 

በመሠረቱ ግዙፉ የአገራችን የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ለአገራችን ብቻ ሳይሆን  በአፍሪካ ትልቁ፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁ አሥር የኃይድሮ ኤሌክትሪክ  ኃይል ማመንጫ ግድቦች መካከል አንዱ መሆኑ የተለየ ያደርገዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ከራሷ በሚፈልቀው የዓባይ ወንዝ ላይ ለዘመናት የቆየውን የግብፅ ብቸኛ ተጠቃሚነትንና ኃያልነትን የሰበረመሆኑ ክንውኑ ታሪካዊ ነው፡፡ ይህ አገራዊ ድል የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የውኃ ሀብታቸው ያለ ጥቅም ለዘመናት ሲፈስ እያዩ ምንም ማድረግ ላልቻሉ የናይል ወንዝ ተጋሪ አገሮችም ጭምር እንደሆነ የመስኩ ተንታኞች ያስረዳሉ።

በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ግን ከኖረው የታችኛው የተፋሰሱ አገሮች ተጠቃሚነት አንፃር ነገሩን መዝኖም ሆነ ግልጽነት ለመፍጠር ካላው ፍላጎት (በተገዳዳሪ ወገን ግድቡን እስከ ማስጎብኘት እየሄደ ያለው አጉል ግልጽነት ብዙም ባይበረታታም) በመነሳት ግድቡን መገንባት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ ተግባሩን ግልጽ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ሥጋት ላላቸው አገሮችም እንዲመክሩበት ሁኔታዎችን ሲያመቻች ቆይቷል፡፡ ይኼው እስካሁንም የመቋጫው እንዴትነት ያልታወቀው የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን ድርድር የአባባሉ ማሳያ ነው፡፡

እዚህ ላይ ግን በበርካቶች አዕምሮ የሚጉላላ አንድ ጥያቄ አለ። ይኼውም፣ ‹‹ለመሆኑ በዓባይ ውኃ ላይ ወሳኙ ማን ነው?›› የሚለው መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ይህንን ጥያቄ መመለስ ምናልባትም ከላይ ለሚነሳው ጉዳይ በቂ አስረጂ ሊሆን ይችላል። እርግጥ ወንዙ ድንበር ተሻጋሪ እንደመሆኑ የተፋሰሱ አገሮች በሙሉ በጋራ የመወሰን መብት እንዳላቸው ዕሙን ነው። አሁን ባለው ዓለም አቀፍ ሁኔታም አገሮቹ እኩል የወሳኝነትና ፍትሐዊ የተጠቃሚነት መብት እንዳላቸውም የሚያጠያይቅ አይደለም። የዓባይ ውኃ ለሁሉም የተፋሰሱ አገሮች ሕዝቦች የተሰጠ የተፈጥሮ ፀጋ በመሆኑ፣ ሕዝቦች በእኩልነትና በመተሳሰብ ሊጠቀሙበት ይገባል መባሉም ለዚሁ ነው።

ከዚህ ነበራዊ ሀቅ ስንነሳ በማንኛውም ጊዜ ቢሆን የተፋሰሱ የታችኛው አገሮች የላይኛዎቹን አገሮችን በማግለል የሚያደርጉት ስምምነት ተቀባይነትም ሆነ ሕጋዊነት አይኖረውም። እንደዚህ ዓይነት በጋራ ሀብት ላይ የተናጠል ውሳኔ ሊኖር እንደማይገባም የታመነ ነው። የተፋሰሱ የላይኛው አገሮችም ቢሆኑ የታችኛው አገሮች መሠረታዊ ጥቅምና  ፍትሐዊ  የውኃ ተጠቃሚነት ሊጎዳ የሚችል ተግባር በተፋሰሱ ላይ ሊያደርጉ እንደማይገባ መግባባት የተደረሰበት ዓለም አቀፍ ሀቅ ነው። 

በሌላ በኩል የላይኛው ተፋሰስ አገሮች የውኃው ምንጮች በመሆናቸው ውኃውን ለልማት የማዋል መብታቸው የተጠበቀ ነው። በተለይ ኢትዮጵያ 85 በመቶ የሚሆነውን ውኃ አመንጪ በመሆኗ፣ ሕዝቦቿን ከዚህ ሀብቷ ተጠቃሚ የማድረግ (ያውም ለቅንጦት አይሉት ችጋርና ድህነትን ለማባረር) ሕጋዊ መብቷ የተጠበቀ ነው።

አገራችን ቀደም ባለው ታሪኳ ይህንን የተፈጥሮ ሀብት መጠቀም የቻለችበት አጋጣሚ አልነበረም። ያለፈው አልፎ በተሻለ የሕዝብ ተሳትፎና የመንግሥት ቁርጠኝነት በውኃው የፍትሐዊነትና የምክንያታዊነት አጠቃቀም መርህ በመገንባት ላይ ባለችበት በዚህ ወቅት ደግሞ፣ ማንም ቢሆን እንቅፋት ሊፈጥርባት አይገባም፣ አይችልምም፡፡ ይህን  እውነታ ነው የግብፅ ፖለቲከኞች በአጽንኦት ሊረዱት የሚገባው የሚል መደምደሚያ መያዝ ተገቢ ነው፡፡  

በመሠረቱ ያለንበት ዓለም የውህደት ምዕራፍ ላይ የተገነባ ነው። በትሪሊዮን የሚቆጠር ካፒታልና የሠለጠነ ሰፊ የሰው ኃይል ያለምንም የድንበር ገደብ የሚያንቀሳቀሱበት ዘመን ነው። ዓለማችን አንድ መንደር እየሆነች የመጣችበት ወቅት ነው መባሉም ለዚሁ ነው። ስለሆነም ለማንም ቢሆን ይህንን ነባራዊ ሀቅ መገንዘብና ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል መርህን መከተል የግድ ይላል። ከናይል አንፃር ሁሉም ወገን ተጠቃሚ የሚሆነው ደግሞ ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀምን ተግባራዊ ማድረግ ሲቻል ብቻ ሳይሆን፣ በጋራ መጠቀም ሲቻልም እንደሆነ አያጠያይቅም። በብዙ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የሚደረገው የአገሮች ስምምነት የሚያረጋግጠውም ይህንኑ ነውና፡፡

ከዚህ አንፃር በምሥራቅ አፍሪካም ሁሉንም የተፋሰሱ አገሮች ሕዝቦች  ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻለው ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀምን በመተግበር ብቻ እንደሆነ  ግብፃዊያን ሊረዱ ይገባቸዋል፡፡ በግልጽም ሊነገራቸው ይገባል፡፡ በእነሱ በኩልም ያረጀ ያፈጀ የቅኝ ግዛት ‹‹ስምምነት›› ተቀባይነት እንደማይኖረውና ለአሁኑ ነባራዊ ሁኔታ  የማይመጥን እንደሆነ ከመገንዘብ ባሻገር፣ በአዲስ አስተሳሰብ ወደ ሰጥቶ መቀበል  ድርድር መመለስ ይበጃቸዋል።    

በእርግጥ ለዓባይ ተፋሰስ አገሮች የጋራ ዕድገት የሚበጅ ከዚህ የተለየ ሌላ አማራጭ እንደሌለ የታወቀ ነው። ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅም ከዚህ ያለፈ አማራጭ እንደማይኖራቸው መገንዘብና በጋራ ሠርቶ በጋራ ለማደግ መተባበር ሲገባቸው፣ በተለይ በግብፃዊያኑ ተደራዳሪዎችም ሆነ አለፍ ሲል መሪዎች በኩል የተያዘው አወዛጋቢ አቋም ለማንም የሚበጅ እንዳልሆነ በገሀድ እየታየ ነው፡፡ ዓባይ ለግብፃዊያን የውስጥ ፖለቲካ መቆመሪያ የመሆኑም ጉዳይ ፀሐይ እየሞቀውና ንፋስ እየመታው መምጣቱን ማጤንና ራስን ማስተካካል በተገባ ነበር፡፡ ግን እየሆነ አለመሆኑ አስገራሚ ነው፡፡ 

በአሁኑ ወቅት ለጋራ ተጠቃሚነት መግባባትና ፍትሐዊ አሠራርን ማስፈን ለቀጣናው ሕዝብ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው። የዓባይ ውኃ ለግብፃዊያን ህልውናቸው የሆነውን ያህል፣ ለኢትዮጵያውያንና ለሌሎች የተፋሰሱ አገሮችም በእጃቸው ያለ የዕድገታቸው አንደኛው አማራጭ ነው። በተለይ ኢትዮጵያ ዓባይን ያህል ትልቅ የተፈጥሮ ፀጋ እያላት፣ ሕዝቦቿ ሊራቡ እንደማይገባ ብርቱ አቋም የያዘ ትውልድ መምጣቱ ብቻ ሳይሆን በቆራጥነት መነሳቱም ተጋግሎ መቀጠል ያለበት ነው።

በመሆኑም አገራችን አቅም እስካገኘችና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያላቸውና ሕዝባዊ አንድነትን ማምጣት የሚችሉ አመራሮች እስከያዘች ድረስ፣ እንዲሁም የውስጥ መረጋጋትና ዴሞክራሲን በማጠናከር ዘላቂው ሰላም አስከተረጋገጠ ድረስ (ከባዱ ፈተና ይህን ማድረግ ተስኖን እንዳሁን በመንገዳገድ ለመቀጠል ያሰብን እንደሆነ ነው)፣ በተፈጥሮ ፀጋዎች ከማልማትና ከመጠቀም የሚያግዳት አንዳች ምክንያት እንደሌለ በሁሉም ወገን ግንዛቤ ሊያዝበት የግድ ይላል።

ተደጋግሞ እንደተገለጸው የኢትዮጵያ ዓላማ ሕዝቦቿን ከድህነት ለማላቀቅ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በተገቢው መንገድ መጠቀም ብቻ እንደሆነ ሁሉም ዜጋ ተገንዝቦታል። አገሪቱ ከድህነት ለመላቀቅ የምታደርገው ጥረት የሚሳካው ደግሞ የሌሎች አገሮችን ሕጋዊና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በመፃረር እንዳልሆነ ደጋግማ አስታውቃለች፡፡ አሁንም የተቀየረ ነገር እንደሌለ ይታመናል።

ይሁንና ግብፅና ሱዳን ከዓባይ ተፋሰስ የሚኖራቸውን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሌሎች የተፋሰሱ አገሮች የተፈረመውን አዲሱን የትብብር ስምምነት መፈረም ሲገባቸው፣ እስካሁንም እየተገበሩት አይደለም፡፡ ከዚያም ብሶ ብዙ ምልልስ የተደረገበትና በግድቡ መጠናቀቅ፣ ውኃ ሙሌትና አካባቢያዊና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ላይ  ያተኮረውን የሦስትዮሽ ስምምነት ዳር ለማድረስ የማያግዝ ዳተኝነት በተለይ በግብፅ በኩል መታየቱ ብዙዎችን እያስገረመ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ ይህን አቋም ከሦስት ዓመት በፊት፣ ከተፋሰሱ 12 አገሮች ለተውጣጡ የኅትመት ሚዲያ ዋና አዘጋጆች ቡድን ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ ጭምር በካይሮ በግልጽ እንዳስገነዘቡ አንዱ ምስክር ነኝ፡፡)

በቅርቡ ደግሞ የሦስቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች (በጥቅምቱ 16ኛው የድርድር መድረክ ወቅት) ግድቡን መጎብኘታቸው የማይቀረውን እውነት ለመገንዘብ ሳያስችላቸው አልቀረም፡፡ በእርግጥም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት  ከግንባታ ጋር ተያያዥ የሚሆኑ ፈተናዎችን በሙሉ እያለፈ ለመሆኑ፣ ቦታው ላይ ተገኝቶ የተመለከተ ሁሉ የሚመሰክረው ነው። ከጊዜ ጋር ተያይዞ ግን እንደ ግዙፍ ፕሮጀክትነቱ የተወሰነ መዘግየት እንደሚያጋጥመው በመነገር ላይ ነው፡፡ ይህም ቢሆን መዘንጋት የሌለበት ግን  ከግድቡ የሥራ ሒደት ውስብስብነት አንፃር ብቻ ሳይሆን፣ ከታችኛው የተፋሰሱ አገሮች ጋር ስምምነት የሚጠይቀው አጠቃላይ ግድቡን በውኃ የመሙላቱ ሥራ ዋነኛው መንስዔ መሆኑን የውስጥ አዋቂ ምንጮች እያስረዱ ነው፡፡

ከዚህ አንፃርም ቢሆን ከወዲህኛው ወገን ያሉ ተደራዳሪዎች ግልጽ አቋም ይዘው  በነበራዊው ሀቅ ላይ ሐሳብን ከማራመድ ይልቅ ወደኋላ ተመልሶ ለመነታረክ መሞከራቸው  እንጂ፣ በስንት ዓመታት ውስጥ ግድቡ ቢሞላ በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ ጉዳት አያደርስም የሚለው ጉዳይ በባለሙያዎች የተደገፈ ስምምነት  እንደሚያስፈልገው የታመነ ነው፡፡ 

በአጠቃላይ በዓለማችን ረዥም በተባለው የዓባይ ወንዝ ላይ አገሪቱ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለመገንባት ከመወሰኗ በፊት ከፍተኛ አገራዊ ቁጭት እንደነበር ማሳያ ነው፡፡ ለዚህም ነው የአገሪቱ ዜጎች በችግር ወቅት እንኳን ዋነኛ የጋራ አጀንዳቸው ዓባይና ግድቡ መሆናቸውን እያሳዩ ያሉት። ይህን ነባራዊ ሀቅ ደግሞ ከግብፅ ፖለቲከኞች በላይ የሚገነዘብ ይኖራል ማለት ዘበት ነው፡፡

ለወደፊቱም ሁሉም የአገራችን ሕዝቦች ዓይንና ጆሮ ወደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ጉባ ወረዳ ዘልቆ እንደቆየው ሁሉ፣ የውስጥ የፖለቲካ ግትርነትና መካረርን በመቅረፍና በመደማማጥ ወደ ወሳኙ ምዕራፍ መገስገስ ያስፈልጋል። በአሁኑ ጊዜ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚገኝበት ደረጃ ከ62 በመቶ በላይ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የግንባታው ሒደትም እንደተለመደው በመፋጠን ላይ መሆኑ ተነግሯል። ይሁንና እንደ ተጀመረውና እንደ ተጋመሰው ይጠናቀቅ ዘንድ መላው ሕዝብ፣ ምሁራንና ፖለቲከኞች ሁሉ በየፊናቸው ካለፈውም በበለጠ ተሳትፏቸው ማጠናከር አለባቸው፡፡ ይኼ ብርታታችን ሁሉንም ወደማይቀረው ድርድር መጎተት ይችላል፡፡ 

በእርግጥ አሁንም ግብፃዊያኑ ፖለቲከኞች ከሚመላለሱበትና ከሚያሠራጩት  ፖለቲካ እየወጡ ወደ ቀልባቸው ከመመለስ ሌላ አማራጭ እንደ ሌላቸው መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ የአገር ፕሮጀክት ፍፃሜው ሩቅ እንደማይሆን ሁሉ፣ ያንን ለማየት የማይጓጓ የዚህ ትውልድ አካል አይኖርም። በተጨማሪም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፍፃሜ የተሻለች ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን፣ እየለማ ያለን ምሥራቅ አፍሪካ ማየት ተገቢና አስፈላጊ ነው። ይህ እውነታ ደግሞ ግብፃዊያኑን ጨምሮ መላውን የተፋሰሱ አገሮች ሊያስደስት የሚገባው እውነታ መሆን ሲገባው፣ ማሰሪያዋን እንደምትበጥስ በቅሎ መሆን፣ ማሰሪያ ከማሳጠር ውጪ መላ የለውም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]. ማግኘት ይቻላል፡፡