Skip to main content
x
አገር የጠላት መጫወቻ እንዳትሆን!

አገር የጠላት መጫወቻ እንዳትሆን!

በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ የተለያዩ ሥፍራዎች እያጋጣሙ ባሉ ግጭቶች የንፁኃን ሕይወት እየጠፋ ነው፣ የነገን ተስፋ የሚያጨልሙ አሳዛኝ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ነው፡፡ በተለይ ሰሞኑን በዜጎች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች ያሳምማሉ፡፡ አገርን እየገጠመ ያለው መከራ ከሐዘን መግለጫ በላይ ነው፡፡ ሲያስቡት ይቀፋል፣ ያሳፍራል፣ ቃላት ሊገልጹት ከሚችሉት በላይ መራር የሆነ ስሜት ይፈጥራል፡፡ መንግሥት ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ እያጋጠሙ ላሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሁሉንም ወገን የሚያስማማ ጠብሰቅ ያለ መፍትሔ ማምጣት አቅቶት አገር ቋፍ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ራሱ የፈጠራቸውን ችግሮች ማስተካከል አቅቶት በተፈጠረው ክፍተት ጠላት እየገባ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ የሰው ክቡር ሕይወት እንደ ቀልድ እየተቀጠፈ፣ በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሥነ ልቦና ቀውስ እያጋጠመ የአገር ዕጣ ፈንታ አጣብቂኝ ውስጥ ወድቋል፡፡ በዚህ መሀል የአገሪቱ መላ ሕዝብ ግራ እየተጋባ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት የሚታወቁበት የአገርን ክብርና ሰንደቅ የማስከበር የጋራ እሴት እየተናደ፣ አክራሪ ብሔርተኞች በሚፈጥሩት ከፋፋይ አጀንዳ የአገር ክንድ እየዛለ ነው፡፡ የሕዝብ  ተስፋ መንምኖ ሥጋት የበላይነቱን ይዟል፡፡ ከዚህ አረንቋ ውስጥ በቶሎ መውጣት ያስፈልጋል፡፡

በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ የኖረች አገር የጠላት መጫወቻ እንድትሆን የሚያመቻቹ አደገኛ ድርጊቶች በስፋት እየታዩ ነው፡፡ ጀግኖቹና ኩሩዎቹ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በመቆም በአገር ፍቅር ስሜት አንፀባራቂ ገድሎችን ሲፈጽሙ የኖሩት፣ በአገር ውስጥ ጨቋኝ ገዥዎች ቁም ስቅላቸውን እያዩ እንደነበር ማንም አይክድም፡፡ ከምንም ነገር በላይ አገር ስለምትበልጥባቸው ነበር፡፡ የአገር ጉዳይ የጋራ በመሆኑና የእርስ በርስ ፍቅራቸውም ከፍተኛ ስለነበር ወራሪዎችንና ተስፋፊዎችን፣ እንዲሁም ቅኝ ገዥዎችን ተራ በተራ አንበርክከዋል፡፡ በታላቁ ፀረ ኮሎኒያሊስት የዓደዋ ድልም ለመላው ጥቁር ሕዝቦች አንፀባራቂ የሆነ ተምሳሌታዊነት አሳይተዋል፡፡ ብሔር፣ እምነት፣ ቋንቋ፣ ባህልና የመሳሰሉት ልዩነቶች ሳይገድቧቸው አንድ ላይ በመቆም አገራቸውን ጠብቀዋል፡፡ ይህንን የመሰለ አንፀባራቂ ገድል በተፈጸመባት በዚህች ታሪካዊት አገር ውስጥ፣ ብሔርን መነሻ ያደረጉ ግጭቶች ተፈጥረው ክቡር የሰው ሕይወት ሲጠፋ ማየት ይረብሻል፡፡ ይህንን አጋጣሚ የሚጠብቁ ታሪካዊ ጠላቶችም የውስጥ ሽኩቻውን እያባባሱ የአገሪቱን ገጽታ ለማበላሸት ተግተው እየሠሩ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ ከታላላቆቹ የዓለም ግንባር ቀደም ከተሞች (ኒውዮርክ፣ ብራሰልስ፣ ጄኔቫ) ተርታ በመሠለፍ በመዲናዋ በአዲስ አበባ የበርካታ አገሮች ኤምባሲዎችን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለያዩ መሥሪያ ቤቶችን፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጽሕፈት ቤቶችን፣ የአፍሪካ ኅብረትንና የመሳሰሉ ተቋማትን ታስተናግዳለች፡፡ በ1955 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተመሠረተው የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በመሆኗ ሳቢያ ነው፣ እነዚህ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ የከተሙት፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ለመሆን ዕድሉን ያገኘችው፣ በዓለም ጥቁር ሕዝቦች ታሪክ አንፀባራቂ የሆነውን ታላቁን የዓደዋ ጦርነት አሸንፋ የኮሎኒያሊስቶችን ቅስም በመስበሯ ምክንያት ነው፡፡ ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ አርዓያ በመሆኗ ነው፡፡ ይህ ታላቅ ድል የተገኘው ደግሞ ኢትዮጵያውያን በጀግንነት አንድ ሆነው ተሠልፈው ቅኝ ገዥውን ወራሪ በመደምሰሳቸው ነው፡፡ ለጠላት አንዳችም ክፍተት ሳይሰጡ በፈጸሙት ገድል ነው፡፡ አሁን ግን ያ ተምሳሌታዊ ተጋድሎ ዋጋ እያጣ ለጠላት መፈንጪያ ቀዳዳ ተፈጥሯል፡፡ ይህንን ቀዳዳ በአስቸኳይ አለመድፈን አገርን የጠላት መጫወቻ ያደርጋል፡፡ ብናውቅበት እኮ ኢትዮጵያችን ከእኛ አልፋ የአፍሪካውያን የጋራ ቤት ነበረች፡፡

ጠላት እርስ በርስ ስንጣላ በእሳቱ ላይ ነዳጅ እያርከፈከፈ ጠቡን ያጋግመዋል፡፡ ከዚያም ገመናችንን ለዓለም እያሳየ ኢትዮጵያን የግጭት ተምሳሌት መሆኗን ያጋልጣል፡፡ መጀመርያ ኢንቨስተሮችን በማስደንበር ድርሽ እንዳይሉ ያደርጋል፡፡ የልማት አበዳሪ ተቋማት እጃቸውን እንዲሰበስቡ ተግቶ ይሠራል፡፡ አገሮች የኤምባሲ ሥራዎቻቸውን እንዲያቀዘቅዙ ወይም እንዲያቆሙ ይቀሰቅሳል፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማት እየለቀቁ እንዲወጡ ያደርጋል፡፡ እንደ ተባበሩት መንግሥታትና የአፍሪካ ኅብረት ሐሳባቸውን እንዲለውጡና መቀመጫቸውን እንዲቀይሩ ይገፋፋል፡፡ በገዛ ራሳችን በፈጠርነው ችግር ምክንያት ጠላት መሀላችን እየገባ ክፍፍሉን ያጧጡፈዋል፡፡ የጎረቤት አገሮችን ሳይቀር የደኅንነት ሥጋት እንደተፈጠረባቸው በማስመሰል የጥፋቱ ተባባሪ ያደርጋቸዋል፡፡ እንኳንስ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማስፈጸም አይደለም፣ የአገሪቱ ህልውና ታይቶ በማይታወቅ መጠን አጣብቂኝ ውስጥ ይገባል፡፡ እርስ በርስ መግባባት ባለመቻል ምክንያት ብቻ፣ አገርና ሕዝብ ከትርምስ ወደ ቀውስ እንደሚሸጋገሩ አለማሰብ ያሳዝናል፡፡ ይህንን የመሰለ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ ይዞ አገርን በአግባቡ መምራት ባለመቻል ብቻ የጠላት መጫወቻ መሆን ያሳፍራል፡፡ ‹‹ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል›› እንዲሉ፡፡

ከላይ የተገለጸው መላምት ነው ብሎ ከማጣጣል ይልቅ በተግባር የሚውል መሆኑን ለመገንዘብ፣ ከቅርብ ርቀት ጀምሮ ያለውን አሠላለፍ ማየት ተገቢ ነው፡፡ በአፍሪካ ቀንድ የሚስተዋለውና አሁንም ድረስ የሚንተከተከው የፖለቲካ ትኩሳት አንዱ ችግር ነው፡፡ አልሸባብ የተባለው የዓለም አቀፍ አሸባሪዎች ጉዳይ አስፈጻሚ በቅርብ ርቀት ላይ ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ የየመን ውድመት፣ በእነ ሳዑዲና ኳታር መካከል ያለው ልዩነት፣ የሳዑዲና የኢራን የበላይነት ፍጥጫ፣ ቀይ ባህርንና የህንድ ውቅያኖስ መተላለፊያን የመቆጣጠር ህልምና የመሳሰሉ ሩጫዎች በግልጽ ይታያሉ፡፡ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምክንያት የተፈጠረው ውዝግብ ይታወቃል፡፡ ዛሬ ወዳጅ የሆነ ነገ ጠላት በሚሆንበት ዓለም ውስጥ ዘላቂ ጥቅምን ታሳቢ ያደረጉ መሳሳቦች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ በዚህ አስፈሪ ጊዜ እንደ አገር አንድ ላይ መቆምና በተለመደው መንገድ አገርን መመከት ሲገባ፣ ከመንደር እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በብሔር ግጭት መታመስ ምን ይሉታል? አገርን ከሚመሩ ግለሰቦች ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ያሉ ፈጻሚዎች ድረስ ምን እየተከናወነ ነው? ከአገርና ከሕዝብ በላይ ምንም ስለሌለ ወደ ቀልብ መመለስ ካልተቻለ መጪው ጊዜ አስፈሪና አደገኛ ነው፡፡ አሁን በመንግሥት ዘንድ የሚታየው ችላ ባይነትና ዘገምተኝነት ችግሮችን የበለጠ ከማወሳሰብ የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ የራስን ውስጣዊ ችግር ትቶ ሌላ ነገር ማነብነብም አይጠቅምም፡፡ በተግባር የማይታጀብ ተስፋ ለሕዝብ መመገብም የበለጠ ጥፋት ነው፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ የሚያኮራ ሕዝብ አገር ናት፡፡ ይህንን ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ ይዞ ተዓምር መፍጠር ይቻላል፡፡ ሰላሳ ሚሊዮን የሚጠጉ ወጣቶች በተለያዩ ደረጃዎች በትምህርት ገበታ ላይ ናቸው ያሉት፡፡ ግማሽ ሚሊዮን ያህሉ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይማራሉ፡፡ ኢኮኖሚው በአግባቡ ተመርቶ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማምጣት፣ ፖለቲካው በአግባቡ ተመርቶ ሥልጣን በነፃና በፍትሐዊ ምርጫ ብቻ እንዲያዝ ማድረግ፣ ሁሉንም መሠረታዊ መብቶች የሚያስከብር ሥርዓት መፍጠር፣ በሕግ የበላይነት ሥር የሚተዳደሩ መንግሥታዊ ተቋማትን መገንባት፣ ሲቪል ማኅበረሰቡን በብዛት ማፍራትና የመሳሰሉትን ማድረግ ቢቻል እኮ የኢትዮጵያ አንድነት የበለጠ ይፈረጥም ነበር፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግን ራስ ወዳድነት በመብዛቱ ብሔር ውስጥ ተወሽቆ መጠዛጠዝ የዘመኑ ልማድ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያዊነት የሚባለው ትልቁ ምሥል ደብዝዞ የሰው ልጅ ሕይወት ከንቱ ሆኗል፡፡ የሰውን ልጅ ሕይወት አደጋ ውስጥ የሚከቱ ግጭቶች ማባሪያ አጥተዋል፡፡ የአገር ህልውና አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ሕዝብን ለዕልቂት የሚዳርጉ ችግሮችን በአስቸኳይ ማስወገድ ካልተቻለ የአገር ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን ለመገመት ነቢይ መሆን አያስፈልግም፡፡ ጠላት ይህን ክፍተት እየተጠቀመ በየቀኑ ከትምርስ ወደ ቀውስ ይገፋናል፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ይህንን አደገኛ ነገር ሊያስቡበት ይገባል፡፡ መንግሥት የራሱን ችግሮች በውጭ አካላት ላይ ማሳሰብ ትቶ፣ ሁሉንም ወገን የሚያስማማ ምኅዳር እንዲፈጠር ማድረግ አለበት፡፡ በአጉል ተስፋ ሕዝቡን መደለል ሊቆም ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያንን ከዳር እስከ ዳር የሚያግባባ ዓውድ ከተፈጠረ ጠላት የሚገባበት ቀዳዳ አይኖርም፡፡ ይህን ቀዳዳ ሳይደፍኑ በውጭ ኃይል እያሳበቡ መቀጠል አይቻልም፡፡ ይህ በፍፁም የማይታለፍ አገራዊ የጋራ ጉዳይ ስለሆነ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ አለበለዚያ አገር የጠላት መጫወቻ ትሆናለች!