Skip to main content
x
‹‹ለዋናው ችግራችን መፍትሔ አግኝተናል ወይ የሚለው ያሳስበኛል››

‹‹ለዋናው ችግራችን መፍትሔ አግኝተናል ወይ የሚለው ያሳስበኛል››

አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፣ የኅብረት ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ

ታዋቂው የኢንሹራንስ ባለሙያ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ የ79 ዓመት አዛውንት ናቸው፡፡ ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ ከሙያቸው ጋር በተያያዙ ሥራዎች በኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ውጭም ሠርተዋል፡፡ ዛሬም ሥራ ላይ ናቸው፡፡ ይበልጡን በኢንሹራንስ ባለሙያነታቸው የሚታወቁት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሲቋቋም የመጀመርያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነበሩ፡፡ ደርግ የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ከመውረሱ በፊት ዓባይና ብሉ ናይል የተባሉ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ውስጥ ሠርተዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ በአንድ ታዋቂ የናይጄሪያ ኩባንያ ውስጥ የቴክኒክ አማካሪ፣ ዳይሬክተርና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከዚያም ወደ አገራቸው እስከተመለሱበት ጊዜ ድረስ በአፍሪካ ሪኢንሹራንስ ኩባንያ ውስጥ መሥራታቸው ይጠቀሳል፡፡ የኅብረት ኢንሹራንስ መሥራችና ከፍተኛ ባለአክሲዮን የሆኑት አቶ ኢየሱስ ወርቅ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚና የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ሠርተዋል፡፡ በተመሳሳይም በኅብረት ባንክ ምሥረታ ውስጥ ቀዳሚ ሚና ነበራቸው፡፡ የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ንግርና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው የሠሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የኅብረት ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው እያገለገሉ ነው፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኙት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ አግኝተዋል፡፡ በሙያቸው በተለያዩ አገሮች ሥልጠናዎችን ወስደዋል፡፡ አዲሱን ዓመት አስመልክቶ በተለይ በግል ሕይወታቸው፣ በአገራዊ ዋና ዋና ጉዳዮች የወደፊት ምኞታቸውን በተመለከተ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡ መልካም አዲስ ዓመት!!!

ሪፖርተር፡- እንደ ዘመን መለወጫ ያሉ በዓላትን እንዴት ያከብራሉ? ዘመን አልቆ አዲስ ሲተካ ምኞትዎ ምንድነው?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- በአንድ በኩል ስታየኝ ‹‹ኦልድ ፋሽንድ›› ነኝ፡፡ ሌላም ዓይነት በዓል ድሮም አላውቅም፡፡ ልጅ እያለሁ ዲያቆን ነበርኩ፡፡ ጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት እንኳን ሳለሁ ለተወሰነ ጊዜ እቀድስ ነበር፡፡ ዓመት በዓላትን እንደ ትልቅ ታሳቢና የደስታና የብዙ የምኞት መያዣ ናቸው፡፡ ‹‹የአምላክ ጉቦ ተመስገን ነው›› ይባላል፡፡ እንደዚህ አንድ ዓመት አልፎ ሌላ ዓመት ሊተካ ሲል ያለፈውን ዓመት በሰላም አልፌ፣ እኔም ቤተሰቤም በጤና በመገኘታችን በእውነቱ እግዚአብሔርን በጣም አመሰግንበታለሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይህንን የማደርገው ቤተ ክርስቲያን በመሄድና ገራገራ ሥር ቆሜ አይደለም፡፡ አሁን ይህን አላደርግም፡፡ ነገር ግን የእኔ ፀሎት አንዳንድ ጊዜም በጀርባዬ ተጋድሜ በማሰብ ነው፡፡ በጣም ብዙ ዓመታትን ወደ ኋላ ተመልሼ ሄጄ የት ነበርኩ? ከየት መጥቼ ዛሬ እዚህ እገኛለሁ? መጪውን ዓመት ደግሞ አምላኬ እንዴት ታደርጋለህ? በማለት ነው፡፡ አንድ ሰው ቢያገኝ ቢደላውም ዓለም የአንድ ሰው ብቻ አይደለችም፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን በጤና ለመኖር እሞክራለሁ፡፡ ነገር ግን ከዓመት ዓመት የማስበው በተለይ ዊንጌት ወደ መጨረሻ አካባቢ እንዲያው ስለአካባቢዬ ማኅበረሰብ ኑሮ፣ ከቀዬ፣ ከሠፈርና ከመንደር እንዲሁም ከክፍለ ሀገር ወጥቼ ስለአገር ስለሌሎች አገሮችና ስለዓለም ሳስብ ሁልጊዜ ካገኘሁት የተሻለ ዓለም ትቼ መሄድ እፈልጋለሁ፡፡ ዜጎች በተሻለ እንዲኖሩ የሁልጊዜ ፍላጎቴ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ብቻውን ሁሉም ነገር ቢሟላለት ደስታ ሊሆነው አይችልም፡፡ በተለይ ለእኔ ዓይነቱ አመጣጥ፡፡

ሪፖርተር፡- ከእኔ ዓይነቱ አመጣጥ ሲሉ ምን ለማለት ፈልገው ነው?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- የገበሬ ልጅ ነኝ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ያደግኩ፣ ችግርን የቀመስኩ፣ ከሞላ ቤቴና ከቤተሰቤ ተለይቼ ሱዳን በረሃ ውስጥ ገብቼ አፈርና አሸዋ ላይ የተኛሁ ሰው ነኝ፡፡ ቤተሰቦቼን ተመልሼ አገኛቸው ይሆን ወይ? ብዬ ብዙ የሆንኩ ስለሆነ ሁልጊዜ ማኅበረሰቡና አካባቢዬ ከአጠገቤ ብቻ ያለው ሳይሆን፣ በአጠቃላይ እኔ ስሄድ የተሻለ አገርና ዓለም እንዲሆንለት እፈልጋለሁ፡፡ እንዲህ እንድሆን እፈልጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙ ችግር ያየሁ ነኝ ብለውኛል እንደ ችግር የሚቆጥሩትንና ያጋጠመዎትን ይነግሩኛል? በሕይወትዎ ደርሶብኛል የሚሉት ችግር ምንድነው?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ወጣት ስለነበርኩኝ ብዙዎቹ ለጊዜው ችግር ቢሆኑም፣ ይህንን ያህል ቅስምን የሚሰብሩ አልነበሩም፡፡ ደግሞ ያልተወጣኋቸው ችግሮች አልነበሩኝም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ችግሬ በጣም ትንሽ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ በቀላሉ ብነግርህ ከአገር በስደት ስወጣ በመተማ አድርጌ ፖሊስ ጣቢያ ስደተኛ ነኝ ብዬ ገብቼ፣ ከዚያ ሰቲት ሁመራ ሲልኩኝ በጣም ተጎሳቁዬ ነበር፡፡ በስደት ስወጣ ፎርድ የተባለ አሮጌ የጭነት መኪና ላይ ተጭኜ ነበር ገዳሪፍ የገባሁት፡፡ እዚያ ስደርስ ሁለመናዬ አፈር ነበር፡፡  

ሪፖርተር፡- ላቋርጥዎትና ለስደት ያበቃዎት ምክንያት ምን ነበር? በወጣትነት ዘመንዎ የተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ ከነበረዎ ተሳትፎ ጋር ይያያዛል? እግረ መንገድዎንም በተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ የነበረዎትን ሚና ያስታውሱኝ፡፡

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- የስደቱ ምንጭ ከብዙዎች ወንድሞቼና እህቶቼ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ በወቅቱ የነበረው አስተዳደር ለአብዛኛው ሕዝብ ጥሩ አልነበረም፡፡ የተሻለ ዓለምና ኑሮ ለአገራችንና ለሕዝብ መምጣት ይገባዋል ብለን ከሚጮሁና ከሚሠለፉ ሰዎች አንዱ ነበርኩ፡፡ በጣም የሚደንቅህ በአንድ ወቅት ለውጡን መፈለጋችን ዓይናችንን እየሸፈነ መጥቶ በምን እንደምንለውጠውና እንዳምንተካው ጊዜ ወስደን እንኳ አላሰብንም ነበር፡፡ የተወሰነ የግለሰብ ጥላቻ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ያን ጊዜ የነበረው ሥርዓት ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ አይበጅም የሚል ነበር፡፡ በ1960ዎቹ መጀመርያ ተማሪዎች ከታች እስከ እላይ የተነሳንበትና በወቅቱ የነበረው የአገዛዝ ሲስተም መለወጥ አለበት ብለን እንፍጨረጨር ነበር፡፡ የሚደንቀው ማንኛችንም ግን ይኼ ሥርዓት ነገ ቢወድቅ በምን መተካት አለበው? ወይም ማነው እንዲተካ የምንፈልገው የሚለው እንዲሁ ጥራዝ ነጠቅ በሆነ መንገድ ነበር የሚታወቀው፡፡ ያን ጊዜ እንደ ልብ መጻፍ ባይኖርም ስለማርክሲዝም ሌኒኒዝም ያነበብን፣ የእዚህን ዓይነት ሲስተም ኢትዮጵያ ውስጥ መምጣት አለበት የሚል እምነት ነው የነበረው፡፡ ይህ አመለካከት የበሰለ አይደለም ወደሚል አመለካከት የገባን ነበርን፡፡ እርግጥ ከጊዜ በኋላ በተለይ የንጉሡ ጊዜ አልፎ ደርግ ከመጣ በኋላ፣ እንዲያው ዝም ብለን ማርክሲዝም ሌኒኒዝም ማለት አይደለም፡፡ እኛ መጀመርያ ላይ ማርክሲዝም ሌኒኒዝም ሲባል ሶቭየት ኅብረትን ነበር የምናስበው፡፡ በኋላ የቻይና መጣና እነዚህ ሶቭየቶች ቀልባሾች ናቸው፣እውነተኛው ማርክሲዝም ሌኒኒዝም የቻይናዎቹ ነው ማለት ተጀመረ፡፡ ከዩኒቨርሲቲ የምንመረቅበት ዓመት ላይ ‹‹ጎበዝ እስኪ እናስብ፡፡ እኛ የሶቭየት፣ የቻይና እያልን ለምን እናስባለን?›› የሚል ጥያቄ ጀመርን፡፡ መጠየቅ ያለብን እኮ ለአገራችን የሚበጀው ምንድነው በማለት ማሰብ ያለብንን እንጂ ዝም ብለን በጭፍን የእነ እከሌን መከተል አለብን ወይ? ብለን የራሳችንን ጥያቄ አመጣን፡፡ ከዚህ በመነሳት እነ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ከመምጣታቸው በፊት ወታደር ሥልጣን እንደሚወስድ  ገምተን ነበር፡፡    

ሪፖርተር፡- እንዴት ወደዚህ ድምዳሜ ገባችሁ? የምታውቁት ነገር ነበር?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ራሳችን የሠራነው ትንተና ነበር፡፡ የተወሰነ ያኔ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሆነን የሠራነው ትንተና ነው፡፡ ይህንን ከሠራነው ውስጥ አንዳንዶቻችን አሁንም አለን፡፡ በተለይ ከመንግሥቱ ነዋይ የመንግሥት ለውጥ ሙከራ በኋላ ንጉሡ የሚችሉ ቢሆንና ቢሆንላቸው ‹‹ኮንስቲትዩሽናል ሞናርኪ›› [ሕገ መንግሥታዊ ንጉሣዊ አገዛዝ] ለማምጣት ቢችሉ ነው፡፡ ምናልባትም ልጃቸውን አንግሠው፣ ነገር ግን ዘውድ እንደ አንድ የኢትዮጵያ ታሪክ ምዕራፍ ተደርጎ ፈላጭ ቆራጭ ያልሆነ አገዛዝ መምጣት ቢችል የሚል ምኞት ነበረን፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ምኞት ከምን የመነጨ ነው?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ምክንያቱም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ወደ መጨረሻው ዓመት ላይ ስንደርስ  የጃንሆይ አገዛዝ በአንድ ምክንያት ወይም በሌላ ቢቋረጥ ምን ሊሆን ይችላል? ከሚል ነው፡፡ እኚህ ሰው እንግዲህ አርጅተዋልና በተፈጥሮም ቢሆን መሞት አለ፡፡ ከዚህም ሌላ የመንግሥቱ ንዋይን ሙከራ አልፈውታል፣ የሚቀጥለውን ላያልፉ ይችላሉና ምን ዓይነት መንግሥት ልናገኝ እንችላለን? ማነው ሥልጣን መያዝ የሚችለው? የሚለውን ጥያቄ አመጣን፡፡ ከዚህ አንፃር ሥልጣን መውሰድ የሚችለው የተደራጀ ኃይል ነው የሚለውን ድምዳሜ ይዘን ስንነሳ፣ በዚያን ጊዜ የተደራጀ ኃይል የነበረው ወታደር ነው፡፡ ስለዚህ ወታደር እንደሚወስድ ከሞላ ጎደል እርግጠኞች ነበርን፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅቱ የተደራጁ ኃይሎች አልነበሩም እንደ ኢሕአፓና መኢሶን የመሳሰሉት?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- እነ ኢሕአፓ እኮ ሥልጣን የሚወስዱበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ይኼ  ቀደም ብሎ ነው፡፡ እንዲያውም እኔ የማስታውሰውን አንድ ነገር ልንገርህ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተማሪ መሪዎች ከነበርነው ውስጥ አንዳንዶቻችን ውጭ ነበርን፡፡ እኔ እዚህ ሁለት ዓመት ሠርቼ ለግራጁዌት ስኩል ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፒተርስበርግ ሄጄ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ጄኔራል አማን አምዶምን ለማግኘት ዋሽንግተን ዲሲ ሄደን ነበር፡፡ ያኔ ጄኔራል አማን አምዶም በዋሽግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የትምህርት አታሼ ነበሩ፡፡ እኚህን ሰው እናናግራቸው ብለን ተነሳን፡፡ እሳቸውን ለማነጋገር ቀደም ብለን ውሳኔ ያደረግነው ግን እዚህ በነበርንበት ወቅት ነው፡፡ አንዱ ዶክተር ነው፣ ሌሎችም ነበሩ፡፡ ወታደር ሥልጣን ሊወስድ ነው የሚል ግምት አለንና እስቲ ወታደሮቹን እንጠጋቸውና ትንሽ አስተሳሰባቸውን እንመልከት፣ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ለመገፋፋት ሙከራ እናድርግ ከማለት ነው፡፡ ይህንን ከምናደርግበት አንዱ ጄኔራል አማን አምዶምን ሄዶ ማነጋገር ነበር፡፡ ሥልጣን ሊወስድ የሚችለው ወታደር ነውና እንደነ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ሳይሆን፣ ፕላን ተደርጎ ደንበኛ የሲቪሎች ድጋፍ ያለው የወታደር ሥርዓት እንዲኖር ከማሰብ እንደነ መንግሥቱ ያለው እንዳይወሰድ ነበር የምንፈልገው፡፡ አስታውሳለሁ እሳቸውን ስናነጋግራቸው ጤናዬም ስለማይፈቅድ በዚህ ነገር ውስጥ አልሳተፍም አሉና ተመልሰን መጣን፡፡ እኛ ይህንን ስናደርግ እነ ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ በአሜሪካ የኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ከመሪዎቹ አንዱ ነበር፡፡ እንግዲህ ዞሮ ዞሮ ደርግ መጣ፡፡

ሪፖርተር፡- ጄኔራል አማን አምዶም ዘንድ ስትሄዱ ዋነኛ ጉዳያችሁ ምን ነበር? ምን ለማድረግ እንደሆነ ይንገሩኝ፡፡ በለውጡ ውስጥ መሳተፍ ስለፈለጋችሁ ነው? ምክንያታችሁ ምን ነበር? ወደ ሥልጣን የመቅረብ ፍላጎት ነው?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- እኛ እኮ ገና ተማሪዎች ነን፡፡ ኃላፊነት ቢሰጠን አብረን እንሠራለን፡፡ ነገር ግን ለአገር መሪነት ብቃት ያለን ነን ብለን አናምንም፡፡ ያኔም እንዲህ ያለው አመለካከት አልነበረንም፡፡ ነገር ግን ፍላጐት የነበራቸው በአውሮፓና በአሜሪካ የተደራጁ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ እኛ ከእነሱ ጋር አልነበርንም፡፡ የእኛ ቤዝ እዚህ ነው፡፡ እዚህ ሆነን ሥውር የሆነ አንድ የጥናት ቡድን ብለን የፈጠርነው ነበር፡፡ በህቡዕ ነው ያደራጀነው፡፡ እንዲያውም ከዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ወጥቼ ኢምፔሪያል ኢንሹራንስ ስቀጠር የመጀመሪያ ደመወዜን ላቋቋምነው የሥውር ጥናት ቡድን የሚሆን መጽሐፍ መግዣ ነበር የዋለው፡፡ በሥውር ሰባ ደረጃ አካባቢ ቤት ተከራይተን በየሳምንቱ ርዕስ እየተከፋፈልን ምንድነው ለአገራችን የሚያስፈልገው? እያልን እንመክር ነበር፡፡ ቅድም ያልኩህን የቻይና፣ የሶቭየት ከማለት ይልቅ የአገራችን ነው የምንለውን ነገር ለማምጣት ጥናት ማድረግ አለብን የሚል ቡድን ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የቡድኑ አባላት ስንት ነበራችሁ? ደርግ ከመጣ በኋላ ምን ተፈጠረ?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- አንድ 15 እንሆናለን፡፡ ጥቂቶቹን እንዲያውም ስማቸውን ዘርዝረን ነበር፡፡ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ አዳማ ላይ አንድ የጥናት ምክክር አዘጋጅቶ ነበር እዚያ መድረክ ላይ የተማሪዎችን ንቅናቄ በተመለከተ በተዘጋጀው ውይይት ላይ አንዱ ተጋባዥ እኔ ነበርኩ፡፡ እዚያ ላይ ስማቸው ተዘርዝሯል፡፡ ይህንን ጉዳይ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴም ጽፎታል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ምኞች ነበረን፡፡ ደርግ መጣ፡፡ ደርግ መጀመርያ ላይ ‹ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም› የሚል መፈክር ያዘ፡፡ በዚህ ጊዜ ብዙዎቻችን እንፈራ ነበር፡፡ የነበረውን ጃንሆይ ቢሄዱ ማነው የሚተካው? ምን ሊመጣብን ነው? ብለን የፈራን ሰዎች ኢትዮጵያ ትቅደም ያለ ምንም ደም የሚል ሥነ አመክኖአዊ የሚመስል መፈክርና መዝሙር ሲዘመር፣ ምናልባት በዚህ ሁኔታ ካለፍን ያለምንም ደም ሕዝብ ሳይተላለቅ ሥርዓቱ የሚለውጥ ከሆነ በጣም ጥሩ አልንና ተሠለፍን፡፡

ደርግ ከመጣ በኋላ እኮ ለሃይማኖት ነፃነትና ለሌሎች መብት መከበሮች መስቀል አደባባይ ተሠልፌያለሁ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን በተለይም እነዚያን 60 ሰዎች በአንድ ቀን ጭጭ አድርገው ካደሩ በኋላ ነገር ተለወጠ፡፡ ትዝ ይለኛል 60ዎቹ የተገደሉት ቅዳሜ ዕለት ነበር፡፡ እሑድ እኔ ተኝቼ ሳለሁ ሁለት ጓደኞቼ በሌሊት መጥተው አስነሱኝና አንተ እንዴት ትተኛለህ? እነዚያን ሰዎች እኮ ጨረሱዋቸው ብለው ነገሩኝ፡፡ እንዴት አድርገው ነው የጨረሱዋቸው ብዬ ጠየቅሁ፡፡ የፖለቲካ ፍርድ ሰጠን ብለው ገደሉዋቸው አሉኝ፡፡ አይ… እንዲህ ከሆነማ አለቃልን አልኩ፡፡ ‹ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቀደም› የተባለው አለቀለት! በዚህ ሁኔታ ደም ከተቃቡ በኋላ እዚህ አገር ውስጥ ሰላም አይኖርም ብዬ ነገሩን ለማረጋገጥ፣ ደርግ ስለመረሸኑ እርግጠኛ ናችሁ ወይ? ብዬ ከጠየቅሁ በኋላ አንዳንድ ተገደሉ የተባሉ ሰዎች ሠፈር ሄድንና አየን፡፡ እና ይህንን ሳውቅ ለራሴ ከእዚህ በኋላ የፈራነው ዓይነት መጥፎ ሒደት አይቀርልንም ወደሚል ድምዳሜ ደረስኩ፡፡

በዚያን ጊዜ ትዝ የሚለኝ በቴሌቪዥን የተላለፈው ነገር ነው፡፡ ካዛንቺስ ከልማት ባንክ በታች ኮከብ ሬስቴራንት ያለበት ሕንፃ አለ፡፡ የእዚህን ሕንፃ ኮርነሩን በቴሌቪዥን ያሳዩና ወዲያው ልዑል መኮንን ትምህርት ቤት መርካቶ ወደ አውቶብስ ተራ ስትሄድ በስተቀኝ በኩል ግንቡ ሥር ሽንት ላይ የሚያድሩ ድሆችን እያነፃፀሩ ያሳዩ ነበር፡፡ ሽንት ላይ ያድሩ የነበሩትን አንተ ማነህ? እንደዚህ ቆሻሻ ላይ ወድቀህ እንዲህ የምትሆነው?  ብለው  ይጠይቁና መልሰው የኮከብ ሕንፃን እያሳዩ ሌላው ኢትዮጵያዊ እንዲህ ባለው ቤት ሲኖር፣ አንተ እዚህ ወድቀሃል እያሉ እያነፃፀሩ ያቀነባበሩትን ተመለከትኩ፡፡ ከዚያ በኋላ የቤት ሠራተኞች ቀጣሪዎቻቸውን እንዲገድሉ፣ እንዲደበድቡ ‹ማማሰያ የለሽም ወይ?› ቢላዋ የለሽም ወይ? በማለት ሴቷ ሠራተኛ እንድትነሳ አደረጉ፡፡ ምክንያቱም ትልቁ ስብከት ማባላት ሆነ፡፡ እና ትንሽ በሀብት ቀና ቀና ያሉትን ኢትዮጵያውያን ጭንቅላታቸውን ሲቆርጡ፣ እነሱ በአንድ ጊዜ ባለፀጋ መሆን እንደሚችሉ የሚያመለክት ምሥል ማሳየት ተጀመረ፡፡ እንግዲህ እንዲህ ካደረጉት ውስጥ አንዳንዶቹ መሪዎች ጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት አብረውኝ የነበሩና የማውቃቸው ናቸው፡፡  

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ እነማን?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ደምሴ ደሬሳ፣ አሁን ጣሊያን ኤምባሲ ታስሮ ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረው ብርሃኑ ባየህ (አንድ ዓመት እቀድመዋለሁ) እንዲያውም አንድ መኝታ ቤት ነበርን፡፡ እንዲህ ያሉ ብዙ ነበሩ፡፡ እነዚህ መሪዎች ናቸው፡፡ እነሱን የሚጠጉም ብዙ ጓደኞቻችን አሉ፡፡ በኋላ እኔ የምታወሩት በሙሉ ስለሀብት ክፍፍል ብቻ ሆነ፣ ሀብት መከፋፈል የሚቻለው ሀብት ሲኖር ነው፣ ይቺ አገር እኮ ደሃ ነች ማለት ጀመርኩ፡፡ በወቅቱ የምጠቀምበት ምሳሌ የእኛን አገር ሕዝብ በሀብት ብታስቀምጡት እንደ ፒራማድ ነው፡፡ . . .ፒራሚዱን ከጭንቅላቱ ላይ ትንሽ ቆርጣችሁ ሌላውን ሁሉ እኩል ልታደርጉት አትችሉም፡፡ አሁን እያደረጋችሁ ያላችሁትና እየሄዳችሁበት ያለው መንገድ እኩልነት በድህነት ነው፡፡ ይኼ ነገር አያዋጣም፡፡ ይህንን ስል አንዳንድ ጓደኞቼ ‹‹አንቺ›› ነበር የሚሉኝና ‹‹እንዴ አንቺ ተማሪ ሆነሽ ስለጭቁኑ ስትታገይ ቆይተሽ ወዴት ነው የምታፈገፍጊው? እዚያ ተራራ ላይ ቤተ መንግሥት የመሰለ ቤት ሠራሽና ቡርዣ ሆንሽ ማለት ነው. . .›› አሉኝ፡፡ በኋላ እንደሰማሁት በሥራው ጐበዝ ነው፡፡ ግን ሕይወቱና ዕይታው የቡርዣው ነው ተብያለሁ፡፡ እዚህ ላይ ወዲያው ተነስቼ ቅዋሜም ባላደርግ ነገሩን ልቀበል አልቻልኩም፡፡ ከዚያ በስመ ሞክሼ ትታሰራለህ፣ ትገደላለህ፡፡ እኔ አስታውሳለሁ ልዑል አልጋ ወራሽ ጋ ይሠራ የነበረ ጣሊያናዊ ልጅ እዚህ መጥቶ ታስሮ ተሰቃይቷል፡፡ እስሩ እየሰፋ መጣ፡፡ ይህንን ሁሉ ሐሳብ ማውጣት ማውረድ ግድ ነበር፡፡ በኢንሹራንስ ሥራ እኔ የመጀመርያው ነኝ ባልልም የተሻለ መታወቅ የነበረኝ ሰው ነኝና በሥራዬ እፈለግ ነበር፡፡ እንዲያውም በአንድ ወቅት ከአንዱ ወደ ሌላው መሥሪያ ቤት ሊወስዱኝ የፈለጉበት ጊዜ ነበር፡፡ 

ሪፖርተር፡- ማንደርግ ነው በምን ዓይነት ሥራ?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- አዎ፡፡ የተወረሰ ንብረት አስተዳዳሪ ሊያደርጉኝ ፈለጉ፡፡ በኋላ እሱማ ከኢንሹራንስ አይወጣም፣ ኢንሹራንሱን በሙሉ ለማን ልንሰጠው ነው ተብዬ ቀረሁ፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅትን ስናቋቁም ስድስት ሆነን ነው፡፡ አንዱ እኔ ነኝ፡፡ ከሌሎቹ የበለጠ የማውቀው ነገር አለ ባልልም፡፡ የተሻለ ዕውቅና ነበረኝ፡፡ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ  እንግሊዝ አገር በኢንሹራንስ፣ ሲዊዘርላንድ በሪ ኢንሹራንስ ሥልጠና አግኝቼ ተመልሻለሁ፡፡ እዚያ የላኩኝ በብሉ ናልይ ኢንሹራንስ የነበረው አለቃዬ አቶ አባተ ፋንታዬ ነበር፡፡ ስለሥራው የተሻለ እንዳውቅ ዕድል ሰጥቶኝ ለንደን ሄጄ ሥልጠና አደረግኩ፡፡ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ስመለስ ዙሪክም ሄጄ እንድማር አድርጎኛል፡፡ ከዚያ የተወረሱ የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን በሙሉ አንድ ኩባንያ አድርጐ ለማቋቋም ሥራ ተጀመረ፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅቱ ግን የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የተመሠረተው በደርግ የተወረሱት  የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንዲጨፈለቁ ከተደረገ በኋላ ነው፡፡ ስንት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ነበሩ?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- 13 ናቸው፡፡ እነዚህን 13 ኩባንያዎች አንድ አደረግንና እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 1975 መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ መድን ድርጅትን ለማቋቋም ስንሠራ የነበርን አባላትና የኢንሹራንስ ካውንስል የሚባለው ውስጥ ያሉ አባላት ሆነን በብሔራዊ ባንክ ገዥ ስብሰባ ተጠራን፡፡

ሪፖርተር፡- ያኔ የብሔራዊ ባንክ ገዥው ማን ነበሩ?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- አቶ ታደሰ ገብረ ኪዳን ነበር፡፡ ያኔ የኢንሹራንስ ቦርድን እሱ ነበር የሚመራው፡፡ የተወረሱትን የኢንሹራንስ ኩባንያዎችንም የሚቆጣጠረው እሱ ነበር፡፡ እዚያ ስብሰባ ላይ ተጠርቼ ደብዳቤ ተሰጠኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ደብዳቤ?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ደብዳቤው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነሃል የሚል ነው፡፡ ምክትሎችህ ደግሞ እከሌና እከሌ ናቸው፡፡ ደብዳቤውን የምትጽፍላቸው ግን አንተ ነህ ተባልኩ፡፡ በዚህ ወቅት ሌሎችም እንዲሾሙ የሚፈልጉ ሰዎች ነበሩ፡፡ ጉዳዩ ብዙ ትግል ነበረበት፡፡ እኔ ግን በዚህ ኃላፊነት ቦታ ላይ የሠራሁት ሁለት ወር አካባቢ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ከሁለት ወር በኋላ አንድ ቅዳሜ ቀን ፍቼ እናቴን ጠይቄ ስመለስ መኪና ውስጥ ሬዲዮ ሳዳምጥ በእኔ ምትክ ሌላ ሰው እንደተሾመ ሰማሁ፡፡ የአጋጣሚ ነገር ሲዋዚላንድ የሚገኘው ሮያል ኢንሹራንስ ኩባንያ (የመንግሥት ተቋም ነው) መሪ እንግሊዛዊ ነበር፡፡ ይህንን ኩባንያ እንዳስተዳድር ደብዳቤ ተልኮልኝ ነበር፡፡ ያንን ደብዳቤ ግን ሸሽጌ ይዥው ቆይቻለሁ፡፡ ምክንያቱም ያንን ባሳይ አልለቀቅም፡፡ ስጠየቅም አሁን ከአገር ልውጣ ማለት ጥሩ አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ መውጣት የአብዮት ሰይፍ ያስመዝዛል ተብሎ ተነገረኝ፡፡ አፌን ይዤ ተቀምጨ ነበር፡፡ በኋላ በእኔ ምትክ ሌላ ሰው ከመጣ ከኢትዮጵያ ወጥቼ የመሥራት ዕቅድ እንደሚኖረኝ ግን አሰብኩ፡፡     

ሪፖርተር፡- ግልጽ ያድርጉልኝ ከኃላፊነት የተነሱበትን ምክንያት አላወቁም? ማረጋገጥ አልሞከሩም?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ምንም ምክንያት የለም፡፡ ብዙ ነገሮች ነው የምሰማው፡፡ ቅድም እንዳልኩህ ጎበዝ ሠራተኛ ነው፣ ግን እንደ ቡርዣ ነው፡፡ ዳገት ላይ ሄዶ ትልቅ ቤት ነው የሠራው እየተባልኩ ታምቻለሁ ሲባል እሰማለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በእርስዎ ኃላፊነት ላይ ሌላ ሰው መተካቱን በሬዲዮ ሲሰሙ ምን አሉ?  በወቅቱ የተሰማዎትን ስሜት ያስታውሳሉ?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- በእኔ ቦታ ሌላ ሰው መተካቱን እንደሰማሁ አንድ ነገር በእንግሊዝኛ ለራሴ ተናገርኩ፡፡ ‹‹ኤ መንኪ ኦፍ ማይ ባክ›› (ዝንጆሮዋ ከትከሻዬ ላይ ተወርውራ ወረደችልኝ) ነበር ያልኩት፡፡ ከዚህ በኋላ ነፃ ነኝ ብዬ ደመደምኩ፡፡ ይገርምሃል በዚያን ጊዜ ይህንን የሰሙና የመጀመርያው ሰው ሆነው ያናገሩኝ ታዋቂው በቀለ ሞላ ነበሩ፡፡ አፈላልገው አስጠሩኝና ንብረቴንም ሥራውንም እንደፈለግክ አድርገው፡፡ እባክህ ልጄ እኔ አላወቅኩበትም ጎበዝ ሰው ያስፈልገኛልና አንተን ስለማውቅህ አብረኸኝ ሥራ አሉ፡፡ በኢንሹራንስ ሥራዬ ያውቁኛል፡፡ እንዲህ ከሥራ ስባረር ሥራ እንካ የሚለኝ ሰው ካለ ከእሱ የተሻለ ምን ዘመድ አገኛለሁ ብዬ በጣም እግዜር ይስጥልኝ ብዬ እሺ አልኩ፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር ማድረግ እፈልጋለሁ አልኳቸው፡፡   

ሪፖርተር፡- አቶ በቀለ ሞላ አብረን እንሥራ ብለው የጠየቁት ሆቴሎችን እንዲያስተዳድሩላቸው ነው?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- አዎ ሆቴሎችን ተረከበኝና አስተዳድር ነበር ያሉት፡፡ ከዚያ እሺ ብዬ መጀመርያ ግን የማላውቃቸውን ሆቴሎች በሙሉ አንድ በአንድ በራሴ ሄጄ ዓይቻቸው ከዚያ በኋላ ሪፖርት አቀርብልዎታለሁ አልኳቸው፡፡ ነገር ግን እኔ ምንም ሪፖርት አልሰጠኋቸውም፡፡ መጀመርያውኑ ብዙ ነገር አስብ ነበርና አላደረግኩትም፡፡

ሪፖርተር፡- ከአቶ ከበቀለ ሞላ ጋር ካልሠሩ ቀጣዩ ማረፊያዎት ምን ሆነ ታዲያ? መቼም ያለሥራ መቀመጥ አይቻልም?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ከአገር ለመውጣት አቅጄ ነበር፡፡ ከባለቤቴ ጋር ተነጋግሬ ከአገር ለመውጣት ወሰንኩ፡፡ በአውቶብስ ተሳፍሬ ጎንደር ገባሁ፡፡ እንደገና በትሬንታ ኳትሮ ተሳፍሬ መተማ ገባሁ፡፡ መተማ አደርኩና በማግሥቱ ጠዋት ቡና ለመጠጣት ያቺን ደረቅ የመተማን ወንዝ አለፍኩ፡፡ እዚያ ኢትዮጵያውያን ወደ ሱዳን ገብተው ቡና ይጠጣሉ፡፡ ሱዳኖችም ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ካቲካላ ይጠጣሉ፡፡ እኔም ቡና ለመጠጣት ተሻገርኩ፡፡ ምንም ነገር የለኝም፡፡ ካኪ ለብሻለሁ፡፡ ፀጉሬ አድጓል፡፡ ቡናዬን ጠጣሁና በዚያው ጉዞዬን ወደ ሱዳን ቀጠልኩ፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ውጭ መውጣት ሲወስኑ ዓላማዎ ምን ነበር?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- የትም አገር ሄጄ ሠርቼ መኖር የምችል ሰው ነኝ፡፡ አሁን እዚህ ከቆየሁ አፌም አያርፍም ይገሉኛል፡፡ ከባለቤቴ ጋር የተነጋገርነው ይህንኑ ነው፡፡ ሌላ ምንም ነገር የለም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ የለሁም፡፡ የማየው ነገር ሁሉ ጥሩ አልነበረም፡፡ ወዳጄ ሰይፉ ሽብሩን አሰሩትና ከዚያ ገደሉት፣ ሚዜዬ ነበር፡፡ እንድወጣ ከገፋፉኝ ምክንያቶች አንዱ ይኼ ነው፡፡ በጣም አስቸጋሪ ጊዜ ነበር፡፡ ይህንንም አልፌ ሄጄ አገራችን ውስጥ ይደረግ የነበረውንና በየዕለቱ የሚሆነውን አውቅ ነበር፡፡ ሁለት ሕፃናት ልጆቼን፣ ሚስቴን፣ ሽማግሌ አባትና እናቴን ጥዬ ነው የሄድኩትና እንዲያው ቤተሰቤን አንድ ቀን አገኛቸው ይሆን ወይ? ብዬ እጨነቅ ነበር፡፡ በሕይወቴ በጣም የማስታውሰው ትልቁ ጭንቀቴ ይህ ነበር፡፡ ሱዳን ሰዎቹ ጥሩ ናቸው፡፡ ሙቀቱ ከባድ ነው፡፡ ሱዳን እንደገባሁ ገንዘብ የለኝምና ጥሩ ቦታ መኖር አልቻልኩም፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ሥራ አግኝቼ ገባሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ሥራ? በሚያውቁት ሙያ ነው ወይስ በሌላ?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ኢንሹራንስ ኩባንያ ውስጥ ነው ሥራ ያገኘሁት፡፡ ‹ቺፍ አንደርራይተር› ሆኜ ነው የተቀጠርኩት፡፡ ሥራ መሥራት ስጀምር መሀል ከተማ አፓርታማ አገኘሁ፡፡ ናይጄሪያ የኢንሹራንስ ኩባንያ ካላቸው እንግሊዛውያን ጋር የተገናኘ ነው፡፡ እነሱም ከናይጄሪያውያን ጋር ያቋቋምነው ኢንሹራንስ ኩባንያ ስላለ እዚያ ናና ሥራ አሉኝ፡፡ ሱዳን ውስጥ ሥራ ማግኝቴ ደግሞ ለራሴ ብቻ ሳይሆን፣ ሱዳን ውስጥ በስደት ለነበሩ ኢትዮጵያውያንም ጭምር ተረፍኩ፡፡ የሱዳን ገንዘብ ዥኔ ይባላል፡፡ 25 ፒያስተር የአንድ ብር አንድ አራተኛ ነው፡፡ ስሙኒ እንደ ማለት ነው፡፡ ይኼ የአንድ ዥኔ አንድ አራተኛ አንድ ሰው ምግብ ያበላል፡፡ እና እኔ ብዙ ስደተኛ ወጣቶችን አበላ ነበር፡፡ ምሳ ብቻዬን አልበላም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በቀን አራት አምስት ልጅ ይዤ ምሳ እበላለሁ፡፡ እዚያ በነበርኩበት ጊዜ የአንድ ወቅት እንግዳዬ የነበረው አቶ ነዋይ ገብረአብ ነበር፡፡ እዚያ በመጣ ጊዜ ፍራሻችንን ሜዳ ላይ አንጥፈን እንተኛለን፡፡ ምክንያቱም አንድ አልጋ ስላለኝ እኔ አልጋ ላይ ተኝቼ እሱ መሬት አይተኛም፡፡

ሪፖርተር፡- ከእሳቸው ጋር እዚያ እንዴት ተገናኛችሁ? እንዴትስ መጡ?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- እሱ ያኔ ለንደን ነበር፡፡ አጎቱ ጄኔራል እያሱ የኢዲዩ አመራር ውስጥ ነበሩና እሳቸው ዘንድ ይመጣ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት እኔ የነበርኩበት መጥቶ እኔና እሱ ከሁለት ወራት በላይ ቆይተናል፡፡ ስለኢትዮጵያም አንድ ወረቀት አብረን እንጽፍ ነበር፡፡ እና ይኼ ነበር ከባዱ ጊዜ፡፡ ከሱዳን ወደ ናይጄሪያ ስሄድ እንደ እንግሊዞቹና ፈረንሣዮቹ እንደ አንድ የውጭ አገር ተቀጣሪ ሆኜ ሁሉ ነገር ተሟልቶልኝ መሥራት ጀመርኩ፡፡ ሁለት መኪኖች፣ ሾፌር፣ የተሟላ ቤት ሁሉ ተሰጠኝ፡፡ ሁሉ ነገር ተሟላ፡፡ የመጀመርያ የጌትነት ኑሮ የጀመርኩት ያኔ ነው፡፡ ናይጄሪያ ከእነሱ ጋር ሰባት ዓመት ሠራሁ፡፡ መጀመርያ ናይጄሪያ እንደሄድኩኝ ግን ሌሎች የገጠሙኝ ዕድሎች ነበሩ፡፡ ያኔ የአፍሪካ የጠለፋ ዋስትና ኩባንያ ገና መቋቋሙ ነበር፡፡ ከእንግሊዞቹ ጋር ተደራድሬ ጨርሼ በነበረበት ወቅት የአፍሪካ የጠለፋ ዋስትና ኩባንያ እንውሰድህ አሉኝ፡፡ የሚቀጥሩኝ ግን አለቃ አድርገው ሳይሆን በተራ ሠራተኛነት ነው፡፡ እኔ ደግሞ ለእንግሊዞቹ ቃል ገብቻለሁና ይህንን ማጠፍ አልችልም አልኩ፡፡ ደግሞም ኩባንያው እንግሊዞቹ በቀጠሩኝ ደረጃ ወይም ጥሩ የሚባል ክፍያ ለመክፈል ያኔ አቅም አልነበረውም፡፡ እነሱ ያሟሉልኝን ነገር ለማሳካት አይችልምና አልችልም አልኩ፡፡ ከዚህም ሌላ ሞንሮቪያ ውስጥ ያለ ኢንሹራንስ ካምፓኒ ኦፍ አፍሪካ ይባል የነበረ ኩባንያ ውስጥ ይሠራ የነበረ አንድ ጓደኛዬ ደግሞ አለቆቹ እኔን እኛ ጋ እንዲሠራ አምጣ ብለውት ጋበዘኝ፡፡ እሱንም ቃል ገብቻለሁ ከቃሌ አልዛነፍም አልኩ፡፡ እንዲህ ካልኩ በኋላ ዝም በልና ጋብዘውና ይምጣ ይየን፣ ምናልባት ካልተመቸው ሊመጣ እንዲችል ብለዋልና እባክህ ናና አነጋግራቸው አለኝ፡፡ ሁሉንም ወጪ እነሱ ይችላሉ ብሎ ጓደኛዬ ወተወተኝ፡፡ እኔም ደርሶ ለመመለስ ከሆነ ችግር የለም ብዬ ግብዣውን ተቀብዬ በአንዱ የእረፍት ቀን ሄድኩ፡፡

ሞንሮቪያ ደርሼ ስመለስ በአክራ ነው የምመጣው፡፡ ሌጎስ፣ አክራ፣ ሞንኖቪያ ትሄዳለህ፡፡ እንደገና ከሞኖሮቪያ አክራ ትመጣና ወደ ሌጎስ ትመለሳለህ፡፡ አክራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይመላለሳል፡፡ የአየር መንገድ ሠራተኞች አክራ ሲመጡ የት ሆቴል እንደሚያርፉ አውቃለሁ፡፡ ባለቤቴን ያገባኋት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኛ ሆና ስትሠራ ነው፡፡ ከተጋባን በኋላ ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለቃ ሌላ ሥራ ነበር የምትሠራው፡፡ እኔ ከተሰደድኩ በኋላ ለመኖር የግድ መሥራት ነበረባትና እንደገና ተመልሳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገብታለች፡፡ እኔም አክራ እንደ ደረስኩ ከአውሮፕላን ጣቢያው በቀጥታ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ሄጄ ክፍል ያዝኩ፡፡ እዚያ የያዝኩት ምናልባት ባለቤቴን የሚያውቋት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች ካሉ አወራለሁ ብዬ ነው፡፡ ክፍሌ እንደገባሁ ወደ ኦፕሬተር ደወልኩና እንዲያው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰዎች ይኖሩ ይሆን? ብዬ ጠየቅኩ፡፡ አዎ! አሉ አሁን በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚሄዱ አሉ፣ ሌሎች በምትካቸው የሚመጡም አሉ አለችኝ፡፡ እባክሽ እንዲህ የሚባል ሰው ይኖር ይሆን ወይ? ብዬ የሚስቴን ስም ጠቅሼ ጠየቅኳት፡፡ አዎ! እንዲህ ያለ ክፍል ውስጥ ናቸው ተባልኩ፡፡ ይህ ተዓምር ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በነገራችን ላይ እርስዎ ከወጡ በኋላ ከባለቤትዎና ከቤተሰብዎ ጋር አይገናኙም ነበር?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- እንዴት ተደርጐ!

ሪፖርተር፡- ለምን?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- እንዴ ምን ማለትህ ነው? አንገቷን ይቁረጧት እንዴ! አገር ጥዬ በመውጣቴ ኮብላይ ተብያለሁ እኮ፡፡ ከእኔ ጋር ስትጻጻፍ፣ በስልክ ብታወራ ብትገኝና ከእኔ ጋር ስትገናኝ ሪፖርት ቢደረግ አደጋ ነው፡፡ ሕግ እኮ ወጥቷል፡፡ ቀጥታ ልትረሸን ወይም ልተታሰር ትችላለች፡፡ መገናኘት አይፈቀድም፡፡

ሪፖርተር፡- ከቤተሰብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሳይኖርዎት፣ ከባለቤትዎም ጋር ሳትገናኙ ምን ያህል ጊዜ ቆያችሁ ማለት ነው?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ሁለት ዓመት፡፡ በዚህ በአጋጣሚ ስንገናኝ ግን ሁለት ዓመት አልሞላም ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- እዚያ ሆቴል መኖራቸውን ሲያውቁ ምን አደረጉ?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ይህንን ነው ተዓምር ያልኩህ፡፡ ደወልኩላት ደነገጠች፡፡ ሌላው የሚገርመው አጋጣሚ ደግሞ የእኔና የእሷ ወዳጆች ደግሞ ቅድም የነገርኩህና ብሉ ናይል ኢንሹራንስ አለቃዬ የነበረው (አቶ አባተ) እሱ አፍሪካ ሪኢንሹራንስ ኮርፖሬሽን ውስጥ ‹አንደርራይተርነት› ተቀጥሮ ቢሮው የሚጀምረው አክራ ነው፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሲዊዘርላንድ ከእኔ ጋር ሪኢንሹራንስ አብሮኝ የሠለጠነ ኤድዋርድ ሜንሳ የሚባል የአፍሪካ ሪ ጄኔራል ማናጀር ሆኖ ተሹሟል፡፡ ይኼ ሰው አባተን ‹አንደርራይተር› አድርጎ አክራ ወስዶታል፡፡ ሌላ ቦታ ስለሌላቸው ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ነው ያለው፡፡ በደወልኩላት ጊዜ ጋሽ አባተም እንዲህ ያለ ክፍል ነው አለችኝ፡፡ እዚያ እሱ ክፍል እንገናኝ ተባባልን፡፡ ምክንያቱም እኔና እሷ ፊት ለፊት መታየት የለብንም፡፡ እሱ ክፍል ተገናኘን፡፡ ተሳስመን ትንሽ ተላቀስን፡፡ ከዚያ ስለቤተሰቦቼ ጠየቅኩ ነገረችኝ፡፡ ከዚህ በኋላ ምን እናድርግ? ምን ላድርጋችሁ?  አልኩኝ፡፡ መውጣት ትፈልጊያለሽ ወይ? ስላት አዎ አለችኝ፡፡ ታዲያ እንዴት እናድርግ አሁን? ከተስማማን ዘዴውን ነው የምንፈልገው ብለን ተነጋገርን፡፡ ተስማማን፡፡

ሪፖርተር፡- ከባለቤትዎ ጋር እዚያች ክፍል ውስጥ ምን ያህል ቆያችሁ?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ከ30 እስከ 35 ደቂቃ ነው የቆየነው፡፡ ምክንያቱም ወደ ኤርፖርት መሄድ ነበረባት፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ መብረር ስለነበረባት ከዚያ የበለጠ መቆየት አልቻለችም፡፡

ሪፖርተር፡- ባለቤትዎ ሆስተስ ስለነበሩ ማለት ነው?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- አዎ፡፡ ከዚያ ይህ በመሆኑ የእግዚአብሔርን ተዓምር አድንቄ ወደ ሌጎስ ተመለስኩ፡፡ ከዚያ በኋላ ምንድነው የሚደረገው ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ጣሊያን ያሉ ወዳጆቼን የድርጅታቸውን ደብዳቤ መጻፊያ ወረቀት እንዲሰጠኝ ጠየቅኩና ሰጡኝ፡፡ በዚያ  ለኮስሞቲክስ ኮንሰልታንት ሥራ ለሚስቴ ቆንጆ የቅጥር ደብዳቤ በእንግሊዝኛ ጽፌ በፖስታ እንዲደርሳት አደረግኩ፡፡ ይህንን ይዛ ጣሊያን ኤምባሲ ቀርባ ዋስ ጥሪ ስትባል ወዳጄን ይስሃቅ አብዱላሂ ዋስ ጠርታ ቪዛ ተሰጣት፡፡ ሁለት ልጆቻችንን ይዛ ጣለሊያን አገር ሄደች፡፡ ጣሊያን ያሉ ወዳጆቼ ዘንድ አሥር ቀናት ቆይታ ወደ ሌጎስ እኔ ጋ መጣች፡፡

ሪፖርተር፡- የልጆችዎ ዕድሜ ምን ያህል ነበር?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- እ.ኤ.አ. በ1987 የስድስትና የስምንት ዓመት ልጆች ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ታሪክ ልመልስዎትና አዲስ ዓመት ነውና ስለአገር ምን ያስባሉ? በአዲሱ ዓመት ምን ቢሆን ይመኛሉ?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- በጎ በጎውን ማሰብ እፈልጋለሁ፡፡ አንዳንድ የሚያሰስበኝ ነገር ቢኖርም በጎ እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ ልበ ሰፊ መሆን የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው፡፡ በጎ በጎ ነገሮች ያሉ ቢሆንም፣ ለዋናው ችግራችን መፍትሔ አግኝተናል ወይ?  የሚለው ያሳስበኛል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አንድ ኢኮኖሚያዊ ኃይል ታይታ መሄድ አለብን፡፡ ከጥላቻ ወጥተን መተሳሰብና መተባበር አለብን፡፡ አሁን እኮ ወጣቱ ትውልድ እየበዛ እንደ አሽን እየፈላ ነው፡፡ መንግሥት ለዚሁ ሥራ መስጥት የሚችልበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡ አዎ! አሁን አሁን መንግሥት ይናገራል፡፡ ብቻዬን እኔ እነዚህን ሁሉ መቅጠር አልችልምና ለሌሎቻችሁም የግል ዘርፉም መሥራት አለበት ይባላል፡፡ ግን አሁንም ለግል ዘርፉ ዕድል እየተሰጠ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት በምን ዓይነት?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ሰሞኑን ሲባል ነበር፡፡ ስለተግዳሮቶች ስናወራና ሲጻፍ ነው የከረመው፡፡ አሁን እየተፍጨረጨርን ነው፡፡ እስካሁን እኮ ሥራንና ሠራተኛን ሳናገናኝ ነው የቀረነው፡፡ ሰዎችን በችሎታቸው ሳይሆን በታማኝነታቸው ስንሾም ከርመናል፡፡ ከልቤ የምልህ ዛሬ የአገር ችግር የማኔጅመንት ችግር ነው፡፡ አንዳንዶቹን ነገሮች ስታይ እንዴት እንዲህ ሊሆን ቻለ? በቀላሉ እኮ ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮች ሲባዙና ሲያብጡ ታያለህ፡፡ ለምን ይህ ይሆናል? ከመንገድ አጠቃቀማችን ጀምሮ ያሉ ችግሮንም ስታይ ምን ውስጥ እንዳለን ይነግረሃል፡፡ ያለ እረኛ መሄድ የማይችል ትውልድ እየፈጠርን ነው፡፡ አንዳንዴ እኮ ፖሊስ አያየኝም ብሎ ካሰበ አንተ በምትሄድበት መንገድ ከፊት ለፊት ይመጣል፡፡ ይኼ ምን ማለት ነው? ወይ እግዚአብሔርን አልፈራን፣ ወይ ግብረ ገብነት የለንም፡፡ እውነት በአዲስ አበባን መንገድ ችግር የፈጠረው ጠቦ ነው? እውነት መኪኖቹ እጅግ በዝተው ነው? በፍፁም! የእኛ የራሳችንን ችግር የሚያንፀባርቅ ነገር ነው በየመንገዱ የምታየው፡፡ ያለመዞሪያው ሲዞር ታያለህ፡፡ አሥር ሜትር ነድቶ ደንበኛ ማዞሪያ እያለ ይህንን ማድረግ አይፈልግም፡፡ ከእሱ ሌላ ሌላ ሰው እንደሌለ አድርጎ የሚያስብና የሚሠራ ትውልድ እየመጣ ነው፡፡ ትልቅ የማኔጅመንት ችግር ነው፡፡ እኔ የማየው ነገሮችን እያወሳሰብን ነው፡፡ ለማንኛውም እኔ የኢንሹራንስ ባለሙያ እንደ መሆኔ መጠን ቀና አሳቢ ነኝ፡፡ ማለቴ በጎ በጎውን ማየትና ማሰብ ብዙ ጊዜ የኢንሹራንስ ሰዎች እንዲህ ናቸው፡፡ ነገር ግን አሁን ይህንን አንድ ሁለት ዓመት የማየው ሁኔታ ያሳስበኛል፡፡ እየሞከርን እንደሆነ ይገባኛል፡፡ ግን ገና እውነተኛውን የችግሩን እምብርት አግኝተነዋል ወይ? መፍትሔውንስ በትክክል አግኝተዋል ወይ? የሚለው ያሳስበኛል፡፡ አሁንም ብዙ መሥራት አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- አሉ ለሚባሉት ችግሮች መፍትሔ ብለው የሚያስቡት ምንድነው? ከዚህ አንፃር በአዲሱ ዓመት ምን ቢሆን ይላሉ?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- መጀመርያ ሕዝቡን አዳምጡት ነው፡፡ እኔ በተለያዩ ሚዲያዎች የገለጽኩት መንግሥት ሕዝቡን ያድምጥ ነው፡፡ እኛ እናውቅልሃለን የሚለውን አመለካከት እንተው፡፡ የተሻለ እናውቅም ይሆናል፡፡ ግን እናውቅልሃለን ከማለት ይልቅ ማዳመጥ ያስፈልጋል፡፡  ዶክተሩ በሽተኛውን እስኪ የቱ ጋ ነው የሚያምህ ብሎ ነው መጠየቅ ያለበት፡፡ እስከቻለ ድረስ ማድመጥ አለበት፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ወደ መፍትሔና መድኃኒት የምትሄደው፡፡ ሕዝቡን እያናገርነው ነው ወይ? እኛው ተሰብስበን እኛው ራሳችን መፍትሔ አስቀምጠን አይሆንም፡፡ አንቀጽና ንዑስ አንቀጽ ጠቅሶ መፍትሔው ይኼ ነው ማለት አይደለም፡፡ መልሱ ማስፈራራት አይደለም፡፡ መልሱ ማዳመጥ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- አሁን መንግሥት የሕዝብን ጥያቄ  እየመለስኩ ነው እያለ ነው፡፡ በቅርቡም ይህንኑ የሚያንፀባርቅ መግለጫ አውጥቷል፡፡ ሕዝቡን አዳምጬ መልስ እየሰጠሁ ነው ብሏል፡፡

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ምን ዓይነት መደማመጥና መገማገም እንደተደረገ አላውቅም፡፡ ሁሌም ሾልኮ የሚወጣ ወሬ ነው የምንሰማው፡፡ እንዲህ ተባባሉ፣ እንዲህ ተደራረጉ የሚለውን ነው የምንሰማው፡፡ እኔ አሁን አንዳንድ የሚባለውን ነገር ለማመንም ያቅተኛል፡፡ ደግሞ የእኛ የሕዝብ ግንኙነት ዘመቻ ሁሉ ነገር አልጋ ባልጋ ነው ተብሎ ነው፡፡ ትንሹን ጥፋት ትልቅ አድርጎ የሚያገዝፈው እሱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ያብራሩልኝ?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ብዙ ጥሩ ነገሮች ተሠርተዋል፡፡ የሚያኮሩ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ኮርቻለሁ፡፡ ረሃብን፣ የዝናብ ዕጦትንና የሚያስከትለውን ጥፋት መቋቋም ተችሏል፡፡ ከሳዑዲ ዓረቢያ የመጡ ዜጎችን ማቋቋም መቻል ራሱ ከዚህ ቀደም ያልነበረ አቅም ነው፡፡ ከዚህ ቀደም እንዲህ ያሉ ችግሮች ሲገጥሙ ተነስተን ዘምቢላችንን ይዘን ልመና ነበር የምንሄደው፡፡ ይህንን ሁሉ መቋቋም መቻል ትልቅ አቅም መፍጠሩን ያሳይሃል፡፡ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን ስላደረግን ሌላው ነገር ሁሉ አልጋ አልጋ አድርገን መውሰድ የለብንም፡፡ ሁሉ ነገር ጥሩ እየሄደ ነው ማለቱ ደግሞ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ብዙ ጉድለቶች አሉ፡፡ ድክመቶችን ማመን ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ለአዲሱ ዓመት ምን አስበዋል?  ለመሥራት ያሰቡት ነገር አለ?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ለዚህ ዓመት ትልቅ አድርጌ የያዝኩዋቸው ፕሮጀክቶች አሉኝ፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች ተሰብስበን ውይይት እያደረግን ያለንበት አንድ ጉዳይ አለ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከክቡር የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጋርም ተነጋግረናል፡፡

ሪፖርተር፡- ጉዳዩ ምንድነው? ምን ለመሥራት አስባችሁ ነው?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ለምሳሌ ጎርፍ መጣ ሲባል ሕዝቡና የግሉ ዘርፍ ድረሱልኝ ይባላል፡፡ ረሃብ መጣ፣ የሳዑዲ ተመላሾች ሊወሩን ነው፣ ምን እንሁን ይባላል፡፡ እርግጥ መንግሥት ወደ ሕዝቡ ተመልሶ ይህንን ነገር አድርጉ ማለቱ ትክክል ነው፡፡ አሁን የቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንቶችና አንዳንድ ይጠቅማሉ የተባሉ ሰዎች የተወሰነ ስብሰባ አደረግን፡፡ አሁን ‹ኮርፖሬት ኢትዮጵያ ሶሻል ሪስፖንስቢሊቲ ፈንድ› ለማቋቋም ነው ዕቅዱ፡፡  

ሪፖርተር፡- ይህንን ሐሳብ እርስዎ ነዎት ያመጡት?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- አይደለሁም፡፡ ስለሳዑዲ ተመላሾች ቁጭ ብለን ስናወራ በዘላቂነት አንድ ነገር ብናደርግ ከሚል ተነስተን ነው፡፡ ማንኛችንም የእኔ ሐሳብ ነው ልንል አንችልም፡፡ ነገር ግን ተሰብስበን በጥናት ላይ የተመሠረተ አንድ ፈንድ እንዲቋቋም ለማድረግ ነው ሐሳቡ፡፡ ፈንዱ በተለያዩ ምንጮች የሚደገፍ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ተቋም ሠርቶ ግብሩን ከፍሎ፣ መጠባበቂያውን ወስዶ ሁሉን ነገር ከጨረሰ በኋላ፣ ለባለ አክሲዮኖች የሚያከፋፍለው መቶ ብር ካለ፣ ከዚያ መቶ ብር ላይ አንድ ብሩን ለኮርፖሬት ኢትዮጵያ ሶሻል ሪስፖስቢሊቲ ፈንድ እንዲውል ያሰበ ነው፡፡ ይኼ ፈንድ ትልቅ ቦርድ ተቋቁሞለት የሚሠራ ነው፡፡ ነገ መንግሥት አንዳንድ ጊዜ የሚያነጋግረውና የሚያወያየው እንዲሆን ነው ፍላጎታችን፡፡ ፈንዱን መንግሥት እንደፈለገ የሚጠቀምበት ሳይሆን፣ መንግሥትና ኮርፖሬት ኢትዮጵያ የሚስማሙባቸውና ለኢትዮጵያ ቀዳሚ ጉዳዮች ድጋፍ የሚያደርግ ነው፡፡ በችግር ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለወጣቱ ሥራ መስጠትና ማሠልጠን የመሳሰሉ ዓላማዎች አሉት፡፡ ምክንያቱም እንደ አሸን የሚፈሉት ወጣቶች ነገ ይዘውን ይጠፋሉ፡፡ ተስፋ ከቆረጡ በምን ታቆማቸዋለህ? ስለዚህ ወጣቱ ትውልድ ተስፋ እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መሥራት አለብን፡፡ ቢዝነሶች የሚሠሩት የተመቻቸ አካባቢ ሲኖራቸው ነው፡፡ የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን ‹ግሎባል ኮምፓክት› የሚባል ፈጠሩ፡፡ ቢዝነሶች ፕሮብሌም ፈጣሪዎች ብቻ መባል የለባቸውም፡፡ ለመፍትሔውም ትልቅ መዋጮ ማድረግ ያለባቸው እነሱ ናቸው፡፡ ይህ የግሎባል ኮምፓክት አይዲያ ትልቅ ነው፡፡ የእኛም ሐሳብ ከዚህ ጋር ይዛመዳል፡፡ ነገ አንድ ነገር ሲፈጠር እባካችሁ ለዚህ አምጡ ከማለት፣ በቋሚነት ከመንግሥት ጋር ተባብረን መሥራት ይሻላል፡፡ የአገር ችግር ነው ስንል ሁለታችንም ተስማምተን የምናደርግበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሌላው በዚህ ዓመት አሳካለሁ ብለው ያሰቡት ሁለተኛው ጉዳይ ምንድነው?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- መቼም ፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ስላለሁ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ተግባር ነው፡፡ እሺ የቦርድ ዳይሬክተር ሆነን ተመረጥን ግዴታችንስ በደንብ አድርገን እናውቃለን ወይ? የተጣለብንን ወይም የተቀበልነውን ግዴታ ሳናሟላ ብንቀርስ የሚከተለው ቅጣት ገደቡ የት እንደሆነ እናውቀዋለን ወይ? ለዚያ ዝግጁ ነን ወይ? ከሚል ተነስተን የምንሠራው ነው፡፡ በኋላ ስቲሪንግ ኮሚቴ ተቋቁሞ የኢትዮጵያ የባንክ ዳይሬክተሮች የምክክር መድረክ የሚል እየሠራን ነው፡፡ አንደኛ የተሻለ ዳይሬክተሮች እንድንሆን ሥራችንን እንድናውቅና የገባንበትን ግዴታ የምንወጣ እንድንሆን ሥልጠና በኮርፖሬት ገቨርናንስ አንድ ላይ ሆነን እንድናካሂድ፣ ሁለተኛ ባንኮቻችንንና ባለአክሲዮኖቻችንን እንዲረዳ ነው፡፡ ተቆጣጣሪውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን እንድንረዳ፡፡ ምክንያቱም ከፋም ለማ ከሕዝብ የተሰበሰበም ቢሆን መጀመርያ ግን ብንከስርም ብናተርፍም ካፒታል አውጥተን ባንኮቹን አቋቁመናል፡፡ ስለዚህ ባንኮቹ ከሚያበድሩት የሚበልጠው የአስቀማጮች  ነው በማለት ሙሉ ለሙሉ ከሥዕሉ ውጪ ማድረግ ትክክል አይደለም፡፡ ስለዚህ ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ ከብሔራዊ ባንክ ጋር በመነጋገር ስለባንኮች መልካም አስተዳደር፣ የተሻለ ሥራ ለማከናወንና ለመመካከር መድረክ መኖሩ አስፈላጊ ነው ከሚል ነው፡፡ አሁን ይህንን አምነንበታል፡፡ ስቲሪንግ ኮሚቴው ሰባት ስብሰባዎች አድርጓል፡፡ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የመተዳደሪያ ደንቡ ለሁሉም የባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢዎች ይቀርባል፡፡ በዚህ ጉዳይ የብሔራዊ ባንክ ገዥን አነጋግረናል፡፡ የስቲሪንግ ኮሚቴ አባላት የአምስት ባንኮች ቦርድ ሰብሳቢዎች ነን፡፡

ሪፖርተር፡- ከብሔራዊ ባንክ ገዥው ጋር በተነጋገራችሁበት ወቅት እንዲህ ባለው ነገር ላይ ስምምነት ደርሳችኋል?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ከእሳቸው ጋር 1 ሰዓት ከ45 ደቂቃ አውርተናል፡፡ መስማማት አለመስማማት ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ አማከርናቸው፡፡ እሳቸውም የሚጠቅም ነገር እንድትሠሩ እፈልጋለሁ፡፡ ይኼ ከተቋቋመ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበርን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ስለሚፈልገው፣ እሱን የሚተካ መሆን የለበትም ብለውናል፡፡ ይኼ መድረክ ነው ማኅበር አይሆንም፡፡ ቢከፋም ቢለማም የባንኮች ፕሬዚዳንቶችን የሚሾመው ቦርድ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ያፀድቅልናል እንጂ ሿሚዎች እኛ ነን፡፡ ስለዚህ ከባንኮች ማኅበርም ጋር ተደጋግፈን ለመሥራት፣ እነሱንም ለማገዝ ይኼ መድረክ አስፈላጊ ነው ስንል ይኼማ ሕጋዊ መብታችሁ ነው፣ ሥሩ ተብለናል፡፡ እንሠራለን፡፡  

ሪፖርተር፡- ከብሔራዊ ባንክ ጋር የሚኖራችሁ ግንኙነት እንዴት ይሆናል? ለምክክር ነው? ወይስ ሌላም ዓላማ ይኖረዋል?

አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ለመመካከር ነው፡፡ ምክንያቱም የቀን ገቢ ግምት ይህንን ሁሉ ንትርክ ያመጣው መጀመርያውኑ በበቂ ሁኔታ ስላልተመከረበት ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ የአገሪቱን የፋይናንስ ፖሊሲ ለማስፈጸም ብዙ ጊዜ በባንኮች ማኅበር አማካይነት ይሠራል፡፡ ይኼኛው ግን ምናልባት አዲስ መመርያ ለማውጣት ወይም የወጡ መመርያዎችን ለማሻሻል፣ በአፈጻጸሙ ላይ ክትትል ለማድረግና ለመገምገም ይህንን የምክክር መድረክ በዓመት ሁለት ጊዜ ከብሔራዊ ባንክ ጋር ተገናኝቶ መነጋገር እንዲቻል ነው፡፡ ለማስተማር ነው ብዬሃለሁ፡፡ ስለዚህ ይኼኛው ደግሞ የባንክ ባለቤቶችን መጀመርያውኑ ስለሚሆኑ ነገሮች ማወያየትና ማሳመን ከተቻለ፣ ለሚፈጸመው ነገር በሙሉ የመጀመርያውን 50 በመቶ መንገድ መጨረስ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ነገር ላይ በጣም አጥብቄ እየሠራሁ ነው፡፡ እነዚህን የተጀመሩ ሥራዎች በዚህ በአዲሱ ዓመት እቀጥላለሁ፡፡ ደግሞም ብዙ በጎ ፈቃድ አለ፡፡ የስቲሪንግ ኮሚቴው አባላት አብረውኝ ይሠራሉ፡፡ የእኔ ኃላፊነት በስቲሪንግ ኮሚቴው የሚደረጉትን ማጥናትና ከዚያ በኋላ ለወጣቱ ትውልድ ሥራውን ማስተላለፍ ነው፡፡ በምንስማማበት መሠረት እንዲሠሩ ነው፡፡ መቼም በአሮጌ ፈረስ ዘለዓለም ሲጋለብ አይኖርም፡፡ ስለዚህ ይህንን ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ እነዚህ ሁለት ጉዳዮች በአሁኑ ጊዜ ለእኔ እንደ ትልቅ ግቦች አድርጌ የምወስዳቸው ናቸው፡፡ የግል ግቦች አይደሉም፡፡  ለእኔ የመንፈስ እርካታ የሚሰጠኝ፣ በሕይወቴም ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እየሄድኩ ስለሆነ ይኼን ጥሩ መደምደሚያዬ አድርጌ ነው የምቆጥረው፡፡