Skip to main content
x

የገበያው እጥንቅጦች በአዲስ ዓመት ይወገዱ

በ2009 ዓ.ም. የሙዝ ዋጋ ጭማሪ ከሌሎች ጭማሪ ካሳዩ ሸቀጦች መካከል አንዱ እንደነበር ይጠቀሳል፡፡ በ2009 አጋማሽ የአንድ ኪሎ ሙዝ የችርቻሮ ዋጋ 15 ብር ነበር፡፡ የሙዝ ዋጋ ከዚህ በላይ ጨምሮ እንደማያውቅ ይነገራል፡፡ ይሁንና ካለፉት ሦስት ወራት ወዲህ ግን ዋጋው ቀስ በቀስ ሲያሻቅብ ቆይቶ፣ በነሐሴ ወር 18 ብር ደርሷል፡፡ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ደግሞ የአንድ ኪሎ የሙዝ የችርቻሮ ዋጋ 24 ብር ደርሷል፡፡

እንደ ሙዝ ሁሉ ፓፓያም ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የዘንድሮውን ያህል ዋጋ ጭማሪ እንዳልታየ የሚናገሩት የአትክልትና ፍራፍሬ ባለመደብሮች፣ የፓፓያ ዋጋ ከአንድ ወር ወዲህ ተለውጧል ይላሉ፡፡

በዓመቱ አጋማሽ አንድ ኪሎ ፓፓያ እስከ አሥር ብር ሲሸጥ ቆይቶ፣ ቀስ በቀስ ወደ 15 ብር ከፍ ባለበት ወቅትም ፓፓያ ሲሸጡ የቆዩት ነጋዴዎች፣ በአሁኑ ወቅት አንዱን ኪሎ ፓፓያ ከማከፋፈያ የምናወጣበት ዋጋ እስከ 25 ብር ደርሷል ይላሉ፡፡ ስለዚህም የችርቻሮ ዋጋው ከ30 እስከ 35 ብር እንደደረሰም ይናገራሉ፡፡

ፓፓዬ በዚህ ያህል ዋጋ የተሸጠበትን ወቅት አናስታውስም የሚሉት ነጋዴዎች፣ የአንድ ኪሎ ቲማቲም ዋጋ 40 ብር የደረሰውም በዚህ ዓመት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ሆኖም ገበያው ተረጋግቶ፣ ቲማቲም በኪሎ ከአሥር ብር በታች እየተሸጠ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ የቲማቲም እጥረት የተፈጠረው፣ በአምራችነቱ የሚታወቀው አካባቢ በበሸታ በመጠቃቱ ቢሆንም፣ በሽታ ካልነካቸው አካባቢዎችም ቢሆን ለገበያ ሲወጣ የነበረው ቲማቲም ዋጋ 40 ብር ደርሶ ነበር፡፡

እንዲህ ያለ የዋጋ ጭማሪ በተለያዩ ምርቶች ላይ ታይቷል፡፡ ከእኛ አገር የገበያ ባህርይ አንፃር አንዳንድ ምርቶች ዋጋቸው በአንድ አጋጣሚ ከጨመረ በኋላ ወደነበረበት መጠን የሚቀንስበት አጋጣሚ እምብዛም በመሆኑ፣ እንደ ሙዝና ፓፓያ ያሉ ምርቶች ሰሞነኛ ዋጋ ሲበዛ ግነት የታየባቸው እንደመሆናቸው መጠን፣ በአጋጣሚ የናረው ዋጋ በዚያው እንዳይቀጥል ምኞታችን ነው፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያሉ የዋጋ ለውጦች የሚከሰቱበትን እውነተኛ ምክንያት ማረጋገጥና መረጃ ማጠናቀር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን፣ በግብይት ሰንሠለቱ ውስጥ ያሉ ደላሎችና ሌሎችም የአየር በአየር ነጋዴዎች ገደብ የሚያኙበትን አሠራር ማጎልበት ይገባል፡፡ ለገበያ መተረማመስ ምክንያት ከሚባሉት ውስጥ በለተይ ሕገወጥ ደላሎች ማቆሚያቸው መቼ እንደሚሆን ይናፍቃል፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ክፍተቶች በአዲሱ ዓመት ይታረሙ ዘንድ ምኞታችን ነው፡፡

በተጠናቀቀው ዓመት የሸመታና የአገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ፣ ብዙ ትችት ሲቀርብባቸው ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ በየመንደሩ ተጋግሮ ለገበያ የሚቀርበው እንጀራ ነው፡፡ ከሰፊው የእንጀራ ገበያ አኳያ፣ የጥራቱ ጉዳይም አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡ ችግሩን ለመቆጣጠር ተገቢው ዕርምጃ እየተወሰደ ባለመሆኑ እየተባባሰና ከቁጥጥር ውጭ በመሆን የበላተኛውን የጤንነት ሥጋት እያናረው ነው፡፡

ይህም ሆኖ ግን በ2009 አጋማሽ ወቅት የሰማነው መልካም ወሬ ተስፋ አሳድሮብን ነበር፡፡ ሊዘልቅ አልቻለም እንጂ፡፡ ከጀሶና ከሳጋቱራ ተቀይጦ የሚጋገር እንጀራ ሲያዘጋጁ የተደረሰባቸው ግለሰቦች በፖሊስ ተይዘው የሚጋገሩበት ቦታ ከሕዝብ በይፋ ታይቶ፣ ጉዳዩ በሕግ ስለመያዙ ምንሰማም፣ ቀጣዩ ሒደት ግን የውኃ ሽታ ሆኗል፡፡

ዕርምጃው ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም፣ በተመሳሳይ ድርጊት የተሰማሩት ላይ ተጨማሪ ዕርምጃ ሲወሰድ አለመታየቱ ግን የአንድ ሰሞን ወሬና ጉሸት ብቻ አድርጎታል፡፡ ስለዚህ አሁንም በአንድ ሰሞን በተደረገ ቁጥጥር ተላላፊቹን ለሕግ ለማቅረብ እንደተሞከረው ሁሉ በአዲሱ ዓመትም እንዲህ ያለውን ዕርምጃ በመውሰድ ሸማቹን መታደግ ያስፈልጋል፡፡

ያላባራው የዘይትና የስኳር ጉዳይ ዛሬም ዘላቂ መፍትሔ አላገኘም፡፡ የቱንም  በቂ ምርት ገበያው ውስጥ አለ ቢባልም፣ ጊዜ እየጠበቀ የሚከሰተው እጥረት ግን ባጠናቀቅነው ዓመት ደጋግሞ ታይቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እጥረቱ ብቻ ሳይሆን፣ ከስኳርና ከዘይት ስርጭት ጋር ተያይዞ የሚታየው ችግር የሸማቾችም ጭምር እየሆነ ነው፡፡

ለግል ፍጆታቸው እንዲጠቀሙበት ከሸማቾች ማኅበራት የሚገዙትን ዘይት አየር በአየር የማሸገርና ለነጋዴ የማስረከብ ልማድ በርትቷል፡፡ ለቤት ውስጥ ፍጀታ የገዙትን ዘይትና ስኳር ከሸማቾች ማኅበር መደብር ፈንጠር ብለው አድፍጠው ለሚጠብቁ ነጋዴዎች አትርፈው ሲሸጡ እየታዩ ነው፡፡ ምንም እንኳ ይህም በራሱ ኢኮኖሚያዊ ሌላ ገጽታ ቢኖረውም፣ ከአቅርቦት አኳያ ሲታይ ግን ድርጊቱ የምርት ሥርጭት ላይ እክል እየፈጠረ ነው፡፡ እርግጥ ነው በትርፍ የገዛው ነጋዴ ምርቱን ካልሸሸገው በቀር ዞሮረ ዞሮ በዋጋ ጭማሪም ቢሆን ምርቱ ገበያ ላይ መታየት ነበረበት፡፡ ይሁንና በአንድ በኩል ስኳርና ዘይት በተገቢው ጊዜ እየመጣልን አይደለም እየተባለ በሌላ በኩል ግን ለነጋዴ መቸብቸብ ከሸማቹ የሚጠበቅ አይደለም፡፡

2010 ዓ.ም. እንዲህ ካሉ ድርጊቶች የምንታቀብበት ይሆን ዘንድ እናስባለን፡፡ የመንግሥት ችግር እንዳለ ሆኖ፣ እኛም ሸማቾች ሲጎልብን የምናማርረውን ያህል ያልተገባ ድርጊት ሲፈጸም እያየን ዝም ማለት አግባብ አይሆንም፡፡

በበዓል ሰሞን የምንመለከተው የቀንድ ከብቶች እንቅስቃሴ ዛሬም ጆሮ ያልተሰጠው ጉዳይ ሆኗል፡፡ የቀንድ ከብቶች በየጎዳናው ከእግረኛና ከመኪና ጋር እየተጋፉ ከሚነዱ ይልቅ በተሽከርካሪዎች ተጭነው እንዲዘዋወሩ ለማድረግ የተወሰደ ዕርምጃ የለም፡፡ ዜጎችን ከአደጋ ለመታደግና የመንገድ ትራፊክ ሕጎችን ማክበር ካስፈለገን፣ እንዲህ ያለው ጉዳይ ሊታሰብበት እንደሚገባ መጠቆም ይገባል፡፡

በግብይት ውስጥ የሚስተዋለው ሌላው ችግር ተመሳሳይ ምርቶችን በሕገ ወጥ መንገድ በማምረት ወይም በማሥመረት ለገበያ ማቅረብ ነው፡፡ ዘንድሮ የኮስሞቲክስ ዕቃዎችን፣ የሚጠጡ የፍራፍሬ ጭማቂዎችንና ሌሎችም ምርቶችን በየጉራንጉሩ ውስጥ ሲያመርቱ የነበሩ መያዛቸውን ሰምተናል፡፡ ለዓመታት እየሠሩ ገበያው እንደደራላቸው ማለት ይቻላል፡፡ በዚያው አንፃር አደጋውንም መገመት አያቅትም፡፡

ታዋቂ የኮስሞቲክስ ምርት ብራንድ በማስመሰል መርካቶ ጉራንጉር ውስጥ የሚመረቱ፣ ነገር ግን ከውጭ እንደመጡ ተደርገው የሚከፋፈሉት እነዚህ ‹‹ፎርጂድ›› በየጊዜ ይያዛሉ፡፡ ሆኖም እንዲህ ያለው ወንጀል የስንቶችን ቆዳ እንደገሸለጠ፣ የስንቶችን ጤና እንዳናጋ ማሰቡ ይሰቀጥጣል፡፡ ስለዚህ ለጤና አደገኛ ለሆኑ የሚችሉ ምርቶች ላይ ጠንካራ ቁጥጥር ያስፈልጋል፡፡ የምርቱን ምንጭ ሸማቾች የሚያውቁበት መንገድ ሊፈጠር ይገባል፡፡ በግብይት ወቅት ሸማቾችም እንዲህ ያለውን ልምድ በማዳበር ራሳቸውን ሊጠብቁ ይገባል፡፡ የዕቃዎችን ትክክለኛነት የማረጋገጥ ኃላፊነት የሸማቹም ጭምር ነውና፡፡

እንዲህ ያሉትን ችግሮች እየነቀስን ብናወጣ ብዙ በተናገር ነበር፡፡ ነገር ግን በ2009 መጨረሻ ሳምንት ወቅት ያደመጥነውን አንድ ጉዳይ ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡

ወሬው የተሰማው ከአንበሳ የከተማ አውቶቡስ ነው፡፡ ድርጅቱ እንደገለጸው፣ ላለፉት 70 ዓመታት ሲገለገልበት የቆየውን የአንበሳ ምስል በአዲስ እንደሚተካ ነው፡፡ ሙሉ የአንበሳ ምስልን የሚያሳየው የድርጅቱ ዓርማ ጭንቅላቱ ብቻ በሚታይ የአንበሳ ምስል ሊተካ ነው፡፡ ለውጡ ያስፈለገበት ምክንያት የቱንም ያህል ቢብራራ ዋናው ጥያቄ ግን የአንበሳ አውቶቡስ ወቅታዊ ችግር ዓርማ መቀየር ነው ወይ? የሚያስብል ነው፡፡

የድርጅቱ ቀዳሚ ተግባር የአገልግሎት አሰጣጡን ማቀላጠፍ ነው፡፡ በየቦታው የሚቆሙ አውቶቡሶችን በአግባቡ በመጠገን ለሕዝብ አገልግሎት ማብቃት ነው፡፡ አዳዲስ መስመሮችን መክፈትና የመሳሰሉት ማድረግና ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠል ነው፡፡

ዓርማውን ለመለወጥ የሚወጣው ወጪ ብቻ ሳይሆን፣ ዓርማውን ለመለወጥ ሲባል አውቶቡሶቹ ያለ ሥራ የሚቆሙበትን ጊዜ ማሰብም የዓርማ ለውጡ ጣጣው ሊበዛ ስለሚችል ለእንዲህ ያለው ነገር መሽቀዳደሙን ምን አመጣው? ያሰኛል፡፡ አገልግሎት ሰጪዎች አሠራራቸውን ፈትሸው በአዲሱ ዓመት ለሕዝቡ በቅን ማገልገል እንዲጀመሩ መመኝ ጸጋ ነው፡፡ የተረጋጋ ግብይት የሚፈጸምበት ከበዓድ ነገሮች ተቀይጦ የሚቀርብ ምርት የሚቀርበት፣ አምራችና ነጋዴም ሐቀኛ የሚሆኑበት፣ ሸማችም ቀልብ የሚገዛበት ዓመት ይሁን፡፡