Skip to main content
x

ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሯቸው ያስጠሩታል

እኛም አሜሪካኖቹ በሶሪያ የሚሠሩትን ግፍ ካላቆሙ ተመሳሳይ ዕርምጃ እንወስዳለን እንበላ፡፡ ምን ዓይነት ዕርምጃ? የአሜሪካ ባለሥልጣናት ወደ ኢትዮጵያ መግባት አይችሉም፡፡ እ… አንድም ዶላር በኢትዮጵያ ባንክ ውስጥ ማስቀመጥ አይችሉም፡፡ እኛ ግን የዶላር እጥረት አለብን እኮ፡፡ አይቻልም አልኩህ አይቻልም፡፡ እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ስለዚህ አሁን የነገርኩህን ነገር እንደ አቋም መግለጫ አድርገህ አዘጋጀው፡፡ ክቡር ሚኒስትር ይህ ግን የአቋም መግለጫ መሆን አይችልም፡፡ ታዲያ ምንድነው? የምኞት መግለጫ!

ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሀብት ጋ ይደውላሉ

አሁንማ ብዙ ነገር ተቀይሯል፡፡ ምንድነው የተቀየረው? ያው አሁን ጊዜው መቀየሩን ያውቃሉ፡፡ ምን አንተም እንደ ሌሎቹ ዶላር ምናምን ጨመረ ልትለኝ እንዳይሆን? እሱም እንዳለ ሆኖ ሌሎችም ለውጦች አሉ፡፡ መቼም የዋጋ ግሽበቱ እንዳትለኝ? ከእነዚህ በላይ በጣም የተለወጠ ነገር አለ፡፡ ምንድነው የተለወጠው ነገር? ይኸው እናንተ ራሳችሁ ጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ አይደላችሁ እንዴ? ሰውዬ ምንም የተለወጠ ነገር የለም፡፡ ክቡር ሚኒስትር ጥልቅ ተሃድሶውስ? እሱ ለሚዲያ ጥቅም ነው፡፡ እኔ ግን ፓርቲያችሁ እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ለውጦች ያሉ እየመሰለኝ ነው፡፡ አትሸወድ ምንም ለውጥ የለም፡፡ እኔ ግን እውነተኛ ተሃድሶ ውስጥ ገብቼ አቁሜያለሁ፡፡ ምንድነው ያቆምከው? እርስዎን መቀለብ!

ክቡር ሚኒስትሩ ማታ ቤት ሲገቡ ልጃቸውን ያስጠሩታል

ክፍል ውስጥ ገብተህ ተምረህ ቢሆንማ፣ እንደዚህ ዓይነት ውጤት ልታመጣ አትችልም? በጣም ከብዶኝ ነው ዳዲ፡፡ ሁለት ከመቶ ታመጣለህ? ፈተናው ለየት ባለ መልኩ ነበር የወጣው፡፡ ለየት ባለ መልኩ ማለት ምንድነው? በፊት ምርጫ ነበር የሚወጣው፡፡ ምርጫ ቢሆንስ? እሱማ ለማጭበርበር ይቀላል፡፡ የአሁኑስ ምንድነው? የአሁኑማ ካልኩሌሽን ነው፡፡ ካልኩሌሽን ቢሆንስ? ትምህርቱ ካልገባህ እንደዚህ ትዋረዳለሃ? አሁን አንተ የእኔ ልጅ ስትባል አታፍርም? ምነው ዳዲ? እኔ ለአንተ ምንድነው ያስተማርኩህ? ምን አስተማርከኝ ዳዲ? መድፈንና መድፈን ብቻ አይደል እንዴ ያስተማርኩህ?

ለክቡር ሚኒስትሩ ዳያስፖራ ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል

- ሰሞኑን በጣም ያዝናናኝን ነገር ግን ላጫውትዎት፡፡ - ምንድነው እሱ? - ሰሞኑን በፌስቡካችሁ የለቀቃችሁት ፎቶ ነዋ፡፡ - የምን ፎቶ? - አንቨርሰሪ ስታከብሩ የለቀቃችሁት ፎቶ ነዋ፡፡ - ምን ሆነ ደግሞ? - አለቆቻችሁ ኬክ እየቆረሱ የተነሱትን ነዋ፡፡ - ለምን ዳቦ አልሆነም ነው ጥያቄህ? - እናንተም ውስጥ ኒዮ ሊብራሎች ገብተዋል ማለት ነው? - መቼ ይጠፋሉ ብለህ ነው? - ለማንኛውም ቤቢ ሻወራችሁን እያከበራችሁ ነው የሚመስለው፡፡ - ምንድነው እሱ ደግሞ? - ያው ሴቶች ከመውለዳቸው በፊት ስጦታ የሚሰጥበት ባህል ነው፡፡ - ልጁ ሳይወለድ እንዴት ስጦታ ይሰጣል? - ያው የፈረንጆች ባህል ነው፡፡ - በእኛ ባህል ግን ከተወለደ በኋላ ነው ስጦታ የሚሰጠው፡፡ - እሱንማ አውቃለሁ፡፡ - እኛም ኬክ የቆረስነው ለቤቢ ሻወር አይደለም፡፡ - ታዲያ ለምንድነው? - ለአራስ ጥሪ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከቀድሞ ጓደኛቸው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

ኩባንያዎቹ የሚፈልጉት የተማረ የሰው ኃይል ነው፡፡ ሥራ አጡ ሁላ የተማረ አይደል እንዴ? እ. . . ያውም ዩኒቨርሲቲ ድረስ ያስተማርነው ሥራ አጥ እኮ ነው ያለን፡፡ ክቡር ሚኒስትር ተማረ የሚባለው ወጣት እኮ በጣም ያሳፍራል፡፡ እንዴት? እኔም ዩኒቨርሲቲ ማስተማር ያቆምኩት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የምትለው አልገባኝም? የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዕውቀታቸው እኮ አሳፋሪ ነው፡፡ ስማ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር የተመሰገንበትን የትምህርት ስኬት ስታጣጥለው አታፍርም? ክቡር ሚኒስትር በየመንደሩ የተቋቋሙት ዩኒቨርሲቲዎች የሚያወጡት ትውልድ የተማረ የሰው ኃይል ነው ማለት ይከብዳል፡፡ ታዲያ ምን ይባል? የተማረረ የሰው ኃይል!

ክቡር ሚኒስትሩ ከጓደኛቸው ጋር እያወሩ ነው

- ክቡር ሚኒስትር የተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ምርጫ እንዴት ነው የሚካሄደው? -በምን ባስረዳህ ይገባሃል? - በፈለጉት ነገር ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ስለሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪ ምርጫ ታውቃለህ? - ስለዋናው ፖፕ ማለትዎ ነው? - አዎን መጀመርያ ጳጳሱን ለመምረጥ የሁሉም አገሮች ጳጳሶች ይሰበሰባሉ፡፡ - እሺ? - ጳጳሶቹ ዋናውን ጳጳስ እስኪመርጡ ድረስ ከሚሰበሰቡበት ቦታ አይወጡም፡፡ - ታዲያ እናንተም ሰሞኑን ካልመረጣችሁ አትወጡም ማለት ነው? - ጳጳሶቹ ያሉበት ቦታ ማንም ስለማይደርስ መስማማታቸውና አለመስማማታቸው የሚታወቀው በጭስ ነው፡፡ - የምን ጭስ? -ጥቁር ጭስ ካጨሱ አልተስማሙም ማለት ነው ሲሆን፣ ነጭ ከሆነ ደግሞ ተስማምተዋል ማለት ነው፡፡ - ስለዚህ የእናንተም ምርጫ ላይ በነጭና በጥቁር ጭስ ሊሆን ነው? -እኛማ የአራት ፓርቲዎች ግንባር ስለሆንን ነጭና ጥቁር ብቻ አይወክሉንም፡፡ -ታዲያ በምድነው የምትወከሉት? -ለምሳሌ ከኦሮሞ ከሆነ አረንጓዴ፣ ከአማራ ከሆነ ቢጫ፣ ከትግራይ ከሆነ ቀይ፣ ከደቡብ ከሆነ ሰማያዊ ጭስ ማጨስ ይቻላል፡፡ - ክቡር ሚኒስትር ሰሞኑን ካለው ሁኔታ ግን በመካከላችሁ መስማማት ያለ አይመስልም፡፡ - ምን እያልክ ነው? - ላናይ ነው፡፡ - ምኑን? - ጭሱን!

ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር ቤታቸው እያወሩ ነው

- ቅድም አስጨፍረህ አስጨፍረኸኝ በአንዴ ደስታዬ ላይ ውኃ ቸለስክበት፡፡ - ምን ሆንሽ? - እኔማ አዲስ ኮሚሽን ተቀብለህ አካውንቴ ውስጥ የከተትክልኝ መስሎኝ ነበር፡፡ - የምን ኮሚሽን ነው? - ቅድም ሁለቱ የባንክ አካውንቶቼ ውስጥ ያለውን ገንዘብ ደምረህ ላክልኝ ብየህ ቢሊየነር አድርገኸኝ ነበር፡፡ - ስደምር ተሳስቼ ይሆናላ፡፡ - እኔማ የሒሳብ ችሎታህ እንዲዳብር እያፈላለግኩልህ ነው፡፡ - ምን? - ስኮላርሽፕ!

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ተቃዋሚ ከውጭ ደወለላቸው

ክቡር ሚኒስትር እኛ ከእናንተ በላይ ስለአገሪቷ እናስባለን፡፡ ለዚያ ነው አሜሪካ ታክሲ የምትነዳው? አሁን ክፉ መነጋገር አያስፈልግም፡፡ ታዲያ አንተ ራስህ ለምን ክፉ ታናግረኛለህ? እኔ የደወልኩት አንድ ነገር ለመጠየቅ ነው፡፡ ምን ልትጠይቀኝ? ቀኑ ተቆርጧል ወይ ለማለት ነዋ? የምኑ ቀን? የድርድር ነዋ፡፡ ማን ከማን ጋር ነው የሚደራደረው? እኛ ከእናንተ ጋር ነዋ፡፡ ሰውዬ በጣም ኮሜዲያን ሆነሃል፡፡ ይኼ ቀልድ አይደለም እኮ አልኩዎት፡፡ ስማ እኛ እዚህ ካሉት ጋር እንደራደራለን፡፡ እኛስ? እናንተም እዚያው ተደራደሩ፡፡ ከማን ጋር? እርስ በርሳችሁ!

አንድ በውጭ የሚኖር ተቃዋሚ ለክቡር ሚኒስትሩ ስልክ ደወለላቸው

ይኸው ሕዝቡ እስረኛ አስፈታችሁ፣ አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሊያስቀይራችሁ ነው፡፡ እናንተ ለዚህ ነው ይህችን አገር ለመምራት ብቃቱም፣ አቅሙም የላችሁም የምንለው፡፡ ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር? እኛ እኮ እስረኞቹንም ለመፍታት ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን እንዲወርዱ ከተስማማን ቆየን፡፡ ክቡር ሚኒስትር እጃችሁን ተጠምዝዛችሁ እንጂ ተስማምታችሁ አይደለም፡፡ ስነግርህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣናቸውን መልቀቅ ከፈለጉ ቆይተዋል፤ እኛ እስክንተካቸው ነበር የቆዩት፡፡ እናንተማ መቼም እንደማታምኑ አውቃለሁ፡፡ ስማ ምንም ይፈጠራል ብለህ እንዳታስብ፡፡ እሱንስ እንኳን ይተውት፡፡ ማለት? እኔ አሁን ጮቤ እየረገጥኩ ነው፡፡ ለምኑ? በቃ ክቡር ሚኒስትር አብቅቶላችኋል፣ እኔም ሻንጣዬን እያዘጋጀሁ ነው፡፡ ምን ለማድረግ? አገሬ ለመግባት ነዋ፡፡ እስቲ አታስቀኝ? ይኸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ይኖራል እያሉ አይደል እንዴ? ዶሮ ብታልም ጥሬዋን አሉ፡፡ አገሬ መግባቴ አይቀርም ስልዎት፡፡ ለነገሩ ይኼንን ማሰቡ አይከፋም፡፡ እንዴት? አንድ ቀን አገራችሁ ትገቡ ይሆናል፡፡ ክቡር ሚኒስትር እርስዎም ውስጥዎት ያውቀዋል በቅርቡ መሆኑ አይቀርም፡፡ በነገራችን ላይ አሜሪካ ጥሩ ቤት አለህ አሉ፡፡ እሱንም ትቼው እምጣለሁ፡፡ እኔም እዚህ ጥሩ ቤት ስላለኝ አንድ ነገር አስቤ ነበር፡፡ ምን ክቡር ሚኒስትር? ብንቀያየር ብዬ ነዋ፡፡ ምኑን? ቤታችንን!

ለክቡር ሚኒስትሩ ከውጭ ዳያስፖራ ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል

• አንተ ሕዝባችንን ስለምትንቀው ነው፡፡ • እንዲያው ሕዝቡን የምትንቁትማ እናንተ ናችሁ፡፡ • እንዴት? • ሕዝቡ የሚጠይቀው ሌላ እናንተ የምታወሩት ሌላ፡፡ • ምን እያልክ ነው? • አሁን ፋብሪካ የሚቃጠለውና መንገድ የሚዘጋው ኒዮሊበራሊዝም በመሸሹ ወይስ በማፈግፈጉ ነው? • ምን? • ክቡር ሚኒስትር ይኼ ሕዝብ በጣም እየታዘባችሁ ነው፡፡ • አንተ ውጭ ስለምትኖር የዚህን አገር ሕዝብ ብዙም አታውቀውም፡፡ • ለነገሩ እኔ ፎቶዎቹንም ሳይ የሥልጠናው ዋናው ነገር ኒዮሊብራሊዝም አለመሆኑ ገብቶኛል፡፡ • የሥልጠናው ዋናው ነገር ምንድነው ታዲያ? • አበሉ!