Skip to main content
x

ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የፖለቲካ ተመራማሪ ጋር እያወሩ ነው

- ክቡር ሚኒስትር ይኼ መርዘኛ ዘረኝነት ነው የአገሪቷን ችግር እያባባሰ ያለው፡፡ - እሱ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ - ምን እንደሚገርመኝ ያውቃሉ? - ምንድነው? - ዘረኞች እኮ ልክ እንደ እንስሳ ናቸው፡፡ - ኧረ አትሳደብ፡፡ - እንስሳ ስድብ መቼ ይገባዋል ብለው ነው? - ቆይ ተረጋጋ፡፡ - ክቡር ሚኒስትር እንስሳ ብቻ ነው የራሱን ዓይነት የሚፈልገው፡፡ - እ… - ይኸው የእኛ አገር ፖለቲከኞች ከዚህ ዘር ውጪ አታግቡ፣ አትነግዱ እያሉ አገር እየበጠበጡ ነው፡፡ - እሱስ እውነት ብለሃል፡፡ - የሚገርምዎት ስለዘረኞች ሳስብ፣ ምናለ ቢያንስ ከበቅሎ ቢማሩ ያስብለኛል፡፡ - እንዴት? - በቅሎ የሚወለደው ከእናቱ ፈረስና ከአባቱ አህያ ነዋ፡፡ - እ… - ታዲያ ዘረኞች ምናለ ከእነዚህ እንስሶች ቢማሩ፡፡ - ጥሩ ምልከታ ነው፡፡ - ለማንኛውም የአገራችንን ዘረኞች ለመፈወስ አንድ ማሠልጠኛ ተቋም ላቋቁም ነው፡፡ - ምን የሚባል? - በቅሎ የዘረኞች ማሠልጠኛ ተቋም!

ክቡር ሚኒስትር አንድ ባለሀብት ይደውልላቸዋል

ከዚህ በላይ ምን የባሰ ነገር ይመጣል ክቡር ሚኒስትር? እንዴት? ፋብሪካዬ ሥራ ካቆመ ወራት ተቆጠሩ፡፡ ለምን? ጥሬ ዕቃ ማስገባት አልቻልኩም፡፡ እዚህ አገር ጥሬ ሥጋ እንጂ መቼ ጥሬ ዕቃ አለ፡፡ በዚህ ምክንያት ምንም ሳላመርት ለሠራተኞች ደመወዝ መክፈል ከበደኝ፡፡ ይገባኛል ወዳጄ፡፡ አሁን ከአቅሜ በላይ በመሆኑ እነሱንም አሰናበትኩ፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡ በዚያ ላይ የፋብሪካ ማሽኖቹ ከጥቅም ውጪ እየሆኑ ነው፡፡ ለምን? በከተማዋ ውስጥ ዘይት ስለጠፋ እየተበላሹ ነው፡፡ እ . . . ክቡር ሚኒስትር በዚህ በዶላር እጥረት ሕይወታችን እያጠረ ነው እኮ፡፡ ችግር የለም በቅርቡ ይፈታል፡፡ ምኑ ነው የሚፈታው? የዶላር እጥረቱ ነዋ፡፡ እኮ በምን? የመንግሥትን ፀጋ እያወቅከው፡፡ ልትለምኑ ነው፡፡ ምን አለበት? ችግሩ በዚያ የሚቀረፍ አይመስለኝም፡፡ ስነግርህ እንዲያውም ዓለም አቀፍ ግብረ ኃይል አቋቁመናል፡፡ የምን ግብረ ኃይል? የለማኞች ግብረ ኃይል!

ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላው ጋር እያወሩ ነው

ያው ከለውጡ በኋላ የሥራ አጡ ቁጥር ጨምሯል ክቡር ሚኒስትር፡፡ እሱማ ይታወቃል፡፡ በለውጡ ደግሞ ሕዝቡ እንደፈለገ ወደ ጎዳና ወጥቶ መሠለፍ ችሏል፡፡ ሥራ ከሌለ ቢሠለፍ ምን ያደርጋል? አሁን ባሰብኩት ሐሳብ ለወጣቱም ሥራ ልንፈጥርለት እንችላለን፡፡ እንዴት? በለውጡ ሁሉም ሰው መሠለፍ ይፈልጋል፡፡ እ… ስለዚህ አጀንዳ ኖሯቸው ሠልፍ ለሚጠሩ ሠልፈኞችን ማቅረብ እንችላለን፡፡ እንዴት? እንዴት? አዩ ክቡር ሚኒስትር እኛ ጎዳና የሚወጡ ሠልፈኞችን በማዘጋጀት አጀንዳ ኖሯቸው ሠልፍ ለሚጠሩ እናቀርባለን ማለት ነው፡፡ አንተ እኮ አባ መላ ነህ፡፡ ሠልፈኞችን ሲፈለግ በፆታ፣ ሲያስፈልግ በዕድሜ፣ ከዚያም በብሔርና በሃይማኖት እየከፋፈልን እናቀርባለን፡፡ ይኼማ ወሳኝ ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ በአስቸኳይ ቢልቦርድ ላሠራ፡፡ ምን የሚል? ሠልፈኞችን ከአሠላፊዎች ጋር እናገናኛለን!

ክቡር ሚኒስትሩን ሾፌራቸው ወደ ቤት እየወሰዳቸው ነው

 እነዚህ ሁሉ መኪኖች መንገድ ዳር ለምንድነው የቆሙት?  ባለቤቶቻቸው መጠጥ እየጠጡ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡  ጠጥተው ይነዳሉ ማለት ነው?  አጠጣጥስ ልክ አለው ክቡር ሚኒስትር?  ትራፊክ ፖሊሶች የሉም እንዴ?  ቢኖሩስ ክቡር ሚኒስትር?  አይቆጣጠሩም እንዴ?  ለሁሉም ነገር መላ አለው ክቡር ሚኒስትር፡፡  የምን መላ?  ሰጥቶ መቀበል የሚሉት መላ ነው፡፡  አንተ በምን አወቅክ?  ከአሥር ዓመት በላይ ሾፌር ነኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡  አሥር ዓመት ሙሉ መኪና ትነዳለህ?  ምን ላድርግ ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?  ለማደግ ጥረት አታደርግም?  እዚህ አገር ለማደግ አቋራጩ ነጋዴ መሆን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

- ለማንኛውም ሕዝቡ ሿሿ ተሠርተናል እያለ ነው፡፡ - ምንድነው ሿሿ? - የታክሲ ላይ የዘረፋ ስልት ናት፡፡ - ሰውዬ ፈር አትልቀቅ እንጂ፡፡ - ምን አደረግኩ ክቡር ሚኒስትር? - ሌቦች እያልክ እየተሳደብክ እኮ ነው፡፡ - ሕዝቡ የሚላችሁን ነው የነገርኳችሁ፡፡ - እኮ ምን አደረግን? - ሰሞኑን እንኳን ያደረጋችሁትን ረሳችሁት? - ምን አደረግን? - በኮንዶሚኒየሙ ነዋ፡፡ - እ… - ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ እንድትታወቅ እያደረጋችኋት ነው፡፡ - በመደመር ፍልስፍናችን ማለትህ ነው? - ኧረ የለም፡፡ - ታዲያ በምንድነው? - መንግሥት ሆኖ መንግሥትን በመቃወም፡፡ - እ… - ራሳችሁ ቤት ሰጥታችሁ ራሳችሁን ትቃወማላችሁ? - እ… - ለማንኛውም እናንተን ለማስመዝገብ ደፋ ቀና እያልኩ ነው፡፡ - የት? ምርጫ ቦርድ? - እዚያማ ተመዝግባችኋል፡፡ - ታዲያ ምን ላይ ነው የምታስመዘግበን? - የድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ!

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው

ይኸው እሳት ላይ አስቀምጣችሁን ሄዳችሁ፡፡ እኛም እኮ ነግረናችሁ ነበር፡፡ ምኑን? አገር መምራት እንዲህ ቀላል እንዳልሆነ፡፡ እናንተ ያጠፋችሁትን እያረምን እኮ ነው የተቸገርነው፡፡ እንዴት ነው ማረም ታዲያ? የጊዜ ጉዳይ እንጂ መጠየቃችሁ አይቀርም፡፡ አለቃችሁን ግን ይኼ ሁሉ የቤት ሥራ ትተው ውጭ መሽከርከራቸው ምንድነው? የእናንተን ስህተት ለማረም ነዋ፡፡ ቢሆንም ሁሉ ነገር ከውስጥ መጀመር ይሻላል፡፡ እንዴት? ተለውጠናል እያላችሁ አይደል እንዴ? ግጥም አድርገን ነዋ የተለወጥነው፡፡ ስለዚህ ወደ ውጭ ከማየት ወደ ውስጥ መመልከቱ ይበጃል፡፡ አሁን እናንተም ለምክር በቃችሁ? ለማንኛውም ሰሞኑን አለቃችሁ የውጭ ጉዞ ስላበዙ ሥልጠናቸው ተቀየረ ወይ ለማለት ነው? ወደ ምንድነው የሚቀየረው? ሳናውቅ ሾማችኋቸው እንዴ? ምን አድርገን? በጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ . . . እ. . . የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር!

ክቡር ሚኒስትሩ ለደላላ ወዳጃቸው ስልክ ደወሉ

ሰው ሁሉ ችግር ነው የሚያወራው፡፡ ለነገሩ እንቅስቃሴ ሁሉ ተዳክሟል፡፡ ኧረ አንተ እንኳን አበረታታኝ፡፡ ምን ተሻለ ታዲያ? እንድታግዘኝ ነው የደወልኩት፡፡ ምን ላግዝዎት? ትኬቱን ሽጥልኝ፡፡ እርስዎን ያልገዙዎት እኔን ማን ይገዛኛል ብለው ነው? አንተ እንደምትሸጠውማ እርግጠኛ ነኝ፡፡ እንዴት ክቡር ሚኒስትር? ይታሰብልሃል፡፡ ምን ክቡር ሚኒስትር? ኮሚሽን፡፡ ስንት ፐርሰንት 10 ፐርሰንት!

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሥልጣን ስልክ ይደውሉላቸዋል

ክቡር ሚኒስትር የእኛ አገር ዘረኝነት እኮ ከሕዝቡም በላይ ሄዶ መሬቱም ዘረኛ ሆኗል፡፡ አልገባኝም? ማለቴ የአማራ መሬት፣ የኦሮሞ መሬት፣ የትግሬ መሬት ምናምን እያልን ከፋፍለነዋል፡፡ ምን እያልከኝ ነው? መሬቱ ራሱ የሚናገረው ቋንቋ አለው፡፡ ሰው እንዴት ነገረኛ ሆኗል ልበል? ፌዴራሊዝሙ በቋንቋ ስለሆነ መሬቱም ቋንቋውን ለምዶታል፡፡ በፌዴራሊዝሙ ቀልድ የለም፡፡ ኧረ እኔ አልቀለድኩም ክቡር ሚኒስትር፡፡ ፌዴራሊዝሙ ለድርድር የሚቀርብ ነገር አይደለም፡፡ ለማንኛውም ሕዝቡ በመንግሥት ሹመት ትችት እያቀረበ ነው፡፡ የምን ትችት? ሹመት በብሔር ተዋጽኦ መሆን የለበትም እያለ ነው፡፡ ታዲያ በምን ተዋጽኦ ይሁን፡፡ በብቃት ተዋጽኦ!

ክቡር ሚኒስትሩ ልጆቻቸው በመኝታ ቤት ሲጨቃጨቁ ከእንቅልፋቸው ነቁ

ሳሎን ቤቱ ላይ እሷ የይገባኛል ጥያቄ አንስታ ነው፡፡ የምን የይገባኛል ጥያቄ ነው? በፊት በፊት የማድርበት እኔ ስለነበርኩ ሳሎኑ የእኔ ነው አለችኝ፡፡ እ . . . ምን እሱ ብቻ የሳሎን ቤቶቹን አትክልቶቹ የምንከባከባቸውና የተከልኳቸው እኔ ስለሆንኩ ሳሎኑ የእኔ ነው አለችኝ፡፡ አንተስ ምን አልካት? እኔማ እንዲያውም ካልሽ ሳሎን ውስጥ ያሉ አብዛኛዎቹ መጻሕፍት የእኔ ስለሆኑ ሳሎኑ የእኔ ነው አልኳት፡፡ እ . . ዳዲ ፕሌይ ስቴሽን እየተጫወትኩ አብዛኛውን ጊዜ የማጠፋው እኮ ሳሎን ቤት ነው፡፡ እኔ የምለው ሁለታችሁም የራሳችሁ መኝታ ቤት አላችሁ አይደል እንዴ? አዎን ዳዲ፡፡ ታዲያ በሳሎን ቤት ምን አጣላችሁ? እሷ ሳሎኑ የእኔ ነው ውጣልኝ ስትለኝ ነዋ፡፡ ለማንኛውም ሳሎኑ የሁለታችሁም አይደለም፡፡ ታዲያ የማን ነው? የሁላችንም!

የቀድሞው ሚኒስትር ወደ ማረሚያ ቤት ይደውላሉ

ሆቴሉ የሚሰጠን አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰብን ነው፡፡ ምን ሆነ? ይኸው እንደበፊቱ የፈለግነውን ምግብ አዘን መብላት አልቻልንም፡፡ እንዴ ለምን? የእስካሁኑን ሒሳብ አልከፈልንማ፡፡ ያሳዝናል፡፡ አንሶላችን እንኳን ከታጠበ ቆይቷል፡፡ ለምን ለሆቴሉ አይናገሩም ታዲያ? ሒሳብ ክፈሉ እያለን ነዋ፡፡ ምን ተሻለ ታዲያ? እኔማ እናንተ እንድትረዱን አስቤ ነበር፡፡ በምን እንርዳዎት? ስማችንን ማጥፋት ብቻ ሳይሆን ጥያቄያችንንም መልሱ፡፡ የትኛውን ጥያቄ? የሆቴል ወጪያችንን ክፈሉልን፡፡ ከየት አምጥተን? ለምን ከበጀቱ ተቀናሽ አድርጋችሁ አትከፍሉልንም? ከየትኛው በጀት? ከታራሚዎች!