Skip to main content
x

ክቡር ሚኒስትሩ ከተቃዋሚ ፖለቲከኛ ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው

- አገሪቱ ውስጥ ያለውን ሪፎርም መቼም እየተከታተልሽው ነው? - ምነው? - ይኼን ሪፎርም እኛም ቤት ውስጥ አስገብተነው ሪኖቬሽን ማከናወን አለብን፡፡ - ምንድነው የምታወራው? - ቤታችንን ማደስ አለብን፡፡ - በጣም ቅርብ ጊዜ ነው እኮ ያስመረቅነው? - አዎን ግን እድሳት ማድረግ እንዳለብን ተሰምቶኛል፡፡ - ምን ዓይነት እድሳት? - ቤዝመንቱ መጋዘን መሆን የለበትም፡፡ - የተሠራው ለዚያ ነበር እኮ? - አዎ ቢሆንም ቤዝመንቱ ውስጥ መዋኛ ማሠራት አለብን፡፡ - እ… - ከዚያም ውጪ አሪፍ አሪፍ ክፍሎችን መገንባት አለብን፡፡ - ኧረ ሰውዬ ተው? - ከመንግሥት የተሰጠውን አቅጣጫ ተከትዬ እኮ ነው እድሳት ለማድረግ የፈለግኩት፡፡ - ምንድነው የምታወራው? - የእኔ ስም ከብዙ ወንጀል ጋር እንደሚነሳ ታውቂያለሽ አይደል? - ታዲያ ለምን አርፈህ አትቀመጥም? - አየሽ መጨረሻዬ እስር ቤት ሊሆን ይችላል፡፡ - እና ምን ይጠበስ? - ስለዚህ እኔ መንግሥት እየቀለበ እንዲያስረኝ አልፈልግም፡፡ - ምን እያልክ ነው? - ወደፊት መታሰሬ የማይቀር ከሆነ ከአሁኑ ነው መገንባት ያለብኝ፡፡ - ምንድነው የምትገነባው? - የግል እስር ቤት!

ክቡር ሚኒስትሩ ለደላላ ወዳጃቸው ስልክ ይደውላሉ

- ለመሆኑ ሰሞኑን ሚዲያ እየተከታተልክ ነው? - ምን አዲስ ነገር አለ ክቡር ሚኒስትር? - በየቦታው እኮ ባንኮች እየተዘረፉ ነው፡፡ - እሱን ሰምቻለሁ፡፡ - ታዲያ ቶሎ ብለህ ሥራውን አትጀምርም እንዴ? - የቱን? - የእጥበቱን ነዋ፡፡ - እ. . . - በአዲስ መልክ ጀምረናል ብለህ ማስታወቂያ ማስነገር እኮ ነው፡፡ - በሚዲያ? - ኧረ በኔትወርክህ፡፡ - የምን እጥበት ነው ግን? - የገንዘብ!

የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ቢሯቸው ገባች

የጥምቀት በዓል ሁሉን አቀፍ ነው፡፡ እንዴት? በመጥምቁ ዮሐንስ የተጠመቀውም፣ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የተጠመቀውም፣ በሙስና የተጠመቀውም ሊያከብረው ይችላል፡፡ እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር? የእውነቴን ነው የምልሽ፡፡ ለማንኛውም ላስፈቅድዎት ነበር፡፡ ምንድነው የምታስፈቅጂኝ? ታቦት ለመሸኘት ልሄድ ነበር? ችግር የለውም አብረን እንወጣለን፡፡ እርስዎም ይሸኛሉ እንዴ? አዎን፡፡ እኔ አላምንም ታቦት ሊሸኙ? ታቦት አይደለም የምሸኘው? ታዲያ ማንን ነው? ጓደኛዬን፡፡ ወዴት? ወደ ቂሊንጦ!

የክቡር ሚኒስትሩ ውሻ በጥሶ የአካባቢውን በርካታ ሰዎች ነክሶ፣ ፖሊስ ቤታቸው ይመጣል

ክቡር ሚኒስትር፣ ውሻዎ በጥሶ ወጥቶ በርካቶች ላይ ጉዳት ከማድረሱም ባሻገር ለአካባቢው የሥጋት መንስዔ ሆኗል፡፡ ምን? ስለዚህ ክቡር ሚኒስትር ውሻዎ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱ የአካባቢው ነዋሪዎች ዕርምጃ እንዲወሰድበት ጠይቀዋል፡፡ ስማ ይኼ ውሻ እኮ ለእኔ የቤተሰቤ አካል ነው፡፡ ሊሆን ይችላል ክቡር ሚኒስትር፣ ሆኖም ውሻዎ አካባቢውን በማሸበሩና ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱ ለእኛ ተላልፎ ሊሰጠን ይገባል፡፡ ለምን? ጉዳት የደረሰባቸው ነዋሪዎች እኮ ስለጤንነታቸው እየሠጉ ነው፡፡ ለምንድነው የሚሠጉት? ለመሆኑ መቼ ነው የተከተበው? የዛሬ 27 ዓመት፡፡ ስለዚህ እኛ የምንፈልገው አንድ ነገር ነው? ምንድነው? ውሻውን. . . ምን? አሳልፈው እንዲሰጡን!

ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ጋዜጠኛ ጋር እየተጨቃጨቁ ነው

እናንተ ግን እንደ ተከታታይ ድራማ በየጊዜው ገቡ እያላችሁ ነው የምትዘግቡት፡፡ ምን እናድርግ ታዲያ ክቡር ሚኒስትር? እንዴት? እናንተ ራሳችሁ ምርጥ የፖለቲካ ድራማ ነው የምትሠሩት፡፡ እ… የፓርቲ አመራሮቹን እንደ ተከታታይ ድራማ በፓርት በፓርት ስታስገቧቸው እኛም ክፍል አንድ፣ ክፍል ሁለት እያልን እንዘግባቸዋለን፡፡ ለማንኛውም እናንተ ትኩረት የምትሰጡት ዜና ገብቶኛል፡፡ ምንድነው? ገቡ የሚለው ዜና ነዋ፡፡ እ… ስለዚህ አንድ ዜና ልንገርህ፡፡ ምን ዓይነት ዜና? እኔም ከረጅም ጊዜ በኋላ ጂም ጀምሬያለሁ፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ታዲያ ሚኒስትሩ ገቡ ብለህ ዜናው ለምን አትሠራውም? የት? ጂም ነዋ፡፡ ይኼ ዜና አይደለም፡፡ የገቡ ዜና ነው የምትሠሩት ብዬ ነው እኮ? በቅርቡ ሲገቡ ዜናውን እንሠራዋለን፡፡ የት ስገባ? እስር ቤት!

ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ሪሰርቸር ጋር እያወሩ ነው

- ዴሞክራሲን በማንኪያ ለለመደ ሕዝብ በአንዴ በቡልዶዘር ዝቀህ ስትሰጠው ይኸው አገሪቱ ተተራመሰች፡፡ - ክቡር ሚኒስትር ሕዝቡ ዴሞክራሲ በዛብኝ ብሎ አያውቅም፡፡ - ዴሞክራሲ መቼ አግኝቶ ያውቅና? - አሁንማ ሕዝቡ የመናገር መብቱን ተጠቅሞ ዴሞክራሲያዊ መብቱን እያጣጣመ ነው፡፡ - አገሪቱ ውስጥ ዴሞክራሲ አለ እያልክ ነው? - በሚገባ፡፡ - አንተ ስለዴሞክራሲ ያለህ አመለካከት የተሳሳተ ነው፣ ለዚያ ነው እኛም እየታገልን ነው ያልኩህ፡፡ - ቆይ ለእርስዎ ዴሞክራሲ ማለት ምን ማለት ነው? - አንድና አንድ ነገር ሲሆን ነው፡፡ - ምን ሲሆን? - የድሮው ሥርዓት ሥልጣን ላይ ሲወጣ!

ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ወዳጃቸው ጋር ተገናኙ

አገሪቱ እንደ ዜጋ ስላልቆጠረችኝ እኔም ጠቅልዬ ልሄድ ነው፡፡ ውጭ አገር ሄደህ ምን ትሠራለህ? ክቡር ሚኒስትር በደህና ጊዜ ውጭ ያሸሸሁት ገንዘብ ስላለኝ በእሱ እኖራለሁ፡፡ ሰሞኑን 36 ቢሊዮን ዶላር ከአገሪቷ ሸሽቷል የሚባለው የአንተም ተጨምሮ ነው? መቼም ዓይኔ እያየ አልበላም? ይኼ አካሄድህ ግን ትክክል አይመስለኝም፡፡ ክቡር ሚኒስትር በፊት ከዚህ አገር ምን አተረፍክ ስባል መሬት እል ነበር፡፡ አሁንስ? አሁንማ ያተረፍኩት መሬት ሳይሆን ሌላ ነው፡፡ ሌላ ምን? ምሬት!

ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላ ወዳጃቸው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው

አላስተዋልከውም እንጂ በዓመት አንዴ የሚከበረው በዓል በየሳምንቱ እየተከበረ ነው፡፡ የምን በዓል ነው? የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ነዋ፡፡ አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር? በአንዱ ሳምንት የሰሜን ሸዋ በርኖስ ይለበሳል፣ ሌላው ሳምንት የራያ ባህላዊ ልብስ ይለበሳል፡፡ ልክ ነዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡ ሌላው ደግሞ የአክሱም ጽዮን የጵጵስና ልብስ ሲለብስ፣ ሌላው ደግሞ የአባ ገዳን ልብስ ይለብሳል፡፡ ጥሩ ያስተውላሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡ አየህ በፊት እነዚህ ልብሶችን የሚያስተዋውቁት ሞዴሎች ነበሩ፣ አሁን ግን ፖለቲከኞቻችን ጥሩ ሞዴሎች ሆነውልናል፡፡ ሐሳብዎት እኮ ሁሌ ያስገርመኛል፡፡    ስለዚህ አሁን ቢዝነሱ የአልባሳት ነው፡፡ እሱማ ጋርመንት ላይ አተኮሮ የሚሠራ ኢንዱስትሪያል ፓርክ አለን አይደል እንዴ? ስለዚህ ቀጣዩ አዋጭ የቢዝነስ ዘርፍ እሱ ነው፡፡ ታዲያ ምን እያሉኝ ነው? ከአንድ አንድ የምንገባበት ቢዝነስ እሱ ነው፡፡ ምን? ሽመና!