Skip to main content
x

ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አድማ በማድረግ ታግደው ከነበሩ ሠራተኞች ከተመለሱት ውስጥ ተወካያቸው ከክቡር ሚኒስትሩ ጋር እያወራ ነው

ክቡር ሚኒስትር አሁንም ጥያቄያችን በአግባቡ ካልተለመሰ ዘለቄታዊ መፍትሔ አይገኝም፡፡ አሁንም ምሕረት ተደርጎላችሁ መሥሪያ ቤቱን ለመበጥበጥ ትፈልጋላችሁ? ክቡር ሚኒስትር እኛ እኮ እንደ ዜጋ እናንተ ከላይ ያላችሁት አመራሮች የምታገኙትን እንደ ቤት ያሉ ጥቅማ ጥቅሞች ይሰጡን ነው ያልነው፡፡ የምን ቤት ነው? ሁላችንም ኑሮ ስለከበደን መንግሥት ቤት እንዲሰጠን እንፈልጋለን፡፡ እኔ እኮ ያልገባኝ ይኼን አመፅ ለማስነሳት የምትሞክሩት ደግሞ በፍፁም የማትግባቡ ሰዎች ናችሁ እኮ? ክቡር ሚኒስትር እኛ ሌላ ጥያቄ የለንም፣ ጥያቄያችን መብታችን እንዲከበርልን ነው፡፡ አሁንማ ሲገባኝ እናንተ ከዚያም በላይ አጀንዳ አላችሁ፡፡ ምን ዓይነት አጀንዳ? መፈንቅለ ሚኒስትር!

ክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ አገር ውስጥ ከገባ ሪሰርቸር ጋር ሆቴል ውስጥ ተገናኝተው እያወሩ ነው

ነገርኩዎት ክቡር ሚኒስትር አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች ሕዝብ በሚናገረው ቋንቋ፣ በሚለብሰው ልብስና በሚበላው ምግብ እየለያዩ የሚያጋድሉበት አገር ዜጋ ነኝ ለማለት አፍራለሁ፡፡ እ. . . ስለዚህ ኢትዮጵያ የሦስተኛ ዓለም አገር መሆን አይገባትም፡፡ እሱማ ካደጉት አገሮች ተርታ ለማሠለፍ ወጥረን እየሠራን ነው፡፡ ወዴት ወዴት ክቡር ሚኒስትር? ምነው? ኢትዮጵያ መመደብ ያለባት ሌላ ዓለም ውስጥ ነው፡፡ የትኛው ዓለም? አራተኛው ዓለም!

ክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ ከውጭ ከመጡ ፖለቲከኞች አንዱን አግኝተው እያወሩት ነው

ክቡር ሚኒስትር እኛ እኮ ለሕዝቡ ስንታገል ነው የቆየነው፡፡ እኛስ ለማን ነበር የታገልነው? እናንተማ የራሳችሁን ሆድ ለመሙላት ነው የታገላችሁት፡፡ እዚህም ገብተህ ስድብ አላቆምክም ማለት ነው? ለነገሩ አሁን ወደ አገር ቤት የገባሁት ለመሳደብ ሳይሆን ሕዝቡን ለማረጋጋት ነው፡፡ እናንተ ደግሞ ከስድብ ውጪ ለሕዝቡ መቼ ፕሮግራማችሁን አስታውቃችሁ ታውቃላችሁ? እሱን እንግዲህ በምርጫው ሜዳ ላይ ይለያል፡፡ ሕዝቡማ ሁሌም ከእኛ ጎን ነው፡፡ ክቡር ሚኒስትር 97 ምርጫ ላይ እንዴት እንደተጫወትንባችሁ መቼም ያስታውሳሉ? ሥራ እንጂ መኮፈስ አያዋጣም፡፡ ክቡር ሚኒስትር እኛ ብቸኛ ፀሎታችን ቀጣዩ ምርጫ ነፃ እንዲሆን ነው፡፡ ከምን? ከኮሮጆ ሌባ!

የክቡር ሚኒስትሩ ዘመድ ከውጭ ይደውልላቸዋል

ስማ ውጭ ያለኝን ቤት አይሉ የባንክ አካውንት የምታንቀሳቅስልኝ ሰው እንዴት ነው አገር ቤት እመለሳለሁ የምትለኝ? ክቡር ሚኒስትር ከዚህ በኋላ በዚህ ሥራ አልቀጥልም፡፡ ምን ማለት ነው? ዘመኑ መቼም የፍቅር፣ የይቅርታና የመደመር መሆኑን ያውቃሉ? ለአንተ የሚጠቅምህ እነሱ ሳይሆኑ የእኔ ሀብት መሆኑን ረሳኸው? ክቡር ሚኒስትር ከዚህ በኋላ በቃኝ፡፡ ውጭ አገር ሃያ ምናምን ዓመት አንደላቅቄ ካኖርኩህ በኋላ እንደዚህ ስትል አታፍርም? ከዚህ በኋላ በቃኝ አልኩዎት እኮ? ስማ ያ ገንዘብ በአንተ ስም መሆኑን ታውቃለህ አይደል? ክቡር ሚኒስትር ገንዘቡ የእርስዎ እንዳልሆነ አያውቁም እንዴ? ምን ማለት ነው? ለዘመናት የለፋሁበት ሀብት እኮ ነው? ለዘመናት የዘረፍኩት ማለትዎ ነው? ሰውዬ አብደሃል እንዴ? ኧረ በፍፁም ክቡር ሚኒስትር፡፡ በቃ በአፋጣኝ መጥቼ ገንዘቡን ወደ እኔ ታዘዋውረዋለህ፡፡ እኔ ቀድሜ አዘዋውሬዋለሁ፡፡ ወዴት? ወደ ትረስት ፈንዱ!

ክቡር ሚኒስትሩ አንድ የእስር ቤት ኃላፊ ጋ ደወሉ

ቆይ ቆይ ሌላው ቢቀር እስር ቤቱ የተሟላ ፈርኒቸር አለው? ምንም አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር? ማለቴ ታሳሪዎቹ ሶፋ ምናምን አላቸው? እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር? የእውነቴን ነው እንጂ፡፡ እኔ እኮ የእስር ቤት ኃላፊ እንጂ የሆቴል ኃላፊ አይደለሁም፡፡ ስማ አሁን ከለውጡ ጋር መራመድ አለብህ፡፡ አልገባኝም? ምናለበት እስር ቤቱን ሆቴል ብታስመስለው? አሁን ነው የገባኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ምኑ ነው የገባህ? በቅርቡ ሊመጡ ነው ማለት ነው፡፡ የት? እኛው ጋ!

ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው

ስለዚህ እኔን አውላላ ሜዳ ላይ ልትጥሉኝ? ክቡር ሚኒስትር ምን ይደረግ እያሉ ነው? እኔ ያለኝ ልምድ ለአገሪቱ ጠቃሚ ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነ ልምድ እንዳለዎትማ እኛም ደርሰንበታል፡፡ ታዲያ እንዴት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቴን ታፈርሱታላችሁ? ሌላ እንዲቋቋምልዎት ነዋ፡፡ የምን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት? የሸርና የተንኮል!

ክቡር ሚኒስትር ጡረታ ከወጡ ሌላ ሚኒስትር ጋር ተገናኙ

የቀድሞ ሚኒስትር ጓደኞቼ ፖስታ ተላላኪ ሆነው ሳይ በጣም ነው የማዝነው፡፡ ሞኝ ነህ እንዴ አንተ? እንዴት ክቡር ሚኒስትር? እነዚህ ሰዎች እኮ በጎን የራሳቸውን ሥራ ስለሚሠሩ በጣም ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ የምን ጥቅም ነው? ይኼው ከአገር መውጣት አስቸጋሪ በሆነበት በዚህ ወቅት ፖስታውን እያመላለሱ በጎን የራሳቸውን ሥራ ይሠራሉ፡፡ እኔ ግን ብዙም አልታየኝም፡፡ እኛ እኮ በቅርቡ በሚደረገው የመዋቅር ለውጥ የቀድሞ ሚኒስትሮች የሚታቀፉበት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እንዲቋቋም እየገፋፋን ነው፡፡ ምን የሚሉት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት? ተላላኪ ሚኒስቴር!

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ እስራት ፈርቶ የተደበቀ ጓደኛቸው ደወለላቸው

ኧረ እኔ የትም መንቀሳቀስ አልችልም፡፡ ራስህን የቁም እስረኛ አድርገሃል ማለት ነው? ምን አማራጭ አለኝ? አማራጩማ መደመር ነው፡፡ ክቡር ሚኒስትር እኔ ምን እንደሚጠብቀኝ አውቀዋለሁ፡፡ ምንድን ነው የሚጠብቅህ? በቅርቡ ሙዚየም የሆነ ቦታ ነዋ፡፡ የት ነው? ማዕከላዊ!

ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር ቢሯቸው እያወሩ ነው

- ክቡር ሚኒስትር ጋዜጠኞቹ ተጠርተዋል፡፡ - የምን ጋዜጠኞች? - ባለፈው የምንሠራቸውን ሥራዎች ማሳወቅ ስላለብን ፕሬስ ኮንፈረንስ ይጠራ ብለውኝ ነበር፡፡ - ታዲያ ሳታማክረኝ ነው የምትጠራቸው? - እኔማ አሁን ትክክለኛው ጊዜ ነው ብዬ አስቤ ነበር፡፡ - እንዴት? - ያው ከተሾሙ መቶ ቀናት ስለሞላዎት በዚህ ጊዜ ያከናወኗቸውን ነገሮችን ነዋ ጋዜጠኞቹ የሚጠይቁዎት፡፡ - በእነዚህ በመቶ ቀናትማ ፍቅር፣ መደመርና ይቅርታ ላይ ነዋ የሠራነው፡፡ - እሱ ላይ ታዲያ እርስዎ ምን ሠርተዋል? - እንደምታውቀው የሻይ ቤታችን ሠራተኛና ጥበቃችን ለረዥም ዓመት ተኮራርፈው፣ እኔ ነኝ መካከላቸው ገብቼ ያስታረቅኳቸው፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው

አሜሪካ ታዲያ ለምን መሄድ ፈለጉ? መደመሬን በተግባር ለማሳየት አልኩህ እኮ፡፡ አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር? ባለፈው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላችሁን ዶላር አምጡ አላሉም? አዎን ብለዋል፡፡ ስለዚህ የእሳቸውን ጥሪ ተቀብዬ መደመር ፈልጌ ነው፡፡ ምን እያሉ ነው? አሜሪካ መሄድ የምፈልገው ለዚሁ ነው፡፡ ለምኑ? ላመጣው ነዋ፡፡ ምኑን? ዶላሩን!