Skip to main content
x

ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላ ወዳጃቸው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው

ቤታችሁ ያለውን ገንዘብ አውጥታችሁ ባንክ አስቀምጡ እየተባልን ነው፡፡ - ባናስቀምጥስ ምን ሊያደርጉን ነው? - ኦፕሬሽን እንጀምራለን ብለዋል፡፡ - የምን ኦፕሬሽን ነው? - ያው እንግዲህ የቤት ለቤት አሰሳ ሊጀምሩ ይሆናላ፡፡ - ካሰሳው በኋላ ምን ሊያደርጉ? - ካገኙማ ይወርሱናል፣ በዚያ ላይ ሌላ መዘዝ ሊኖረው ይችላል፡፡ - ታዲያ አንተ ምን አሳሰበህ? - እንዴ ክቡር ሚኒስትር ከመንግሥት ኦፕሬሽን በፊት ብሩን ባንክ እንዲያስገቡት ነዋ? - እኔማ ሰሞኑን ይኼንኑ መግለጫ ሰምቼ ብሩን ወደ ሌላ ቦታ ለማሸሽ አስቤ ነበር፡፡ - ክቡር ሚኒስትር ብቻ በመንግሥት ኦፕሬሽን ጉድ እንዳይሆኑ፡፡ - ከመንግሥት ኦፕሬሽ በፊት በሌላ ኦፕሬሽን ጉድ ተሠርቻለሁ፡፡ - በምን ኦፕሬሽን? በአይጥ ኦፕሬሽን!

ለክቡር ሚኒስትሩ ደላላ ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል

- ሁለቱ አገሮች ሰላም ከሆኑ እኮ አዳዲስ ቢዝነሶች አቆጠቆጡ ማለት ነው፡፡ - የምን አዳዲስ ቢዝነስ? - ክቡር ሚኒስትር ኢትዮጵያን በ11 በመቶ ስናሳድጋት ምን ያህል እንደተጠቀምን ያውቃሉ አይደል? - እሱማ ልክ ነህ፡፡ - ኤርትራንም በዚሁ ፍጥነት አሳድገን የድርሻችንን መጠቀም አለብን፡፡ - እኔ የኤርትራ ማደግ መቼ አስጨነቀኝ አልኩህ? - ክቡር ሚኒስትር የኤርትራ ዕድገት ያስጨንቅዎታል ብዬ ሳይሆን የእርስዎን ጥቅም አስቤ ነው፡፡ - የእኔ ጥቅም ምንድነው? - እርስዎ እንደ ምንም ብለው የኢትዮጵያ ገንዘብ ኤርትራ ውስጥ እንዲሠራ ያስደርጉ፡፡ - ለምን ተብሎ? - እዚህ በጥሬው የያዝነውን ገንዘብ እዚያ ይዘን ሄደን መሥራት እንችልበታለና፡፡ - እንዴት? እንዴት? - አዩ ቤት ያለው ገንዘባችን ሕገወጥ ነው ሊባል ስለሚችል፣ ኤርትራ ወስደነው ኢንቨስት ልናደርገው እንችላለን፡፡ - ለሚስቴ ጭንቀት መፍትሔ ተገለኘት ነው የምትለኝ? - ክቡር ሚኒትር ቆሻሻው ብራችን እዚያ ታጥቦ ይነፃል፡፡ - የት? - ቀይ ባህር!

የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር አርፍዶ ቤታቸው መጣ

አንጋፋዎቹ እኮ ከውድድሩ የተባረሩት አዳዲሶቹ ላቅ ያለ የእግር ኳስ ችሎ ስላላቸው ነው፡፡ እንዳይመስልህ አትሳሳት፡፡ ታዲያ በምንድን ነው አንጋፋዎቹ የተባረሩት? በአሻጥር፡፡ ክቡር ሚኒስትር ስመለከትዎ እርስዎ ከሚያውቁት ውጪ የሆነ ነገር አይወዱም፡፡ ምን እያልከኝ ነው? ይኸው በአገሪቱ ውስጥ የመጣውን ለውጥ ራሱ መቀበል አይፈልጉም፡፡ አንጋፋዎቹ የሌሉበትን ለውጥ አልቀበለውም፡፡ እንደዚያ ከሆነ የእኔ ምክር አንድ ነው፡፡ ምንድነው ምክርህ? በጊዜ ቢቆርጡ ይሻልዎታል፡፡ ምንድነው የምቆርጠው? ትኬት ነዋ፡፡ የምን ትኬት? የስንብት!

ክቡር ሚኒስትሩ በጣም ተናደው ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው

እሺ ሁሉም ይቅርና እኔን ክብር ያለኝን ሰው አይጥ ብሎ ማዋረድ አይከብድም? - እሱንም እኮ ያገኘኸው በይቅርታ ነው፡፡ - የምን ይቅርታ? - ከጅብነት ወደ አይጥነት የተደረገልህ በይቅርታ መርህ ነው፡፡ - አንቺ ራሱ የምታወሪውን አታውቂም፡፡ - ለማንኛውም እኔንም አንድ የአይጥና የድመት ፊልምን አስታወስከኝ፡፡ - የምን ፊልም? - ፊልሙ ላይ አይጧ ልክ እንደ አንተ ሌባ፣ አጥፊ፣ ተንኮለኛና ሴረኛ ነች፡፡ - ምንድነው የምታወራው? - ስለዚህ እኔም ከዚህ በኋላ አዲስ የቤት ስም አውጥቼልሃለሁ፡፡ - ማን ልትይኝ? - ጄሪ!

ለክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ ከእስር የተፈታ ደላላ ይደውልላቸዋል

ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ ብቻዬን ፋብሪካ የዋጥኩ ሰው ነኝ፡፡ - እሱስ ልክ ብለሃል፡፡ - ይኸው አሁን የዋጥኩትን ፋብሪካ እዚሁ አገሬ ላይ እተፋዋለሁ ብዬ ተነቃቅቼ ሳበቃ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውኃ ቸለሱብኝ፡፡ - ስማ ዋናው ነገር አንድና አንድ ነው፡፡ - ምንድነው ክቡር ሚኒስትር? - ይህች አገር እንድትለማ ትፈልጋለህ? - ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር? - ማለት? - ይኸው የዋጥሁትን ፋብሪካ ለመትፋት ተዘጋጅቼያለሁ ስልዎት? - በቃ ለልማቱ ይኼን ያህል ተነሳሽነት ካለህ ችግር የለውም፡፡ - እንዴት ማለት ክቡር ሚኒስትር? - አንተ በልማቱ የምትሳተፍበትን ቦታ እኔ አመቻችልሃለሁ፡፡ - የማለማው ቦታ ያገኙልኛል? - በሚገባ፡፡ - የትኛውን ቦታ እንዳለማ ፈልገው ነው? - ማረሚያ ቤቱን!

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ደላላ ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል

- ስማ እንኳን ኢትዮጵያ ዓለም ላይም ስለተነሳ አውሎ ንፋስ ምንም አልሰማሁም፡፡ - ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወስዶዎታል ልበል? - የምን እንቅልፍ? - አውሎ ንፋሱ ያስነሳው ጎርፍ ሲወስድዎት ያኔ ይነቃሉ፡፡ - ሰውዬ የምታወራው ነገር ግራ እያጋባኝ ነው፡፡ - ምን ሆነዋል ክቡር ሚኒስትር? - ምን ሆንኩ? - አገሪቱ ውስጥ የሚነፍሰው የለውጥ አውሎ ንፋስ እየተሰማዎት አይደለም? - እሱን ነው እንዴ የምትለው? - ክቡር ሚኒስትር ፕሮጀክቶቻችን እኮ መና ሊቀሩ ይችላሉ፡፡ - እንዴት ሆኖ? - ይኸው ለውጡ ብዙ ነገሮችን እየቀያየረ ነው፡፡ - ታዲያ እኛ ምን አገባን? - ክቡር ሚኒስትር ነገሮች እንደ ድሮው ላይቀጥሉ ይችላሉ፡፡ - የምትለው አልገባኝም? - ከፍተኛ ኮሚሽን የምናገኝባቸው ፕሮጀክቶች ላይሳኩ ይችላሉ፡፡ - ለምን ተብሎ? - ይኸው የእኛ ወሳኝ ሰዎች እኮ እየተፐወዙ ነው፡፡ - እ. . . - የውጭ ወዳጆቻችንም ደውለው ግራ ተጋብተናል እያሉኝ ነበር፡፡ - ምንም ሥጋት አይግባችሁ በላቸው፡፡ - ክቡር ሚኒስትር ሁኔታውማ በጣም አሥጊ ነው፡፡ - እንዴት ሆኖ? - አለቃችሁ እኮ እየተጫወተባችሁ ነው፡፡ - ምን? - ቀዩን ያዬ!

ክቡር ሚኒስትሩ ከውጭ ከመጣ ደላላ ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው

ክቡር ሚኒስትር መንግሥት እያደረገው ያለው ለውጥ በጣም ያስደስታል። ማለት? አገሪቷ ላይ እየነፈሰ ያለው የተስፋ ንፋስ ያስደስታል። ምን ማለት ነው? እስረኞች እየተለቀቁ ነው፣ ፖለቲከኞች እየተፈቱ ነው። በዚህ ላይ ከመንግሥት ጋር የሚቃረኑ ፓርቲዎች ራሳቸው ጥሪ እየተደረገላቸው ነው። ከዚህ በኋላ እኛ ሰላምና ልማት ላይ ብቻ ነው የምናተኩረው። እኔም አገሬ የገባሁት ይህንን ተረድቼ ነው። ለመሆኑ ምንድነው የምትሠራው? እኔ ፈረንጆቹ አገር የታወቅኩኝ ደላላ ነኝ። ኒዮሊብራል ነህ ማለት ነው? እኔ አገር ወዳድ ሰው ነኝ። ለምንድነው የመጣሁት አልከኝ? መጀመርያ ራሴን ለማሳደግ፣ ቀጥሎ ደግሞ አገሬን ለማሳደግ ነው። እሱስ ጥሩ ሐሳብ ነው። ክቡር ሚኒስትር ከእርስዎ ጋር ብዙ ሥራ መሥራት እፈልጋለሁ። ምን ዓይነት ሥራ? እኔ ብዙ ኢንቨስተሮች ማምጣት እችላለሁ፣ እርስዎ ደግሞ እዚህ መሬቱንም ሆነ ሌላውን ማመቻቸት ይችላሉ። እኔ ምን እጠቀማለሁ? እንዴ ክቡር ሚኒስትር በኮሚሽን እንጠቃቀማለን። ችግሩ እኮ አንተ ኒዮሊብራል መሆንህ ነው። ለምን ክቡር ሚኒስትር? ኒዮሊብራል ሳይ ሰውነቴን ይወረዋል። እኔም እኮ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባለውን ነገር ሳስበው ሰውነቴን ይወረዋል። ምን እያልከኝ ነው? እርስዎም አብዮታዊ ዴሞክራት እንደሆኑ፣ እኔም ኒዮሊብራል እንደሆንኩኝ መቀጠል እንችላለን። ለነገሩ አሁን በምትለው መንገድ መሥራት የምንችልበት ዕድል አለ። እንዴት? ያው መንግሥታችንም አቅጣጫ አስቀምጦልናላ። የምን አቅጣጫ? ከእኛ ጋር ከሚቃረኑ ፖለቲከኞች ጋር አብረን እንድንሠራ አቅጣጫ ስለሰጠን በዚያ መንገድ ማስኬድ እንችላለን። ምን እያሉኝ ነው ክቡር ሚኒስትር? እኔና አንተም በዚህ መንገድ ነው የምንሠራው። በምን? በጥምረት!

ክቡር ሚኒስትር በቅርቡ ታስረው ከተፈቱ የመንግሥት ባለሥልጣን ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው

እንኳን ደስ አለህ፡፡ እንኳን አብሮ ደስ አለን ክቡር ሚኒስትር፡፡ እንኳን ለቤቶችህ በሰላም አበቃህ፡፡ አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፣ እርስዎ ብቻ ነዎት እንዲህ ደፈር ብለው የሚናገሩኝ፡፡ ያው አሥራ አምስት ቤቶች ኖሮህ እንዴት ለቤት ብቻ አበቃህ ልበልህ? እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ባይገርምህ እኔ ራሴ ዘረፋ ውስጥ የገባሁት አንተን ዓይቼ ነው፡፡ ክቡር ሚኒስትር እስር ቤት ቀላል ነገር እንዳልሆነ ያውቃሉ፡፡ ዋናው ነገር ግን ሕዝብም ምን ያህል እንደተበደልን ዓይቶ ስላስፈታን እናመሠግናለን፡፡ ምን አልክ? እኛ አይደለም አሥራ አምስት፣ አርባ ቤቶች ይገቡን ነበር፡፡ እሱስ ልክ ነህ፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር እያወሩ ነው

- አንድ መሪ ምን ዓይነት ችሎታ ሊኖረው እንደሚገባ፣ ስለጊዜ አጠቃቀሙ፣ ስለትጋት ምናምን በአግባቡ ሳያውቅ እንዴት መሪ ሊሆን ይችላል የሚል ጥያቄ ነው ሕዝቡ የጠየቀው፡፡ - ሌላስ ምን ይላል? - ባለሥልጣናቱ የሕዝብ አገልጋይ ሳይሆኑ በሕዝቡ ተገልጋይ መሆናቸው ተጋለጠ እየተባለ ነው፡፡ - የእኛ ሕዝብ ሁሌም ነገር ማወሳሰብ ይወዳል፡፡ - ደግሞ ከፓርላማ ጋር ሥራ ተቆጣጥራችሁ ትረካከባላችሁ ተብሏል አሉ፡፡ - ምን ችግር አለው? - በሚቀጥለው ዓመት ከፓርላማው ጋር የሥራ ኮንትራት ልትፈራረሙ ነው ተብሏል፡፡ - ስንትና ስንት ውል የምፈራረምና በፊርማዬ የታወቅኩ ሚኒስትር አይደለሁ እንዴ? - ይህችኛዋ ግን ትንሽ የምታስቸግር ይመስለኛል፡፡ - እኔን ብዙ አታውቀኝም ማለት ነው? እኔ እኮ በቢሊዮን ገንዘብ የሚያወጡ ፕሮጀክቶችን የተፈራረምኩ ሰው ነኝ፡፡ - ታዲያ የቢሊዮን ገንዘብ ፕሮጀክቶቹ አንዳቸውም ተግባራዊ መሆን አልቻሉም፡፡ - ቀስ እያሉ ይሠራሉ፣ ምን ፕሮጀክት ማራዘም እኮ የተለመደ ነው፡፡ - ለማንኛውም ይኼን ኮንትራት የሚፈርሙ ከሆነ፣ በዚያው አንድ ነገር መከታተል አይርሱ? - ምን? - የሥራ ማስታወቂያ!

ክቡር ሚኒስትሩ ከስብሰባ በኋላ የሻይ ዕረፍት ላይ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው

ከጠዋት ጀምሮ ስብሰባው ላይ እያንቀላፉ እኮ ነው፡፡ ለምን አንከባበርም? ይኸው ፎቶ አንስቼዎታለሁ፡፡ ማሸለብ ብርቅ ነው? ኧረ ሙሉ ስብሰባውን ነው የተኙት፡፡ አሁን አንተ ንቁ ነኝ እያልክ ነው? እኔማ ስብሰባው የእርስዎን መሥሪያ ቤት ስለሚመለከት ብዙ አስተያየት ይሰጣሉ ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ ስማ እኔ ተኝቼ ሳይሆን እያሰላሰልኩ ነበር፡፡ ኪኪኪ… ምን ያስቅሃል? ለማንኛውም ሁኔታዎን ሳየው እንዲያው የደከምዎት ይመስለኛል፡፡ ማን ነው የደከመው? እርስዎ ነዎታ፡፡ ለዚህ ሥርዓት እኮ እኔ አድራጊ ፈጣሪ ነኝ፡፡ ክቡር ሚኒስትር አሁን ግን አድራጊ ፈጣሪ አይደሉም፡፡ እና ምንድነኝ? ተጧሪ!