Skip to main content
x

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ተቃዋሚ ከውጭ ደወለላቸው

ክቡር ሚኒስትር እኛ ከእናንተ በላይ ስለአገሪቷ እናስባለን፡፡ ለዚያ ነው አሜሪካ ታክሲ የምትነዳው? አሁን ክፉ መነጋገር አያስፈልግም፡፡ ታዲያ አንተ ራስህ ለምን ክፉ ታናግረኛለህ? እኔ የደወልኩት አንድ ነገር ለመጠየቅ ነው፡፡ ምን ልትጠይቀኝ? ቀኑ ተቆርጧል ወይ ለማለት ነዋ? የምኑ ቀን? የድርድር ነዋ፡፡ ማን ከማን ጋር ነው የሚደራደረው? እኛ ከእናንተ ጋር ነዋ፡፡ ሰውዬ በጣም ኮሜዲያን ሆነሃል፡፡ ይኼ ቀልድ አይደለም እኮ አልኩዎት፡፡ ስማ እኛ እዚህ ካሉት ጋር እንደራደራለን፡፡ እኛስ? እናንተም እዚያው ተደራደሩ፡፡ ከማን ጋር? እርስ በርሳችሁ!

አንድ በውጭ የሚኖር ተቃዋሚ ለክቡር ሚኒስትሩ ስልክ ደወለላቸው

ይኸው ሕዝቡ እስረኛ አስፈታችሁ፣ አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሊያስቀይራችሁ ነው፡፡ እናንተ ለዚህ ነው ይህችን አገር ለመምራት ብቃቱም፣ አቅሙም የላችሁም የምንለው፡፡ ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር? እኛ እኮ እስረኞቹንም ለመፍታት ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን እንዲወርዱ ከተስማማን ቆየን፡፡ ክቡር ሚኒስትር እጃችሁን ተጠምዝዛችሁ እንጂ ተስማምታችሁ አይደለም፡፡ ስነግርህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣናቸውን መልቀቅ ከፈለጉ ቆይተዋል፤ እኛ እስክንተካቸው ነበር የቆዩት፡፡ እናንተማ መቼም እንደማታምኑ አውቃለሁ፡፡ ስማ ምንም ይፈጠራል ብለህ እንዳታስብ፡፡ እሱንስ እንኳን ይተውት፡፡ ማለት? እኔ አሁን ጮቤ እየረገጥኩ ነው፡፡ ለምኑ? በቃ ክቡር ሚኒስትር አብቅቶላችኋል፣ እኔም ሻንጣዬን እያዘጋጀሁ ነው፡፡ ምን ለማድረግ? አገሬ ለመግባት ነዋ፡፡ እስቲ አታስቀኝ? ይኸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ይኖራል እያሉ አይደል እንዴ? ዶሮ ብታልም ጥሬዋን አሉ፡፡ አገሬ መግባቴ አይቀርም ስልዎት፡፡ ለነገሩ ይኼንን ማሰቡ አይከፋም፡፡ እንዴት? አንድ ቀን አገራችሁ ትገቡ ይሆናል፡፡ ክቡር ሚኒስትር እርስዎም ውስጥዎት ያውቀዋል በቅርቡ መሆኑ አይቀርም፡፡ በነገራችን ላይ አሜሪካ ጥሩ ቤት አለህ አሉ፡፡ እሱንም ትቼው እምጣለሁ፡፡ እኔም እዚህ ጥሩ ቤት ስላለኝ አንድ ነገር አስቤ ነበር፡፡ ምን ክቡር ሚኒስትር? ብንቀያየር ብዬ ነዋ፡፡ ምኑን? ቤታችንን!

ለክቡር ሚኒስትሩ ከውጭ ዳያስፖራ ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል

• አንተ ሕዝባችንን ስለምትንቀው ነው፡፡ • እንዲያው ሕዝቡን የምትንቁትማ እናንተ ናችሁ፡፡ • እንዴት? • ሕዝቡ የሚጠይቀው ሌላ እናንተ የምታወሩት ሌላ፡፡ • ምን እያልክ ነው? • አሁን ፋብሪካ የሚቃጠለውና መንገድ የሚዘጋው ኒዮሊበራሊዝም በመሸሹ ወይስ በማፈግፈጉ ነው? • ምን? • ክቡር ሚኒስትር ይኼ ሕዝብ በጣም እየታዘባችሁ ነው፡፡ • አንተ ውጭ ስለምትኖር የዚህን አገር ሕዝብ ብዙም አታውቀውም፡፡ • ለነገሩ እኔ ፎቶዎቹንም ሳይ የሥልጠናው ዋናው ነገር ኒዮሊብራሊዝም አለመሆኑ ገብቶኛል፡፡ • የሥልጠናው ዋናው ነገር ምንድነው ታዲያ? • አበሉ!

ክቡር ሚኒስትሩ ተመልሰው የፓርቲ ስብሰባ ውስጥ ገቡ

ክቡር ሚኒስትር በእርስዎ ጉዳይ ተወያይተናል፡፡ ምን ወሰናችሁ? እርስዎ መሰናበት አለብዎት፡፡ ምን? በክብር መሸኘት አለብዎት፡፡ አልገባኝም? ክቡር ሚኒስትር ከዕለት ወደ ዕለት የሚያጠፉት ጥፋት ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡ አሁን ራሳችሁን ከችግር የፀዳ አድርጋችሁ ስታወሩ አታፍሩም? እኛ ንፁህ ነን እያልን ሳይሆን የእርስዎ የባሰ ነው፡፡ አሁን እኔን ወህኒ ልታወርዱ? ኧረ በፍፁም፣ እሱማ መዘዝ አለው፡፡ ሁላችሁንም ጠራርጎ እንደሚያስገባችሁ ማወቃችሁም ጥሩ ነው፡፡ ስለዚህ አይታሰሩም፡፡ ምን ልታደርጉ ነው ታዲያ? አገር ስላገለገሉ በክብር ይሸኛሉ፡፡ ምን ማለት ነው? አገር ላገለገሉበት በደብል ቪ ነው የምንሸኝዎት፡፡ ምንድነው ደብል ቪ? ቪ8 እና ቪላ ነዋ፡፡ ይህቺን ይወዳል? ምነው ክቡር ሚኒስትር? እኔ ስንቱን ቪ8 ሳገላብጥ አልነበር እንዴ? እ. . . ቪላስ ቢሆን እኔ ጀማሪ ካድሬ አይደለሁ? ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር? እኔ ሥልጣኔን መልቀቅ አልፈልግም፡፡ እሱማ አይቀርም፡፡ ከለቀቅኩ ደግሞ ባልረባ ነገር ስሜ እንዲነሳ አልፈልግም፡፡ ምን ማለት ነው? አገራችን እኮ በደብል ዲጂት እያደገች ነው፡፡ እናውቃለን ክቡር ሚኒስትር፡፡ ወደፊትም ምናልባት የባህር በር ሊኖረን ይችላል፡፡ ምንድነው የሚያወሩት ክቡር ሚኒስትር? እኔ የእናንተን ቪ8 እና ቪላ አልፈልግም፡፡ ታዲያ ምንድነው የሚፈልጉት? መርከብ!

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሀብት ደወለላቸው

እኔ ስለወዳጃችን አይደለም ያወራሁት፡፡ - ታዲያ ስለማን ነው? - ዋናው የሳዑዲ ቢሊየነር፡፡ - እሱ ተፈታ አልተፈታ ለእኔ ምን ይፈይዳል? - እንዴት ክቡር ሚኒስትር? - እሱ ቤት አልገዛልኝ፣ ወይ አያሳክመኝ ምን ያደርግልኛል? - ዶሚኖ ኢፌክት አለዋ፡፡ - ምን እያልክ ነው? - የእኛም ወዳጅ ሊፈቱ ይችላሉ እያሉ ነው፡፡ - ምን ያህል እርግጠኛ ነህ? - ሰሞኑን ይገባሉ እየተባለ ነው፡፡ - ስማ ባለፈው ይፈታሉ ብላችሁኝ ኤርፖርት ድረስ አበባ አስታቅፋችሁ ላካችሁኝ፡፡ - ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡ - የስንት ሰው መሳለቂያ እንዳደረጋችሁኝ ታስታውሳለህ አይደል? - አሁን ግን እርግጥ ነው እየተባለ ነው፡፡ - በምን አወቅክህ? - ይኸው ሁላችሁም አንድ ዓይነት ሙሉ ልብስ አሰፉ ተብለን አሰፍተናል፡፡ - ሌላስ? - በቃ የሚያርፉበትም ቤት ቀለም እየተቀባ ነው፡፡ - ፌክ ኒውስ እንዳይሆን? - ፌክማ ከሆነ ማመላለሳችንን እንቀጥላለን፡፡ - ምኑን? - ስንቁን!

ክቡር ሚኒስትሩ ከቀድሞ ጓደኛቸው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው

• ምንድነው የያዙት ክቡር ሚኒስትር? • ይኼ አሪፍ መጽሐፍ ነው፡፡ • ምን ዓይነት መጽሐፍ? • ፊክሽን ነው፡፡ • ፊክሽን ያነባሉ እንዴት ክቡር ሚኒስትር? • እኔ ከፊክሽን ውጪ መቼ አነባለሁ? • እንዴት ክቡር ሚኒስትር? • ፊክሽን በጣም ነው የሚያስደስተኝ፡፡ • ይኼን ያህል? • በተለይ ይኼኛው ጸሐፊ በጣም አሪፍ ጸሐፊ ነው፡፡ • መጽሐፉ ግን ትልቅ ይመስላል? • እኔ እኮ ይኼን መጽሐፍ በሦስት ቀን ነው የምጨርሰው፡፡ • ምን ይቀልዳሉ? • ቮራሺየስ አንባቢ ነኝ እኮ፡፡ • ቪሸስ ነው ያሉኝ? • ቮራሺየስ ነው ያልኩህ፡፡ • እኔ እኮ እንግሊዝኛ ላይ ብዙም አይደለሁም፡፡ • ለማንኛውም ይኼ ስለአንድ ባለሥልጣን ነው የሚያወራው፡፡ • ምን ዓይነት ባለሥልጣን? • በቃ ይኼ ባለሥልጣን ሲስተሙን እንዴት አድርጎ እንደሚጫወትበትና እንደሚያምታታው ታያለህ በዚህ መጽሐፍ፡፡ • በጣም ይገርማል፡፡ • ሰውዬው እንዴት ባለሀብቶችና ፖለቲከኞች ላይ እንደሚጫወትባቸው ታያለህ? • እና እንደዚህ ዓይነት መጽሐፍ ነው የሚወዱት? • ሱስ ሆኖብኛል ስልህ? • ከፊክሽን ውጪም አያነቡም? • ለሌላው ብዙም ግድ የለኝም ስልህ? • ክቡር ሚኒስትር ፊክሽን ግን በሰዎች ምናብ የሚፈጠሩ ታሪኮች አይደሉም እንዴ? • ታዲያ ምን ችግር አለው? • ማለቴ እርስዎ እንደ ፖለቲከኛ እውነታ ላይ ያተኮሩ መጽሐፎችን ቢያነቡ ይጠቀማሉ ብዬ ነው፡፡ • ለእኔ እንዲያውም የሚጠቅመኝ ፊክሽኑ ነው፡፡ • አሁን አገሪቷ ላይ ምን እየተጫወታችሁ እንደሆነ ገባኝ፡፡ • ምንድነው የምንጫወተው? • ዕቃ ዕቃ!

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ደላላ ይደውልላቸዋል

• ክቡር ሚኒስትር ስልክዎ እኮ በጣም አስቸገረኝ? • ዛሬ ስንት ጣጣ ውስጥ ገብቼ ነበር፡፡ • ምነው? • ሲያቀብጠኝ የሚስቴን ልደት አክብሬ ሠራተኞቼ አመፁብኝ፡፡ • በዚህ ወቅት እንዲህ በግልጽ ድግስ ማድረግ ምን አስፈለገ? • እኔማ ትልቅ ትምህርት ነው የተማርኩት፡፡ • አሁን የደወልኩት አንድ ነገር ላማክርዎት ነው፡፡ • ምንድነው እሱ? • አንድ ሁለት ሰው ደውሎ ሲጠይቀኝ ለምን ወደ ቢዝነስ አንቀይረውም ብዬ ነው፡፡ • ጉዳዩ ምንድነው? • መንግሥት ምሕረት አደርጋለሁ ብሏል አይደል? • አዎ ብሏል፡፡ • ታዲያ ይኼን ለምን ወደ ቢዝነስ አንቀይረውም? • እንዴት አድርገን? • እንዲፈቱላቸው የሚፈልጉ ሰዎች አናግረውኝ ነበር፡፡ • እሺ? • አንዱ ደውሎ የሚደረገውን ነገር አደርጋለሁ ብቻ ወንድሜን አስፈቱልኝ ብሏል፡፡ • ኧረ እባክህ? ሁሉን ነገር ማድረግ ይችላል? • ስለእሱ አያስቡ ስልዎት? ከእኛ የሚጠበቀው ሊስት ውስጥ ወንድሙ እንዲገባ ማድረግ ነው፡፡ • የምኑ ሊስት? • የሚፈቱት ሊስት ውስጥ ነዋ፡፡ • ይቺ አሪፍ ሐሳብ ናት፡፡ • አሁን ወደ ሥራ መግባት ነው፡፡ • ምንድነው የምናደርገው? • ካስፈለገ ማስታወቂያ ማስነገር ነው፡፡ • ምን ብለን? • የታሰሩ እናስፈታለን!

ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር ቢሯቸው እየተወያዩ ነው

• መንግሥት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መንደፉን ታውቃለህ? • በሚገባ እንጂ፡፡ • ለተከታታይ ዓመታት ያስመዘገብነውን ዕድገት የውጭ ተቋማት ሳይቀሩ መስክረዋል፡፡ • እሺ? • አሁን ሕዝቡ እየጠየቀ ያለው ትራንስፎርሜሽኑ የታለ እያለ ነው፡፡ • ትራንስፎርመሩማ በየጊዜው እንደ ፈንዲሻ እየፈነዳ ነው፡፡ • እኔ ያልኩህ ትራንስፎርሜሽን ነው፡፡ • እሱስ የታለ? • ይኸው ተጀመረ፡፡ • እንዴት? • እስር ቤቱን ወደ ሙዚየም ቀየርነው፡፡ • እሺ? • ከዚያም አልፎ ገራፊዎቹን ወደ አስጎብኚነት ልንቀይራቸው ነው፡፡ • ኪኪኪ… • ምን ያስቅሃል? • ገርሞኝ ነዋ፡፡ • እሱ ብቻ አይደለም፡፡ • እሺ? • ጥፍር ነቃዮቹንም በአነስተኛና ጥቃቅን አደራጅተን ትራንስፎርም ልናደርጋቸው ነው፡፡ • ወደ ምን? • ወደ ጥፍር አስዋቢነት!

ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሮ ያስጠሩታል

• በኢንተርኔት ልቀቀው፡፡ • ፌስቡክ ለማለት ነው? • አዎን እሱ ላይ፡፡ • እሱማ ተዘግቷል ክቡር ሚኒስትር፡፡ • ማን አባቱ ነው የዘጋው? • መንግሥት ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡ • ለምን ተብሎ? • ለአገሪቷ ሰላምና ደኅንነት ሲባል ተዘግቷል፡፡ • እሱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጊዜ አልነበር እንዴ የተዘጋው? • አሁንም ግን ተዘግቷል፡፡ • እንዴት ግን ሊዘጋ ቻለ? • ምናልባት በይፋ ያልታወጀ የአስቸኳይ ጊዜ ላይ እንሆናለና? • ለነገሩ ፌስቡክ ሲዘጋ የሚታይበት መንገድ አለ አይደል? • ቪፒኤን ማለትዎ ነው? • ነው መሰለኝ፡፡ • ታዲያ በቪፒኤን ተጠቅሜ ፌስቡክ ላይ ልልቀቀው? • እህሳ፡፡ • ይህ ግን ትዝብት ውስጥ አይከተንም? • የምን ትዝብት? • መንግሥት ራሱ ፌስቡክን ዘግቶት፣ መግለጫውን በፌስቡክ ሲለቅ ነዋ?

ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሮ ያስጠሩታል

• ምንድነው የሚያምርህ? • ሥልጣን፣ የደረጃ ዕድገትና ሹመት፡፡ • የምር እነዚህን ነገሮች ትፈልጋቸዋለህ? • በሚገባ እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡ • ታዲያ ሥራህን ለምን በአግባቡ አትሠራም? • ኪኪኪ… • ምን ያስገለፍጥሃል? • ሹመት ለማግኘት ሥራዬን በአግባቡ መሥራት አይጠበቅብኝም፡፡ • እንዴት? • የመንግሥታችንን ባህል ስናውቀው ብቃት አያሾምም፡፡ • ታዲያ ምንድነው የሚያሾመው? • ለፓርቲው ታማኝ መሆን፡፡ • ሌላስ? • ሌሎች በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ • ምን እያልክ ነው ታዲያ? • እኔ አሁን ሹመት አምሮኛል፡፡ • ምን ልታደርግ ነው ታዲያ? • አንድ ነገር ብቻ፡፡ • እኮ ምን? • መስነፍ!