Skip to main content
x

ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ሌላ ሚኒስትር መጡ

• ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር? • አገሪቷ ከባድ ቀውስ ውስጥ ናት እኮ፡፡ • ታዲያ ይኸው እኛ አመራር እየሰጠን አይደል እንዴ? • እ… • እርስዎ እኮ ቢሮም የሉም፣ ከእኛም ጋር የሉም፡፡ • ስማ አገሪቷ ቀውስ ውስጥ ስለገባች እኮ ነው የጠፋሁት፡፡ • እንዴት ማለት? • በዚህ ጊዜ ነገ የሚፈጠረው ስለማይታወቅ ንብረት በጊዜ መሰብሰብ ነው፡፡ • የመንግሥትን ሥራ እርግፍ አድርገው የራስዎን ቢዝነስ እያሯሯጡ ነው? • ታዲያ ምን ማድረግ እችላለሁ? • ክቡር ሚኒስትር ግን አላበዙትም? • ምን አጠፋሁ? • በዚህ ሕዝብ ላይ ግን እየቀለዱ መሆኑን ያውቃሉ? • ይህ ሕዝብ እኮ ምስኪን ነው፣ ምንም አያውቅም፡፡ • ክቡር ሚኒስትር የሚነዱትን መኪና፣ ያለዎትን ሀብት፣ የሚኖሩበትን ቤት ቢያምኑም ባያምኑም ይህ ሕዝብ ጠንቅቆ ነው የሚያውቀው፡፡ • እሺ የእኔ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም? • እየቀለድኩ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፣ በዚህ ከቀጠልን እንደ እሱ መሆናችን አይቀርም፡፡ • የድሮ ሥርዓት ናፋቂ ሆነሃል ማለት ነው? • አሁን ያለውን ሁኔታ መካድ ምንም ስለማያዋጣ፣ ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ መስጠት ነው የሚያዋጣን፡፡ • እኔ ሕዝቡ ጥያቄ አለው ብዬ አላምንም፡፡ • ማን ነው ጥያቄ ያለው? • አመራሩ ነው፡፡ • አመራሩ የምን ጥያቄ ነው ያለው? • እከሌ የሰረቀው እከሌ ከሰረቀው ይበልጣል፣ ስለዚህ እከሌ እከሌን ሊያዘው አይችልም የሚል ነዋ፡፡

ለክቡር ሚኒስትሩ የድሮ ጎረቤታቸው ይደውሉላቸዋል

• ክቡር ሚኒስትር እኔ ግን የደወልኩት የዩኒቨርሲቲዎቹ ጉዳይ በጣም አሳስቦኝ ነው፡፡ • ምኑ ነው የሚያሳስብህ? • የመጀመርያ ልጄ ዩኒቨርሲቲ ገብታለች፡፡ • እንኳን ደስ አለህ፡፡ • ደስ የሚያሰኘው በፊት ነበር አሁን የተረፈኝ ሥጋትና ሰቆቃ ነው፡፡ • ምን እያልክ ነው? • ይኸው በየዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በብሔር ተከፋፍለው እየተጋጩ ተማሪዎች እየሞቱ እኮ ነው፡፡ • ይኼ እኮ ፀረ ሰላም ኃይሎች የሚያናፍሱት ወሬ ነው፡፡ • ክቡር ሚኒስትር ይኼ ወሬ ሳይሆን የአሁኒቷ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት እውነታ ነው፡፡ • ምን እያልክ ነው? • እኔ የምፈራው ልጄ አገሪቷ የደረሰችበት የብሔርተኝነት ፖለቲካ ሰለባ እንዳትሆን ነው፡፡ • እንዴት? • ይኸው የብሔር ፖለቲካው ጦዞ ጦዞ ተማሪዎቻችን ዘንድ ደርሷል፡፡ • ይኼ እኮ በዕድገት ላይ ያለች አገር ከሚገጥሟት ፈተናዎች አንዱ ስለሆነ ብዙ መጨነቅ የለብህም፡፡ • ክቡር ሚኒስትር እርስዎማ ልጅዎን ውጭ ልከው ስለሚያስተምሩ ምንም ላይመስልዎት ይችላል፡፡ • ምን እያልክ ነው ታዲያ? • አገሪቱ ውስጥ ባለው የብሔር ፖለቲካ ሳቢያ መፍትሔው አንድና አንድ ነው፡፡ • ምንድነው እሱ? • ልጆቻችን አጠገባችን ሆነው ይማሩልን፡፡ • ምንድነው የምትለው? • ዩኒቨርሲቲ እዚሁ ይሠራልን፡፡ • የት? • በየቀበሌያችን!

[የክቡር ሚኒስትሩ የእህት ልጅ ስልክ ይደውልላቸዋል]

• ሰሞኑን መንግሥት ያወጣውን መግለጫ አልሰማህም? • የትኛውን መግለጫ? • ይኸው ራሳችሁን አጋልጡ እየተባለ ነው፡፡ • ሙሰኞችን ነው? • በሌላ ቋንቋ ሙስኛ በለው፡፡ • ታዲያ አንተ የምን ሙስና ውስጥ ገብተህ ነው? • ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያላችሁ ራሳችሁን አጋልጡ እየተባለ ነው፡፡ • አንተ ታዲያ ከዚህ ጋር ምን አገናኘህ? • ረሳኸው እንዴ ጋሼ? • ምኑን? • አንተ እኮ ነው የገዛህልኝ፡፡ • ምኑን? • ዲግሪዬን፡፡ • ምን? • ቤት ለምን ትቀመጣለህ ስትለኝ ነጥብ አልመጣልኘም ስልህ አትጨነቅ ብለህ እኮ ነው የገዛህልኝ፡፡ • ለአንተ ነው እንዴ ያስመጣሁት? ለወንድምህ መስሎኝ? • ለእሱም አስመጥተህለታል ጋሼ፡፡ • ታዲያ እሱ አልተጠየቀም? • እሱማ ውጭ ስለሄደ ማን ይጠይቀዋል? • ምን ላድርግልህ ታዲያ? • እኔም እኮ ላማክርህ ነው የደወልኩት፡፡ • አሁን አንተን ጠይቀውሃል? • መጠየቄ አይቀርም፣ ሰሞኑን ደግሞ ጥሩ ትምህርት አለህ ብለው አሳድገውኛል፡፡ • ማን ነው አንተን የሚጠይቅህ? • የሰው ኃይል አስተዳደሩ ነዋ፡፡ • በቃ እደውልለታለሁ፡፡

ክቡር ሚኒስትር አንድ በጣም ከተገመገመ ባልደረባቸው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው

• እኔ የሚገርመኝ ገምጋሚዎቹ ሁሉ ሕንፃ እያከራዩ ሌላውን ኪራይ ሰብሳቢ ሲሉ አያፍሩም? • ምን ይደረጋል? • ይኼ ግን ብዙ የሚያሳስብ አይደለም፡፡ • እንዴታ ክቡር ሚኒስትር? • እኔን ሲገመግሙ እኮ ሥጋ ያየ የተራበ አንበሳ ነው የሚመስሉት፡፡ • እንዴት ነው ግን የሚችሉት? • ግምገማው ሲብስብኝ እኔም ጉርሻዬን አጠነክረዋለሁ፡፡ • የምን ጉርሻ ነው? • ኮሚሽኔን ነዋ፡፡ • እ… • እሱ ነው እንደዚህ የአዞ ቆዳ እንዲኖረኝ ያደረገው፡፡ • አይ ክቡር ሚኒስትር፡፡ • ትለምደዋለህ ስልህ? • ክቡር ሚኒስትር በአሁኑ ግምገማ ግን መነሳቴ አይቀርም፡፡ • ከተነሳህ ምን ትሆናለህ? • ምንም እኮ የለኝም ክቡር ሚኒስትር? • ምርጫህን ብቻ ማስተካከል ነው፡፡ • የምን ምርጫ ነው? • ከሁለቱ ‹‹አ›› አንዱን መምረጡ ላይ ነዋ፡፡ • ከየቱና ከየቱ? • ከአምባሳደርና… • እ… • ከአማካሪ!

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ሚኒስትር ደወሉላቸው

• ምን ፈለክ? • ክቡር ሚኒስትር ተረጋግተው ያውሩኝ እንጂ? • ቅድም ግምገማ ላይ ያደረጋችሁኝ ታውቋችኋል? • የፓርቲያችንን ባህል መቼም ጠንቅቀው ያውቁታል? • አሁን ለምን ደወልክ? • አንድ ሪፖርት ስለምልክልዎት ዓይተው በጠዋት እንዲልኩልኝ ነው፡፡ • እኔ ጠዋት ላይ ሥራ ስላለኝ የአንተን ሪፖርት ማየት አልችልም፡፡ • ይኼ ነው ችግርዎ ክቡር ሚኒስትር፡፡ • የምን ችግር ነው? • ቅድም የብቃት ማነስ የተባለው፡፡ • እናንተ የትኛው ብቃት ኖሯችሁ ነው? • ለማንኛውም ከሰሞኑ ዕርምጃ ይወሰድብዎታል፡፡ • የምን ዕርምጃ? • መነሳትዎ አይቀርም፡፡ • ማን ወንድ እንደሚነካኝ አያለሁ፡፡ • ለነገሩ በቀላሉ እንደማይነሱ አውቃለሁ፡፡ • እንዴት ማለት? • ሰሞኑን ቅፅል ስምም ወጥቶልዎታል፡፡ • ምን የሚል? • ሙጋቤ!

ክቡር ሚኒስትሩ ልብሳቸውን ቀይረው ኤርፖርት ሲሄዱ ባለሀብቱን ለመቀበል አርቲስቶች፣ ጋዜጠኞችና ባለሀብቶች ተሰብስበው አገኙ፡፡ ከጋዜጠኛው ጋር እያወሩ ነው

• ብዙ ሰው ሊቀበላቸው መጥቷል አይደል እንዴ? • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡ • ይኼ ሁሉ ሰው ግን እንዴት መጣ? • ባለሀብቱ እኮ ብዙ ወዳጆች አሏቸው፡፡ • አንተም ወዳጃቸው ነህ? • እኔማ በዚሁ ለመወዳጀት አስቤ ነው፡፡ • ይኼ ሁሉ ሰው እንደሚኖር አላወቅኩም ነበር፡፡ • አብዛኛው ሰው እኮ ሊያስጨርስ ነው የሚመጣው፡፡ • ምንድነው የሚያስጨርሰው? • የጀመሯቸውን ፕሮጀክቶች ነዋ፡፡ • ያልከኝ አልገባኝም፡፡ • እዛ ጋ ያለውን ባለሀብት አዩት? • አዎን፡፡ • እሱ የጀመረውን ሕንፃ እንዲጨርሱለት ነው የመጣው፡፡ • እሺ፡፡ • እዛ ጋ ያለውን አርቲስት አዩት ደግሞ? • አዎን፡፡ • እሱ ደግሞ የጀመረውን ቤት ሊያስጨርስ ነው የመጣው፡፡ • አንተስ ምን ልታስጨርስ ነው? • ዕቁቤን!

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ኢንቨስተር ይደውልላቸዋል

• ክቡር ሚኒስትር ሰሙ አይደል? • ምኑን? • ፌስቡክ ላይ የሚወራውን አልሰሙም እንዴ? • እኔ እኮ ፌስቡክን ስም አውጥቼለታለሁ፡፡ • ምን ብለው? • ፌክቡክ፡፡ • ለምን? • እንዴ ፌስቡክ እኮ የአደገኛ ቦዘኔዎች መፈንጫ ሠፈር ነው፡፡ • እንዴት ክቡር ሚኒስትር? • ስማ እዛ የሚወራው ወሬ ፌክ ነው፣ ሰዎቹም ፌክ ናቸው፡፡ • መረጃ ታዲያ ከየት ነው የሚያገኙት ክቡር ሚኒስትር? • እሱን ለእኛ ተወው፡፡ • ከየት ነው የሚያገኙት? • ከተለያዩ የመረጃና ደኅንነት ምንጮቻችን አሊያም ከታወቁ ሚዲያዎች መረጃ እናገኛለን፡፡ • ስለዚህ ፌስቡክ አይሆንም እያሉ ነው? • ነገርኩህ እኮ እሱ ፌክቡክ ነው፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ ለአንድ ብሎገር ጋ ደወሉ

• የበሬ ወለደ ጽሐፎች ያን ያህል ተቀባይነት እያገኙ አይደለም፡፡ • ስማ የምትጽፈው ጽሑፍ እውነት እንዲመስል የሚያደርጉ ሰዎችንም መልምለሃል አይደል? • እሱማ መልምያለሁ ግን ትንሽ የበጀት ጭማሪ ያስፈልገኛል፡፡ • ተጨማሪ በጀት መንግሥት ራሱ መከልከሉን አልሰማህም እንዴ? • ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር ወድጄ አይደለም? • ምንድነው የምታወራው ሰውዬ? • የጫት ወጪዬ ከአቅሜ በላይ ሆኖብኝ ነው፡፡ • እና የጫት እርሻ ይገዛልህ? • ከተቻለማ ደስ ይለኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡ • ቀልዱን ትተህ ሥራህን በአግባቡ ሥራ፡፡

ከክቡር ሚኒስትሩ ጋር ውጭ አገር ቢዝነስ የሚሠራ ወዳጃቸው ደወለላቸው

የት ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትር? አገሬ ነዋ። አሁን እንደው አፍ ሞልቶ አገር አለ ማለት ይቻላል? ምን እያልክ? ደግሞ ምን ተፈጠረ? ይኸው በየቀኑ የምንሰማው እልቂት፣ መፈናቀል፣ ግጭትና ረብሻ አይደል እንዴ? እባክህ ይኼ የፀረ ሰላም ኃይሎች ወሬ ነው። እና አገር ሰላም ነው እያሉኝ ነው? ሰላም ቢሉህ ሰላም ነው እንዴ? ኧረ ተው ክቡር ሚኒስትር። እውነቴን ነው የምልህ፤ ሰሞኑን ራሱ ከአንድ ሥራ ያገኘሁት ትርፍ ቀላል እንዳይመስልህ? ከምንድን ነው ትርፍ ያገኙት? ከዶላር ጭማሪው። እውነት? በቃ የጀመርኩትን ሕንፃ የሚያስጨርሰኝ ነው ስልህ? ግብር ከፈሉ ታዲያ? የምን ግብር? ይኼን ንፋስ አመጣሽ ታክስ ምናምን የሚሉትን ነዋ። ንፋሱን ያመጣሁት እኔ አይደለሁ እንዴ? ለነገሩ እርስዎ እንኳን ንፋስ አውሎ ንፋስ ማስነሳት ይችላሉ።

የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር በጠዋት ከቤት ሊወስዳቸው መጣ

ክቡር ሚኒስትር የሚያሳዝነኝ መጥፎ መሆናችሁ አይደለም፡፡ ምን እያልክ ነው? አሪፍ መጥፎ እንኳን አይደላችሁም፡፡ ምን ይዘባርቃል ይኼ? ለማንኛውም ያኔ ትግል እንዴት ነበር የገቡት? ምን እያልከኝ ነው? ማለቴ ለመታገል ያነሳሳዎት ምንድን ነበር? ያው ሕዝቡ ተበድሏል፡፡ ተጨቁኗል ብዬ አስብ ነበር፡፡ እሱ ነበር ምክንያትዎ? በወቅቱ የነበረው መንግሥት አፋኝና ጨቋኝ ስለነበር ያንን ሥርዓት ለመጣል ነው የታገልኩት፡፡ ስለዚህ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ እያሉኝ ነው? ወዴት ልትሄድ ነው ደግሞ? እኔም ልታገል ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡