Skip to main content
x

የሳምንቱ ገጠመኝ

አሁን የዘነጋሁት አንድ የጎንደር ቅኔ እንዲህ ይላል፡፡ ባለቅኔው አንድ ድግስ ላይ ይጠራሉ፡፡ ገበታም ላይ ይሰየማሉ፡፡ ጠጅ አሳላፊው ይመጣና በተሰነጠቀ የሸክላ ዋንጫ ጠጅ ይቀዳላቸዋል፡፡ እያዘኑ ተቀብለው ጠጁን ቀመስ ያደርጉታል፡፡ ‹ከመ ወይን ጣዕሙ› የሚባልለት ዓይነት ነው፡፡ ጠጁንና የቀረበበትን ዋንጫ አስተያይተው ‹ዋንጫው በጠጁ ከብሯል፣ ጠጁ ግን በዋንጫው ተዋርዷል፣ ዋንጫው ጠጁን ይዞ ይስቃል፣ ጠጁ ግን ዋንጫው ውስጥ ገብቶ ያለቅሳል፤› የሚል ቅኔ ተቀኙ ይባላል፡፡ ያ ሰባራ ዋንጫ ያንን ለመሰለ ምርጥ ጠጅ መጠጫ መሆኑ የማያገኘው ክብርና ዕድል ነው፡፡ እንደ ባህሉ ቢሆን የተሰነጠቀ ዋንጫ የቅራሪ መጠጫ ከመሆን ያለፈ ክብር አልነበረውምና፡፡ ለጠጁ ግን በሰንጣቃ ዋንጫ መቅረቡ ውርደት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ጠጅ ሲሆን የወርቅ፣ ሲቀር ደግሞ የቀንድ ዋንጫ ይገባው ነበር፡፡

አንዳንድ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ክብር ጋር በማይመጥኑ ሰዎች እጅ ወድቀው ሳይ የእኒህ ጎንደሬ ቅኔ ትዝ ይለኛል፡፡ ለእነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያን የምታህል የታሪክ አገር፣ የቅርስ አገር፣ የነፃነት አገር፣ የጥበብ አገር፣ የጀግኖች አገር፣ የልዩ ልዩ ባሕሎችና ወጎች አገር በእጃቸው መግባቷ በሥዕለት የማያገኙት ክብራቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ናትና፡፡ ለኢትዮጵያ ግን በእነዚህ በማይመጥኗት ሰዎች እጅ መውደቋ ውርደቷ ነው፡፡ እነርሱ ሲስቁ፣ ኢትዮጵያ ታለቅሳለች፡፡

‹የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ጳጉሜን 5/6 እኩለ ሌሊት አይገባም› የሚለውን መስማት የማይፈልጉ ሰዎች፣ ጊዜውና ሁኔታው ፈቅዶላቸው ጣፋጯ ጠጅ ኢትዮጵያ እንደ ሰባራው ዋንጫ በእጃቸው ስለገባችላቸው ብቻ አሁንም ‹በከፍታው ዘመን› ሲያወርዷት አየናቸው፡፡ የእጅ ሰዓታቸው ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት እያለ፣ በሥልጣናቸው ከጠዋቱ 12 ሰዓት አደረጉት፡፡ ወይ አይረዱ ወይ አያስረዱ፣ ሰው እንዴት ከሁለቱም ይወጣል? ወይ እኩለ ሌሊት አዲስ ዓመት ገብቷል ሲሉ መከራከሪያውን አምጥቶ ማስረዳት ነው፡፡ ያለበለዚያ ደግሞ የሚቀርበውን መከራከሪያ መቀበል ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዕለት በእኩለ ሌሊት ይገባል ከተባለ፣ በእኩለ ሌሊት የሚገባው መስከረም 1 ቀን ብቻ ነውን? ለምን መስከረም ሁለትስ በእኩለ ሌሊት አይገባም? ሞቅታ፣ ዕውቀትና እውነትን እየሻረ እስከ መቼ መጓዝ ይቻላል? አገር ከፍ የምትለው በጭፈራና በሆታ አይደለም፡፡ በእውነትና በዕውቀት እንጂ፡፡ ችግሩ ግን አሁን ኢትዮጵያ በእጃቸው የገባችላቸው አንዳንድ ሰዎች እውነትም ዕውቀትም የማይፈልጉ መሆናቸው ነው፡፡ ዕውቀት ወደ እውነት፣ እውነትም ወደ ቆራጥነት ይመራልና፡፡ አውሮፕላኑን አብርር ተብሎ ሲሰጥህ እኮ በተፈቀደልህ ከፍታ፣ በተፈቀደልህ ፍጥነት፣ በተፈቀደልህ ሕግ መሠረት፣ ወደ ተፈቀደልህ ቦታ አብርር ማለት እንጂ መሪው እጅህ ስለገባ ብቻ ወደ ፈለግከው ቦታ በፈለግከው መንገድ ይዘህ መሄድ አትችልም፡፡

ሌሊት እንጨፍር፣ ሌሊት ርችት እንተኩስ፣ ሌሊት እንጠጣ ማለት ይቻላል፡፡ የእነርሱ ጭፈራ፣ የእነርሱ አሥረሽ ምችውና ርችት እንዲያምር ስለተፈለገ ግን የኢትዮጵያ ታሪክና ቅርስ መናድ የለበትም፡፡ የኢትዮጵያ ሚሊኒየም የተከበረበትን አሥረኛ ዓመት አከበርን እያልን በሚሊኒየሙ ጊዜ ስናወድሰው የነበረውን ቅርስ ማበላሸት አለብን? ‹ኢትዮጵያ የራሷ የዘመን አቆጣጠር ያላት አገር ናት› ስንል አልነበረም እንዴ ያኔ? ዛሬ በአሥር ዓመቱ ረስተነው እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በእኩለ ሌሊት ለምን ዘመኑን አባትነው? መሠረቱን እያፈረሱስ ከፍታ እንዴት ይገኛል? መቀየርም ካስፈለገ ለተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ፣ በምክንያት መቀየር የሚችለው የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር በሥልጣኑ ይህን የኢትዮጵያ ታሪክ ለምን አባሪ ተባባሪ ሆኖ ሊቀይር ፈለገ?

ዕውቀት ሥልጣን ይሰጣል፣ ሥልጣን ግን ዕውቀት አይሰጥም፡፡ ጊዜ ሥልጣን ይሰጣል፣ ጊዜ ግን ዕውቀት አይሰጥም፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ጊዜ የሰጠው ቅል በድንጋይ ቤት አይሠራም፣ ድንጋይ ይሰብራል እንጂ›› የተባለው፡፡

በጣሊያን ወረራ ጊዜ ጊዜ ስጠን ብለው እሙር እሙር ይሉ የነበሩትን ሰዎች፣

‹አርኩም ይሄድና

ሶልዲውም ያልቅና

ያስተዛዝበናል ይኼ ቀን ያልፍና›

ብሎ ነበር ሐበሻ . . . ፡፡ እንዲህ ዛሬ መድረኩ በእግራችሁ፣ ማይክራፎኑ በእጃችሁ፣ ሚዲያው በፊርማችሁ ሥር ስለሆነ ብቻ የፈለጋችሁትን ታሪክ ሠርዛችሁ የፈለጋችሁትን ለምትጽፉ ‹አርቲስቶች›፣ ለምታስጽፉም ባለሥልጣናት፣  

መድረክ ይፈርስና

ማይኩም ይጠፋና

ሥልጣኑም ያልቅና

ያስተዛዝበናል አግዳሚ ወንበር ላይ እንገናኝና፡፡ እንላችኋለን፡፡

(ዳንኤል ክብረት በፌስቡክ ገጹ እንዳሰፈረው)