Skip to main content
x

የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን ድሮና ዘንድሮ

በወዳጅ ቲ.

አገራችን እ.ኤ.አ. ከ1991 እስከ 2001 ድረስ  ባልተጻፈ፣ ከ2002 ደግሞ በተጻፈ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ተመርታለች። አንዳንዶች ከ1991 እስከ 2001 የነበረውን የውጭ ግንኙነት እንቅስቃሴ እንደ ሁኔታዎች አመጣጥ በደመነፍስ የተከናወነ አድርገው ይወስዱታል። አሥር ዓመታት ግን አጭር ጊዜ አይደለም። ለማንኛውም የአሁኑን የውጭ ግንኙነት ይዘት ከመፈተሽ በፊት የቀድሞውን ማየት ስለሚበጅ እስኪ እንደሚከተለው እንመልከተው።

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት አጀማመር የረዥም ጊዜ ታሪክ ያለው ሲሆን፣  በተነፃፃሪ በይፋና በተደራጀ መልኩ  ከውጭ ዓለም የተጀመረው ግን በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን፣ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚህ ወቅትም የመጀመርያው ሊባል የሚችልና በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ ያተኮረ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሰል ሰነድ ተዘጋጅቶ በተግባር ላይ የዋለ እንደነበር በታሪክ ተመራማሪዎች የተደረሰበት ሲሆን፣ ይኼም በዚያን ጊዜ አገሪቱን ከማዘመን ጋር የተሠራ ታላቅ ሥራ ተደርጎ በወቅቱ ተወስዷል፡፡ አፄ ቴዎድሮስን የተኩት ዮሐንስ አራተኛም ምንም እንኳን በአውሮፓያውያን ተስፋፊነትና በጣሊያን ሰርጎ መግባት የተነሳ ከግራም ከቀኝም የተወጠሩበት ሁኔታ ቢኖርም፣ መለስተኛ በሆነ ደረጃም ቢሆን የአፄ ቴዎድሮስን የውጭ ፖሊሲ ለማስቀጠል ጥረት ማድረጋቸውን ታሪክ መዝግቦታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1889 አፄ ዮሐንስን  የተኩትና  በ1913 ያረፉት አፄ ምኒሊክ ጣሊያንን በወቅቱ የባህላዊ ዲፕሎማቲክ ሥልት በሆነው በምልጃና በሽምግልና  ማሳመንና ከአገር ማስወጣት ባለመቻላቸው፣ አይቀሬው ዘመቻ ተከስቶ እ.ኤ.አ. በ1896 የመጀመርያውን የዓድዋ የጦርነት  ድል ሊያደርጉ ችለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1913 ጀምሮ ብዙም የጎላ ዲፕሎማቲክ ክስተት ሳፈጠር ቆይቶ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት በተለይም የውጭውን ዓለም አሠላለፍ በመቃኘት በአዲስ መልክ የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ1930 አፄ ኃይለ ሥላሴ ከነገሡበት ጀምሮ ነው፡፡  በወቅቱም አገሪቱ ሥርዓት ያላት፣ ጠንካራና ዓለም አቀፋዊ ሕጎች ተገዢ እንደሆነች በተለያዩ መንገዶች ማሳየት ጀመሩ፡፡ የንጉሠ ነገሥት ዘመናቸውን ሳይጀምሩ እንኳን ገና አልጋ ወራሽ በነበሩበት ወቅት አገሪቱ የመንግሥታት ሊግ ( ሊግ ኦፍ ኔሽን) አባል እንድትሆን እ.ኤ.አ. በ1923 ተደራድረው መሥራች እንድትሆን አስችለዋታል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1936 እስከ 1941 ድረስ የጣሊያን ወረራ እክል ሆኖ፣ ባያደናቅፍና ሒደቱን ባይቀለብስ ኖሮ ኢትዮጵያን በዓለም የፖለቲካ አሠላለፍ ጉልህ ሥፍራ እንዲኖራት የጀመሩት ጥረት ይሳካላቸው እንደነበር ብዙዎቹ ይስማሙበታል፡፡ ሆነም ቀረ ጣሊያን ተሸንፎ ከወጣ፣ እሳቸውም ከግዞት ከተመለሱና  እ.ኤ.አ. በ1941 እንደገና የንግሥና መንበራቸውን ከያዙ በኃላ የጀመሩትን አገሪቱን ከቀሪው ዓለም ጋር የማስተሳሰሩ፣ አቋሟን የመገንባትና ተሰሚነትን የማግኘት ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡

አፄ ኃይለ ሥላሴ ከሁለተኛው ጦርነት በኃላ በተለይም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ መታወቅ በመጀመራቸው፣ ከምራባዊያን ጋርም መቀራረብ በመፍጠራቸውና ለአፍሪካ አገሮች ነፃነት ድምፅ ማሰማት በመጀመራቸው በወቅቱ  ከአፍሪካ አገሮች ሁሉ የተለየ ተደማጭነትንና ተቀባይነትን ማግኘት ችለዋል፡፡ በጋራ ጉዳዮችም ላይ በግንባር ቀደምነት ከሚሠለፉ ተርታ አገሪቱን ለማሠለፍ በቅተዋል፡፡

በጋራ የሰላምና ደኅንነት ተሳትፎ እንደ አብነት የሚጠቀሰውም እ.ኤ.አ. ከ1951 እስከ 1953 የኮሪያ ጦርነት ወቅት አትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ሥር ከአፍሪካ አገሮች የመጀመርያዋ እግረኛ ወታደር ላኪ አገር ሆና መሳተፍዋ ነው፡፡ በወቅቱ አሥራ ስድስት አገሮች ብቻ ነበሩ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔና ጥሪ ምላሽ የሰጡት። በዚህ ጦርነት ኢትዮጵያ 6,037 ወታደሮች ያሳተፈች ሲሆን፣ በ235 የውጊያ ግንባሮች ተሳትፋ ሁሉንም አሸንፋለች፡፡ በጦርነቱ 121 ወታደሮች የተሰው ሲሆን፣ በመጨረሻ በጦርነቱ ማብቂያ በተደረገው ማጣራት የጦር ምርኮኛና እስረኛ ያልነበራት ብቸኛ አገር ኢትዮጵያ እንደሆነች በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም እ.ኤ.አ. በ1960 ለኮንጎ የሰላም ማስከበር የሰላም አስከባሪ ሠራዊት በመላክ ተሳትፎ ተደርጓል፡፡ በሌላ በኩል አገሪቱ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጎልበት በዲፕሎማቲክና በወታደራዊ ትብብር ላይ ያካሄደችው እንቅስቃሴ ከኃያልዋ አሜሪካ ልዩ ግምት እንዲቸራትና የአሜሪካ ወዳጅ አገሮችም አትኩሮት እንዲሰጧት አስችሏታል፡፡ ይኼ የመጀመርያው የሰላም ማስከበር ተልዕኮዋ ነበር

ከዚህ በመነሳትም በተባበሩት መንግሥታትም ድርጅትም ይሁን በሀያላን አገሮች የተገኘውን አዎንታዊ ድጋፍና ትኩረት መሠረት በማድረግም፣ የአፍሪካ አገሮች ነፃ የሚወጡበት ሁኔታ የማመቻቸት ሥራ ንጉሡ ሠርተዋል፡፡ በዚህም መሠረት የአፍሪካውያን የነፃነት ጉዳይ በአጀንዳነት ተይዞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መድረክ ውይይት እንዲካሄድበት ከማስቻል ባሻገር፣ የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ እንዲያስተላለፍ ያላሰለሰ ጥረትና ግፊት አድርገዋል፡፡ በዚህም የአፍሪካ ልሳን ተብለው የተጠቀሱ የመጀመርያ የአገር መሪ ለመሆን አስችሏቸዋል፡፡ በወቅቱም የፓን አፍሪካኒዝም ጽንሰ ሐሳብና መርህ ውስጥ ለውስጥ ሲሠራበትና ሲመከርበት የነበረ በመሆኑ፣ ይኼንን በተደራጀ መንገድ ለማካሄድና ለማስተባበር እንዲረዳ የአፍሪካ አንድነት ጽሕፈት ቤትን ማቋቋም አስፈላጊ እንደሆነ የማስተማር ሥራን ንጉሡ ሠሩ፡፡ ከፍተኛ የማሳመን ተግባራትን በማከናወን የአፍሪካ አንድነት ደርጅት ጽሕፈት ቤት (OAU) በአዲስ አበባ እ.ኤ.አ. በ1963 ተመሠረተ፡፡ ይኼም የንጉሡን ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች ብቃትና ውጤት አረጋገጠ፡፡ በአፍሪካ መሪዎች በኩል ተቀባይነትንና ከበሬታን፣ በዓለም መሪዎች በኩል ደግሞ አድናቆትንና ዕውቅናን እንዲያገኙ አስቻላቸው፡፡      

ደርግ በመጀመርያዎቹ ዓመታት ንጉሡን የውጭ ግንኙነት ሳይቀይር ነበር የተጓዘው፡፡ ይሁንና የዘመኑ ማርክሲስታዊ አይዲዮሎጂ በሲቪሉም ሆነ በወታደራዊ መሪዎች ዘንድ እየተስፋፋ በመምጣቱና ይኼም የአሜሪካንን ወዳጅነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ በመክተቱ፣ አንዳንድ በውጭ ግንኙነት መርሆዎች ላይ ለውጦች መታየት ጀመሩ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1953 በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል በተፈረመው “የጋራ መከላከያ ትብብር ስምምነት” መሠረት የአሜሪካን ጥቅም የሚጠበቅበት የቃኘው ሚሊታሪ ቤዝን በተመለከተ ደርግ በ1970ዎቹ አጋማሽ ላይ ጀርባ ማሳየት ጀመረ፡፡ በተለይም በወቅቱ ከሶቭየት ኅብረት መስፋፋት ጋር እንዲህ ዓይነት ጠቀሜታ ያለውን ስትራቴጂካዊ የሚሊተሪ ቤዝ ማጣት ፍፁም ሊዋጥላቸው አልቻለም፡፡ ይኼንን በማንኛውም መንገድ ማስጠበቅንና ተፅዕኖ ማሳደር እንደሚኖርባቸው ቢያምኑም ለተወሰኑ ዓመታት ግን ምንም ሳያደርጉ ቆይተዋል።   

አሜሪካ ከዚህ አቋሟ ወጥታ የደርግን ሰብዓዊ መብት ረገጣ በግልጽ ማውገዝ የጀመረችው እ.ኤ.አ. በኖቬምበር 23 ቀን 1974 በታሪክ “ደማዊው ቅዳሜ” (Bloody Saturday) ተብሎ ከሚታወቀው ግድያ በኋላ ነው፡፡ ይኼም 59 ከሚሆኑ የንጉሡ መኳንንትና ባለሥልጣናት ጋራ በተያያዘ ነበር። ከዚያም በመቀጠል በአሜሪካ የተወሰደው ሌላው የውግዘት ዕርምጃ ደርግ  የኤርትራን ችግር በወታደራዊ ዕርምጃ እደመድመዋለሁ ብሎ፣ መደበኛ ሠራዊቱንና የሚሊሺያ ጦር ወደ ኤርትራ ባዘመተበት ጊዜ ነበር፡፡ ጊዜውም ከ“ደማዊው ቅዳሜ” ግድያ ጥቂት ወራት በኋላ ነበር፡፡  ፕሬዚዳንት ካርተር ከፕሬዚዳንት ፎርድ በተለየ ሁኔታ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ጉዳይ የአስተዳደራቸው የውጭ ግንኙነት እምብርት አድርገው ወሰዱት፡፡ ከአሜሪካ ማንኛውንም ዓይነት ወታደራዊ ድጋፍ ለማግኘት የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ዋነኛ መሥፈርት እንደሆነ በይፋ አሳወቁ፡፡  ደርግ በዚህ ወቅት አጣብቂኝ ውስጥ ገባ፡፡ በአገር ውስጥ ያለው የውስጥ የፖለቲካ ፍትጊያው ይኼንን ለማድረግ እንደሚያዳግተው ተገነዘበ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ደርግ  ከኤርትራ በኩል ያለውን ችግር በወታደራዊ ኃይል ለመፍታት የጦር መሣሪያዎች ያስፈልገዋል። በምሥራቅ የዚያድ ባሬ መንግሥት አቆብቅቦ የሚጠብቀው አመቺ ጊዜን ለማምከን የመከላከያ ኃይሉን መገንባት ለነገ እንደማይባል አወቀ። በዚህ የተነሳም አማራጭ መፈለግ የግድ በመሆኑ ፊቱን ወደ ቻይናና ሶቭየት ኅብረት አዞረ፡፡ በዕርምጃውም የአሜሪካና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ መሄድ ጀመረ፡፡ ደርግ ይባስ ብሎ እ.ኤ.አ. በ1977 ቃኘውን በመዝጋት የተወሰኑ የአስተዳደር ሠራተኞች ብቻ እንዲቆዩ ፈቀደላቸው፡፡ መሻከሩ ወደ መቆራረጡ ተሻገረ፡፡ ይኼ ሁኔታ ያስደሰታት ሶቭየት ኅብረት ደግሞ ለደርግ ወታደራዊ መሣሪያ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ጀመረች፡፡ የአገሪቱ የውስጥ አጠቃላይ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ በውስጥ የተደራጁ ኃይሎች ጥቃት፣ እንዲሁም በውጭ ወረራ ምክንያት ደርግ ከሶቭየት ኅብረት ጋር እ.ኤ.አ. ከ1976  እስከ 1990 ድረስ ለ14 ዓመታት ተቆራኝቶ እንዲኖር አስገድዶታል፡፡ አማራጭም አልነበረም፡፡ ሶቭየት ኅብረት በዚህ ጊዜ ውስጥ ለወታደራዊ ድጋፍ ብቻ ወደ 13 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ድጋፍ መስጠቷን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የደርግ መንግሥት በስተመጨረሻም ከሶቭየት ኅብረት አቋም ጋር  ባለመጣጣሙና በአገር ውስጥ ያሉ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ተዳምረው እ.ኤ.አ. በ1989 ደርግ የተወሰኑ ማሻሻያዎችን ማድረግ ጀመረ፡፡ በዚህም መሠረት ከዚህም ከዚያም የሚያጣቅስ ገሚስ ገበያ መር (Mixed Economy) የሚል ስትራቴጂ በመጨረሻ ሰዓት ቀርፆ ተግባራዊ ማድረግ ተጀመረ፡፡ በዚሁ ቀጥሎም የሶቭየት ኅብረት የኢትዮጵያ ጥምረት (Alliance) እ.ኤ.አ. በ1990 አበቃለት፡፡ ደርግ ከዚህ ፍቺ በኋላ የወታደራዊ ድጋፍ ፍላጎቱን ለሟሟላት ቻይናንና እስራኤልን ቢቀርብም፣ የሶቭየትን ያህል ሊሆኑለት ባለመቻሉ ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡

  ደርግ እ.ኤ.አ. ከ1976 እስከ 1990 ድረስ አሠላለፉን ከሶቭየት ኅብረት ጋር ያድርገው እንጂ፣ ከምዕራባዊን የአውሮፓ አገሮች የሚያገኘው የኢኮኖሚ ልማት ድጋፍና የሰብአዊ ዕርዳታ ነበር፡፡ በእነዚህ ጊዜያት የአውሮፓ ኮሚሽን በአውሮፓ የልማት ፈንድ (European Development Fund - EDF) ይሰጥ የነበረው አልተቋረጠም፡፡ የዓለም ባንክ  እ.ኤ.አ. እስከ 1981 ድረስ የማንገራገር ሁኔታ ቢያሳም፣ ከዚያ በኋላ ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የፋይናነስ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይታል፡፡ የዓለም የገንዘብ ፈንድ በተመሳሳይ የተለያዩ ኢኮኖሚ ማረጋጊያ ድጋፎች ሲያደርግ ነበር፡፡ የስዌዲሽ ተራድኦ ድርጅት (SIDA) እና የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID)፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ በመስጠት በዋነኛነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1980 ከልማትና ከሰብዓዊ ዕርዳታ ጋር በተያያዘ የምዕራባዊያን ድርሻ 80 እጅ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የምዕራባዊያን የግል ባለሀብቶችም በመጀመርያ ጊዜ ብቅ ብቅ ብለው ይታዩ የነበረ ሲሆን፣ በመጨረሻው የደርግ ዘመን ግን በአንዳንድ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት ፍላጎት አሳይተው ሲንቀሳቀሱ ተስተውለው ነበር፡፡  

  “የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና የብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ” ተብሎ የሚታወቀውና እ.ኤ.አ. በኖቬምበር 2002 ይፋ የሆነው ፖሊሲ አገሪቱ ለረጅም ዓመታት ሳይኖራት የቆየ፣ በአሁኑ ጊዜ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ የዳሰሰና አገሪቱን ወደ ላቀ የዲፕሎማቲክ እንቅስቃሴ ያሸጋገረ መሠረታዊ ሰነድ እንደሆነ በመሪ ድርጅቱ ሲነገርለት ቆይቷል፡፡ ሰነዱ ከመግቢያ ክፍሉ ውጪ በሁለት የተከፈለ ሲሆን፣ የመጀመርያው መሠረታዊ መርሆዎችን የያዘና ሁለተኛው ደግሞ አገሪቱ ከሌሎች አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት በተመለከተ የሚዳስስ ነው፡፡ የመሠረታዊ መርሆዎቹ ክፍል ሦስት ዓበይት ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስስ ሲሆን፣ አንደኛው የውጭ ግንኙነትና የብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲው መሠረቶች፣ ሁለተኛው የፖሊሲው ግቦች፣ ሦስተኛው ደግሞ የፖሊሲው ስትራቴጂዎች ብሎ ያስቀምጣቸዋል፡፡ እንደ ፖሊሲው ምሰሶ መርሆዎች (Pillars) ሦስት ዓበይት ጉዳዮች የተካተቱ ሲሆን፣ እነሱም ልማትና የዲሞክራሲ ግንባታ፣ ብሔራዊ ኩራት፣ እንዲሁም ግሎባላይዜሽን የሚሉ ናቸው፡፡

እንደ ፖሊሲው ዋነኛ ዓላማ የተቀመጠው “ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ለአገሪቱ ልማትና ለዴሞክራሲ ምቹ መሆናቸውን ማረጋገጥ” የሚል ነው፡፡ በተጨማሪም የፖሊሲው መሠረቱና ግቡ በተመሳሳይም “ልማትንና ዴሞክራሲን ዕውን ማድረግ ነው” ይላል፡፡ እነዚህን ዓላማዎችና ግቦች መሠረት በማድረግም ግልጽ የሆነ ስትራቴጂ ማውጣቱ ተገቢ እንደሆነ በመግለጽ ስትራቴጂዎቹን በስድስት ትኩረት መስኮች ማለትም በአገር ውስጥ ክንውኖች ላይ፣ ስትራቴጂው ኢኮኖሚን ማዕከል በማድረግ ላይ፣ በበቂ ትንተና ላይ በመመሥረት አገራዊ ጥቅምን አሟጦ በመጠቀም ላይ፣ በበቂ ትንተና ላይ በመመርኮዝ ሥጋቶችን በመቀነስ ላይ፣ ለሥጋት ተጋላጭነትነት በመቀነስ ላይ፣ እንዲሁም አስተማማኝ የመከላከያ አቅም በመገንባት ላይ እንደሚያተኩር ተቀምጧል፡፡

አገሪቱ ከውጭው ዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት በተመለከተም ስትራቴጂው በታሪካዊ ግንኙነት፣ የግንኙነቱ ጠቀሜታና የፖሊሲ አቅጣጫዎች በሚሉ ክፍሎች ከፋፍሎ ለማስቀመጥ ሞክሯል፡፡ ከአንዳንድ አገሮችና ሪጅኖች ጋር ያለውን ግንኙነት በሚዳሰስበት ወቅት በግንኙነቶቹ ሒደት ያሉት ችግሮች ተነስተዋል፡፡

ሰነዱ አገሪቱ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት በተመለከተ በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ በመዳሰስ ከተናጥል አገሮች ጋር ማለትም ከኤርትራ፣ ከሶማሊያ፣ ከሱዳን፣ ከጂቡቲ፣ እንዲሁም ከኬንያ ጋር ያለውን ይዳስሳል፡፡ በተጨማሪም ከኢጋድ ጋር ያለውን ግንኙነት በአጭሩ ያሰፍራል፡፡ ከዚያም በመቀጠል ከቀሩት የአፍሪካ አገሮች ጋር ያለውን በጥቅሉ የሚዳስስ ሲሆን፣ በመቀጠል በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሥር የግብፅን፣ የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮችን፣ የሰሜን አፍሪካ አገሮችን፣ የእስራኤልን፣ የቱርክንና የኢራንን ይዳስሳል፡፡ በማስከተልም በአውሮፓ ሥር የአውሮፓ ኅብረትንና የሩሲያ ፌዴሬሽንን ይነካካቸዋል፡፡ ከእስያ አገሮት ከጃፓን፣ ከቻይናና ከህንድ ጋር ያለውን ግንኙነት ለየብቻው የዳሰሰ ሲሆን፣ በመጨረሻም ከዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ከዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ያለውን ግንኙነት ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡

እንደ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በተፈጥሮው ወጥ የሆነ አቀራረፅ የለውም፡፡ አገሮች ከራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በመንተራስ የየራሳቸውን ይቀርፃሉ፡፡ ብዙዎች የሚስማሙባቸውና የሚጋሩዋቸው መሠረታዊ ሐሳቦች ግን አሉ። የመጀመርያው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የውስጥ ፖሊሲ ተቀጥላ አድርጎ መውሰድን ነው። ሁለተኛው ደግሞ ፖሊሲው የአገሪቱን የፖለቲካዊ፣ የደኅንነት፣ የኢኮኖሚና ሌሎች ጠቃሚ ፍላጎቶችን መጠበቅ (Defend) እና ማስተዋወቅና ማሟላት (Promote) የሚለው ነው። በተጨማሪም ሁሉም አገሮች እንደ መሠረታዊ መርሆዎቸ የሚያሰቀምጧቸው ሉዓላዊነትንና ጥገኛ አለመሆንን፣ በሌሎች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባትን፣ መልካም ጉርብትናን፣ በሰላም አብሮ መኖርን፣ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ መርሆዎቸን ማከበር የሚሉት ናቸው። የውጭ ጉዳይ ግንኙነት ፖሊሲ በሁሉም አገሮች ዘንድ አንኳር እሴቶች ተብለው የሚታወቁትን ሰላምን፣ ሰብዓዊነትን፣ ፍትሕንና እኩልነትን መሠረትና ማዕከል በማድረግ መዘጋጀት እንዳለበት ሁሉም ይስማሙበታል።

ይሁንና የኢሕአዴግ ሰነድ በርካታ በጎ ጎኖች እንዳሉት ሁሉ በብዙ ገጽታዎቹ ይተቻል። በመጀመርያ የውጭ ግንኙነት ሥራዎችና ግቦች ምንም እንኳን ከብሔራዊ ደኅነነት ጋር የተያያዙ ቢሆንም፣ ፖሊሲው ከዲፕሎማሲ ይልቅ ለመከላከያና ለደኅንነት ሰፊ ክፍል ሰጥቶ እንደተዘጋጀ ብዙዎች ያምኑበታል። የደኅንነቱ ጉዳይ ለብቻው መስተናገድ እንደነበረበት በርካቶች ይስማማሉ። በዚህ የተነሳም ሰነዱ በዘመኑ የሰጥቶ መቀበል ዲፕሎማሲ መርህ ድርቅ ተጠቅቶ ጠብ ጠብ በሚሉ አገላለጾች ከመንበሽበሽ ባሻገር ፎካሪ ነው ይሉታል።

በሁለተኛ የሚነሳው የይዘቱ ጉዳይ ነው። የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የአገር ውስጥ ፖሊሲ ተቀጥላ ነው ከተባለ፣ በቅድሚያ የውስጥ ችግሮችንና እጥረቶችን በመተንተን በውጭ ግንኙነት ሥራዎች መሸፈንና መያዝ ያለባቸው መለየት ይኖርባቸዋል። በዚሀ ደረጃ ለፖለቲካ ፍጆታ ሳይሆን ለአገር ጥቅምና ህልውና ሲባል ችገሮቻችን የእኛው የፖለቲካ ክስረት ውጤት ናቸው ብሎ አምኖ የመቀበልና ለዚህም ተስማሚ ፖሊሲ መቅረፅ ያስፈልጋል። ድፍረት፣ ቆራጥነትና ተዓማኒነትንም ይጠይቃል። በመሆኑም አገራችንን ቀፍድዶ የያዛት ድህነትና ኋላ ቀርነት፣ የዴሞክራሲ እጥረት፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ እንዲሁም የፍትሕ ዕጦት መሆኑ አያጠያይቅም። እነዚህ ጉዳዮች ከውጭ ግነኙነት ሥራዎች ጋር በእጅጉ ይቆራኛሉ። በእርግጥ ከእነሱ ጋር የተያያዙ ቸገሮቻችንን ለመፍታት በዋናነት የመንግሥት መሪነትና የአስፈጻሚ ብቃት አስፈላጊና ቁልፉ  ቢሆንም፣ ከውጭ ግነኙነት እንቅስቃሴዎች ከሚገኘው ፋይዳ አንፃር የመንግሥት የመሪነት ድርሻ ከፍተኛ  ያደርገዋል። በማደግ ላይ ያሉ ብቻ ሳይሆኑ አደጉ የሚባሉ አገሮቸ ሁሉ እነዚህን መሠረታዊ ጉዳዮች በወጭ ግንኙነት ፖሊሲዎቻቸው ውስጥ አካተው እንደሚገኙ  ሰነዶቻቸውን በመፈተሽ ማወቅ ይቻላል። በእርግጥ የፖሊሲ ይዘት አነዳደፋቸው እንደ ተጨባጭ ሁኔታቸውና ፍላጎታቸው ይለያያል። የአገራችን  ፖሊሲ አንዱ እጥረት ይኼንኑ በውሉ ተንትኖ አለመያዙ እንደሆነ ይታያል።

ሌላው ጉድለት በስትራቴጂው ውስጥ የተቀመጡትና ከአገሮች ጋር ያለውን ግነኙነት የሚመለከቱ ናቸው። ከተመረጡ አገሮች ጋር ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት በሚፈተሽበት ወቅት፣ በቅድሚያ የተሞከረው የታሪካዊ ግንኙነትና በመካከል ያሉ የቸግሮች ደረጃን መዳሰስና መለየት ነው። በዚህ ሒደት ግልጽ ካልሆኑት መካከል በመጀመርያ በእርግጥ በሰነዱ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ የሥጋት ትንተና መካተት ነበረበት የሚለው ነው። አንዳንድ አገሮች እንዲህ ዓይነቱን የተናጠል የሥጋት ትንተናን በይፋ ሰነድ ላይ አያወጡትም። ምክንያቱም ችግር አለብን ብለው በሰነድ በይፋ ካስቀመጡ በኋዋላ ዲፐሎማሲያዊ ሥራን በተሟላ መንገድ ማካሄድ ስለሚያስቸግር ነው። ይኼም በመተማመን ላይ እክል እንደሚፈጥር ያምኑበታል።  በርካታ አገሮች ከሌሎች አገሮች ጋር ችግር ቢኖርባቸው እንኳር በፖሊሲ አቀራረፃቸው በቅድሚያ መነሻ የሚያደርጉት ችግር የለሽነት (Zero Problem) የሚለውን መርህ ነው። በዚህም የተነሳ የመፍትሔ አቅጣጫዎቻቸው በትብብርና ጉድኝት (Cooperation and Partnership) ላይ ያተኮሩ እንዲሆኑ ያደርጋሉ። በልማትና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባለው ትብብር ጠፍንጎ በመያዝ  የሚያቃቅሩ ስሜቶችን ማምከን እንደሚቻል ያምኑበታል። የእኛው በተፃራሪው የተዘጋጀ ይመስላል።

በሰነዱ ትኩረት ካላገኙት መካከል የዳያስፖራን ጉዳይ የሚመለከት ነው። በእርግጥ ምንም አልተነሳም ማለት አይቻልም። ይሁንና በስም ደረጃ ከመጥቀስ ባሻገር እንደ አንድ መሠረታዊ ጉዳይ መቀመጥ ይኖርበታል። የበርካታ አገሮችን ፖሊሲ ማየት እንደሚቻለው በውጭ የሚኖሩ ዜጎቻቸውን መብትና ጥቅም በማስጠበቅ ደረጃ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ይቀርፃሉ። ፊሊፒንስና ማሌዥያ እንደ አብነት የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በፖሊሲያቸው ካስቀመጡት ሦስትና አራት የፖሊሲ ምሰሶዎች (Pillars) መካከል በውጭ የሚኖሩ ዜጎቻቸውን መብትና ጥቅም ማስጠበቅ  አንደኛው በማድረግ ያስቀምጣሉ።  በመሆኑም ይኼ ጉዳይ በቂ ትኩረት በሰነዱ ውስጥ ተሰጥቶታል ለማለት አያስደፍርም።

ሌላው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ይዘቶች በየወቅቱ መፈተሽ እንደሚኖርባቸው የሚያስገድዱ ሁኔታዎች አሉ። ዋነኛዎቹም የየአገሪቱ የውስጥ ተጨባጭ ሁኔታ፤ የአካባቢያዊ ሁኔታና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎቸና ከስተቶች ናቸው። የውጭ ፖሊሲ በየወቅቱ የሚፈተሽ መሆን እንዳለበት ቢታመንም፣ እስካሁን በአገራችን ድፍረቱ ወይም ፍላጎቱ አልታየም። ለአብነት በሰነዱ ሱዳን አሁንም ድሮ የምናውቃት አንድ ሱዳን ነች። በሰነዳችን ወዳጅ ለምትባለው ደቡብ ሱዳን እስካሁን ዕውቅና አልተሰጠም። የአውሮፓ አባል አገሮች በሰነዱ አሁንም 15 ናቸው። አሥራ ሁለቱ ከእኛ ዕውቅና ለማግኘት መደራደር ይኖርባቸዋል የሚል ጥያቄ ያስነሳል። በሰነዱ ውስጥ ከተለያዩ አገሮች ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት ያለው ትንታኔ አሁን ባለንበት ሁኔታ አይሠራም። ሁኔታዎች ተለዋውጠዋል። 

የውጭ ግንኙነት ሥራችን የፖሊሲ ብቻ ሳይሆን በውስጥ የአሠራርና አደረጃጀት ደዌ ክፉኛ የተጠቃ ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው። ከሚነሱት መካከል አንዱ የመሥሪያ ቤቱ ባሀሪይ ነው።  መሥሪያ ቤቱን በጥናት ከማያምኑት ውስጥ የሚፈርጁት በርካታ ናቸው። በተለይም የእሳት ማጥፋት ዓይነት አካሄድ የተጠናወተው አሠራራችን የተጠናና የሰከነ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳናካሄድ አስቸሎናል ብለው የሚያምኑት ቁጥር አነስተኛ አይደለም። ጥናት የሚባል ነገር የለም፣ የሁኔታዎች ትንተናና የወደፊት ትንበያ  የሚባል የለም፣ ለዚህ ተበሎ የተመሠረተ ብቁ ማዕከል የለም፣ ስትራቴጂያዊ አስተሳሰብና አሠላለፍ አይታወቅም፣ በአጠቃላይ እንደ ጓያ ለቃሚ የፊት የፊቱን ብቻ የሚያይ ተቋም ይሉታል። ፊውዳላዊ አስተሳሰብ ተንሰራፍቶበት ያለበት ብቸኛው መሥሪያ ቤት አድርገው የሚያዩትም አሉ።  የተጋነኑ ሪፖርቶች በማቅረብም ከሚታሙ መሥሪያ ቤቶች አንዱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤታችን ነው።

ዲፕሎማሲያችን ከባህላዊ አሠራር የሚላቀቅበት ጊዜ እንዲያው አንዳች ነገር ካልተፈጠረ በስተቀር  ቅርብ ላይሆን እንደማይችል ግምታቸውን  ሳይሸሽጉ የሚናገሩ በርካቶች ናቸው። እስቲ ምን ያህሉ ነው በባይላተራል (በሁለትዮሽ) ሆነ በመልቲላተራል (በባለ ብዙ) ግንኙነት ዙሪያ ሥልጠና ወስዶ እየሠራ ያለው? ምን ያህሉ ነው ልምድና ክህሎት እንዲያገኝ በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ መደረኮች እንዲሳተፍ የተደረገው? እንዲያው እስቲ የድርድር ብቃት ያለው ዲፕሎማት ለማፍራት ምን ተደርጓል? መቼ ነው ዲፕሎማቶቻችንን ከአይናፋርነትና ከድንጉጥነት የሚላቀቁት? አቅም ካልገነባንና ብቃትንና ክህሎትን ካላሳደግን ዲፕሎማሲያችን የበለጠ ደርዝ የለሽና ፈዛዛ እንደሚሆን ብዙዎች ይስማሙበታል።

መቼም ያለፈን ናፋቂ አያድርገንና በንጉሡ ጊዜ በየመድረኮቹ ተሰሚነታችን የተለየ ነበር ይባላል። ዋናው የአገራችን ልዑክ አባላት ከአገር ሲወጡ በቂ ዝግጅት አድርጎ ነው አሉ የሚጓዙት። በተለይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መድረክ ለሚደረግ ተሳትፎ ልዩ ግምት እንደሚሰጥ ይነገራል። በንጉሡ ሳይቀር የቅርብ ክትትል ይደረግበታል ይባላል። በንጉሡ ዘመን አብዛኛው የአፍሪካ አገሮች  ነፃነታቸውን ስላላገኙ  በሚነሱ ጉዳዮች ላይ አቋም መያዝ ይቸገራሉ። ታዲያ ወደ ዋናው መሥሪያ ቤታቸው ደውለው የሚያገኙት መልስ በወቅቱ መሪነታችንን የሚያሳይ ነበር። በየመድረኩ ለሚነሱ ማናቸውም ጉዳዮች የኢትዮጵያን ልዑክ ቡድን ተከትለው እጅ እንዲያወጡና ድምፅ እንዲሰጡ ይታዘዙ እንደነበር የቀድሞ ዲፕሎማቶች ያስታውሳሉ። ብዙዎች በአሁኑ ይዞታችን  በእጅጉ ይቆጫሉ።

   እንግዲህ ይኼ “ሳይሸራረፍ” የሚለውን ትተን ለመሠረታዊ የፖሊሲ ፍተሻ መነሳቱ ኃላፊነት ከሚሰማው አካል የሚጠበቅ ሆኖ ይገኛል። ለነገሩ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ፖሊሲዎች ማለት ይቻላል መሠረታዊ ለውጥ ይሻሉ፡፡ ምክንያቱም ለ26 ዓመታት መሠረታዊ የዕድገት ለውጥ አላመጡም።

በስተመጨረሻም  እስካሁን ድረስ 25 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተሹመው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን መምራታቸውን ያውቃሉ፡፡ የአሁኑ 26ኛው ናቸው፡፡  በአገራችን ታሪከ የመጀመርያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር ራስ ሙሉጌታ ይገዙ ይባላሉ፡፡ የተሾሙበት ጊዜም እ.ኤ.አ. በ1916 ነበር፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ አልጋ ወራሽ በነበሩበት ጊዜ እ.ኤ.አ. ከ1917 እስከ 1930 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ አሥረኛው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ፡፡ ለአጭር ጊዜ የመሩት አቶ ተስፋዬ ታደሰ የተሰኙ ሲሆኑ፣ በደርግ የመጨረሻ ዓመት እ.ኤ.አ. በ1991 ለአንድ ወር ብቻ አገልግለዋል፡፡ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉት ደግሞ አቶ ሥዩም መስፍን ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1991 እስከ 2010 ለ20 ዓመታት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡