Skip to main content
x
ከዳያስፖራው 78 በመቶ ያህሉ መደበኛ ባልሆኑ የሐዋላ መላኪያዎች እንደሚጠቀሙ በጥናት ተመለከተ

ከዳያስፖራው 78 በመቶ ያህሉ መደበኛ ባልሆኑ የሐዋላ መላኪያዎች እንደሚጠቀሙ በጥናት ተመለከተ

ዘንድሮ 4.6 ቢሊዮን ዶላር ይጠበቃል
በተመድ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት (አይኦኤም) አማካይነት የሚተገበረውና፣ የአውሮፓ ኅብረት ድጋፍ ያደረገበት የውጭ ሐዋላ ገቢን የተመለከተው ጥናት ይፋ እንዳደረገው፣ በውጭ ከሚኖሩና ቁጥራቸው ከሦስት ሚሊዮን በላይ ከሚገመቱ ኢትዮጵያውን መካከል፣ 78 በመቶ ያህሉ መደበኛ ባልሆኑ የሐዋላ ዘዴዎች ለመጠቀም ተገደዋል፡፡

የኢትዮጵያን መደበኛ የሐዋላ ገቢ ማሳደግ ወይም “Scaling up Remittances to Ethiopia” የተሰኘውን ጥናት ያካሄዱት የዘርፉ ባለሙያ ሊዮን አይዛክስ እንደጠቀሱት፣ በውጭ ከሚኖሩ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ውስጥ በመደበኛ ባልሆኑ የሐዋላ በተለይ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን በመደበኛና ሕጋዊ መንገድ ከውጭ ገንዘብ ለመላክ እየተቸገሩ እንደሚገኙ በጥናታቸው ይፋ አድርገዋል፡፡

ኢትዮጵያውያኑ በመደበኛ መንገድ ገንዘብ መላክ ካልቻሉባቸው ጋሬጣዎች መካከል የመላኪያ ዋጋ መወደድ አንዱ ነው፡፡ በአብዛኛው የዓለም ክፍል የሐዋላ መላኪያ ክፍያ እስከ አሥር በመቶ እንደሚደርስ የጠቀሱት አይዛክስ፣ በኢትዮጵያ የሚከፈለው የሐዋላ አገልግሎት ክፍያ ዋጋ 7.3 በመቶ ገደማ በመሆኑ ከሌሎች አካባቢዎች አነስተኛ ነው ቢባልም የተጋነነ ዋጋ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይሁንና ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገሮች ለገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት የሚከለፈው መጠን ከ15 እስከ 20 በመቶ እንደሚደርስ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህም ማለት 100 ዶላር ለመላክ እስከ 20 ዶላር ለመላኪያ ይከፈላል እንደማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን እንዲህ ያሉ ሪፖርቶች ከዚህ ቀደም ሲወጡ ቢታይም፣ አይዛክስ ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም ያለው የገንዘብ ማስተላለፊያ ዋጋ ከአሥር በመቶ ወደ አምስት በመቶ ለማውረድ በተመድ የተመራው የዘላቂ ልማት ግቦች አንዱ ዕቅድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  

ከገንዘብ ማስተላለፍ  አገልግሎት ውድነት ባሻገር፣ በገጠራማ አካባቢ የሚኖሩ ገንዘብ የተላከላቸው ሰዎች፣ አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉበት የተቀላጠፈ አሠራር አለመኖሩ፣ የባንኮችና ሐዋላ አስተላላፊ ድርጅቶች በቅርበት ያለመገኘት፣ በላኪ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵውያንም ሆኑ ሌሎች ዜጎች የሚገጥማቸው የሕግ ገደብ፣ በተለይም እንደ ሳዑዲ ዓረቢያና ደቡብ አፍሪካ ካሉ አገሮች ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎች ገንዘብ ወደ አገሮቻቸው እንዳይልኩ መከልከላቸው በጋሬጣነት ከሚጠቀሱ ችግሮች መካከል ይመደባሉ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባቀረበው የቴክኒክ ድጋፍ ጥያቄ መሠረት በአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓስፊክ አገሮች ድጋፍና በአውሮፓ ኅብረት የፋይናንስ ድጋፍ ዘለግ ላለ ጊዜ በተደረገው ጥናት መሠረት፣ በየጊዜው ወደ አገሪቱ እየተላከ የሚገኘው ገንዘብ በየዓመቱ ጭማሪ እንዳሳየ ተጠቅሷል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል፣ ዳይሬክተር ጄኔራል ደመቀ አጥናፉ እንዳስታወቁት፣ እ.ኤ.አ. በ2009 400 ሚሊዮን ዶላር የነበረው የውጭ ሐዋላ ገቢ ከፍተኛ ዕድገት እያሳየ በመምጣት በአሁኑ ወቅት አራት ቢሊዮን ዶላር አስመዝግቧል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተጠቀሰው ዓመት በሐዋላ አገልግሎት አሰጣጥ መመርያ ላይ ባደረገው ማሻሻያ ጭምር ለውጡ እየታየ መምጣቱን አመላክተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2010 እስከ 2011 1.4 ቢሊዮን ዶላር የተመዘገበበት የሐዋላ ገቢ፣ ከ2011 እስከ 2012 2.4 ቢሊዮን ዶላር፣ ከ2012 እስከ 2013 2.9 ቢሊዮን ዶላር፣ ከ2013 እስከ 2014 ሦስት ቢሊዮን ዶላር፣ ከ2014 እስከ 2015 3.7 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ከ2015 እስከ 2016 አራት ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ዓመትም ከ4.6 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ የሐዋላ ገቢ እንደሚጠበቅ አቶ ደመቀ ገልጸዋል፡፡

ይህ ይባል እንጂ የዓለም ባንክ ግምቶች ግን ከዚህ ይቃረናሉ፡፡ ባንኩ በሚከተለው የትንበያ ሥልት መሠረት ባለፈው ዓመት ወደ ኢትዮጵያ እንደተላከ የሚታመነው የገንዘብ መጠን ከ624 ሚሊዮን ዶላር አይበልጥም፡፡ የዓለም ባንክ ይህን ይበል እንጂ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በበኩሉ ከመንግሥት ጋር ተቀራራቢ የሆነውን የ3.7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን እንዳሠፈረ አይዛክስ ባቀረቡት የጥናት ሪፖርት ጠቅሰዋል፡፡

ምንም እንኳ የአሠራርና የሥሌት ሥልቶቻቸው የተለያዩ ቢሆኑም ገዥ የሆነው መረጃ የብሔራዊ ባንክ እንደሚሆን በመጥቀስ አይዛክስ ተቀባይነቱን ሲያብራሩ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አማካሪው አቶ ኤልያስ ሎሃ በበኩላቸው የዓለም ባንክ ያቀረባቸው አኃዞች የተሳሳቱና ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው ብለዋል፡፡ ምክንያቱም ብሔራዊ ባንክ በየባንኮቹ በኩል የተላከውን የውጭ ገንዘብ መጠን ሪፖርት እንዲያደርጉ ስለሚጠይቅና ስለሚከታተል፣ ከዓለም ባንክ ግምታዊ ሥሌት ይልቅ ብሔራዊ ባንክ እውነታውን የሚያመላክቱ አኃዞች ስላሉት ነው ብለዋል፡፡

በመደበኛ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች አማካይነት የሚላከው ገንዘብ እንዲጨምር የሚረዱ ዕርምጃዎች መወሰዳቸውን ያብራሩት አቶ ኤልያስ፣ በብሔራዊ ባንክ ከተወሰዱ ዕርምጃዎች መካከል የሐዋላ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች የሚያስከፍሉትን የአገልግሎት ዋጋ መጠን በድረ ገጽ ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርጉ ማስገደድ አንዱ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ተጠቃሚዎች በብሔራዊ ባንክ ድረ ገጽ የሚወጣውን የገንዘብ አስተላላፊዎች ዋጋ በማነፃፀር አዋጭ ሆኖ ባገኙት መላክ የሚችሉበት የግልጽ ውድድር ሜዳ ተመቻችቷል ብለዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ሌሎችም የገንዘብ ማስተላለፊያ ሥርዓቶች ማሻሻያ የተደረጉበት የብሔራዊ ባንክ መመርያ ባሻገር፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ሌሎችም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በመደበኛ የገንዘብ ማስላለፊያ ዘዴዎች ተጠቅመው ገንዘብ እንዲልኩ የማመቻቸት ሥራ ይጠበቅባቸዋል ያሉት አይዛክስ፣ በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ጉዞ የሚደርጉበት አሠራር እንዲስፋፋም ይመክራሉ፡፡

ይህም ሆኖ በ2009 ዓ.ም. እንዲሁም ከዚያም በፊት በነበሩ ዓመታት ሲገኝ ከቆየው የወጪ ንግድ ይልቅ በሐዋላ የሚገኘው አብላጫ ይዞ ይገኛል፡፡ በ2009 ዓ.ም. ከወጪ ንግድ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 2.9 Anchorቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ይታወሳል፡፡ በአንፃሩ ከሐዋላ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ግን አራት ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡