Skip to main content
x

የሳምንቱ ገጠመኝ

ባለፈው ሳምንት ማለዳ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በራፍ ላይ ሆኜ ከሽሮሜዳ አቅጣጫ የሚመጣ ታክሲ ስጠባበቅ አንድ ዲፎርዲ (ዶልፊን) ሚኒባስ መጣ፡፡ ወያላው፣ ‹‹ብሔራዊ ሜክሲኮ የቸኮለ . . .›› እያለ ሲጣራ እኔም በጣም ቸኩዬ ነበርና ተንደርድሬ ገባሁ፡፡ መሀል መቀመጫ ሁለት ሰዎች ተቀምጠው ስለነበር ተጠጋግተውልኝ ሦስተኛ ሆኜ ተደረብኩ፡፡ ሚኒባሱ ከአፍ እስከ ገደፍ ከሞላ በኋላ መንቀሳቀስ ሲጀምር አጠገቤ መሀል ላይ የተቀመጠ ሰው ጎንተል ያደርገኝ ጀመር፡፡ እኔ ደግሞ አልተመቸው ይሆናል በማለት ሸሸት ስለው፣ እሱ የበለጠ ጎሸም ያደርገኛል፡፡ ይኼኔ በስጨት ብዬ ፊቴን ወደ እሱ ሳዞር ፈገግ ብሎ ወደ ወለሉ ዓይኖቹን ላካቸው፡፡ ከፈገግታው ወዲያውኑ አወቅኩት፡፡

ከ45 ዓመት በፊት ተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት አብረን የተማርን፣ ዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ አብረን የዘመትን፣ ከዘመቻ መልስ ከቀይ ሽብር ዕልቂትና ትርምስ በኋላ ዩኒቨርሲቲ አብረን የተማርን፣ በኋላም በሥራ ዓለም ውስጥ በተለያዩ አጋጣሚዎች አብረን የሠራን፣ ወዘተ የጥንት ወዳጄ ነበር፡፡ ይኼንን ወዳጄን ላለፉት አሥር ዓመታት በላይ አይቼው አላውቅም፡፡ በእርግጠኝነት ለመጨረሻ ጊዜ ያየሁት በምርጫ 97 አካባቢ የፖለቲካ ወበቅ በነበረበት ጊዜ ነው፡፡ በሥራም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች የሚያገናኘን አጋጣሚ ስላልነበር እነዚህ ሁሉ ዓመታት አላገናኙንም፡፡ አሁን ሳገኘው በአሳሳቁ አወቅኩት እንጂ፣ የፊት ገጽታው ከመለወጡም በላይ ሙሉ በሙሉ ሸብቷል፡፡ በእርግጥ እኔ ላይም ብዙ ለውጦች አሉ፡፡

ከስድስት ኪሎ እስከ ሜክሲኮ የናፍቆት ሰላምታችንን እየተለዋወጥንና የባጥ የቆጡን እያነሳን ብዙ አወራን፡፡ ሜክሲኮ ሻይ ቡና እያልን ማውራት የግድ ስለሆነ (ምንም ብቸኩል ሐበሻ አይደለሁ?) ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ገባን፡፡ የምንወደውን ቡና አዘን ወጋችንን ጀመርን፡፡ ጓደኛዬ በጤና ችግር ምክንያት ለዓመታት ታማሚ መሆኑን፣ በባለቤቱና በልጆቹ ድጋፍ እስካሁን በሕይወት መቆየቱን ሲነግረኝ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ይታይበት ነበር፡፡ እኔ ለማፅናናት ባለቤቱና ልጆቹ ካሉለት ፈጣሪውን ማመስገን እንደሚገባው፣ እንዲህ ዓይነቱን ዕድል አጥተው የትም የቀሩ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ስነግረው አንገቱን በአሉታ ነቀነቀ፡፡ ስላልገባኝ፣ ‹‹ምነው?›› አልኩት፡፡ ‹‹አሁን እኔን የሚሰማኝ የራሴ ሕመም ሳይሆን የአገሬ ሕመም ነው፡፡ በመድኃኒት ኃይል የራሴን ሕመም እያስታገስኩ ነው፡፡ አሁን ግን አገሬ የሚያስቡላትና የሚብሰለሰሉላት ልጆች የሌሏት ይመስል ግራ ስትጋባ አጥንቴ ድረስ ዘልቆ ይሰማኛል፤›› በማለት ያላሰብኩትን ዱብ ዕዳ ጣለብኝ፡፡ በወቅቱ የአገር ጉዳይ ላይ በጣም በርካታ ጉዳዮችን እያነሳንና እየጣልን ከቆየን በኋላ ቀጠሮ ተሰጣጥተን ተለያየን፡፡

ከጥንቱ ወዳጄ ጋር ተሰነባብተን ጉዳዬን ወደ ምተኩስበት ቄራ ለመሄድ ታክሲ ያዝኩ፡፡ የመጨረሻ ወንበር ላይ ሁለት አዛውንቶች ተቀምጠዋል፡፡ ሦስተኛ ሆኜ ከመቀመጤ አንዲት ወጣት ተከትላኝ ተቀላቀለችን፡፡ ጉዞ ተጀመረ፡፡ ወጣቷ የሞባይል ስልኳን አውጥታ የጆሮ ማዳመጫውን ከሰካች በኋላ ወደ ራሷ ጉዳይ ስትገባ፣ እኔ ደግሞ የምሄድበትን ጉዳይ በተመለከተ የገዛ ሐሳቤ ውስጥ ሰጠምኩ፡፡ ይኼኔ አንደኛው አዛውንት ለጓደኛቸው፣ ‹‹አንተ ወንድሜ የዚህች አገር ጉዳይ በጣም እያሳሰበኝ ነው. . .›› ብለው ሲናገሩ ጆሮዬ ጥልቅ አለ፡፡ ጓደኛቸው በመፀፀትና በመከፋት በሚመስል አነጋገር፣ ‹‹አገሪቱ ውስጥ ሽማግሌ የሌለና ምራቃቸውን የዋጡ ሰዎች ያለቁብን ይመስል እርስ በርስ ስንባላ ያሳዝናል፡፡ የሃይማኖት አባቶች እስክንታዘባቸው ድረስ በተራ መግለጫ አልኩ ለማለት ያህል ተራ ነገር ሲያወሩ ያሳፍራል፡፡ ዋሽቶ የማስታረቅና የማስማማት ባህላችን ተንቆ ሁሉም ፈሪ ሲሆን፣ ያሳዝናል፡፡ እግዚአብሔር ይቅር ይበለን እንጂ ሁኔታችንስ ለንሰሐም አያበቃንም . . .›› ሲሉ ጉዳዩን ያነሱት አዛውንት፣ ‹‹እውነት ብለሃል፡፡ መንግሥትንም ሆነ የሚቃወሙትን ወገኖች አንድ ላይ ቁጭ አድርጎ ማነጋገር ካልተቻለ የእዚች አገራችን ጉዳይ የበለጠ አሳሳቢ መሆኑ አይቀሬ ነው . . .›› አሉ፡፡ ቄራ ደርሼ ባልወርድ ኖሮ ወደ ጎፋ ሠፈር የሚሄዱት አዛውንቶች ብዙ የሚናገሩት ነበራቸው፡፡

ቄራ ደርሼ የሄድኩበትን ጉዳይ በስንት መከራ ካስጨረስኩ በኋላ አመሻሽ አካባቢ የሳሪስ ታክሲ ይዤ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡ ሳሪስ የምሄደው ከውጭ የተላኩልኝን አልባሳት ልቀበል ነው፡፡ ዕድሜ ለአሜሪካና ለካናዳ ስደተኛ ወገኖቼ ቢያንስ በልብስና በጫማ ችለውኛል፡፡ ከካናዳ ከመጣው ዳያስፖራ ጋር የተቀጣጠርነው አደይ አበባ አካባቢ የሚገኘው የአባቱ መኖሪያ ቤት ስለነበር ጉዞ ቀጥያለሁ፡፡ ታክሲው ውስጥ አንድ ወያላና ወጣት ይጨቃጨቃሉ፡፡ ወጣቱ ዝርዝር ስለሌለው የአንድ መቶ ብር ኖት ይሰጠዋል፡፡ ወያላው ተናዶ ለምን ሳይነግረው እንደተሳፈረ ይነተርከዋል፡፡ ወጣቱ፣ ‹‹በአሁኑ ጊዜ መቶ ብር ማለት እኮ ያው ዝርዝር ማለት ነው . . .›› እያለ ሲያሾፍበት፣ ወያላው ደግሞ፣ ‹‹አውቀህ ልብህ ውልቅ ብሏል፡፡ የዘመኑ ወጣቶች ቀለብ ትፈጃላችሁ እንጂ ቀልብ የላችሁም . . .›› እያለ ይነጫነጫል፡፡ ይኼኔ አንድ ጎልማሳ መቶ ብሩን ዘርዝሮ ሰላም አሰፈነ፡፡

እኔ ከተቀመጥኩበት መቀመጫ ፊት የተቀመጡ ትልቅ ሰው፣ ‹‹ወዳጄ እግዚአብሔር ይስጥህ . . .›› ብለው ጎልማሳውን ካመሰገኑ በኋላ፣ ‹‹ልጆቼ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ አጉል ትነታረካላችሁ፡፡ ለነገሩ በመላ አገሪቱስ ቢሆን በተለይ ተምረናል የሚሉ ችግር ለማባባስ እንጂ፣ የችግሩ አካል ሆኖ መፍትሔ ለመፈለግ አይደለም፡፡ ልጆቼ እኔ አሁን 65 ዓመቴን እያገባደደኩ ነው፡፡ ከወጣትነቴ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ችግር ሲፈጠር ለማጋጋልና የበለጠ ጥፋት ለማድረስ እንጂ፣ እንካችሁ መፍትሔ ለማለት የሚተጋ ማግኘት አዳጋች መሆኑን ስነግራችሁ በታላቅ ሐዘን ነው፡፡ አገር ችግር ውስጥ ሆና ችግሩን ለማባባስ ካልሆነ ለመፍትሔ ደንታ የሌላቸው ብዙ ናቸው፡፡ መፍትሔ ለመጠቆም ጥረት ለማድረግ የሚጣጣሩትን ከማበረታታት ይልቅ፣ መጥፎ ስያሜ እየሰጡ ሞራል መግደል የሚቀናቸውም ሞልተዋል፡፡ አሁንማ ዘር ማንዘራችን እየተቆጠረ መሰዳደብና መዘላለፍ በዝቷል፡፡ ልጆቼ እስኪ እንደዚህ ወንድማችን     (ጎልማሳው) ወገኖቻችን ሲጨቃጨቁ መፍትሔ አምጥቶ ማስማማት ይልመድብን…›› ካሉ በኋላ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያንን አለፍ ብለው ወርደው ተለዩን፡፡ ከጧት ጀምሮ እስከ አመሻሽ ድረስ የገጠሙኝ ያለንበትን ወቅት ኪሳራ የሚገልጹ አይመስላችሁም?

(ፋሲል ተሾመ፣ ከጃንሜዳ)