Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ ከቤት ሊወጡ ሲሉ ከልጃቸው ጋር እያወሩ ነው

ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር በስልክ እያወሩ ነው

[ክቡር ሚኒስትሩ ከቤት ሊወጡ ሲሉ ከልጃቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • አንተ ትምህርት ቤት አትሄድም እንዴ?
 • ሙድ የለኝም ባክህ ዳዲ፡፡
 • ምንድነው ያልከው?
 • ሙዴ ተከንቷል አልኩህ እኮ ዳዲ፡፡
 • ምንድነው የምታወራው?
 • ምነው ዳዲ?
 • ሙድ መከነት ምንድነው?
 • የአራዳ ቋንቋ አታርፍም አይደል ዳዲ?
 • ስማ አንተ ልጅ ከፀረ ልማት ኃይሎች ጋር መዋልህን አልተውክም ማለት ነው?
 • ጀመረህ ደግሞ ዳዲ?
 • ትምህርት ተጀምሯል አይደል እንዴ?
 • በቃ ደብሮኛል ዳዲ፡፡
 • ምን ሆነህ ነው የደበረህ?
 • ሁሉም ነገር ነዋ ዳዲ፡፡
 • ለትምህርትህ የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ተደርጎልሃል አይደል እንዴ?
 • አልተደረገልኝም ዳዲ፡፡
 • ምን ጎደለህ ደግሞ?
 • ብዙ ነገር ዳዲ፡፡
 • እስቲ አንዱን ንገረኝ?
 • በጣም የሚያሳፍር ነገር ነው የተደረገብኝ፡፡
 • እኮ ምን?
 • ክረምቱን እንዴት እንዳሳለፍኩት ረሳኸው?
 • ክረምቱ ምን ሆነ?
 • ያለፈውን ክረምት አስታውሰው እስኪ?
 • ያለፈው ክረምት ምን ሆነ?
 • ቫኬሽን የት ነበር የላከኝ?
 • አውሮፓ ነበር አይደል የሄድከው?
 • ምን ቫኬሽን ብቻ ሾፒንግ የት ነበር የላከኝ?
 • ዱባይ ነዋ፡፡
 • እሺ በዚህ ዓመት ቫኬሽን የት ነበረ?
 • ገጠር ነዋ፣ አገርህንም ማወቅ አለብህ?
 • ሾፒንግስ የት ነበር?
 • ቦሌ ነዋ ያደረከው፣ ምን ችግር አለው?
 • እኔ ይኼ መመርያ ምናምን የተባለው ነገር ከወጣ በኋላ ተቀያይረህብኛል፡፡
 • ምን ሆኜ ነው የተቀያየርኩት?
 • ባለፈው ዓመት ትምህርት ቤት በምንድን ነበር የምሄደው?
 • በምንድን ነበር የምትሄደው?
 • ሰኞ በነጭ ቪ8 ከሄድኩ፣ ማክሰኞ በጥቁሩ ነበር የምሄደው፡፡
 • እሺ፡፡
 • ረቡዕ በሲልቨር ቪ8 ከሄድኩ፣ ሐሙስ በመርሴዲስ ነበር፡፡
 • እሺ…
 • ዓርብ ደግሞ በሀመሩ ነበር፡፡
 • አሁንስ?
 • አሁንማ ከሰኞ እስከ ዓርብ በስኩል ባስ ነው የምመላለሰው፡፡
 • ለመሆኑ አንተ ተማሪ ነህ የመኪና ነጋዴ?
 • አንተው እኮ ነው ያስለመድከኝ?
 • ምን ላድርግህ ታዲያ?
 • እኔ እኮ ሳይኮሎጂካሊም ተጎዳሁ፤ እንዴት ብዬ ነው ከሌሎቹ ተማሪዎች ጋር አብሬ የምሄደው?
 • ከሌሎቹ ተማሪዎች ጋር አብረህ ብትሄድ ምን ችግር አለው?
 • እኔ የሚኒስትር ልጅ አይደለሁም እንዴ?
 • እኔ እኮ ሚኒስትር የሆንኩት ሕዝብ ለማገልገል ነው፡፡
 • ሕዝብ አገልግለህ ነው ፎቅ የሠራኸው?
 • እ…
 • ይኼን ሁሉ ቤት የሠራኸው ሕዝብ በማገልገል ነው?
 • ምን አልክ አንተ?
 • ለነገሩ አንተ ሕዝብ ማገልገል ሳይሆን የምትወደው…
 • እ…
 • በሕዝብ መገልገል ነው!

 

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር በስልክ እያወሩ ነው]

 • በቃ እኔ እኮ ታገትኩ?
 • ቤት ውስጥ አሸባሪዎች ገቡ እንዴ?
 • ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ እኮ አልቻልኩም?
 • የምን እንቅስቃሴ ነው?
 • ስማ በዓል በመጣ ቁጥር የምሠራውን ሥራ ረሳኸው እንዴ?
 • ሴትዮ አሁን ጊዜው ጥሩ አይደለም፡፡
 • እና እጅና እግሬን አጣምሬ ቁጭ ልበል?
 • እንደዚያማ መሆን የለበትም፡፡
 • ለምንድን ነው ግራ የምታጋባኝ?
 • ግራ መጋባትን ምን አመጣው?
 • ልንቀሳቀስ ስልህ ጊዜው ጥሩ አይደለም ትለኛለህ፤ ልቀመጥ ስልህ ደግሞ እንደዛ መሆን የለበትም ትለኛለህ፡፡
 • እንደዚያ ያልኩሽ እኮ ዓይኖች ሁሉ እኛ ላይ ስለሆኑ ነው፡፡
 • ምን ተሻለ ታዲያ?
 • መጠንቀቅ አለብን፡፡
 • ታዲያ ተጠንቅቀን መሥራት አንችልም?
 • ተጠንቅቀን መሥራት ማለት ምን ማለት ነው?
 • የማያስታውቅ ሥራ መሥራት ነዋ፡፡
 • ስሚ እንደ እኔ እንደ እኔ አንቺ ዝም ብለሽ ብትሄጂ ይሻላል፡፡
 • የት?
 • ዱባይም ምናምን ቢሆን ነዋ፡፡
 • ስማ ሰውዬ እኔ ልጆቼን ጥዬ የትም መሄድ አልፈልግም፡፡
 • እሱን እንኳ ተይው፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ቂሊንጦ ስትገቢ ልጆችሽን ጥለሽ አይደል እንዴ?
 • እውነቱን እናውራ ከተባለማ ከእኔ ይልቅ አንተ ነህ ለቂሊንጦ ቅርብ፡፡
 • አብዛኛው ነገር በአንቺ ስም መሆኑን ረሳሽው እንዴ?
 • ታዲያ እኔ ባለሥልጣን አይደለሁ፤ ግፋ ቢል ንብረቴን ያግዳሉ እንጂ አያስሩኝም፡፡ ባለሥልጣን ስላልሆንኩ፣ ቢዝነስ መሥራት መብቴ መስሎኝ?
 • ሙስና የግል ሴክተሩም እንደሚነካ መቼም ታውቂያለሽ፡፡
 • እኔን አይመለከተኝም አልኩህ፡፡
 • አሁን ደግሞ ዋና ትኩረትቸው በባለሥልጣናት ዙሪያ ያሉ ሰዎች ላይ ነው፡፡
 • እያስፈራራኸኝ ነው?
 • ለማንኛውም ወደ ዱባይ ብትሄጂ ጥሩ ነው፡፡
 • ስማ እኔ የመጣብኝን እቀበላለሁ፡፡
 • እስርም ቢሆን?
 • ለምን እታሰራለሁ?
 • ያልተገባ ሀብት አካብተሻል ተብለሽ ነዋ፡፡
 • በቃ እንደሌሎቹ በስሜ ያለን ሀብት ሸጣችሁ ውሰዱት ብሎ መገላገል ነዋ፡፡
 • አሁን አንቺን በዛ ይምሩሻል ብለሽ ነው፡፡
 • እኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሳውቀው ምስኪንና መሃሪ ሕዝብ ነው፡፡
 • ለዚያ ነው እንደዚህ ያለ ይሉንታ የምትበይው?
 • አንተም ከመቼ ጀምሮ ነው ለሕዝቡ ተሟጋች የሆንከው?
 • ሕዝብ ከተነሳብሽ ጥሩ አይደለም ብዬ ነው፡፡
 • ምን አድርጊ እያልከኝ ነው?
 • በቃ ለጊዜው ከአገር ውጪ፡፡
 • ከዱባይ ግን ለምን ወደ ቻይና አልሄድም?
 • ለምን?
 • በዛው ዕቃ አስጭናለኋ፡፡
 • ምን ዓይነት ዕቃ?
 • በቃ ብዙ ዓይን ውስጥ የማይከት ዕቃ፡፡
 • እኮ ምንድነው?
 • ለምሳሌ ርችት፡፡
 • ርችት ምን ያደርግልሻል?
 • በቃ ሰው በየልደቱም፣ በየበዓሉም ይተኩሰዋላ፡፡
 • ጥሩ ዕቃ አይመስለኝም፡፡
 • ለምን?
 • ሰው እንደድሮው ለርችት ቦታ መስጠት አቁሟል፡፡
 • ለምን ተብሎ?
 • መንግሥት በየቦታው እንደ ርችት የሚያፈነዳው ነገር ስላለ፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • ትራንስፎርመር!

 

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ዳያስፖራ ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል]

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ማን ልበል?
 • ወዳጅዎት ነኝ ከአሜሪካ፡፡
 • ዛሬ ከየት ተገኘህ?
 • ሁሌም ሲናፍቁኝ እኮ እደውላለሁ፡፡
 • ለመስቀል በግ መግዣ ልከህልኝ ነው?
 • ባለሥልጣን ስጦታ መቀበል ይችላል እንዴ?
 • ምን ችግር አለው?
 • ያው እዚህ አሜሪካ ባለሥልጣናት ስጦታ መቀበል ስለማይችሉ ነው፡፡
 • አሁን በግ ስጦታ መሆኗ ነው?
 • ለነገሩ እርስዎ ፎቅ ለምደው በግ ምንም ናት፡፡
 • ስማ እርሱ ድሮ ቀረ፡፡
 • እንዴት?
 • አሁን እንኳን ፎቅ በግ የሚሰጥ የለም፡፡
 • ዛሬ እንኳን የደወልኩት የዚህች አገር ጉድ ማለቂያው መቼ ይሆን ለማለት ነው፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ክቡር ሚኒስትር የሰማሁትን ነገር ከእርስዎ ለማጣራት ነው የደወልኩት፡፡
 • እኮ ምን ሰምተህ ነው?
 • ሚዲያ ላይ የሚወራው እውነት ነው?
 • ስለግጭቱ ነው?
 • እሱማ እውነት መሆኑን እናንተም ተናግራችኋል፡፡
 • ታዲያ ምን ሰምተህ ነው?
 • ስለስኳር የሚወራው ወሬ፡፡
 • ምን አወሩ ደግሞ?
 • ኢትዮጵያ ወደ ጎረቤት አገር ስኳር ኤክስፖርት አድርጋ ነበር አሉ፡፡
 • ታዲያ ኤክስፖርት ማድረግ ምን ችግር አለው?
 • የራሷ አሮባት የጎረቤቷን ታማስላለች አሉ፡፡
 • ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
 • አገሪቷ ውስጥ ስኳር የሚባል ነገር ጠፍቶ በብቸኝነት የሚገኘው ስኳር በሽታ ነው ይባላል፡፡
 • ስማ አሁንም ከእነዚያ ፀረ ልማት ኃይሎች ጋር ነው አይደል የምትውለው?
 • እኔ የምለው ክቡር ሚኒስትር፣ ኢምፖርት የተደረገውን ነው መልሳችሁ ኤክስፖርት የምታደርጉት?
 • ኢምፖርት ኤክስፖርት ሲባል አልሰማህም?
 • ኪኪኪ…
 • ምን ያስቅሃል?
 • ለነገሩ አገሪቷን በግምት እንደምትመሯት ይታወቃል፡፡
 • ምን?
 • አገሪቷ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆና እናንተ ለጎረቤት አገሮች ኃይል ትልካላችሁ፡፡
 • ሰውዬ ከአገሪቷ የኤክስፖርት ፖሊሲ ጋር ችግር አለብህ?
 • እውነት አንዳንዴ ሳስባችሁ እንኳን አገር ቤተሰብም በቅጡ መምራት የምትችሉ አይመስለኝም፡፡
 • ለመሳደብ ነው እንዴ የደወልከው?
 • ለነገሩ የደወልኩት ስኳሩ ጠረፍ ላይ መያዙ አስገርሞኝ ነው፡፡
 • ምኑ ነው የሚያስገርመው?
 • ስኳሩን አስይዛችሁ…
 • እ…
 • የላሱትን ማስመለጣችሁ!

 

[ክቡር ሚኒስትሩ ማታ ቤታቸው ደመራ እየተበራ አማካሪያቸው መጣ]

 • እንዴት መጣህ አንተ?
 • ክቡር ሚኒስትር ደመራ እኮ ከዓመት ዓመት እርስዎ ቤት ነው የማበራው?
 • ዘንድሮ መቼ ጠራሁህ ታዲያ?
 • ልማዴን ለማድረስ ነበር፣ ግን አንድ ነገር ግር ብሎኛል፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • በር ላይ ብዙ መኪናም የለም፤ በዛ ላይ እንደ ድሮው ሰውም የለም፤ እርስዎ ፈቃድ ያስፈልግዎታል እንዴ?
 • የምን ፈቃድ?
 • አይ አሁን አሁን ለአልበም ምርቃት፣ ለሠልፍ ምናምን ፈቃድ ስለሚያስፈልግ፣ እርስዎ ቤት ያነሰው ስላላስፈቀዱ ነው ብዬ ነው፡፡
 • ስማ እንደ ድሮው ድግስ መደገስ እንደማልችል ታውቃለህ?
 • ለነገሩ ሰው እኮ ክቡር ሚኒስትሩ ደመራ የሚያበሩት እስር ቤት ነው እያለ ነው የሚያወራው፡፡
 • ታዲያ አንተ እዚህ ምን ልታደርግ መጣህ?
 • ልተነብይ ነዋ፡፡
 • ምንድነው የምትተነብየው?
 • ወደ ምሥራቅ ከወደቀ ቂሊንጦ፣ ወደ ምዕራብ ከሆነ ደዴሳ፣ ወደ ሰሜን ከሆነ ደግሞ ሸዋሮቢት፣ ወደ ደቡብ ከሆነ ደግሞ ዝዋይ ነው የሚገቡት የሚለውን ነዋ፡፡
 • እኔ ጠፋሁ?
 • የሚሻለው መፀለይ ነው፡፡
 • ለምኑ?
 • ቅርቡ እንዲደርስዎት!

 

[ደመራው ወደ ምሥራቅ ወደቀ]

 • በእውነት ክቡር ሚኒስትር ፀሎትዎ ተሰምቷል፡፡
 • እንዴት?
 • የወደቀው ወዴት እንደሆነ አዩት?
 • ወዴት ነው?
 • ወደ ቂሊንጦ!