Skip to main content
x
የለውጥ ያለህ የሚለው የግሉ ሚዲያ

የለውጥ ያለህ የሚለው የግሉ ሚዲያ

በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ኢትዮጵያ በሚኖሩ ዜጎች ወይም ውጭ አገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል የሚደረጉ የሐሳብ ልውውጦችን የተመለከተ ሰው፣ የአገሪቱ ዜጎች የፖለቲካ አመለካከት በተለያየ ጽንፍ ላይ እንደሚገኝ ይገነዘባል፡፡ በአብዛኛው በጥላቻ የተሞሉት የሐሳብ ልውውጦች እየተባባሱ ሲመጡ እንጂ መሠረታዊ ለውጥ ሲያመጡ አልተስተዋሉም፡፡

እነዚህ ሐሳቦች ግን በአገሪቱ ዋና ዋና መደበኛ የሚዲያ ተቋማት በመጠኑም ቢሆን ሲስተናገዱ አይታይም፡፡ ከማኅበራዊ ድረ ገጾች በተቃራኒ መደበኛ የሚዲያ ተቋማት ኃላፊነት የሚሰማቸውና የሙያ ሥነ ምግባርን መሠረት አድርገው የሚሠሩ ናቸው ተብለው ስለሚገመቱ፣ በእነዚህ ሐሳቦች ላይ በሠለጠነ መንገድ፣ የሐሳብ ልውውጦች፣ ክርክሮችና ሙግቶችን በመደበኛነት በማስተናገድ በዜጎች መካከል የተሻለ ቅርርብ መፍጠር እንደሚቻል የሚዲያ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

ይህንኑ ጥረት እጅግ በቀጭን መስመርም ቢሆን የሚሞክረው የግሉ ሚዲያ ቢሆንም፣ የአገሪቱ የሚዲያ ኢንዱስትሪ ላይ ግዙፍ ተፅዕኖ ያላቸው በመንግሥት ሥር ያሉትና በተለምዶ ግን የሕዝብ ሚዲያ የሚባሉት ናቸው፡፡ የግሉ ሚዲያ ወቅታዊ ይዞታ ከቁጥርም ሆነ ከጥራት አኳያ አበረታች እንዳልሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ እርግጥ ነው ይህን ውጤት ያስከተለው መነሻ ምክንያት ላይ የተለያዩ ገለጻዎች ይቀርባሉ፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ነሐሴ 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ በአዘጋጀው ስብሰባ የግሉ ሚዲያ ስኬቶችና ተጋዳሮቶች ላይ ምክክር ሲደረግም፣ የግሉ ሚዲያ ደካማ ይዞታ ላይ እንዲገኝ አስተዋጽኦ አድርገዋል የተባሉ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ሐሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በዕለቱ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ “ሚዲያ ጠቃሚም፣ ጎጂም ሊሆን ይችላል፤” ያሉ ሲሆን፣ ይህ እንደ አያያዙ እንደሚወሰንም አስምረውበታል፡፡ ሚዲያ የዴሞክራሲ መድረክ የሚሆነው ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ መረጃ በሠለጠነና የሙያ ሥነ ምግባሩን በሚከተል ሙያተኛ ተዘጋጅቶ ሲቀርብ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡ “አቀራረቡ በሙያና በሥነ ምግባር የተደገፈ ካልሆነ ሕዝቦችን የማደናገር፣ ተስፋ የማስቆረጥ፣ ጥላቻን የማስፋፋትና የማጋጨት ዕድሉ ሰፊ ነው፤” ሲሉም አክለዋል፡፡

ዶ/ር ነገሪ ባለፉት ዓመታት የግሉ ሚዲያ ገንቢና አፍራሽ ሚና እንደተጫወተ ጠቅሰዋል፡፡ “በጣም ጥቂት የግል ሚዲያዎች ከሙያና ሥነ ምግባር ባፈነገጠ መንገድ መንግሥትን በመጣል ላይ ብቻ አልመው ከመንቀሳቀሳቸው ውጪ፣ በአጠቃላይ ሲታይ የግሉ ሚዲያ ለሰላም፣ ለልማት፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጠናከርና ለአገር ግንባታ የበኩሉን ገንቢ ሚና ተጫውቷል፤” በማለትም ገልጸዋል፡፡

ተደራሽነቱን በማስፋት፣ ጥራቱን በማሳደግና ተወዳዳሪነቱን በማጠናከር ረገድ ሰፊ የአቅም ክፍተት እንዳለበትም ዶ/ር ነገሪ ጠቁመዋል፡፡ ስለሆነም መንግሥት የግሉን ሚዲያ አቅም በማጎልበት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚጫወተውን ሚና አጠናክሮ እንዲወጣ ለማስቻል ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

“የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ በብዝኃነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የእምነት፣ የባህል፣ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የአስተሳሰብና የፍላጎት ጉዳዮችን በጥንቃቄና በኃላፊነት መንፈስ በማስተናገድና የሕዝብን ጥቅም ማዕከል ባደረገ መንገድ መንቀሳቀስ ከሁሉም የሚዲያ አካላት የሚጠበቅ ተግባር ነው፤” በማለትም አስገንዝበዋል፡፡

“በመረጃ የበለፀገና ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያለው ኅብረተሰብ በመፍጠር ረገድ ሁላችንም የበኩላችንን ሚና መወጣት ይኖርብናል፤” ያሉት ዶ/ር ነገሪ፣ ሚዲያው ካሉበት መሠረታዊ የአመለካከት፣ የሙያና የሥነ ምግባር ችግሮች ተላቆ በሰላም፣ በልማት፣ በዴሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ግንባታ ውስጥ የደረጀ ሚና እንዲጫወት ለማስቻል ታቅዶ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ሪፎርም ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የመጡት አቶ ደሬሳ ተረፈ በአገሪቱ ያለው የግል ሚዲያ የሚገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ የቃኙበትን ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በብሮድካስት ዘርፍ አሥር የንግድ ሬዲዮ (አንድ ያልጀመረ)፣ አምስት የንግድ ቴሌቪዥን (ሦስት የጀመሩ ሁለት ያልጀመሩ)፣ አንድ ሰብስክሪፕሽን ጣቢያዎች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡

አብዛኞቹ በአዲስ አበባና በአካባቢው የሚሠራጩ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ደሬሳ፣ ዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ እንዳልተስፋፋ ገልጸዋል፡፡ በክልሎችና በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲስፋፉ ሰፊ ዕድል ቢሰጥም ወደ ዘርፉ የገቡት ውስን መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡

“ከአንድ ክልል በላይ የሚሠራጩ ከ1,000 በላይ የተመዘገቡ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት 18 የግል ጋዜጦችና 43 መጽሔቶች በሥርጭት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በቀጣይነትና በተከታተተይ ገበያ ውስጥ የሚሠራጩት የተወሰኑ ጋዜጦችና መጽሔቶች ናቸው፤” በማለትም የኅትመት ሚዲያው ያለበትን ወቅታዊ ይዞታ ገልጸዋል፡፡

አቶ ደሬሳ የግሉ ሚዲያ በተለይም የንግድ ብሮድካስተሮች በጥንካሬና በድክመት የሚገለጹባቸው ባህርያት እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ በጥንካሬ ከሚገለጹባቸው ባህርያት መካከልም አብዛኞቹ የንግድ ብሮድካስተሮች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የዜና ሽፋን የሚሰጡ መሆኑ፣ በአንዳንድ የንግድ ብሮድካስተሮች የሐሳብና የአመለካካት ብዝኃነትን በድፍረት በማስተናገድ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው አስተዋፅኦ በማበርከት ረገድ የሚታይ ጅምር ጥረት መኖሩ፣ እንዲሁም በአንዳንድ የንግድ ብሮድካስተሮች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በድፍረት በማቅረብ ረገድ የመልካም ጅምር ጥረት መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

በአንፃራዊነት በእጥረት የሚገለጹባቸው ደግሞ አብዛኞቹ የግል ሚዲያ በዓበይት አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን የሚያጎለብቱ ተከታታይ ይዘቶችን ከማሰራጨት አንፃር ሰፊ ክፍተት ያለባቸው መሆኑ፣ በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነትና መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ተከታታይነት ያላቸው ፕሮግራሞችን ከማቅረብ አንፃር ክፍተት መኖሩ፣ ሕገ መንግሥቱን የማሳወቅ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የማስጠበቅ ሚና ያላቸው ፕሮግራሞችን በቀጣይነት ከማቅረብ አንፃር ውስንነት መታየቱ፣ ወጣቱ በመልካም ሥነ ምግባር የታነፀ፣ ልማታዊ አስተሳሰብ ያለው፣ ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን የተላበሰ፣ በመከባበር፣ በመቻቻል፣ በእኩልነት፣ በሕግ የበላይነት፣ በምክንያታዊነት የሚያምን፣ መልካም ዜጋ እንዲሆን የሚያስችሉ ተከታታይ ፕሮግራሞችን ከማቅረብ አንፃር ሰፊ ክፍተት መኖሩ፣ አንዳንድ የንግድ ሚዲያዎች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ከመወጣት ይልቅ ለስፖርትና ለመዝናኛ ፕሮግራሞች ትኩረት የሚሰጡ መሆናቸው ተጠቃሽ እንደሆኑ አስገንዝበዋል፡፡

የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን አስመልክቶ በሚቀርቡ አንዳንድ ፕሮግራሞች የሚመለከታቸው አካላትን አለማሳተፍ፣ በበቂ ጥናትና መረጃ  ላይ የተመሠረተ የምርመራ ጋዜጠኝነት ፕሮግራሞችን አለማቅረብና የችግሮችን መንስዔና መፍትሔን አለመጠቆም እጥረት መኖሩንም አቶ ደሬሳ ጠቁመዋል፡፡ አልፎ አልፎ በበቂ መረጃ ላይ ሳይመሠረቱና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትን ሳያሳትፉ ስም የሚያጠፉ ዘገባዎችን የማቅረብ አዝማሚያና በተሠራጨ ይዘት ላይ ለሚቀርቡ ቅሬታዎች በወቅቱ መልስ የመስጠት መብትን አለማክበር ከተስተዋሉ ድክመቶች መካከል እንደሚካተቱ ተናግረዋል፡፡

ከውጭ አገር ፈቃድ አግኝተው በአገር ውስጥ ቋንቋ በሳተላይት የሚሠራጩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቁጥር አምስት እንደደረሰ አቶ ደሬሳ አስታውሰው፣ አማራጭ የመዝናኛ ሚዲያ ቢሆኑም አስተሳሰብን የሚገነቡ ዜናና ትምህርታዊ ፕሮግራሞች፣ በዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ፕሮግራሞች የሌሉዋቸው መሆኑን፣ በዋነኛነት በመዝናኛና በውጭ አገር ፊልሞች ላይ የሚያተኮሩና አንዳንዶቹ ደግሞ አገራዊ ይዘት የሌላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የግል ሚዲያው በርካታ ተግዳሮቶች እንዳሉበት ያመለከቱት አቶ ደሬሳ፣ በተለይ መረጃ ከማግኘት መብት ጋር በተያያዘ አንዳንድ የመንግሥት ተቋማትና ኃላፊዎች መረጃ ሲጠየቁ አለመስጠት፣ የሚዲያ ውይይትና የክርክር መድረክ መሸሽ፣ ሚዲያውን በጥርጣሬ ዓይን ማየት፣ መረጃን አደራጅቶ አለመያዝና ድረ ገጽ አለመኖር ትልቅ ችግር እንደፈጠረ አስገንዝበዋል፡፡ ከሚዲያው ነፃነት ጋር በተያያዘ አልፎ አልፎ የአንዳንድ አስፈጻሚዎች ጣልቃ ገብነት መኖሩ፣ በተሠራጨ ፕሮግራም ላይ አንዳንድ አስፈጻሚዎች ቅሬታ ካላቸው ለባለሥልጣኑ ወይም ለፍርድ ቤት ከማቅረብ ይልቅ፣ ሚዲያው  ላይ ጣልቃ የመግባት አዝማሚያ እንዳላቸውም ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የመንግሥትና የልማት ድርጅቶች ማስታወቂያ ክፍፍል ፍትሐዊ አለመሆኑ፣ ከብሮድካስት ማሠራጫና የስቱዲዮ መሣሪያዎች ግብዓቶች ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቀረጥ መጠየቁና ለዘርፉ ልዩ ልዩ የማበረታቻ ሥርዓት አለመኖር፣ በኅትመት ሚዲያው የኅትመት ግብዓቶች ከፍተኛ ቀረጥ፣ ለዘርፉ ልዩ ልዩ የማበረታቻ ሥርዓት አለመኖር፣ የኅትመት ዋጋ መናር፣ የአከፋፋዮች ጫና፣ የአማተር አሳታሚዎች ድጋፍ ማጣት ከኅትመት እያስወጣቸው መሆኑ፣ በዘርፉ የሚታይ የማስፈጸም አቅም ውስንነት (በአመለካከትና በክህሎት) እና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን የሚሠራ ማዕከል አለመደራጀቱ ሌሎች ተግዳሮቶች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህር አቶ ተሻገር ሽፈራው በበኩላቸው “የግል መገናኛ ብዙኃን የይዘት አቅጣጫዎች” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት፣ የኢትዮጵያ የግል መገናኛ ብዙኃን የይዘት ባህሪ ወጥነት እንደሚጎድላቸው አመልክተዋል፡፡ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን የመንግሥት አንደበት ሆነው የሚሠሩ፣ የተቃዋሚዎችን ዓላማዎች የሚያራምዱ፣ እንዲሁም በጋዜጠኝነት ሙያዊ መርህ መሠረት ማኅበረሰባቸውን የሚያገለግሉ ተብለው ሊከፈሉ እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡ “የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በሦስት ፈርጆች የተቀመጡባቸው ብያኔዎች የተመሠረቱት በዘገባዎቻቸው የይዘት አቀራረብና አተረጓጎም ላይ በተደረጉ የአጥኚዎች ትንተና ላይ ብቻ ተመሥርተው አይደለም፡፡ ብያኔው የመነጨው የመገናኛ ብዙኃን ተደራስያን አስተያየቶችንም መሠረት በማድረግ ነው፡፡ በተደራስያን ዘንድ የተቃዋሚዎች ድምፅ ተደርገው የሚወሰዱ ብዙኃን መገናኛዎች የመኖራቸውን ያህል፣ በሙያዊ መርሆዎች መሠረት የሚሠሩ ነፃ የሚባሉ መገናኛ ብዙኃን አሉ፤” ሲሉም አስረድተዋል፡፡

 አቶ ተሻገር የግል መገናኛ ብዙኃን ዓብይ ትኩረት የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የማይዘግቧቸውና ገበያው ግን የሚፈልጋቸው ጉዳዮች እንደሆኑም አስገንዝበዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሚያጓድሏቸው የዜና ይዘቶች ላይና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ቢዘግቧቸውም ተደራስያን ከዘገባ አንፃርና ከአተረጓጎም ልዩነት ሊሳቡ በሚችሉባቸው አርዕስቶች ላይ በማተኮር እንደሚሠሩ ጠቁመዋል፡፡

የልዩነቱ ዋና ምክንያት ዘገባዎቹን የሚያቀርቡባቸው ቅኝቶች እንደሆኑ የተናገሩት አቶ ተሻገር፣ በዚህ ረገድ የምንጮች አመራረጥና የምንጮቹ ፖለቲካዊ አቋም ከፍ ያለ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግም አመልክተዋል፡፡ “የዜና ምንጮች ድርሻ የዜና መረጃ ከመስጠት አልፎ መረጃ መተርጎምንም ስለሚያካትት፣ መገናኛ ብዙኃኑን የሁለት ጽንፍ ድምፆች የማድረግ ድርሻቸው ከፍ ያለ ነው፤” ብለዋል፡፡

በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩሩ የሚገልጹ የግል መገናኛ ብዙኃን በአብዛኛው በአገሪቱ ውስጥ አሉ የሚሏቸውን ከዴሞክራሲ፣ ከፍትሕ፣ ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ፣ ከሙስናና ከአስተዳደር በደሎች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ አተኩረው እንደሚሠሩም ጠቅሰዋል፡፡ ሆኖም ዘገባዎቹ የተሟላ መረጃና የሁሉንም ባለጉዳዮች ሐሳብ ከማካተት አንፃር ጉልህ ችግሮች እንሚታዩባቸው ከመግለጽ አልተቆጠቡም፡፡ 

“ብዙዎቹ ዘገባዎች የመንግሥትን ሕጎችና ፖሊሲዎች የሚተቹ፣ በአፈጻጸም እንከኖች ላይ የሚያተኩሩና በመንግሥት ቅቡልነት ላይ ጥያቄ በሚያስነሱ ማዕቀፎች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፤” ያሉት አቶ ተሻገር፣ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘወትር የሚዘገቡ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስኬቶችን እውነተኛነት በመጠየቅና ደካማ ጎኖችን ማሳየት ላይ እንደሚያተኩሩም አስረድተዋል፡፡

በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በቂ ሥፍራ ለማይሰጣቸው ለተቃዋሚ ቡድኖችና ድርጅቶች መሪዎችና አባላት፣ እንዲሁም እነሱ ለሚያራምዷቸው አስተሳሰቦችና ፖለቲካዊ እምነቶች ሥፍራ መስጠት አንደኛው የግል መገናኛ ብዙኃን የዜና ምንጭ ችግሮች መፍትሔዎች እንደሆኑም አቶ ተሻገር አመልክተዋል፡፡ የግል መገናኛ ብዙኃንም ይህንኑ ተግባራቸውን የድምፅ የለሾች ድምፅ እንዲሰማ የማድረግ ማኅበረሰባዊና ሙያዊ ግዴታቸውን እንደመወጣት እንደሚቆጥሩትም አክለዋል፡፡

የግል መገናኛ ብዙኃን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በማይዘግቧቸው ነገር ግን ተደራስያኑ በሚሿቸው ጉዳዮች ላይ በማተኮራቸው ምክንያት፣ ከተማን ማዕከል ባደረጉ ውስን ተደራሲዎቻቸው ዘንድ አንፃራዊ ተዓማኒነት ለማግኘት መብቃታቸውን አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩም አቶ ተሻገር ጠቅሰዋል፡፡ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የማይዘግቧቸው በማኅበረሰቡና በራሱ በመንግሥት ውስጥ የሚታዩ አሉታዊ ጉዳዮችም ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ መውደቅ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን  አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙ ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ዓበይት የሚባሉ የቡድንና የግለሰብ መብቶችን፣ የአገር አንድነትንና የሉዓላዊነት ጉዳይን የሚመለከቱ ነባር ጥያቄዎችን ከተለያዩ ፖለቲካዊ አንፃሮች በማንሳት የግል ሚዲያው ዘላቂ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸውም አቶ ተሻገር ጠቁመዋል፡፡ የግሉ ሚዲያ የማኅበረሰቡን ፍላጎቶች የማያሟሉ፣ የተዛቡና የመረጃ ጉድለት የሚታይባቸውና የአስተያየት ጭነት የሚበዛባቸው ዘገባዎችን እንደሚያቀርብ አመልክተዋል፡፡

“ከተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መረጃ ማግኘት ከባድ ፈተና በመሆኑ ብዙ የግል መገናኛ ብዙኃን በከፊል የበሰለ ወይም ያልተሟላ ዘገባ እንዲያቀርቡ አስገድዷቸዋል፡፡ በእርግጥ መረጃ በተቀላጠፈ ሁኔታ የማግኘት ችግር በግል መገናኛ ብዙኃን ላይ የበረታ ችግር ቢሆንም፣ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞችም የችግሩ ተጋሪዎች ናቸው፤” ብለዋል፡፡

አቶ ተሻገር የግል መገናኛ ብዙኃን ተደራሽነት በአብዛኛው ከተማ ተኮርና አካባቢያዊ በመሆኑ በከተሞችና በማዕከላት ላይ እንደሚያተኩሩ ገልጸዋል፡፡ በከተማ የሚታየው አድሎአዊ የሆነ ገበያ መር የመገናኛ ብዙኃን ባህሪ፣ እንዲሁም የኢኮኖሚያዊና የሙያዊ አቅም ውስንነት ለዚህ አዝማሚያ መነሻ ምክንያቶች እንደሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ “ይህም ብዝኃነት ዓብይ ገጽታ በሆነበት ማኅበረሰብ ውስጥ በውስን ባህላዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ርዕዮተ ዓለማዊ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ አድርጓቸዋል፤” ብለዋል፡፡

እነዚህ ጥናታዊ ጽሑፎች ከቀረቡ በኋላ ተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶችን ሰንዝረዋል፡፡ ከዛሚ ኤፍኤም ሬዲዮ የመጡት ወ/ሮ ሚሚ ስብሃቱ የሕዝብና የግል መገናኛ ብዙኃን ሚዲያው ራሱን በራሱ የሚቆጣጠርበት ሥርዓት ለመፍጠር የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት አቋቁመው፣ አስፈላጊውን መሥፈርት በሙሉ ቢያሟሉም ተቋሙ እስካሁን ሕጋዊ ሰውነት ለማግኘት አለመመዝገቡን አስታውሰዋል፡፡ “ይኼን ችግር በተመለከተ በተለያዩ መድረኮች ለመንግሥት ያነሳንና በአስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጠው የሚገባ ቢሆንም እስካሁን ይህ አልሆነም፤” ብለዋል፡፡

የጋዜጠኞችን መብት ከማስከበር አኳያ በተጨባጭ ምን እንደሠሩ በውል ከማይታወቁ የጋዜጠኛ ማኅበራት መካከል የአንዱ የኢነጋማ ሊቀመንበር አቶ ወንድወሰን መኮንን በበኩላቸው፣ የግል ሚዲያውን በተመለከተ ትልቁ ችግር ራሱ መንግሥት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ “መንግሥት የግል ሚዲያውን ለማገዝና የተሻለ ደረጃ ለማድረስ ተገቢ የሆነና የሚያዝና የሚጨበጥ ምንም የሠራው ነገር የለም፡፡ የግል ሚዲያ አሁን አለ ብዬ ለመናገር ይከብደኛል፡፡ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባለባት አገር በጣት የሚቆጠሩ ጋዜጦች ነው ያሉት፡፡ ሪፖርተር፣ ፎርቹን፣ ካፒታል፣ አዲስ አድማስና ሰንደቅ ብሎ ሌላ መጨመር የሚቻል አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ የመዝናኛ ጋዜጦችና መጽሔቶች አሉ፡፡ ነገር ግን ትልቁን የሕዝብ ችግር ሊያስተናግዱ፣ ሕፀፁን ሊያወጡና ለመንግሥት ለራሱ መስታወት ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉ አይደሉም፡፡ መንግሥት ረዥም ርቀት ሄዶ ልማት ላይ የሠራውን ያህል ሚዲያው ላይ አልሠራም፡፡ ስለዚህ ዜጎች አማራጭ የመረጃ ምንጭ ፍለጋ ወደ ውጭ ሚዲያ ዞረዋል፡፡ የግል ሚዲያው በአብዛኛው የገንዘብ አቅም የለውም፤›› ያሉት አቶ ወንድወሰን፣ ጋዜጠኞች በነፃነት ተንቀሳቅሰው እንዲሠሩ የሚያስችል ምኅዳርም እንዳልተፈጠረ ተችተዋል፡፡ “ሚዲያውን ማሻሻል የሚቻለው በመድፈቅ አይደለም፡፡ ማሻሻያ ለማድረግ በመጀመርያ የጠበቡት መድረኮች መስፋት አለባቸው፤” ብለዋል፡፡

የሰንደቅ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ አቶ ፋኑኤል ክንፉ፣ “በአሠራር የተጠፈሩና መንቀሳቀስ የማይችሉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ኤክስፐርቶች ባሉበት የመረጃ ነፃነት ሊኖር አይችልም፡፡ ተጠሪ በሆኑለት ሥራ አስፈጻሚ ተፅዕኖ ሥር ያሉ ናቸው፡፡ ነፃ ያልወጣ የሕዝብ ግንኙነት ነፃ መረጃ ሊሰጥ አይችልም፡፡ መረጃ አሳልፈህ ሰጠህ የሚለው የተንሸዋረረው የአስፈጻሚው አስተሳሰብ መጀመርያ መነቀል አለበት፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ፋኑኤል የመንግሥት ድርጅቶች ማስታወቂያ የሚሰጡበትና የሚከለክሉበት መሥፈርት ግልጽ እንዳልሆነም አመልክተዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ማሻሻያ ለማድረግና ፍትሐዊ ክፍፍል ለማድረግ በተደጋጋሚ ቃል ቢገባም ወደ ተግባር እስካሁን እንዳልተገባ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮ ምኅዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ጌታቸው ወርቁ እንደ አቶ ወንድወሰን ሁሉ ለግል ሚዲያው የተመቸ ምኅዳር እንደሌለ ወቅሰዋል፡፡ መንግሥት የግል ሚዲያውን በአሉታዊ ጎን እንደ አፍራሽ ማየት እንደሌለበትም አሳስበዋል፡፡ “ላይመቸው ቢችልም መንግሥት ራሱ ከሚመራው ሚዲያ በላይ ሊያገለግለው የሚችለው የግሉ ወይም ነፃ ሚዲያ ነው፤” ብለዋል፡፡