Skip to main content
x

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ጉዳይ

በያሲን ባህሩ                                                   

          ሞቷም ሽረቷም መላውን አገር ይመለከታል፡፡ ቢያንስ በብሔር ፖለቲካ ስለማንገፋፋባት (አሁን አሁን ከኦሮሚያ ጥቅም ጋር በተያያዘ የሚነሳው ግራ አጋቢና ግልጽነት የሌለው የፖለቲካ ጨዋታ በመጪው ጊዜ ጣጣ እንዳያመጣ ቢያሠጋም)፣ የአገሪቱ የረዥም ጊዜ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማዕከል በመሆኗ፣ እንዲሁም ከየትም መጥተን የምንጠለጠልባት ጎጇችን ስለሆነች የአዲስ አበባ ጉዳይ ይመለከተናል፡፡

    በዓለም ከሚገኙ አሥር የዲፕሎማቲክ ከተሞች አንዷ ነች ምትባለውና በ130 ዓመታትን ዕድሜ ያስቆጠረችው ሸገር፣ እንደ አገር ለተመዘገበው ዕድገት ጉልህ ምልክት  እንደሆነችም እርግጥ ነው፡፡ ይቺ ከተማ በአሥር ክፍላተ ከተሞችና፣ በ116 ወረዳዎች የተከፋፈለ አስተዳደራዊ መዋቅር ቢኖራትም፣ አሁንም ከዚህም በታች ያልተማከለ አስተዳደር የሚያስፈልጋት ጊዜ ላይ እንደ መሆኗ የዛሬው ጽሑፍ በዚሁ ዙሪያ መለስ ጉዳይ ላይ ያተኩራል፡፡ 

     አዲስ አበባ በ54,000 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈች ከተማ ብትሆንም፣ ወደ ጐን የምትለጠጥ እንጂ ወደ ላይ ያላደገች ከተማ ናት፡፡ በእርግጥ ወደ ላይ የመመዘዝ  ዕድገቷ ከዛሬ አሥር ዓመት በፊት ጀምሮ ጥሩ ዕርምጃ አሳይቷል፡፡ ዛሬ አዲስ አበባ በሁሉም ዘርፎቿ ከፍተኛ ለውጥ ብታመጣም በዚያው ልክ ሥራ አጥነት፣ ድህነትና ኢፍትሐዊነትም እንደተንፀባረቁባት ነዋሪዎቿ ይናገራሉ፡፡

     አሁንም የሀብት ክፍፍል የብዙ ዓለም ከተሞች ፈተና ቢሆንም፣ የአዲስ አበባ በትኩረት መታየት ያለበት የደሃ አገር መዲና በመሆኗ ነው፡፡ የመዲናዋ ነዋሪዎች በቀንና በሌሊት በጎዳና ከሚኖረው ለማኝና በቀን ሚሊዮኖችን እስከ ሚያጋብሰው ቱጃር፣ የተሰባጠሩ ናቸው፡፡ መኖሪያዎቿም ከደሃ ጉሮኖዎችና የወንዝ ዳር የላስቲክ ቤቶች  በወር መቶ ሺሕ ብር እስከሚከራዩ ትልልቅ ቪላና አፓርታማዎች ድረስ ይነታቸው ብዙ ነው፡፡

    አዲስ አበባ ከፍርፋሪ (ቡሌ) መሸጫ ጥጋ ጥጐች እስከ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ድረስ ይገኙባታል፡፡ ከዘመናዊ የሪል ስቴት ቪላዎች እስከ ፈራረሱ የቀበሌ ቤቶችም ገና እንደተመሰቃቀሉበት ናት፡፡ ጉሮሮውን ለማራስ ጠብታ ውኃ ከሚለምነው ዜጋ፣ በዓለም ውዱ ውስኪ አዳሩን ጮቤ እየረገጠ እስከሚደነፋው ቅንጦተኛም ይኖሩባታል፡፡ ሸገር ሁሉም ነገር በየዓይነቱ የሞላባት ሆናለች፡፡ ይኼም ሆኖ ከእነ ችግሯም ቢሆን፣ ሁልጊዜ በለውጥ ሒደት ላይ ናት፡፡ በዚህ ላይ ሙስናው፣ አታላይነቱ፣ የሞራል ክስረቱና ሱስ  እንደ ብዙዎቹ ታዳጊ የዓለም ከተሞች ወገቧን እንደያዛት ነው፡፡

        ለዚህም ነው ይቺህን ከተማ ማስተዳደር እጅግ በጣም ከባድ ኃላፊነት ነው የሚባለው፡፡ የዚህን አባባል መገለጫዎች መፈተሽ ግን ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የከተማችን ችግሮቿ ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡ የኑሮ ውድነት፣ የቤት እጥረት፣ የሥራ ዕጦት፣ መሠረታዊ የፍጆታ ግብዓቶች እጥረት (ለምሳሌ ስኳርና ዘይት በስለት የሚገኙ መሆኑ)፣ የመሠረተ ልማት፣ የውኃ፣ የመብራት የስልክ፣ የትራንስፖርት፣ የጤና፣ የአነስተኛና ጥቃቅን፣ የሴቱ፣ የሕፃናቱ፣ የበሽታው፣ የመድኃኒቱ፣ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛው፣ ለሥራ ወደ ውጭ በሚሄዱ ዜጐች ላይ የሚደርስ ስቃይና እንግልቱ፣ የመሬት አስተዳደሩ፣ የታክስና የፍትሕ ተግባራዊ ሒደቱ፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉድለቱ፣ ኧረ ስንቱ? እነዚህን ሁሉ ችግሮች በቅደም ተከተል ብቻ ሳይሆን በአፋጣኝ መፍታት ለነገ የሚባል ተግባር አይደለም፡፡ ከፓርቲና ከመንግሥትም በላይ የትውልድ ኃላፊነትም ሊሆን ይገባል፡፡

       ባለፉት አሥር ዓመታት ገደማ አዲስ አበባ በዘመናዊ መንገዶች አሸብርቃለች፡፡ ከዚህ ቀደም ያልታዩ ማሳለጫዎችና ቀለበት መንገዶችን ለአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡ አዲስ አበባን እየከተሙባት የመጡት የኮንዶሚንየም ቤቶችና ዘመናዊ ሕንፃዎች፣ እንዲሁም ግዙፍ የገበያ ማዕከላት ሁሉ የከተማዋ ብቻ ሳይሆኑ የአገሪቱ ፈጣን ዕድገት ማሳያ ሆነዋል፡፡ ይሁንና አሁንም ከከተማዋ ዕድገት ጋር ተያይዞ ያለፍላጎት የሕዝብ መፈናቀል፣ ያለበቂ ካሳና ምትክ ቦታ መፍለስ እንደሚታይ፣ ይህም ቀላል የማይባል ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እያስከተለ እንደሆነ በግልጽ ይታያል፡፡

      ከዚያም አልፎ ነባሩ የከተማ ይዞታና የመኖሪያ አካባቢ ሲለማ ለሕዝቡ ማኅበራዊ ትስስር፣ ለባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች በቂ ትኩረት አለመሰጠቱ ብዙዎችን እያስቆጨም ነው፡፡ እንዲውም አንዳንዶች ኢሕአዴግ የሚጨነቀው የራሱን አዲስ ታሪክ ለመጻፍና ማኅበራዊ መሠረቴ የሚለውን ሕዝብ በአዲስ መልክ ስለማስፈር እንጂ፣ ስላለፈው ታሪክና የቀደመው ማኅበረሰብ ማንነትም ሆነ መስተጋብር ብዙም ደንታ ስለሌለው የሚታይ ችግር ነው እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡

    የከተማ አስተዳደሩ በመዋቅር መብዛት፣ በአመራርና ፈጻሚ ብዛት፣ በግብዓትና በአሠራር ጋጋታ ብቻ ሳይሆን በሚሰበስበው ዓመታዊ ግብር (በዓመት እስከ 40 ቢሊዮን ብር) እና በሚሸጠው የሊዝ መሬት ገቢ (በዓመት በአማካይ እስከ 15 ቢሊዮን ብር) ከፍተኛ የሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አሁንም ግን ወጥ ሥርዓትና ዘመናዊ የአመራር ጥበብ ያለው አስተዳዳር ተዘርግቷል ለማለት አያስደፍርም፡፡ መዋቅሩ አሁንም የሕዝብ ተጠያቂነትና ግልጽነት መጉደል ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ችግር አለበት፡፡

      ለአብነት ያህል የሕዝብ ምሬትና ቅሬታ በታየ ቁጥር የሥራ መደቦችን መዝጋትና አመራሩን በአልሸሹም ዞር አሉ ዓይነት ማቀያየርን እንደ ብቸኛ መፍትሔ መውሰድ አይበጅም፡፡ የመልካም አስተዳደር ጉድለትና ሙስና በተከሰተ ቁጥር፣ ሠራተኞችን ማባረርም አዋጭ የአስተዳደር ዘይቤ አይደለም፡፡ ይህም ቢያንስ ባለፉት 15 ዓመታት በመስተዳድሩ በተደጋጋሚ ሲወሰድ የቆየ ዕርምጃ ነው፡፡

      በእርግጥ የተበላሸውንና የለየለትን ሌባ ማባረር ብቻ ሳይሆን፣ በሕግ መፋረድም አለበት፡፡ ባሳለፍነው የ2009 ዓ.ም. ዓመት በአፈጻጸም ድክመት፣ በሙስናና በመሳሰሉት ምክንያቶችና ሰበቦች በየደረጃው ከዋና መሥሪያ ቤት አንስቶ እስከ ክፍላተ ከተሞች ድረስ ከ600  የማያንሱ በግምገማና በቅጣት ተባረዋል፡፡ ለዓመታት ተዓምር ሠሩ ሲባሉ የቆዩትም በዘረፋና በሙስና ተወንጅለው እግረ ሙቅ ገብተዋል፡፡ የማጥራት ወላፈኑ ያልገረፋቸው አንገታቸውን እንደ ሰጎን ደብቀው በመዋቅሩ የተሰገሰጉ አመራሮችም ቀናቸውን እየጠበቁ ናቸው፡፡

        እየተወሰደ ያለው ርምጃ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ያግዛልን? ብሎ መጠየቅ ግን ተገቢ ይሆናል፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳዳርና ምክር ቤት ስህተትም ይህንን እየፈተሸ አለመሄዱ ነው፡፡ እስካሁን በተለይ በድክመት፣ በጠባብነትና በዘረኝነት እንዲሁም አድልኦ በመፈጸም የተገመገሙ ሠራተኞችና ኃላፊዎችን ወደ ሌላ መሥሪያ ቤት ወይም ከወረዳ ወደ ሌላ ወረዳ ከማዛወር በቀር ለቀሪው ሙሰኛ አስተማሪ የሆነ፣ የሚቆጠቁጥ ቅጣት የወሰደበት አጋጣሚ ዝቅተኛ መሆኑም መፈተሽ የነበረበት ነው፡፡

      እዚህኛው ወረዳ ‹‹ሙሰኛ›› የተባለ ሠራተኛ እዚያኛው ወረዳ ሥልጣን ጨብጦ፣ ለሌላ ጥፋት ሲሰናዳ ወይም ባልሠራሁት ታማሁ እያለ ራስን ለማዳን ሲወራጭ  ይገኛል፡፡ ግማሹ ከደረጃ ዝቅ ተደርጓል ይባላል፡፡ ከደረጃው ዝቅ ቢልም ደመወዙን ይዞ ነው፡፡ ‹‹የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ ከተሰጠው በኋላ አይቀነስም›› የሚል ሕግ መሰል የመብት ተቆርቋሪነቱ መንፈስ አለ፡፡ ተሿሚም ሆነ ሠራተኛ ዜጋ በመሆኑ የመንግሥት ቤት ውስጥ ካለ ከዚያ የዜግነት መብቱ ተገፍቶ ይሳደድ፣ ልጆቹም ይበተኑ ባይባልም እንኳን በድብቅ ያካበተው ገንዘብ፣ ትርፍ መሬትና ሀብት በዝምታ ይታለፍ ማለት ግን ሌብነቱን ያባብሰው እንደሆነ እንጂ ሊያርመው አይችልም፡፡

      በከተማይቱ አስተዳደር ውስጥ ከዋናው መሥሪያ ቤት (ማዘጋጃ) ጀምሮ በየክፍላተ ከተሞች በኩል ቁልቁል በወረዳ ዘልቆ ቀበሌ እስኪደርስ ድረስ ብዙ የተሿሚዎች/ሠራተኞች ገመናና ጉድ አለ፡፡ በዘመድ አዝማድ እየተጓተተና እሱም በተራው የራሱን ዘመድ እየጐተተና እያስጐተተ ቦታውን የያዘ መኖሩ የሕዝቡ መነጋገሪያ ነበር፣ አሁንም  ነው፡፡ በተለይ በጤና ቢሮና እስከ ታች ጤና ጣቢያዎች ድረስ ያለው ንክኪ በውኃና ፍሳሽ፣ በመሬት ልማትና ያበላሉ በሚባሉ መሥሪያ ቤቶች አስገራሚ ነው፡፡

      በርከት ባሉ አገልግሎት ሰጪ የላይና የታች መሥሪያ ቤቶች ቁጭ ብሎ ሲያወራና ከቢሮ ወጥቶ ሲዞር የሚውለው አመራርም ሆነ ፈጻሚ ይበዛል፡፡ ሕዝቡ በዚህ ረገድ ከንቲባውን ለማግኘት መድረክ ባገኘበት አጋጣሚ ሁሉ ምሬቱን ሳይገልጽ ያለፈበት ጊዜ የለም፡፡ አንዳንድ ሠራተኞች በሥራቸው አጋጣሚ ካገኟት እያንዳንዷ ቀዳዳ ውስጥ ለራሳቸው የሚሆን ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ሲያሰሉ የሚያድሩ ሆነዋል፡፡ ሁሉም ማለት ባይቻልም ይኼ በሽታ ግን የአስተዳደሩ ነቀርሳ ነው ማለት ድፍረት አይመስለኝም፡፡ (በነገራችን ላይ በቅርቡ ተሃድሶ የእገሌ የበላይነት ወደሚል የብሔር ፍረጃ መገፋት የመጣው በአመራሩ ኢፍትሐዊ አሠራርና በአንዳንዱ አድርባይነት ቅጥ ያጣ አካሄድ ጎልቶ በመታየቱ መሆኑን ለመካድ አይቻልም) ግን እንዲያው እንዴት ዓይነት የሞራል መላሸቅና ስግብግብነት ወረረን አያ?!!

      በእርግጥ የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክር ቤት የከተማይቱን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት ማድረግ ያለበትን በተሟላ ሁኔታ ባያደርግም፣ ባለው አቅምና ግብዓት ልክ የተቻለውን ለማድረግ መሞከሩ እውነት ነው፡፡ የሥራ አጥነት ችግርን ለመፍታት አስተዳደሩ በርካታ የሥራ ዕድሎችን ፈጥሯል፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ አደራጅቶ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ለማስቻልም ሠርቷል (ምንም እንኳን እዚህም ላይ የለየለት መድልኦና አንድ ወገንን እየመረጡ የማገዝ ቆሻሻ አካሄድ በገሃድ ታይቶ ለሕዝብ ኩርፊያ ሰበብ ቢሆንም)፡፡  

      አዲስ አበባን ከየክልሉ እየፈለሰ የሚመጣው (በፖለቲካም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ግፊት የሚፈልሰው) ዜጋ እየሞላባት ነው፡፡ የስታትስቲክስ ኤጀንሲ መታወቂያ ያልያዘውን ነዋሪ ስለማይቆጥረው እንጂ ነዋሪው ስድስት ሚሊዮን አይደርስ ይሆን? በዚህም ምክንያት የሥራ ፈላጊው ዜጋ ቁጥር እያደር እየጨመረ ነው፡፡ ከፅዳትና ከጥበቃ ሠራተኝነት ጀምሮ ክፍት የሥራ ማስታወቂያ በወጣ ቁጥር የአመልካቹ ሠልፈኛ ብዛት በሁለትና በሦስት ዙር እንደ መቀነት መጠምጠሙ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

    ሥራ ተመዝግቦ ለማግኘት ብቻ ሳይሆን የክፍት ሥራ ማስታወቂያ ለማየትም   መተላለፊያ እስኪጠፋ ድረስ ሠልፉ ይረዝማል፡፡ ለአንዲት ክፍት የሥራ ቦታ ከ500 ያላነሰ አመልካች ይሠለፋል፡፡ የሥራ ፈላጊው ብዛት ለሥራው መከፈል ያለበትን ደመወዝ ዝቅተኛ እንዲሆን በማድረግ በነባሩ ሠራተኛ ላይ ተፅዕኖ ያደርጋል፡፡ በተለይ በግሉ ዘርፍ ምግብና መኝታ ከተቻሉ ‹‹በነፃ ገብቼ ልሥራ›› እያሉ ዋጋ የሚሰብሩ  እንዳሉም ይደመጣል፡፡ በእርግጥ እዚህ ላይ ሌላ ተቃርኖ እንዳለ የሚታየው ለቤት ሠራተኛነት የሚቀጠር እንኳን የማይገኝባት ከተማ የመሆን ጉዳይ ነው፡፡ ገዥና ሻጭ ያልተገናኘበት ገበያ፡፡

      በዚህ አገር ከትምህርት ቤት የተመረቀውም ሆነ የወደቀው ሁሉም ሥራ ፈላጊ ነው፡፡ ሥራ አጥነት ለባህርይ መበላሸትና ለተለያዩ ወንጀሎች ያጋልጣል፡፡ በእርግጥ ይህ የሥራ አጥነት ችግር ከተማይቱ የፈጠረችው አይደለም፡፡ ለችግሩ መኖር በርካታ ባለድርሻ አካላት አሉበት፡፡ ዜጐች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ ጠቃሚና አስፈላጊ መሆኑ ቢታመንም፣ የአገሪቱ የሥራ ትከሻ ሊሸከም ከሚችለው በላይ ኃይል መኖር ግን ለጊዜውም ቢሆን የመስተዳድሩ ራስ ምታት መሆኑ አይቀርም፡፡

    ለአዲስ አበባ የሥራ አጥነት ችግር አስተዋጽኦ የሚያደርጉት ሌሎች ባለድርሻ አካላትም አሉ፡፡ የክልል መስተዳድሮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሥራ ፍለጋ ወደ ከተማ የሚጐርፈውን የሰው ኃይል ለክልላቸው ልማት መጠቀም አልቻሉም፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሰው የሰው ኃይል ከከተማይቱ አቅም በላይ ነው (በተለይ የጎጃም፣ የትግራይ፣ የወላይታና የሐዲያ ተወላጆች ፍልሰት ወደር የለውም)፡፡ ዜጐች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው በመረጡት አካባቢ ሠርተው መኖራቸው የማይገሰስና የማይደፈር ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ አማራጭ በማጣት ሳይሆን በምርጫ እንዲሆን ግን ክልሎች የድርሻቸውን መጫወት አለባቸው፡፡

     ሌሎች ምክንያቶችም አሉ፡፡ የኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማምጣት የሚደረገው ብሔራዊ ራዕይ በአብዛኛው በከተሞች አካባቢ በመሆኑ የገጠር ከተማ ፍልሰቱን ፍጥነት ይጨምራል፡፡ የፖለቲካ ዝግጁነት አለመኖርም ሌላው ምክንያት ነው፡፡ በከተማዋ ነባሩ ኗሪ ሥራ ፈጥሮ ለመሥራት ያለው ዝግጁነት ደካማ መሆንና ለማኅበራዊ ሕይወት ጠንቅ የሆኑ ሱሶች ላይ መጠመድም ተጨማሪ ችግር ነው፡፡

          ከዚህ አንፃር እንደ መፍትሔ መታየት ያለበት አዲስ አበባ ያላትን የሀብት ግብዓት ለየፕሮጀክቶቿ የምትመድብበት አሠራር በማያዳግም እርግጠኝነት ላይ በተመሠረተ ጥናትና ቅደም ተከተል አግባብ መሠረት የማድረግ ብቃቷን ማሻሻልና ማጠናከር ያስፈልጋታል፡፡ የትኛውም መንግሥት ወይም የትኛውም ከተማ የማያልቅና የተትረፈረፈ ሀብት የለውም፡፡ የሀብት ግብዓት ከግለሰብ ጀምሮ እስከ መንግሥት ድረስ እጅግ በጣም ውስን ነው፡፡ ሁሉንም ችግሮቹን በአንዴ ለመፍታት የሚያስችል ሀብት የትም የለም፡፡ ይኼ እውነት ነው፡፡

      ስለዚህ ከተሞች በተለይ እንደ አዲስ አበባ ያሉ ደሃ ከተሞች ያላቸውን ውስን ሀብት በአግባቡ የመጠቀም ብቃት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ዛሬ የተሠራው ነገ የሚፈርስ ከሆነ ብክነት ነው፡፡ ምክንያት ወይም ሰበብ ይኑረውም፣ አይኑረውም ዋናው ጉዳይ ሰበብ መደርደሩ አይደለም፡፡ አስቀድሞ የማያዳግም ጥልቅ ጥናት ማድረጉ ላይ ነው፡፡  የሰው ኃይሉ፣ ግብዓቱና አመራሩ ከብክነት በፀዳ መንገድ ሥራ ላይ መዋል የሚኖርበትም ለዚሁ ነው፡፡

      በዚህ ዓይነት ሸገርን ቤተ ሙከራ ልናደርጋት አይጠበቅብንም፡፡ ያላትን ውስን ግብዓት እጅግ አስፈላጊ ለሆኑ ሥራዎች ብቻ ወጪ ማድረግ አለብን፡፡ በእርግጥ የከተማ አስተዳደር ሥራ ወጪው ብዙ ነው፡፡ የአንድን ከተማ ወጪ መብዛት ወይም ማነስ ከሚወስኑት ጉዳዩች አንዱ የሕዝብ ሁኔታ (Population Characteristics) ነው፡፡

   በሕዝብ አሠፋፈር (አቀማመጥ)፣ በመባዛት (የቁጥር ዕድገት) በውልደት የመጨመር ምጣኔ መሥፈርት ወጪው ይወሰናል፡፡ ይኼ ማለት ተጠጋግቶ የሠፈረ ሕዝብ (High Density) ያላት ከተማ ብዙ ወጪ ይጠብቃታል፡፡ የሕዝቡን ኑሮ ለማረጋገጥ፣ አስፈላጊውን አገልግሎት ለማቅረብ፣ ሕግና ሥርዓትን ለማስፈን፣ የእሳት አደጋ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የትራንስፖርት፣ የአረንጓዴ ሥፍራ፣ የመቃብር ቦታ፣ የባህላዊና የመዝናኛ ሥፍራዎች፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ሙዚየም፣ ቴአትር ቤት፣ መናፈሻ፣ ወዘተ ለማሟላት ብዙ ገንዘብ ያስፈልጋታል፡፡

     የሕዝብ ዕድገት (Population Growth) በራሱ ሀብት ቢሆንም፣ ለአስተዳደሩ ግን ራስ ምታት የሚሆንበት ሁኔታም ይኼው ነው፡፡ ለጋራ የመኖሪያ ቤቶች ተመዝገበው ፈጣሪያቸውንና መንግሥትን በመማፀን ላይ ያሉትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎች (ገና እየደረሰ ያለውን አዲስ ትውልድ ሳይጨምር) ብዛት በማየት ብቻ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

        ከዚህ አንፃር መሠረተ ልማቱ የሕዝቡን ዕድገት ማስተናገድ በሚችልበት ሁኔታ ካልተደራጀ ከተማዋ ሥራ ታቆማለች፡፡ ከተማዋ ይኼን ለማድረግ የሀብት ውስንነት ስላለባት ነው ‹‹ወጪ ተጋሩ፣ ሥራ ፍጠሩ፣ ቆጥቡ፣ . . . ›› የምትለው፡፡ በሌላ በኩልም የኢንዱስትሪ መንደር የሆኑ በርካታ ሥፍራዎች ያሏት ከተማ ወጪዋ ብዙ ነው፡፡ ውኃ፣ ብዙ መብራት፣ ቴሌ፣ መንገድ፣ ወዘተ ማቅረብ መቻል አለባት፡፡

      ስለዚህ እያንዳንዷ የአስተዳደሩ ገንዘብ የወርቅ ያህል የምትቆጠርና ብዙ ሥራ ያለባት ናት፡፡ እንኳን በሙስናና በነጣቂ እየተዘረፈ ከአገር ሊሸሽና ጥቂቶችን ያበለፅግ ይቅርና ለማይገባ የሕዝብ አገልግሎት ተብሎ ሊወድም አይገባም፡፡ ገንዘብ ደግሞ እንደ ልብ የሚገኝ ወይም ከየትም የሚታፈስ ስላልሆነ የተገኘውን አብቃቅቶና በቁጠባ ተጠቅሞ ዕድገቱን የማስቀጠል ግዴታ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤትና አስተዳዳር ሕዝባዊ ኃላፊነት ነው፡፡

        በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር መዋቅር ብቃት ባላቸው፣ ዓለም አቀፍ ግንዛቤን በጨበጡ (እንደ አንዳንዶች የከተማዋ ልጆች ይምሩን ባንልም) ምሁራንና ልበ ሙሉ በሚባሉ ፖለቲከኞች መመራት አለበት፡፡ በዚህም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ብቻ ሳይሆን የከተማዋን ፖለቲካዊ ክፍተቶች እየሞሉ፣ ሕዝቡን በስፋት እያሳተፉ የተጀመረውን ተስፋ ሰጪ ጉዞ ማስቀጠል ይቻላል፡፡ ይገባልም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡