Skip to main content
x

ዘንድሮ ምክር ቤቱ የሕዝብ እንደራሴነቱን በተግባር ያረጋግጥ!

ሰኞ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስተኛ ዙር ሦስተኛ ዓመት የጋራ የመክፈቻ ጉባዔውን እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡  መቼም አዲስ ዓመትና ዘመን ሲመጣ አዲስ ነገር መጠበቅ የሰው ልጅ ባህሪ ስለሆነ፣ እኛም ምንም እንኳን ምክር ቤቱ ባለፉት ዓመታት የነበረ ቢሆንም መጭው ጊዜ አዲስ ዓመት በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አገር በብዙ ፈተናዎች ያለፍንበት በመሆኑ ለውጥና መሻሻልን መመኘት ጤነኝነት ነው፡፡

ይሁንና የሠለጠነው ማኅበረሰብ አዲስ አስተሳሳብን ከትውልድ ወደ ትውልድ መቅረፁ ብቻ ሳይሆን፣ ከዓመት ዓመትና ከጊዜ ጊዜ የሚያፈልቀውን ያህል በእኛ ዓይነቱ የሦስተኛው ዓለም ማኅበረሰብ ውስጥ እምብዛም የሚታይ አይደለም፡፡ በተለይ በመንግሥታዊ ሥርዓት ውስጥ ሁሉም እየተነሳ በአሮጌው በሬ ለማረስ (ለየት ቢልም አዲስ ወይን በአሮጌ አቁማዳ እንደሚሉት ዓይነት) መሯሯጥ እንጂ፣ ትውልድ በሚቀበለውና በዘመናዊና በአዲስ መንፈስ አቀናጅቶ በመምራት በኩል የጎላ ክፍተት ያጋጥማልና መልዕክቴን ምክር ቤቱና የሚመለከታቸው አካላት ሳያጤኑት እንዳያልፉ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡

አገራችን በፓርላማ፣ በብሔራዊ ሸንጎም ይባል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‹‹ትልቁ የሥልጣን ባለቤትነት›› መመራት ከጀመረች በርከት ያሉ ጊዜያት  ተቆጥረዋል፡፡ ይሁንና ግን ምክር ቤቶቻችን በተሟላ መንገድ የሕዝብ ውክልናና አስተሳሰብ የተንፀባረቀባቸው ናቸው ለማለት አዳጋች ነው፡፡ የንጉሡን ዘመን የገዥ መደቡ ፊውዳላዊ ምክር ቤትንም ሆነ የደርጉን አምባገነንነት የሚያስቀጥል የይስሙላውን  ብሔራዊ ሸንጎ ትተን፣ ባላፉት 25 ዓመታት በአገራችን በሥራ ላይ የነበሩትን የሕዝብ ምክር ቤቶች ስንፈትሽ በጎ ጅማሮዎች ቢኖሩም ቀላል የማይባሉ የታዩ ክፍተቶች መኖራቸውን እንገነዘባለን፡፡

አንደኛው ምንም እንኳን የአገራችንን ብሔር ብሔረሰቦችን ውክልና የያዙ ተመራጮች ወንበር ማግኘታቸው አንድ ዕርምጃ ቢሆንም፣ የአስተሳሳብ ብዝኃነትን በመድፈቅ የአንድ ፓርቲ አባላት በስም ለውጥ ብቻ የሕግ አውጭነት ተግባር ላይ መገኘታቸው ቀላል የማይባለውን ሕዝብ አማራጭ ድምፅ የሚያፍን አካሄድ ነው፡፡ ይህ የሆነው ሕዝቡ ፈቅዶ በመረጠው ውጤት ላይ ተመሥርቶ ነው ቢባል እንኳን ከምርጫ ሕጉ ገዳቢነት፣ ከምርጫው ዴሞክራሲያዊነት መጓደልና ነፃ አለመሆን ጋር ተያይዘው የሚነሱ ቅሬታዎች መልስ ያገኙ አይደሉም፡፡ ለዚህም ነው ሕዝቡ በአብላጫ ድምፅ ገዥውን ፓርቲ ‹‹መረጠ›› በተባለ ማግሥት በየመንደሩ ከፍ ያለ መንግሥታዊ ተቃውሞ እየገጠመ ያለው የሚሉ ተከራካሪዎች በርክተዋል፡፡

 ለሁሉም አሁን ያለው ኢሕአዴግ መራሹ ምክር ቤት ከእነ ክፍተቶቹም ቢሆን የጀመራቸውን ጥርስ ያለው ምክር ቤት የመሆን ተግባራት ስለማጠናከር መነጋገሩን መርጫላሁና እሱ ላይ ላተኩር፡፡ በተለይ አስፈጻሚውን የመቆጣጣር፣ አሳታፊነትን በተላበሰ መንገድ ለብዙኃኑ ሕዝብ የሚጠቅሙ ሕጎችን በማውጣትና ስምምነቶችን በማድረግ፣ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት እንዳይዘረፍ በተለይ ዋና ኦዲተርን በመሰሉ ተጠሪ መሥሪያ ቤቶቹ በመቆጣጣር፣ እንዲሁም መሾምና የተሾሙትን በተግባር የመገምገም ብሎም የማንሳት ተግባር፣ ወዘተ ምን ያህል ሚናውን አጠናክሮ ለመወጣት አቅዷል? ደግሞስ በአዲስ መንፈስና በተነቃቃ መንገድ አገሪቱ ላይ ያንዥበቡ የሕዝብ ቅሬታቸውንና የፖለቲካ ቀውሶችን እንደምን ለመፍታት አስቧል? ብሎ መነሳትም ተገቢ ይመስለኛል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተሰጠው ሥልጣንና ተግባር እጅግ ከፍተኛ ስለመሆኑ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 55 ማንበብ ብቻ በቂ ነው፡፡ ሕግ የማውጣትና ሹመቶችን የማፅደቅ ኃላፊነቱ ምንም እንኳን በሕግ የተገደበ ቢሆንም፣ የምክር ቤቱ የሥልጣን ደረጃ ወይም ልዕልና ምን ያህል ላቅ ያለ ስለመሆኑም ከዚህ አንቀጽ ድንጋጌዎች ላይ መረዳት ይቻላል፡፡

ከዚህ እውነታ ተነስቶ በአንድም በሌላም የዚህች አገር ወደ ፊት የመቀጠል ህልውና ከሕገ መንግሥቱ በተቀዳውና ለምክር ቤቱ በተሰጠው ሥልጣንና ተግባር ላይ የተወሰነ ነው ብሎ ማስቀመጥ ስህተት አይሆንም፡፡ ምክንያቱም የፖለቲካውንም ሆነ የኢኮኖሚውን ብሎም የማኅበራዊውን ዘርፍ የሚዘውሩ ባለሥልጣናትን ሹመት የሚያፀድቀው ምክር ቤቱ ነው፡፡ አገሪቷ የምትመራባቸውን ሕጎች የሚያወጣው፣ ስምምነቶችን የሚያፀድቀው አሁንም ይኼው ምክር ቤት ነው፡፡ ስለሆነም የዚህ ምክር ቤት መጠናከር ጠንካራ አስፈጻሚና ጠንካራ የሕግ ተርጓሚ በሚዛናዊ ተደጋጋፊነት ለመፍጠር ብቻ ሳይሆን፣ ጠንካራ አገር ለመገንባትም ያለው ድርሻ አቻ የለውም፡፡

አገራችን ከደርግ ሥርዓት ነፃ ከወጣችና የኢፌዴሪ መንግሥት ከተመሠረተ ወዲህ አምስት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶችን ዓይተናል፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችን በማካተት የምርጫው ውጤት ቢለያይም ከመጀመሪያው ሁለተኛው፣ ከሁለተኛው ሦስተኛውና አራተኛው በተሰጣቸው ተልዕኮ መሠረት የመሥራታቸው ነገር እየተውተረተረ መጥቶ እነሆ በአሁኑ አምስተኛ የምክር ቤት ዘመን ላይ ደርሰናል የሚሉ አሉ፡፡ በተቃራኒው ከምርጫ 1997 ወዲህ በተለይም የምርጫ 2002 እና 2007 ምክር ቤቶችን፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ጥበት የወለዳቸውና የተለየ ሐሳብ የማይራመድባቸው ምክር ቤቶች ሲሉም ደመጣሉ፡፡ ምንም ተባለ ምን የአሁኑ ምክር ቤት ሦስተኛውን ዓመት ሲጀምር፣ አቅሙና ነባሩ አሠራር በሚፈቅድለት ልክ ወደ ሥራ ሲመጣ በርካታ አገራዊ ጉዳዮች አጀንዳ ሆነው ይጠብቁታል፡፡

 በዋናነት በአንዳንድ ክልሎች መካከል በወሰንና በማንነት ጥያቄ ስም እየተነሳ ያለውን ውዝግብ በመፍታት፣ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርና ኅብረ ብሔራዊ አንድነቱ የሚጠናከርበትን ሕግጋትና አሠራሮችን በሥራ ላይ ማዋል  ቁልፍ ጉዳይ  ነው፡፡ ይኼ ሰፊና አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳይ እንደ ፌዴሬሽን ምክር ቤትና የፌደራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴርን ብርቱ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው፡፡

ሌላኛው ወሳኝ ተግባር ብዙዎቹ በዚሁ ምክር ቤት የተሾሙ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ከኃላፊነታቸው እየተነሱ፣ አንዳንዶቹም በአስከፊው ሙስና እየተጠረጠሩ ወደ ማረሚያ ቤት እየወረዱ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም ምክር ቤቱ ከቦታው በወረደው፣ ወደ ሌላ ሥፍራ በሄደውና በመሳሰለው ምትክ አዳዲስ የሚቀርቡለትን ሹመቶች  ከማፅደቅ ባለፈም፣ ከዚህ በፊት ሹመታቸውን ያፀደቀላቸው አስፈጻሚዎች ሹመት ለምን እንደሚነሳም መጠየቅ፣ ለሕዝብ ግልጽ ማድረግና የሕዝብ ውክልናውን ማረጋጋጥ  አለበት፡፡

  በዚህ ረገድ አስፈጻሚውን መጠየቅም ብቻ ሳይሆን አጥፊዎች፣ የሕዝብና የአገር አደራ ያጎደሉና አስፈላጊው እርምት ያልተወሰደባቸው ካሉም (በይሉኝታና በአድርባይነት ሳይደበዝዝ) በሕገ የሚጠየቁበትን አግባብ መፍጠር ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የአዳዲስ ተሿሚዎችን ማንነት፣ ብቃትና ፖለቲካዊ ታማኝነት እንዲሁ ለማፅደቅ መትጋት ይጠበቅበታል፡፡ ለአሉባልታና ላለመተማመን በር የሚከፍቱ ድርጊቶችንም መድፈን እንዲሁ፡፡

የምክር ቤቱ አባላት የመላው ሕዝብ ተወካዮች ናቸውና ተገዥነታቸውም ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝቡና ለኅሊናቸው እንደሆነ ራሱ ሕገ መንግሥቱ ይደነግጋል፡፡ ስለሆነም ተገዥ የሆኑለትን ሕዝብ ያገለግላል ብለው ሹመቱን ያፀደቁለት አካል በተቃራኒው ሆኖ ሲገኝ ዝም ብለው የሚያልፉ ከሆነ፣ የሕዝብ ውክልናቸው ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባ ማጤን ሕገ መንግሥታዊ ግዴታቸው እንደሆነ ማስተዋል ለነገ የሚባል ተግባር አይደለም፡፡ ስለሆነም አባላቱ በግላቸው፣ ምክር ቤቱ ደግሞ በጋራ የሕዝብ እንደራሴነታቸውን በተጨባጭ ማሳየት ያለባቸው ጊዜ ላይ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የፌዴራል ባለሥልጣናትን ለጥያቄ የመጥራትና የሕግ አስፈጻሚውን አካል አሠራር የመመርመር ሥልጣን ያለው ምክር ቤት፣ ለሕግ አስፈጻሚው አካል በተሰጠ ማንኛውም ሥልጣን ላይ በአንድ ሦስተኛ ድምፅ እስከተጠየቀ ድረስ የመወያየት፣ የመመካከርና አስፈላጊ መስሎ የታየውን ዕርምጃ የመውሰድ ሥልጣን ያለው የሕዝብ ምክር ቤት የሕዝብ ጥያቄዎችን የሚሰማበት ይኼ ዘመን ነው፡፡ ስለሆነም በመልካም አስተዳደርና በብልሹ አሠራሮች የተማረረውንና የሚያነባውን ሕዝብ እንባ ማበስ፣ በተለይ መንግሥትና አስፈጻሚው አካል ካሳለፈው ተሃድሶ አንፃር ተግባሩን መመርመር ከምክር ቤቱ ይጠበቃል፡፡

ሕዝብን አደባባይ ድረስ እንዲወጣ ያስገደደ የመልካም አስተዳደር ችግር የፈጠረ የሥራ አስፈጻሚ በውብ ቃላት የተከሸነ የሥራ ሪፖርት እያቀረበ ምክር ቤቱን ለማሳመን የሚሞክርበት አካሄድ መቆም አለበት፡፡ ይህን የምንለው ባለፉት ጊዜያት በተለይ ከመንገድ ግንባታና ከስኳር ኮርፖሬሽን እንቅስቃሴዎች ጋር በተያያዘ ለዓመታት ሲነገር የነበረው ስኬት፣ አሁን እየተሰማ ካለው የምዝበራ ወሬ አንፃር የጥልቀት ግምገማ እንዳልተደረገበት አመላካች በመሆኑም ነው፡፡

በድምሩ አሁን ለሚታየውም ሆነ በመጭው ጊዜ ሊያጋጥም በሚችለው ችግር  መፍትሔ ለማፈላላግ ደግሞ አሁንም የሕዝብ እንደራሴ ከሆነው ምክር ቤት ሌላ ማንም ሊመጣ አይችልም፡፡ በመሆኑም ምክር ቤቱ የጀመረውን የመስክ ምልከታ ብቻ ሳይሆን፣ በክዋኔና በፋይናንስ ኦዲት ላይ የተመሠረተ የቁጥጥር ሥርዓት አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ያን ጊዜ የሚቀርቡ ሪፖርቶችና መሬት ላይ ያለው እውነታ ምን ያህል ድርና ማግ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

ከመስክ ጉብኝት ባሻገርም ምክር ቤቱ አዳዲስ የፍተሻና የቁጥጥር ሥርዓቶችን መዘርጋት ቢችል መልካም ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ምንም እንኳን የጊዜ፣ የሰው ኃይልና የአቅም ውስንነት ቢኖርም በአስፈጻሚ ተቋማት ላይ ድንገተኛ ጉብኝት ማድረግ አንዱ አካሄድ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ጉብኝት በየተቋማቱ ያሉ የአገልግሎት አሰጣጦችን፣ የሠራተኞችንና የተገልጋዮችን ቅሬታና ትክክለኛ ስሜት፣ እንዲሁም የሕዝቡን ዕርካታና ቅሬታ ማግኘት ይቻላል፡፡ ስለሆነም ምክር ቤቱ በእንደዚህ ዓይነትና እስከ ዛሬ ባልሄደበት የቁጥጥርና የክትትል መንገድ መሄድ ይገባዋል፡፡

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ እንደ ዋናው ኦዲተር ዓይነት ተቋማት የሚያቀርቡለትን አስደማሚ ሪፖርቶች ተከታትሎ ዕርምጃ በማስወሰድ በኩል ያለበትን ክፍተት ማረም ይገባዋል፡፡ ምንም እንኳን እስከ ዛሬ አስደማሚ የኦዲት ሪፖርቶችን እያዳመጠ በአብላጫ ድምፅ ቢያፀድቅም፣ በዋናው ኦዲተር የሚቀርቡ የየተቋማት ሪፖርቶችን ተከትሎ ስለተጠየቀ አስፈጻሚ፣ ዕርምጃ ስለተወሰደበት ተቋምም የተሰማም ሆነ የታየ ነገር የለም፡፡ ለምን? ዓለም ከተባለ በትክክል ለሕዝቡ ሊነገረው ይገባል፡፡ እከሌ አሁን መንግሥት እየከሰሳቸው ባሉ የሥራ ኃላፊዎች ፋይል ላይ የዋና ኦዲተር ሪፖርትን ማካተቱ ሲታይ፣ ምክር ቤቱ ከዚህም ቀድሞ እርምት እንዲወሰድ የማድረግ ዕድል እንደነበረው ያመላክታል፡፡ ስለዚህ በቀጣዩ ጊዜ ሕግ የማስከበር ተግባር መታረምና መጠናከር ግድ ይለዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚከታታላቸውን የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን፣ የምርጫ ቦርድ፣ የሕዝብ እንባ ጠባቂና ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን የመሳሰሉ ሕገ መንግሥታዊ አካላትንም ጠፍንጎ በመያዝ የሕዝብ አደራቸውን እንዲወጡ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ይኼንን ማድረግ ሲቻልም ነው ሕዝብ በወኪሎቹ ላይ ሙሉ እምነት የሚኖረው፣ ብሎም ይበልጥ ተጠቃሚ የሚሆነው፡፡

እስካሁን እየታየ እንዳለው ግን እነዚህ ተጠሪ ተቋማት ሕዝብ አለማርካታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከ25 ዓመታት በፊት በተደራጁበት ቁመና ላይ መገኛታቸውና ከሁሉም በላይ በሕገ መንግሥቱም በጉልህ የተሰጧቸውን ኃላፊነቶች አሟልተው አለመተግበራቸው ክፉኛ የሚያስቆጭ ጉድለት ነው፡፡ ይህን ዝንባሌ ማስተካካል ደግሞ ቀዳሚው የፓርላማው ኃላፊነት መሆን ይኖርበታል ቢባል ግድፈት አይመስለኝም፡፡ 

በዳግም አሳምነው ገብረ ወልድ   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡