Skip to main content
x
‹‹ለአገሪቱ ሶሽዮ ኢኮኖሚ ዕድገት የበኩላችንን አስተዋጽኦ እያደረግን ነው››

‹‹ለአገሪቱ ሶሽዮ ኢኮኖሚ ዕድገት የበኩላችንን አስተዋጽኦ እያደረግን ነው››

አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ከአሜሪካው ትራንስ ወርልድ ኤርላይን ጋር በገባው ውል እ.ኤ.አ. 1945 የተመሠረተው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ቀዳሚ አየር መንገድ ነው፡፡ 72 ዓመት ሊሞላው የተቃረበው አየር መንገዱ በርካታ የአፍሪካ አየር መንገዶች በተለያዩ ምክንያቶች ሲፈርሱ በየጊዜው የተጋረጡበትን ችግሮች ተቋቁሞ መዝለቅ ችሏል፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት አዳዲስ አውሮፕላኖች በመግዛትና የበረራ አድማሱን በማስፋት በፈጣን የዕድገት ጎዳና ላይ ይገኛል፡፡ ሰባት የትርፍ ማዕከላት በማቋቋም ወደ አቪዬሽን ቡድንነት ያሸጋገረ ሲሆን፣ በቅርቡ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትና የሆቴልና ጉዞ አገልግሎት ኩባንያ አቅፎ እንደ አዲስ በመዋቀር ላይ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ከቃለየሱስ በቀለ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- እ.ኤ.አ. የ2016-2017 በጀት ዓመት የአየር መንገዱ አፈጻጸም ምን ይመስላል?

አቶ ተወልደ፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ፈታኝ ዓመት አሳልፏል፡፡ በተለይ የአፍሪካ አየር መንገዶች በተለያዩ ችግሮች የተፈተኑበት ዓመት ነበር፡፡ ለእኛ ግን በጣም ጥሩ ዓመት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የራዕይ 2025 የዕድገት መርሐ ግብር ከጀመርን ሰባት ዓመት ሆኗል፡፡ የ15 ዓመቱን የዕድገት መርሐ ግብር ተግባራዊ እያደረግን ግማሽ ላይ እንገኛለን፡፡ በመርሐ ግብሩ የተቀመጡትን ግቦች በሙሉ እያሳካን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ስንገመግመው እ.ኤ.አ. በ2016 እስከ 2017 ጥሩ ውጤት የተመዘገበበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በበጀት ዓመቱ የተጋፈጥናቸው በርካታ ችግሮች ነበሩ፡፡ የነዳጅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ እ.ኤ.አ. ከ2014 ጀምሮ እየቀነሰ መጥቷል፡፡

ሪፖርተር፡- የነዳጅ ዋጋ መቀነስ ለአየር መንገዶች የምሥራች አይደለም እንዴ?

አቶ ተወልደ፡- ትክክል ነው፡፡ የአንድ አየር መንገድ የነዳጅ ወጪ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ የነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆል ወጪያችንን እንድንቀንስ ረድቶናል፡፡ ነገር ግን በዓለም አቀፍ ገበያው ላይ የነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆል ነዳጅ አምራች የሆኑ የአፍሪካ አገሮች ኢኮኖሚን አላሽቆታል፡፡ እንደ ናይጄሪያ፣ አንጎላ፣ ቻድ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ጋቦን፣ ሱዳንና ካሜሩን ያሉ ነዳጅ ላኪ አገሮች የነዳጅ ዋጋ በመውረዱ ምክንያት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ገጥሟቸዋል፡፡ የየአገሮቹ ገንዘብ ዋጋ ወርዷል፣ ግብፅም ተመሳሳይ ችግር ገጥሟታል፡፡ በእነዚህ ችግሮች ምክንያት በእነዚህ አገሮች የሸጥነውን የአየር ቲኬት ወደ ዶላር መንዝረን ወደ አገራችን ማስተላለፍ አልቻልንም፡፡ ይህ በገቢያችን፣ በትርፋማነታችንና በገንዘብ ዝውውራችን ላይ ትልቅ ሳንካ ፈጥሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ነዳጅ ላኪ አገሮች ኢኮኖሚያቸው በመጎዳቱ ምክንያት ለአየር ጉዞ የሚያወጡት ወጪ ቀንሷል?

አቶ ተወልደ፡- በትክክል፡፡ ነዳጅ ላኪ አገሮች የነዳጅ ዋጋ በማሽቆልቆሉ ገቢያቸው ክፉኛ ተናግቷል፡፡ በመሆኑም መንግሥትም ሆነ የግሉ ዘርፍ ለጉዞ የሚያወጡትን ወጪ ቀንሰዋል፡፡ ለአየር ጉዞ ያለው ፍላጎት ቀንሷል፡፡ በተለያዩ የምሥራቅ፣ የመካከለኛውና የምዕራብ አፍሪካ አገሮች፣ እንዲሁም በግብፅ በተፈፀሙ የሽብር ጥቃቶች የቱሪዝም ኢንዱስትሪውም ተጎድቷል፡፡ ከአፍሪካ ሁለተኛ ትልቁ ኢኮኖሚ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ የኢኮኖሚዋ መቀዛቀዝ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ በገቢያችን ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ቁጥሮች ሊሰጡን ይችላሉ? ገቢያችሁን፣ ትርፋችሁንና ያጓጓዛችሁዋቸውን መንገደኞች ብዛት ቢገልጹልን

አቶ ተወልደ፡- ቅድም የገለጽኳቸው ችግሮች ተደማምረው ገቢያችንን ቀንሰውታል፡፡ ገቢያችን በአሥር በመቶ ያደገ ቢሆንም ያቀድነውን ያህል አላደገም፡፡ ከ2016 እስከ 2017 በጀት ዓመት የ2.7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝተናል፡፡ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የአሥር በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ወደ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚጠጋ መንገደኛና 338,000 ቶን ጭነት አጓጉዘናል፡፡ ትርፋችን 230 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ትርፋችን መጠነኛ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ነገር ግን ከነበረው ፈተና አንፃር አፈጻጸሙ በጣም ጥሩ የሚባል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከምንዛሪ ችግር ጋር ተያይዞ ገንዘባችሁን ወደ ኢትዮጵያ ማስተላለፍ እንደቸገራችሁ ገልጸዋል፡፡ በናይጄሪያና በግብፅ ያላችሁን ገንዘብ በአብዛኛው አውጥታችኋል፡፡ አንጎላና ሱዳን ዘንድ አሁንም ትልቅ ችግር እንዳለ ነው የሰማነው፡፡ ይህን ቢያብራሩልን?

አቶ ተወልደ፡- በእውነት ትልቅ ፈተና ነው የገጠመን፡፡ እንደ ማኔጅመንት ሌሊት ከእንቅልፋችን የሚያባንነን ሐሳብ ነው፡፡ ናይጄሪያ፣ አንጎላ፣ ሱዳንና ግብፅ የተያዘብን ገንዘብ መጠን 220 ሚሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር፡፡ ግብፅ ወደ 20 ሚሊዮን ዶላር ነበረን፡፡ የግብፅ መንግሥት ከፍተኛ የምንዛሪ ለውጥ አደረገ፡፡ አንድ ዶላር በስድስት የግብፅ ፓውንድ ይመነዘር የነበረውን ወደ 16 ፓውንድ ቀየረው፡፡ በዚህ ምክንያትት 15 ሚሊዮን ዶላር ከስረን አምስት ሚሊዮን ዶላር ብቻ ለማውጣት ችለናል፡፡ በናይጄሪያ የተያዘብን ገንዘብ 150 ሚሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር፡፡ በአገሪቱ ኒያራ ገንዘብ የሸጥነው ቲኬት መጠን በዶላር ሲሰላ 150 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በናይጄሪያ አምስት መዳረሻዎች ያሉት ትልቅ አየር መንገድ ነው፡፡ ሽያጫችን በናይጄሪያ ትልቅ ነው፡፡ ከናይጄሪያ መንግሥት ጋር በቅርበት ተባብረን በመሥራት በየጊዜው እየቀነስን እያወጣን፣ በአሁኑ ጊዜ አብዛኛውን ማውጣት ችለናል፡፡ ቀሪ ያለን ከ20 እስከ 30 ሚሊዮን ዶላር ቢሆን ነው፡፡ ያ ደግሞ በየዕለቱ የሚደረግ ሽያጭ ነው፡፡ ትልቁ ቀውስ ያለው አንጎላ ነው፡፡ በአገራቸው ገንዘብ ኩዋንዛ የሸጥነው 110 ሚሊዮን ዶላር እስካሁን እንደተያዘብን ይገኛል፡፡ ከአንጎላ መንግሥት ጋር በተደጋጋሚ ብንወያይም በገጠማቸው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ውጤት ማግኘት አልቻልንም፡፡

      የአፍሪካ አየር መንገዶች ማኅበርና የዓለም አቀፍ አየር ትራንስፖርት ማኅበር ሁሉንም አየር መንገዶች ወክለው ገንዘቡን ለማስለቀቅ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ አንጎላ ውስጥ በነሐሴ ወር ብሔራዊ ምርጫ ተካሂዷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ አዲስ መንግሥት (ካቢኔ) በማዋቀር ላይ ናቸው፡፡ ከአዲሱ መንግሥት ጋር ተደራድረን ችግሩን እንፈታለን የሚል እምነት አለን፡፡ በጎረቤታችን ሱዳን 30 ሚሊዮን ዶላር ተይዞብናል፡፡ እንደሚታወቀው ሱዳን ወዳጅ አገር ናት፡፡ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ጠንካራ የሆነ የሁለትዮሽ ግንኙነት አለ፡፡ ሁለቱ መንግሥታት ችግሩን ለመፍታት በጋራ እየሠሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በአጋርነት አየር መንገዶች ለመመሥረት በመንቀሳቀስ ላይ ነው፡፡ በናይጄሪያም ከአሪክ ኤር ጋር የተጀመረ ድርድር ነበር፡፡ እነዚህ ጥረቶች ምን ላይ ደርሰዋል?

አቶ ተወልደ፡- ይህን ለመግለጽ የአፍሪካ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ያለበትን ሁኔታ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ገበያ በውጭ አየር መንገዶች የተያዘ ነው፡፡ በአፍሪካና በሌሎች አኅጉሮች መካከል ባለው ገበያ የአፍሪካ አየር መንገዶች ድርሻ 60 በመቶ የነበረው ወደ 20 በመቶ አሽቆልቁሏል፡፡ ዛሬ 80 በመቶ የገበያ ድርሻ በውጭ አየር መንገዶች (አፍሪካዊ ባልሆኑ) የተያዘ ሲሆን፣ የአፍሪካ አየር መንገዶች የገበያ ድርሻ 20 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህ መለወጥ አለበት፡፡ ቢያንስ 50 በመቶ የገበያ ድርሻ ሊኖረን ይገባል፡፡ የገበያ ድርሻ ጉዳይ ብቻ አይደለም፣ የህልውና ጥያቄም ጭምር ነው፡፡ የአፍሪካ አየር መንገዶች ቀስ በቀስ እየሞቱ ነው፡፡ ከ20 ዓመት በፊት የነበሩ ጠንካራ የአፍሪካ አየር መንገዶች ግብዓተ መሬታቸው ተፈጽሟል፡፡ እንደ ናይጄሪያ ኤርዌይስ፣ ጋና አየር መንገድ፣ ኤር አፍሪክ፣ ኮንጎ (ዛየር ኤር)፣ ዛምቢያ፣ ኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢስት አፍሪካን ኤርዌይስ ትልልቅ አየር መንገዶች ነበሩ፡፡ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በስተቀር ሌሎቹ ጠፍተዋል፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኬንያ ኤርዌይስ፣ ሳውዝ አፍሪካ ኤርዌይስ፣ ኢጅፕት ኤር፣ ሮያል ኤር ሞሮክ፣ ታግአንጎላ፣ ቱኒዝ ኤር እና ኤር አልጄሪ አየር መንገዶች ቢኖሩም ከገበያው እኩል አላደጉም፡፡ የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ገበያ አድጓል፡፡ ነገር ግን 80 በመቶውን የውጭ አየር መንገዶች ናቸው የተቆጣጠሩት፡፡ የአፍሪካ አየር መንገዶች የተቀረውን ይቀራመታሉ፡፡

ይህ አሳሳቢ ችግር ነው፡፡ ይህንን ሚዛናዊ ያልሆነ የገበያ ድርሻ ካልቀየርን ማን ያውቃል ከአሥር ዓመት በኋላ ሁሉም የአፍሪካ አየር መንገዶች ሊጠፉ ይችላሉ፡፡ የአፍሪካ አገሮች የገበያ ድርሻ የሚያሳየው ግራፍ እየወረደ ነው፡፡ የአፍሪካ አገሮች ተባብረን ግራፉን መቀልበስ ካልቻልን አንድም የአፍሪካ አየር መንገድ ላይገኝ ይችላል፡፡ አሁን ያለው ፍትሐዊ ያልሆነ የገበያ ድርሻ እንደ ፓን አፍሪካ አየር መንገድ ያሳስበናል፡፡ በአጠቃላይ በአፍሪካ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ እየታየ ያለው አካሄድ አሳሳቢ ነው፡፡ የአፍሪካ አየር መንገዶችና አገሮች ተባብረው ሁኔታውን መለወጥ አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡ እኛም የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ እንፈልጋለን፡፡ የተለያዩ ክልላዊ መናኸሪያዎችን ማቋቋም የምንፈልገው ከዚህ አንፃር ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ስኬታማ የሆኑ የአፍሪካ አየር መንገዶችና ክልላዊ መናኸሪያዎች ሲኖሩ፣ የአፍሪካ አገሮችን በአየር ትራንስፖርት የበለጠ ማስተሳሰር ይቻላል፡፡ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በእስያ ክልላዊ መናኸሪያዎች በመመሥረት ያደረጉት ጥረት ውጤታማ ነው፡፡ በአውሮፓ ብትመለከት ለንደን፣ ፍራንክፈርት፣ ፓሪስና አምስተርዳም የተዋጣላቸው መናኸሪያዎች ናቸው፡፡ በአሜሪካም ዋሽንግተን ዳላስ፣ ኒውዮርክ (ጄኤፍኬ)፣ አትላንታና ዳላስ ግዙፍ መናኸሪያዎች ናቸው፡፡ ክልላዊ መናኸሪያ የንግድ አሠራር እስካሁን ውጤታማ ነው፡፡

በአፍሪካ ከመካከለኛው አፍሪካ አገሮች ጋር ተነጋግረን አንድ ክልላዊ መናኸሪያ መካከለኛው አፍሪካ ላይ ብናቋቁም፣ የምዕራብና የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችን፣ የምዕራብና ደቡብ አፍሪካ አገሮችን በተሻለ በአየር ትራንስፖርት በማገናኘት የኢኮኖሚ ትስስር ማጠናከር ይቻላል፡፡ ክልላዊ መናኸሪያው ዛምቢያ፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ወይም ጎንኮ ብራዛቪል ካሉ የመካከለኛው አፍሪካ አገሮች ጋር በመነጋገር የሚቋቋም ይሆናል፡፡ የጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ቢታይ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ በሰሜንና ደቡብ አፍሪካ፣ በምዕራብና በምሥራቅ አገሮችን ለማግኘት አማካይ ቦታ ላይ የምትገኝ በመሆኑ ክልላዊ መናኸሪያውን ለማቋቋም ወሳኝ ቦታ ነበረች፡፡ ሆኖም አሁን ባለው የአገሪቱ  የፀጥታ ችግር የማይታሰብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዛምቢያ መንግሥት ጋር በመተባበር በሽርክና አየር መንገድና ክልላዊ መናኸሪያ ለማቋቋም በጋራ እየሠራ ይገኛል፡፡ ድርድሩ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ሲሆን በቅርቡ ድርድሩን አጠናቀን የሽርክና ስምምነት እንፈራረማለን የሚል እምነት አለን፡፡ አየር መንገዱ በሉሳካ የሚቋቋም ሲሆን የመካከለኛው አፍሪካ መናኸሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ የሞዛምቢክ መንግሥት አየር መንገድ እንድናቋቁም ይሁንታ ሰጥቶናል፡፡ የሞዛምቢክ መንግሥት አየር መንገዶች በሞዛምቢክ የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ አየር መንገድ እንዲያቋቁም ባቀረበው ግብዣ መሠረት ዕቅዳችንን አቅርበን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በአገር ውስጥ አየር መንገድነት ሞዛምቢክ ውስጥ ለማስመዝገብ ሒደት ላይ ነን፡፡

ቻድ የነዳጅ ሀብት ያላት ትልቅ አገር ናት፡፡ በምዕራብ አፍሪካ ስትራቴጂካዊ ቦታ የምትገኝ ናት፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድና በቻድ መንግሥት ባለቤትነት አዲስ አየር መንገድ ለማቋቋም ንግግር ጀምረናል፡፡ ንግግሩ በጥሩ ሁኔታ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ከጂቡቲ መንግሥትም ጋር ድርድር ጀምረናል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጂቡቲ ጥሩ የሶሽዩ ኢኮኖሚክ ዕድገት እየታየ ነው፡፡ ቻይና ለመጀመርያ ጊዜ ትልቅ የጦር ካምፕ በጂቡቲ አቋቁማለች፡፡ ሌሎችም ኃያል አገሮች የጦር ካምፕ አላቸው፡፡ በርካታ አገሮች ግዙፍ የጦር መርከብ አሰማርተዋል፡፡ የጂቡቲ መንግሥት የባሕር ወደቡን በከፍተኛ ደረጃ እያስፋፋ ነው፡፡ ኤርፖርቱንም እያሳደገ ነው፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገ ነው፡፡ ሁኔታዎች በአግባቡ ከተመቻቹ ጂቡቲ የአፍሪካ ዱባይ ልትሆን ትችላለች፡፡ ይህን ከግንዛቤ በመክተት ከኤር ጂቡቲ ጋር ሽርክና ለመመሥረት ከኤር ጂቡቲ ሊቀመንበር ጋር ውይይት አካሂደናል፡፡

ሪፖርተር፡- በናይጄሪያስ ዕቅዳችሁ ምንድነው? ናይጄሪያ ትልቅ አገር ነው፡፡ ከፍተኛ የነዳጅ ሀብት አለ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አምስት መዳረሻዎች አሉት፡፡ ናይጄሪያ ውስጥ ምን ለመሥራት አቅዳችኋል?

አቶ ተወልደ፡- ናይጄሪያ ትንሽ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አሉ፡፡ አሪክ ኤር የተሰኘው የግል አየር መንገድ ከስሮ ሊዘጋ ሲል አምኮን የተባለው የናይጄሪያ መንግሥት ኩባንያ ተረክቦ እያስተዳደረው ይገኛል፡፡ አምኮን እንደተረከበው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማኔጅመንት ኮንትራት ወስዶ እንዲያስተዳድረው የተጀመረ ድርድር ነበር፡፡ ሆኖም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ድርድሩ ተቋርጧል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አየር መንገድና በአሪክ ኤር መካከል እየተካሄደ ያለ ድርድር እንደሌለ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡

አምኮን አሪክ ኤርን እያስተዳደረ በመሆኑ እኛም አሪክ ኤር ባለበት የተወሳሰቡ የገንዘብና የሕግ ጉዳዮች አየር መንገዱን የመረከብ ፍላጎት የለንም፡፡ ስለዚህ ንግግሩ ተቋርጧል፡፡ ነገር ግን የናይጄሪያ መንግሥት አዲስ ብሔራዊ አየር መንገድ ለማቋቋም ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ሉፍንታንዛ ኮንሰልቲንግ ከተባለ ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ጋር በመሆን ጥናት አካሂደዋል፡፡ የናይጄሪያ መንግሥት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት እኛም ተባብረን ለመሥራት ያለንን ፍላጎት የሚገልጽ ዕቅድ አቅርበናል፡፡ በሌላ በኩል በናይጄሪያ ከሚንቀሳቀሱ የግል አየር መንገዶች ጋር አብረን ለመሥራት ፍላጎት አለን፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሥራ ኃላፊዎች ሁለት የናይጄሪያ የግል አየር መንገዶችን በመገምገም ላይ ናቸው፡፡ አንዳቸውን መርጠን አብረን ልንሠራ እንችላለን፡፡

ነገር ግን ይህን ስናደርግ መርሐ ግብራችን ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ከናይጄሪያ በቅርብ ርቀት ላይ ቶጐ ሎሜ አስካይ አየር መንገድ ይገኛል (የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስካይ አየር መንገድ ላይ 40 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ያለው ሲሆን በማኔጅመንት ኮንትራት ወስዶ አየር መንገዱን በማስተዳደር ላይ ይገኛል)፡፡ ስለዚህ የቢዝነስ ስትራቴጂያችን በግልጽ መቀመጥ ይኖበታል፡፡ ከጋና መንግሥት ጋርም የጀመርነው ጥረት አለ፡፡ የጋና አቪዬሽን ሚኒስትር በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከልዑካቸው ጋር የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጎብኝተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የገነባቸውን የጥገና ማዕከል፣ የካርጎ ተርሚናል፣ የምግብ ማደራጃና የአቪዬሽን አካዳሚ ጎብኝተው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዕድገት ጉዞ ለመረዳት ጥረት አድርገዋል፡፡ ከእኛ ጋር አብሮ ለመሥራት ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ሚኒስትሯ ባቀረቡልን ጥያቄ መሠረት ከጋና መንግሥት ጋር ተባብረን መሥራት እንደምንፈልግ የሚገልጽ ሰነድና የሥራ ዕቅድ አዘጋጅተን አቅርበንላቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በጋና አዲስ ብሔራዊ አየር መንገድ ለማቋቋም ነው የታሰበው?

አቶ ተወልደ፡- አዎ፡፡ የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪ ውስብስብ ነው፡፡ አየር መንገድ ለማቋቋም ከፍተኛ ካፒታልና ዕውቀት ይጠይቃል፡፡ አየር መንገድ አቋቁሞ መምራት ብዙ ፈተናዎች አሉት፡፡ የመጠንም ጉዳይ ወሳኝነት አለው፡፡ ምን ያህል ገበያ አለ የሚለውም ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ በመስኩ የሠለጠኑ ብቃት ያለው ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ አየር መንገድ ለማቋቋም የሚፈልግ አገር ሁሉ ሮጦ የሚገባበት ሥራ አይደለም፡፡ ተባብሮ መሥራት የተሻለ አማራጭ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አቪዬሽን ቡድን ተቀይሯል፡፡ በቅርቡም የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትና የሆቴልና ቱር አገልግሎት ኩባንያ አካቶ እንደ አዲስ እየተቀየረ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ጋር የመቀናጀቱ ሥራ እንዴት እየሄደ ነው?

አቶ ተወልደ፡- ከኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ጋር መዋሀድ ያስፈለገበት ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ከባድ ውድድር ነው፡፡ ከሥራው ባህሪ አንፃር የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውድድር የበዛበት ነው፡፡ በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳድረህ አሸናፊ መሆን ይጠበቅብሃል፡፡ አለበለዚያ ትጠፋለህ፡፡ በራዕይ 2025 ባስመጥናቸው ግቦች የኢትዮጵያ አየር መንገድን ከአፍሪካ ትልቁ የአቪዬሽን ግሩፕ ማድረግ ችለናል፡፡ ትልቁን የበረራ ምግብ ማደራጃ፣ የአውሮፕላን ጥገና አገልግሎት ማዕከል፣ ትልቁን የካርጎ ተርሚናልና ትልቁን የአቪዬሽን አካዳሚ ገንብተናል፡፡ እነዚህ የአየር መንገዱ ዕድገት መሠረት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ የቦይንግ ዘመናዊ ምርት የሆነውን ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላንና የኤርባስ አዲስ ምርት የሆነውን ኤርባስ A350 አውሮፕላኖችን ጨምሮ 92 አውሮፕላኖች ባለቤት ነው፡፡ በአፍሪካ አየር መንገዶች ማኅበር የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ መሆኑ የተመሰከረለት ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ቀዳሚ አየር መንገድ እንደሆነ በሪፖርቱ አስቀምጧል፡፡ በአየር መንገዱ በኩል የተሳካልን ቢሆንም በኤርፖርት አገልግሎት ወደኋላ ቀርተናል፡፡

      በአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪ የምትወዳደረው በአየር መንገድህ ብቻ ሳይሆን በኤርፖርትህም ነው፡፡ ጥሩ አየር መንገድ ኖሮህ ኤርፖርትህ ዘመናዊ ካልሆነ ተወዳዳሪ መሆት አትችልም፡፡ እንደ አየር መንገዱ አዲስ አበባን ከአፍሪካ ምርጥ መዳረሻ ማድረግ አልተሳካልንም፡፡ የአዲስ አበባ ኤርፖርት በአገልግሎቱ፣ በፋሲሊቲና በደንበኞች አገልግሎት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አይደለም፡፡ ይህ ችግር አየር መንገዱን ወደኋላ ሲጎትተው ቆይቷል፡፡ መንግሥት ችግሩን ተመልክቶ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በኢትዮጵያ አቪዬሽን ግሩፕ እንዲዋሀድ ወስኗል፡፡ የራሱን ማኔጅመንት ይዞ በአቪዬሽን ቡድኑ ሥር ከአየር መንገዱ ጋር ተናቦና ተቀናጅቶ እንዲሠራ ተወስኗል፡፡ በዚህ መሠረት የማቀናጀቱ ሥራ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ከ500 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች በኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ ሥልጠና እየሰጠን ነው፡፡ በኤርፖርት ኦፕሬሽን፣ የደንበኞች አገልግሎትና የመንገደኞች አያያዝ ሰፊ ሥልጠና እየሰጠን ነው፡፡ ደንበኛ ንጉሥ ነው፣ ደንበኛ ሁልጊዜ ትክክል ነው የሚለውን እሳቤ ለማስረፅና ለመንገደኞች ሊደረግ ስለሚገባው መስተንግዶ ጥልቅ ግንዛቤ ለማስያዝ እየሠራን ነው፡፡ መንገደኞች በኤርፖርት የሚያሳልፉት ጊዜ ወሳኝነት አለው፡፡ በዚህ ረገድ በዚህ አጭር ጊዜ በአዲስ አበባ ኤርፖርት ለውጥ እያመጣን ነው፡፡ ነፃ የገመድ አልባ ኢንተርኔት አገልግሎት መስጠት ጀምረናል፡፡ ይህ ያልነበረ አገልግሎት ነው፡፡ አንዳንድ ኤርፖርቶች የሚያስከፍሉ ቢሆንም እኛ ነፃ እንዲሆን አድርገናል፡፡

      ብዙ ሺሕ ማይልስ አቋርጦ የመጣ መንገደኛ በኢሜይል፣ በፌስቡክ ከቤተሰቡ ጋር መገናኘት ይፈልጋል፡፡ ነጋዴው የሥራ እንቅስቃሴውን በኢንተርኔት መከታተል ይፈልጋል፡፡ ወጣቶች የሚቀጥለው በረራቸው እስከሚደርስ እየተዝናኑ መቆየት ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ የኢንተርኔት አገልግሎት ወሳኝ ነው፡፡ ሌሎችም የሱቆች፣ የምግብ ቤትና የካፌ አገልግሎቶች፣ የመፀዳጃ ቤቶች ይዞታቸው ለመንገደኛው ምቹ መሆን አለባቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ነው የኤርፖርቶች ድርጅት ውህደት ያስፈለገበት ምክንያት፡፡ የማቀናጀቱ ሥራ በመልካም ሁኔታ እየተካሄደ ነው፡፡ የሆቴልና ቱር አገልግሎትን በተመለከተ አዲስ አበባ ውስጥ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እጥረት አለ፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ውስን ሆቴሎች ነው ያሉት፡፡ ሸራተን አዲስ፣ ራዲሰን ብሉና ማሪየት ሆቴል ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቁ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ የኮንፈረንስ ቱሪዝም እያደገ ነው የመጣው፡፡ የአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት ኢኮኖሚ ኮሚሽን መቀመጫ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ አዲስ አበባ በርካታ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን ታስተናግዳለች፡፡ እነዚህን የሚመጥኑ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች በብዛት የሉንም፡፡

በዚህ ምክንያትት እንግዶቻችን የምናሳርፍበትት ሆቴል በማጣት ስንቸገር ኖረናል፡፡ ከዚህ ተነስተን ባለአምስት ኮከብ 373 ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ መኝታ ክፍሎች ያሉት ሆቴል እየገነባን ነው፡፡ ይህ ሆቴል ሲጠናቀቅ ለደንበኞቻችን የጥቅል አገልግሎት መስጠት ያስችለናል፡፡ ለአሜሪካ፣ ለአውሮፓና ለእስያ ጎብኚዎች የአየር ጉዞ ቲኬት፣ ሆቴልና ጉብኝት (ቱር) በጥቅል መሸጥ ያስችለናል፡፡ ቱሪስት ቲኬት ከአንድ ቦታ ሆቴል፣ ከሌላ ቦታ የጉብኝት አገልግሎት ከሌላ ድርጅት ከሚገዛ ሁሉም አገልግሎት በአንድነት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በአንድ መስኮት አገልግሎት መግዛት ይችላል፡፡ ይህ ለቱሪስቱ ምቹና ቀላል ያደርገዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣውን ቱሪስት ቁጥር ለማሳደግ ይረዳናል፡፡ ዕቅዳችን የቱሪዝሙን ዘርፍ ለማሳደግ ነው እንጂ፣ ገበያ ውስጥ ያሉትን ሆቴሎች ገበያ ለመቀራመት አይደለም፡፡ ይህ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- የመንግሥት ሆቴሎችን ተረክባችሁ ለማስተዳደር እያሰባችሁ ነው?

አቶ ተወልደ፡- ይህ የማድረግ ውሳኔ በእጃችን አይደለም፡፡ ሥልጣኑ የለንም፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴልና ግዮን ሆቴልን የተመለከተ እንደሆነ ውድ የሆኑ የአገር ሀብት ናቸው፡፡ ከጊዜ ብዛት ደረጃቸው ወርዷል፡፡ በደረጃ አሰጣጥ ሒልተን ሆቴል የገጠመው ችግር የሚታወቅ ነው፡፡ እነዚህን የአገር ቅርስ የሆኑ ሆቴሎችን አድሶና አስፋፍቶ ብቃታቸውን ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ሲወስን ሆቴሎችን ተረክበን ለማስተዳደር ዝግጁ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር በቅርቡ ይፋ ባደረገው ወደ ግል ይዞታ የሚዛወሩ ድርጅቶች ዝርዝር ውስጥ የአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል ይገኝበታል፡፡ በጨረታ ትሳተፋላችሁ?

አቶ ተወልደ፡- የመንግሥት ድርጅት እንደ መሆናችን በፕራይቬታይዜሽን ጨረታ መሳተፍ አንችልም፡፡ ወደ ግል ለማዞር ጨረታ ከወጣ እዚያ ውስጥ አንገባም፡፡ ይህ የመንግሥት ውሳኔ ነው፡፡ ነገር ግን ከግል ኩባንያዎች ጋር በጋራ ለማልማት የምንችልበት ዕድል ይኖራል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአየር ጭነት ዘርፍ ትልቅ ትኩረት የሰጠ ይመስላል፡፡ በቅርቡ ግዙፍ የካርጎ ተርሚናል አስመርቃችኋል፡፡ በሰኔ ወር በተካሄደው የፓሪስ ኤርሾው ሁለት ቦይንግ 777 ዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ገዝታችኋል፡፡ የኢትዮጵያ ካርጎ ስሙን በመቀየር የኢትዮጵያ ካርጎና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ብላችሁታል፡፡ አዲሱ የቢዝነስ መርሐ ግብር በካርጎ ዘርፍ ምንድነው?

አቶ ተወልደ፡- የአየር ጭነት አገልግሎት ዘርፍ የተመዘገበው ዕድገት በራዕይ 2025 በተቀመጠው ግብ መሠረት የተገኘ ውጤት ነው፡፡ ስምንት የጭነት አውሮፕላኖች አሉን፡፡ ስድስቱ አዲስና ዘመናዊ የሆኑት ቦይንግ 777 አውሮፕላኖች ናቸው፡፡ ሁለቱ ቦይንግ 757 ናቸው፡፡ ከአፍሪካ ትልቁ የካርጎ ኦፕሬተር ለመሆን በቅተናል፡፡ ዛሬ የምንወዳደረው ከመካከለኛው ምሥራቅ አየር መንገዶች ጋር ነው፡፡ ለዚህም ነው ግዙፍ የሆነ የካርጎ ተርሚናል የገነባነው፡፡ ሁለት ተጨማሪ ግዙፍ ቢ 777 አውሮፕላኖችም አዘናል፡፡ የአፍሪካ አገሮች ኢኮኖሚ እያደገ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት በማደግ ላይ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቀዳሚ ለመሆን ዕቅድ ነድፋ እየሠራች ያለች አገር ናት፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ ነው፡፡ የሐዋሳ፣ የመቐለና የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተጠናቀው ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፣ የአዳማና የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ ነው፡፡ እነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተቀላጠፈ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ያስፈልጋቸዋል፡፡ አምራች ኢንዱስትሪውን አሳድገህ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሎጀስቲክስ አገልግሎት ካላዘጋጀህ ውድቀት ይከተላል፡፡ በዚህ ረገድ ለሎጂስቲክስ ዘርፍ ዕድገት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ፣ የካርጎ አገልግሎት ከሎጂስቲክስ ዘርፍ ጋር አቀናጅተን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት እንፈልጋለን፡፡ የሎጂስቲክስ ዘርፉን እንቀላቀላለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ጋር ተቀናጅታችሁ ማለት ነው?

አቶ ተወልደ፡- ከባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ጋር ስትራቴጂያችንን እያቀናጀን አይደለም፡፡ እነሱ የራሳቸው ውጥኖች አሏቸው፡፡ እኛ በራሳችን አቅም እየሠራን ነው፡፡ አምራችና ላኪዎችም አማራጮች ይኖራቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር ትተባበራላችሁ?

አቶ ተወልደ፡- ከኮርፖሬሽኑ ጋር ተባብረን እንሠራለን፡፡ ሐዋሳ በተገነባው ኤርፖርት አማካይነት ለሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ቀጥታ የካርጎ አገልግሎት ልንሰጥ እንችላለን፡፡ የተቀላጠፈ የሎጂስቲክስ ዘርፍ ካልገነባን አምራች ኢንዱስትሪው በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሊሆን አይችልም፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለዚህ ዘርፍ ዕድገት በምን መንገድ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል?

አቶ ተወልደ፡- ዕውቅና ካለው ግዙፉ የዲኤችኤል ኩባንያ ጋር በሽርክና ለመሥራት እየተደራደርን ነው፡፡ ጥረታችን ሰምሮ ከዲኤችኤል ጋር በጥምረት የሎጂስቲክስ ኩባንያ ከመሠረትን ኩባንያው በአዲስ አበባ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሚገነቡባቸው ከተሞችና በሌሎች ዋና ዋና የኤክስፖርት ማዕከላት ቅርንጫፎች በመክፈት ለኤክስፖርት ዘርፍ በሎጂስቲክስ አገልግሎት ትልቅ እገዛ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በመጨረሻ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሠራተኞቹ የገነባቸውን ቤቶች በቅርቡ እንደሚያስረክብ ሰምተናል፡፡ ግንባታው ብዙ ዓመታት እንደ ፈጀና የዘገየ ፕሮጀክት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለቤቶቹ ግንባታ ቢነግሩን?

አቶ ተወልደ፡- ከብዙ ጥረትና ድካም በኋላ 1,300 ቤቶች ገንብተን ለሠራተኞቻችን ለማስረከብ በዝግጅት ላይ ነን፡፡ እንደተባለው ፕሮጀክቱ ብዙ ችግሮች ነበሩበት፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የቤቶቹ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ አንድ ሺሕ ሦስት መቶ የሚሆኑ ባልደረቦቻችን በቅርቡ የቤት ባለቤት ይሆናሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚ በቤት ሥራ ማኅበሩ ዓቢይ ኮሚቴ አባል በመሆን ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ዕውቀታቸውን ሰውተው በትዕግሥትና በፅናት ረዥም ጊዜ የሠሩትን የድርጅቱ ሠራተኞች ላመሠግን እወዳለሁ፡፡ በትዕግሥት የጠበቁ የቤት ባለቤቶችንም አመሠግናለሁ፡፡ የተገነቡት ቤቶች ጥራት ያላቸው ቪላና አፓርትመንት ቤቶች ናቸው፡፡ ይህ አንደኛ ዙር ነው፡፡ በጥቅምት ወር ውስጥ ለባለቤቶቹ ለማስረከብ ዝግጅት እየተደረገ ነወ፡፡

ሰፊ ቦታ ያለን በመሆኑ የፕሮጀክቱ ሁለተኛ ክፍል ይጀመራል፡፡ በሁለተኛው ዙር 7000 ደረጃቸውን የጠበቁ አፓርትመንት ቤቶች ይገነባሉ፡፡ የቤት ባለቤት መሆን የሚፈልጉ ሠራተኞች ምዝገባ በቅርቡ እንጀምራለን፡፡ የቤቶች ግንባታ ብቻ ሳይሆን፣ የአካባቢውን መሠረተ ልማት በማልማት ‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ መንደር›› በሚባል ስያሜ ለኑሮ ምቹ መንደር እናደርገዋለን፡፡ እንደሚታወቀው የመኖሪያ ቤት ጉዳይ በተለይ በአዲስ አበባ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ሠራተኞቻችን የተመቻቸ መኖሪያ እንዲኖራቸው እንጥራለን፡፡ ይህም ባለሙያዎቻችንን ከኩባንያው ጋር ለማቆየት ከምናደርገው ዘርፍ ብዙ ጥረት አንዱ አካል ነው፡፡ ለኩባንያ ስኬትም ሆነ ውድቀት ሠራተኛው ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬታማ ሊሆን የቻለው ኩባንያውን የሚወዱ፣ በአግባቡ የሠለጠኑና ታታሪ የሆኑ ሠራተኞች ስላሉት ነው፡፡