Skip to main content
x
ከቱርክ የሚመጡ 78 ኩባንያዎች የሚሳተፉበት የ‹‹አዲስ ቢውልድ›› ዓውደ ርዕይ የ12 አገሮችን ተሳትፎ ይጠብቃል

ከቱርክ የሚመጡ 78 ኩባንያዎች የሚሳተፉበት የ‹‹አዲስ ቢውልድ›› ዓውደ ርዕይ የ12 አገሮችን ተሳትፎ ይጠብቃል

ከ125 በላይ ከአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉበት የሚጠበቀው ስምንተኛው ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ዕቃዎችና የቴክኖሎጂ ዓውደ ርዕይ ከመጪው ዓርብ ጥቅምት 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለአራት ቀናት በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚከናወን ተገለጸ፡፡ በዓውደ ርዕዩ 78 የቱርክ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡

ለአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የዘርፉ ባለሙያዎች  የልምድ ልውውጥ መናኸሪያ ለመፍጠር ከ12 አገሮች ማለትም ከጣልያን፣ ከህንድ፣ ከቤልጂየም፣ ከቻይና፣ ከቱኒዝያ፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ከቡልጋሪያና ከአሜሪካ የሚመጡ ኩባንያዎች በኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽኑ እንደሚሳተፉ የኢቴል አድቨርታይዚንግና ኮሙዩኒኬሽን ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሃይማኖት ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

ከውጭ ተጋባዥ ከሆኑት የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳትፎ በተጓዳኝ፣ የተለያዩ ቴክኖሎጂ ቀመስ የኮንስትራክሽን መሣሪያዎችንና የዲዛይን ሥራዎች ለዕይታ እንደሚቀርቡም ዋና ሥራ አስኪያጅዋ አስረድተዋል፡፡ ከመጪው ዓርብ ጀምሮ ለአራት ቀናት በሚቆየው ዓውደ ርዕይ፣ ዘርፉን የተመለከቱ የውይይት መድረኰች እንደሚያካሄዱም ተጠቅሷል፡፡

በዓውደ ርዕዩ መሳተፍ የሚፈልጉ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች 100 ዶላር በመክፈል ቦታ መግዛት እንደሚችሉ አዘጋጁ አኳል አስታውቋል፡፡ ከ125 ተሳታፊ ኩባንያዎች ውስጥም እስካሁን 23 የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ለመሳተፍ መመዝገባቸውን ወ/ሮ ሃይማኖት ገልጸዋል፡፡

በሰባተኛው አዲስ ቢውልድ ዓውደ ርዕይ፣ ከ4,500 በላይ ጎብኚዎች የተገኙ ሲሆን፣ በዘንድሮው ዓውደ ርዕይ ከ5,000 በላይ ጎብኚዎችን እንደሚጠበቁም አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡