Skip to main content
x

ከፍታና መንጠራራት

ስለመንጠራራት ሳስብ ቃሉ በራሱ ቅኔ ይመስለኛል፡፡ አንድም መንጠራራት ማለት ከእንቅልፋችን ስንነሳ አሊያም በሥራ ሰንደክም እጃችንን ወደ ጎንና ወደ ላይ በመወጠርና በመለጠጥ የምናሳየው እንቅስቃሴ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ መንጠራራት ማለት ወደ ላይ የማይደርሱበትን ቦታ፣ የሆነ ከፍ ያለን ሥፍራ መመኘት ወይም ያላቅሚቲ መፍጨርጨርን የሚገልጽ ይመስለኛል፡፡ በሁለቱም ትርጓሜዎች ብንሄድ አንድ የሚያሳየን ነገር ይኖራል፡፡ እሱም ምንድነው? ከሆነ በፊት ከነበርንበት ነገር የመላቀቅና ወደ አንዳች እረፍትና ዕፎይታ መሄድን ወይም ለመሄድ መመኘትን ያመላክታል፡፡

መንግሥታችን ‹‹መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው›› በማለት የያዝነውን አዲስ ዓመት በአዲስ መሪ ቃል ጀምሯል፡፡ በዚህ መሪ ቃል ላይ የማይገባኝን ነገር አብዝቼ ልጠይቅ ካልኩ ብዙ የምጠይቀው ነገር ይኖራል፡፡ ለምሳሌ መጪው ዘመን ማለት የትኛው ነው? አንድ ዘመን ስንት ዓመት ነው? በቅድሚያ የዓመቱን ዕቅድና መሪ ቃል ማስቀደም ሲኖርብን፣ ለተጠያቂነት የማያጋልጥ ወይም ለመጠየቅ የማይመች ክፍት የሆነ የረዥም ዓመት መሪ ቃል ለምን ተመረጠ . . . ? ኢትዮጵያን እንደ ኢትዮጵያ ጠብቆ ማቆየት የተሳነው መንግሥትስ ጭራሽ መጪው ዘመን በማለት ዘመንን ለሚያህል ሰፊ ዕድሜ በኢትዮጵያ ላይ የመንገሥ ህልሙን እንዴት ለማርዘም ደፈረ . . . ? ሌላውና ዋነኛው ጥያቄዬ ደግሞ ከፍታ ማለት ምንድነው? ምን ዓይነት ከፍታ ነው ከፍ ልንል የወደድነው? በምንድነው ከፍ የምንለው? ወዴትስ ነው ከፍ የምንለው? የሚለው ነው፡፡

በቅድሚያ አንድ ዘመን 100 ዓመት መሆኑ እየታወቀ፣ እንዴት ዛሬ ላይ ቆመን ለመቶ ዓመት የሚፈጸም ቃል እንናገራለን? እንዳልኩት በአዲስ ዓመት መባቻ ላይ የተያዘው ዓመት ዕቅድና አካሄድ ቢነገር የበለጠ ተስማሚና ተቀባይነት ያለው ይመስለኛል፡፡ እናም ደግሞ ግዴታ መናገር ካለብን መጪው ዘመን በማለት ፋንታ፣ መጪው ዓመት በሚል ቢተካ የበለጠ ተጨባጭና ውጤቱን በቅርብ ለማየት የሚያጓጓ ይሆን ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያችን የጋራ የሆነ ማንነትን አንግባ እንደ አገር ለመቆም እየተንገዳገደች ነው፡፡

በአማራ ክልል ያለውን የጎጥና የአውራጃ መቆራረስ ልብ ይሏል፡፡ ወዲህ ደግሞ በስተደቡብ በኦሮሚያና በሶማሌ መካከለው ያለውን የቅርብ ገጠመኝ እናስታውሳለን፡፡ እንደ አገር ትልቅ አንድነትንና ትልቅ ፍቅር መክነን ባለበት ሁኔታ፣ በየት በኩል ነው ተስማምተን ለዘመን ለመቆየት ከፍታ ብለን ለማቀድ የደፈርነው? የፈለግነውን መሪ ቃል በትልቁ ጽፈን ስለለጠፍን በገሃድ መከወን እንችላለንን? መሬት ላይ የሚሆነውንና የሆነውን ልብ ሳንል ቀርተን ነው? ወይስ እንዲያው የምንግዴ ከፍ ትላላችሁ ብያለው ብያለሁ ዓይነት አይጨበጤ ሲሳይ ነው የሚወራው? ጥያቄያችን በጥያቄ ብቻ የሚመለስ እየሆነ ግራ ተጋባን እኮ ጎበዝ!

ቻይና በቅርቡ እ.ኤ.አ. በ2025 ወደ ጨረቃ ለመምጠቅ በዚያም ሰው ለማሥፈር ሁሉ አቅዳለች የሚል ዜና በቅርቡ እንደሰማሁ አስታውሳለሁ፡፡ ተመልከቱልኝ እነሱ ዛሬ እ.ኤ.አ. 2017 ላይ ሆነን ከስምንት ዓመት በኋላ ስለሚያከናውኑት ከፍተኛ ከፍታ ይናገራሉ፡፡ እኛ ግን ወዲህ ምንም እንኳ ከእነ ቻይና ባንወዳደርም ስለ መቶ ዓመት ዕቅድ ያውም በውል ጠርቶ ስላልታወቀ ከፍታ እናወጋለን፡፡ ያሳዝናል፡፡ ከፍታን ስለተመኘነው አይመጣም፡፡ ስላወራነውም አይከሰትም፡፡ ከፍ የማለት ዕቅድና ምኞት አለን? ይህ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ከፍ የምንለው የጠፋብንን ፍቅርና አንድነት ነው ወይ እንዳንል ሕዝብ በየጎጡ እየተከፋፈለ ነው፡፡ ከፍ የምንለው ልማታችንን አዕምሮ ተኮር በማድረግ ነው ወይ እንዳንል አሁንም እየተሠራበት ያለው አሠራርና በሥነ ሥርዓት ታቅዶበት የተዘረጋው ሲስተም የተማረን ሰው በማቅለልና ቁስ አካልን በማግነን ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ከፍ የምንለው ኢኮኖሚያችንን በማሻሻል ነው ወይ እንዳንል አሁን ባለው ልቅ የኢኮኖሚ አስተዳደር ሥርዓት ይኼ ምኞት ‹ላም አለኝ በሰማይ› ነው የሚሆነው፡፡ ለምን ቢባል በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ዛሬም ድረስ መሠረታዊ ፍላጎቱ ሳይመለስ ይባስ ብሎ በረሃብ በሚቆጋበት አገር ላይ፣ አልፈን ተርፈን ስለከፍታ ማውራት ‹በሰው ቁስል እንጨት ስደዱበት› ዓይነት ጭካኔም ያስመስላል፡፡ ከፍ የምንለው ባህልንና ትውፊትን በመጠበቅና በመንከባከብ ነው ወይ እንዳንል ሕዝቡ ላይ ያለው የኢትዮጵያዊነት ስሜት ተሸርሽሮ በመነመነበት በዚህ ወቅት፣ ይህን ለማንሳትና ለመጠበቅ መቅደም ያለበት ያኛውን የመጠገን ጥልቅ የቤት ሥራ ይጠበቅብናል፡፡ ታዲያ በየትና ወዴት ይሆን ከፍ እንላለን የተባለው? በመሠረታዊ ደረጃ ገና የቤት፣ የምግብ፣ የልብስና ልዩ ልዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ሳይፈቱ ዘሎ ስለከፍታ ማውጋቱ አጉል ያላቅሚቲ መፍጨርጨር ወይም መንጠራራት ይመስለኛል፡፡ እናም አሁንም ጥያቄያችን በጥያቄ ነው እየተመለሰ ያለው፣ ምን ተይዞ ነው ከፍ የምንለው?

በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጣሊያን የ “Renaissance” (ህዳሴ) ዘመኗን ስታውጅ፣ እንዲህ እንደኛ በዘፈቀደ ለማለት ያህል አልነበረም ያለችው፡፡ በሁሉም ዘርፍ ሁለንተናዊ ቅንጅቶችን ፈጥራ የተለያዩ የሥራ ዘርፎቿ በሙሉ ከሥር መሠረቱ ህዳሴያቸውን ለማፋጠን የእውነት ስለሠሩ ነው፣ ዛሬ ያ የእውነተኛ ሥራ ለውጥ ተጨባጭ ሆኖ የምናየው . . . በጣም ወደ ኋላ ሳብ ብለን ያየን እንደሆነ ደግሞ እነ ቻይና፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ዛሬ ለደረሱበት ዕድገት መሠረት የጣለ እንዲህ እንደ ወጉ ለወግ ያህል ብቻ ያላሉትን የህልውናቸው መሪ ቃል በአንድ ወቅት ለጥፈው ነበር፡፡ በለጠፉትና ባወጉት ቃል ልክ ከሥሩ ችግራቸውን ነቅሰው በማጥፋት እንዲህ ለውጣቸውን እያየን እየዳሰስን ነው፡፡ ሌሎችም ብዙ ብዙ አገሮች ምኞታቸውን በሥራ ቀይረው ውጤታቸውን ያማረ አድርገው ሠርተውታል፡፡ 

እኛ ‹ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን› ብንል እንኳ ከመመኘት በዘለለ ትልቅነት በየመንደራችን የየዕለት ክንዋኔ በውል ካልታየ በቀር፣ በማውራትና ምኞቱን በመለፈፍ ብቻ ያደገ የተረት አገር በታሪክ አላየንም፡፡ ይህ ደግሞ የፖለቲከኞቻችንን ቁርጠኝነትና ከልብ ለሕዝብ በሕዝብ ያደረ አገር ወዳድነትን ይጠይቃል፡፡ አሁን አገሪቱን የሚመሯት ሰዎች ለዚህ መሥፈርት ይመጥናሉ ወይ? ይኼ ራሱ ሌላ በጥያቄ የሚመለስ ጉዳይ ነው፡፡

ደርግን የሥራ መፈክር ያበዛል እያለ ሲወቅስ የነበረው ታጋይ ዛሬ ላይ እሱ መጥቶ በገሃድ የማንጨብጠውን፣ የማንዳስሰውን የመፈክር መዓት በየጎዳናው፣ በየአደባባዩ፣ በየጋዜጣውና በየቴሌቪዥኑ ቢለጥፍ ‹አታሞ በሰው እጅ ምር ሲይዙት ያደናግር› ከመሆን አያልፍም፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ዕለት ጀምሮ እስካሁን ድረስ የሚያወራውና ሪፖርት የሚያቀርበው ጉዳይ ከገሃዱ የኢትዮጵያ እውነታ ጋር ፈጽሞ ባለመገናኘቱ፣ የመንግሥትን ዜናና ዘገባ ሰው እንደ ውሸት ቋት ከቆጠረው ሰነባብቷል፡፡

እንግዲህ እንዲህ ያለ አየር በሚነፍስበት በዚህ ጊዜ እንዲህ ያለ የከፍታ ወሬ ማውራት አሁንም እንደለመዱት የማይሠሩትን ያውሩ፣ አሊያም ደግሞ ሕዝቡ የሚፈልገው ሌላ እነሱ የሚያወሩት ሌላ ተብሎ መንግሥት ከመታማቱ ውጪ ሌላ በእርግጠኝነት እናገራለሁ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ ኧረ እንዲያውስ ወሬ ባናወራስ? ካልፎከርን አንሠራም እንዴ? አገርን በወሬ ካላደነዘዝን ሥራው አይሠራልንም እንዴ? መንግሥት ዝም ብሎ ሥራውን ቢያከናውን ማን የሚቀየመው መስሎት ነው? ፈረንጆች ሲናገሩ “Action Speaks Louder than Words” ይላሉ፡፡ ተግባር ከቃላት ይበልጣል እንደ ማለት ነው፡፡

በአጠቃላይ እንደ አገር ከፍ ለማለት ስንንጠራራ ከፍ ለማለት የተሰናዳ ኅብረተሰብ በጉያችን መያዛችንን እርግጠኞች መሆን አለብን፡፡ ከፍ የምንልበትን አጀንዳም ከምንመራው ሕዝብ ጋር ተነጋግረን በስምምነት ማፅደቅ መቻል አለብን፡፡ የከፍታችንንም ዲብ ለይተን ማወቅ መቻል አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡ አገራችንን ኢትዮጵያን ፈጣሪያችን ይጠብቅልን እያልኩ ለዛሬው በዚሁ አበቃሁ፡፡

በስንታየሁ ዓለማየሁ

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡