Skip to main content
x

አቶ አባዱላ ገመዳና ወቅቱን ያልጠበቀ ከሥራ የመልቀቅ ውሳኔያቸው

ኦሕዴድ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ የኦሮሞን ሕዝብ በማታገልና በመምራት፣ ለኢትዮጵያ ዕድገት የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ የመጣና እያደረገ ያለ ድርጅት ነው፡፡ ክቡር አቶ አባዱላ ገመዳም ኦሕዴድን ከውልደቱ እስከ ዕድገቱ  የመሩት፣ ያታገሉትና ፈተናዎችን አልፎ እዚህ ደረጃ እንዲደርስ የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡

የክቡር አባዱላ ገመዳ ከሥራ የመልቀቅ ጥያቄ ሲሰማ እጅግ የሚያስደነግጥ፣ በብዙዎቹም ዘንድ ያልተጠበቀና የሚያስገርም ነበር፡፡ አሁን አሁን በአገራችን እየታዩ ያሉ ችግሮች ዋና መንስዔ የኢሕአዴግ የመታገል መንፈስ መዳከምና አመራሩ በግል ሀብት የማበልፀግ (ኪራይ ሰብሳቢነት) አስተሳሰብ መተብተቡ ነው፡፡ የዚህ ኪራይ ሰብሳቢነትና የመበስበስ አደጋ መገለጫ አለው፡፡ አመራሩ በሚከፈለው ደመወዝና በሚያገኘው ሕጋዊ ጥቅማ ጥቅም ብቻ ሊኖረው የሚችል ሀብትና አሁን በተጨባጭ እያፈራው ያለ ሀብት ሲነፃፀር የሰማይና የመሬት ያህል የተራራቀ መሆኑ ነው፡፡

ኢሕአዴግ ራሱ ባመነበት የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ በራሱ በድርጅቱ ውስጥና የድርጅቱ አስኳል በሆነው አመራሩ ውስጥ መከሰቱን በተለያዩ ጊዚያት የገለጸ ሲሆን፣ ይህም ኢሕአዴግ በወቅቱ ችግሩን መፍታት አለመቻሉና ለመታገል ቁርጠኛ አለመሆኑ ችግሩ እንዲባባስ በማድረግ፣ አገራችን አሁን ያለችበት አስቸጋሪና አስፈሪ ሁኔታ ላይ እንድትደርስ አድርጓል፡፡

አሁን አገራችን የተጋረጠባት አደጋ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሥልጣን ናፋቂ የኢሕአዴግ አመራሮች የፈጠሩት ችግር መሆኑን፣ ይህ ችግር ሊቀለበስ የሚችለው ራሱ አመራሩ ሲፀዳና በፅናትና በቁርጠኝነት ሲታገል ብቻ መሆኑን ሊሰመርበት ይገባል፡፡

አገራችን በአንድነት እንደ አገር ለመቀጠል ወሳኝና ፈታኝ ወቅት ውስጥ ባለችበት ጊዜ የክቡር አቶ አባዱላ ገመዳ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባት፣ በግሌ በምንም ሁኔታ ተቀባይነት የሌለውና ከአንድ ታጋይ የማይጠበቅ ተግባር ነው ብዬ አምናለሁኝ፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ አገራችን በተለያዩ ጊዜያት ልዩ ልዩ ፈተናዎች ያጋጠሟት ቢሆንም፣ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወደህ ያጋጠማት ችግር ግን ከወትሮው ለየት ያለ ነው፡፡ በሕዝቦች መካከል መተማመን እንዲጠፋ የሚያደርጉ ኃይሎች በበዙበት ወቅት፣ የክቡር አባዱላ ገመዳ ከሥራ ለመሰናበት ጥያቄ ማቅረብ እጅግ የሚያሳዝንና ምናልባትም ‹ሲቀዘቅዝ በእጅ ሲያቃጥል በማንኪያ› የሚለውን ብሒል የሚያስታውስ ይመስላል፡፡

ይህችን አገር ወደዚህ ሁኔታ የመሯት የበሰበሱ የኢሕአዴግ የውስጥ አመራሮችንና አባላትን ለመለየት በሚሞከርበት ወቅት፣ ‹አይ እኔ እዚህ ላይ ይብቃኝ› ብሎ እንደ አመራርም እንደ አባልም ሆነው የፈጠሯቸውን ችግሮች ሳያስተካክሉ ገለል ለማለት መሞከር ከሥጋዊም ይሁን ከህሊና ተጠያቂነት ሊያስጥል አይችልም፡፡

ክቡር አባዱላ በአቅም ሆነ በልምድ የተሻሉና የትግሉን ታሪካዊ አመጣጥ ሆነ ታሪካዊ ዓላማ ከሥር መሠረቱ በደንብ ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ አገራችን አሁን ካለችበት ማጥ ውስጥ በማውጣት ረገድ የበኩላቸውን ማበርከት በሚችሉበት ጊዜ ራሳቸውን ለማግለል መወሰናቸው ግርታ ፈጥሮብኛል፡፡

ታጋይ ማለት ላመነበት መልካም ዓላማ የሚታገል፣ ተከታዮች ለማፍራት የሚጥር፣ ኢትዮጵያ በአንድነትና በሰላም በዕድገት ጎዳና እንድትመራ የሚሠራና ራሱን መስዋዕት የሚያደርግ ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ታጋይ ማለት ለሕዝብ ጥቅም እንጂ፣ ለግል ጥቅም ያልቆመ ማለት ነው፡፡ ራሱም ሆነ የቅርብ ዘመዶቹ የሚያልፍላቸው አገር ስታድግ ብቻ እንጂ፣ እሱ ሥልጣኑን ተጠቅሞ በሚያጋብሰው ሀብት የሚያልፍለት እንዳልሆነ የሚያምን ማለት ነው፡፡

የታጋይ ትርጉም ይህ ከሆነ ዘንድ ታጋይ አገርና መንግሥት በሚፈተኑበት ወቅት የሚሸሽ፣ በሰላምና በሙገሳ ጊዜ ብቻ የእኔም ድርሻ አለበት እያለ የሚፎክር አይደለም፡፡ ከዚህ አኳያ ክቡር አባዱላ ገመዳ አሁን ፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ በተጀመረበትና በተፋፋመበት ወቅት፣ የመጣ ይምጣ ብሎ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም መቆም አለባቸው፡፡ ከመታገል ይልቅ ‹እኔ ከሞትኩኝ ሰርዶ አይብቀል› እንዳለችው መሆን አያስፈልግም፡፡

በኦሮሚያ ክልል አሁን የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ ሲጠናከር ከውጭም ከውስጥም በተደራጀ መልኩ ኪራይ ሰብሳቢዎች የኦሮሚያ ሕዝብ በማነሳሳትና ወዳልተፈለገ አመፅ እንዲገባ፣ እንዲሁም ከሌሎች ብሔርና ብሔረሰቦች ጋር እንዲጋጭ ማድረግ፣ የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ ቀዝቀዝ ሲል አመፁን እንዲበርድና እንዲቀዛቀዝ የሚያደርግና በሪሞት ኮንትሮል መቆጣጠር የሚያስችል አደረጃጀት በተፈጠረበት ሁኔታ፣ እንዲሁም ዋና ዋና አንኳር ጥያቄዎች ማለትም ይህንን ችግር ማን ፈጠረው? መፍትሔውስ በማን እጅ ላይ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ሳይመለሱ ጓዝ መጠቅለል ምን ያስከተለው ይሆን?

ለማጠቃለል ያህል ክቡር አቶ አባዱላ ገመዳ አገሪቱን በዚህ ፈታኝ ወቅት ቻው ብለው መሄዳቸው ከሞራልም አኳያ ትክክል ነው ብዬ አላስብም፡፡ በመሆኑም እርስዎ ያለዎትን የትግል ልምድ በመጠቀምና በግንባር ቀደምትነት ግለ ሒስ በማካሄድ ለሌሎች ከሥርዎ ያሉትን የኦሮሚያን ሕዝብ አመፅ መደበቂያ ያደረጉ ትልልቅና ትንንሽ ኪራይ ሰብሳቢ የኦሕዴድ አመራሮች አርዓያ በመሆን ትግሉ እንዲሰፋና ኢትዮጵያ ወደ ነበረችበት አንድነትና ሰላም እንድትመለስ የበኩልዎን ይወጡ፡፡

ከኦሕዴድ ውጪ ያሉ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችም ራሳቸውን እንዲፈትሹና ሥር ነቀል የሆነ ግምገማ በማካሄድ፣ አገሪቷ ካለችበት ፈተና ሊታደጓት ይገባል የሚል መልዕክት ማስተላለፍ እወዳለሁ፡፡ ሀቀኞች የኢሕአዴግና የኦሕዴድ አመራሮችስ ቢሆኑ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሉ ይሆን? መሰንበት እንጂ ሁሉንም እንሰማለን፡፡ ከመስማት ባለፈም እናየዋለን፡፡ ለአገራችን ሰላሙን ያብዛልን አሜን!

በአ. ገመቹ

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡