Skip to main content
x
የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ እሑድ ይጠናቀቃል

የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ እሑድ ይጠናቀቃል

  • ከምድብ ጨዋታው 2.2 ሚሊዮን ብር ከትኬት ገቢ ተገኝቷል ተብሏል

ለወትሮው በደጋፊዎች ድርቅ የሚታወቀው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በሁለቱ ተቀናቃኞች የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ኅብረ ዝማሬ ደምቆ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ ዛሬ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጅማ አባ ጅፋር፣ ነገ (ጥቅምት 9 ቀን 2010 ዓ.ም.)   ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በሚያደርጉዋቸው የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ለእሑድ የፍጻሜ ጨዋታ የሚበቁት ቡድኖች ይታወቃሉ፡፡

‹‹አንድ ለእናቱ›› ሆኖ ለዓመታት የዘለቀው የአዲስ አበባ ስታዲየም እንደ አለመታደል ሆኖ በሚያስተናግዳቸው እግር ኳሳዊ ኩነቶች ጥቂት ለማይባሉ ዓመታት የተመልካቾች ድርቅ ነበረበት፡፡ ከዓምና ጀምሮ ግን በተቀናቃኝነታቸው በሚታወቁት የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች አማካይነት በሚደመጡ ኅብረ ዝማሬዎች መናፈቅ ጀምሯል፡፡

የፕሪሚየር ሊጉ የፉክክር መንፈስ እየወረደ ባለበት በዚህ ወቅት የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች የአዲስ አበባ ስታዲየምን ለሚያውቁት ብቻ ሳይሆን ለማያውቁትም ተወዳጅ መሆኑ አልቀረም፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ ተመልካቾች የሁለቱን ክለቦች ቡድኖችን ጨምሮ ሜዳ ውስጥ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተማርከው ሳይሆን ደጋፊዎቹ በየፊናቸው የሚያሰሟቸው ኅብረ ዝማሬዎች ተስበው መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የዝግጅቱ ባለቤት የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንደገለጸው፣ እስከ 2009 ዓ.ም. ድረስ በተደረጉት ውድድሮች ከሜዳ ገቢ የተገኘው ከፍተኛው የገንዘብ መጠን 2.2 ሚሊዮን ብር አካባቢ ነበር፡፡

የከተማው እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዮናስ ሐጎስ እንደሚናገሩት፣ በዘንድሮው ውድድር ፌዴሬሽኑ የግማሽ ፍጻሜውንና የፍጻሜውን ጨዋታ ሳይጨምር እስካሁን ከ2.2 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ከትኬት ብቻ አግኝቷል፡፡