Skip to main content
x
ከመጨፍጨፍ በተጠበቀ 12 ሺሕ ሔክታር መሬት የ5.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ተቻለ

ከመጨፍጨፍ በተጠበቀ 12 ሺሕ ሔክታር መሬት የ5.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ተቻለ

  • በካይ ጋዞችን ለማመቅ ያስቻሉት የባሌ ጥብቅ ደኖች ለሕዝቡ የሚያበረክቱት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ይጠበቃል

በባሌ ጥብቅ ደኖች አማይነት ሲተገበር በቆየው የደን ጭፍጨፋን በማስቀረት የሙቀት አምጪ በካይ ጋዞችን የመቀነስ ትግበራ ውጤት በማስገኘት 12,500 ሔክታር ደን መሬት የሚሸፍን የደን ሀብትን በመጠበቅ 5.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የካርቦን ጋዝ ልቀትን ማስቀረት እንደተቻለ ይፋ ተደረገ፡፡

ፋርም አፍሪካ የእንግሊዙ ተራድኦ ድርጅት ከኦሮሚያ ክልል ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ኢንተርፕራይዝና ከፌደራል መንግሥትና ከሌሎችም አጋሮቹ ጋር በመተባበር ሲተገብር በቆየው ፕሮጀክት አማካይነት ሊጨፈጨፍ ይችላል ተብሎ ይጠበቅ ከነበረው ከ20,300 ሔክታር የደን ሽፋን ውስጥ ከመጨፍጨፍ የዳነው 12,500 ሔክታር ገደማ የደን ሀብት እንደሆነ ተቋሙ አስታውቋል፡፡

በአሳታፊ የደን ልማትና አስተዳደር ፕሮግራም አማካይነት በባሌ ከሚገኙና ከግማሽ ሚሊዮን ሔክታር ከሚሸፍኑ ጥብቅ የደን መሬቶች ውስጥ በፕሮጀክቱ የታቀፈው የደን ሽፋን 360 ሺሕ ሔክታር መሬት እንደሚሸፍን፣ በፋርም አፍሪካ የደንና የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር ኃላፊው ሙሉጌታ ልመንህ (ዶ/ር) ይፋ አድርገዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2012 እስከ 2015 በነበረው ጊዜ ውስጥ በተደረገ ክትትል ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ሲተገበር ከቆየው የበካይ ጋዞች ቅነሳና የደን ጭፍጨፋን የመቀነስ ፕሮጀክት (ሬድ ፕላስ)፣ የተጠቀሰው 12,500 ሔክታር የደን ይዞታ፣ ከ20,300 ሔክታር ገደማ አኳያ ከ62 በመቶ በላይ እንደሚሸፍን አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም በደን ጭፍጨፋ ምክንያት ሊከሰት ይችል የነበረውን የ5.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የካርቦን በካይ ጋዝ ልቀትን በማመቅ ለማስቀረት እንደተቻለም ኃላፊው አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም በካርቦን ንግድ መስክ ኢትዮጵያ ለመሰማራት የሚያስችላት ዕምቅ ክምችት በመፍጠሯ ወደ ዓለም ገበያ ለመግባት መዘጋጀቷም ተጠቅሷል፡፡

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ከሆነ፣ የካርቦን ዕምቅ ክምችት በፈቃደኝነትና በአስገዳጅነት ላይ በተመሠረቱ የገበያ ሥርዓቶች ይመራል፡፡ ሆኖም እስካሁን ያለው የገበያ ሁኔታ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች፣ የበጎ አድራጎት ተቋማት ሌሎችም ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተገናኘ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚፈልጉ አካላት ምርቱን ለመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው ወይም በዓለም ላይ ገበያው እንዳለ መረጋገጡን የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡

የካርቦን ክምችቱ ምን ያህል ዋጋ ሊያወጣ እንደሚችል ለቀረበው ጥያቄ የፎረም አፍሪካ ኃላፊው በሰጡት ማብራሪያ መሠረት አንድ ቶን ከሦስት እስከ አምስት ዶላር ሊያወጣ ወይም ከዚህ ቀደም በነበረ የገበያ ዋጋ መሠረት ከተሰላ ከዚህም በላይ ሊያወጣ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ይሁንና ከሦስት እስከ አምስት ዶላር ባለው ዋጋ መሠረት ይሸጥ ቢባል እንኳ፣ የ5.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በደን አማካይነት የታመቀው ካርቦን፣ ከ17 እስከ 28 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ገቢ ሊያስገኝ እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡   

ደን መንከባከብና መጠበቅ የካርቦን ሽያጭን ለማካሔድ ከማስቻል በላይ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ያብራሩት በሬድ ፕላስ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ብሔራዊ አስተባባሪ ይተብቱ ሞገስ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ባለሙያው በሰጡት ማብራሪያ ደንን በመጠበቅ ብቻ ከፍተኛ የውኃ ምንጭ ማጎልበት እንደሚቻል ጠቅሰዋል፡፡ አገሪቱን በውኃ ሀብት ማበልጸግ ይቻላል ሲሉም ‹‹የኢትዮጵያ ተራሮች የውኃ ማማዎች ናቸው፡፡ ሆኖም በአሁኑ ጊዜ ውኃ መቋጠር የማይችሉ በርሜሎች ሆነዋል፤›› ያሉት ይተብቱ፣ ገበሬዎች ካካበቱት ዕውቀት መካከል ደን ውኃ ይስባል የሚለው አባባላቸው ዓይነተኛ ማሳያ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

ይህ ይባል እንጂ እንደ ሚኒስትሩ ገመዶ ዳሌ (ዶ/ር) አባባል ግን በአገሪቱ የሚገኙ በርካታ ጥብቅ የደን ይዞታዎች፣ በሕገወጥ ሰፋሪዎችና በእርሻ መሬቶች መስፋፋት የተነሳ ችግር ውስጥ እየወደቁ የሚገኙት በመንግሥት አካላት ተሳትፎዎች ጭምር እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ‹‹የመንግሥት አካላት በደን ውስጥ በሕገወጥነት የሰፈሩትን ሕጋዊ በማስመሰል ሲያስተናግዱ እየታዩ ነው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ የሒርና ልዩ የደን ሀብት በዚሁ አኳኋን ለአደጋ መጋለጡን፣ ከደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል የሚደርሳቸው ሪፖርትም ተመሳሳይ ይዘት እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ‹‹በደን መሬት ውስጥ እርሻ መስፋፋት አይችልም፡፡ ሕግ መከበር  አለበት፡፡ ደን ውስጥ መስፈር የድርድር መነሻ መሆን አይችልም፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

በአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ከበደ ይማም በበኩላቸው፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በፓርላማ ሕግ ሆኖ ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ እንዲሁም የሬድ ፕላስ ፕሮጀክት ላለፉት አራት ዓመታት ሲያደርግ የቆየውን የዝግጅት ጊዜ በማጠናቀቅ አሁን ወደ ሙሉ የኢንቨስትመንት ሥራ ለመግባት መሰናዳቱን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ለሥራው የዓለም ባንክ የ18 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የሰጠበት የኦሮሚያ ‹‹ፎርስት ላንድስኬፕ›› የተሰኘው ፕሮጀክት እንዲሁም የኖርዌይ መንግሥት ያበረከተው የ80 ሚሊዮን ዶላር የፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ገንዘብ መሰባሰቡን አስታውቀዋል፡፡

የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ልማት ኢንርፕራይዝ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዲዳ ድሪባ በበኩላቸው ኢንተርፕራይዙ ከተቋቋሙት ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ የደን ጥበቃና ልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ በየዓመቱ የ50 ሚሊዮን ብር በጀት ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የሚያውለው ይህ ኢንተርፕራይዝ፣ ካሉት ከ4,600 በላይ ሠራተኞች ግማሹ ለደን ጥበቃ ሥራ እንደተመደቡ አስታውቀዋል፡፡ ይሁንና በሕገወጦች መስፋፋት፣ በእርሻ መሬት መስፋፋትና በእሳት ቃጠሎ ሳቢያ ችግሮች የተጋረጡበት የደንና የዱር እንስሳት ልማት ኢንተርፕራይዙ፣ ከተገኘው የደን ሀብት ጥበቃና ክብካቤ ባሻገር ሕዝቡ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እየተጠባበቀ እንደሚገኝ አስታውሰዋል፡፡ ከካርቦን ሽያጭ ከሚገኘው ገንዘብ ውስጥ የመንግሥት ድርሻ 20 በመቶ ሲሆን፣ የሕዝብ በተለይም የኅብረት ሥራ ማኅበራት ድርሻ 80 በመቶ እንደሚሆን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ምንም እንኳ በደን ክብካቤና ጥበቃ ሥራ ውጤታማነት ታይቷል ቢባልም፣ ከፍተኛ ጭፍጨፋ እንደሚካሔድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በየዓመቱ ከ20 ሔክታር መሬት በላይ የደን መሬት እንደሚመነጠር ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ይህም በየዓመቱ የሚተከለው ችግኝ ይተካዋል ተብሎ ከሚታሰበው ባሻገር ነው፡፡