Skip to main content
x
የፓዌ እርሻዎችን ያጥለቀለቀው  ‹‹የአህያ አብሽ››

የፓዌ እርሻዎችን ያጥለቀለቀው ‹‹የአህያ አብሽ››

የፓዌ እርሻዎችን ያጥለቀለቀው

‹‹የአህያ አብሽ››

የ57 ዓመቱ አቶ ሁሴን አህመድ አርሶና አርብቶ አደር ናቸው፡፡ ባላቸው አራት ሔክታር መሬት ላይ ሩዝ፣ በቆሎ፣ አኩሪ አተርና ለውዝ ያመርታሉ፡፡ ወደ 20 የሚሆኑ ከብቶችም አሏቸው፡፡ ግብርናውን ከሚፈታተኑ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መካከል የሆነው አረም እንደ አቶ ሁሴን ላሉ አርሶ አደሮች ትልቅ ፈተና ሆኗል፡፡ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ ህልውናቸውን አደጋ ላይ የመጣል ሥጋት ውስጥ ከቷቸዋል፡፡  ለእርሻውም ለከብት ዕርባታውም ፈተና ሆኗል፡፡

አቶ ሁሴን በማሳቸው ከሚያለሟቸው ሰብሎች መካከል የሆነው፣ ሩዝ በከፍተኛ ሁኔታ በአረም የሚጠቃ ሰብል ነው፡፡ በወቅቱ ካልታረመ በምርታማነቱ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ እንደቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ስለዚህም በተወሰኑ ጊዜያት ከሦስት እስከ አራት ጊዜያት ያህል መታረም አለበት፡፡ የመጀመርያው እርምት ሰብሉ በበቀለ ከ15 እስከ 20 ቀናት ውስጥ የሚደረግ ነው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ሰብሉ ከበቀለ ከ30 እስከ 35 ቀናት ውስጥ ይደረጋል፡፡ ሌላው ሰብሉ ከበቀለ ከ45 እስከ 50  ባሉት ቀናት የሚደረገው ሲሆን፣ ከዚያ በላይ ያለው እንደየ አስፈላጊነቱ የሚደረግ ነው፡፡

‹‹አቀንጭራ የሚባል ሩዝና በቆሎ የሚያጠፋ አረም አለ፤›› የሚሉት አቶ ሁሴን፣ አደገኛ ከሚባሉት የተለያዩ የአረም ዝርያዎች አቀንጭራ የሚባለው በአካባቢው ለሚገኙ አርሶ አደሮች ፈተና እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ ደግሞ ሌላ አደገኛ የሆነ አረም በቅርቡ ተከስቶ ግራ አጋብቷቸዋል፡፡ አረሙ አብሽ ስለሚመስል ‹‹የአህያ አብሽ›› ብለውታል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ በፓዌ ወረዳ በሚገኙ ማሳዎች የተሠራጨው ይህ አረም ከአቀንጭራ የበለጠ ጉዳት እንደሚያስከትል የአካባቢው አርሶ አደሮች ይናገራሉ፡፡

አረሙን አደገኛ የሚያደርገው በአጭር ጊዜ ውስጥ በሰፊ ቦታ ላይ መሠራጨት መቻሉ እንዲሁም በተስፋፋበት ቦታ ሌሎች ሰብሎች እንዳይበቅሉ ማገዱ ነው፡፡ ይህንንም በአካባቢው ተገኝተን ያረጋገጥነው ጉዳይ ነው፡፡ ከተከሰተ ገና አጭር ጊዜ ቢሆንም በቀላሉ መዛመት ችሏል፡፡ በዚህ አረም የተያዘ ቦታም ሌላ ዓይነት ሰብል ቀርቶ ሌላ አረም አይታይበትም፡፡ ከአብዛኛዎቹ ማሳዎች መሳ ለመሳ ሆኖ መጣሁ ደረስኩባችሁ እያላቸው ነው፡፡

‹‹ካልጠፋ ሙሉ ለሙሉ ሰብሎቹን ያጠፋል፡፡ ሊያጠፋው የሚችል መድኃኒት ቢዘጋጅልን ጥሩ ነው፤›› ይላሉ ከማሳቸው በቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ የሚያስፈራራቸውን ይኼን አደገኛ አረም የፈጠረባቸውን ስሜት ሲገልጹ፡፡ ይህ አደገኛ አረም ማሳውን እንዳልነበር አድርጎ ድምጥማጡን እንዳያጠፋ በእጅ ከማረም ውጪ የሚከላከሉበት ሌላ የተሻለ ዘዴ የላቸውም፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ብቻቸውን የማይታሰብ ነው፡፡ ስለዚህም ለአንድ ሔክታር 2,000 ብር ከፍለው ለማሳረም ተገደዋል፡፡

በዚህ መልኩ ወደ ማሳቸው ገብቶ ጉዳት ከማድረስ ቢገቱትም የማሳቸው አካል ያልሆነው የከብቶች የግጦሽ ቦታ ግን ሙሉ ለሙሉ በአረሙ ተሸፍኗል፡፡ ‹‹ከብቶች የሚሰማሩበት የግጦሽ መሬት በአብዛኛው በአረሙ ተውጧል፡፡ የከብቶች መኖ ሳይቀር ነው የሚፈጀው፡፡ በዚህ ከቀጠልን ወደፊት እንኳንስ ከብት ለማርባት አርሶ ለማደርም ከባድ ነው፤›› በማለት አቶ ሁሴን ሁኔታውን ይገልጻሉ፡፡

ከእርሻው ባልተናነሰ መጠን ከከብቶቻቸው የሚያገኙት ጥቅም በዚህ ክፉ አረም እንዳይቋረጥ ከሩዝና ከሌሎች ሰብሎች የሚገኙ ተረፈ ምርቶችን ለከብቶቻቸው እየመገቡ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ጥያቄው እስከ መቼ እንደዚህ መቀጠል ይቻላል የሚለው ነው፡፡

በአገሪቱ ግብርና ከተጋረጡ ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች መካከል አረም አንደኛው ነው፡፡ የማይናቅ መጠን ያለው ምርት በአረም ምክንያት ይባክናል፡፡ የተለያየ ዓይነት የፀረ አረም ኬሚካሎች ጥቅም ላይ ቢውሉም፣ በየጊዜው አዳዲስ የአረም ዓይነቶች እየተከሰቱ አዝጋሚ ዕድገት ያለውን የአገሪቱ ግብርና ወደ ታች ይኮረኩሙታል፡፡ እንደ ‹‹የአህያ አብሽ›› ያሉት አረሞች ደግሞ ፈጣንና አስደንጋጭ በሆነ መልኩ የግብርናውን ምርታማነትና የምግብ ዋስትና ሥጋት ውስጥ ይከታሉ፡፡ ለዚህም በፓዌ ወረዳ የተከሰተው የመጤ አረም ወረርሽኝ ዋነኛ ማሳያ ይሆናል፡፡

በፓዌ ወረዳ 12 ሺሕ አርሶ አደሮች ይገኛሉ፡፡ በብዛት የመኸር ሰብሎችን ያለማሉ፡፡ ዳጉሳ፣ በቆሎ፣ አኩሪ አተር፣ ማሽላ፣ ሰሊጥና የመሳሰሉት በወረዳው የሚመረቱ ዋና ዋና ሰብሎች ናቸው፡፡ የፓዌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሉጌታ ዓባይ እንደሚሉት፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ማለትም በ2008 ዓ.ም እና 2009 ዓ.ም. የበጀት ዓመት ከ640 ሺሕ ኩንታል በላይ የተለያዩ ምርቶች ተሰብስቧል፡፡ ምርታማነቱም በሔክታር በአማካይ 25.5 ኩንታል ሲሆን፣ ለመሰብሰብ ታቅዶ የነበረው ግን በሔክታር 30 ኩንታል ነበር፡፡ በዘንድሮ በጀት ዓመትም 930 ሺሕ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል፡፡

ይህንን ከግብ ለማድረስ ግን የተለያዩ ችግሮች ተጋርጠውባቸዋል፡፡ ‹‹የተለያዩ የሰብል ችግሮች አሉ፤›› የሚሉት አቶ ሙሉጌታ በቅርቡ የወረዳው ዋነኛ ሰብል በሆነው በዳጉሳ ላይ በሽታ ተከስቶ በምርታማነቱ ላይ ተፅዕኖ እንደ ፈጠረ ያስታውሳሉ፡፡ በሽታውን ለማጥፋት የሚረዳ መፍትሔ ባይገኝለትም ምርምር እየተደረገ ይገኛል፡፡ ስለዚህም የዳጉሳ ምርታማነት በበሽታው አደጋ ውስጥ ስለወደቀ በወረዳው የሚገኙ አርሶ አደሮች ዳጉሳ ማምረታቸውን ወደ ጎን ብለው ፊታቸውን ወደ በቆሎና አኩሪ አተር ምርት ማዞራቸውን አስተዳዳሪው ይናገራሉ፡፡

ሌላው ለወረዳው አርሶ አደሮች ትልቅ ችግር የሆኑት መጤ አረሞች ናቸው፡፡ የወፍ ቆሎ፣ ሁሉ ዘመዴና በሳይንሳዊ ስሙ ፓርትኔም የሚባለው ‹‹የአህያ አብሽ›› የተባለው አረም ነው፡፡ ‹‹ይህ በጣም አደገኛ አረም ነው፡፡ የግጦሽ መሬት ሁሉ እያሳጣ ነው፡፡ አብዛኞቹ የግጦሽ ቦታዎች በአረሙ እየተሸፈኑ ነው፡፡ ከብቶች የሚመገቡት ዓይነት እንኳን አይደለም፤›› በማለት ከእርሻ ማሳዎች ባሻገር በግጦሽ መሬቶች ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን አቶ ሙሉጌታ ይገራሉ፡፡

በወረዳው 20 ቀበሌዎች ሲኖሩ፣ በእያንዳንዱ ቀበሌዎችም በአማካይ 4,000 ከብቶች ይገኛሉ፡፡ የግጦሽ መሬት በዚህ መልኩ እየጠፋ በመጣ ቁጥር ከብቶችን ማርባት የማይታሰብ ይሆናል፡፡ ‹‹በወረዳው ከፍተኛ የመሬት ጥበትም አለ፡፡ ስለዚህ በቂ የግጦሽ መሬት ማግኘት ይከብዳል፡፡ እየቆየ ሲሄድ ደግሞ ከዚህ የበለጠ ይጠባል፡፡ ስለዚህም አጋጣሚው ዘመናዊ የከብት ዕርባታ ዘዴ መጠቀምን እንደ አማራጭ እንዲታይ የጥሪ ደወል ይሆናል፤›› በማለት ከብቶችን ለማርባት አማራጮችን መከተል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የፓዌ ወረዳ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙ 20 ወረዳዎች መካከል ስትሆን፣ በምሥራቅና ከፊል ሰሜናዊ ምሥራቅ የአማራ ክልል ጃዊ ወረዳ፣ በምዕራብና ከፊል ደቡባዊ ምዕራብ የዳንጉር ወረዳና የማንዱራ ወረዳዎች ያዋስኗታል፡፡ 1,050 ሜትር ከባህር ጠለል ከፍ ብላ ትገኛለች፡፡ ቆላማ የአየር ንብረት ያላት ሲሆን፣ አማካይ የዝናብ መጠኗም 1,150 ሚሊ ሜትር ይደርሳል፡፡ የሙቀት መጠኗም ከ28 እስከ 43 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ነው፡፡

አጠቃላይ የቆዳ ስፋቷ 643 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ነው፡፡ 27,101 ሔክታሩ በእርሻ፣ 11,000 በደን፣ 7,748 ለግጦሽ የዋለ ነው፡፡ 18,451 ደግሞ ምንም ዓይነት አገልግሎት ላይ ያልዋለ ነው፡፡ ፓዌ ለመስኖ ልማት የሚውሉ 16 ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች ባለቤት ነች፡፡ ግልገል በለስ፣ አባት በለስ፣ ቻንኩር፣ አሊስፕሪንግ፣ ጥቁር ውኃ፣ ሚድሚዳ የተባሉት ዋና ዋናዎቹ ወንዞች ናቸው፡፡ 1023.668 ሔክታር መሬትም በመስኖ ይለማል፡፡

ከአዲስ አበባ 588 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኘው ፓዌ እንደ ሙቀቷ ደረቅ ሳትሆን ለምለም የምትባል ነች፡፡ ለዚህም ይመስላል የማይፈለግ አረም ሁሉ ተመችቶት መሬቷን የሙጥኝ የሚለው፡፡ ዘንድሮ 900 ሺሕ ኩንታል ምርት ለማግኘት ወገቧን አስራ ደፋ ቀና እያለች ቢሆንም፣ ‹‹የአህያ አብሽ› ሥጋት ሆኖባታል፡፡