Skip to main content
x

እነሆ ሦስት መድኃኒት ለኢሕአዴግ

አገራችን በአሁኑ ጊዜ ያለችበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ብዙ ሰዎች ብዙ ብለውበታል፡፡ አንዳንዶች ‹‹አጣብቂኝ ውስጥ ያለች አገር›› ሲሏት፣ ሌሎች ደግሞ ‹‹መስቀለኛ መንገድ ላይ የቆመች አገር›› ይሏታል፡፡ ‹‹ነፋስ የሚያንገላታት መርከብ››፣ ‹‹ገደል አፋፍ ላይ የቆመች›› የሚሉትና ሌሎች አስተያየቶችም ለዚችው ጥንታዊቷ አገር የገባችውን ሥጋት የሚገልጹበት ቋንቋ ነው፡፡

እነዚህን ሁሉ አስፈሪ ግምቶች ሊያስተካልና ሊያርም የሚችለው ዋንኛው ባለድርሻ የኢሕአዴግ መንግሥት ነው፡፡ ለዚህም ቁርጠኝነት፣ ድፍረትና ቅንነት ያስፈልጉታል፡፡ ኢትዮጵያ በአንድነት፣ በፍቅር፣ በእኩልነት፣ በሰላም ጠንካራ አገር ሆና በልማትና በዕድገት ጎዳና ብትቀጥል፣ አትራፊው ከማንም በላይ ኢሕአደግ ነው፡፡ ስለዚህ የዚህ አገራዊ ትርፍና ጥቅም ባለታሪክ ለመሆን ምን ያዳግተዋል? ለምንስ ያመነታል? እንዴትስ ድፍረት አጣ? የሚሉ ሞጋች ጥያቄዎችን የማነሳው አሁንም ቁርጠኝነትና ቅንነት ይኖረዋል በማለት ነው፡፡ በመሆኑም የእኔን የአንድ ተራ ዜጋ ሦስት ዋና ዋና ምክሮች በአስቸኳይ ሳይውል ሳያድር ተግባራዊ እንዲያደርግ በማክበር አጠይቃለሁ፡፡

 ኢትዮጵያ እንደተተነበየው ወደ ከፍታ ማማዋ ለመውጣትና ለማምራት የሚያስችሏትን ፅኑ መሠረት አሁን ላይ መገንባት ከፈለገች ያለምንም ማንገራገር በቅድሚያ ልጆቿ መታረቅ፣ መስማማት፣ መደማመጥና መከባበር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይኼ የሚታይ ጥሬ ሀቅ ነው፡፡ በቅርቡ አዲሱ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት እንደተናገሩት፣ ትግሬም የእኔ ነው፣ አማራም የእኔ ነው፣ አፋርም ሶማሌም የእኔ ነው ቤንሻንጉልም ደቡብም የእኔ ነው፡፡ የእኛ ነው፡፡ ሁላችንም አንድ ነን የሚለውን አባባላቸውን በትህትና መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ድንቅ አባባል በመሆኑ ልናከብራቸውና ልናጨበጭብላቸው ይገባል፡፡ አቶ ለማ መገርሳን ያመጣውና ያፈራው ኦሕዴድ ኢሕአዴግ ነው፡፡ እውነትም ከላይ ከፈጣሪ የተላኩ አዳኝ ይሆኑ እንዴ? ለማለት ያስደፍራል፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ እንደነዚህ ዓይነት ወጣት ባለራዕይ መሪዎች እንዲያበዛለት እፀልያለሁ፡፡ ብቻ  እነአቶ ዓለማየሁ አቶምሳን የበላቸው ‹‹ቡዳ›› እኝህንም ግለሰብ እንዳያይብን ነው ምኞቼ፡፡ ይኼን ካልኩ ዘንዳ፣ ለኢሕአደግ ወደማቀርባቸው ምክሮች ላምራ፡፡ ሦስቱ ዋና ዋና ምክሮቼን ያለማመንታት ኢሕአዴግ ተግባራዊ ካደረጋቸው ለሚቀጥሉት ሃያና ሰላሣ ዓመታት ኰሽ ሳይልበት በሥልጣን ላይ የሚቆይበትን መንገድ ጠረገ ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ በየዋህነት ያደምጠኛል ብዬ በማመን የሚከተሉትን እናገራለሁ፡፡

 ምክረ ሐሳብ አንድ ወይም የመጀመርያው መድኃኒት የታሠሩ ፖለቲከኞችን እና ጋዜጠኞችን በድፍረትና በፍጥነት ሳይውል ሳያድር ይፍታ፡፡ በዚህ ቁርጠኛ ውሳኔ ኢሕአዴግ ሁለት ነገሮች ያተርፋል፡፡ አንደኛ የሕዝብ አመኔታንና ይቅርባይነትን ይጎናጸፋል፡፡ በዚህ የሚያገኘው ድል ደግሞ ኢትዮጵያን ከፍ ከማድረጉም በላይ መልካምና ቀናነት ያለው መንግሥት ስላለን ዕድሜውን ያርዝመው እንድንል ይጋብዘናል፡፡ ሁለተኛው የኢሕአዴግ ትርፍ ለታሳሪ ሰዎች የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስና ፖለቲካዊ ጫጫታዎችን ለማስወገድ ስለሚረዳ፣ ሁላችንም እፎይ እንላለን፡፡

ስለዚህ የፖለቲካ እስረኞችንና ጋዜጠኞችን በአስቸኳይ መፍታት መንግሥትን አሸናፊ ከማድረጉም በላይ ለሚቀጥሉት ዓመታት በመንግሥትነት ቢቀጥል እንኳ ጉልህ ተቃውሞም ሆነ ያለመመረጥ ችግር አይገጥመውም ብዬ አምናለሁ፡፡ የአገራችንን ትኩሳትም ቀዝቃዝ ያደርጋል ብዬ እገምታለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ከፍታም የሚጀመረው ከዚህ ዓይነቱ ዕርምጃ ነው፡፡ ሁለተኛው ልመናዬ ወይም ምክሬ የዴሞክራሲ መብቶችን ማክበር ማስከበር፣ ነፃ ፕሬስን ማስፋፋትና ማሳደግ ለኢሕአዴግ የሚቀርብ ግዴታና ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ስለሆነ፣ ይኼንንም በትክክልና በሕግ ተፈጻሚ ካደረገ ኢሕአዴግን ያስመሰግነዋል፡፡ በርታ ግፋበት ይባላል እንጂ ቅሬታን አያስነሳም፡፡

ያለፉትን  የኢሕአደግ ጥፋቶች ሁሉ ትተን የቅርብ ጉዳይ ብናነሳ፣ ቀላልና አትራፊ የሆኑ የፖለቲካ ጨዋታዎችን ኢሕአዴግ ለምን እንደማይወጣቸው ይደንቃል፡፡ እስቲ በእኔ ሞት ቴዲ አፍሮ ያወጣውን የሙዚቃ አልበም ማስመረቅ አትችልም ብሎ የታጠቁ ወታደሮችን በሒልተን ሆቴል ግቢ ውስጥ አሰማርቶ መከልከል ምን የሚሉት የቂል ፖለቲካ ነው? ታዲያ ከአፋኙ የደርግ ሥርዓት በምን ተሻለ?

ልጁ አልበሙን ለእያንዳንዱ ዜጋ በሠልፍ የሸጠ፣ ከዳር እስከዳር ተቀባይነትነና ተወዳጅነትን ያገኘ ሆኖ ሳለ፣ እደግ ተመንደግ ክፉ አይንካህ ከሚለው ብዙኃኑ ሕዝብ፣ በተለይ ወጣቱ ብዛቱ እልፍ ሆኖ ሳለ ኢሕአዴግ ግን ማስመረቅ አትችልም ብሎ በወታደር ኃይል አንድ ትልቅ ያውም የውጭ ዜጎች መናኸሪያ የሆነ አንጋፋ ሆቴልን መክበብ፣ ማስፈራራትና ማዋከብ ትልቅ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከመሆኑም በላይ ኮንሰርት ማዘጋጀት ልዩ ፈቃድ የሚያስፈልገው ሆኖ ነው ወይስ ለቴዲ አፍሮ ብቻ የወጣ ውስጣዊ ሕግ ይኖር ይሆን? ያሰኘ አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡

ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱን በጣም ቀላል ስህተት ኢሕአዴግ ፈጽመህ አትድገመው አደጋ እላለሁ፡፡ በቅርቡ ሰማያዊ ፓርቲ የጠራው ሰላማዊ ሠልፍ መከልከሉም ያሳዝናል፡፡  ይኼም ቢሆን እንደ ደርግ አክሳሪ የፖለቲካ ስልት ይሆናል እንጂ በምንም ዓይነት መለኪያ የዴሞክራሲ መብቶችን ያውም በሕገመንግሥት የፀደቁትን መከልከልና  መገደብ፣ አትራፊና አሸናፊ አያደርግም፡፡ ያለፈውን ሁሉ እንተውና ኢሕአዴግ ሆይ ለሕገ መንግሥት ዘብ በመቆም አዲስ ታሪክ ለመሥራት በአስቸኳይ ተዘጋጅ እላለሁ፡፡ ለሚቀጥሉት ሃያና ሠላሳ ዓመታት በሥልጣን ለመቆየት ይኼ ትልቅና አዋጭ ዘዴ ነው፡፡ ይህንን ምክር በድፍረትና በቅንነት ከተቀበለ፣ ኢሕአደግ ያለጥርጥር አሸናፊ ይሆናል እላለሁ፡፡ በዚህም ኢትዮጵያን እፎይ እንላለን፡፡ ሦስተኛው ምክር ሐሳብ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በውጭ ያሉትንም ጨምሮ፣ የሲቪክ ተቋማትንና የሙያ ማኅበራትን ማበረታታት፣ ጽሕፈት ቤቶቻቸውን በፈለጉበት ቦታና አካባቢ እንዲከፍቱና አባላትን በነፃነት እንዲቀላቀሉ ማበረታታት፣ የፋይናንስ ድጎማ ማድረግ ኅብረ ብሔራዊ የፖለቲካ ፓርቲ እንዲሆኑ መጣር፣ መደገፍ፣ ምርጫ ቦርድን ገለልተኛ ማድረግ፤ ስለኢትዮጵያዊነትና አንድነት መስበክ ይገባዋል እላለሁ፡፡

ኢትዮጵያን ካስቀደመ ያለ ጥርጥር ራሱ ኢሕአዴግም ወደ አንድ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ ተሸጋግሮ ሌሎችንም አሸጋግሮ መንገዱን ቢሳይ፣ ኢሕአዴግ ተከባሪና ተወዳጅ ይሆናል፡፡ ካስፈለገም የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 39 እና ሌሎችንም ቢያሻሽል ያስከብረዋል፡፡ የአንድ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ምሰሶዎች እነኚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ሦስቱ ዋነኛ ጉዳዮች በመሆናቸው፣ ኢሕአደግ ሆይ ምሰሶዎቹን በቅንነትና በይቅርባይነት ዛሬ መትከል ከጀመርክ ምሰሶዎቹ ላይ ቋሚ፣ ዘላቂ፣ የማይነቀንቅ ቤት የምትሠራው አንተው ራስህ ትሆናለህ እላለሁ፡፡ ካልሆነ ግን መንገዱም፣ ግዱቡም፣ ኢንዱስትሪውም ቢስፋፋ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች፣ ነፃ ፕሬስና ሌሎችም ዘላቂነት ላይኖራቸው ይችላል ብሎ ማሰብ ደግ ነው፡፡ ይህች ኢትዮጵያ ትፈርስብህና ኢሕአዴግ ሆይ የታሪክ ተወቃሽም ተጠያቂም ከመሆን በፊት አንተም እኛም ከማለቅ፣ ዓለም ዳግማዊት ሶሪያን በአፍሪካ እንዳያይ አደራ ኃላፊነትህን ተወጣ እላለሁ፡፡

(ተክልዬ ጀማነህ፣ ከአዲስ አበባ)