Skip to main content
x

የነባር አመራሮች መልቀቅ ለምን ያስደነግጠናል?

በገነት ዓለሙ

የአምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የእስካሁኑ የሁለት ዓመት የሥራ ዘመን አገርን ጤና የነሱ ችግሮች፣ ተቃውሞዎችና ግጭቶት ታይተው በማይታወቁበት ዓይነትና ግዝፈት የተመዘገቡበት ወቅት ነበር፡፡ የ2007 ምርጫ ያቋቋመው አምስተኛው ምክር ቤት የጀመረውም በአፈ ጉባዔው የመሰናበቻና ሥራ የመልቀቅ ልዩ ልዩ ትርጉም ሥጋትና ግንዛቤ ባገኘ ዜና ታጅቦ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የፌዴራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው ይላል፡፡ ይህ ሕገ መንግሥቱ የሚለው ነው፡፡ በዚህ መሠረት ፓርላማው (ፓርላማ ማለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው) ከፍተኛው የሥልጣን አካል ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 8 መሠረት ደግሞ ፓርላማው ከሕገ መንግሥቱ በታች የሕዝቦች የሉዓላዊነት ሥልጣን መገለጫ ነው፡፡ ስለዚህም አፈ ጉባዔው የፓርላማውም፣ በፓርላማው ውስጥም ከማንኛውም ሰው የበለጠ ከፍተኛ የሕግ ኃይልና ሥልጣን ያለው ሹምና ተመራጭ ነው፡፡ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ እሱ ነው፡፡ ምክር ቤቱን በበላይነት የሚመራውና የሚያስተዳድረውም አፈ ጉባዔው ነው፡፡ ስብሰባውን የሚመራው፣ የምክር ቤት አባላትን የፓርላማ ስብሰባ ውስጥ ንግግር የሚፈቅደውና የሚወስነው፣ ሥነ ሥርዓት የሚያስከብረው እሱ ነው፡፡ በተለይ በዚህ ዘርፍ አፈ ጉባዔው ሥነ ሥርዓት የሚያስከብርበትና ውሳኔውንም የሚያስፈጽምበት ‹‹አስፈላጊው ሥልጣን›› ሁሉ አለው፡፡ ንግግር ያስቆማል፣ ‹‹የዕርምት ማሳሰቢያ ይሰጣል››፣ የተሰጠውን ማሳሰቢያ የማያከብር አባል ወይም እንደራሴ ከስብሰባ ያስወጣል፡፡ ለዚህም ተጠሪነቱ ለእሱ ለራሱ የሆነውን የምክር ቤቱን የክብር ጥበቃ ኃይል (Sergeant-at Arms) ያዛል፡፡

በአጠቃላይ አፈ ጉባዔው የሥነ ሥርዓት ችግር ቢፈጠር፣ ‹‹የተፈጠረው የሥነ ሥርዓት ችግር አጠቃላይ የዕለቱን የስብሰባ ሒደት በጎላ መልኩ የሚያውክ፣ ወይም በአባላት መካከል ጠብ ሊያስከትል የሚችል ወይም የፀጥታ መደፍረስ ሊፈጠር ይችላል ብሎ ከገመተ፣ ወይም የፀጥታ መደፍረስ የተፈጠረ እንደሆነ ስብሰባውን ሊያቋርጥ››፣ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የምክር ቤቱ የጥበቃ ኃይል ጣልቃ ገብቶ ችግሩን እንዲያስወግድ ሊያዝ የሚያስችል ሥልጣን ያለው ባለሥልጣን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ ላይ የሚፈጠር የሕግ ክፍተት የምክር ቤቱን የራሱን ልምዶች የዓለም አቀፍ የፓርላማ መርሆዎችና ልምዶች፣ እንዲሁም የአገሪቱ ሌሎች ሕጎችን በማጣጣም ወይም እንደ ጉዳዩ ክብደት ሕግ በማውጣት ሊሞላ ይችላል ተብሎ ስለተደነገገ፣ አፈ ጉባዔው በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ በስብሰባ ወቅት ለሚነሱ የትርጉም ጥያቄዎች ውሳኔ የመስጠት ወይም ለሚመለከተው አካል የመምራት ሥልጣን ያለው ‹‹ሕግ ተርጓሚ›› ጭምር ነው፡፡

ከዚህ በላይ እንደተገለጸው ፓርላማው የአገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል ነው፡፡ አፈ ጉባዔውም የፓርላማው አቻ የሌለው ከፍተኛ ባለሥልጣን ነው፡፡ ይህ ግን እንደ ሕጉና እንደ ሕገ መንግሥቱ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ አለመታደል ሆኖ ግን (የአለመታደሉ ብቸኛ ምክንያት ደግሞ ከየትኛውም ወገን ቡድን ወይም ፓርቲ ጋር ያልተጣበቀ ለማንም የማያዘነብል ዓውደ መንግሥት መመሥረት አለመቻላችን ነው) ሕጉና ሕገ መንግሥቱ ወዲያ፣ ቅዝምዝም ወዲህ ናቸው፡፡

በዚህ ምክንያት ጉዳታችንና ችግራችን ብዙና ሁሉ አቀፋዊ ነው፡፡ የአገር ምድሩ ሁሉ የበላይ የሥልጣን አካል የሆነውን የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምርጫ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ከመሆን ከሁሉ አስቀድሞ የሚከለክለው፣ በምርጫው ውስጥ ማጭበርበር ሳይሆን ከዚያ በፊትና ማጭበርበርም ሳያስፈልግ ምርጫና የሕዝብ ፍላጎት ያለመገጣጠም ፍጥርጥር ችግር ነው፡፡ ምርጫ በኢትዮጵያ ውስጥ በፍጥርጥሩ የኑሮ ግዴታን፣ የህልውና ግዳጅን፣ የመንግሥትን ፍላጎት የማሟላት ጉዳይ ሆኖ ተቋቁሟል፡፡ የኢሕአዴግ ድርጅቶች አባል መሆንና የሌሎች ፓርቲዎች አባል መሆን ልዩነት ጉዳዩን አሳምሮ ያሳየዋል፡፡ ከገዢው ፓርቲ አንፃር በፓርቲው አቋምና ፖሊሲ ማመንና የእንጀራ ገመድ ነገር ተለያይተው እንኳን ለተመልማዮቹ ለመልማዮቹ ያልተሰወረ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በመንግሥትና በፓርቲ ተግባራትና እንቅስቃሴዎች መካከል ለዕይታና ለማስመሰል ወግ ያህል እንኳን ልዩነት ማበጀት አቅቶ፣ ይኸው በየዕለቱ ዜናዎች ፓርቲና መንግሥት እንዴት እንዴት እያደረጉና እየሆኑ ልብስ እንደሚጋፈፉ ያለተጠያቂነት እየመሰከርን ነው፡፡

የአንዱን ወይም የሌላውን ተቃዋሚ ፓርቲ የቤት ውስጥ ስብሰባ ሆቴሎች ጭምር በተጠንቀቅ ቆመው በሚከላከሉበት፣ ለፓርቲ ቤት ማከራየት፣ መዋጮ መስጠት፣ ጋዜጣቸውን ማተምና ማንበብ አደገኛ በሆነበት አገር፣ የአገር ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን አካላት የሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች፣ የክልል የምክር ቤት፣ የቀበሌ (የወረዳ) መስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች የደኢሕዴንን የልደት በዓል ሥራዬ ብለውና ሥራ ፈትተው ከላይ እስከ ታች ሲያከብሩ እናያለን፡፡

ኢሕአዴግ አመለካከቴን፣ አቋሜንና ፖሊሲዬን፣ እንዲሁም ድርጅቴን የሚቀናቀን ሁሉ ጠላትና አፍራሽ ነው በሚል አስተሳሰቡና ተግባሩ መንግሥትንና ኅብረተሰቡን እንደ ‹‹ሕግ›› እና ከሕግ በላይ ቀስፎ ከመያዙ የተነሳ፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(3) (ከምርጫ ውጪ የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የተከለከለ መሆኑ) እና ሥልጣን መያዝም ሆነ ከሥልጣን መውረድ በሕገ መንግሥታዊ መንገድ ብቻ ነው የሚለው የፓርቲው ልፈፋ በተግባራዊ ትርጉሙ ኢሕአዴግን በምርጫም ሆነ በሌላ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ጭምር ማውረድ የተከለከለ መሆኑን የሚያውጅ ነው፡፡

ሲጀመር ነፃ ምርጫ በጣም በጣም ሲበዛ የሚያስቸግረውና የማይኖረው፣ ነፃ ምርጫ ድንገት ቢኖር እንኳን በሰላምና ያለቀውስ አሸናፊው ከተሸነፈው ሥልጣን መረከብ የማይችለው፣ ድንገት አሸናፊው ሥልጣን መረከብ ከቻለ ደግሞ ሥልጣን የተረከበው ፓርቲ የነባሩን የዓምደ መንግሥት አካላት መልሼ አደራጃለሁ፣ አበራያለሁ ሳይል ሥራውን የማይጀምረው በተጠቀሰው ጉድለት ምክንያት ነው፡፡ ፓርቲያዊ ወገንተኝነት በተጠናወተው ዓምደ መንግሥት ላይ ዴሞክራሲ መገንባት ስለማይቻል ነው፡፡

የሕገ መነግሥቱን ቃልና ድንጋጌ እያጣቀስን፣ የሕዝብ ሉዓላዊነትን፣ የፓርላማውን የበላይነት፣ የአፈ ጉባዔውን ኃይልና ሥልጣን ልክና መልክ አስታውሰን ‹‹የአዋጁን››፣ የሥርዓቱንና የመሠረቱን ተናግረናል፡፡ ይህ ግን መሬት ላይ እንደሌለ ነባራዊ ፖለቲካችንና ተጨባጭ ኑሯችን ውስጥ እንደሌለ የታወቀ ነው፡፡ የእዚህን ምክንያት መረዳት ወደ መፍትሔው የሚሸኝ በመሆኑ አስረግጦና ደጋግሞ ማብራራት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ የዚህ ምክንያት ከስም ጌጡ ይልቅ የሕዝቦች ሕይወትና ግንኙነት እስትንፋስ የሆነ ዴሞክራሲ አለመገንባታችን ነው፡፡ ለፓርቲያዊም ሆነ ለብሔርተኛ አድልኦ ዓይናቸው የተጋረደ ገለልተኛ የሆኑ የሁሉምና የሁላችንም የጋራ አለኝታ ተደርግው ለመታየት የበቁ መንግሥታዊ አምዶችን ማደራጀትና መገንባት ስላልቻልን ነው፡፡ በሕዝብና በሁሉም ፓርቲዎች መካከል ቀርቶ በራሱ በገዢው ፓርቲ ውስጥም የተሻለ ሐሳብና የተሻለ ችሎታን በክርክር የማንጠር ወይም በድምፅ የመለየት እስትንፋስ የሌለበት አገር በመሆኑ ነው፡፡

የገዢውን ፓርቲ እንውሰድ፡፡ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች አባላት የድርጅቱ የገደል ማሚቶዎች ናቸው፡፡ የድርጅቱ አቋም፣ አቅጣጫና አካሄድ ፈታይና አደራጊ ፈጣሪ የድርጅቱ ቁንጮ አመራር ነው፡፡ የድርጅቱ ቁንጮ አመራር የመንግሥታዊ ሥልጣኑም ቁንጮ ነው፡፡ ሕግ የማውጣት፣ አስፈጻሚውን የመጠየቅና የመመርመር፣ ሕግ ተርጓሚውን የመሾምና መንግሥታዊ የመገናኛ ብዙኃንን የመምራት ሥልጣን አለው የተባለለት በኢሕአዴግ ተመራጮች የተሞላው የተወካዮች ምክር ቤት፣ በፓርቲው የበላይ መሪ ወይም አመራር መጻፍ ውስጥ ነው፡፡ ኢሕአዴግን የሚመሩት ጥቂት ግለሰቦች የመንግሥቱን የሥራ አስፈጻሚ አካል ይመራሉ፡፡ በኢሕአዴግ ቧንቧ ወይም የመስመር ግንኙነት በኩል ደግሞ በፓርላማ ውስጥ ያሉትን ተወካዮች ያዛሉ፡፡ መናገር፣ መደገፍና መቃወም ያለባቸውን ሁሉ ይሰፍሩላቸዋል፡፡ በአጭሩ ሥራ የማስፈጸሙም፣ ሥራ አስፈጻሚውን የመመርመርና የመጠየቅ፣ ሕግ የማውጣትና ዳኛ የመሾም ሥራ ሁሉ በአንድ ቡድን እጅ ነው፡፡ የቡድን አመራሩ በአንድ ግለሰብ እጅ ከወደቀም (ከ1993 እስከ 2004 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ነበር እንደሚባለው) በአንድ ግለሰብ እጅ ይወድቃል፡፡

ይህን የመሰለ የተቋቋመና ምንም ዓይነት ለውጥ ያልነካውና ያላናጋው የዘወትር የፓርቲው አሠራር ውስጥ ‘ድርጅቴ በመደበኝ ቦታ እሠራለሁ፣ ሊስትሮ ሁን ቢለኝ ሊስትሮ ሆኜ አገለግላለሁ’ ማለት የፓርቲው አባላት የማይናወጥ ማተብ መሆኑን የሪፐብሊኩ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሁሉ (ሁለቱም በየተራ) የነገሩን ‹‹ሀቅ›› ነው፡፡ ስለዚህም የአቶ አባዱላ ገመዳን ከአፈ ጉባዔነት ኃላፊነታቸው የመልቀቅ ጥያቄ ማቅረብ፣ ሰነባብቶም ደግሞ የአቶ በረከት ስምኦን ከመንግሥት የሥራ መደብ ኃላፊነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው እለቃለሁ የማለታቸውን ውሳኔ የሰማነው፣ በተደባለቀ ስሜትና ቅጥ አምባሩ በጠፋበት ያልሰከነ መንፈስ ነው፡፡

መጀመርያ ነገር የወሬው አወጣጥና አረዳድ ከአደጋ የፀዳ አይደለም፡፡ ካሁን በፊት የሚታወቁት የ26 ዓመታት ተሞክሮዎቻችን አሳምረው እንደሚያረጋግጡት ወሬው ወይም መረጃው (አስቀድሞ) በመውጣቱ ምክንያት ብቻ፣ ወይም መረጃውን አደባባይ ያወጣውን ‹‹ወሬ ነጋሪ›› ቢያንስ ቢያንስ መሳሳት አለዚያም ‹‹ውሸታምነት›› ለማረጋገጥ ሲባል ብቻ፣ የመንግሥት የሹመት/ሽረት ወይም ዝውውር ዕርምጃ በሚቀለበስበት አገር፣ የአቶ አባዱላ የሥራ መልቀቂያ ዜና የተለያዩ ፍላጎቶች የውጪ ነፍስ ግቢ ነፍስ መዋደቂያ ነበር፡፡ ዕድሜ የ2008/2009 ቀውስ ለፈጠረው የአንዳንድ የመንግሥት/የክልል ሚዲያዎች የተለየ አንፃራዊ ነፃነት ይሁንና የአፈ ጉባዔውን የሥራ መልቀቂያ ማቅረብ ወሬ በገዛ ራሳቸው አንደበት ሲረጋገጥ ሰማን፡፡ እዚህ ሐሳቤ ውስጥ የገለጽኩት ‹‹የደስታ›› ስሜት ምንም አፈ ጉባዔው እንኳን ለቀቁ ከሚል ምኞት በጭራሽ የተቀዳ አይደለም፡፡ መልዕክተኛውን ለማሳፈር ብቻ ዕርምጃውን መቀልበስና ስለዚህም የመልዕክቱን ውሸትነት ለማረጋገጥ የሚኬድበት የማናለብኝነትና የቢሻኝ ውሳኔ ቢያንስ ቢያንስ በዚህ ጉዳይ ባለመደገሙ ነው፡፡ የአቶ በረከት ስምኦንን ከ‹‹ቀራቸው›› የመንግሥት ሥራ የመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸው ወሬም የተረጋገጠው (በዚያ አጭር ጊዜ ውስጥም ቢሆን) ከስንት የማስተባበያ ዓይነት፣ የማስተባበያ ማብራሪያና ‹‹እኛም የሰማነው ከሶሻል ሚዲያ ነው›› ከሚል ብዙ ጣጣ በኋላ ነው፡፡

ዋናው ጥያቄ ግን የአንድ ወይም የሌላ ከፍተኛ የፓርቲ አባል ከሥራ የመልቀቅ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ወይም ከዚያ በላይ የሆነው የግልጽነት ነገርም አይደለም፡፡ ‘ፓርቲው በመደበኝ ቦታ እሠራለሁ፣ ሥራዬ ብቻ ሳይሆን ከፓርቲው የተለየ ሕይወት የለኝም’ የሚል ምድብ ሠራተኛ የሥራ ዘመኑ ሳያልቅ እንዴት አድርጎ ምን ሆኖና ምን ነክቶት የመልቀቂያ ጥያቄ ያቀርባል የሚለው ነው፡፡ በሌላ አባባል የድርጅቱ አባላት የገደል ማሚቶነታቸው ቀረ ወይ? ሲገፈትሯቸው ተወርውረው ከመከስከስ፣ ዝለሉ ሲሏቸው ምን ያህል ብለው ከመጠየቅ ልክ የለሽና ገደብ የለሽ ‹‹አምባገነንነት›› ወጡ? ይህንን የሚያነቃንቅና የሚያናውጥ ለውጥ መጣ? ወይ ነው፡፡

በእኔ በኩል በገዢው ፓርቲ ውስጥ እንዲህ ዓይነት አርድ አንቀጥቅጥ ሱናሚ ተፈጥሯል ቀርቶ ሊፈጠር ይችል እንደሆነ መገመት/መጠርጠር አልችልም፡፡ ቀድሞ የገለጽነው የፓርቲው ችግር መቀጠሉ (አባላት የገደል ማሚቶዎች መሆናቸው መንግሥትም ፓርቲም የሚመራው በጥቂቶች እጅ መሆኑ) ራሱ አንድ አደጋ ነው፡፡ የፍፁማዊ አገዛዝ አደጋ ነው፡፡ ከ15 ዓመታት በፊት በ1994 ዓ.ም. ክረምት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከምሁራን ጋር በተደረገ ስብሰባ ላይ የድርጅቱ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ እንዳሉት፣ የኢሕአዴግ ወደ ፍፁማዊ አገዛዝ (Autocracy) መዝቀጥ ለድርጅቱ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱም ጭምር በእሳት ተበልቶ የመጥፋት አደጋ ነው፡፡ የዚህ ምክንያት የአገሪቱ ህልውና ከኢሕአዴግ ጋር ስለተጣበቀ ከኢሕአዴግ በጎ ፈቃድ የወጣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊደራጅ ስላልተቻለ ነው፡፡

ዛሬ በሕገ መንግሥት የተዘረዘሩትን መብቶቻችንንና ነፃነቶቻችንን በሥልጣን ላይ ያለ አካል ሲያሻው ሊነጥቀን በማናስችልበት ማኅበራዊ ፍጥርጥር ውስጥ አይደለንም፡፡ ዜጎች ከግለሰብ አድራጊ ፈጣሪነት ብቻ ሳይሆን ከመንግሥትም አድራጊ ፈጣሪነት የሚከልላቸው፣ የሚመክታቸው፣ ከመንግሥት አወቃቀርና አሠራር እስከ ሕዝብ ዓይንና ወሳኝነት ድረስ የዘለቀና የጠለቀ የራሱ መጠበቂያ ያለው ሥርዓት መሠረት አልጣልንም፡፡ የመንግሥት አስተዳደርና ክንዋኔዎች በሕዝብና እውነትን በሚሻ ጋዜጠኝነት ዓይን ውስጥ እንዳይገባ መንግሥትና ፓርቲ ገድግደው ይዘውታል፡፡ መንግሥታዊ አውታሩ የዕለት ተዕለት ፅዳት ሊያገኝ ማለትም ዘረፋን፣ በሥልጣን መባለግንና አድልኦን መዋጋት የሚችልበት ውስጣዊ ኃይሉ ጎድሏል፡፡ የመንግሥት ሕግ አስከባሪነት፣ የመንግሥት ከሳሽነትና የዓቃቤ ሕግ ለሕግ ተከራካሪነት ወደ ዜጎች መብት ድፍጠጣ የማይንሸራተትበትን ሚዛኑን ያልሳተ ሥርዓት መገንባት አልቻልንም፡፡ እንዲያውም ለዓቃቤ ሕግ ‹‹የመንግሥት ከሳሽ›› ወይም ‹‹የመንግሥት ጠበቃ›› የሚል ስም እስኪወጣለት ድረስ ሕግና ፍትሕ ተገን አጥቷል፡፡ ይህ ተስፋፍቶ ቀጥሏል፡፡ እስከ ቀጠለ ድረስም የፍፁማዊ አገዛዝ አደጋው እንዳፈጠጠ ይኖራል፡፡

ይህም ሆኖ በፓርቲው ውስጥ የሚፈጠር የመበበስበስ (የመሰንጠቅ) ችግር የራሱ የፓርቲው ችግር ሆኖ የሚቀርበት ሁኔታ እስካልተፈጠረ ድረስ፣ ማለትም ይበልጥ የለየለት ፀረ ዴሞክራሲን የማስፈን ሙከራ ሲታይና የገዢው ፓርቲ ፍላጎት ከሕዝብ ሲቃረን ሕዝቡ ሳይሸማቀቅ የሚቃወምበትና (በሰላማዊ መንገድ አውርዶ ዘጭ የሚያደርግበት ጭምር) ገዢው በእንቢተኝነት ሊቆይ የማይችልበት፣ የመከላከያውንና የፀጥታውን ኃይል የቡድናዊ ፖለቲካዊ ተቀጥላና ተገን አድርጎ መጠቀም የማይችልበት፣ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ባለመገንባቱ የገዥው ፓርቲ ዳፋ የአገር ዕዳ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

እጅ የመስቀል ወግ ከማሟላት የተሻለ ሥራ የሌለበት ፓርላማ አፈ ጉባዔ የአፈ ጉባዔ፣ የሥራ መደቤን እለቃለሁ ሲሉና በመደቡ (Normally) እዚህ ግባ የሚባል የመንግሥት የሥራ መደብ የሌላቸው የአቶ በረከት ስምኦን የሥራ መልቀቂየ ደብዳቤ ማቅረብ ራሱ፣ ዜና የሆነውና ይህ ሁሉ ያሳሰበን በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የገዢው ፓርቲ ዳፋ የአገር ዕዳና ጠንቅ ሊሆን ስለሚችል ነው፡፡

ኢሕአዴግ ግንባር ነው፡፡ የኢሕአዴግ አባላትም ድርጅቶች እንጂ ግለሰቦች አይደሉም፡፡ የተሻሻለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 ግንባር ማለት ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተናጠል ሕጋዊ ህልውናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የጋራ የሆነ ስያሜ፣ የፖለቲካ ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ ኖሯቸው ለመንቀሳቀስ ሲወስኑ የሚደራጅ አካል ነው በማለት ይተረጉማል፡፡ ኢሕአዴግ ግንባር የሆነው አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ነው፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ የኢሕአዴግ አባል፣ በተለይም መሥራች ድርጅቶች በተንቀሳቀሱበትና እንቅስቃሴያቸውን አምጦ በወለደው ፖለቲካ ውስጥ በተቋቋመው የታወቀ ልምድና አሠራር መሠረት ግንባር ዘለዓለማዊ ወይም ቋሚ አይደለም፡፡ የትግል ዓለም በመፈላቀቅ፣ በመንሸራተት፣ በመፈነጋገጥና በአሠላለፍ ለውጥ የተሞላ በመሆኑ ግንባር ሁሉ መተጋገዝን የሚጠይቁ የጋራ ጥቅምና ውዴታ እስካለ የሚፀና ጊዜያዊ ጉድኝት ነው፡፡ ግንባር እስከ መቃብር ዓይነት ቃለ መሃላዊ ትስስር አይደለም፡፡ ከውህደት የሚለየውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡

በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል አንድም ዓይነት የፕሮግራም ልዩነት የለም፡፡ ሁሉም የግንባሩ ድርጅቶች፣ አሁን አሁን የግድ መጠርጠርና መጠራጠር እስከ ጀመርን ድረስ፣ በአንድ አውራ ጅርጅትና መሪ (ምናልባትም መሪዎች) በግልጽም ሆነ ውስጥ ለውስጥ የሚቃኙ መሆናቸው ተብሎ ተብሎ ያለቀለት የአደባባይ ብይን ነው፡፡ ያልተዋሀዱትም የአቋም ልዩነት ወይም የየቡድን የሥልጣን ሽኩቻ አስቸግሮ ሳይሆን፣ የብሔራዊ ክልላዊ ‹‹የራስ በራስ›› መስተዳደርን ‹‹ወክለው›› እንዲቆይ ስለተፈለገ ብቻ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል (በዘመኑ ቋንቋ)፡፡ ከይፋ ‹‹አዋጅ›› አልፎ በተግባር ያለውን እውነት ለማየት ከተፈለገም የገዢው ግንባር አባላት አራት ብቻ ሳይሆኑ ‹‹አጋር›› የሚባሉትንም የሚያካትት ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ እያንዳንዱ አባል ድርጅት የገዛ ራሱ ‹‹ነፃነት›› አለው ማለት የኢሕአዴግን መንግሥት ‹‹ጥምር›› መንግሥት አድርጎ እስከ መውሰድ የሚያሳስት ራሱን ኢሕአዴግን የሚያስደንቅና ‹‹ድንቄም!›› የሚያሰኝ ምልከታ ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ የእስከዛሬው ሁኔታ ይህንን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

የኢሕአዴግ ፓርቲ አመራርና አባል የሆኑት አቶ አባዱላ ገመዳ፣ እንዲሁም የብአዴን ፓርቲ አመራርና አባል የሆኑት አቶ በረከት ስምኦን ከፓርቲ አባልነታቸውና አመራራቸው ሳይሆን ከመንግሥት የሥራ መደብ የመነሳታቸው ወሬ ሲሰማና ሲረጋገጥ፣ የሠጋነውና የደነገጥነውም ይህ ግንባር እስከ መቃብር መሃላ ፈርሶ፣ ሊፈርስ ተነቃንቆ ነው ወይ ብለን ነው፡፡ የኢሕአዴግ ችግርና ዳፋ ለኢትዮጵያም የሚተርፍ ዕዳ ያለው መሆኑን ስለምናውቅ ነው፡፡

በጋራ መታገልን ግድ የሚያደርገው ‹‹ጊዜያዊ ጉድኝታቸው›› አበቃ? እንደዚህ ዓይነትስ ችግር ሲፈጠር፣ ወይም እንዲህ ያለ ደረጃ ላይ ሲደረስ ወይም በማናቸውም ጊዜ በዴሞክራሲያዊ መብቶችና መቻቻል ውስጥ መኗኗርን መሠረት ያስያዘ፣ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የሚረባረቡ ችግሮችም ሲመጡ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገዶች ለመፍታትና ውጤቱንም ለመቀበል የሚችል ባህልና ፍጥርጥር አለን ወይ?

ለዚህ ሁሉ ያበቃን፣ በምንገኝበት ሁኔታ ውስጥ ቀስፎ የያዘን ዴሞክራሲን መገንባት በተለይም የመንግሥት ዓምዶችን ገለልተኛ አድርገን ማዋቀር ባለመቻላችን ነው፡፡ ከቡድን ቁጥጥር የተላቀቀ ሥርዓት ባለመገንባታችን ነው፡፡ በዚህ ላይ ሥልጣንና ትክክለኛነት የእኔ ብቻ ነው ማለት ሰፈነ፡፡ መሰሪ መንገዶችና በሥልጣን መማገጥ የትግል መሣሪያዎች ሆኑ፡፡

አሁንስ በገዢው ፓርቲ በራሱ ውስጥ አለመግባባት መፈጠር ወይም የፓርቲዎቹ ‹‹መሥራች›› አባቶች ራሳቸው በፓርቲያቸው ላይ ወይም በግንባሩ ውስጥ ቅሬታ ቢኖራቸውና የተለየ ሐሳብ ቢያነሱ፣ በሐሳብ መለያየትንና ተቃራኒ ሐሳብ ማንሳትን ከመወንጀልና በዱላና በጥይት ከመቅጣት ወዲህ ማዶ ያለ ተደማምጦ የሚወያይ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የቅራኔ መፍቻ ሥርዓት አለን ወይ?

አንድ የአገር ፓርላማ አፈ ጉባዔ ሥራውን በገዛ ፈቃዱ ቢለቅ ዜና ነው፡፡ ከዜና በላይ የአገር የሥጋት ምንጭ የጭንቅና የጥብ ምክንያት ሲሆን ግን ጤና አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካና የትግል ኃይሎች ተባብረው መለወጥ ያለባቸው ይህንን ያልተገላገልነውን የገዢው ፓርቲ ዳፋ የአገር ጠንቅ የሚሆንበትን አደጋ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡