Skip to main content
x

ምርጥ ዘር ፍለጋ 

ለመንደሩ ነዋሪዎች አገልግሎት ከሚሰጠው ጥርጊያ መንገድ ገባ ብሎ የሚገኝ ሰፊ እርሻ ነው፡፡ በተንጣለለው የእርሻ መሬት የለማው የሩዝ ማሳ አስደሳች መስህብ አለው፡፡ የተዘራው እንደ ነገሩ ሳይሆን፣ በጥንቃቄና በመስመር ነው፡፡ ንብረትነቱ የአንድ ጎበዝ አርሶ አደር ስለመሆኑ ከማወቃችን በፊት የአካባቢው አርሶ አደሮች በጋራ የሚያርሱት ማሳ መስሎን ነበር፡፡

ማሳውን ለመጎብኘት የግብርና ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች በቦታው የተገኙት ጀምበር ስትወጣ ነበር፡፡ አርሶ አደሮቹ ቀደም ተገኝተዋል፡፡ በወፍ መጠበቂያ ማማው ላይ ከተቀመጡት ወጣቶች አጠገብ የተሰቀለው የድምፅ ሳንጥን (ሞንታርቦ) የሚወጣው ድምፅ ከዳር ዳር እያስተጋባ ጆሮ ቢያደነቁርም ወጣጦቹ ግን በሞንታርቦው ዙሪያ መሰባሰብን መርጠዋል፡፡ አቶ ዘገየ ካሳዬ ግን ከሰው ሳይቀላቀሉ ከማዶ ፈንጠር በማለት ዛፍ ስር ቆመው የሚካሄደውን ከሩቅ ይታዘባሉ፡፡

በማሳው ውስጥ ከተሰበሰቡት ከፍተኛ አምራች አርሶ አደሮች አንዱ ስላለመሆናቸው ከሁኔታቸው መገመት ይቻላል፡፡ የለበሱት በ1990ዎቹ ወቅት ይዘወተር የነበረው ክሬሽን ጃኬት ተበጣጥሷል፡፡ እንደ ነገሩ ወደ ላይ የጠቀለሉት የጨርቅ ሱሪም ለአመል ያህል ገላቸውን ሸፍኖታል ቢባል ነው፡፡ ከኪሱ ጀምሮ እስከ ጉልበታቸው የተቀደደ ሲሆን፣ እግራቸውን በከፊል ያሳያል፡፡ የተጫሙት ቦቲም እርጅና ተጭኖት የቅያሪ ያለህ ይላል፡፡

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በምትገኘው ፓዌ ወረዳ የሚኖሩት የ65 አመት አዛውንቱ አቶ ዘገየ፣ ሦስት ሄክታር መሬት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ጉብዝናቸውን ሲገልፁም ‹‹በጨረቃ ነው የማርሰው፡፡ ደከመኝ ሰለቸኝ አልልም፡፡ ችግሩ አስሜ ሲነሳብኝ ነው፡፡ ድክም ስለሚያደርገኝ ማረሱን ትቼ ቁጭ እላለሁ፤›› በማለት ከአቅማቸው በላይ የሆነው ህመም ካልተነሳባቸው በቀር ከእርሻቸው እንደማይለዩ ይናገራሉ፡ ይህንን ያህል ጠንክረው ቢሠሩም ከእርሻቸው የሚያገኙት ግን በምሳሌነት ከቀረበው ማሳ ጋር አይተካከልም፡፡ ለዚህም ይመስላል ከሰው ተነጥለው ምርኩዛቸውን እንደተደገፉ የሚተክዙት፡፡

ለምርታቸው አጥጋቢ አለመሆን የተለያዩ ችግሮች በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡ ዋናው ችግር ግን የተሻሻለ ዘር አለማግኘታቸው ነው፡፡ ‹‹እኛ የነበረንን ዘር ነው የምንጠቀመው፡፡ እሱ ግን አምና ያገኘውን ምርጥ ዘር ቆጥቦ አስቀምጦ ነው የዘራው፤›› በማለት ወደ ተንጣለለው ማሳ በእጃቸው ይጠቁማሉ፡፡ ምርታማነቱም ከሳቸው እንደማይዳደር ሲያስረዱም ‹‹የእኔ እንደዚህ አይሆንም፡፡ ሰውየው በጣም ጠንካራ ነው፤›› አሉ፡፡ ምርጥ ዘር የሚሸጥበት ዋጋ ውድ ስለሆነባቸው ግን ዘር ገዝቶ የማልማት ፍላጎት የላቸውም፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ አንድ ኪሎ የሩዝ ዘር በ15 ብር ይሸጣል፡፡ አንድ ሄክታር ለማልማት ደግሞ በትንሹ አንድ ሺህ ብር ይፈጃል፡፡ ይህም ከሌሎች የተለያዩ ወጪዎች ጋር ሲደመር ከአቅማቸው በላይ ይሆናል፡፡ ዘር ቢገዙም ለማዳበሪያ የሚሆናቸውን ገንዘብ አጥተው የሚቸገሩባቸው ጊዜያትም በርካታ ናቸው፡፡ ስለዚህ በተቻላቸው መጠን የሚያወጡትን ገንዘብ መቆጠብ፣ አንዱን ከሌላው መምረጥ ግድ ይሆንባቸዋል፡፡

በአርሶ አደሮቹ ዘንድ የተሻለ ምርታት የሚሰጠውን ዘር እርስ በርስ መለዋወጥ የተለመደ  ነው፡፡ ይህ ግን በቀላሉ አይሆንም፡፡ በመካከላቸው ዝምድና፣ ጠበቅ ያለ ቅርርብ ሊኖር ይገባል፡፡ ይህ ከሌለ ልምምጡና ልመናው መከራ ነው፡፡ ገዝቶ ለመዝራት አቅም ስለማይኖራቸው ሌላ አማራጭ የላቸውም፡፡ ሰውየው እሺታውን እስኪሰጣቸው ይለማመጡታል፡፡ አለዚያ ግን ነባሩንና ሲንከባለል የመጣውን ዘር ለመዝራትና ከሱም የተገኘውን ውጤት ይሰበስባሉ፡፡ ችግሩ የአቶ ዘገየ ብቻ ሳይሆን፣ በአካባቢው ብሎም በክልሉ የሚገኙ ብዙዎቹ አርሶ አደሮች የሚጋሩት ነው፡፡ የተሻሻሉ ዝርያዎች ላይ የሚደረግ ምርምርና ጥናት ባለመኖሩ የተከሰተ ግን አይደለም፡፡

የፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል በሰብል፣ በእንስሳትና በተፈጥሮ ሀብት ላይ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ ማዕከሉ አዳዲስ ዝርያዎችን ከማውጣት ባሻገር የማስተዋወቅ፣ የማባዛትና የቅድመ ማስፋፋት ሥራዎችም ይሠራል፡፡ የአኩሪ አተር ምርምርን ሲያስተባብር የቆየ ሲሆን፣ ሰፊ ትኩረት በመስጠት የሚሠራውም በዚሁ በአኩሪ አተር ላይ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በበቆሎ፣ በሩዝ፣ በዳጉሳ፣ በማሽላ፣ በማሾ፣ በከብቶች መኖ፣ በሙዝና በማንጎ ላይ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን ያካሂዳል፡፡ እስካሁን በማዕከሉ ከተካሄዱ የምርምር ሥራዎች የላቀ ውጤት የተመዘገበው በአኩሪ አተር እንደሆነ የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ያለው ማዘንጊያ ይናገራሉ፡፡

አኩሪ አተር ወደ ኢትዮጵያ የገባው እ.ኤ.አ በ1950ዎቹ ነበር፡፡ እስከ 1963 ዓ.ም ድረስ 20 የአኩሪ አተር ዝርያዎችን ከተለያዩ አገሮች በማስገባት በደብረ ዘይት፣ በጅማና በቁሉምሳ ምርምር ማዕከላት ተስማሚ ዝርያዎችንና ተስማሚ አካባቢዎችን የመምረጥ ሥራዎች ሲሠሩ እንደቆዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል የአኩሪ አተር ምርምርን በብሔራዊ ደረጃ እንዲያስተባብር ሥልጣን የተሰጠው በ2004 ዓ.ም ነበር፡፡ ምርምሩን ማስተባበር ከጀመረ ወዲህ ስድስት፣ ከዚያም በፊት ሦስት የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማውጣት በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲሠራጩ አድርጓል፡፡

የሩዝ ምርምር ሥራውም የሚጠቀስ ነው፡፡ በአገሪቱ 33 የተለያዩ የሩዝ ዝርያዎች ተለቀዋል፡፡ ከ30 ሚሊዮን ሔክታር በላይ ሩዝ ለማምረት የሚያስችል መሬት መኖሩም ታውቋል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የሩዝ ማሳዎች በከፍተኛ መጠን እየተስፋፉ ይገኛሉ፡፡ ከተለቀቁ አዳዲስ ዝርያዎች መካከል ፓዌ-1፣ ነሪካ-3፣ ነሪካ-4፣ ሱፐሪካ-1፣ ነሪካ-12፣ ህዳሴ፣ ዓባይ፣ እርብና ሌሎችም የፓዌ ምርምር ማዕከል ከሌሎች ጋር በመተባበር ከለቀቃቸው ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በሩዝና በአኩሪ አተር ባሻገር በአሁኑ ወቅት ከ200 በላይ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ዳሩ ግን በወረዳውም ሆነ በክልል ደረጃ እንዚህን የተሻሻሉ ዝርያዎች ተቀብሎ በማባዛት ለተጠቃሚ የሚያደርስ የዘር ብዜት ኢንተርፕራይዝ የለም፡፡ ይህም በብዙ ልፋት የሚገኙ የምርምር ውጤቶች በበቂ ደረጃ ለአርሶ አደሩ እንዳይደርሱ እያደረገ ነው፡፡ እንደ አቶ ዘገየ ያሉ አርሶ አደሮችም በምርጥ ዘር እጦት እንዲቸገሩ እያደረገ ይገኛል፡፡

‹‹ማዕከሉ የሚያወጣቸውን ቴክኖሎጂዎች አባዝቶ ለተጠቃሚ የሚያደርስልን የለም፡፡ ነገር ግን የምርምር ሥራዎች መደርደሪያ ላይ ተቀምጠው እንዳይቀሩ ማዕከሉ ከዞኑ ግብርና እና ገጠር ልማት መምሪያ ጋር በመተባበር እየሠራ ነው፣›› በማለት የምርምር ሥራዎቹን ለአርሶ አደሩ የሚያደርስበት የራሱን መንገድ መቀየሱን አቶ ያለው ገልጸዋል፡፡ ይህም ለተመረጡ ሞዴል አርሶ አደሮች ከማዕከሉ የዘር ግብዓትና ሙያዊ ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ የተሻሻለና የተመሰከረለት ዘር እንዲያመርቱ ማስቻል ነው፡፡

ባለፈው ዓመት ብቻ ከ200 በላይ አርሶ አደሮች ጋር የምርምር ማዕከሉ አብሮ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከባለሀብቶችም ጋ እንዲሁ ግንኙነት ፈጥሯል፡፡፡ በዚህ ዓመትም መንግሥት ባወጣው ስትራቴጂ መሠረት በክላስተር እየተዘጋጁ የሚባዙ ዘሮች አሉ፡፡ ብዙ ተለፍቶባቸው የሚወጡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የመደርደሪያ ሲሳይ ሆነው እንዳይቀሩ ርብርብ እየተደረገ ቢሆንም ትርጉም ያለው ሥራ ሊሠራ አልተቻለም፡፡

‹‹ያለውን የዘር ዕጥረት ለመቅረፍ ዋናው መፍትሔ የምርጥ ዘር ድርጅት ማቋቋም ነው፡፡ ዘር የማብዛት ሥልጣኑና ኃላፊነቱ ያላቸው እነዚህ ድርጅቶች ናቸው፡፡ እኛ ይህንን ሥራ የምንሠራው አዲስ የሚወጡ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ የምናደርስበት ሌላ አማራጭ ስለሌለን ነው፤›› በማለት የፈጠረው አሠራር አማራጭ በማጣት እንጂ ሥልጣኑ ለምርምር ማዕከሉ ተሰጥቶ አለመሆኑን፣ ተደራሽነታቸውም ካለው ፍላጎት አንፃር ሲታይ አነስተኛ እንደሆነ አቶ ያለው ይናገራሉ፡፡

ከዚህ ቀደም የዘር አቅርቦት ፍላጎት ያላቸው አርሶ አደሮች ብቻ ነበሩ፡፡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በሰርቶ ማሳያ ሲተዋወቁና ምርታማነታቸው ሲታይ የዘር ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህንን ፍላጎትና አቅርቦት ለማጣጣምም ትልቅ ችግር ሲያገጥም እንደቆየ አቶ ያለው ይልጻሉ፡፡ ይባሱን ደግሞ በመተክል ዞን ጉባና ዳንጉር ወረዳዎች በርካታ ባለሀብቶች በእርሻ ሥራ መሰማራታቸው የነበረውን የዘር ፍላጎት በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር አድርጎታል፡፡ ከዚህ ሲያልፍም እንደ ጣና በለስ ያሉት ተቋማት ታከሉበት፣ ከነበረው የዘር ፍላጎት ጋር ተደምሮ ፍላጎቱን ከአቅርቦቱ በላይ እንዲንር አድርጎታል ይላሉ፡፡

በየጊዜው ተሻሽለው የሚወጡ በርካታ ቴክኖሎጂዎች ቢኖሩም አሁንም ድረስ ምርታማነት ትልቅ ጥያቄ ሆኗል፡፡ የምግብ ዋስትና ችግርን መቅረፍ አለመቻሉ እንዲሁም በየዓመቱ ከፍተኛ ገንዘብ ወቶባቸው ከውጭ የሚገቡ የእህል ምርቶች የችግሩ ዋነኛ ማሳያ ናቸው፡፡

ለአብነት ያህል በ2008 ዓ.ም 171 ሚሊዮን ዶላር የፈጀ 312009 ቶን ሩዝ ወደ አገሪቱ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ይህም ከዓመቱ ከቅባት እህሎች የወጪ ንግድ ከተገኘው 480 ሚሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር አንድ ሦስተኛውን ይይዛል፡፡ ከዚህ ባሻገር አገሪቱ እስካሁን ድረስ የአኩሪ አተር ዘይት፣ ከአኩሪ አተር የሚዘጋጁ የህፃናት አልሚ ምግቦችን ከውጭ በማስገባት ላይ ትገኛለች፡፡ እ.ኤ.አ በ2006፣ 6060 ቶን የአኩሪ አተር ዘይት ወደ አገሪቱ ሲገባ፣ የ4.82 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ጠይቋል፡፡ ይህንን መጠን እ.ኤ.አ በ2010 ወደ 4328 ቶን ዝቅ ማድረግ ቢቻልም አሁንም ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ከውጭ እየገባ በመሆኑ ብዙ ሥራ እንደሚቀር አመላካች ነው፡፡

ለዚህ በምክንያትነት ከሚጠቀሱ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች መካከል የዘር አቅርቦት ተደራሽ አለመሆን አንዱ ነው፡፡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በምርምር የማውጣት ኃላፊነት ያለበት የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ማዕከልና በየክልሉ የሚገኙ ማዕከላት ሲሆን፣ ከእነዚህ ተቋማት የሚወጡ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ተቀብሎና አባዝቶ ለአርሶ አደሩ የማድረስ ኃላፊነትና ድርሻ ደግሞ የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ሥር የሚገኘው የምርጥ ዘር አቅርቦት ተቋም ነው፡፡ ይህ በመደበኛ አሠራር የሚደረግ የዘር አቅርቦት ሥርዓት ነው፡፡ መደበኛ ያልሆነው አሠራር ደግሞ የፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል እንደሚሠራው ዓይነቱ ማኅበረሰብ አቀፍ የዘር ብዜት አሠራር ነው፡፡

በመደበኛው የዘር አቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ በጣት የሚቆጠሩ የግል ድርጅቶችና የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ኃላፊነቱን ወስደው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ይሁንና የተደራሽነታቸው መጠን ዝቅተኛ ነው፡፡ በተለይ ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያለው ተደራሽነት ዝቅተኛ ነው፡፡ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ሕዝቦች፣ በትግራይና በአማራ ክልሎች 10 ቅርንጫፎች እንዳሉት የሚናገሩት በኮርፖሬሽኑ የምርጥ ዘር አቅርቦት ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ፈለቀ ገዛኸኝ ናቸው፡፡

በእነዚህ ቅርንጫፎች ውስጥ በሚገኙ 6 የተለያዩ እርሻዎች 6000 ሔክታር ላይ ዘር የማባዛት ሥራ ያከናወናል፡፡ በተጨማሪም በአርሶ አደሩ ማሳዎች ውስጥ ዘር ይባዛል፡፡ ተደራሽነታቸውም ቅርንጫፎቹ በሚገኙበት ክልሎች ብቻ ሳይወሰን በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች እንደሆነ አቶ ገዛኸኝ ይናገራሉ፡፡ በክልል ደረጃ የተቋቋሙ አራት ዘር የሚያባዙ ድርጅቶችም ወደ ሥራው እንደገቡና ኮርፖሬሽኑ የማይደርስባቸውን ቦታዎች እንደሚያዳርሱ ጠቅሰዋል፡፡

‹‹በሁሉም ቦታ እንሸጣለን፡፡ ነገር ግን ማባዣው ውስን ነው፡፡ ኦሮሚያ ላይ ስንዴ አባዝተን እስከ ትግራይ ወስደን እንሸጣለን፡፡ የአርሶ አደሩን መሬት ተከራይተን የመነሻ ዘር በመስጠት እንዲያባዙ እንዳርጋለን፡፡ ከዚያም በኩንታል እንገዛቸዋለን፤›› ያሉት አቶ ገዛኸኝ፣ የሚገዟቸው የተመሰከረለት ዘርና የሚሸጡበት ዋጋ ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው በመግለፅ አርሶ አደሮች እንደሚያማርሩ አስታውሰው ይህ ግን በኮርፖሬሽኑ  የተፈጠረ ችግር አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለምሳሌ በአርሶ አደሩ ማሳ የተባዛ አንድ ኩንታል ስንዴ በ800 ብር ገዝተው እስከ 1300 ብር ይሸጣሉ ያሉት አቶ ገዛኸኝ፣ ‹‹አርሶ አደሮችም ከእኛ በርካሽ ገዝታቹ በከፍተኛ ትርፍ ትሸጣላቹ በማለት ቅሬታቸውን ይገልፃሉ፤›› ብለዋል ‹‹ከምንገዛው አንድ ኩንታል ስንዴ ውስጥ ሲበጠር የሚቀረው 80 ኪሎ አካባቢ ነው፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ነው ዋጋውን ከፍ አድርገን የምንገዛው፡፡ በሌላ በኩል ዘር ከውጭ የሚያስገቡ ድርጅቶች እኛ ጋር በኩንታል እስከ 2900 ብር የሚሸጠውን ዘር እስከ 5000 ብር ይሸጣሉ፤›› በማለት፣ እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች በአጠቃላይ ዘር የሚሸጥበት ዋጋ ከፍተኛ መስሎ እንዲታይ ማድረጉን ያብራራሉ፡፡ ዘሮች, የሚሸጡበት የትርፍ ህዳግም ከአምስት እስከ ሰባት በመቶ ሲሆን፣ አንዳንድ ዘሮች ምንም አይነት ትርፍ ሳይገኝባቸው አንዳንዴም በኪሳራ እንደሚሸጡ ጠቅሰዋል፡፡

‹‹መነሻ ቴክኖሎጂዎች ከምርጥ ዘር ድርጅቶች ይቀርብልናል፡፡ በግል የሚመጡ የዘር ጥያቄዎችም አሉ፡፡ ከዚህ ውጪ የተመረጡ ሞዴል አርሶ አደሮችን በማደራጀት ዘሩን እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ ሥልጠና እና መነሻ ዘር እንሰጣቸዋለን፡፡ በሰፊው አባዝቶ ለብዙኃኑ ለማዳረስ የማሽንና የመሠረተ ልማት ችግሮች አሉ፤›› የሚሉት በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአእምሯዊ ንብረት ባለቤትነትና የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፍሰሃ ዘገየ ናቸው፡፡

በብዛት ከሚቀርቡላቸው የዘር ጥያቄዎች መካከል ስንዴ፣ ማሽላ፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ገብስና  ስትራቴጂክ የሚባሉና ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሰብሎችን የተመለከቱ ናቸው፡፡ በቆሎ ከሁሉም ዘንድ በግንባር ቀደምነት ተፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በሔክታር የሚገኘው የበቆሎ ምርት ከሌሎቹ አንፃር ከፍተኛ በመሆኑ ሲሆን፣ ዘሩ አንዴ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ለማዋል ስለማያስችል ነው፡፡ አምራቾች በየዓመቱ አዳዲስ ዘር መግዛት ግድ ስለሚሆንባቸው ለዘር አባዥ ድርጅቶች ደግሞ ይህ አዋጭ በመሆኑ እንደሆነ አቶ ፈለቀ ይናገራሉ፡፡ እንደ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የከብት መኖ፣ ሽምብራ፣ ምስር ያሉትን ዘሮች በተደጋጋሚ ጊዜ ጥቅም ላይ ማዋል ስለሚቻል ግን ለዘር አባዥ ድርጅቶች ያንን ያህል ጥቅም የሚያስገኙ አይደሉም፡፡ እንደ አተርና ቦሎቄ ያሉ ጥራጥሬዎችም ከስትራቴጂክ ሰብሎቹ አንፃር ተፈላጊነታቸው እምብዛም ነው፡፡

‹‹የእኛ ተልዕኮ አማራጭ ቴክኖሎጂዎች እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡ መድረስ የምንችለውም ለተወሰኑ አርሶ አደሮች ነው፡፡ ኢንተርፕራይዞቹ ተቀብለውን ሊያስፋፉ ይገባል፡፡ ነገር ግን በበቂ ሁኔታ እየሠሩ አይደሉም፤›› በማለት አቶ ፍሰሃ ይናገራሉ፡፡ አቶ ፈለቀ በበኩላቸው አርሶ አደሩ አዳዲስ የምርምር ውጤቶች ሊደርሱት እንደሚገባ፣ አንድን ዘር በተደጋጋሚ ጊዜ መጠቀም በምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር፣ ይህንን ለማስረዳትም አርሶ አደሩ በያለበት ለመድረስ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

ይህም በምርምር ተቋማት የሚሠሩ ምርምሮች እንደ አቶ ዘገየ ላሉ አርሶ አደሮች ማሳ እንዳይደርስ፣ ምርታማነታቸውም ከእጅ ወደ አፍ ሆኖ እንዲቀጥል እያደረገ ይገኛል፡፡ አንድ የሰብል ቴክኖሎጂ በምርምር ለማውጣት በትንሹ ሦስት ዓመት ይወስዳል፡፡ ተመራማሪውን ጨምሮ የስድስት ባለሙያዎችን ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡ የቀን ሠራተኞችም ይሳተፉበታል፡፡ ምርምሩ እስኪጠናቀቅ ድረስ በትንሹ እስከ 500000 ብር ይፈጃል የሚሉት፣ የፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ይህንን ያህል ገንዘብና ጉልበት ፈሶባቸው የሚሠሩ የምርምር ሥራዎች ግን በሰበብ አስባቡ ተደራሽነታቸው ውሱን ሆኖ መቅረቱ ልብ የሚነካ ነው፡፡ የአገር ሀብት በሜዳ የሚያሰኝ ነው፡፡