Skip to main content
x
የአይቴል ሞባይል ስልኮች አምራች የ300 ሚሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ ለማከናወን መነሳቱን አስታወቀ

የአይቴል ሞባይል ስልኮች አምራች የ300 ሚሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ ለማከናወን መነሳቱን አስታወቀ

  • በዚህ ዓመት 40 ሚሊዮን ዶላር ለማስገባት አቅዷል

በኢትዮጵያ የሞባይል ስልኮችን በመገጣጠም ሥራ መስክ አሥረኛ ዓመቱን ባስቆጠረውና ትራንሽን ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በተባለው የቻይና ኩባንያ ሥር ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች አንዱ የሆነው አይቴል ኩባንያ፣ በዚህ ዓመት የሞባይል ስልኮች የወጪ ንግድ ገቢውን 40 ሚሊዮን ዶላር ለማድረስ ማቀዱን ገለጸ፡፡ የተንቀሳቃሽ ስልኮች ምዝገባ ምርቱንና የገበያ ድርሻውን የበለጠ እንደሚያሳድገው አስታውቋል፡፡

ኩባንያው በኢትዮጵያ ሥራ የጀመረበትን አሥረኛ ዓመት ባለፈው ሳምንት ባከበረበት ወቅት፣ የሞባይል ስልኮችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ፈር ቀዳጅ መሆኑንና እስካሁንም ከ35 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማስገኘቱም አስታውቋል፡፡ በዚህ ዓመት መጨረሻም ከሞባይል ስልኮች የወጪ ንግድ 40 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ከማቀዱም በተጨማሪ፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጨረሻ  የወጪ ንግዱን ወደ 300 ሚሊዮን ዶላር ለማድረስ እንደተነሳ አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚታየውን የገበያ ዕድል በመመልከት በ2004 ዓ.ም. ከአሥር የማይበልጡ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞችን በመቅጠር፣ በወር እስከ አሥር ሺሕ ሞባይሎችን የመገጣጠም አቅም በመያዝ ሥራ ጀምሮ ነበር፡፡ አይቴል ከኢትዮጵያ ውጭ በአፍሪካ ደረጃ ከፍተኛ የተጠቃሚ ቁጥር ካላቸው አምስት የሞባይል ስልክ ምርቶች አንዱ ለመሆን መብቃቱንም የኩባንያው ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡  

ኩባንያው በኢትዮጵያ ያለውን የሞባይል ስልኮች ገበያ በማጥናትና ሥራውን በማሳደግ በአሁኑ ወቅት በሁለት ማምረቻዎች በወር እስከ 700 ሺሕ ሞባይል ስልኮች የማምረት አቅም ገንብቷል፡፡ የሠራተኞቹን ቁጥርም 1,800 ለማድረስ እንደቻለ ገልጿል፡፡

በአፍሪካ ያገኘውን ተቀባይነት በማጠናከር ገበያውን የበለጠ ለማሳደግ እንደሚሠራና ለደንበኞቹም አዳዲስ የሞባይል ሞዴሎችን በማስተዋወቅ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት በኢትዮጵያ የአይቴል ኃላፊ ሚስተር ሊ ዮን ናቸው፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት የአፍሪካ ገበያው በእጥፍ እንዳደገ የጠቀሱት ሚስተር ዮን፣ በአዳዲስ ፈጠራዎች በመታገዝ ባለፉት አሥር ዓመታት አፍሪካ ውስጥ 100 ሚሊዮን ሞባይሎችን ለመሸጥ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ምርቱ በ45 አገሮች ውስጥ እየተሸጠ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

የአይቴል ኩባንያ ምክትል የግብይት ኃላፊ አቶ ቢንያም አርዓያ በበኩላቸው፣ ኩባንያው በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ውስጥ ያለውን ገበያ ድርሻ ለማሳደግ ዘመናዊ የሞባይል ስልኮችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ እየሠራ ነው፡፡ ዘመናዊ የሚባሉት ስልኮቹም ከመቶ ዶላር ባነሰ ዋጋ ለገበያ ስለሚቀርቡ በርካታ ደንበኞችን ለማፍራት እንደረዳው ጠቅሰዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና በኢትዮ ቴሌኮም አማካይት የሞባይል ስልኮችን የመመዝገብ ሥርዓት መተግበሩ በአገር ውስጥ የሚገጣጠሙ ስልኮች ገበያ እንዲጨምር ማገዙን የአይቴል ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

የሞባይል ስልኮች ምዝገባ እንዲካሄድ ኩባንያው በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ቆይቷል ያሉት አቶ ቢንያም፣ ጥያቄው አወንታዊ ምላሽ በማግኘቱ በአገር ውስጥ ለሚገጣሙ የሞባይል ስልኮች ትልቅ የገበያ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ይኼንን የምዝገባ ሥርዓት አስመልክቶ በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ስልኮች የሚያስከትሉትን የአገልግሎት ጥራት መጓደል እንዲሁም ተመሳስለው በተሠሩና ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ሕገወጥ ስልኮች አማካይነት እየደረሰ ያለውን ችግር ለመከላከል የሚረዳ ዕርምጃ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር አዲሱ የምዝገባ አሠራር መመርያ የወንጀል ድርቶችን ለመከላከል እንዲሁም በሕጋዊ አስመጪዎችና በአገር ውስጥ ሞባይል ገጣጥመው ለገበያ በሚያቀርቡ ኩባንያዎች ላይ እየፈጠረ ያለውን አግባብነት የሌለው የገበያ ውድድር ለማስቀረት እንደሚረዳ ኢትዮ ቴሌኮም መግለጹ ይታወሳል፡፡

አቶ ቢንያም እንደገለጹት፣ የአገር ውስጥ የሞባይል መገጣጠሚያዎች በአዳዲስ ፈጠራዎች ታግዘው ገበያ የማስፋት ሥራ እንዲሠሩ ያግዛል፡፡ የኮንትሮባንድ ስልኮች መገደብም የሞባይል መገጣጠሚያዎች አሁን ካላቸው የገበያ ሽፋን በተጨማሪ አዳዲስ ገበያዎችን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡ አይቴል በቅርቡ ወደ ጠረፋማ አካባቢዎች በማቅናት ጭምር የገበያ አድማሱን ያሰፋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መመርያው ያግዘዋል ተብሏል፡፡

ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ የኩባንያው ወኪሎች በታደሙበት በ10ኛው የአይቴል የምሥረታ ሥነ ሥርዓት ወቅት አዳዲስ ምርቶች ተዋውቀዋል፡፡ S-32 እና S-12 የተባሉ ዘመናዊ ስልኮች ቀርበዋል፡፡