Skip to main content
x

ገደብ ያልተበጀለት የቤት ኪራይ ጭማሪና የተከራዮች እሮሮ

 ብርሃኑ በቀለ

 ‹‹አዲስ አበባ በትልቅ የእግር ኳስ ሜዳ ትመሰላለች›› ያለው ማን ነበር? ድሆች በዙሪያ ተኮልኩለው ሲመለከቱ ሀብታሞች መሀል ላይ ይጫወታሉ፡፡

  ለማንኛውም ይህ ጽሑፍ ‹መሀል ከተማ የነበረን ቤት ለሀብታም ተሰጥቶ ለእኛ ከከተማ ጫፍ ተሰጠን. . . ባማረው ሰፊ ግቢ ምትክ በኮንዶሚኒየም ብቻ ሸነገሉን. . .› ስለሚሉ ባለካርታ ሰዎች አይደለም፡፡ ‹የነበርኩት መሀል ፒያሳ ለሀብታም ተሸጦ እኔን  የዳር ተመልካች አደረጉኝ . . . የሠራሁት ቤትና አከራይቼ ስተዳደርበት የነበረው ቤት ጨረቃ ቤት ነው በሚል ሊያፈርሱብኝ አንገላቱኝ ስለሚሉም አይደለም. . .›፣ ‹‹አዲስ አበባ ከአሁን በኋላ ወደ ላይ እንጂ ወደ ጎን አትሰፋም››  የሚል መግለጫ ሰምተው፣ ‹ባለን የቤትም ይሁን የመሬት ካርታ ወደ ላይ ሰማይጠቀስ ፎቅ መገንባት የማንችል መሬትና ቤታችንን እንዴት እናደርገዋለን› ስለሚሉ የቅንጦች ችግረኞችንም አይመለከትም. . .

ይልቅስ ይህ ጽሑፍ ገደብ በሌለው የቤት ኪራይ ጭማሪ ምክንያት ፍራሻቸውን ተሸክመው ከቤት ቤትና ከሠፈር ሠፈር. . . ከጎረቤት ጎረቤት. . . ስለሚቀያይሩና ስለሚንከራተቱ ምስኪኖች ነው፡፡  ይልቅስ ይኼ ጽሑፍ የአዲስ ዓመቱን መስከረም ከቤት ኪራይ፣ ጭማሪ ጋር በሰቀቀን  ስለሚቀበሉት፣ ከሁለት ስዓት በኋላ መግባትና መውጣት፣ ውኃ አንድ ጀሪካን ብቻ፣ ማንኛውንም እንግዳ ወደ ግቢ ይዞ መግባት ዋ! ስለሚባሉት፣ ተከራይ በብድር አሊያም በእቁብ የገዛውን ፍሪጅ ሲያስገባ ዓይተው ለቆጣሪው አታስብም እንዴ? በል ሦስት መቶ ብር ጨምሬብሃለሁ ተብለው ከፍሪጁ ጋር መርዶውን ይዘው ስለሚገቡት  ምስኪን ተከራዮች ነው፡፡

 በአንድ ወቅት መምህር የሆነው ጓደኛዬ ‹RIP› የደመወዝ ጭማሪ›› የሚል ታፔላ በፌስቡክ አካውንቱ ላይ ለጥፎ ዓይቼ ምንድን ነው ብዬ ጠይቄው ነበር፡፡ ለካ ደመወዝ ለመምህራን ይጨመራል እየተባለ ከስድስት ወራት ባላነሰ ጊዜ፣ በመንግሥት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ሲወራ የመምህራንን ልብ ሰቅሎ ኑሯል፡፡ በኋላ የተባው ጊዜ ደርሶ ሲታይ ጭማሪው እዚህ ግባ የማይባል ከመቶ ብር ብዙም ያልዘለለ ሁኖ ተገኘ፡፡

‹እህሳ ጭማሪው የት አለ?› ተብሎ ሲጠየቅ፣ ‹‹ማን አባታችሁ ነው የደመወዝ ጭማሪ ያለው? የተደረገው ጭማሪ እኮ የእርከን ጭማሪ ነው፤›› ተብሎ እቅጩ ተነገራቸው፡፡ ዓይናቸውን ከቴሌቪዥን  ተክለው ሲነዛ የነበረውን የጭማሪ ዜና ሲከታተሉ የነበሩ የጓደኛዬ አከራይ ሁለት መቶ ብር ጨመሩበት፡፡ አንድ መቶ ምናምን  ብሯ የደመወዝ ጭማሪ ማለቴ የእርከን ጭማሪ ሁለት እጥፍ ዕዳ ይዛ መጣች፡፡ ለዚህ ነበር ጓደኛዬ ‹RIP› የደመወዝ ጭማሪ›› ያለው፡፡

ይህ ታሪክ የጓደኛዬ ብቻ አይደለም፡፡ የብዙ አዲስ አበቤ የቤት ተከራዮች ታሪክ ነው፡፡ ድሮ ቢሆን ኖሮ ዝንጥ ሊያደርግ የሚችል ብር በቀን ሠርተው እያገኙ ማደሪያቸውን በረንዳና ጎዳና ያደረጉ አዲስ አበቤዎችን በረንዳውም  ጎዳናውም  ይቁጠራቸው፡፡

ሌላም አንድ አቤቱታ ልጨምርላችሁ፡፡ አንድ የግል ባንክ የሚሠራ ነው ሰውዬው. . . (እዚህ ላይ መቼም ባንክ ቤት  ብር የሚቆጥረውን ሠራተኛና የሚያስቆጥረውን አከራይ ለይተው ያውቃሉ ብየ እገምታለሁ) እና የግል ባንክ ውስጥ የሚሠራ ተከራይ ከተከራየው ቤት  ማልዶ ወደ ሥራ  ቦታ ሲወጣ፣ አከራዩዋ ‹እንኳን ደስ አለህ ስለደመወዝ ጭማሪው በቴሌቪዥን ሰማሁ እኮ› ይሉታል በፊታቸው ላይ የደስታ ስሜት እየተነበበባቸው፡፡

ያኔ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ይጨመራል እየተባለ ከዓመት በላይ ይወራ ስለነበር የግል ባንክ ላይ  ስለሚሠራ ጭማሪው እሱን የሚመለከተው ባይሆንም፣ ‹የእኛ እኮ አይደለም የተጨመረው. . .› ምናምን ብሎ ይህንን የቅን ፈገግታና ደስታ ላለማጨለም ሲል ‹እንኳን አብሮ ደስ አለን› ማዘር ይላቸዋል፡፡ ማታ ከሥራ ሲመለስ ታዲያ አንድ የወጪ መርዶ ጠበቀው፡፡ ‹ልጄ እኛም እንግዲህ በዚህ ቤት ኪራይ ነው የምንተዳደረው ከወዴት አናመጣለን፣ ሁለት መቶ ብር ጨምሬብሀለሁ› አሉት፡፡

የነዋሪውን ገቢ ለማያገናዝብ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ተጠያቂው አከራይ ብቻ ነውን?

 እውነቱን ለመናገር አብዛኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ (ቤት አልባው) የሚለፋውና የሚሠራው፣ የቤት ኪራይ ለመሸፈን የማያስችል ደመወዝ ለማግኘት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ለመሆኑ የቤት ኪራይ የዋጋ ተመን የወጣው የትኛውን የማኅበረሰብ ክፍል የገቢ መጠን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ይሆን? ምን አልባት ጉርሻ አገኝ ይሆናል ብላ በወር አምስት መቶ ብር ደመወዝ እያገኘች በስምንት መቶ ብር ቤት የምትከራይ ምስኪን የቡና ቤት አስተናጋጅ? ወይስ በስህተት በሚመስል አኳኋን ያላቅሙ ልጅ ወልዶ ልጅ ላለው ሰው ቤት አናከራይም ተብሎ ከሠፈር ሠፈር ለሚንከራተት የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛ? ወይስ በአራት መቶ ብር የፅዳት ሥራና እዚህ ግባ በማይባል የቀን ሥራ ድንጋይ እየፈለጡ ለሦስትና ለአራት በደባልነት ኑሮአቸውን ለሚገፉ ምስኪኖች? ወይም   በሥራ ዕጦት  ጎዳናውን ሞልተው የሥራ ማስታወቂያ ያለበትን ጋዜጣ ለሚያሳድዱ ሥራ አጦች? ወይም ደግሞ ለስም ሥራና ደመወዝ ኖሯቸው በሆድ ይፍጀው በጥሩ ልብስ ሽክ ብለው የሚወጡ ገመናቸውን የኪራይ ቤታቸው (ወሬው የኪራይ ቤት አይደል) የሸፈነላቸውን  ብዙኃን?

  አራተኛውን ለጊዜው እናቆየውና ለሰው ልጅ በጣም ከሚያስፈልጉ ሦስት መሠረታዊ ነገሮች መካከል መጠለያ አንዱ እንደሆነ ሁሉም የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህን መሠረታዊ ነገሮች የማግኘት መብት ያለው የአንድ አገር ዜጋ፣ አንደኛውን መጠለያ ብቻ ለማግኘት የሚጠየቀው ገንዘብ ሠርቶ ከሚከፈለው ገቢ የላቀ ሲሆን ከማየት በላይ አሳፋሪ ነገር የለም፡፡

ለዚህ ቅጥ ያጣ የቤት ኪራይ ዋጋ ንረት አከራይ ብቻ ሳይሆን መንግሥትስ ተጠያቂ አይሆንም? ለማንኛውም መንግሥት ስለዚህ ጉዳይ ከነገ ዛሬ እመለስበታለሁ እያለ  በተደጋጋሚ  በይደር ማለፉ አንድ ነገር  እንድንጠረጥርና እንድንጠይቅ ያደርጋል፡፡ እነዚህ አከራዮች መንግሥትና የመንግሥት ዘመዶች ይሆኑ እንዴ? ቸር እንሰንብት! ዙሮ መግቢያ የኪራይ ቤት አያሳጣን!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]    ማግኘት ይቻላል፡፡