Skip to main content
x
ለምረጡኝ እንደማይቀርቡ የተናገሩት የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ዳግም መታጨታቸው ተገለጸ

ለምረጡኝ እንደማይቀርቡ የተናገሩት የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ዳግም መታጨታቸው ተገለጸ

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በመጪው ዓርብ ጥቅምት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚያካሂደው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት በፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር አራት ዕጩዎች መቅረባቸው ሲታወቅ፣ የደቡብ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትን በፕሬዚዳንትነት እየመሩ የሚገኙትን አቶ ሰሎሞን አፈወርቅን ለፕሬዚዳንትነት እንዳጫቸው ተሰማ፡፡ አቶ ሰሎሞን ከዚህ ቀደም ለምክር ቤቱ ፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር እንደማይቀርቡ ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡

አቶ ሰሎሞን ግን ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ራሳቸውን ለዳግም ምርጫ እንደማያቀርቡ ሲገልጹ ቢቆዩም፣ በደቡብ ንግድ ምክር ቤት ለድጋሚ ምርጫ ታጭተዋል መባሉ ጉዳዩን አነጋጋሪ አድርጎታል፡፡

ስለ ጉዳዩ ያነጋገርናቸው አቶ ሰሎሞን፣ የክልሉ ንግድ ምክር ቤት ዕጩ እንዳደረጋቸው እንደሚያውቁ ጠቅሰው፣ ነገር ግን ዳግመኛ ለመወዳደርም ሆነ ከዕጩነት ለመውጣት እንዳልወሰኑ ገልጸዋል፡፡ እስካሁን በነበረው አቋማቸው ምክር ቤቱን ለመምራት እንደማይወዳደሩ ቢሆንም፣ አሁን ዕጩ ሆነው እንዲቀርቡ በመጠየቃቸው የሚወዳደሩ ከሆነ፣ ለዘንድሮው ምርጫ በፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩት ዕጨዎችን ቁጥር  ወደ አምስት ከፍ ያደርገዋል፡፡

በአቶ ሰሎሞን ድጋሚ ለውድድር መቅረብ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ሲሆን፣ በአንድ ወገን አልወዳደርም ብለው ድጋሚ ለመወዳደር ማኮብኮባቸው አግባብነት እንደሌለው የሚገልጹ አሉ፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ አቶ ሰሎሞን ከክልላቸውም ሆነ ከተለያዩ ወገኖች ድጋሚ እንዲመረጡ ባለው ፍላጎትና ግፊት ዳግም ለምርጫ እንደታጩ ይነገራል፡፡

በተለይ የደቡብ ንግድ ምክር ቤት አቶ ሰሎሞን በድጋሚ ለመመረጥ ብቁ መሆናቸውን በማሰብ ወክለውት እንዲወዳደሩ ቢፈልግም፣ እሳቸው ግን መወዳደር አልፈልግም ሲሉ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም የሚወክሉት የደቡብ ንግድ ምክር ቤት እፈልጋቸዋለሁ፣ በዕጩነት አቀርባቸዋለሁ በማለቱ በግፊት ውሳኔ እንዳስተላለፈ እየተገለጸ ይገኛል፡፡

ጥቅምት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚደረገው ምርጫ፣ ከአቶ ሰሎሞን ጋር ለፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደሩ ከተገለጹት ግለሰቦች መካከል ከኦሮሚያ ንግድ ምክር ቤት አቶ ፈይሳ አራርሳ፣ ከአማራ ንግድ ምክር ቤት አቶ መላኩ እዘዘው (ኢንጀነር)፣ ከአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት አቶ ውብሸት ኃይሉ (ኢንጂነር) እና ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራቾች ማኅበር አቶ ፋሲል ታደሰ ይገኙበታል፡፡ የተወዳዳሪዎቹ ቁጥር ከወትሮው ብዛት ያለው በመሆኑ፣ የዘንድሮውን ከቅርብ ጊዜያት ምርጫዎች ሁሉ ለየት ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት በተገኘው መረጃ መሠረት፣ የአዲስ አበባና የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች በምክትል ፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩ ዕጩዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ ለምክትል ፕሬዚዳንትንት ታጭተው የቀረቡት ከትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አቶ አሰፋ ገብረ ሥላሴ ሲሆኑ፣ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ደግሞ አቶ አበባው መኮንን የተባሉትን ዕጩ በምክትል ፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ አጭቷቸዋል፡፡

አቶ አሰፋ በአሁኑ ጊዜ የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ አቶ አበባው በበኩላቸው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ አቶ አበባው በ2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ዘርፍ ምክር ቤት ቦርድ አባልነት ተመርጠው ነበር፡፡ የዘርፍ ምክር ቤቱ ያካሔደው ምርጫ ሕግን አልተከተለም በተባለበት ወቅት፣ አቶ አበባው የተካተቱ በመሆናቸው እሳቸውና ቀሪዎቹ ተመራጮች እንዲታገዱ ተደርጎ በአዲስ ተመራጮች መተካታቸው ይታወሳል፡፡