Skip to main content
x
ሕዝብን መበጥበጥ ይብቃ!

ሕዝብን መበጥበጥ ይብቃ!

አሁንም የሰው ክቡር ሕይወት እየተቀጠፈ ነው፡፡ የአካል ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡ ንብረት እየወደመ ነው፡፡ ሰላማዊና ሥልጡን የፖለቲካ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸው ችግሮች ገጽታቸውን እየቀያየሩ ሰላምና መረጋጋት እየጠፋ ነው፡፡ ባልታሰበ አጋጣሚ የሆነ ሥፍራ ሁከት ይቀሰቀስና የንፁኃን ሕይወት እንደ ዋዛ ያልፋል፡፡ በዚህ መሀል ሕዝብ ግራ ይጋባል፡፡ በሰላም ወጥቶ መግባት ጥርጣሬ ውስጥ ይወድቃል፡፡ የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ይስተጓጎላል፡፡ የችግሮችን መንስዔ ለይቶ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ፣ በየቦታው ለሚነሱ ሁከቶች የሚሰጠው ምላሽ አደጋውን እያባባሰው ነው፡፡ ንፁኃን ዜጎች ይሞታሉ፣ የአካል ጉዳት ይደርስባቸዋል፣ ንብረት ይወድማል፣ ሒደቱ ይቀጥላል፡፡ በአንድ ሥፍራ የደረሰን አደጋ ከማረጋጋት የዘለለ ዘለቄታዊ መፍትሔ እየጠፋ፣ ሌላ ሥፍራ ሌላ ችግር ሲከሰት የሚጎዳው ሕዝብ ነው፡፡ ትርምስ የሚፈጠረው አገር ላይ ነው፡፡ ሰላማዊና ሥልጡን የፖለቲካ ትግል ጨርሶ እያከተመለት አምባጓሮ በርትቷል፡፡ ለሕዝብና ለአገር ህልውና አደጋ ነው፡፡ መቋጪያ ያስፈልገዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ሥፍራዎች በተከታታይ የሚነሱ ሁከቶች የዜጎችን ሕይወት ከመቅጠፍ በተጨማሪ ለአገር አሳሳቢ እየሆኑ ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የክልሉ መንግሥት በሰከነ መንገድ የችግሩን መንስዔ በመለየት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት አለባቸው፡፡ በተባራሪ ወሬዎች በሚነሱ ግርግሮች አገር ለምን ይታመሳል? ግልጽ ሊወጡ ባልቻሉ ውስጣዊ ሽኩቻዎች ምክንያት ሕዝብ ለምን ይደናገራል? የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ወጣቶችም ሆኑ ኅብረተሰቡ ማን እንደጠራው በማይታወቅ ሠልፍ ወይም እንቅስቃሴ እንዳይሳተፉ ጥሪ እያቀረበና ሕዝብ አብሮት መሆኑን እየገለጸ ለምን ችግር ይፈጠራል? የፌዴራል መንግሥትም በእሱ በኩል የሚፈለግበትን ለመወጣት ለምን ዳተኝነት ያሳያል? ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመረጃ አሰጣጥም ሆነ በተለያዩ ጉዳዮች መቃቃርን የሚያሳዩ ነገሮች እየታዩ ምክንያታቸው ለምን ግልጽ አይደረግም? ተጠያቂነትና ግልጽነት የሌለበት ብልሹ አሠራር እስከ መቼ ይቀጥላል? በእነዚህና በመሰል ጉዳዮች ምክንያት ሕዝብ እየተደናገረ ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ በተደጋጋሚ የዜጎች ሞት ይሰማል፡፡ አገር እየታመሰ ሕዝብ እየተበጠበጠ ነው፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

ሕዝብ መሠረታዊ ለውጥ እንደሚፈልግ በተደጋጋሚ በተለያዩ መንገዶች ገልጿል፡፡ ይህንንም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ባለሥልጣናት አምነዋል፡፡ መሠረታዊ ለውጥ ያስፈልጋል ሲባል ለውጡ ለአገርና ለሕዝብ ጠቃሚነቱ ሊሰመርበት ያስፈልጋል፡፡ ለውጥ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምኅዳር ይፈልጋል፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር የሚካሄድ ለውጥ ሰላማዊ ከመሆኑም በላይ ለብሔራዊ መግባባት በር ይከፍታል፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩት ግትርነት፣ በጥላቻ የተበከሉ አመለካከቶችና ፋይዳ ቢስ ስሜታዊነቶች ለውይይትና ለድርድር እጃቸውን ይሰጣሉ፡፡ አምባገነናዊ አስተሳሰቦች ይወገዳሉ፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ ሥልጡን ግንኙነት ይጀመራል፡፡ ሥርዓተ አልበኝነትና ነውጠኝነት አደብ ይገዛሉ፡፡ በሕዝብ ጥያቄ የተነሳባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች በቅደም ተከተል እየቀረቡ መፍትሔ ያገኛሉ፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበራሉ፡፡ ለማኅበራዊ ፍትሕ መስፈን የሚረዱ አሠራሮች ተግባራዊ መሆን ይጀምራሉ፡፡ ዘገምተኛው የፖለቲካ ሥነ ምኅዳር ነፍስ ይዘራል፡፡ ዜጎች በነፃነት ሐሳባቸውን ይገልጻሉ፣ ይደራጃሉ፣ በአገራዊ ጉዳዮች በስፋት ይሳተፋሉ፡፡ ይህንን መሰል የፖለቲካ ምዕራፍ ማስጀመር የሚቻለው ግን በደመነፍስ በሚካሄድ ነውጠኛ ትግል ሳይሆን፣ በበሳልና በሥልጡን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ብቻ ነው፡፡ የንፁኃን ደም በከንቱ የሚፈስበት ሽኩቻ ሕዝብን ከመበጥበጥ ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ አገርን ለአደጋ ከመዳረግ የዘለለ ትርፍ አይገኝበትም፡፡

በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደሞከርነው ከምንም ነገር በላይ መከበር ያለበት ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ ይህ ኩሩና ጨዋ ሕዝብ እንዳለመታደል ሆኖ የሚያዳምጠው የለም፡፡ መንግሥት በፊናው ያሻውን እያደረገ ከሕዝብ ጋር ስለማይደማመጥ ችግሮች ተቆለሉ፡፡ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ አለን የሚሉ ኃይሎች ለሕዝብ ደንታ ስለሌላቸው ከእነ መኖራቸውም ተረስተዋል፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ ራሳቸውን በራሳቸው የሾሙ ስመ ፖለቲከኞች መሬት ላይ በተጨባጭ ከሚታየው የሕዝብ ፍላጎት ጋር የማይገጥም ቅዥት ውስጥ ናቸው፡፡ ሕዝቡን በብሔር ከፋፍለው አገር ለማፈራረስ ያቆበቆቡ ኃይሎችም ለአገሪቱም ሆነ ለሕዝብ ደንታ የላቸውም፡፡ ኃላፊነት የጎደላቸው ድርጊቶችን እየፈጸሙ ንፁኃንን ያስፈጃሉ፡፡ ለአገር የሚጠቅም ምክር የሚያስተላልፉ ወገኖችን በስድብ እያዋከቡ አንገት ያስደፋሉ፡፡ ዘረኛ መልዕክቶችን እያሠራጩ ሕዝብን በሕዝብ ላይ በማነሳሳት ስለተጠመዱ፣ ወደ ህሊናቸው ለመመለስ ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ለእነሱ ዋናው ቁም ነገር የሞትና የውድመት ዘገባ ለማሠራጨት መጣደፍ ነው፡፡ ሰሞኑን እያየነው የሰነበትነውም ይህንኑ ነው፡፡ ኃላፊነት የጎደላቸው ራስ ወዳዶች ሕዝብ እያመሱ ነው፡፡ አገር የሚያስተዳድረው መንግሥትም ሆነ ገዥው ፓርቲ የምናውቀውን ችግር ከመናገር በዘለለ ለዘለቄታዊ መፍትሔ ሲተጉ አይታይም፡፡ ሁሉም በየፊናው ባመቸው ጎዳና እየነጎደ አገር ትተራመሳለች፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡

ሌላው በጣም የሚያሳዝነው ጉዳይ አገሪቱ ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችና ተቆርቋሪ ዜጎች የሌሏት ይመስል ዝምታው መክበዱ ነው፡፡ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ዜጎች ሲሞቱ፣ አካላቸው ሲጎድልና የአገር ሀብት ሲወድም ‹ይህቺ አገር ወዴት እየሄደች ነው?› ከሚል እንጉርጉሮ በመላቀቅ፣ የመፍትሔ ያለህ ማለት የሚገባቸው ወገኖች አድፍጠዋል፡፡ በመደበኛውም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያ ስለወቅታዊ የአገር ጉዳይ ለመነጋገር የሚሞክሩትም ቢሆኑ፣ የጎራ ፖለቲካ ከማራገብ በላይ የተሻለ ነገር ይዘው ሲመጡ አይታይም፡፡ እጅግ በጣም ውስን የሆኑ ግለሰቦች ቁም ነገር ሲናገሩ የሚያዳምጣቸው የለም፡፡ ይህ ኩሩና ጨዋ ሕዝብ ግን ግራ እየተጋባ ነው፡፡ ከቀን ወደ ቀን የሚሰማቸው ዜናዎች ከተስፋ ይልቅ መርዶ ይዘው ሲመጡ ይሳቀቃል፡፡ ታዳጊ ወጣቶችና ሕፃናት ሳይቀሩ የሰቆቃ ወሬ እየሰሙ ምን ተስፋ ይኖራቸዋል? በዚህ ጊዜ ነው የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ከያሉበት ተጠራርተው ለዘለቄታዊ መፍትሔ መነሳት ያለባቸው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው እንጉርጉሮና በእሮሮ የታጀበ ከንፈር መጠጣ ለአገር የሚፈይደው የለም፡፡ የሚመለከታችሁ ሁሉ ለአገራችሁና ለሕዝባችሁ ስትሉ አለን በሉ፡፡ ያለበለዚያ የእናንተ መኖር ፋይዳ የለውም፡፡ ለሕዝብም አይጠቅምም፡፡

ሕዝብ የሚደሰተው በአገሩ ብቻ ነው፡፡ አገሩ ደግሞ ሰላም መሆን አለባት፡፡ ልማት የሚኖረው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ሰላም እንዲኖር ደግሞ ዴሞክራሲያዊነት ይጠበቃል፡፡ ሥርዓተ አልበኝነት ግለሰብንም ሆነ አገርን ያጠፋል፡፡ በሥርዓተ አልበኝነት የሚመራ እንቅስቃሴ ትርፉ ጥፋት ነው፡፡ መብትን ለመጠየቅም ሆነ ጥያቄን ለማቅረብ ሕጋዊ መሆን ተገቢ ነው፡፡ የመብት ጥያቄ የቀረበለት መንግሥትም ሆነ ባለሥልጣን ከሕግ በታች መሆን አለበት፡፡ በሙስና የተዘፈቀ ሹምም ሆነ ቡድን መጀመርያ ራሱን ማጥራት አለበት፡፡ በፖለቲካው ውስጥ እንሳተፋለን የሚሉ ወገኖችም መጀመርያ መታገል ያለባቸው ከራሳቸው ብልሹ አስተሳሰብ ጋር ነው፡፡ ዴሞክራሲ ባህል መሆን የሚችለው አሁን በምናየው የተንሸዋረረ ጽንፈኛ አቋም ውስጥ አይደለም፡፡ የመብት ረገጣን እታገላለሁ የሚል ፖለቲከኛ የሌሎችን መብት ላለመደፍጠጡ ማስተማመኛ ማቅረብ አለበት፡፡ በዘረኝነት ካባ ውስጥ የተደበቀ የፖለቲካ አቀንቃኝ ዴሞክራሲን ከልብ መቀበል አይችልም፡፡ ምክንያቱም ውግናው ለቆመለት ዓላማ እንጂ ለመላው ሕዝብ አይደለምና፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለአገር የሚያስቡ ቅኖች ያሉትን ያህል ዘረኝነት፣ ሌብነት፣ ራስ ወዳድነትና አድሎአዊነት የተጠናወታቸውም አሉ፡፡ እነዚህ መጀመርያ ከዚህ ዓይነቱ ጉድፍ ሊጠሩ ይገባል፡፡ ያኔ ሕዝብን በአንክሮ አዳምጠው ለመሠረታዊ ለውጥ መነሳት ይችላሉ፡፡ አሁን የተያዘው ግን አገርን ማተራመስና ሕዝብን ማወክ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሕዝብን መበጥበጥ ይቁም የሚባለው!