Skip to main content
x
የኢትዮጵያን የጥራት ሽልማት አስገዳጅ የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ ተዘጋጀ

የኢትዮጵያን የጥራት ሽልማት አስገዳጅ የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ ተዘጋጀ

በመንግሥት ልዩ ልዩ የግንባታ ፕሮጀክቶች ውስጥ የሚሳተፉ አምራቾችና አገልግሎት ሰጪዎች በተለይም የግንባታ ተቋራጮች ራሳቸውን በኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት ካላስፈተሹ በቀር ወደ ጨረታ እንዳይገቡ የሚያስገድድ ረቂቅ ሕግ ተዘጋጀ፡፡

የኢትዮጵያ የጥራት የሽልማት ድርጅት ረቂቅ ሕጉን ለማፀደቅ መንቀሳቀስ የጀመረ ሲሆን፣ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

‹‹በተለያዩ የመንግሥት የግንባታ ፕሮጀክቶች ውስጥ በመሳተፍ ላይ የሚገኙ ከ160 በላይ የግንባታ ተቋራጮች እንዳሉ መረጃው አለኝ፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ መካከል በጥራት ሽልማት ውድድሩ ላይ የተሳተፉት ስድስት ብቻ ናቸው፤›› ያሉት የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ መብራቱ ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች ውድድሩን አስገዳጅ እየሆነ እንዲመጣ ምክንያት መሆናቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ረቂቅ ሕጉ ተወዳድረው ለሚያሸንፉ ድርጅቶችም የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችን ማግኘት የሚያስችሏቸውን አንቀጾች ያካተተ ነው፡፡ አሸናፊዎቹ ተቋማት ከዕውቅና ባሻገር በኅብረተሰቡ ዘንድ የታወቁ ብራንድ ለመሆን እንደሚረዳቸውም አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል፡፡

አሸናፊዎቹ ተቋማት በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ማስታወቂያ በማስነገር፣ የመንግሥት ድርጅቶች የአሸናፊ ተቋማትን ምርትና አገልግሎት ብቻ እንዲጠቀሙ የማድረግ፣ ሰፊው ማኅበረሰብም ምርትና አገልግሎታቸውን መርጦ እንዲጠቀም በማድረግ በውድድሩ የሚገባቸውን ጥቅማጥቅም እንዲያገኙ ማድረግ በረቂቁ የተካተቱ ናቸው፡፡

አቶ ቴዎድሮስ እንዲህ ያሉትን ሐሳቦች ስላካተተው ረቂቅ የገለጹት፣ አምስተኛው የጥራት ሽልማት፣ ማክሰኞ ጥቅምት 14 ቀን 2010 ዓ.ም. በቤተ መንግሥት በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ወቅት ነበር፡፡ በትምህርት፣ በጤና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽንና በሌሎች ሦስት ዘርፎች የተሰማሩ 63 ተቋማት በጥራት ውድድሩ ተሳትፈዋል፡፡ ኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላቦራቶሪ፣ ሐረር ቢራ፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ውድድሩን በበላይነት በማሸነፍ የአንደኛ ደረጃ የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላቦራቶሪ ለሦስተኛ ጊዜ የአንደኛ ደረጃ የዋንጫ ተሸላሚ በመሆኑ የልዩ ዋንጫ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡

 ባህር ዳር ጋምቢ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ አላማጣ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ በላይ አብ ኬብል አምራች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ አርባ ምንጭ ፓራዳይዝ ሎጅ፣ በደሌ ቢራ አክሲዮን ማኅበር እንዲሁም ኦሪጂን ውኃ የሁለተኛ ደረጃ የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ብሩኅ ተስፋ መስኖና ውኃ ቴክኖሎጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ አማራ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽ፣ ሼባ የቆዳ ኢንዱስትሪና አዳማ ዴቨሎፕመንት ደግሞ የሦስተኛ ደረጃ የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

ሌሎች በውድድሩ ለተሳተፉ ተቋማትም የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡ ነገር ግን ለውድድሩ ካመለከቱ ተሳታፊዎች መካከል 18ቱ በተለያዩ ምክንያቶች ውድድሩን አቋርጠዋል፡፡ ወደ ውድድሩ ለመግባት የሚከፈለው የገንዘብ መጠን 15,000 ብር ሲሆን፣ ያቀረቡት ዶክመንት ተገምግሞ ወደ ሁለተኛው ዙር የሚያልፉት ከ60 ነጥብ በላይ ያስመዘገቡ ናቸው፡፡

ያስመዘገቡት ነጥብ ከ60 በታች በመሆኑ የቀሩ ተቋማት አሉ፡፡ መጠይቁን ተመልክተው ‹‹ይኼንን አናሟላም ተወዳድረን ብንሸነፍ ለስማችን ጥሩ አይደለም፤›› ብለው ውድድሩን ያቋረጡ በብዛት የግል ተቋማት መሆናቸው ተገልጿል፡፡

‹‹ተወዳድረን ብንሸነፍ አመራር ላይ ጥያቄ ያስነሳል ብለው፣ በጀት የለንም በሚል ውድድሩን ያቋረጡ የመንግሥት ተቋማትም አሉ፤›› የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ ውድድሩ አስገዳጅ ቢሆን መሰል አጋጣሚዎች እንደማይከሰቱ ይናገራሉ፡፡

ተቋማቱ የሚከተሉት አመራር፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ፣ የሀብት አጠቃቀም፣ የሥራ ሒደት፣ የደንበኞች አያያዝ፣ የሥራ አፈጻጸምና ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት ተቋማቱ የተፈተሹበት የጥራት ሞዴሎች ናቸው፡፡ በአገሪቱ በጥራት ላይ ትኩረታቸውን አድርገው ከሚሠሩ ድርጅቶች መካከል የሆነው የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት በየሁለት ዓመቱ ይኼንን የሽልማት ሥነ ሥርዓት ሲያዘጋጅ ቆይቷል፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ ድርጅቶችን በጥራት ሽልማት በማወዳደር፣ ዕውቅና በመስጠት፣ መልካም ተሞክሮዎችን በማስተላለፍና ጥራት ብሔራዊ አጀንዳ እንዲሆን ኅብረተሰቡን ማስተማር ዋነኛ ተልዕኮው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት፣ የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲና የኢትዮጵያ ብሔራዊ አክሬዲቴሽን ጽሕፈት ቤት ተመሳሳይ ራዕይ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ናቸው፡፡

እነዚህ ድርጅቶች ከሚሰጡት የጥራት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት አልያም ሽልማት ውጪ የኋላ ታሪካቸውን የማይታወቅ የጥራት ውድድር ሽልማት እንሰጣለን የሚሉ ድርጅቶች አሉ፡፡ ‹‹‹ከውጭ ተገዝተው የሚገቡ ሽልማቶች በጣም እየረበሹን ነው፡፡ ለምሳሌ መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስምንት ጊዜ ያህል የጥራት ሽልማት ውድድር አሸንፈሃል ተብሎ ተደውሎለታል፡፡ መሥራቻችን ለሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በዚህ ዓመት ብቻ አምስት ጊዜያት ያህል ተደውሎ በዚህ ሽልማት ዘርፍ አሸንፈሀል 4,000 ዩሮ ከፍለህ ሽልማቱን ውሰድ ብለውታል፡፡ እነዚህ ተቋማት አሠራሩን ስለሚያውቁ ነው ሽልማት የተባለውን ነገር ያልወሰዱት እንጂ ሌሎች ድርጅቶች ግን ይሸወዳሉ፤›› በማለት ያልተገባ ድርጊት የሚፈጽሙ የውጭ ተቋማት መብዛታቸውን ተናግረዋል፡፡